በፓሪስ ዳይመንድ ሊግ ገንዘቤ ዲባባ እና አልማዝ አያና በ5000ሜ. የሚያደርጉት ፉክክር በጉጉት ይጠበቃል

Ayana v Dibaba

Ayana v Dibaba

ቅዳሜ ሰኔ 27/2007 በሚደረገው የአሬቫ ፓሪስ ዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይ በጉጉት ከሚጠበቁት ፉክክሮች ዋነኛው ገንዘቤ ዲባባ እና አልማዝ አያና አንድ ላይ የሚሮጡበት የሴቶች 5000ሜ. መሆኑን የውድድሩ አዘጋጆች ይፋ አድርገዋል፡፡
በዓለም የምንግዜም ምርጥ የ5000ሜ. ሯጮች ዝርዝር ከጥሩነሽ ዲባባ እና መሰረት ደፋር ቀጥለው በ3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሁለቱ አትሌቶች የዘንድሮውን የውድድር ዓመት በምርጥ ብቃት የጀመሩ ሲሆን በዓለም የምንግዜም ምርጦቹ ዝርዝር ላይ በ3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ያበቋቸውን ሰዓቶች ያስመዘገቡትም ምርጥ ጅማሬያቸውን ባሳዩባቸው የዘንድሮ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ላይ ነው፡፡ አልማዝ በሻንግሀይ ዳይመንድ ሊግ የራሷን ምርጥ ሰዓት በማሻሻል ያሸነፈችበት 14፡14.32 ጥሩነሽ ዲባባ በ5000ሜ. የዓለም ሪኮርድነት ከያዘችው ሰዓት በ3.17 ሰከንድ ያነሰ ነበር፡፡ ገንዘቤ በዩጂን ያሸነፈችበት 14:19.76 የሆነ ሰዓትም የራሷን ምርጥ እና የውድድር ስፍራውን ሪኮርድ ያሻሻለችበት ነበር፡፡
አልማዝ እና ገንዘቤ በ2014 ዓ.ም. በ5000ሜ. ውድድር በተገናኙባቸው አጋጣሚዎች እኩል ሁለት ሁለት ግዜ የተሸናነፉ ሲሆን ገንዘቤ በዳይመንድ ሊግ (በጣልያን ሮም እና በሞናኮ) አልማዝ በአፍሪካ ሻምፒዮና እና በኮንቲኔንታል ካፕ (ሁለቱንም በሞሮኮ ማራካሽ) የበላይነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ሁለቱ አትሌቶች የፊታችን ቅዳሜ በፓሪስ ስታድ ደ ፍራንስ እርስ በርስ በሚፎካከሩበት ውድድር ላይ እስከ ውድድሩ አጋማሽ ድረስ በሁለት አሯሯጮች (ፔስ ሜከሮች) እንደሚታገዙ የተገለፀ ሲሆን ጥሩነሽ ዲባባ በ2008 ያስመዘገበችውን እና 14፡11.15 የሆነውን የሴቶች 5000ሜ. የዓለም ሪኮርድ የመስበር ሙከራ እንደሚያደርጉም ይጠበቃል፡፡
ገለቴ ቡርቃ፣ አዝመራ ገብሩ፣ ነፃነት ጉደታ፣ አለሚቱ ሀሮዬ፣ በላይነሽ ኦልጂራ እና ሰንበሬ ተፈሪ በዘንድሮው አሬቫ ፓሪስ ዳይመንድ ሊግ የሴቶች 5000ሜ ውድድር እንደሚካፈሉ አስቀድሞ ስማቸው ይፋ ከሆነው ተወዳዳሪዎች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሲሆኑ ብርቱ ተፎካካሪ ሊሆኑ ከሚችሉት ኬንያውያን መካከል ፌይዝ ኪፕዬጎን እና ሜርሲ ቼሮኖ ይገኙበታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.