አልማዝ አያና በግማሽ ማራቶን የመጀመሪያ ውድድሯን ከሁለት ሳምንት በኋላ በህንድ ዴሊሂ ታደርጋለች

16th IAAF World Athletics Championships London 2017 - Day Two

አልማዝ አያና በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ10 ሺህ ሜትር ውድድር ላይ (Photo by Andy Lyons/Getty Images for IAAF)

በምድረ ሕንድ የተመዘገበ ብቸኛው የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ የወርቅ ደረጃ ያለው የጎዳና ላይ ውድድር የሆነው የኤርቴል ዴሊሂ ግማሽ ማራቶን የፊታችን ሕዳር 10/2010 ዓ.ም. ለ13ኛ ግዜ ሲከናወን የ10 ሺህ ሜትር የወቅቱ የኦሊምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮን ኢትዮጵያዊት አልማዝ አያና በርቀቱ የመጀመሪያ የውድድር ተሳትፎዋን የምታደርግ ይሆናል፡፡

በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. በሞሪሺየስ ባምቡ በተከናወነው የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና በሴቶች 3000ሜ. መሰናክል ሀገሯን ወክላ የብር ሜዳልያ አሸናፊ በመሆን የዓለም አቀፍ ተሳትፎ ውድድሯን አሀዱ ያለችው አልማዝ ባሳለፍነው ነሐሴ 2009 ዓ.ም. ለንደን ላይ የዓለም የ10ሺህ ሜትር የወርቅ እና የ5000ሜ. የብር ሜዳልያ አሸናፊ ለመሆን እስከበቃችበት ግዜ ድረስ የነበሩትን ስምንት ዓመታት በ3000ሜ. መሰናክል እንዲሁም ከ3000ሜ. እስከ 10000ሜ. ባሉት የትራክ ላይ ውድድሮች ላይ አተኩራ በመስራት አሳልፋለች፡፡ በነዚህ ግዜያት በጎዳና ላይ ውድድር የአንድ ግዜ ብቻ የተሳትፎ ሪኮርድ ያላት ሲሆን እርሱም እ.አ.አ በዲሴምበር 2010 ዓ.ም. አንጎላ ሉዋንዳ ውስጥ በ10 ኪ.ሜ. 32 ደቂቃ ከ19 ሰከንድ በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችበት ነው፡፡

አልማዝ ከወዲሁ ሕዳር እና ታሕሳስ ወር መጀመሪያ ላይ በሕንድ እና ኔዘርላንድ ሀገሮች በሚከናወኑት የዴሊሂ ግማሽ ማራቶን እና የፒፊክስ ሶላር ሞንተፈርላንድ 15 ኪ.ሜ. ፉክክሮች ላይ እንደምትሳተፍ ማሳወቋ ዘንድሮ ለወትሮው ከምትታወቅባቸው የውድድር አይነቶች ውጪ የሆኑ ረዥም የጎዳና ላይ ሩጫዎችን በመሞከር ለየት ያለ የውድድር ዓመትን ለማሳለፍ እየተዘጋጀች እንደምትገኝ ጠቋሚ ነው፡፡

አልማዝ አያና በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ10 ሺህ ሜትር ውድድር ላይ (Photo by Andy Lyons/Getty Images for IAAF)

የኤርቴል ዴሊሂ ግማሽ ማራቶን ውድድር አዘጋጆች ባደረሱን ፕሬስ ሪሊዝ እንዳስታወቁት አልማዝ አያና እና የለንደኑ ዓለም ሻምፒዮና የወንዶች ማራቶን አሸናፊ ኬንያዊው ጂኦፍሬይ ኪሩይ የሚሳተፉበት የዘንድሮው ውድድር በሁለቱም ፆታዎች የውድድር ስፍራው ሪኮርድ ይሰበርበታል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ የውድድር ስፍራው የወንዶቹ ሪኮርድ በ2014 አሸናፊው ኢትዮጵያዊ ጉዬ አዶላ የተመዘገበው 59 ደቂቃ ከ06 ሰከንድ ሲሆን ረዘም ያለ ግዜ የቆየው የሴቶቹ ሪኮርድም ኬንያዊቷ ሜሪ ኬይታኒ በ2009 ዓ.ም. ያሰመዘገበችው 1፡06.54 ነው፡፡

በሴቶቹ ፉክክር አልማዝ አያና በርቀቱ የዳበረ ልምድ ካላት፣ ያለፈው ዓመት አሸናፊነት ክብሯን ለማስጠበቅ ከምትሮጠው እና በውድድሩ ላይ ከሚካፈሉት መካከል ፈጣን የሆነ 66 ደቂቃ ከ14 ሰከንድ ሰዓት ባለቤት ከሆነችው የሀገሯ ልጅ ወርቅነሽ ደገፋ እንዲሁም ከነፃነት ጉደታ (67፡31) ጋር ብርቱ ትንቅንቅ እንደምታደርግ ይጠበቃል፡፡ ኬንያዊቷ ሄላ ኪፕሮፕ (67፡39)፣ ኢትዮጵያዊቷ አባበል የሻነህ (67፡52)፣ ባሕሬንን ወክላ የምትሮጠው ሚሚ በለጠ (69፡15) እና የፖላንዷ ካሮሊና ናዶልስካ (69፡54) ሌላኛዎቹ ተፎካከሪዎች ናቸው፡፡

በወንዶቹ ምድብ ከሁለት ዓመት በፊት በዚሁ ውድድር ላይ ስድስተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ያስመዘገበው 59፡38 የሆነ የርቀቱ የራሱ ምርጥ ሰዓት ካለው ጂኦፍሬይ ኪሩይ በተጨማሪ ኢትዮጵያውያኑ ይግረም ደመላሽ (59:19)፣ ብርሀኑ ለገሰ (59:20)፣ አባዲ ሀዲስ እና አንዳምላክ በልሁም የሚሳተፉ ሲሆን ብርቱ ተፎካካሪዎቹ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡ የዴሊሂው ፉክክር ለአባዲ ሀዲስ እና አንዳምላክ በልሁም በግማሽ ማራቶን የመጀመሪያ ተሳትፏቸውን የሚያደርጉበት ነው፡፡

በአጠቃላይ 275 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ለሽልማትነት በተዘጋጀበት በዚህ ውድድር ላይ በሁለቱም ፆታዎች ቀዳሚ ሆነው የሚያጠናቅቁት አትሌቶች የ27 ሺህ ዶላር ተሸላሚ ይሆናሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.