መሐመድ አማን ለዋሊያዎቹ መልካም ዕድልን ተመኝቷል

 

By Bizuayehu Wagaw from Monaco

 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ለ2014 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በናይጄሪያ ካላበር ወሳኝ ፍልሚያ የሚያደርግበት ዕለት በሁለቱም ፆታዎች የ2013 የዓለም ኮከብ አትሌቶች ተመርጠው ይፋ ከሚደረጉበት የሞንቴካርሎው ‹‹2013 World Athletics Gala›› ፕሮግራም ጋር ተገጣጥሟል፡፡ በዘንድሮው የኮከብ አትሌቶች ምርጫ በሁለቱም ፆታዎች ከመጨረሻዎቹ 10 ምርጦች ተርታ ከገቡት አራት አፍሪካውያን አትሌቶች ሶስቱ (ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋር እና መሐመድ አማን) ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን (IAAF) እና በኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፋውንዴሽን (IAF) የበላይነት በሚከናወነው ምርጫ ከመጨረሻዎቹ አስር ምርጦች ተርታ የገቡት አትሌቶች ደግሞ ዛሬ ምሽት በሞናኮ በሚደረገው የሽልማት አሰጣጥ ስነስርዓት ላይ እንዲገኙ ተጋብዘው በስፍራው ይገኛሉ፡፡ ዛሬ ጠዋት ባረፈበት ፌይርሞንት ሆቴል የIAAF ስፖንሰር የሆነው የጣልያኑ የመሮጫ ትራክ አምራች ድርጅት ‹‹MONDO›› በስጦታ መልክ ያበረከተለትን ‹‹FIFA WORLD CUP BRAZIL›› የሚል ፅሁፍ ያላት ኳስ አነስተኛ ኳስ ከመሰረት ደፋር ባለቤት ቴዎድሮስ ጋር ሲቀባበል ያገኘሁት መሀመድ አማን ‹‹አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አይተው ቢሞክሩኝ ጥሩ ነው›› የሚል ቀልድ ጣል ካደረገ በኋላ ‹‹በዛሬው ዕለት በናይጄሪያ ካላበር ወሳኝ ጨዋታ ላለባቸው ዋሊያዎቹ መልካም ዕድል እንዲገጥማቸው እመኝላቸዋለሁ›› በማለት መልካም ምኞቱን ገልፃDል፡፡ የእግር ኳስ ፍቅሩ ከፍተኛ የሆነው የመሰረት ደፋር ባለቤት ቴዎድሮስ የዛሬውን ጨዋታ እዚህ ካለው ፕሮግራም ጋር እንደምንም አቻችሎ መመልከት እንደሚፈልግ የነገረኝ ሲሆን ቡድናችን አሸንፎ ሲያልፍ የማየት ጉጉቱም ከፍ ያለ ነው፡፡ በሞናኮው የሚገኙ አትሌቶች፣ ጋዜጠኞች (ብዙአየሁ ዋጋው እና ሐይማኖት ጥሩነህ) እንዲሁም ሌሎች የፕሮግራሙ ተካፋይ ኢትዮጵያውያን (ወ/ሮ ብስራት ጠናጋሻው እና አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ) በሙሉ እዚህ ያለውን ፕሮግራም የሚታደሙት ግማሽ ልባቸውን ለዋሊያዎቹ ጨዋታ ሰጥተው ሲሆን ሁሉም ለብሔራዊ ቡድናችን መልካም ዕድል እንዲገጥመው ተመኝተዋል፡፡ ስለ2013 ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ተጨማሪ ነገሮችን ከመሐመድ አማንና መሰረት ደፋር አስተያየቶች ጋር በኋላ ላይ ይጥብቁ፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ ባልታወቀ ምክንያት በሞናኮው ፕሮግራም ላይ መገኘት እንዳልቻለች የፕሮግራሙ አዘጋጆች ገልፀውልኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.