አልማዝ አያና ለ2017 የዓመቱ ምርጥ አትሌትነት ከታጩት አስር አትሌቶች አንዷ ሆነች

Almaz

ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማሕበር በመጪው ህዳር ወር አጋማሽ ላይ የመጨረሻ አሸናፊዎቹ ተለይተው ለሚታወቁበት የ2017 የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች ምርጫ በሁለቱም ፆታዎች የመጨረሻዎቹን አስር ዕጩዎች ይፋ ሲያደርግ ኢትዮጵያዊቷ የኦሊምፒክ እና የዓለም የ10 ሺህ ሜትር ሻምፒዮን አልማዝ አያና ከሴቶቹ ዕጩዎች መካከል አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡

ለዓለም ኮከብነት ምርጫ ከታጩት አስር አትሌቶች መካከል ከአልማዝ አያና ሌላ ኬንያዊቷ የ5000ሜ. የዓለም ሻምፒዮን እና የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ ሔለን ኦቢሪ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካዊቷ የ800ሜ. የዓለም ሻምፒዮን እና የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ ካስተር ሴመንያ በሴቶች አህጉራችን አፍሪካን መወከል ችለዋል፡፡  በወንዶቹ በኩል ከኢትዮጵያ አንድም አትሌት ከአስሩ ዕጩዎች መካከል ለመሆን ባይበቃም ኬንያዊው የ1500ሜ. የዓለም ሻምፒዮን ኤላያህ ማናንጎይ፣ ደቡብ አፍሪካዊው የዓለም እና የኦሊምፒክ የ400ሜ. ሻምፒዮን ቫይዴ ቫን ኒከርክ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካዊው የዓለም የርዝመት ዝላይ ሻምፒዮን ሉቮ ማንዮንጋ አፍሪካን ለመወከል የበቁ አትሌቶች ሆነዋል፡፡

በሁለቱም ፆታዎች ከቀረቡት አስር አትሌቶች መካከል ለመጨረሻ ዕጩነት የሚቀርቡትን ሶስት አትሌቶች የመምረጥ ሂደቱ በሶስት አይነት መንገድ የሚከናወን ሲሆን በምርጫው ላይም የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ካውንስል ድምፆች 50 በመቶ፣ የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ቤተሰብ ድምፆች 25 በመቶ እንዲሁም የሕዝብ ድምፅ 25 በመቶ ዋጋ ይኖራቸዋል፡፡ የዚህ ምርጫ ሂደት መጠናቀቂያ ቀንም ጥቅምት 6/2010 ዓ.ም. (በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ኦክቶበር 16/2017) ሲሆን ከምርጫው መጠናቀቅ በኋላም በሁለቱም ፆታዎች ለመጨረሻው ምርጫ በዕጩነት የሚቀርቡት ሶስት ሶስት አትሌቶች በሚያገኙት ድምፅ መሰረት በአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ይፋ የሚደረጉ ይሆናል፡፡

በሁለቱም ፆተዎች የዓመቱ ኮከብ ተብለው የሚመረጡት አትሌቶችም ሕዳር 15/2010 ዓ.ም. በሞናኮ በሚካሄደውና የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን በሚያገኘው የሽልማት ስነስርዓት ላይ ይፋ ይደረጋሉ፡፡

ከስድስቱም የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ አህጉራዊ ቅርንቻፎች በተውጣጡ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ኤክስፐርቶች በተደረገው ምርጫ ለ2017 የዓመቱ ኮከብ አትሌትነት በመጨረሻዎቹ አስር ዕጩዎች ውስጥ የተካተቱት

በሴቶች
አልማዝ አያና (ኢትዮጵያ) – የረጅም ርቀት ሩጫ ተወዳዳሪ

ማሪያ ላሲትስኬኔ (ሀገሯ በቅጣት ላይ በመሆኗ ፍቃድ አግኝታ በግሏ የምትወዳደር) – የከፍታ ዝላይ ተወዳዳሪ

ሔለን ኦቢሪ (ኬንያ) – የረጅም ርቀት ሩጫ ተወዳዳሪሳሊ ፒርሰን (አውስትራሊያ) – የ100ሜ. መሰናክል ሩጫ ተወዳዳሪ

ሳንድራ ፔርኮቪች (ክሮሺያ) – የዲስከስ ውርወራ ተወዳዳሪ

ብሪትኒ ሪስ (ዩ.ኤስ.ኤ.) – የርዝመት ዝላይ ተወዳዳሪ

ካስተር ሴመንያ (ደቡብ አፍሪካ) – የመካከለኛ ርቀት ሩጫ ተወዳዳሪ

ካተሪኒ ስቴፋኒዲ (ግሪክ) – የምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳሪ

ናፊሳቱ ቲያም (ቤልጂየም) – የሄፕታትሎን ተወዳዳሪ

አኒታ ቮዳርቺክ (ፖላንድ) – የመዶሻ ውርወራ ተወዳዳሪ

በወንዶች

ሙታዝ ባርሺም (ኳታር) – የከፍታ ዝላይ ተወዳዳሪ

ፖቬል ፋይዴክ (ፖላንድ) – የመዶሻ ውርወራ ተወዳዳሪ

ሞሐመድ ፋራህ (ግሬት ብሪቴይን) – የረጅም ርቀት ሩጫ ተወዳዳሪ

ሳም ኬንድሪክስ (ዩ.ኤስ.ኤ.) – የምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳሪ

ኤላያህ ማናንጎይ (ኬንያ) – የመካከለኛ ርቀት ሩጫ ተወዳዳሪ

ሉቮ ማንዮንጋ (ደቡብ አፍሪካ) – የርዝመት ዝላይ ተወዳዳሪ

ኦማር ማክሊኦድ (ዩ.ኤስ.ኤ.) – የ110ሜ. መሰናክል ሩጫ ተወዳዳሪ

ቫይዴ ቫን ኒከርክ (ደቡብ አፍሪካ) – የአጭር ርቀት ሩጫ ተወዳዳሪ

ክርስቲያን ቴይለር (ዩ.ኤስ.ኤ.) – የስሉስ ዝላይ ተወዳዳሪ

ዮሀን ቬተር (ጀርመን) – የጦር ውርወራ ተወዳዳሪ

በዓለም የዓመቱ ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ላይ ለአልማዝ አያና ድጋፋችሁን መስጠት የምትፈልጉ
የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማሕበር (አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ) ማሕበራዊ ግንኙነት ገፆች በሆኑት የፌስቡክ እና ትዊተር አካውንቶች በመጠቀም ድምፅ መስጠት ትችላላችሁ፡፡

አልማዝን ለመምረጥ ተከታዮቹን ሊንኮች በመጠቀም ላይክ ማድረግ ወይም ‹‹favorite›› ብሎ ኮመንት ማድረግ ብቻ ነው

በፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/WorldAthleticsClub/videos/1474338835948282/

በትዊተር፡- https://twitter.com/iaaforg/status/915149596258635778

መልካም ዕድል ለአልማዝ አያና!

Leave a Reply

Your email address will not be published.