መከላከያ በድል ኢትዮጵያ ቡና በሽንፈት ወደ ረዥሙ የሊጉ እረፍት አምርተዋል

Defence-Force

አዲሱ ዓመት 2008 ሲጀምር የመከላከያ ዓመት መስሎ ነበር፡፡ ውድድሩ የ2007 ቢሆንም ለዚህ ዓመት በተሻገረው የጥሎ ማለፍ ውድድር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከነማን በመርታት ባለድል ሆኑ፤ እንደ ቅድመ-ውድድር ዘመን የዝግጅት ውድድር በሚታየው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (አምበር ዋንጫ) ውድድር ላይም እንደ እነሱ አጀማመሩ ያማረ ቡድን አልነበረም፡፡ የገብረመድህን ኃይሌ ቡድን እጅግ በርካታ ቋሚ ተሰላፊ ተጨዋቾቹን ሳይዝ አዳማ ከነማን እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በማሸነፍ ከሁሉም ቀድሞ ከምድቡም ማለፉን አረጋግጦ ነበር፡፡ ቡድኑ ቁልፍ ተጨዋቾችን ሳይዝ እነዚህን ትልልቅ ቡድኖች ማሸነፉ፣ በየአንዳንዱ ስፍራ በቂ የተጨዋቾች ስብስብ መያዙ፣ የተረጋጋ ቡድን መሆኑ እና ከፍተኛ ልምድ ባለው አሰልጣኝ መመራቱ ካለፉት ዓመታት በበለጠ ለሊጉ ውድድር ተፎካካሪነትም ከፍ ያለ ተስፋ እንዲጣልበት አድርጎ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ በሰፋ ውጤት ተሸነፈ፤ በግማሽ ፍፃሜው በመለያ ፍፁም ቅጣት ምቶችም ቢሆን በዳሸን ቢራ ተረታ፤ ከዚያም ፍፁም ሳይጠበቅ በፕሪምየር ሊጉ መክፈቻ በኤሌክትሪክ ሽንፈት ደረሰበት፡፡ ከእነዚህ ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ የቀድሞዎቹ ጥያቄዎች መነሳት ጀመሩ – መከላከያ ዘንድሮም በተስፋ ብቻ ሊቀር ነውን? ቡድኑ የተሰጥኦ እና ልምድ ችግር የለበትም፤ ተስፋውን የማያሟላው መቀረፍ ያልቻለ የስነ-ልቦና ችግር ኖሮበት ይሆን? መከላከያዎች ኢትዮጵያ ቡናን ለመግጠም ሲዘጋጁ እነዚህን ጥያቄዎች ይዘው ወደ 40 ቀናቱ የሊጉ እረፍት በመሄድ ስጋት ውስጥ ሆነው ነበር፡፡ ከዚህ የሚያተርፋቸው ብቸኛ ነገር ኢትዮጵያ ቡናን ማሸነፍ ብቻ ነበር፡፡ እናም ጨዋታው ገና የሁለተኛ ሳምንት ቢሆንም ለጥሎ ማለፍ ሻምፒዮኖቹ የሞት-ሽረት ፍልሚያ ነበር፡፡

የገብረመድህን ቡድን ጨዋታውን ሲጀምር በግብ ጠባቂ ስፍራ ይድነቃቸው ኪዳኔን ሲያሰልፍ፣ አዲሱ ተስፋዬ እና ሙሉቀን ደሳለኝን በመሀል ተከላካይ፣ እንዲሁም ሽመልስ ተገኝ እና ነጂብ ሳኒን በቀኝ እና ግራ ተከላካይ ስፍራዎች አሰልፏል፡፡ በኃይሉ ግርማ እና ሚካኤል ደስታ በመሀል አማካይነት ሲሰለፉ፣ ፍሬው ሰሎሞን፣ ሳሙኤል ታዬ እና ምንይሉ ወንድሙ ከብቸኛ አጥቂው መሀመድ ናስር ጀርባ ነበሩ፡፡ ተጋጣሚያቸው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ኮአሲ ሀሪስተንን በግብ ጠባቂ ስፍራ፣ ወንድይፍራው ጌታሁን እና ተስፋዬ ሀይሶን በመሀል ተከላካይ፣ አብዱልከሪም መሀመድን በቀኝ ተከላካይ እና አህመድ ረሺድን በግራ ተከላካይ ስፍራ ሲያሰልፍ፣ ጋቶች ፓኖም በአምበልነትም ሆነ በተከላካይ አማካይነት ጉዳት ላይ ያለው መስኡድ መሀመድን ተክቶ ገብቷል፡፡ ከእሱ ፊት ኤልያስ ማሞ፣ ኢያሱ ታምሩ፣ ጥላሁን ወልዴ እና ዮሴፍ ደሙዬ ሲሰልፉ ዊልያም ያቡን የብቸኛ አጥቂነት ሚና ተሰጥቶታል፡፡

ጨዋታው ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ ሞቅ ያለ፣ የተመጣጠነ ፉክክር የተሞላበት እና ትኩረት የሚስብ ነበር፡፡ በአምስተኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ማሞ ለዊልያም ያቡን በተከላካዮች መሀል ያቀበለውን ኳስ ዊልያም አምልጦ ገብቶ በሚገባ ከመቆጣጠሩ በፊት ከጎል ክልሉ በወጣው ይድነቃቸው ኪዳኔ ጥፋት ተሰርቶብኛል ብሎ የወደቀ ቢሆንም አርቢትሩ ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ ጨዋታው እንዲቀጥል ወስነዋል፡፡ በሰባተኛው ደቂቃ ለመሀመድ ናስር በመሬት የተላከን ኳስ ኮአሲ ሀሪስተን ከእግሩ ላይ ካወጣበት በኋላ ሳሙኤል ታዬ ወደጎል የሞከረው ኳስ በአግዳሚው ላይ ወጥቶበታል፡፡ በ11ኛው ደቂቃ ኢያሱ ታምሩ ያሻገረውን ኳስ ዊልያም በጭንቅላቱ ቢሞክረውም ይድነቃቸውን ለመፈተን በቂ አልነበረም፡፡ በ12ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰሎሞን ከቀኝ በኩል ለራሱ ክፍተት ፈጥሮ አዙሮ የመታው ኳስ ጥንካሬ ስላልነበረው በሀሪስተን ተይዞበታል፡፡ በ14ኛው ደቂቃ ነጂብ ሳኒ በግራ መስመር አብዱልከሪም መሀመድን አልፎ ሄዶ በመሬት ያሻገረው ኳስ መሀመድ እንዳገኘ ወደ ጎል ቢመታውም ኢላማውን ሳያገኝ ወጥቶበታል፡፡ በ16ኛው ደቂቃ ቡናዎች ወደፊት ሄደው ዮሴፍ ደሙዬ በቅንጦት እግሩን አጠላልፎ ለማቀበል የሞከረው ኳስ በመከላከያ ተከላካዮች ተጨናግፎበታል፡፡ ወዲያውኑም ኢያሱ ኳሱን አግኝቶ ለኤልያስ ያዘጋጀውን ኤልያስ ወደጎል መትቶ ለጥቂት ወጥቶበታል፡፡ በ22ኛው ደቂቃ ነጂብ አብዱልከሪምን አምልጦ ገብቶ ኳሱን ቢያሻግርም ለአጥቂዎቹ ከመድረሱ በፈት ወንድይፍራው እንደምንም አውጥቶታል፡፡ በ23ኛው ደቂቃ ሚካኤል ደስታ ከሩቅ የመታው ኳስ ኢላማውን አላገኘለትም፡፡ በ26ኛው ደቂቃ ምንይሉ ወንድሙ በቀኝ መስመር ገብቶ ያሻገረውን እና የቡናው ተከላካይ ተስፋዬ ሀይሶ አወጣለሁ ብሎ የሳተውን ኳስ ሀሪስተን ይዞታል፡፡ በ28ኛው ደቂቃ በዊልያም ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘን የቅጣት ምት ኤልያስ መትቶ ግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ሲመለስበት ተስፋዬ ደርሶ የተመለሰውን ኳስ ከሶስት ሜትር ርቀት በአግዳሚው ላይ በመላክ ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል፡፡ በ31ኛው ደቂቃ መከላከያዎች ያገኙትን የቅጣት ምት በፍጥነት ጀምረውት ነጂብ እንደለመደው አልፎ ገብቶ ተከላካዮቹ አውጥተውበታል፡፡ በ44ኛው ደቂቃ የመከላከያን የማእዘን ምት ምንይሉ በጭንቅላቱ ሞክሮ ቤኒናዊው ግብ ጠባቂ አውጥቶበታል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛው ጊዜ ተጠናቆ በባከኑ ደቂቃዎች አህመድ ረሺድ ከግራ መስመር ተነስቶ ወደ መሀል በመግባት ከርቀት የሞከረው ኳስ ኢላማውን ሳያገኝለት ቀርቷል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት ከመጀመሪያው ያነሱ ሙከራዎች የተደረጉበት እና የቡድኖቹም እንቅስቃሴ በመጠኑ ቅርፅ ያጣ የመሰለበት ነበር፡፡ በ62ኛው ደቂቃ የመከላከያን የቅጣት ምት ከ20 ሜትሮች ገደማ ምንይሉ በቀጥታ ወደ ጎል መትቶት ሀሪስተን አውጥቶበታል፡፡ በ66ኛው ደቂቃ ዮሴፍ ከፍፁም ቅጣት ክልል ውጪ ወደ ጎል የመታው ማራኪ ኳስ ለጥቂት ወጥቶበታል፡፡ ዮሴፍ ከዚህ ሙከራው በኋላ ብዙም ሳይቆይ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡ የቀድሞውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ተክቶ የገባው ሳዲቅ ሳቾ ሲሆን፣ አክሊሉ ዋለልኝም ኤልያስ ማሞን ተክቶ ወደሜዳ ገብቷል፡፡ መከላከያዎች በበኩላቸው ባዬ ገዛኸኝን በመሀመድ ፈንታ አስገብተዋል፡፡ በቡና በኩል ተቀይሮ የገባው አክሊሉ በ78ኛው ደቂቃ ከ30 ሜትሮች ገደማ የመታውን ጠንካራ ኳስ ይድነቃቸው በሚገባ ለመያዝ ተቸግሮ በመከራ ጎል ከመሆን አድኖታል፡፡ በ80ኛው ደቂቃ ጥላሁን ወልዴ ከቀኝ መስመር ወደ ግራ መስመር የላከው ረዥም ኳስ ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብሎ ኢያሱን ተክቶ የገባው ሳላምላክ ተገኝ ጋር ደርሶ ወጣቱ ወደ ጎል ሞክሮት ለጥቂት ወጥቶበታል፡፡ በ83ኛው ደቂቃ አሰልጣኝ ገብረመድህን፣ ሳሙኤል ሳሊሶ ምንይሉን ተክቶ እንዲገባ አድርገዋል፡፡ ፈጣኑ ሳሙኤል በጨዋታው ላይ ልዩነት ለመፍጠር እና መከላከያዎች አጥብቀው የሻቱትን ድል ለማስገኘትም ያስፈለገው አራት ደቂቃዎች ብቻ ነበር፡፡ 87ኛው ደቂቃ ሳሙኤል አስደናቂ ፍጥነቱን ተጠቅሞ በቀኝ በኩል ጥሶ ከገባ በኋላ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ሌላኛው ሳሙኤል – ሳሙኤል ታዬ በቀላሉ ጎል አድርጎታል፡፡ ከዚያ በኋላም ብዙም ስጋት ሳይፈጠርባቸው መከላከያዎች የጓጉለትን ሶስት ነጥብ አስከብረው ጨዋታውን አጠናቅቀዋል፡፡

አሰልጣኞቹ ምን አሉ?

ጨዋታውን በድል የተወጣው መከላከያ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ባገኙት ድል ደስ እንደተሰኙ ገልፀዋል፡፡ በብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት እና ጨዋታዎች ምክንያት ሊጉ ከ40 ቀናት በላይ ሊቋረጥ መሆኑ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝንም አሰልጣኙ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች ግን ረዥሙ መቋረጥ ቡድናቸውን በሚፈልጉት መንገድ ለማሻሻል እድል እንደሚሰጣቸው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ ቡድናቸው የአጥቂ ትልቅ ችግር እንዳለበት ያመኑት ሰርቢያዊው አሰልጣኝ የእሳቸው ቡድን መልካሞቹን የጎል እድሎች ፈጥሮ ማሸነፍ አለመቻሉ እንዳስከፋቸው ገልፀዋል፡፡

አንዳንድ ነጥቦች በመከላከያ እና ኢትዮጵያ ቡና ዙሪያ

ለሊጉ ዋንጫ ተፎካካሪ ሊሆኑ ከሚችሉ ቡድኖች መካከል የሚመደቡትን መከላከያ እና ኢትዮጵያ ቡና በተለያዩ ውድድሮች ላይ ብዙ ጨዋታዎቻቸውን መመልከት ችለናል፡፡ እነዚህን ነጥቦችም ታዝበናል፡፡

  • የመከላከያ የወጥ አቋም አለመያዝ ችግር ዘንድሮም እየታየ ይገኛል፡፡ ከላይ በዘገባው መግቢያ ላይ እንደሰፈረው ለጠንካራ ተፎካካሪነት የሚያስፈልጉ ቅንጣቶችን ሁሉ የያዘ የሚመስለው የገብረመድህን ኃይሌ ቡድን በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ ከሚጠበቀው በታች ሲፍረከረክ ይታያል፡፡ የዘንድሮው ቁጥሩን ብንመለከት እንኳን በፉክክር ጨዋታዎች አምስቱን አሸንፎ በአራቱ ተረትቷል፡፡ ይህ የዋንጫ ተፎካካሪ ቡድን ቁጥር ነውን?
  • የኢትዮጵያ ቡና የተጨዋቾች ስብስብ የጥራትም ሆነ የጥልቀት ችግር አለበት፡፡ አሰልጣኙ ድራጋን ፖፓዲችም በተደጋጋሚ እንዳመኑት በብዙ ቦታዎች ላይ አሁን ከሚያሰልፏቸው ተጨዋቾች የተሻሉ ተጨዋቾችን ይፈልጋሉ፡፡ የበለጠ የሚያሳስበው ግን ከተጠባባቂ ወንበር ላይ የሚነሱት ተጨዋቾች ጥራት ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ብዙዎቹ በኢትዮጵያ ቡና ደረጃ የሚገኙ አይደሉም፡፡ የቋሚ ተሰላፊ ተጨዋቾች ጉዳት ወይም ቅጣት ቡድኑን ችግር ውስጥ ሊያስገባው ይችላል፡፡ በእሁዱ ጨዋታ የመስኡድ አለመኖር በቡድኑ እንቅስቃሴ ላይ የፈጠረው መመሳቀል በምሳሌነት ሊነሳ ይችላል፡፡
  • የመከላከያ የፈጠራ አማራጮች ብዛት ሌሎች ቡድኖችን የሚያማልሉ ናቸው፡፡ ሚካኤል ደስታ እና ፍሬው ሰሎሞን ከመሀል፣ ሳሙኤል ታዬ፣ ማራኪ ወርቁ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ከመስመር፣ ምንይሉ ወንድሙ እና ባዬ ገዛኸን (ከመስመር እና ከፊት)፣ እንዲሁም መሀመድ ናስር፣ ሙሉዓለም ጥላሁን እና ካርሎስ ዳምጠው ከፊት በተለያዩ መንገዶች የጎል እድሎችን መፍጠር ይችላሉ፡፡ የመስመር ተከላካዮቹ ነጂብ ሳኒ እና ሽመልስ ተገኝም ወደ ፊት ለመሄድ የማይፈሩ የመጨረሻ ኳሶቻቸውም የተስተካከሉ ሌሎቹ ፈጣሪዎች ናቸው፡፡
  • የኢትዮጵያ ቡና የጎል አግቢ አጥቂ ችግር እንዳለበት ግልፅ ቢሆንም የተከላካይ ክፍሉም ብዙ ጥያቄዎች ይነሱበታል፡፡ አንዳንዴ መስመር ያለፈ ቀዥቃዥነት እና ቅብጠት የሚታይበት ግብ ጠባቂው ኮአሲ ሀሪስተን በአምበር ዋንጫ ፍፃሜ በዳሸን ቢራ ለተቆጠረባቸው ጎል ምክንያት እንደነበረው የግዜ አጠባበቅ ስህተት በተደጋጋሚ ሲሰራ ታይቷል፡፡ ተከላካዮቹን የሚያናግርበት መንገድ ለቁጣ የቀረበ መሆኑም በግንኙነታቸው ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ የመሀል ተከላካዮቹ ወንድይፍራው ጌታሁን እና ተስፋዬ ሀይሶ ከስህተት የሚፀዱ አይመስሉም፡፡ በተለይ ወንድይፍራው ከእሁዱ ጨዋታ ውጪ በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ዋጋ ሊያስከፍሉ የሚችሉ ስህተቶችን በግዴለሽነት እና በውሳኔ ስህተቶች ሲሰራ ተመልክተነዋል፡፡ የቀኝ ተከላካዩ አብዱልከሪም መሀመድ በሁለቱ የሊግ ጨዋታዎች ምናልባትም በዋና ቡድን የአጭር ጊዜ ቆይታው መጥፎዎቹን ቀናት አሳልፏል፡፡
  • በመከላከያው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት ባይጫወትም መስኡድ መሀመድ እንደገና የተወለደ መስሏል፡፡ በአዲስ የተከላካይ አማካይነት ሚና እየተጫወተ የነበረው የቡናው አምበል እድሜውን ሁሉ እዚያ ቦታ የተጫወተ እስኪመስል ድረስ በአዲሱ ሚናው እጅግ ድንቅ ነበር፡፡ ቀድሞ ከምናውቀው ውጪ ታጋይነት እና ታታሪነትን የጨመረው መስኡድ እነዚህን ብቃቶች ከሚታወቅበት የቴክኒክ ተሰጥኦው፣ አደራጅነቱ፣ ብስለቱ እና ጨዋታን የማንበብ ብቃቱ ጋር አዳብሎ የቡድኑ ወሳኝ ተጨዋች ሆኖ ነበር፡፡ ውድድሩ መልሶ ሲጀመር አሰልጣኙ ከእሱ እና ከጋቶች ፓኖም ይህን ቦታ ለማን እንደሚሰጡ እና እንዴት እንደሚያዋህዷቸው መመልከትም ከአሁኑ ያጓጓል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.