በ2021 የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ውድድሮች ሶስት ኢትዮጵያውያን በነጥብ የአጠቃላይ አሸናፊ ሆኑ

3-Ethiopian-overall-winners-of-the-2021-World-Athletics-Indoor-Tour

በስፔን ማድሪድ በተደረገው የመጨረሻ ውድድርም በአራት የሩጫ ፉክክሮች በአሸናፊነት አጠናቀዋል

በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ የበላይ ተቆጣጣሪነት ከጥር ወር መጨረሻ አንስቶ በአውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ በሚገኙ ስድስት ከተሞች ሲካሄዱ የቆዩት የወርቅ ደረጃ ያላቸው የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች በትላንትናው ዕለት በስፔን ማድሪድ በተካሄደው የመጨረሻ ፉክክር ተጠናቀዋል፡፡ የወርቅ ደረጃ ባላቸው ስድስቱ (በካርልስሩህ – ጀርመን፣ በቦስተን – ዩ.ኤስ.ኤ.፣ በሌቪን – ፈረንሳይ፣ በኒው ዮርክ ሲቲ – ዩ.ኤስ.ኤ.፣ በቶሩን – ፖላንድ፣ እና በማድሪድ – ስፔን) ውድድሮች ላይ የተሳተፉ አትሌቶች በነጥብ የአጠቃላይ አሸናፊ ለመሆን ያደርጉት የነበረው ፉክክርም ትላንት ፍፃሜ አግኝቷ፡፡ የነጥብ ፉክክሩ ትላንት ሲጠናቀቅ ሶስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የአጠቃላይ አሸናፊ በመሆን እያንዳንዳቸው የ10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ተሸላሚ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ከግራ ወደ ቀኝ ለምለም ኃይሉ 3000 ሜ. ፣ ሰለሞን ባረጋ 1500 ሜ. እና ሀብታም አለሙ 800 ሜ. የአጠቃላይ አሸናፊዎች ዋንጫቸውን ይዘው (Photo Real Federación Española de Atletismo)

በማድሪድ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ካስመዘገቧቸው አራት ድሎች የመጀመሪያውን ያሳካችው በሴቶች 800 ሜትር የውድድር ቦታውን ሪኮርድ በማሻሻል ጭምር በአንደኛነት ያጠናቀቀችው ሀብታም አለሙ ነች፡፡ ሀብታም የነጥብ የአጠቃላይ አሸናፊነቷን ቀደም ብላ በፈረንሳይ ሌቪን እና በፖላንድ ቶሩን ባገኘቻቸው 17 ነጥቦች አረጋግጣ የነበረ ቢሆንም ምንም አይነት መዘናጋት ሳታሳይ 1 ደቂቃ ከ58.94 ሰከንድ በሆነ ሰዓት ሌላ ድልና ተጨማሪ አስር ነጥቦችን አስመዝግባለች፡፡ በአጠቃላይ ፉክክሩም 27 ነጥብ በማስመዝገብ የ2021 ዓ.ም. የዓለም የቤት ውስጥ ውድድሮች የሴቶች 800 ሜትር አሸናፊ እና የ10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ተሸላሚ ሆናለች፡፡

የሴቶች 800 ሜትር አሸናፊዋ ሀብታም አለሙ

በማድሪዱ ውድድር ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አሸናፊ የዓለም የቤት ውስጥ ውድድሮች የነጥብ ፉክክሩ አካል ባልሆነው የሴቶች 1500 ሜትር በርቀቱ የመጀመሪያ የውድድር ተሳትፎዋን ያደረገችው ሂሩት መሸሻ ናት፡፡ በይበልጥ በ800 ሜትር ሯጭነቷ የምትታወቀው ሂሩት በርቀቱ የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ሻምፒዮን መሆን የቻለች ሲሆን በዚህ ወር ውሰጥ የሀገሯ ልጅ ጉዳፍ ፀጋዬ በፈረንሳይ ሌቪን ለሰበረችው የዓለም የቤት ውስጥ 1500 ሜትር አዲስ ክብረ ወሰን በአሯሯጭነት ጥሩ አስተዋፅኦ ማድረጓም ይታወሳል፡፡ በማድሪድ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የ1500 ሜትር ውድድሯን ሳትጠበቅ በርቀቱ ልምድ ካላቸው ተፎካካሪዎቿ ልቃ 4 ደቂቃ ከ09.42 ሰከንድ በሆነ ሰዓት በአንደኛነት አጠናቃለች፡፡      

በወንዶች በ 1500 ሜትር የዕለቱ ውድድር እንዲሁም የአጠቃላይ የነጥብ ፉክክሩ አሸናፊ ለመሆን የበቃው ኢትዮጵያዊው ሰለሞን ባረጋ ድሉን ያሳካው ከተፎካካሪዎቹ ምንም አይነት ፈተና ሳያጋጥመው ነው፡፡ ከውድድሩ መጀመር አንስቶ አሯሯጩን እግር በእግር ሲከታተል የቆየው ሰለሞን በመጨረሻም ፉክክሩን ከሰዓት ጋር በማድረግ የውድድር ቦታውን ሪኮርድ ባሻሻለበት  3 ደቂቃ ከ35.42 ሰከንድ አንደኛ ሆኖ ጨርሷል፡፡ ስፔናዊው የአውሮፓ የቤት ውስጥ የ1500 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት ሄሱስ ጎሜዝ የራሱ ምርጥ በሆነ 3 ደቂቃ ከ36.32 ሰከንድ ሁለተኛ ሲወጣ የሀገሩ ልጅ ሰርጂዮ ፓኒያጉዋ የራሱ ምርጥ በሆነ 3 ደቂቃ ከ39.09 ሰከንድ ሶስተኛ ወጥቷል፡፡ የሰለሞን የቅርብ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ ተጠብቆ የነበረው ፖላንዳዊው ማርሲን ሌቫንዶቭስኪ አራተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ ሰለሞን ባረጋ በማድሪድ ባመዘገበው ድል የአጠቃላይ ነጥቡን ድምር ወደ 20 ከፍ በማድረግ የ2021 ዓ.ም. የዓለም የቤት ውስጥ ውድድሮች የወንዶች 1500 ሜትር አሸናፊ እና የ10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ተሸላሚነቱን አረጋግጧል፡፡

የወንዶች 1500 ሜትር አሸናፊው ሰለሞን ባረጋ

በዕለቱ ተጠባቂ ከነበሩት ውድድሮች አንዱ ሁለቱን የወቅታዊ ድንቅ አቋም ባለቤት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች (ጉዳፍ ፀጋዬ እና ለምለም ሀይሉን) ያገናኘው የሴቶች 3000 ሜትር ሲሆን በሁለቱ ብርቱ ፉክክርም ሌላ የዓለም ሪኮርድ ሊመዘገብ እንደሚችል ተጠብቆ ነበር፡፡ ከአሯሯጮቻቸው መውጣት በኋላ በመሪነቱ ስፍራ ላይ እየተፈራረቁ የተጓዙት ጉዳፍ እና ለምለም እንደተጠበቀው የዓለም ሪኮዱን ለመስበር ባይበቁም ሁለቱም የየራሳቸውን ምርጥ ሰዓት ያሻሻሉበትን ስኬት አስመዝግበዋል፡፡ ውድድሩን የራሷ ምርጥ በሆነ 8 ደቂቃ ከ22.65 ሰከንድ በአንደኛነት ያጠናቀቀችው ጉዳፍ የጨረሰችበት ሰዓት የሴቶች የዓለም የቤት ውስጥ 3000 ሜትር የምንግዜም ሁለተኛው ፈጣን ሆኖም ተመዝግቦላታል፡፡ ከአስራ አምስት ቀን በፊት በፈረንሳይ ሌቨን የ1500 ሜትር የዓለም የቤት ውስጥ ሪኮርድን ለመስበር የበቃችው ጉዳፍ በማድሪድ የ3000 ሜትር ውድድሩን ብታሸንፍም ሪኮርዱን ለማሻሻል ባለመቻሏ ስትበሳጭ ታይታለች፡፡ በሁለተኛነት ያጠናቀቀችው ለምለም በበኩሏ ባለፉት አስራ አምስት ቀናት ውስጥ ለሶስተኛ ግዜ የራሷን ምርጥ ለማሻሻል የበቃችበትን 8 ደቂቃ ከ29.28 ሰከንድ የሆነ ሰዓት አስመዝግባለች፡፡ በቀደሙት ሁለት ውድድሮች በፈረንሳይ ሌቪን 8:32.55 እንዲሁም በፖላንድ ቶሩን 8:31.24 በሆነ ሰዓት የርቀቱ አሸናፊ መሆን መቻሏም ይታወሳል፡፡ ለምለም በሶስት ውድድሮች ባስመዘገበችው 27 ነጥብ የ2021 ዓ.ም. የዓለም የቤት ውስጥ ውድድሮች የሴቶች 3000 ሜትር የአጠቃላይ አሸናፊ በመሆንም የ10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ተሸላሚነቷን አረጋግጣለች፡፡

የሴቶች 3000 ሜትር አሸናፊዋ ጉዳፍ ፀጋዬ

በሙሉ በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተያዙት የዓለም የቤት ውስጥ የሴቶች 3000 ሜትር የምንግዜም ፈጣን ሰዓት የመጀመያ አምስት ደረጃዎች

ደረጃ    ሰዓት              አትሌት            ቀን እ.ኤ.አ.     የውድድር ቦታ   

1      8:16.60       ገንዘቤ ዲባባ           6 ፌብሩዋሪ 2014      ስቶክሆልም

2      8:22.65        ጉዳፍ ፀጋዬ           24 ፌብሩዋሪ 2021     ማድሪድ

3      8:23.72        መሰረት ደፋር         3 ፌብሩዋሪ 2007      ስቱትጋርት

4      8:23.74        መሰለች መልካሙ      3 ፌብሩዋሪ 2007      ስቱትጋርት

5      8:25.27        ስንታየሁ እጅጉ        6 ፌብሩዋሪ 2010      ስቱትጋርት