በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን ዛሬ እና ነገ የሚያደርጉት የ5000ሜ. የፍፃሜ ፉክክር በጉጉት ይጠበቃል

Mo vs Ethiopians

ገንዘቤ ዲባባ በ5000ሜ. ማጣሪያው ላይ ያልተሳተፈችው ለመወዳደር በሚያስችላት የመንፈስ ዝግጁነት፣ የብቃት እና የጤንነት ላይ ስላልነበረች መሆኑን በለንደን የሚገኙት የቡድኑ ኃላፊዎች አሳውቀዋል

ሊጠናቀቅ በተቃረበው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ እና ነገ የሚካሄዱት የሁለቱም ፆታዎች የ5000ሜ. የፍፃሜ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተጨማሪ ሜዳልያዎችን እንደሚያስመዘግቡባቸው የሚጠበቁባቸው ናቸው፡፡ ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ ሙክታር እድሪስ እና ሰለሞን ባረጋ ከእንግሊዛዊው ሞ ፋራህ እንዲሁም አልማዝ አያና፣ ሰንበሬ ተፈሪ እና ለተሰንበት ግደይ ከኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪ ጋር ብርቱ ትንቅንቅ እንደሚያደርጉ የሚጠበቁባቸው የ5000ሜ. የፍፃሜ ውድድሮች በኢትዮጵያ አቆጣጠር የወንዶቹ ዛሬ ምሽት 4፡20 የሴቶቹ ነገ ምሽት 3:35 የሚደረጉ ይሆናል፡፡

Mo vs Ethiopiansኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሞ ፋራህን ለማሸነፍ ከምንግዜውም በላቀ ቁርጠኝነት በቀረቡበት በዚህ የዓለም ሻምፒዮና ባለፈው ረቡዕ በተካሄደው የማጣሪያ ውድድር ከምድብ አንድ ዮሚፍ ቀጄልቻ በ13፡30.07 አንደኛ፣ ሞ ፋራህ በ13፡30.18 ሁለተኛ፣ ሙክታር እድሪስ በ13፡30.22 ሶስተኛ በመሆን ዛሬ ምሽት በጉጉት ለሚጠበቀው ፍፃሜ ያለፉ ሲሆን ሶስተኛው የኢትዮጵያ ተወካይ ሰለሞን ባረጋም ፈጣን ሰዓት የተመዘገበበትን የሁለተኛው ምድብ የማጣሪያ ፉክክር በ13:21.50 በቀዳሚነት በመጨረስ በፍፃሜው ከቡድን ጓደኞቹ ጋር ሞ ፋራህን ለመፈተን የሚያስችለውን ዕድል አመቻችቷል፡፡ ሰለሞን የማጣሪያ ውድድሩን ከጨረሰ በኋላ በሰጠን አስተያየት ‹‹የነበረው ዝናባማ የአየር ሁኔታ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ውድድር ሲገባ ሁልግዜም ቢሆን የፍራቻ ስሜት መኖሩ አይቀርም ነገር ግን ውድድሩ ውስጥ ከገባሁ በኋላ ብዙም ተፅዕኖ አይፈጥርብኝም፡፡ በፍፃሜው ውድድር ላይ እንዲህ እናደርጋለን ብንል ላይሆን ይችላል ነገር ግን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ውጤት ለማምጣት እንጥራለን›› ያለ ሲሆን ከምድብ አንድ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ሞ ፋራህ በበኩሉ ‹‹ሁሉም ተወዳዳሪዎች ለእኔ ተዘጋጅተው እንደሚመጡ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ እኔም ለፍፃሜው ፉክክር ዝግጁ ነኝ›› በማለት ቢናገርም ዩሴይን ቦልት በ100 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ላይ የገጠመውን ያልተጠበቀ ሽንፈት ጠቅሶም የ5000ሜ. የፍፃሜ ፉክክሩ ቀላል እንደማይሆንለት አመላክቷል፡፡ በወንዶች 5000ሜ. ለፍፃሜ የበቁት ሶስቱም ኢትዮጵያውያን በዘንድሮው የውድድር ዓመት በርቀቱ የምርጥ ሰዓት ካላቸው የመጀመሪያ አምስት አትሌቶች መካከል እንደመሆናቸው ሞ ፋራህን የማሸነፍ ብቃቱ እና ዕድሉ እንዳላቸው ይታመናል፡፡

ሐሙስ ዕለት በተካሄደው የሴቶቹ ማጣሪያ ለፍፃሜው ያለፉት ሶስቱ ኢትዮጵያውያን (አልማዝ አያና፣ ሰንበሬ ተፈሪ እና ለተሰንበት ግደይ) በነገው ፍፃሜ ከቅድመ ውድድር ተጠባቂዋ ኬንያዊት ሔለን ኦቢሪ ጋር ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡  በሴቶች 5000ሜ. የአሸናፊነቱ የቅድሚያ ግምት የተሰጣት ኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪ በማጣሪያው ውድድር ከምድብ አንድ በ14፡56.70 በቀዳሚነት ያጠናቀቀች ሲሆን ኢትዮጵያውያኑ አልማዝ አያና (14፡57.06) እና ሰንበሬ ተፈሪ (14.57.23) ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመውጣት ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል፡፡ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ ተወካይ ለተሰንበት ግደይ ለፍፃሜ ያለፈችውም ከምድብ ሁለት በ14፡59.34 አንደኛ በመውጣት ነው፡፡

Obiri vs Ethiopiansተጠባቂዋ ኬንያዊት ሔለን ኦቢሪ ከማጣሪያው ውድድር በኋላ በሰጠችው አስተያየት ‹‹በጥሩ ስሜት እና በጣም ጥሩ በሆነ ብቃት ላይ እገኛለሁ፡፡ ማንንም አልፈራል፡፡ ለውድድሩ በደንብ ተዘጋጅቼ የመጣሁ ሲሆን በዕሁዱ የፍፃሜ ውድድር ላይም ምርጥ ብቃቴን ማሳየት እፈልጋለሁ፡፡ የዕሁዱ የፍፃሜ ውድድር በጣም ጥሩ ፉክክር የሚደረግበት ይሆናል፡፡ ምናልባትም ፍፃሜው በፍጥነት የታጀበ ሩጫ እንዲሆን እፈልግ ይሆናል፡፡ አልማዝ አያና ወደፊት የምትወጣ ከሆነ ተከትያት እወጣለሁ፡፡ አልማዝን በርቀት መከተል የማይታሰብ ነው፡፡ እርሷ በውድድሩ ላይ የምትሰጠውን ምላሽ ማየትም የሁሉም ሰው ፍላጎት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ትኩረቴን በ1500 ሜትር ላይ ብቻ አድርጌ በመቆየቴ የ5000ሜ. ብቃቴ በጣም ጥሩ አልነበረም፡፡ ዘንድሮ ግን በ5000 ሜትርም በተሻለ ብቃት ላይ እገኛለሁ፡፡ አሁንም 1500 ሜትር የፍጥነት ልምምዶችን እየሰራሁ እገኛለሁ ስለዚህ ለጥሩ አጨራረስ የምተቀምበት ፍጥነቱም አለኝ›› ብላለች፡፡ በፍፃሜው ፉክክር እንደ ቡድን የኢትዮጵያ እና ኬንያ በግል ደግሞ የአልማዝ እና ኦቢሪ የሚያደርጉት ፉክክር የብዙዎችን ቀልብ የሚስብ የውድድሩ የትኩረት ማዕከል እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡

ዘግይቶም ቢሆን በትላንትናው ዕለት ይፋዊ ምላሽ ከቡድኑ ኃላፊዎች የተሰጠበት የገንዘቤ ዲባባ በ5000ሜ. የማጣሪያ ውድድር ላይ አለመሳተፍ ምክንያቱ ‹‹አትሌቷ ከ1500ሜ. ውድድሯ በኋላ እራሷን እንደገመገመችው የብቃት ደረጃዋ እየወረደ መሆኑና ለመወዳደር በሚያስችላት የመንፈስ ዝግጁነት እንዲሁም የጤንነት ሁኔታ ላይ አለመገኘቷ ነው›› በማለት በለንደን የሚገኘው የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝደንት እና የቡድን መሪው አትሌት ገብረእግዚአብሄር ገብረማሪያም በትላንትናው ዕለት ቡድኑ ባረፈበት ሆቴል በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አሳውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.