በሰኔ 16ቱ የቦንብ ጥቃት በተጠረጠሩ 5 ግለሰቦች ላይ የሽብር ወንጀል ክስ ተመሰረተ

Abiy Ahmed Meskel Square

የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ በሰኔ 16ቱ የቦንብ ጥቃት ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች ላይ በሽብር ወንጀል ክስ መሰረተባቸው።

ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ በሽብር ወንጀል ክስ የመሰረተባቸው ጌቱ ግርማ ፣ብርሃኑ ጁፋር ፣ጥላሁን ጌታቸው ፣ባህሩ ቶላና ደሳለኝ ተስፋዬ ላይ ነው፡፡።

ዓቃቢ ህግ ሁሉንም ተከሳሾች ሰኔ 16 በነበረው የድጋፍ ሰልፍ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ላይ ጥቃት ለማድረስ ብሎም በሀገሪቱ እየታየ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ በጠቅላይ ሚንስትሩ የሚመራ መንግስት መኖር የለበትም የሚል ዓለማ ይዘው እንደነበር በክሱ ተጠቅሷል።

እንደ ክሱ ገለፃ ከሆነ ይህ ዓለማ ቀድሞ በተደራጀ በኦነግ ስም በሚንቀሳቀሱና የቦንብ ጥቃት ማድረስ በሚችሉ አባላት አማካኝነት መሆን እንዳለበትም የሚያስችል ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎ ነው ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተቀባይነት የሌላቸው በተለይም በኦሮሞ ብሔር ዘንድ እንደማይፈለጉ አድርጎ ለማሳየት በሚረዳ መልኩ ጥቃቱን ለመፈፀም ዐቅደው መንቀሳቀሳቸውም በክሱ ተጠቁሟል።

ለዚህ ደግሞ በኬንያ የምትኖር ገነት ታምሩ ወይንም በቅፅል ስም ቶሎሺ ታምሩ በምትባል የቡድኑ አባል አማካኝነት ተልዕኮ እንደተሰጣቸው በክሱ ተገልጿል።

አንደኛ ተከሳሽ ጌቱ ግርማ ከዚች ሴት ጋር ሰኔ 2010 በስልክ በመገናኘት ‘ ለጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የድጋፍ ሰልፍ መካሄድ የለበትም’ ፣’መሰረታዊ ለውጥ አልመጣም ‘፣ ‘ ሰልፉን የጠራው ገለልተኛ ወገን ሳይሆን ኢህአዲግ ነው ‘፣ ‘ HR128 የተባለውና በአሜሪካ ኮንግረንስ የተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ እንዳይሆን ያደርጋል’ በሚል ሰልፉ እንዲበተን አድርጉ የሚል ተልኮ እንደተቀበለም ክሱ አመልክቷል።

አንደኛ ተከሳሽ ጌቱ ግርማ ከሁለተኛ ተከሳሽ ብርሃኑ ጁፋር ጋር በሰኔ 15/2010 ሱሉልታ ላይ ስለ ተልኮው በመነጋገር ቦንብ እንዲያዘጋጅ ፣ ቦንቡን የሚወረውር እንዲያፈላልግ ተነጋግረው ለሶስተኛ ተከሳሽ ጥላሁን ጌታቸው ደውሎ ቦንብ የሚወረውር ሰው እንዲፈልግ ተልኮ መስጠቱንም ክሱ ያሳያል።

ሁለተኛ ተከሳሽ ያዘጋጀውን ሁለት ኤፍ 1 ቦንብ እንዲሁም አንድ የጭስ ቦንብ በአንደኛ ተከሳሽ ቤት በማስቀመጥ ከሱሉልታ በመነሳት ሰልፉን በመቀላቀል በሶስተኛው ተከሳሽ አማካኝነት ቦንቡን በማፈንዳት ሙሳ ጋዲሳና ዬሴፍ አያሌው የተባሉ ግለሰቦች ላይ የሞት 165 የሚሆኑ ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል ጉዳት ማድረሳቸውም በክሱ ተጠቁሟል።

በዘህም መሰረት ዓቃቢ ህግ ክስ መስርቶባቸዋል።

በመንግስትና በግል ከሚቆምላቸው ጠበቃ ጋር ተመካክረው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል᎓᎓ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል᎓᎓

ከሳሽ አቃቤ ህግ በበኩሉ ክሱ በፀረ ሽብር አዋጁ ዋስትና እንደሚያስከለክል ጠቅሶ በቦንብ ጥቃቱ የሰው ህይወት ማለፉንም ገልጿል᎓᎓

በነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የዋስትና መብታቸው ተከልክሎ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ አመልክቷል᎓᎓

የዋስትና ጥያቄአቸው ውድቅ ሆኖ ከጠበቃ ጋር ተማክረው አንዲቀርቡ ለጥቅምት 2 ተቀጥሯል᎓᎓

ምንጭ:- ኢቲቪ