በቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት የተጠናቀቀው የ2007 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ዕለት ክስተቶች

St. George best 11 against Dedebit - May 31-2015

St. George player’s receiving their medals

የ2007 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስን አንግሶ፣ ወልዲያ ከነማን እና ሙገር ሲሚንቶን አውርዶ፣ ኤሌክትሪክን በመውረድ ስጋት አሳቅቆ ተጠናቋል፡፡ ቀጣዩ ፅሁፍ የወራጅ ቀጠና ግብግቡ ልብ-ሰቃይ የነበረበትን የሊጉን የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች እና የፍፃሜውን ስነ-ስርዓት ይዳስሳል፡፡

 

የአሳዳጊዎቹ ያለመውረድ ትንቅንቅ

በ1980ቹ እና በ1990ቹ በቀድሞው የሊጉ መዋቅርም ሆነ በአዲሱ የፕሪምየር ሊግ የመብራት ኃይልን (የአሁኑ ኤሌክትሪክ) ያህል በየዓመቱ ለአዳዲስ ወጣት ተጨዋቾች እድል ይሰጥ የነበረ ክለብ ማስታወስ ያስቸግራል፡፡ መብራቶች በየዓመቱ ወደተለያዩ ክለቦች የሚጓዙባቸውን ተጨዋቾች ከወጣት ቡድናቸው በሚያሳድጓቸው በርካታ ወጣቶች እና ከሌሎች ክለቦች በሚያመጧቸው ጥቂት ብዙም የማይታወቁ ተጨዋቾች በመተካት ድንቅ እንቅስቃሴ የሚያደርግ እና ለዋንጫዎች የሚፎካከር ቡድን ይገነቡ ነበር፡፡ የ1980ቹ አጋማሽ የወንድማገኝ ከበደ እና የ1990ቹ መጀመሪያ የሀጎስ ደስታ ቡድኖች ለዚህ ተጠቃሽ ይሆናሉ፡፡ መብራቶች በአዲሱ ሚሌኒየም የሌሎቹን ክለቦች አካሄድ በመከተል ከዚህ ማንነታቸው ሲያፈገፍጉ፣ አሳዳጊነታቸውን እና ለወጣቶች እድል የመስጠት ማንነታቸውን ከተረከቡ ጥቂት ቡድኖች አንዱ ሙገር ሲሚንቶ ነበር፡፡ ሙገሮች እንደመብራት ኃይል ዋንጫዎችን አያግኙ፣ አልያም ለዋንጫዎች አይፎካከሩ እንጂ በወጣቶች ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው በመስራት ከታች ከመጡበት ከ1991 ጀምሮ ለ16 ዓመታት በሊጉ መቆየት ችለዋል፤ በርካታ ከዋክብትንም በማፍራት ብሔራዊ ቡድናችንን እና ታላላቆቹን ክለቦች ጠቅመዋል፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት ወጣቶችን ከስር አሳድጎ በትልቁ ሊግ እድል በመስጠት ረገድ ከሙገር የተሻለም ሆነ የሚፎካከር ቡድን አልነበረም፡፡ እነዚህ ሁለት ‘አሳዳጊ’ ቡድኖች ባለፉት ጥቂት ዓመታት ላለመውረድ ሲጫወቱ እና በመጨረሻ ሲተርፉ ቆይተው ዘንድሮ ግን ከሁለቱ አንዱ መውረዱ ግድ እንደሆነ ሊጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲቀሩ ተረጋገጠ፡፡

St. George best 11 against Dedebit - May 31-2015

ኤሌክትሪክ አሁን ከአሳዳጊነት ይልቅ ብዙ ገንዘብ በማውጣት እና የውጪ ዜጎችን በመቅጠር ላይ ትኩረት ቢያደርግም (አሁንም ግን ጥቂት ከስር ያደጉ ተጨዋቾች እንዳሉት ሳይዘነጋ) የቀድሞው ታሪኩ እና ውለታው እንዲሁም የሙገር በእዚህ ገንዘብ ሁሉን በተቆጣጠረበት ዘመን ለመርሆው ታማኝ ሆኖ መቆየቱ ለገለልተኞች ለማን ድጋፍ መስጠት እንዳለባቸው ግራ እንዲጋቡ አድርጓቸው ነበር፤ የመውረድ ነገር ሁለቱንም ባይጠጋቸውም የብዙዎች ምርጫ ነበር፡፡ ነገር ግን የአንዱ ከሊጉ መለየት የግድ ነበርና በመጨረሻው ወሳኝ ጨዋታ የኤሌክትሪክ ነጥብ መጣል እና የእራሱ ድል ማድረግ ያስፈልገው የነበረው የግርማ ሀብተዮሐንስ ሙገር መከላከያን በመርታት የእራሱን ስራ ቢወጣም፣ ቦዲቲ ላይ ኤሌክትሪክ በወላይታ ድቻ ላይ ድል በማግኘቱ አሰላን መቀመጫው ያደረገው ቡድን በአሳዛኝ ሁኔታ በከ16 ዓመታት በኋላ ከሊጉ ተሰናብቷል፡፡ እሁድ በስምንት ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ፍልሚያ ሙገሮች በርካታ አዳዲስ ወጣቶችን ይዞ ወደሜዳ የገባው መከላከያን ለማሸነፍ ተቸግረው የነበረ ቢሆንም (በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያዎች በርካታ ጥሩ የማግባት እድሎችን አምክነዋል) በጨዋታው መጠናቀቂያ ገደማ በረከት ሳሙኤል በጭንቅላቱ ገጭቶ ባስቆጠረው ጎል እጅግ ‘ውድ የመሰሉ’ ሶስት ነጥቦችን ወስደዋል፡፡

Ethi Premier League Player of the year-Behailu Assefa St. George

ጨዋታው እንደተጠናቀቀ የታየው ነገር አስገራሚ ድራማ ነበር፡- በተመሳሳይ ሰዓት በቦዲቲ በተደረገው ጨዋታ ኤሌክትሪክ በወላይታ ድቻ የመረታቱን የተዛባ መረጃ በመስማታቸው የሙገር ተጨዋቾች በደስታ አበዱ፤ ሜዳውንም በመዞር ሲደግፋቸው ከዋለው የአዲስ አበባ ስታዲየም ታዳሚ ጋር ፈነጠዙ፡፡ በ2003 ዋንጫውን በኢትዮጵያ ቡና ለመነጠቃቸው የኤሌክትሪክን ሚና የማይረሱት (በወቅቱ ፈረሰኞቹ አስደናቂ የድል ጉዞ ላይ እያሉ መብራቶች ወሳኝ ሁለት ነጥብ አስጥለዋቸው ነበር) የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችም በሙገር ‘መትረፍ’ እና በኤሌክትሪክ ‘መውረድ’ በደስታ አዜሙ፤ ጨፈሩ፡፡ ጥቂት የኤሌክትሪክ ደጋፊዎችም በሰሙት ዜና ተደናግጠው ከራሳቸው ጋር መቆዘም ጀመሩ፡፡ የሙገር አባላት ሜዳው ውስጥ ደስታቸውን ከገለፁ በኋላ ወደ መልበሻ ክፍል ገቡ፡፡ በዚህ አፍታ ሁሉ ነገር ግልፅ የሆነ መስሎ ነበር፡፡ በቀጣይ ሊጫወቱ የተዘጋጁት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ተጨዋቾች ጨዋታቸውን ለመጀመር ወደ ሜዳ ሊገቡ ሲሉ ግን ከስታዲየሙ አስተዋዋቂ አንድ ግራ አጋቢ ዜና ተሰማ – ኤሌክትሪክ ወላይታ ድቻን 1ለ0 አሸንፏል፤ እናም የተረፈው ሙገር ሳይሆን ኤሌክትሪክ ነው፡፡ አስተዋዋቂው የህዝቡን ግራ መጋባት በመረዳቱም ይመስላል ዜናውን በመደጋገም ይፋ አደረገ፡፡ እናም ስሜቶች ተገለባበጡ፤ የተደሰቱት አዘኑ፤ ያዘኑት ባልጠበቁት የምስራች ፈነጠዙ፡፡ በዚህ ሁሉ ውዥንብር ውስጥ ግን በዚህ ዘመን እንዲህ አይነት የመረጃ መዛባት እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ እና የሊጉ አወዳዳሪ አካል ለምን በፍጥነት ውዥንብሩን እንዳላጠራ ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኗል፡፡ የሙገሩ አሰልጣኝ ግርማ ሀብተዮሐንስ ከጨዋታው በኋላ ለኢ.ብ.ኮ በሰጡት ቃል ባለፉት ዓመታት እጅግም ባልተሻሻለው ‘ሚጢጢዬ’ በጀታቸው ለዝውውር ሚሊዮኖችን ከሚያፈሱ ቡድኖች ጋር ለመፎካከር እንደተቸገሩ ገልፀዋል፤ በየዓመቱ ብዙ ተጨዋቾች እየለቀቁባቸው በአዳዲስ ወጣቶች አዲስ ቡድን በመገንባት የመፎካከር ፈተናን ከዚህ በላይ መቋቋም እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡ የረዥም ጊዜ አገልጋዩ አሰልጣኝ ከዚህ መሰረታዊ ምክንያት ባሻገርም አነጋጋሪ የነበረው የኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከነማን ጨዋታም ለመውረዳቸው በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡

Top Scorrer of the year Samuel Sanumi- DedebitGoal keeper of the year Robert Odankara St. georgeFair play award winner - Dedebit

 

ሌሎች መነጋገሪያ ነጥቦች

  • ሻምፒዮኖቹ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኝ የነበረው ደደቢትን በመርታት አጨራረሳቸውን አሳምረዋል፡፡ 1ለ0 በተጠናቀቀው ጨዋታ ዘንድሮ በጎል አግቢ አማካይነት የተገለጠው ምንተስኖት አዳነ ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሯል፡፡ የቀድሞው የተከላካይ አማካይ ወደ ፊት ገፋ ባለ አዲስ ሚና ድንቅ ዓመት (በተለይ በሁለተኛው ዙር) አሳልፏል፡፡ ምንተስኖት ከመሀል ሜዳ እየተነሳ በሊጉ ብቻ ስምንት ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን ይህም አጥቂዎች ካልተቆጠሩ በሊጉ ከፍተኛ ጎል አግቢ ያደርገዋል፤ ከአዳነ ግርማ በመቀጠልም የክለቡ ከፍተኛ ጎል አግቢ ነው፡፡
  • ፍፁም ሳይጠበቅ ሁለተኛ ለመሆን የተጫወቱት አዳማ ከነማዎች የዓመቱ የመጀመሪያ የሜዳ ሽንፈታቸውን አስተናግደው ምኞታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ የደደቢት በቅዱስ ጊዮርጊስ መረታት ለአሸናፊ በቀለ ቡድን መልካም አጋጣሚ የነበረ ቢሆንም በበረከት ወልደፃዲቅ ብቸኛ ጎል በአርባምንጭ ከነማ ተረተው አጋጣሚውን ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡
  • የውድድር ዘመኑ የመጨረሻ ሩብ ያልተመቸው ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር 2ለ2 ተለያይቷል፡፡ ሞገስ ታደሰ እና ፍፁም ተፈሪ ለሲዳማ እንዲሁም ፊሊፕ ዳውዝ እና ሰሎሞን ገብረመድህን ለንግድ ባንክ ጎሎቹን አስቆጥረዋል፡፡ በወልዲያ በተደረገው ጨዋታም ወልዲያ ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ 2ለ2 ተለያይተዋል፡፡ ማይክ ሰርጂ እና ወሰኑ ማዜ የወልዲያን ከሊጉ የመሰናበቻ ጎሎች በስማቸው ሲያስመዘግቡ ጋቶች ፓኖም እና ዮናስ ገረመው ለቡናማዎቹ አግብተዋል፡፡ ሀዋሳ ከነማ በበኩሉ በሜዳው ዳሸን ቢራን 4ለ2 ረትቷል፡፡ አንተነህ ተሻገር፣ ታፈሰ ሰሎሞን፣ ተመስገን ተክሌ እና ሙሉጌታ ምህረት የሀዋሳን ጎሎች ሲያስቆጥሩ የዳሸንን ጎሎች ኤዶም ሆሶሮቪ እና የተሻ ግዛው አስቆጥረዋል፡፡
  • የ26 ሳምንቱ የሊግ ጉዞ ሲፈፀም ባለድሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 57 አድርሷል፡፡ ደደቢት በ13 ነጥቦች ርቆ ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ አዳማ ከነማ በ42 ነጥብ የሜዳልያውን ስፍራ አሟልቷል፡፡ ሲዳማ ቡና (40)፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (39)፣ ኢትዮጵያ ቡና (36) እና አርባ-ምንጭ ከነማ (35) ከደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ በላይ ሲያጠናቅቁ፣ መከላከያ (34)፣ ወላይታ ድቻ (33)፣ ሀዋሳ ከነማ (33)፣ ኤሌክትሪክ (30) እና ዳሸን ቢራ (30) ከደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ በታች ከወራጅ ቀጠናው በላይ ሆነው ፈፅመዋል፡፡ ሙገር ሲሚንቶ (27) እና ወልዲያ ከነማ (16) ወደ ብሔራዊ ሊጉ ወርደዋል፡፡
  • በጎል አግቢነት የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኑሚ በ22 ጎሎች ከፍተኛ ጎል አግቢ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ የንግድ ባንኩ ናይጄሪያዊ የሀገሩ ልጅ ፊሊፕ ዳውዝ በ19 እና የኢትዮጵያ ቡናው ቢኒያም አሰፋ በ16 ጎሎች ተከታትለውት ጨርሰዋል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አዳነ ግርማ እና የሃዋሳ ከነማው ተመስገን ተክሌ (11 ጎሎች) እና የሲዳማ ቡናው ኤሪክ ሙራንዳ (10) ሁለት አሀዝ ጎል ላይ የደረሱ ሌሎቹ ተጨዋቾች ናቸው፡፡
  • ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት የዘንድሮው ውድድር መዝጊያ ጨዋታ በኋላ በተካሄደው ደማቅ ዝግጅት ለሻምፒዮኖቹ ዋንጫ እና ገንዘብ እንዲሁም የሜዳልያ ስፍራ ይዘው ላጠናቀቁትም የገንዘብ ሽልማቶች ከመሰጠታቸው ባሻገር፣ ከፍተኛ ጎል አግቢው እና በየዘርፉ የዓመቱ ምርጥ ተደርገው የተመረጡ ግለሰቦችም ተሸልመዋል፡፡ ከፍተኛ ጎል አግቢው ሳሙኤል ሳኑሚ፣ ኮከብ ተጨዋች ተደርጎ የተመረጠው የቅዱስ ጊዮርጊሱ በኃይሉ አሰፋ እና ኮከብ አሰልጣኙ ፋሲል ተካልኝ በነፍስ-ወከፍ 25 ሺህ ብር ሲሸለሙ፣ ለአራተኛ ተከታታይ ዓመት ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኖ የጨረሰው ሮበርት ኦዳንካራ 15 ሺህ ብር ተሸልሟል፡፡ ኃይለየሱስ ባዘዘው ኮከብ የመሀል ዳኛ 10 ሺህ ብር እንዲሁም ሀይለራጉኤል ወልዳይ ኮከብ ረዳት ዳኛ 8 ሺህ ብር ተሸልመዋል፡፡ የፀባይ ዋንጫ አሸናፊ ደደቢት ሆኗል፡፡

Referre of the Year Haileyesus BazezewBest Assistant ref Haileraguel Welday

በቡድን 1ኛ ለወጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ 150 ሺህ፣ 2ኛ ለወጣው ደደቢት 100ሺህ፣ 3ኛ ሆኖ ላጠናቀቀው አዳማ ከነማ 75ሺህ ብር በሽልማትነት ተበርክቷል፡፡

 

6 thoughts on “በቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት የተጠናቀቀው የ2007 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ዕለት ክስተቶች

  1. Mengizem Giyorgis ! Bulla Gellebba Dengay Kenemma Were Kenemma kechalachu deresoubin be were be sedebe wancha yelem respect St.George fc we are 12 times champions !

  2. The conclusion of the league was cecpensing,and dramatic.All clubs do there best .For the next year we are expecting more.

Leave a Reply

Your email address will not be published.