በ24ኛው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ኢትዮጵያ አንድ የወርቅ ፣ አንድ የብር እና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎችን አሸነፈች

Team Gold Podium

በፖላንዷ ግድኒያ ከተማ አስተናጋጅነት በተከናወነው 24ኛው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የተናጠል ፉክክሩ በኬንያዊቷ ፔሬስ ጄፕቺርቺር እና በኡጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞ የበላይነት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተናጠል ሁለት የነሐስ በቡድን ደግሞ አንድ የወርቅ እና አንድ የብር ሜዳልያ አሸናፊ በመሆን አጠናቀዋል፡፡

የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የሴቶች የተናጠል ሜዳልያ አሸናፊዎች  Photo © Dan Vernon for World Athletics

በሴቶቹ ፉክክር አሸናፊ የሆነችው ኬንያዊቷ ፔሬስ ጄፕቺርቺር ውድድሩን በበላይነት ያጠናቀቀችው በራሷ ተይዞ የነበረውን ሴቶች ብቻ የተወዳደሩበት የዓለም ሪኮርድ ባሻሻለችበት 1:05፡16 የሆነ ሰዓት ነው፡፡ ጄፕቺርቺር የዓለም ሪኮርድ በመስበሯ በአሸናፊነቷ ከምታገኘው 30 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የገንዘብ ሽልማት በተጨማሪ የ50 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ጉርሻ አግኝታለች፡፡ 1:05፡18 በሆነ ሰዓት የብር ሜዳልያ ደረጃውን በመያዝ ያጠናቀቀችው ጀርመናዊቷ ሜላት ቀጄታም ሴቶች ብቻ የተወዳደሩበት የአውሮፓ ሪኮርድን ለማሻሻል በቅታለች፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ያለምዘርፍ የኋላው የራሷ ምርጥ በሆነ 1:05፡19 ሰዓት ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳልያ አሸንፋለች፡፡

እንደተጠበቀው የውድድሩ ፉክክር በዋነኛነት በኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን አትሌቶች መካከል ሆኖ የተስተዋለበት የሴቶቹ ውድድር ተጠባቂ ለነበሩት ኢትዮጵያውያኑ ነፃነት ጉደታ እና አባበል የሻነህ መጥፎ አጋጣሚንም የያዘ ነበር፡፡ ሁለቱ አትሌቶች በውድድሩ ላይ ያጋጠማቸው የመውደቅ አደጋ ባስመዘገቡት ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ በፊት መሪነቱ ቦታ የነበሩት ተፎካካሪዎች ወደመጨረሻው መስመር እየተቃረቡ በነበረበት ሁኔታ የተፈጠረው የአባበል የሻነህ እና የኬንያዊቷ ጄፕኮስጋይ የእግር መጠላለፍ የፉክክሩን መልክ የቀየረው ነበር፡፡ ከውድድሩ በፊት የአሸናፊነት ከፍ ያለ ግምት ከተሰጣቸው መካከል የነበሩት ሁለቱም አትሌቶች ወድቀው ሲነሱ በእነርሱ እና በሌሎች ተፎካካሪዎቻቸው መካከል የተፈጠረውን የ30 ሜትር ያህል ልዩነት ማጥበብ ሳይችሉ አባበል አምስተኛ ጄፕኮስጋይ ስድስተኛ ሆነው ለማጠናቀቅ ተገደዋል፡፡ ሌላኛዋ ተጠባቂ አትሌት ኢትዮጵያዊቷ ነፃነት ጉደታም በሶስተኛው ዙር ዘጠና ዲግሪ መታጠፊያ ላይ ከወደቀች በኋላ ከፊት መሪዎቹ ጋር የተፈጠረውን ልዩነት ማጥበብ ሳትችል ውድድሩን በስምንተኛነት አጠናቃለች፡፡ ነፃነት በዚህ ውድድር ላይ ድልን በመቀዳጀት ያለፈው ውድድር የሻምፒዮንነት ክብሯን የማስጠበቅ ሕልም ነበራት፡፡ አባበል እና ጄፕኮስጋይ እስከወደቁበት ሰዓት ድረስ የጄፕቺርቺር ብርቱ ተፎካካሪዎች ሆነው ቢቆዩም ባልተጠበቀው የመደነቃቀፍ ክስተት ወደኋላ መቅረታቸውን ተከትሎ ፔሬስ ጄፕቺርቺር ከተቀሩት ተፎካካሪዎቿ የተሻለ የአጨራረስ ብቃትን በማሳየት ድልን ተቀዳጅታለች፡፡ ውድድሩ በከተማ ውስጥ በተዘረጋ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀትን የሚሸፍን የዙር መወዳደሪያ ስፍራ ላይ እንደመከናወኑ መታጠፊያዎች ይበዙበት ነበር፡፡ ይህም ለሁሉም አትሌቶች ውድድሩን ትንሽ ያከበደባቸው ይመስላል፡፡ 

በመጀመሪያዎቹ ሶስት ጨራሽ አትሌቶች የሰዓት ድምር አሸናፊዎቹ በተለዩበት የሴቶች የቡድን ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች 3:16:39 በሆነ አዲስ የሻምፒዮናው ሪኮርድ ሰዓት የወርቅ ሜዳልያና የ15 ሺህ ዶላር አሸናፊ ለመሆን በቅተዋል፡፡

የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የሴቶች የቡድን ሜዳልያ አሸናፊዎች  Photo © Dan Vernon for World Athletics

በሴቶች ኢትዮጵያን ወክለው የተወዳደሩት አትሌቶች ውጤት

3ኛ ያለምዘርፍ የኋላው (1:05:19 የግል ምርጥ ሰዓቷ)

4ኛ ዘይነባ ይመር (1:05:39 የግል ምርጥ ሰዓቷ)

5ኛ አባበል የሻነህ (1:05:41)

8ኛ ነፃነት ጉደታ (1:06:46 የዓመቱ ምርጥ ሰዓቷ)

15ኛ መሰረት ጎላ (1:09:02 የግል ምርጥ ሰዓቷ)

የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የወንዶች የተናጠል ሜዳልያ አሸናፊዎች  Photo © Dan Vernon for World Athletics

በወንዶቹ ፉክክር ጃኮብ ኪፕሊሞ የሻምፒዮናውን ሪኮርድ ጭምር ባሻሻለ 58 ደቂቃ ከ49 ሰከንድ የሆነ ሰዓት በውድድሩ የ28 ዓመት ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ የወርቅ ሜዳልያ ያሸነፈ ኡጋንዳዊ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ኪፕሊሞ ለራሱም ለሀገሩም የረጅም ግዜ ታሪክ የሚሆን ገድል በፈፀመበት የግድኒያው ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የቅድመ ውድድር ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምቱ ተሰጥቶ የነበረው ለሀገሩ ልጅ ጆሹዋ ቼፕቴጊ ነበር፡፡ ሆኖም ኪፕሊሞም በዚህ ውድድር ላይ ለሀገሩ ልጅ ቼፕቴጊ እና ሌሎች ተፎካካሪዎቹ በቀላሉ የሚረታ እንደማይሆን የነበረውን ግምት እውን በማድረግ ተፎካካሪዎቹን ድል ነስቷቸዋል፡፡ በዚህ ውድድር ታሪክ ከዚህ በፊት በተናጠል ሜዳልያ ያሸነፈ አንድም ኡጋንዳዊ ያልነበረ ሲሆን በቡድን ያስመዘገቡት ብቸኛ የነሐስ ሜዳልያም እ.ኤ.አ. በ2004 ዓ.ም. የተገኘ ነበር፡፡ ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኡጋንዳውያን የረጅም ርቀት ሩጫ ውድድር ተፎካካሪነት እያደገ ከመጣበት ሁኔታ አንፃር የዛሬው ውጤታማነታቸው ብዙም አያስደንቅም፡፡ በግድኒያው ፉክክር ኬንያዊው ኪቢዎት ካንዲዬ በ58 ደቂቃ ከ54 ሰከንድ ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ኢትዮጵያዊው አምደወርቅ ዋለልኝ የግሉ ምርጥ በሆነ 59 ደቂቃ ከ08 ሰከንድ ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ከውድድሩ በፊት የመገናኛ ብዙኃን ዋነኛ የትኩረት ማዕከል የነበረውና ከዚህ በፊት በግማሽ ማራቶን ተወዳድሮ የማያውቀው የወቅታዊ ምርጥ ብቃት ባለቤቱ ኡጋንዳዊ ጆሹዋ ቼፕቴጊ የራሱ ምርጥ በሆነ 59:21 ሰዓት አራተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡  

በመጀመሪያዎቹ ሶስት ጨራሽ አትሌቶች የሰዓት ድምር አሸናፊዎቹ በተለዩበት የወንዶች የቡድን ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች 2:58:25 በሆነ ሰዓት የብር ሜዳልያና የ12 ሺህ ዶላር አሸናፊ ሆነዋል፡፡

የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የወንዶች የቡን ሜዳልያ አሸናፊዎች  Photo © Dan Vernon for World Athletics

በወንዶች ኢትዮጵያን ወክለው የተወዳደሩት አትሌቶች ውጤት

3ኛ አምደወርቅ ዋለልኝ (59:08 የግል ምርጥ ሰዓቱ)

5ኛ አንዳምላክ በልሁ (59:32 የዓመቱ ምርጥ ሰዓቱ)

10ኛ ልዑል ገብረስላሴ (59:45 የዓመቱ ምርጥ ሰዓቱ)

11ኛ ሀይለማሪያም ኪሮስ (1:00:01 የግል ምርጥ ሰዓቱ)

22ኛ ጉዬ አዶላ (1:00:50 የዓመቱ ምርጥ ሰዓቱ)

በዓለም የግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ በሁለቱም ፆታዎች ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ለወጡ አትሌቶች እና ቡድኖች የገንዘብ ሽልማት (በአሜሪካን ዶላር) የሚሰጥ ሲሆን የሽልማት ገንዘብ አሰጣጡም እንደሚከተለው ነው፡-

በግል

1 ኛ $ 30,000

2 ኛ $ 15,000

3 ኛ 10,000

4 ኛ $ 7000

5 ኛ $ 5,000

6 ኛ $ 3000

ቡቡድን

1 ኛ $ 15,000

2 ኛ $ 12,000

3 ኛ $ 9000

4 ኛ $ 7500

5 ኛ $ 6000

6 ኛ $ 3000