በበርሚንግሀሙ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለሀገራቸው የምንግዜም ሁለተኛውን ምርጥ ውጤት አስመዘገቡ

Medal Winners
  • የገንዘቤ ዲባባ ድርብ ድል በዓለም እና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ውድድሮች ታሪክ አዲስ የስኬት ሪኮርዶችን አስጨብጧታል
  • ዮሚፍ ቀጄልቻ የ3000ሜ. የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮንነት ክብሩን ማስጠበቅ ችሏል
  • ብዙም ዕውቅና የሌለው ሳሙኤል ተፈራ በ1500ሜ. ተጠባቂዎቹን አትሌቶች በመርታት በወርቃማ ድል ብቅ ብሏል

ላለፉት አራት ቀናት በእንግሊዝ በርሚንግሀም በተከናወነው 17ኛው የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በጀግኖች አትሌቶቿ ብርታት በእስከዛሬ ተሳትፎዋ የምንግዜም ሁለተኛውን ምርጥ ስኬት ለማስመዝገብ በቅታለች፡፡ እ.አ.አ. በ1989 ዓ.ም. በሀንጋሪ ቡዳፔስት ከተከናወነው ሁለተኛ ውድድር አንስቶ በመሳተፍ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ግዜ አራት የወርቅ ሜዳልያዎችን ማሸነፍ በቻለችበት የበርሚንግሀሙ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ላይ በሴቶች ገንዘቤ ዲባባ በ1500ሜ. እና 3000ሜ. ድርብ የወርቅ ሜዳልያ ድልን ስታስገኝ በወንዶች 3000ሜ. ዮሚፍ ቀጄልቻ በ1500ሜ. ሳሙኤል ተፈራ ለሀገራቸው ወርቅ ሜዳልያ ያስገኙት አሸናፊዎች ናቸው፡፡ ወጣቱ ሰለሞን ባረጋም በወንዶች 3000ሜ. የብር ሜዳልያ አሸናፊ ለመሆን በቅቷል፡፡

የሜዳልያ አሸናፊዎቹ

ገንዘቤ ዲባባ ድንቅ ብቃቷን በማሳየት የኢትዮጵያን ስም ከፍ አድርጋ ማስጠራት በቻለችበት የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ውድድር የመክፈቻ ዕለት በ3000ሜ. ያሸነፈች ሲሆን ከሁለት ቀን በኋላ በተሳተፈችበት የ1500ሜ. የፍፃሜ ፉክክር ላይም ሌላ የወርቅ ሜዳልያ ድል በማስመዝገብ ኢትዮጵያ ከዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ቀጥላ በሜዳልያ ሰንጠረዡ ከዓለም ሁለተኛ ሆና እንድታጠናቅቅ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ አድርጋለች፡፡

በተከታታይ ሶስት ቀን የተወዳደረችው ገንዘቤ የ3000ሜ. ፍፃሜ ውድድሯን ባደረገች ማግስት በ1500ሜ. ማጣሪያ ላይ ተሳታፊ የነበረች ሲሆን በሁለቱም ርቀቶች ገንዘቤን በመከተል የብር እና ነሐስ ሜዳልያ አሸናፊ መሆን የቻሉትም የኔዘርላንድ እና እንግሊዝ አትሌቶች ናቸው፡፡ በ3000ሜ. ፉክክሩ ላይ የብር ሜዳልያ ተሸላሚ የነበረችው ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሀሳን በ1500ሜ. ከሁለት ዓመት በፊት ያገኘችውን የ1500ሜ. አሸናፊነት ክብር ለማስጠበቅ የገባች ቢሆንም በገንዘቤ እና እንግሊዛዊቷ ላውራ ሙዪር ተቀድማ ሶስተኛ ሆና ለማጠናቀቅ ተገዳለች፡፡ ሁለቱ አትሌቶች በ1500ሜ. የፍፃሜው ውድድር ላይም እንደ 3000 ሜትሩ የቅርብ ተፎካካሪ ለመሆን ቢሞክሩም ሲፋንም ሆነች በደጋፊዋ ፊት የሮጠችው የአውሮፓ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና የድርብ ድል ባለቤቷ ሙዪር የገንዘቤን የመጨረሻ ሁለት ዙሮች ፍጥነት መቋቋም አልተቻላቸውም፡፡

ገንዘቤ ሁለተኛ የወርቅ ሜዳልያ ድሏን ካሳካች በኋላ ለውድድሩ አዘጋጆች በሰጠችው አስተያየት ‹‹የድርብ ድል ባለቤት ለመሆን በመብቃቴ በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ባለፈው ዓመት ጤናዬ የተስተካከለ አልነበረም ነገር ግን ዘንድሮ ለሀገሬ ለመሮጥና ውጤት ለማስመዝገብ በደንብ ተዘጋጅቼ ነበር›› ብላለች፡፡

ከዚህ በፊትም ኢትዮጵያን በመወከል በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ሜዳልያዎችን የማስገኘት ገድል ያላት ገንዘቤ በ2016 የሪዮ ኦሊምፒክ በ1500ሜ. የብር ሜዳልያ፣ በ2015 የቤይጂንግ ዓለም ሻምፒዮና በ1500ሜ. የወርቅ እንዲሁም በ5000ሜ. የነሐስ ሜዳልያ፣ በ2008 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከ20 ዓመት በታች የወርቅ ሜዳልያ፣ በ2014 የዓለም ዋንጫ አፍሪካን ወክላ በ3000ሜ. የወርቅ ሜዳልያ፣ በ2008 ከ20 ዓመት በታች የዓለም ሻምፒዮና በ5000ሜ. የብር ሜዳልያ፣ በ2010 ከ20 ዓመት በታች የዓለም ሻምፒዮና በ5000ሜ. የወርቅ ሜዳልያ እንዲሁም በ2014 በአፍሪካ ሻምፒዮና ላይ በ5000ሜ. የብር ሜዳልያ ድሎችን ማስመዝገብ የቻለች ድንቅ አትሌት ናት፡፡ በአሁኑ ሰዓትም አምስት የዓለም የቤት ውስጥ (የ1500ሜ.፣ የአንድ ማይል፣ የ2000ሜ. የ3000ሜ. እና 5000ሜ.) እንዲሁም የቤት ውጭ 1500ሜ. የዓለም ሪኮርዶች በስሟ ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡

በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ላይም ኢትዮጵያን በመወከል ከዚህ ቀደም ሶስት ግዜ የወርቅ ሜዳልያ ድሎችን (በ3000ሜ. ሁለት በሶፖት 2014 እና በፖርትላንድ 2016 እንዲሁም በ1500ሜ. አንድ በኢስታንቡል 2012) አስመዝግባ የነበረችው ገንዘቤ ዘንድሮ በበርሚንግሀም ባከለቻቸው ተጨማሪ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች ከኢትዮጵያ በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ውድድሮች ላይ አምስት የወርቅ ሜዳልያ ማስገኘት የቻለች ብቸኛዋ አትሌት ለመሆን በቅታለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በአንድ ውድድር ላይ የ1500ሜ. እና 3000ሜ. የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ በመሆኑ ረገድ በ1999ዓ.ም. ይህን ገድል ከፈፀመችው ሮማኒያዊቷ ጋብሬላ ዛቦ ቀጥሎ ብቸኛዋ ተጠቃሽ ሆናለች፡፡ ኢትዮጵያዊቷ መሰረት ደፋር በወርቁ ብዛት አሁን በገንዘቤ ብትበለጥም በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በ3000ሜ. 4 የወርቅ፣ 2 የብር እና አንድ የነሐስ ሜዳልያ (በድምሩ 7 ሜዳልያዎችን) በማስገኘት አሁንም ተጠቃሽ ነች፡፡

በውድድሩ ላይ በአራት ሴት እና አምስት ወንድ አትሌቶች የተወከለችው ኢትዮጵያ የትኩረት ማዕከል ከነበረችው ገንዘቤ ዲባባ ውጪም ውጤት እንደሚያመጡላት የምትጠብቃቸው ሌሎች አትሌቶቿ በውድድሩ መዝጊያ ዕለት አኩሪ ድልን አስመዝግበውላታል፡፡ ከፍተኛ ተጠባቂነት በነበረው የወንዶች 3000ሜ. ፍፃሜ የወቅቱ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮንነት ክብሩን ለማስጠበቅ የሮጠው ዮሚፍ ቀጄልቻ የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ ለመሆንና ክብሩን ለማስጠበቅ የበቃ ሲሆን ወጣቱ ተስፈኛ ሰለሞን ባረጋም የብር ሜዳልያ ድልን ተቀዳጅቷል፡፡ ሀጎስ ገብረሕይወት በኬንያዊው ቤትዌል ኪፕሮቲች ተቀድሞ አራተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡

ዮሚፍ ቀጄልቻ ውድድሩን በአሸናፊነት ሲጨርስ (Photo © Getty Images for IAAF)

የውድድሩ አሸናፊ የሆነው ዮሚፍ ከድሉ በኋላ በሰጠው አስተያየት ‹‹በድጋሚ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮን ለመሆን በመቻሌ በጣም ተደስቻለሁ፡፡ በውድድሩ ላይ ሁሉም ተፎካካሪዎቼ በራስ የመተማመን ስሜታቸው ሙሉ እንደነበር አይቻለሁ፡፡ ሆኖም ሁሉንም መቆጣጠር የጫልኩት እኔ ነበርኩ፡፡ ውድድሩን ከጓደኞቼ ጋር ሳፈጥነው ያለኝን አቅም ማሳየት ችያለሁ፡፡ በዚህ ዓመት በአንዳንድ ውድድሮች ላይ በሁለተኛነት አጠናቅቅ ነበር፡፡ አሰልጣኜም አቋሜ እንከንየለሽ እንዲሆን ከእኔ ጋር ሲሰራ ነበር፡፡ ይህን ድል ለሀገሬ እና ለህዝቤ ስላስገኘሁም በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ከዚህ በፊት በመጨረሻዎቹ ጥቂት ዙሮች ላይ የፍጥነት እንዲሁም ውድድሮችን ያለመቆጣጠር ችግሮች ነበሩብኝ፡፡ እነዚህን ድክመቶቼን ለማስተካከልም በደምብ ስለማመድ ነበር፡፡ አሁን የአጨራረስ ፍጥነቴም በጣም ጥሩ ሆኗል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት የ5000ሜ. የዓለም ሪኮርድን መስበር እፈልጋለሁ›› ብሏል፡፡

ሰለሞን ባረጋ የማጣሪያ ውድድሩን በቀዳሚነት በጨረሰበት ወቅት (Photo © Getty Images for IAAF)

በመጨረሻዎቹ ጥቂት ሜትሮች ውስጥ ያለውን አቅም በመጠቀም ፍጥነቱን ጨምሮ ኬንያዊውን አትሌት በመቅደም የብር ሜዳልያ ባለቤት መሆን የቻለው ሰለሞን ባረጋ ‹‹የዘንድሮ ዕቅዴ አንደኛ ሆኖ መጨረስ ነበር ነገር ግን ዮሚፍ በጣም ጠንካራ አትሌት ነው፡፡ ሁለተኛ ሆኜ በመጨረሴና የብር ሜዳልያ በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ አሁን ጓደኛዬ ዮሚፍ አሸናፊ ሆኗል፡፡ የእኔም ቀጣይ ዕቅድ አንድ ቀን የዓለም ሻምፒዮናውን ድል መቀዳጀት ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ብቃት ያላቸው ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጮች ሀገር ናት ዛሬም ምርጥ መሆናችንን አሳይተናል›› ብሏል፡፡

ሳሜኤል ተፈራ ውድድሩን በአሸናፊነት ሲጨርስ (Photo © Getty Images for IAAF)

ብዙም ዕውቅና የሌለው ሳሙኤል ተፈራ ኢትዮጵያን ወክሎ በመወዳደሩ ረገድ ያለው ብቸኛ የከዚህ ቀደም ተሞክሮው ባለፈው ነሐሴ ወር ለንደን ላይ በተከናወነው የዓለም ሻምፒዮና በ1500ሜ. ማጣሪያ 8ኛ በመሆን ያጠናቀቀበት ነው፡፡ ባለፈው ጥር ወር መጀመሪያ ላይ በፈረንሳይ ቫል ደ ሩዪ በተካሄደ የቤት ውስጥ የ1500ሜ. ውድድር ላይ ለመጀመሪያ ግዜ ተሳትፎ ባስመዘገበው ፈጣን ሰዓት በበርሚንግሀሙ የዓለም ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን ለመወከል ተቀዳሚ ተመራጭ መሆን ችሏል፡፡ ወደ ዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮናው ሲመጣ የአሸናፊነቱ የቅድሚያ ግምት ባይሰጠውም ከፍ ያለ ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩትን እና ልምድ ያላቸውን አትሌቶች ጭምር በመቅደም ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ የተካበተ ልምድ ያላቸው ፖላንዳዊው ማርሲን ሌቫንዶቭስኪ እና ሞሮኳዊው አደላቲ ኢጉዴር ሳሙኤልን ተከትለው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሲወጡ ኢትዮጵያዊው አማን ወጤ አራተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ ሳሙኤል ከድሉ በኋላ ስሜቱን ሲገልፅ ‹‹ውድድሩ ሲጀመር በጣም ቀዝቃዛ ነበር፡፡ በታክቲክ የተሳሰረ መሆኑም ለእኔ ጥሩ አልነበረም ነገር ግን በመጨረሻዎቹ ሁለት ዙሮች ያለኝን አቅም ለመጠቀምና ለማሸነፍ ችያለሁ›› ብሏል፡፡

በመጨረሻው ቀን ከተካሄዱት የፍፃሜ ውድድሮች መካከል ኢትዮጵያዊቷ ሀብታም አለሙ የተሳተፈችበት የሴቶች 800ሜ. አንዱ ነበር፡፡ ብሩንዲያዊቷ ፍራንሲኔ ኒዮንሳባ አሜሪካዊቷ አጄ ዊልሰን እና ከግሬት ብሪቴይን ሼላይናን በማስከተል ባሸነፈችበት በዚህ ውድድር ሀብታም አለሙ አራተኛ ወጥታለች፡፡

ከ144 አገሮች የመጡ ከ600 በላይ አትሌቶችን ለአራት ቀናት ሲያፎካከር ቆይቶ በተጠናቀቀው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና 27 የዲስኳሊፋይድ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡ ከውሳኔዎቹ መካከል 4ቱ የአነሳስ ስህተት የፈፀሙ አትሌቶች ከውድድሩ ውጭ እንዲሆኑ የተደረጉባቸው ሲሆኑ ከመሮጫ መስመር በመውጣት 14 አትሌቶች፣ ከመሮጫ ትራክ ጠርዝ ውጪ በመርገጥ 6 አትሌቶች፣ ተፎካካሪ አትሌት ላይ መንገድ በመዝጋት 1 አትሌት፣ ሆን ብሎ መሰናክል በመጣል 1 አትሌት እንዲሁም በ4X400ሜ. የዱላ ቅብብል ውድድር ላይ የመቀበያ ስፍራን ባለመጠበቅ አንድ ቡድን (4 አትሌቶች) ከተወዳደሩ በኋላ ያስመዘገቡት ውጤት እንዲሰረዝ ተደርጓል፡፡ በዚህም በድምሩ 30 አትሌቶች የውድድር ሕጉን አስደሳች ያልሆነ የውሳኔ ፅዋ በመቅመስ አዝነው ተመልሰዋል፡፡

ውድድሩ ሲጠናቀቅ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ በ6 የወርቅ፣ 10 የብር እና 2 የነሐስ በድምሩ በ18 ሜዳልያዎች የሜዳልያ የደረጃ ሰንጠረዡን የበላይነት ስትወስድ ኢትዮጵያ በ4 የወርቅ እና 1 የብር ሜዳልያ በድምሩ በ5 ሜዳልያ ሁለተኛ ሆና ለማጠናቀቅ በቅታለች፡፡  ይህ ውጤት በ2008 ዓ.ም. ስፔን ቫሌንሲያ ላይ ተካሂዶ 4 የወርቅ 1 የብር እና 1 የነሐስ ሜዳልያ ከተገኘበት ቀጥሎ የኢትዮጵያ የምንግዜም ሁለተኛው ምርጥ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.