ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ የአፍሪካ መድረክ ቆይታቸውን በሳምንቱ መጨረሻ ይወስናሉ

የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ እና የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊዎቹ ሁለቱ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ከ10 ቀናት በፊት የመጀመሪያ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በሜዳቸው ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የሲሼልሱ ሴንት ሚሼል ዩናይትድን 3ለ0 ከረቱበት እና መከላከያዎች በምስር ኤል-ማቃሳ 3ለ1 ከተሸነፉበት ጨዋታዎች በኋላ የፊታችን ቅዳሜ ከሜዳቸው ውጪ የመልስ ጨዋታዎቻቸውን ያደርጋሉ፡፡ ቀጣዩ ፅሁፍ ከመልስ ጨዋታዎቹ በፊት በጨዋታዎቹ ዙሪያ ሊነሱ ስለሚገባቸው ነገሮች ያነሳል፡፡

የመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች

ቅ

ከ10 ቀናት በፊት የተደረጉትን የክለቦቹን የመጀመሪያ ጨዋታዎች በትንሹ ለማስታወስ እንሞክር፡፡ በበርካታ ደጋፊዎቻቸው ፊት የሲሼልስ ሻምፒዮኖቹን ያስተናገዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጀመሪያው ግማሽ በተጋጣሚያቸው ላይ ጫና ማሳደር የቻሉ ሲሆን በአዳነ ግርማ እና በኃይሉ አሰፋ ጎሎች 2ለ0 እየመሩ ለእረፍት መውጣትም ችለዋል፡፡ ፈረሰኞቹ በሁለተኛው አጋማሽ ቀዝቅዘው የታዩ ሲሆን የጎል አጋጣሚዎችን ለመፍጠርም ተቸግረው ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ተቀይሮ የገባው ኦክዋራ ጎድዊን የቡድኑን ሶስተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡ ግዙፉ ናይጄሪያዊ አጥቂ በአዲሱ ክለቡ ጎል መዝገቡን ለመክፈት የወሰደበት አምስት ደቂቃዎችን ብቻ ነበር፡፡ ከእሱ ጎል በኋላ በ3ለ0 ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው በኋላ ቃላቸውን የሰጡት የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ማርት ኖይ ‹‹በስምንት እና ዘጠኝ ተጨዋቾች ለመከላከል የመጣውን ቡድን›› ሰብሮ መግባት አስቸጋሪ እንደነበር እና በዚህም ምክንያት ጎል ሳያስተናግዱ ሶስት ጎሎችን በማስቆጠራቸው ደስተኛ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡ የሴንት ሚሼል ዩናይትዱ አሰልጣኝ አንድሪው ዦን-ሉዊ በበኩላቸው በአልቲቲዩዱ ምክንያት ጨዋታው እንደከበዳቸው እና በውጤቱ ብዙም እንዳልተከፉ ተናግረዋል፤ በጉዳት ላይ የሚገኙ ተጨዋቾቻቸው ስለሚመለሱላቸው በሜዳቸው የተሻለ ውጡት እንደሚጠብቁም ገልፀዋል፡፡

ድ

ወደ መከላከያ ስናመራ፣ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊዎቹ ሊያስታውሱት የማይፈልጉትን ቀን አሳልፈዋል፡፡ ተጋጣሚያቸው ምስር ኤል-ማቃሳ በሁሴን ራጋብ እና አምር ባራካት ጎሎች ገና በ20 ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ጎሎች ያስቆጠረባቸው መከላከያዎች ወደ ጨዋታው ለመግባት ተቸግረው የዋሉ ሲሆን በሁሉ ረገድ በተጋጣሚያቸው ተበልጠውም ታይተዋል፡፡ በጨዋታው መገባደጃ ላይ ቢያንስ ልዩነቱን ለማጥበብ ሲታገሉ በፈጠሩት ክፍተት ተቀይሮ የገባው ኤል-ሰኢድ ሀምዲ ሶስተኛ ጎል አስቆጥሮባቸዋል፡፡ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ግን መሀመድ ናስር የማስተዛዘኛ ጎል አስቆጥሮላቸው 3ለ1 በሆነ ውጤት በሜዳቸው ተሸንፈዋል፡፡

የመልስ ጨዋታ ዝግጅት

ሁለቱም ክለቦቻችን ከጨዋታዎቻቸው መልስ በሀገራቸው ልምምዶቻቸውን ሲያደርጉ የሰነበቱ ሲሆን ወደ ፕሪምየር ሊግ ውድድርም ተመልሰው ነበር፡፡ የሊጉ መሪ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያለ ጎል አቻ ተለያይተው በጎል ልዩነት መሪነቱን ይዘው መቀጠል የቻሉ ሲሆን በሳምንቱ አጋማሽ እነሱ አርፈው አዳማ ከተማ በማሸነፉ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀራቸው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ መከላከያዎች በበኩላቸው የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ደካማ አቋማቸውን በሊጉም በመድገም በሜዳቸው በወላይታ ድቻ ሽንፈት ደርሶባቸው በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ መቀመጣቸውን ቀጥለውበታል፡፡

ሌሎች ነጥቦች፡-

  • ሴንት ሚሼል ዩናይትድን ከረቱበት ጨዋታ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሰልሀዲን ሰኢድን ማስፈረማቸው ተረጋግጧል፡፡ አጥቂያቸው ብሪያን ኦሞኒን በጉዳት ለረዥም ጊዜ ላጡት ፈረሰኞቹ በሰሜን አፍሪካ ትልልቅ ክለቦች ሲጫወት የቀየው የቀድሞ አጥቂያቸው ሰልሀዲንን መመለስ መቻል ትልቅ ዜና ነው፡፡
  • በርካታ (ከ100 የሚበልጡ) የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ቡድናቸውን ለመደገፍ ወደ ሲሼልስ ማቅናታቸው ተሰምቷል፡፡ ደጋፊዎቹ የተለያዩ የጉዞ እና የቆይታ ፓኬጆችን ተጠቅመው በራሳቸው ወጪ እንደተጓዙ ማወቅ ተችሏል፡፡
  • የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሴንት ሚሼል ዩናይትድን ጨዋታ የሚመሩት ሌሶቷዊያን አርቢትሮች ሲሆኑ የመከላከያ እና ምስር ኤል-ማቃሳ ጨዋታ በሱዳናዊያን አርቢትሮች ይመራል፡፡
  • ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ማሸነፍ፣ አቻ መለያየት እንዲሁም ጎል አስቆጥረው በሶስት ጎሎች ልዩነት መሸነፍ ይበቃቸዋል፤ 3ለ0 ከተሸነፉ ወደ መለያ ምቶች ይጓዛሉ፡፡ መከላከያዎች ከቅዱስጊዮርጊስ በተለየ የጠበበ የማለፍ እድል ያላቸው ሲሆን በግብፅ ከሁለት ጎል ልዩነት በበለጠ ማሸነፍ አልያም 3ለ1 አሸንፈው ወደ መለያ ምቶች መጓዝ ግድ ይላቸዋል፡፡
  • ክለቦቻችን ይህን ዙር ማለፍ ከቻሉ በቀጣዩ ዙር ከዲ.ሪ.ኮንጎ ክለቦች ጋር ይፋጠጣሉ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቲ.ፒ ማዜምቤ እንዲሁም መከላከያ ከሲ.ኤስ ዶን ቦስኮ፡፡
  • ሁለቱም ጨዋታዎቹ የሚደረጉት ቅዳሜ የካቲት 19 ሲሆን፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ በ10፡30 በቪክቶሪያ ከተማ ስታድ ሊኔቴ እንዲሁም የመከላከያ በ12 ሰዓት በፋዩም ስታዲየም ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.