ብቸኛው የኢትዮጵያ ተወካይ ከፈታኝ ጉዞ በኋላ የናይጄሪያውን ክለብ ለመግጠም ተዘጋጅቷል

ባለፈው የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ የክለቦች ጥሎ ማለፍ ዋንጫን በድል በመወጣቱ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ተሳታፊ መሆን የቻለው ደደቢት በመጀመሪያ የደርሶ መልስ ፍልሚያው የሲሼልሱን ኮት ዲ ኦር በድምር 5ለ2 ውጤት በመርታቱ ለቀጣዩ ዙር ማለፉ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሰረት ከዚህ ዙር ተጋጣሚው የናይጄሪያው ዋሪ ዎልቭስ ጋር የመጀመሪያ ጨዋታውን ለማድረግ ወደ ምዕራብ አፍሪካዋ ሀገር አምርቷል፡፡ ቀጣዩ ፅሁፍ ከቅዳሜ ምሽቱ የዋሪ ጨዋታ በፊት በሰማያዊዎቹ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እና ስለተጋጣሚያቸው ይዳስሳል፡፡

የተሻሻለ የመሰለው ደደቢት

የውድድር ዘመኑን በጥሩ ሁኔታ ጀምረው በኋላ ላይ አቋማቸውም ሆነ ውጤታቸው በአስደንጋጭ ሁኔታ ያሽቆለቆለው ደደቢቶች አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታን አሰናብተው ኢንስትራክተር ዮሐንስ ሳህሌን ሲሾሙ ፈጣን መሻሻል ቢጠብቁም እንዳሰቡት አልሆነም፡፡ አሰልጣኝ ዮሐንስ ከፈጣን ውጤት ይልቅ ቡድኑን በራሱ ፍልስፍና መገንባትን የመረጠ በሚመስል መንገድ ለአዳዲስ እና ተጠባባቂ ወንበር ላይ ለነበሩ ወጣቶች እድል የሠጠ ሲሆን ይህ ከአንዳንድ ወሳኝ ተጨዋቾች ጉዳት ጋር ተዳምሮ የተፈለገውን ፈጣን የውጤት መሻሻል እንዳይታይ አድርጓል፡፡ ሰማያዊዎቹ በሊጉ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠሩባቸው ጎሎች ነጥብ የጣሉባቸውን አስቆጪ አጋጣሚዎች ጨምሮ በርካታ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ያልቻሉ ሲሆን በዮሀንስ ቆይታ ያሸነፏቸው ጨዋታዎች ቁጥር ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመት ባለድል በሆኑበት የጥሎ ማለፉ ውድድርም ገና በመጀመሪያው ዙር ተሸንፈው ተሰናብተዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በአፍሪካ ውድድርም እንዳይደገም ደጋፊዎችን ስጋት ውስጥ ቢከታቸውም ቡድኑ ጥቂት ከማይባሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋር ተጋፍጦ ብዙም ሳይቸገር የሲሼልሱን ቡድን መርታት ችሏል፤ አሁን የናይጄሪያውን ተጋጣሚ ለመግጠምም ተዘጋጅቷል፡፡ የዮሀንስ ቡድን በተለይ ከሜዳው ውጪ በሲሼልስ ያሳየው እንቅስቃሴ እና ይዞ የመጣው ድል ድንቅ ነበር፡፡ ቡድኑ ኮት ዲ ኦርን በረታባቸው ሁለቱ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች የእንቅስቃሴ እና የውህደት መሻሻል ያሳየ ሲሆን የአዲሱ ጋናዊ ግብ ጠባቂ ሱሌይማና አቡበከሪ፣ ዘንድሮ ጥሩ ያልነበረው አጥቂው ዳዊት ፍቃዱ እንዲሁም በድንቅ ሁኔታ ጀምሮ ቀስ በቀስ የወረደው ሌላው አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚ የተሻሻለ ብቃት እንዲሁም የቁልፉ አማካይ ታደለ መንገሻ ከጉዳት መመለስ ለቡድኑ ሰዎች ሁሉ ደስታ እና ተስፋን የሰጠ ሆኗል፡፡ በቅዳሜው ጨዋታ ላይ ምናልባት ሊያሳስባቸው የሚችለው የቡድኑ የመጀመሪያ ተሰላፊዎች የሆኑት አክሊሉ አየነው እና ሳምሶን ጥላሁን በጉዳት፣ አዳሙ መሀመድ በቅጣት ምክንያት አለመኖራቸው ይሆናል፡፡

 

አድካሚው እና አወዛጋቢው ጉዞ

እንደሲሼልሱ ጉዞ ሁሉ የናይጄሪያውም ጉዞ ለደደቢቶች ፍፁም አድካሚ፣ ደስታን ያልሰጠ እና ተጋጣሚያቸውንም በማዳከም ሴራ እንዲጠራጠሩ ያደረጋቸው ነበር፡፡ ሐሙስ ረፋድ ላይ ጉዛቸውን ወደ ሌጎስ ያደረጉት ደደቢቶች ከሰዓታት በረራ በኋላ ሌጎስ የደረሱ ሲሆን ጨዋታውን ወደሚያደርጉበት ዋሪ ከተማ የአውሮፕላን በረራ ባለማግኘታቸው ከሌጎስ ወደጎረቤት ቤኒን በርረው ከዚያ 100 ኪሎ ሜትሮች ገደማ በመኪና ወደ ዋሪ አምርተዋል፡፡ የዋሪ ዎልቭስ የሚዲያ ኦፊሰር ኤቱ ሞሰስ እንዳሉት ደደቢቶች አርፍደው በመምጣታቸው ወደዋሪ ከተማ በሚወስደው አውሮፕላን ላይ ቦታ ማግኘት አልቻሉም፤ የተሻለው አማራጭም ለዋሪ ወደምትቀርበው ቤኒን በአውሮፕላን ተጉዞ ከቤኒን ዋሪ ያለውን 100 ኪሎ ሜትር በመኪና መሸፈን ነበር፡፡ የደደቢት አባላትም ሆኑ ዜናውን የሰሙ ኢትዮጵያዊያን ነገሩን ከተለመደው የምዕራብ አፍሪካ ክለቦች ተጋጣሚያቸውን የማዳከም እና የማበሳጨት ሸፍጥ ጋር ቢያያይዙትም የናይጄሪያው ክለብ ሰዎች ግን በደደቢቶች መምጣት ዙሪያ ቀድሞ እንዳልተነገራቸው እና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለስልጣን ለናይጄሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ረዳት ዲሬክተር አዴሞላ ኦላጂሬ የስልክ ጥሪ የደረሳቸው አባላቱ በሌጎስ ጉዟቸው አየር ላይ እንዳሉ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በሁኔታውም ተደናግጠው ብዙ ስልኮችን በመደዋወል እና እንግዶቹን ለመቀበል የተጣደፈ ዝግጅት በማድረግ ከውርደት እንደዳኑም ናይጄሪያዊያኑ ጨምረው ሲናገሩ የአውሮፕላን ቦታ ቀድሞ ባለመያዙ የተነሳ የቤኒኑን ጉዞ ለማዘጋጀት መገደዳቸውንም አስረድተዋል፡፡

Warri Wolves - 1

የደደቢት ተጋጣሚ ማን ነው?

ደደቢትን የሚያስተናግደው የናይጄሪያው ክለብ ዋሪ ዎልቭስ (ቀድሞ የናይጄሪያ ወደብ ባለስልጣን ይባል ነበር) መቀመጫውን በዋሪ ከተማ ያደረገ ሲሆን ከሰባት ዓመታት በፊት ከታችኛው ዲቪዚዮን ፕሪምየር ሊጉን የተቀላቀለ እና በፕሪምየር ሊጉ ፈጣን መሻሻል አድርጎ ባለፈው ዓመት ለሊጉ ዋንጫ መፎካከር የቻለ ክለብ ነው፡፡ የተኩላዎቹን ያለፉት ሶስት ዓመታት የሊግ ውጤት እንኳን ብንመለከት (በ2012 – 15ኛ፣ በ2013 – 7ኛ እና ዓምና 3ኛ) ቡድኑ ከዓመት ዓመት እንዴት እንደተሻሻለ መረዳት እንችላለን፡፡ ዎልቭስ ለዚህ ውድድር የበቁት በባለፈው ዓመቱ ሊግ ከሻምፒዮኑ ካኖን ፒላርስ በአምስት እና ከተከታዩ ኢኒዬምባ በአራት ነጥቦች ብቻ አንሰው ሶስተኛ ሆነው በማጠናቀቃቸው ሲሆን በቅድመ-ማጣሪያውም የቡርኪናፋሶውን አር.ሲ ቦቦ-ዲዮላሶን ከሜዳቸው ውጪ 1ለ0 እና በሜዳቸው 3ለ0 በድምር 4ለ0 በመርታት የደደቢት ተጋጣሚ ሆነዋል፡፡ ናይጄሪያዊያኑ ዓምናም በዚህ ውድድር ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን የወጡት አሁን ባሉበት ተመሳሳይ ዙር (የ32 ቡድኖች ዙር) በቱኒዚያው ቢዘርቲን በድምር 2ለ1 ውጤት ተረትተው ነበር፡፡ በወቅቱ የቡድኑ አሰልጣኝ ፖል አይግቦጉን የተሸነፉት ተበልጠው ሳይሆን ‘በአፍሪካ እግር ኳስ ፖለቲካ’ ምክንያት እንደሆነ አነጋጋሪ ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡

Warri Wolves - 2

ዋሪ ዎልቭስ ከጨዋታው በፊት

ስለደደቢት ተጋጣሚ ዋሪ ዎልቭስ ወቅታዊ አቋም ብዙ ማለት አይቻልም፡፡ አሁን በናጄሪያ የሊግ ሰንጠረዥ ወለል ላይ መገኘታቸውም የሚሰጠን የጎላ ምስል አይኖርም ምክንያቱም በሊጉ የተደረገው አንድ ጨዋታ ብቻ ነውና (የናይጄሪያ ሊግ የሚጀመረው በእነሱ ማርች መጀመሪያ፣ በእኛ የካቲት መጨረሻ ላይ ነው)፡፡ ቡድኑ በአዲሱ የውድድር ዘመን ያደረጋቸው ጨዋታዎች ሶስት ብቻ ሲሆኑ እነዚህም አር.ሲ ቦቦ-ዲዮላሶን የረታባቸው ሁለቱ ጨዋታዎች እና ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ በጋብሮስ ዩናይትድ 2ለ0 የተሸነፈባቸው ጨዋታዎች ናቸው፡፡ ያለፈው ሳምንቱን የሊግ ሽንፈታቸውን ተከትሎ የቡድኑ ማኔጂንግ ዲሬክተር ዴቪሰን ኦዉሚ የቡድኑ ተጨዋቾች ካምፕ ገብተው ትልቅ ግምት ለሰጡት የደደቢት ጨዋታ በትኩረት እንዲዘጋጁ አሳስበው ነበር፡፡ የደደቢት አባላት ከአዲስ አበባ ከመነሳታቸው በፊት በሰጥዋቸው ቃለ-መጠይቆች ዎልቭስ የቡርኪናፋሶውን ቡድን የረታበትን ቪዲዮ አግኝተው እንደተመለከቱ እና ባዩት መሰረት እንደተዘጋጁም ገልፀዋል፡፡

Warri Wolves - 3

የዎልቭስ አባላት ምን አሉ?

የዋሪ ዎልቭስ ተጨዋቾች፣ አሰልጣኙ፣ የሚዲያ ኦፊሰሩ እና ማኔጂንግ ዲሬክተሩ ሁሉም በተመሳሳይ የደደቢትን ጥንካሬ እና ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ብዙ ተጨዋቾች ማስመረጥ እንዲሁም በመልሱ ጨዋታ በግዙፍ ስታዲየም በበርካታ ሺዎች ደጋፊዎች ፊት ስለመጫወት ፈተና ሲናገሩ ሰንብተዋል፡፡ የቡድኑ አምበል እና የ2013 አፍሪካ ዋንጫ አሸናፊው የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ተሰላፊ አዙቡዪኬ ኤግዌክዌ የመጀመሪያ ጨዋታቸው ከባድ እንደሚሆን ተናግሮ ደጋፊዎቻቸው ወደ ስታዲየም በመጉረፍ እንዲያበረታቷቸው አሳስቧል፡፡ እንደ አምበሉ አገላለፅ ደደቢት ብዙ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾችን ከመያዙ እና በመልሱ ጨዋታ በባህር ዳር ስታዲየም በአርባ ሺዎች ደጋፊዎች ፊት ከመጫወት ፈተና መነሻ በሜዳቸው በዋሪ ጨዋታውን ለመጨረስ መጣር ይኖርባቸዋል፡፡ የናይጄሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባዘጋጀው እድል ለስምንት ቀናት በእንግሊዝ በነበራቸው ቆይታ የአርሰናሉን አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር በማግኘታቸው እና ከፈረንሳዊው በእግር ኳስ ፍልስፍና፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የፕሮፌሽናል ክለብ አመራር ዙሪያ የልምድ ማካፈል በማግኘታቸው እጅግ የተደሰቱት አሰልጣኙ ፖል አይግቦጉን ይህ ልምድ ለደደቢቱ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ለቀሪው የአሰልጣኝነት ህይወታቸው እንደሚጠቅማቸው ገልፀው ነገር ግን ከደደቢት ከባድ ፈተና እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፤ ለሳምንታት ለደደቢት ጨዋታ እንደተዘጋጁም አረጋግጠዋል፡፡

ተጨማሪ ነጥቦች በጨዋታው ዙሪያ

  • ጨዋታውን የሚመሩት አርቢትሮች ሀሰን ሞሀመድ ሀጊ፣ ሀምዛ ሀጊ አብዲ፣ ባሺር አብዲ ሱሌይማን እና ባሺር ኦላድ አራብ ከሶማሊያ ሲሆኒ የጨዋታው ኮሚሽነር አል-ሀጂ ጃዉሉ ከጋና ናቸው፡፡
  • ደደቢቶች 18 ተጨዋቾችን ጨምሮ የ24 አባላት የልኡካን ቡድን ይዘዋል፡፡
  • ጨዋታው የሚደረገው በሞቃታማዋ እና 311.970 ህዝብ በሚኖርባት ዋሪ ከተማ 20.000 ተመልካቾችን በሚይዘው ዋሪ ታውንሺፕ ስታዲየም ቅዳሜ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይሆናል፡፡
  • የመልሱ ጨዋታ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በባህር ዳር ስታዲየም ይካሄዳል፡፡
  • የደርሶ መልስ ፍልሚያው አሸናፊ ከሱዳኑ አል አህሊ ሸንዲ እና ከዴ.ሪ ኮንጎው ኤም.ኬ ኤታንሼቴ አሸናፊ ጋር ይጫወታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.