በሽንፈት የጀመሩት ዋልያዎቹ በሽንፈት አጠናቅቀዋል

Waliya vs Angola - 1

በሽንፈት የጀመሩት ዋልያዎቹ በሽንፈት አጠናቅቀዋል

የ2016 ቻን ውድድር ተሳታፊው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድብ የመጨረሻ ጨዋታውን ከአንጎላ ጋር  አድርጎ ተጨማሪ ቆይታ ይኖረው አልያም አይኖረው እንደሆነ ወስኗል፡፡ ቀጣዩ ዘገባ ዋልያዎቹ የጠበበ የማለፍ እድል ይዘው የገቡበትን ጨዋታ ይዳስሳል፡፡

ዋልያዎቹ በመጀመሪያ ጨዋታቸው በዲ.ሪ.ኮንጎ በሰፊ ውጤት ቢረቱም በሁለተኛ ጨዋታቸው ከካሜሩን ላይ የወሰዱት አንድ ነጥብ የጠበበም ቢሆን ከምድባቸው ወደቀጣዩ ዙር የማለፍ እድልን ይዘው የመጨረሻ የምድብ ጨዋታቸው እንዲጀምሩ አድርጓቸዋል፡፡ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌም ይህን በሌላ ጨዋታ ላይ የተመሰረተ ተልዕኮ ለማሳካት ቢያንስ የራሳቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እንደሚያስችላቸው የገመቱትን አሰላለፍ ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ አሰልጣኙ ቀዳሚ ተመራጩ ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ ጉዳት ስላጋጠመው ይድነቃቸው ኪዳኔን በቋሚዎቹ መካከል ሲያቆሙ፣ በተከላካይ ስፍራ ግን ከካሜሩኑ ጨዋታ ለውጥ አላደረጉም፡፡ አማካይ ክፍል ላይ በጉዳት ምክንያት መሰለፍ ባልቻለው የሁልጊዜ ቀዳሚ ተመራጫቸው ጋቶች ፓኖም ምትክ ተስፋዬ አለባቸውን ሲጠቀሙ ፈጣሪ አማካዩ ኤልያስ ማሞ ከመጀመሪያ ተሰላፊነት ተቀንሶ ሁለቱ አጥቂዎች ታፈሰ ተስፋዬ እና ሙሉዓለም ጥላሁን አብረው ጀምረዋል፡፡ በነዚህ ተጨዋቾችም ቡድኑ ዝርግ 4-4-2 አሰላለፍን የተጠቀመ ይመስል ነበር፡-

ግብ ጠባቂ፡- ይድነቃቸው ኪዳኔ

ተከላካዮች፡- ስዩም ተስፋዬ፣ አስቻለው ታመነ፣ ያሬድ ባዬ እና ተካልኝ ደጀኔ

አማካዮች፡- አስራት መገርሳ፣ ተስፋዬ አለባቸው፣ በኃይሉ አሰፋ እና ራምኬል ሎክ

አጥቂ፡- ታፈሰ ተስፋዬ እና ሙሉዓለም ጥላሁን

ዋና አሰልጣኝ፡- ዮሐንስ ሳህሌ

በቀደምት ሁለት የምድቡ ጨዋታዎቻቸው በካሜሩን እና ዲ.ሪ.ኮንጎ ሽንፈቶችን ያስተናገዱት እና ከምድብ ማለፍ እንደማይችሉ አረጋግጠው ወደሜዳ የገቡት አንጎላዊያኑ በበኩላቸው የሚከተሉትን ተጨዋቾች ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡      

ግብ ጠባቂ፡- ዶሚኒክ

ተከላካዮች፡- ናታኤል፣ ሲልቫ፣ ጎሚቶ እና አይዛክ

አማካዮች፡- ማኑቾ፣ ቡአ እና ያኖ

አጥቂዎች፡- ጌልሰን፣ ሚንጎ ቢሌ እና አሪ ፓፔል

ዋና አሰልጣኝ፡-  ዦዜ አንቶኒዮ ኪላምባ

 

Waliya vs Angola - 2

በዋና ከተማዋ ኪጋሊ፣ በአማሆሮ ስታዲየም የተካሄደው ጨዋታ አጀማመር የተጠበቀውን እና የወሳኝነቱን ያህል የሞቀ አልነበረም፡፡ በተለይም ከምድባቸው ለማለፍ በብዙ ጎሎች ማሸነፍ ያስፈልጋቸው የነበሩት ዋልያዎቹ ቀዝቅዞ መታየት የሚያስገርም ነበር፡፡ ለሱፐርስፖርት ቴሌቪዥን ጨዋታውን ያስተላልፍ የነበረው ኮሜንታተርም ይህን በተደጋጋሚ ይገልፅ ነበር፡፡ እንዲያውም ምንም የማለፍ እድል ያልነበራቸው አንጎላዊያኑ ከዋልያዎቹ በተሻለ ኳሱን ለመቆጣጠር እና ስጋት ለመፍጠር ይጥሩ ነበር፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ከዋልያዎቹ በኩል በኃይሉ አሰፋ አንዴ ቅጣት ምት መቶ በአግዳሚው ላይ ከወጣበት እና በሌላ አጋጣሚ ራሱ በኃይሉ ደካማ ምት መትቶ በግብ ጠባቂው በቀላሉ ከተያዘበት ሙከራ ውጪ ያልተመለከትን ሲሆን በተሻለ ቁጥር ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎችን ያደረጉት አንጎላዊያኑ በበኩላቸው የግራ ተከላካያቸው ናታኤል በመስመር ወደውስጥ ገብቶ ብቻ ለብቻ ከተገናኘ በኋላ ወደጎል መትቶ በይድነቃቸው የተያዘበት ሙከራ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ዋልያዎቹ ከእረፍት ሲመለሱ የተጨዋች ቅያሬ በማድረግ ታፈሰ ተስፋዬን አስወጥተው ኤልያስ ማሞን ተክተዋል፡፡ የአሰልጣኛቸው ምክር የሰራላቸው የመሰሉት ግን አንጎላዊያኑ ነበሩ፡፡ በበለጠ የማሸነፍ ፍላጎት እና አላማ ባለው አጨዋወት የተመለሱ የመሰሉት የአሰልጣኝ ዦዜ አንቶኒዮ ኪላምባ ልጆች ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በ54ኛው ደቂቃ የአሪ ፓፔል ጎል መሪ መሆን ችለዋል፡፡ አሪ ፓፔል ራሱ ለቡድን ጓደኛው ጌልሰን ያቀበለውን ኳስ ጌልሰን ከቀኝ በኩል መልሶ ወደ ሳጥን ውስጥ በመሬት አሻግሮለት አሪ ፓፔል በቀላሉ ጎል አድርጎታል፡፡ አጥቂው ኳሱን ወደጎልነት ሲቀይር ግን በጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ የነበረ ይመስል ነበር – የመስመር ዳኛው አልተመለከቱትም እንጂ፡፡ ከዚያ በኋላ በ65ኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ በማራኪ የተረከዝ አቀባበል ለስዩም ተስፋዬ ያዘጋጀለትን የዋልያዎቹ አምበል ወደጎል ቢመታውም ምቱ ጥንካሬ ስላልነበረው የግብ ጠባቂው ሲሳይ ሆኗል፡፡ በ74ኛው ደቂቃ በጥሩ የቡድን ስራ የመጣው ኳስ ወደመስመር ወጥቶ ሚንጎ-ቢሌ ከቀኝ መስመር በመሬት ያሻገረለትን ኳስ አሪ ፓፔል በቀላሉ ወደጎል በመቀየር የቡድኑን መሪነት አስፍቷል፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች ብቻ በኋላ ግን ከበኃይሉ የተሻገረውን ጥሩ ኳስ ስዩም ከጠበበ ማእዘን መትቶ ወደጎል በመቀየር በዚህ ውድድሩም ሆነ ባጠቃላይ በቻን የዋልያዎቹን የመጀመሪያ ጎል አስመዝግቧል፡፡ የጎሉ አስደናቂነት ምነው ወሳኝ ጎል በሆነ የሚያስብል ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ዋልያዎቹ አቻ ለመሆን ቢፍጨረጨሩም የጎል አጋጣሚዎችን እምብዛም ለመፍጠር ሳይችሉ በ2ለ1 ሽንፈት ጨዋታውን አጠናቅቀዋል፡፡

ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ያለፈጣሪ አማካይ ወደሜዳ የመግባታቸውን እውነታ ተከላክለዋል፡፡ ለማለፍ የግድ ማሸነፍ ስለነበረባቸው አጥቂዎቻቸውን በሙሉ ወደሜዳ ማስገባታቸውን የተናገሩት አሰልጣኙ በሁለት ተከላካይ አማካዮች የገቡት የቡድኑ ‹ዘይቤ› በመሆኑ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ ዮሐንስ በውጤቱ ብዙም እንዳልተከፉ እና ብዙ ታላላቅ ሀገራት ባልተሳተፉበት ውድድር ላይ መሳተፋቸው በራሱ ስኬት እንደሆነም በስፍራው ለነበሩት ጋዜጠኞች አረጋግጠዋል፡፡

ዋልያዎቹ ሲመዘኑ

ግብ ጠባቂ

ይድነቃቸው ኪዳኔ፡- በዋናው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ መጎዳት ምክንያት የተሰለፈው ይድነቃቸው አስከፊ ጨዋታ አላሳለፈም፤ ጎሎቹም የተቆጠሩት ከቅርበት ነበር፡፡

ተከላካዮች   

ስዩም ተስፋዬ፡- በቅርብ ጊዜያት እየተለመደ የመጣው ክስተት ተደግሟል – ስዩም ከተከላካይ መስመር ተነስቶ በመሄድ ጎል አስቆጥሯል፡፡ አምበሉ ጎል ያገባ እና በቡድኑ ጥቂት የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ ነበረ ቢሆንም በመከላከሉ ረገድ ግን አሁንም ጥያቄዎች ይነሱበታል፡፡

አስቻለው ታመነ፡- አስቻለው የቡድኑን እንቅስቃሴ ከኋላ ለማስጀመር ሲሞክር ቢውልም በመከላከል ስራው ላይ ግን አቋሙ እየወረደ ለመሆኑ ማሳያ የሚሆን እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡

ያሬድ ባዬ፡- እንደ አስቻለው ያሬድም የአንጎላን አጥቂዎች በተለይም አሪ ፓፔልን ለማቆም ተቸግሮ ነበር፡፡

ተካልኝ ደጀኔ፡- በማጥቃቱ ረገድ ቡድኑን የማያግዘው ተካልኝም በአሪ ፓፔል እና ሚንጎ-ቢሌ ፍጥነት እና ክህሎት ሲቸገር ውሏል፡፡

አማካዮች

አስራት መገርሳ፡- በመጀመሪያው አጋማሽ የቀድሞውን አስራት መሆን ተስኖት የነበረው አማካይ በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ ሲያደራጅ እና የቡድኑን ቅርፅ ሊያስተካክል ሲጥር ነበር፡፡

ተስፋዬ አለባቸው፡- ኳስ አስተካክሎ የማቀበል ችግር በግልፅ ለታየበት ተስፋዬ ጨዋታውም ሆነ ውድድሩ አስከፊ ነበሩ፡፡ የሚታወቅበት ኳስ የማስጣል ብቃቱም አብሮት አልነበረም፡፡

በኃይሉ አሰፋ፡- በኃይሉ ለስዩም ጎል ያቀበለው ኳስ የሚደነቅ ቢሆንም ራሱ ያገኘውን ጥሩ ኳስ ግን ሊጠቀምበት አልቻለም፡፡

ራምኬል ሎክ፡- ራምኬል በሁሉ ረገድ ደካማ ነበር፡፡ በተለይ የሚያገኛቸውን ኳሶች የሚያበለሽበት መንገድ ፍፁም ከእሱ የማይጠበቅ ነበር፡፡ እንዴት ጨዋታውን ሊጨርስ እንደቻለ ከአሰልጣኙ ሌላ የሚያውቅ አይኖርም፡፡

አጥቂ

ታፈሰ ተስፋዬ፡- ከአንድ ግማሽ የበለጠ ሜዳ ውስጥ እንዲቆይ ያልተፈቀደለት አንጋፋው አጥቂ ከአቅሙ በላይ ሜዳ እንዲሸፍን የተገደደ ይመስል ነበር፡፡

ሙሉዓለም ጥላሁን፡- ሙሉዓለም እንደተለመደው በመታገሉ ረገድ መጥፎ ባይሆንም እንደአጥቂ የጎል እድሎችን የመፍጠር አቅሙ ግን ደካማ ነበር፡፡

ተቀይረው የገቡ

ኤልያስ ማሞ፡- ሁለተኛውን ግማሽ የተጫወተው አማካይ ጥቂት መልካም ነገሮችን አሳይቷል፤ በቀላሉ ኳስ የተነጠቀባቸው አጋጣሚዎችም አይዘነጉም፡፡

ቢኒያም በላይ፡- ለመመዘን የሚያበቃ የጨዋታ ጊዜ አልነበረውም፡፡

ዋና አሰልጣኝ፡- ዮሐንስ ሳህሌ፡- አሰልጣኙ ይዘውት ከገቡት አሰላለፍ እና ተጨዋቾች ጀምሮ የጨዋታ አቀራረባቸውም ሆነ ቅያሬዎቻቻው ጥያቄ የሚያስነሱ ነበሩ፡፡

ተጨማሪ ነጥብ

  • ዋልያዎቹ ከሚገኙበት ምድብ ዲ.ሪ.ኮንጎን 3ለ1 የረታችው ካሜሩን በአንደኛነት እና ዲ.ሪ.ኮንጎ በሁለተኛነት አልፈዋል፡፡ በሩብ ፍፃሜው የምድብ አንድ አላፊዎቹን ኮትዲቯርን እና ርዋንዳን ይገጥማሉ፡፡ ዋልያዎቹ በአንድ ነጥብ እና አራት የጎል እዳ መጨረሻ ሆነው አጠናቅቀዋል፡፡

2 thoughts on “በሽንፈት የጀመሩት ዋልያዎቹ በሽንፈት አጠናቅቀዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published.