መንግሥት የሽብርተኝነት ጥቃት አሳሳቢ አይደለም አለ

19 OCTOBER 2014 ተጻፈ በ ነአምን አሸናፊ

-ለኢቦላ ወረርሽኝ ተገቢው ዝግጅት መደረጉን አስታወቀ

በቅርቡ የአሜሪካ መንግሥት በአዲስ አበባ ለሚኖሩ ዜጐቹ የሽብር ጥቃት ሊደርስ ይችላል በማለት ያስተላለፈው መልዕክት ይህን ያህል አሳሳቢ ባለመሆኑ፣ በከተማዋ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ተረጋግተው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን እንዲያከናውኑ መንግሥት አስገነዘበ፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ይህንን ያሉት፣ የሽብር ጥቃቱን በተመለከተና ሥጋቱን በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች የኢቦላ ቫይረስ በኢትዮጵያ ተገኘ በሚል ለተናፈሰው ወሬ በሚመለከት በተሰጠ መግለጫ ነው፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎችና የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኃላፊም በአዲስ አበባ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብና ለጋዜጠኞች ባለፈው ዓርብ ዕለት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ማንኛውንም የሽብር ጥቃት በጥንቃቄ የሚከታተል በመሆኑና በንቃት ስለሚንቀሳቀስ፣ በከተማዋ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ተረጋግተው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ተነግሮአቸዋል፡፡ የኢቦላ ቫይረስን በተመለከተም እየተላለፈ ያለው መረጃ መሠረተ ቢስ እንደሆነ አክለው ከማስረዳታቸውም በላይ፣ ወረርሽኙን ለመከላከል ተገቢውና አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎች አክለው ገልጸዋል፡፡

ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ አባላትና ለጋዜጠኞች፣ ‹‹ሽብርተኝነትን በተመለከተ ሁልጊዜ ንቁ ሆነን መጠበቅ አለብን፡፡ ይህን ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ሲያደርገው የቆየና ወደፊትም የሚያደርገው ነው፤›› በማለት የመንግሥትን ንቁ እንቅስቃሴ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ለይስሙላ የተቋቋመ አይደለም፡፡ ሁልጊዜም ንቁ ሆኖ ሥጋቶችን ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር ይዋጋል፤›› በማለት፣ የአገሪቱ የደኅንነት ተቋም ማናቸውንም የሽብር ጥቃቶችንና ሥጋቶችን ለመከላከልና ለመቀልበስ ብቁና ዝግጁ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በቅርቡ በአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አማካይነት ስለተላለፈው በተለይም ቦሌ አካባቢ ሊፈጸም የችላል ስለተባለው የሽብር ጥቃት ሥጋት አምባሳደሩ ምሥጋናቸውን አቅርበው፣ አልሸባብና መሰል የሽብር ተቋማት አደጋ ለማድረስ እንዳይችሉ እግር በእግር ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡ አልሸባብ በአዲስ አበባም ሆነ በመላው አገሮቹ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይችል ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ አረጋግጠዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ዜጐቹንና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡን ከተለያዩ አደጋዎችና ጥቃቶች የመከላከል ግዴታ ያለበት በመሆኑ፣ ሁልጊዜም በተጠንቀቅና በዝግጁነት ላይ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም የሽብር ሥጋቶች ተጨባጭ ቢሆኑም ባይሆኑም፣ መንግሥት የሚከተለውን አካሄድ ለመገምገምና ለመረዳት ከማስቻላቸውም በላይ፣ የንፁኃን ዜጎችን ሕይወት ለመቅጠፍ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለመከላከል ይረዳል ብለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ መንግሥት ምንጊዜም ቢሆን በከፍተኛ ደረጃ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ዝግጁ በመሆኑና እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን በከፍተኛ ንቃት የሚከታተል ስለሆነ፣ በከተማዋ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ተረጋግተው የዕለት ተዕለት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ መክረዋል፡፡

የኢቦላ ቫይረስ አለመከሰቱን ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ያረጋገጡት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲና በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ዳዲ ጂማ ናቸው፡፡ አምባሳደር ዲና በቅርቡ በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች በኢትዮጵያ የኢቦላ ቫይረስ መከሰቱን በተመለከተ የተሠራጩት መረጃዎች መሠረተ ቢስና አሉባልታዎች ናቸው ብለው፣ ‹‹ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች ሆን ብለው በኅብረተሰቡ ላይ ጭንቀት ለመፍጠር በማለም ያሠራጩት ነው፤›› በማለት መረጃዎቹን አጣጥለዋቸዋል፡፡

ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራሉ አቶ ዳዲ በበኩላቸው፣ ‹‹በኢቦላ ቫይረስ በሽታ የተጠረጠረ ምንም ሰው አለመኖሩን አረጋግጠው፣ ነገር ግን ከኅብረተሰቡና ከጤና ሠራተኞች መረጃዎች እንደሚደርሷቸውና መረጃዎቹ በዓለም ጤና ድርጅትና በአሜሪካ የበሽታዎች መከላከል ማዕከል አማካይነት ከወጡት ምልክቶች ጋር እንደማይገናኙ በመሥሪያ ቤቱ ኤክስፐርቶች ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት የኢቦላ ቫይረስ በኢትዮጵያ እንዳልታየም አስታውቀዋል፡፡

ኢቦላን ለመከላከል እየተደረገ ስላለው የመንግሥት ዝግጁነት ያስረዱት ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራሉ፣ ‹‹በመጀመርያ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመለየት ሥራ የሚሠሩ ባለሙያዎችን መድበናል፤›› ብለው፣ በቀጣይ ደግሞ ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ ባለሙያዎችና ግለሰቦች ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

ሥልጠና የተሰጣቸው ግለሰቦችና ባለሙያዎችም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የመንግሥትና የግል ጤና ተቋማት ለሚያገለግሉ 250 የጤና ባለሙያዎች፣ ከአውሮፕላን ማረፊያ ለ365 ሰዎች፣ ከ20 በላይ ለሚሆኑ ለክልል ጤና ቢሮ ሠራተኞች፣ ከ100 በላይ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለሚያገለግሉ የጤና ባለሙያዎችና ለ145 የሆቴል ሥራ አስኪያጆች መሆኑ ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ሁለት የማቆያ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን፣ እነዚህም በአማኑኤል ሆስፒታልና በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ጤና ጣቢያ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ እያንዳንዳቸው ማቆያ ጣቢያዎች 50 አልጋዎች ያሉዋቸው ሲሆኑ፣ በአማኑኤል ሆስፒታል የሚገኘውን ጣቢያ የአልጋ ብዛት ወደ 100 ማሳደግ እንደሚቻልም ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራሉ አስረድተዋል፡፡

ኢቦላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮንጐና በሱዳን እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ የታየ መሆኑን፣ እስካሁን ድረስ ከ20 ጊዜ በላይ ወረርሽኞች መከሰታቸውን፣ የአሁኑ ግን ከሁሉም የላቀና በርካታ ሺሕ ሰዎችን ያጠቃ ነው በማለት አቶ ዳዲ ገልጸዋል፡፡

ምንጭ፦ ሪፖርተር

Leave a Reply

Your email address will not be published.