ባሬቶ ሲሸኙ ዮሐንስ ተሹሟል

team

Mariano Barreto (Left) and Yohannis Sahle.

Mariano Barreto (Left) and Yohannis Sahle.

ያለፉት 10 ቀናት ቀድሞውንም ውዝግብ እና ክርክር በማያጣው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዙሪያ በርካታ ነገሮች ተከስተዋል፤

አነጋጋሪ ጉዳዮችም ተነስተዋል፡፡ ዋሊያዎቹን ለ12 ወራት በዋና አሰልጣኝነት የመሩት አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ የሁለት ዓመታት

የኮንትራት ጊዜያቸውን ሳያጠናቅቁ ‘በስምምነት’ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ሲለያዩ ይህ የሁለቱ ወገኖች ፍቺ በይፋ በተገለፀ ልክ

በሳምንቱ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ተደርገው መመረጡን ፌዴሬሽኑ ራሱ በይፋ

መግለጫ ልኳል፡፡ ከዚህ ውሳኔ ሶስት ቀናት በኋላ ደግሞ የቀድሞው ፖርቹጋላዊ የቡድኑ አለቃ በብዙ ጉዳዮች ዙሪያ

አስተያየቶቻቸውን የገለፁበትን የስንብት ፕሬስ ኮንፈረንስ ሰጥተዋል፡፡

የባሬቶ ስንብት

ማሪያኖ ጄሬኒሞ ባሬቶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ያሳለፏቸው ያለፉት 12 ወራት በብዙ ውጣውረዶች፣ ውዝግቦች እና

አለመግባባቶች የተሞሉ ነበሩ፡፡ ፖርቹጋላዊው ኃላፊነቱን ከተረከቡበት እለት ጀምሮ ለስራው ከተፎካከሯቸው ሌሎች እጩዎች

በልጠው የስልጣን መንበሩን ከያዙበት አከራካሪ መንገድ ጀምሮ በውጪ ምንዛሬ እስከሚከፈላቸው ደመወዝ እና ጥቅማጥቅም፣

እንዲሁም ለዝግጅት ወደ ብራዚል ቡድኑን ይዘው ከሄዱበት ውሳኔያቸው አንጋፎችን ትተው ለወጣቶች የመጫወት እድሎች

እስከሰጡባቸው ውሳኔዎቻቸው ድረስ የብዙ ውዝግቦች ምንጭ ሆነው የነበረ ሲሆን በኋላ በፉክክር ጨዋታዎች ያስመዘገቧቸው

ውጤቶች እና የቡድኑ አጨዋወትም እንዲሁ የመነጋገሪያ ርዕስ ነበር፡፡

 ውጤታማነት፡- በቁጥሮች ብቻ ከተመለከትነው የባሬቶ የፉክክር ጨዋታዎች ሬኮርድ ደካማ የሚባል ነው፡፡ በአፍሪካ

ዋንጫ ማጣሪያው ቡድኑ ወደ ባማኮ ተጉዞ በማሊ ላይ ካስመዘገበው ያልተጠበቀ አስገራሚ የ3ለ2 ድል ውጪ ማሸነፍ

ያልቻለ ሲሆን ከቀሪዎቹ አምስት ጨዋታዎች በአንዱ አቻ ተለያይቶ (ከማላዊ)፣ በአራቱ ሽንፈት አስተናግዷል (ሁለቴ

በአልጄሪያ እንዲሁም በማሊ እና ማላዊ)፡፡ በመላው የአፍሪካ ጨዋታዎች ማጣሪያም በባሬቶ የተመራው የ23 ዓመት

በታች ቡድኑ በጎረቤት ሱዳን በደርሶ መልስ ተረቶ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ዋልያዎቹ በፖርቹጋላዊው

አመራር ቀድሞ ጠንካራ ምሽጋቸው በነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም ካደረጓቸው ሶስት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ

ጨዋታዎች በአንዱም አለማሸነፋቸው እና የኦሊምፒክ ቡድኑም በድሬዳዋ ስታዲየም በሱዳን መረታቱ ሳይነሳ የማይታለፍ

በባሬቶ ዘመን የታየ የሜዳ አድቫንቴጅን ያለመጠቀም ችግር ነበር፡፡ ባጠቃላይ የባሬቶ የፉክክር ጨዋታዎች ሬኮርድ

እንዲህ ይነበባል፡- አንድ ድል፣ አንድ አቻ እና ስድስት ሽንፈቶች፡፡

 የአጨዋወት ዘይቤ፡- የባሬቶ የኢትዮጵያ ቡድኖች በተለይም ዋናው ብሔራዊ ቡድን ባደረጓቸው ጨዋታዎች በጠቅላላው

ማለት ይቻላል የ4-3-3 አሰላለፍን ይዘው ወደ ሜዳ ቢገቡም አንድ አይነት ማንነት ያላቸው ቡድኖችን በተለያዩ

ጨዋታዎች ላይ ተመልክተናል ለማለት ያስቸግራል፡፡ አሰልጣኙ ተጨዋቾቼ እንደዚያ እንዲጫወቱ አላዘዝኩም ቢሉም

በርካታ ዓላማ-የለሽ ረዥም ኳሶችን የሚጫወት፣ በማጥቃት ላይ ያተኮረ ይሁን በመከላከል ላይ የማይታወቅ፣

በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ ያልተዋጣለት ቡድንን ስንመለከት ቆይተናል፡፡

 የተጨዋቾች ምርጫ፡- ትውልደ-ህንዱ ባሬቶ ብዙ ተቃውሞ ካስተናገዱባቸው ጉዳዮች አንዱ ለአንጋፋ ተጨዋቾች ቦታ

የነፈጉበት እና ለአዳዲስ ወጣቶች እድሎች የሰጡበት የተጨዋቾች ምርጫቸው ነበር፡፡ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በፊት

ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ያበቁት እና በደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፉት እንዲሁም ከዚያ በኋላ ለዓለም

ዋንጫም ለማለፍ ተቃርበው የነበሩትን በርካታ ተጨዋቾች መጠቀም አለመፈለጋቸው በአንዳንዶች በመረረ ሁኔታ

አስወቅሷቸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በመደበኝነት የሚከታተሉ እና ያልተጠሩት አብዛኞቹ ሲኒየር ተጨዋቾች

አቋም በአስደንጋጭ ሁኔታ መውረዱን ያስተዋሉ አንዳንዶች ደግሞ በባሬቶ እነዚያን ከዋክብት አለመጥራት ብዙም

አልተገረሙም ነበር፡፡ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝን በብዙ ነገሮች ልንተቻቸው ብንችልም አቋማቸው የወረዱ ባለትልቅ

ስሞችን ባለመምረጥ ድፍረታቸው እና በብሔራዊ ቡድኑ ማልያ ባሳዩን በርካታ ወጣት ተስፈኞች (ናትናኤል ዘለቀ፣

አንዳርጋቸው ይላቅ፣ ዳዋ ሆጤሳ፣ አብዱልከሪም መሀመድ፣ ራምኬል ሎክ…) አለማድነቅ ያስቸግራል፡፡ ለክለቦቻቸው

እንኳ ገና አዲስ የሆኑት ተጨዋቾች በትልቅ መድረክ ከታላላቅ ተጨዋቾች በተቃራኒ ትከሻ ለትከሻ ሲገፋፉ መመልከት

ተስፈ እና ደስታን የሚሰጥ ነበር፡፡ ለወጣቶች እድል በመስጠት በማይሞገሰው እግር ኳሳችን ባሬቶ እነዚህን ተጨዋቾች

በተለይ ናትናኤልን ለእግር ኳሳችን እንዳበረከቱ በድፍረት ብንናገር ስህተት አይሆንም፡፡

 ዝግጅት፡- ማሪያኖ ባሬቶ ገና እንደመጡ ለእኛ ባልተለመደ መንገድ በራሳቸው ጥረት ቡድናቸውን ለሳምንታት ዝግጅት ወደ

ብራዚል ከወሰዱበት አንስቶ በራሳቸው ግንኙነቶች የአንጎላ ብሔራዊ ቡድንን ለወዳጅነት ከገጠሙበት እንዲሁሙ በሀገር

ውስጥም ሲዘጋጁበት የነበሩባቸው መንገዶች የሚደነቁ ነበሩ፡፡ በተመለከትናቸው በሀገር ውስጥ ዝግጅቶቻቸው ላይ ያሳዩት

የነበረው መሰጠት፣ ታታሪነት፣ የእንዳንዱን ተጨዋቾቹን መሰረታዊ የእግር ኳስ እውቀት ለማሳደግ ሳይሰለቹ ያደርጓቸው

የነበሩት ጥረቶች ሁሉ ምስጋና የሚያስቸሯቸው ነበሩ፡፡ በእነዚያ የልምምድ ፕሮግራሞች ባሬቶ ከፊታቸው ላሉ ጨዋታዎች

በታክቲክ ከመዘጋጀት ይልቅ መሰረታዊ እና ተጨዋቾቹ በታዳጊነታቸው ሊማሯቸው ይገቡ የነበሩ መሰረታዊ ነገሮች ላይ

ጊዜያቸውን ለማጥፋት ይገደዱ ነበር፡፡

 ግንኙነቶች፡- ባሬቶ እንደብዙሀኑ የእግር ኳስ አሰልጣኞች በአንድ ጎራ የሚደነቁ፣ በሌላኛው ጎራ የሚተቹ፤ ከተለያዩ

ወገኖች ጋር ያላቸው ግንኙነትም እንደዚያው የሚለያይ ነበሩ፡፡ እራሳቸውም በተለያዩ ቃለመጠይቆቻቸው እንዳነሱት

በፌዴሬሽኑ ውስጥ የሚቀርቧቸው እና በተቃራኒው ሊያዩዋቸው የማይፈልጉ ሰዎች ነበሩ፤ ከተጨዋቾቻቸው ጋር ከጥቂቶቹ

ጋር ካልሆነ (ለምሳሌ ባለመግባባት የቀነሱት አዳነ ግርማ) ጥሩ ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን ከጋዜጠኞች ጋርም

ከአንዳንዶቹ ጋር መልካም ከአንዳንዶቹ ጋር ግን ግላዊ ጉዳይ እስኪመስል መጥፎ ግንኙነት ነበራቸው፡፡

ባጠቃላይ የማሪያኖ ባሬቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ዘመን በበርካታ ውዝግቦች የታጀበ እና በመጨረሻም

ለፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የእርስ በእርስ መቃቃር ምክንያት ሆኖ የተጠናቀቀ ነበር፡፡ እናም በመጨረሻ

‘በስምምነት’ ተብሎ በተገለፀ የውል ማቋረጥ ባሬቶ የሶስት ወራት ደመወዝ በካሳ መልክ ተከፍሏቸው ከዋልያዎቹ ጋር

ተለያይተዋል፡፡

ባሬቶ ከስንብት በኋላስ

ማሪያኖ ባሬቶ በስምምነት ኃላፊነታቸውን እንደለቀቁ በይፋ በተገለፀ በ10ኛው ቀን ባለፈው ማክሰኞ በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፅህፈት

ቤት የስንብት ፕሬስ ኮንፈረንሳቸውን ሰጥተዋል፡፡ ፖርቹጋላዊው በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በተናገሩበት እና ስሜታዊ ሆነው በታዩበት

በዚህ ፕሬስ ኮንፈረንስ ላይ ግዴታቸው ሆኖም ይሁን እንዲሁ በፈቃደኝነት የረዷቸውን ጥቂት ግለሰቦች በስም ጠርተው ሲያመሰግኑ፣

ሊያግዙኝ ሲገባ አንድም ቀን ከጎኔ አልነበሩም ያሏቸውንም እንዲሁ በስም ጠርተው ወቅሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቺፍ

ኦፍ ስታፍ ጄነራል ሳሞራ የኑስን፣ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ እና አሰልጣኝ አብርሀም

ተክለሀይማኖትን በተለየ ሁኔታ ሲያመሰግኑ የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሀፊ አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝ፣ እንዲሁም አሰልጣኞቹ ጳውሎስ ጌታቸው፣

ፀጋዬ ኪዳነማሪያም እና ገብረመድህን ኃይሌም በቀና አጋዥነት የባሬቶ ምስጋና የደረሳቸው ሰዎች ሆነዋል፡፡ በተቃራኒው የቴክኒክ

ኮሚቴው እና የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ስራቸው ሆኖ ግን ምንም እገዛ ባለማድረግ በተሰናባቹ አሰልጣኝ ተተችተዋል፡፡

የውጪ እግር ኳስን አብዝተው የሚዘግቡት ሚዲያዎች፣ ለታዳጊ ተጨዋቾች ትኩረት የማይሰጠው እግር ኳሳችን እና መዋቅሩ

የተዛባው አጠቃላዩ የእግር ኳሱ ሲስተምም የባሬቶ የትችት ሰይፍ ያረፈባቸው እና እንድናሻሽላቸው ምክር የተሰጡን መስኮች

ሆነዋል፡፡ የእነሳልሀዲን ሰዒድ እና ጌታነህ ከበደ አይነት የብሔራዊ ቡድኑን ወሳኝ ተጨዋቾች በጉዳት እና ቅጣት ሳቢያ በብዙዎቹ

ጨዋታዎች ላይ ማሰለፍ አለመቻላቸውን ለስኬት አልባነታቸው በምክንያትነት ያነሱት ባሬቶ ምሳሌ ያደረጉት ሀገራቸው ፖርቹጋል ያለ

አንድ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ምንም ማድረግ እንደማትችል በመግለፅ ነበር፡፡ እግር ኳስ ወዳዱን እና ክብር የሰጣቸውን የኢትዮጵያን

ህዝብ በልባቸው ይዘው ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱም ባሬቶ ተናግረዋል፡፡

የዮሐንስ ሳህሌ ሹመት

የማሪያኖ ባሬቶ ከዋልያዎቹ ጋር መለያየት ይፋ በተደረገ ልክ በሳምንቱ፣ አራት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች

ለእጩነት መቅረባቸው በጭምጭምታ መልክ ከተሰማ 24 ሰዓታት እንኳን ሳይሞላ ከእጩዎቹ መካከል የደደቢቱ አሰልጣኝ

ዮሐንስ ሳህሌ (ኢንስትራክተር) ለብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነት መመረጡ መጀመሪያ በጭምጭምታ ደረጃ ከዚያም በፌዴሬሽኑ

ይፋዊ መግለጫ ተረጋግጧል፡፡ ከፌዴሬሽኑ ይፋዊ መግለጫ አስቀድሞ ዮሐንስ ቅዳሜ ከቀትር በኋላ ኢትዮጵያ ቡናን ከረቱበት

ጨዋታ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ ድረ-ገፅ በሰጠው ቃል ስለጉዳዩ እንደማያውቅ እና ለመወዳደር ሲል ያስገባው ፋይል እንደሌለ፣

ከፌዴሬሽኑ ሰዎች ጋርም በጉዳዩ ዙሪያ ምንም እንዳላወራ ገልፆ ነበር፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን ዮሐንስ ለቢቢሲ ዘጋቢ በሰጠው

ቃል በተጨዋችነት ያገለገለበትን ብሔራዊ ቡድን የማሰልጠንም እድል ስላገኘ እጅግ መደሰቱን ተናግሯል፤ ቡድኑን ውጤታማ

ለማድረግም በአቅሙ የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀቱንም አረጋግጧል፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ጁነይዲ ባሻ በበኩላቸው

ከሱፐር ስፖርት ጋር ባደረጉት ቆይታ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባለድርሻ አካላትን እና የእግር ኳስ ደጋፊዎችን በማዳመጥ ለዚህ

ውሳኔ እንደደረሰ ገልፀዋል፡፡ “የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የደደቢቱን አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና

አሰልጣኝ አድርጎ መርጧል፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ለሚዲያው እና በአጠቃላይ ለህዝቡ ግልፅ በነበረ ሂደት ነው፡፡ አንዳንድ

ጊዜ የሰዎችን ስሜት ከግምት ማስገባት ይኖርብናል” ያሉት ጁነይዲ “በቅርቡ ከአሰልጣኙ ጋር ተቀምጠን በሁሉም ነገሮች ዙሪያ

እንወያያለን፡፡ ብሔራዊ ቡድኑን ወደ ታላቅ ስኬት ለመምራትም ትክክለኛው ሰው እንደሚሆን ተስፋ አለን” ብለዋል፡፡ ይህ

የፕሬዚዳንቱ አስተያየት ግን ትንሽ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ አቶ ጁነይዲ የምርጫ ሂደቱ ለሚዲያው እና ለህዝቡ ግልፅ ነበር ማለታቸው

ፍፁም የማያሳምን ነው ምክንያቱም “ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋና አሰልጣኞች የመምረጫ መስፈርት በማዘጋጀትና የሁሉንም

ብቃትና ደረጃ በዝርዝር በማየት አራት ተወዳዳሪዎችን በኮሚቴው አማካኝነት ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለይቶ የማቅረቡ ሂደት

ከተጠናቀቀ በኋላ ዮሐንስ ሳህሌ በተዘጋጀው መመዘኛ መሰረት በቀዳሚነት ሊመረጥ ችሏል” ከሚለው የፌዴሬሽኑ የድህረ-

ምርጫ መግለጫ ውጪ አራቱን እጩዎች (ዮሐንስ ሳህሌ፣ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም፣ ፋሲል ተካልኝ እና አሸናፊ በቀለ) ለእጩነት

ያበቃቸውም ሆነ ዮሐንስን ለመመረጥ ያበቃው መስፈርት በትክክል ምንድ ነው የሚለው እስካሁን ግልፅ አልሆነም፡፡ እንደ ውበቱ

አባተ አይነት በፕሪምየር ሊጉ ስኬት ከሁሉም የሚልቅ አሰልጣኝ ለእጩነት እንኳ ሳይቀርብ በዋና አሰልጣኝነት በጣት ከሚቆጠሩ

ጨዋታዎች በላይ ያላደረገው ፋሲል ተካልኝ መታጨት እንዲሁም በሲኒየር ቡድን አሰልጣኝነት (በብሔራዊ ቡድንም ሆ በክለብ

ደረጃ) ከወራት ያልዘለለ ልምድ ያለው ዮሐንስ ከመታጨትም አልፎ መሾም እጅግ አነጋጋሪ እና የአቶ ጁነይዲን መግለጫ ፉርሽ

የሚያደርግ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ተሿሚው እና እጩዎቹ በአንድ ላይ በይፋ የተገለፁበትን ሂደት በምን አተያይ ግልፅ እንዳሉት መረዳት

ያስቸግራል፡፡

ዮሐንስ ሳህሌን በአጭሩ

የአዲስ አበባ ተወላጁ ዮሐንስ ሳህሌ በተጨዋችነት ለራስ ሆቴል እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን

ከተጫወተ በኋላ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ለመጫወት ካመራበት ኬንያ ሳይመለስ ቀርቶ ወደ አሜሪካ አቅንቷል፡፡ እዚያም

ማስሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽንን በመጀመሪያ ዲግሪ እና ስፖርት ሊደርሺፕ እና ኮቺንግን በሁለተኛ ዲግሪ ለተማረባቸው ኮሌጆች

ሲጫወት ነበር፡፡ በአሰልጣኝነት ሲ እና ቢ ፍቃዱም ከዚያ በኋላ የተለያዩ ኮሌጆችን ማሰልጠን ችሏል፤ በብራድ ፍሪድል አካዳሚም

በልጆች እና ታዳጊዎች ስልጠና ላይ ሰርቷል፡፡ የ49 ዓመቱ ዮሐንስ የካፍ ኢንስትራክተርም ሲሆን ወደ ትውልድ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ

ረዥም ጊዜ ባልቆየባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቴክኒክ ዲሬክተርነት፣ የደደቢት ጄነራል ማኔጀርነት እና የኢትዮጵያ ከ17

ዓመት በታች ቡድን አሰልጣኝነት ሚናዎች ሰርቷል፡፡ ዮሐንስ ባለፉት ጥቂት ወራት ደደቢትን በዋና አሰልጣኝነት ሲመራ የሰነበተ

ሲሆን በወጣቶች ላይ ያለውን ትልቅ እምነት እያሳየ የነበረበት ቡድን እየገነባ ይመስል ነበር፡፡ ግን ይህ ፕሮጄክት ከግብ ሳይደርስ

ዋሊያዎቹን የማሰልጠን ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ የሚደርስ ከሆነም በቅርቡ ስራውን

ይረከባል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.