ማሊዎች ግባቸው ማሸነፍ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል

የቦርዶው አጥቂ ሼክ ዲያባቴ በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ውጪ መሆኑ ለዋልያዎቹ መልካም የሚባል ዜና ነው

የኢትዮጲያ ብሔራዊ ቡድን ነገ ከቀትር በኋላ በአዲስ አበባ ስታዲየም የማሊ አቻውን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ይገጥማል፡፡ ቀጣዩ ፅሁፍ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአፍሪካ ኃያላን የእግር ኳስ ቡድኖች አንዱ እየሆነ ስለመጣው የምዕራብ አፍሪካው ተጋጣሚያችን ያስቃኛችኋል፡፡

‹‹በሚገባ ተዘጋጅተናል፤ ዓላማችን ማሸነፍ ብቻ ነው›› የቡድኑ አባላት

ለቅዳሜው ጨዋታ ዓርብ ማለዳ አዲስ አበባ የደረሰው የማሊ ብሔራዊ ቡድን በካፒታል ሆቴል አርፎ ከቀኑ አስር ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ልምምድ የሰራ ሲሆን አሁን የጨዋታውን መጀመሪያ ሰዓት እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ በፖላንዳዊው አሰልጣኝ ሄንሪ ካስፔርዣክ የሚሰለጥኑት ‹ንስሮቹ› ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በፈረንሳይ ፓሪስ በትንሽዋ መዶ (Meudon) ከተማ ሲዘጋጁ የቆዩ ሲሆን አሰልጣኙ በዝግጅታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ሲገልፁ ‹‹በጥሩ ስፍራ እና በጥሩ ሁኔታዎች ውስጥ መልካም ዝግጅት አድርገናል፡፡ በውቧ ከተማም በሰላማዊ ድባብ የታጀበ ምቹ የህብረት ጊዜን አሳልፈናል›› ብለዋል፡፡ ተጨዋቾቹ በዝግጅቱ ወቅት ጥሩ ስሜት የታየባቸው ሲሆን ከእነዚህም አንዱ የቡድኑ አዲስ ተስፈኛ አብዱላዬ ዲያቢ በቡድኑ ውስጥ መገኘቱ የሰጠውን ደስታ ተናግሯል፡፡ በቤልጅየሙ ጁፒለር ሊግ ለሙስክሮን የሚጫወተው እና በሊጉ በ8 ጨዋታዎች 7 ጎሎች አስቆጥሮ ጎል አግቢነቱን እየመራ የሚገኘው የ23 ዓመቱ ወጣት ‹‹በጣም ጥሩ ድባብ አለ፤ ጥሩ አቀባበል አግኝቻለሁ፤ ከሁሉም ጋር ተግባብተናል፤ እንደዚህ አይነት የአብሮነት ጊዜ በትልልቅ ውድድሮች ላይ ስኬታማ ለመሆን ወሳኝ ይመስለኛል፤ ለማሊ ለመጫወት በመምረጤ አልፀፀትም፤ ከታላላቆቹ ተጨዋቾች ጎን ለመማር ደስተኛ ነን›› ሲል ስሜቱን ገልጿል፡፡ ዘግየት ብሎ ቡድኑን የተቀላቀለው የቡድኑ አምበል እና ኮከብ ተጫዋች ሴይዱ ኬይታም ኢትዮጲያን ማሸነፍ ብቸኛ አላማቸው መሆኑን ሲናገር ‹‹ዓላማችን ከኢትዮጲያ ጋር የምናደርጋቸውን ሁለት ቀጣይ ጨዋታዎች ማሸነፍ ነው›› ያለ ሲሆን ሌላኛው የቡድኑ አማካይ ባካዬ ትራኦሬም ‹‹ግባችን ግልፅ ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ የምንጓዘው ድል ለማድረግ ነው›› በማለት ተናግሯል፡፡ የማሊ ቡድን ኬይታን ጨምሮ አብዛኞቹ ከዋክብቱን ይዞ ቢመጣም የቦርዶው አጥቂ ሼክ ዲያባቴ በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ውጪ መሆኑ ለዋልያዎቹ መልካም የሚባል ዜና ነው፡፡ በፈረንሳዩ ሊግ 1 ጥሩ ጅማሮ ያደረገው ግዙፉ እና ጉልበተኛው አጥቂ ለካስፔርዣክ ቡድንም ወሳኝ ሰው ሲሆን የእርሱ አለመኖር ለተከላካዮቻችን እፎይታን ሊሰጥ ይችላል፡፡

Team Mali Training at Addis Ababa Stadium


የማሊ ብሔራዊ ቡድን ወደ አዲስ አበባ ይዟቸው የመጣው ተጨዋቾች የሚከተሉት ናቸው፡

ግብ ጠባቂዎች፡ ማማዱ ሳማሳ (ገንጎ/ ፈረንሳይ)፣ ኦማር ሲሶኮ (አጃሲዮ/ ፈረንሳይ)፣ ዤርሜይ ቤርቴ (ኦንዜ ክሬቶ/ ማሊ)

ተከላካዮች፡ አላሳኔ ታምቤ (ኮርትሬይ/ ቤልጅየም)፣ ኦስማን ኩሊባሊ (ፕላታኒያስ/ ግሪክ)፣ ፎውሴይኒ ዲያዋራ (ቱር/ ፈረንሳይ)፣ አዳማ ታምቡራ (ራንደርስ/ ዴንማርክ)፣ ኢድሪሳ ኩሊባሊ (ዲፋ ኤል ጀዲዳ/ ሞሮኮ)፣ ሳሊፍ ኩሊባሊ (ቲፒ ማዜምቤ/ ..ኮንጎ)፣ ሞሀመድ ኮናቴ (ቤርካኔ/ ሞሮኮ)

አማካዮች፡ባካዬ ትራኦሬ (ቡርሳስፖር/ ቱርክ)፣ ሴይዱ ኬይታ (ሮማ/ ጣሊያን)፣ ቶንጎ አህመድ ዱምቢያ (ቱሉዝ/ ፈረንሳይ)፣ ሲጋማሪ ዲያራ (ቫሎንሲዮን/ ፈረንሳይ)፣ ማሞቱ ንዲያዬ (ዙለቴ ቫሬጋም/ ቤልጂየም)፣ ያኩባ ሲላ (ኤርሲዬስፖር/ ቱርክ)፣ ሳምቡ ያታባሬ (ገንጎ/ ፈረንሳይ)፣ ባካሪ ሳኮ (ዎልቨርሀምፕተን/ እንግሊዝ)

አጥቂዎች፡ ሙስታፋ ያታባሬ (ትራብዞንስፖር/ ቱርክ)፣ ሞሀመድ ትራኦሬ (ኤል ሜሪክ/ ሱዳን)፣ አብዱላዬ ዲያቢ (ሙስክሮን/ ቤልጂየም)፣ ሼክ ዲያራ ፋንታሜዲ (ኦክሴር/ ፈረንሳይ)

ማሊን በአጭሩ

ንስሮቹ (The Eagles) በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የማሊ ብሔራዊ ቡድን ዓለማ አቀፋዊም ሆነ አህጉራዊ የእግር ኳስ ታሪኩ ያን ያህል የሚነገርለት አይደለም፡፡ ሀገሪቱ በዓለም ዋንጫ መድረክ ተሳትፋ የማታውቅ ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫም ዋንጫውን የማሸነፍ ወይም ለፍፃሜ የመድረስ ስኬት የላትም፡፡ ትልቁ አህጉራዊ ውጤቷም በመጨረሻዎቹ ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች (2012 እና 2013) ያገኘችው ሶስተኛ ደረጃ ነው፡፡ነገር ግን ቡድኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ለመሆኑ ይህ ተከታታይ ስኬቷ እና 59ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝበት ወቅታዊ የፊፋ ደረጃዋ ይመሰክራሉ፡፡


አሰልጣኝ ሄንሪ ካስፔርዣክ

ዜግነት ፖላንዳዊ

በተጨዋችነት ዘመናቸው ለሀገራቸው በሁለት ዓለም ዋንጫዎች (1974 እና 1978) የተጫወቱት እና በ1976 በሞንትሪያል ኦሊምፒክ ከሀገራቸው ጋር የብር ሜዳል ያገኙት ፖላንዳዊው ሰው በአሰልጣኝነት ህይወታቸውም በሶስት አህጉራት ከአምስት ካላነሱ ሀገራት እና ከ10 ከበለጡ ክለቦች ጋር የመስራት የገዘፈ ልምድ አላቸው፡፡ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ታላላቆቹን የአፍሪካ ቡድኖች ቱኒዚያ፣ ኮትዲቯር፣ ሞሮኮ፣ ሴኔጋል እና ማሊን ሲያሰለጥኑ በአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች በ1996 ከቱኒዚያ ጋር ለፍፃሜ መድረስ፣ በ1994 ኮትዲቯርን ለ3ኛ ደረጃ እና በ2002 ማሊን ለ4ኛነት ማብቃት ችለዋል፡፡ በክለብ ደረጃ ከበርካታ የፈረንሳይ ክለቦች ጋር ሲሰሩ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና በቻይናም ሰርተዋል፡፡ የሀገራቸውን ክለብ ቪስላ ክራኮውንም ለሶስት የሊግ ድሎች አብቅተዋል፡፡ የአሰልጣኙን ፍልስፍና ስንመለከት በአካል ብቃት የዳበረ፣ በታክቲክ የተዋጣለት እና እንደየጨዋታው የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ሊጫወት የሚችል ቡድን በመስራት የተካኑ ናቸው፡፡ ያሁኑ ቡድናቸው ተጨዋቾች ተፈጥሯዊ ተክለሰውነት፣ በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የመጫወት ልምድ እና የረዥም ጊዜ የአብሮነት ቆይታም ካስፔርዣክን በቡድኑ ግንባታ እንዳይቸገሩ አድርጓቸዋል፡፡

Mali Coach & his Star player Seydou Kieta


ኮከብ ተጨዋች፡ሴይዱ ኬይታ

የንስሮቹ ቁልፍ ተጨዋች ከደርዘን ዓመታት በላይ ሀገሩን ያገለገለው ሴይዱ ኬይታ እንደሆነ አያከራክርም፡፡ የቀድሞው ዝነኛ ተጨዋች ሳሊፍ ኬይታ (በአንድ ወቅት የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች ነበር) የስጋ ዘመድ የሆነው ሴይዱ በአጎቱ ስም በተሰየመው የወጣት ማዕከል ካደገ በኋላ ማርሴይ፣ ሲቪያ፣ ባርሴሎና እና ቫሌንሲያን ጨምሮ ለበርካታ የአውሮፓ ክለቦች የተጫወተ ሲሆን በተለይም ከፔፕ ጓርዲዮላ ባርሴሎና ጋር 14 ታላላቅ ድሎችን አጣጥሟል፡፡ አሁን ለሌላው ታላቅ ክለብ የጣሊያኑ ሮማ በመጫወት ላይ የሚገኘው የማሊው አምበል በ6 የአፍሪካ ዋንጫዎች የሀገሩን ማሊያ የለበሰ ሲሆን በ1999 በፊፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ላይ ሀገሩ የነሀስ ሜዳሊያ እንድታገኝ ረድቶ በግሉም የውድድሩ ኮከብ ሆኖ ተሸልሟል፡፡ ኬይታ በመሀል/ተከላካይ አማካይነት የሚታወቅ ቢሆንም በአሰልጣኞች እጅግ ተወዳጅ የሚያደርገው ሁለገብነት፣ የታክቲክ መረዳት እና መሪነትን አዋህዶ የያዘ ተጨዋች ነው፡፡


የማሊ የማጣሪያ ጉዞ

2015ቱ የሞሮኮ አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የእስካሁን ጉዞ ንስሮቹ አንዱን ጨዋታቸውን አሸንፈው በአንደኛው ተሸንፈዋል፡፡ በባማኮው ስታድ 26 ማርስ ስታዲየም በተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታቸው ማሊዎቹ ግብ ጠባቂያቸው ማማዱ ሳማሳን በቀይ ካርድ ቢያጡም በባካሪ ሳኮ እና ሼክ ዲያባቴ ጎሎች ማላዊን 20 መርታት ችለው ነበር፡፡ ከሶስት ቀናት በኋላ ግን በአልጄርሱ ኤል ቦሌይዳ ስታዲየም የአማካያቸው ማሞቶ ንዳዬን በቀይ መውጣት መቋቋም ሳይችሉ ቀርተው በ83ኛው ደቂቃ የካርል ሜጃኒ ጎል ሽንፈትን አስተናግደዋል፡፡ አሁን በሶስት ቀናት ውስጥ ሁለት ጊዜ ዋልያዎቹን ለመግጠም ተዘጋጅተዋል፡፡

1 thought on “ማሊዎች ግባቸው ማሸነፍ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published.