”አሁንም ቢሆን አርበኞች ግንቦት 7 አልፈረሰም” አቶ ኤፍሬም ማዴቦ

PG7 denies split

የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ከግንቦት 7 ጋር በይፋ መለያየቱን የተለያዩ የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም የፓርቲው ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ይህንን “የተለመደ የማኅበራዊ ሚዲያ” አሉባልታ ነው ማለታቸውን ከዚህ በፊት ዘግበን ነበር።

ነገር ግን የአርበኞች ግንባር አባላት የሆኑ ሰዎች ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ግንባሩ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ ንቅንቄ አካል መሆኑ ቀርቶ ለብቻው ለመንቀሳቀስ ማስታወቁን የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃኑ ዘግበዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ ንቅንቄ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ማዴቦን ቢቢሲ በድጋሚ አነጋግሯቸው ነበር።

”እኔም ጉዳዩን የሰማሁት ከመገናኛ ብዙሃኑ ነው።” መረጃውም ፍጹም ሃላፊነት በጎደለው መልኩ መዘገቡን ለመግለጽም ከሚመለከታቸው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሃላፊዎች ጋር በስልክ መገናኘታቸውንና በደንብ ለመነጋገር ቀጠሮ መያዛቸውን ገልጸውልናል።

”አርበኞች ግንቦት ሰባት በይፋ ወደ ሃገር ቤት ተመልሷል። ከድርጅቱ ተገንጥያለሁ የሚል ”መንገደኛና ወንጀለኛ” አካል አቅርበው እኛን ሳያናግሩና ሳያሳውቁ አርበኞች ግንቦት 7 ለሁለት ተከፍሏል የሚለውን ዜና ያስተላለፉ የመገናኛ ብዙሃን በሙሉ ፍጹም ተጠያቂነት የጎደላቸው ናቸው” ብለዋል።

አክለውም ”አርበኞች ግንባር የሚባል ድርጅት የለም። ግንቦት 7 የሚባልም ድርጅት የለም። አሁንም ቢሆን ያለው አርበኞች ግንቦት 7 ብቻ ነው።”

”እ.አ.አ በ2001 ዓ.ም የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባርና ግንቦት 7 ተዋህደው፤ በስብሰባቸው ወቅት የመረጧቸው አመራሮች ድርጅቱን እ.አ.አ እስከ 2017 ድረስ ሲመሩ ቆይተዋል። በዚሁ ዓመት የንቅናቄው ጠቅላላ ጉባኤ ኤርትራ ውስጥ አካሂዶ አዲስ አመራር መርጧል።” ሲሉ ምስረታው እንዴት እንደተካሄደ ያስረዳሉ።

በዚህ ሂደትም የቀድሞ አመራሮቹ በድጋሚ መመረጥ አልቻሉም። ይህ መሆኑ ያላስደሰታቸው ሰዎች ናቸው ግንባሩ ፈርሷል በማለት የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም የተሳሳተ መረጃ እያሰራጩ የሚገኙት ብለዋል አቶ ኤፍሬም።

በተጨማሪም ”አቶ መንግስቱ ወልደስላሴ እና አቶ ክፈተው አሰፋ የተባሉት ግለሰቦች ድርጅቱን የማይወክሉና ምንም አይነት ኃላፊነት የሌላቸው የግንባሩ አባላት ናቸው ብለዋል። እንደውም በድርጅቱ ስም መግለጫ ሲሰጡ የነበሩት አቶ መንግስቱ ወልደስላሴ ግልጽ በሆነ መንገድ ከድርጅቱ በወንጀል ተባርረው የወጡና ላለፈው አንድ ዓመት ተኩል የድርጅቱ አባል ያልነበሩ ሰው ናቸው” በማለት ከመባረርም አልፎ ሰውዬው በወንጀል ታስረው እንደነበረ ቃል አቀባዩ ይናገራሉ።

ከአቶ ኤፍሬም ሃሳብ በተቃራኒው የአርበኞች ግንባርን በመወከል ሲያስተባብሩ የነበሩትን አቶ አቶ ክፈተው አሰፋን ቢቢሲ አነጋግሯቸው ነበር።

ድርጅቱ ይፋዊ ጉባኤውን አካሂዶ አመራሮቹን እስኪመርጥ ድረስ አቶ መንግስቱ ወልደስላሴ ከተባሉ ግለሰብ ጋር በመሆን በማስተባበር ላይ እገኛለሁ ያሉት አቶ ክፈተው አሰፋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ለመለያየታቸው ዋነኛው ምክንያት የድርጅታዊ መርህ መጣስ ነው።

መጀመሪያውኑ ስንዋሃድ ይላሉ አቶ ክፈተው፤ እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ተስማምተንባቸው የነበሩት የውህደት ህጎች ስላልተከበሩና የአርበኞች ግንባር አመራሮችና አባላት በጎ ገጽታ እንዳይኖራቸው መደረጉ አርበኛውን ስላስቆጣ እዚህ ውሳኔ ላይ ደርሰናል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ”ከ1993 ጀምሮ ለ17 ዓመታት ስንታገል የቆየን ቢሆንም፤ ትግሉ የዛሬ አስር ዓመት የተጀመረ በማስመሰል ከእዛ በፊት የተሰዉትን አርበኞች ክብርና ጥቅም የማያስከብር ሆኖ ስላገኘነው አማራጩ ከእነሱ መለየት ነው ብለን መግለጫ ሰጥተናል” በማለት አቶ ክፈተው አክለዋል።

ወደ ኋላ መለስ ብለውም ”ውህደቱ ሲካሄድ የሁለቱም ድርጅቶች አባላትና አመራሮች ነበሩ የመሰረቱት። ነገር ግን በውህደቱ ወቅት የነበሩት የአርበኞች ግንባር የምክር ቤት አባላትና የስራ አስፈጻሚዎች በተለያዩ ምክንያቶች እንዲወገዱ ተደርገው አሁን ላይ በቦታቸው የሉም። ስለዚህ የግንቦት ሰባት ብቻ ስብስብ ሆኗል፤ እኛን አይወክሉንም” ብለዋል።

”ከዚህ በኋላ ግንቦት ሰባት እንጂ አርበኞች ግንቦት 7 የሚል ድርጅት የለም” ሲሉ አቶ ክፈለው አቋማቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ በኋላስ ግንባሩ ዕጣፈንታው ምን ይሆናል? ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ አቶ ክፈለው ሲመልሱ፤ በመጀመሪያ ድርጅታዊ ጉባኤ ያደርጋል፤ በመቀጠልም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር አብሮ የሚሰራ ይሆናል ብለዋል።

ይህንን ለማሳካትም ከወልቃይት የማንነት ኮሚቴ፤ ከአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶች ጋር ውይይት በማድረግ ኢትዮጵያዊ መንፈሱን ያልለቀቀ አንድ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት ለመመስረት ማሰባቸውን ይናገራሉ።

አሁን እያነሳችኋቸው ያሉት ጥያቄዎች ቢመለሱ ተመልሳችሁ የመቀላቀል ሃሳብ ይኖራችኋል ወይ? የቢቢሲ ጥያቄ ነበር።

”ከግንቦት 7 ሰባት ጋር በድጋሚ የምንቀላቀልበት ምንም አይነት ምክንያት አይኖርም” የአቶ ክፈለው ምላሽ ነው።

ምንጭ:- ቢቢሲ አማርኛ