ሙክታር እድሪስ በጣልያን ትሬንቶ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር አሸነፈ

Photo © Daniele Mosna

በጣልያን ትሬንቶ ጊሮ አል ሳስ በሚል ስያሜ በሚታወቀውና ዘንድሮ ለ71ኛ ግዜ በተከናወነው የወንዶች ብቻ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ኢትዮጵያዊው የ5000ሜ. የዓለም ሻምፒዮን ሙክታር እድሪስ የሀገሩን ልጆች ጥላሁን ሀይሌ እና ያሲን ሀጂ በማስከተል አሸናፊ ሆኗል፡፡     

ሙክታር እድሪስ ውድድሩን በአሸናፊነት ሲያጠናቅቅ (Photo © Daniele Mosna)

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሶስት ተከታትለው በገቡበት እና በትላንትናው ዕለት በተካሄደው ጊሮ አል ሳስ የጎዳና ላይ 10 ኪ.ሜ. ፉክክር ሙክታር ውድድሩን በቀዳሚነት ለማጠናቀቅ የበቃበት ሰዓት 28 ደቂቃ ከ54 ሰከንድ ሲሆን እስከመጨረሻው የቅርብ ተፎካካሪው የነበረው ጥላሁን ሀይሌ በ28 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ ሁለተኛ ያሲን ሀጂ በ29 ደቂቃ ከ13 ሰከንድ ሶስተኛ በመሆን ጨርሰዋል፡፡

የ71ኛው ጊሮ አል ሳስ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር አሸናፊዎች (Photo © Daniele Mosna)

የመጀመሪያዎቹ አራት ኪሎ ሜትሮች በመጠባበቅ በተሮጡበት ፉክክር ላይ ሙክታር አስቀድሞ የመሪነቱን ስፍራ ይዞ የነበረ ሲሆን ጥላሁን፣ ያሲን፣ የ2012 ኦሊምፒክ የ5000ሜ. የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊው ኬንያዊ ሉንጎሲዋ እና ጣልያናዊው የአውሮፓ ከ23 ዓመት በታች የ5000 ሜትር ሻምፒዮን የማነብርሀን በቅርብ ርቀት እየተከተሉት ነበር፡፡ የውድድሩ አጋማሽ ላይ ሲደርሱ በቀዳሚነት ለጨረሰ የሚሰጠውን ጉርሻ ለማግኘት ሲል ፍጥነቱን ጨምሮ የሮጠው ሙክታር ከውድድሩ አጋማሽ በኋላ የመሪነቱን ስፍራ ለጥላሁን አስረክቦ የነበረ ሲሆን ወደስድስተኛው ኪሎ ሜትር ሲቃረቡም ጥላሁን ውድድሩን በሰፊ ልዩነት ለመምራትም ችሎ ነበር፡፡ ሙክታር በእርሱ እና በጥላሁን መሀል የነበረውን ልዩነት ቀስ በቀስ በማጥበብ ውድድሩ ሶስት ዙር ሲቀረው የደረሰበት ሲሆን ለውድድሩ አሸናፊነት የተደረገው የመጨረሻ ትንቅንቅ የተካሄደውም በሁለቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ነበር፡፡ በመጨረሻው ዙር ጥላሁን አስቀድሞ በመፍጠን አጨራረሱን ለማሳመር ቢሞክርም በመጨረሻዎቹ ጥቂት ሜትሮች ውስጥ በሙክታር ተቀድሟል፡፡

በዚህ ውድድር ላይ ዘንድሮ በተከታታይ ሶስተኛ ድሉን የተቀዳጀው ሙክታር ከውድድሩ በኋላ ለውድድሩ አዘጋጆች በሰጠው አስተያየት ‹‹በከፍተኛ አልቲቲዩድ ላይ መለማመዴ ለውጤታማነቴ የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ የዓለም ሻምፒዮና ላይ አሸናፊ መሆን ተጠባቂነትን ከፍ የሚያደርግ በመሆኑ ልምምዴን ይበልጥ አጠናክሬ መስራቱን መቀጠል ይኖርብኛል፡፡ በትሬንቶ በተከታታይ ለሶስተኛ ዓመት ማሸነፍ መቻሌ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ወደዚህ በመጣሁ ቁጥር ሁሉም ሰው አሸናፊ እንደምሆን ይጠብቃል፡፡ በውድድሩ መሀል ድካም በተሰማኝ ግዜ በማያቋርጥ የሞራል ድጋፋቸው ለአሸናፊነት እንድበቃ እገዛ ያደረጉልኝን የትሬንቶ ደጋፊዎች ላመሰግናቸው እወዳለሁ›› ብሏል፡፡

በ71ኛው ጊሮ አል ሳስ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር የመጀመሪያዎቹን 10 ደረጃዎች ይዘው ያጠናቀቁት አትሌቶች   
1 ሙክታር እድሪስ (ኢትዮጵያ) 28፡54
2 ጥላሁን ሀይሌ (ኢትዮጵያ) 28፡55
3 ያሲን ሀጂ (ኢትዮጵያ) 29፡13
4 የማነብርሀን ክሪፓ (ጣልያን) 29፡20
5 ናታን አዬኮ (ኡጋንዳ) 29:41
6 ቶማስ ሉንጎሲዋ (ኬንያ) 29:42
7 ሎሬንዞ ዲኒ (ጣልያን) 29:44
8 ሀቪዬር ሸቭሪዬ (ጣልያን) 30:06
9 ማሩዋን ራዚኔ (ጣልያን) 30:17
10 ኦሳማ ዞግላሚ (ጣልያን) 30:21

1 thought on “ሙክታር እድሪስ በጣልያን ትሬንቶ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር አሸነፈ

Leave a Reply

Your email address will not be published.