መለያ ምቶች ዋልያዎቹን ወደ ግማሽ ፍፃሜ መርተዋል

Waliya vs Tanzania CECAFA

  • የአዘጋጇ አቋም አሁንም ደጋፊዎችን አላስደሰተም
  • የውድድሩ ንጉስ ሳትቸገር አልፋለች
  • የውድድሩ ባለክብር በግዜ ተሰናብታለች
  • አዲስ አበባ ስታዲየም በተመልካች እጥረት ተመትቷል

የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት ዓመታዊ የእግር ኳስ ውድድር (ዲኤስቲቪ ሴካፋ ቻሌንጅ ካፕ) የሩብ ፍፃሜ ፍልሚያዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂደው ለግማሽ ፍፃሜ የበቁት የመጨረሻዎቹ አራት ሀገራት ታውቀዋል፡፡ ቀጣዩ ፅሁፍ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎቹን ይዳስሳል፡፡

 

  • ዋልያዎቹ ከተቃውሞ ጋር ጉዟቸውን ቀጥለዋል

 

ታንዛኒያ፣ ርዋንዳ እና ሶማሊያ ይገኙበት ከነበረበት ምድብ አንድ ጨዋታ (ሶማሊያን) ብቻ አሸንፎ፣ የታንዛኒያ ተጨዋች በባከነ ሰዓት በራሱ ጎል ላይ ባስቆጠረው ጎል ተረድቶ በምርጥ ሶስተኛነት ሩብ ፍፃሜውን መቀላቀል የቻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 48 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከታንዛኒያ ጋር ተፋልሟል፡፡ የቡድኑን ነባር ተከላካዮች ሰልሀዲን ባርጊቾ እና ስዩም ተስፋዬን እንዲሁም ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነትን በጉዳት ምክንያት መጠቀም ያልቻሉት ዋልያዎቹ አቤል ማሞ (ግብ ጠባቂ)፤ ያሬድ ባዬ፣ አስቻለው ታመነ፣ አንተነህ ተስፋዬ እና ዘካሪያስ ቱጂ (ተከላካዮች)፤ ጋቶች ፓኖም፣ ኤልያስ ማሞ፣ አስቻለው ግርማ፣ በረከት ይስሀቅ እና ቢኒያም በላይ (አማካዮች)፤ መሀመድ ናስር (አጥቂ) በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ተጠቅመዋል፡፡ እንደ ቅዳሜው የምድብ የመጨረሻ ጨዋታ ሁሉ ይህንንም ጨዋታ ታንዛኒያዊያኑ ከመነሻው ጀምሮ ለመቆጣጠር የሞከሩ ሲሆን ተጋጣሚዎቻቸው በሚገባ ወደ ጨዋታው ቅኝት ከመግባታቸው በፊትም ለጎል የቀረበ እጅግ የሚያስቆጭ እድል አምክነዋል፡፡ ዋልያዎቹም ግን ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ገብተው መሀመድ ናስር ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ በላዩ ላይ ሰቅሎ ለማግባት ሲሞክር በግብ ጠባቂው ከተመለሰበት በኋላ የደረሰው ቢኒያም በላይ ከጎል አፋፍ እንዲሁ ትልቅ የጎል አጋጣሚ አምክኗል፡፡ ከዚያም ግን በ25ኛው ደቂቃ ላይ የታንዛኒያው አምበል ጆን ቦኮ በድንቅ መንገድ በጭንቅላቱ ገጭቶ ጎል በማስቆጠር ሀገሩን መሪ አድርጓል፡፡ ከ10 ደቂቃዎች በኋላ በረከት ይስሀቅ እና መሀመድ በጥሩ ቅብብል ሄደው በረከት ወደ ጎል የሞከረው ኳስ በአግዳሚ ተመልሶበት ዋልያዎቹን አቻ ማድረግ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ታንዛኒያዊያኑ በመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ገደማ መሪነታቸውን ሊያሰፉባቸው የሚያችሏቸው ወርቃማ አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡ በተለይ በባከኑ ደቂቃዎች ላይ ከቅርብ ርቀት በጭንቅላት ገጭተው ባዶ ጎል የሳቱት ደጋፊዎቻቸውን ያስቆጨ ነበር፡፡ ቡድኖቹ ለሁለተኛው አጋማሽ እንደተመለሱም ታንዛኒያዊያኑ በእንቅስቃሴ የበላይነታቸው የቀጠሉ ሲሆን ያስቆጠሩት ተጨማሪ ጎልም በትክክለኛ ውሳኔ ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ተሽሮባቸዋል፡፡ በ55ኛው ደቂቃ ላይ ግን ቢኒያም ያቀበለውን ኳስ በረከት ይዞ ወደ ጎል ሲገባ በፍፁም ቅጣት ክልል ውስጥ በታንዛኒያው ተከላካይ ሾማሪ ካፖምቤ ጥፋት ስለተሰራበት ርዋንዳዊው አርቢትር ለአዘጋጆቹ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል፡፡ ታንዛኒያዊያኑ ግን በውሳኔው ፍፁም ደስተኛ አልነበሩም፡፡ አምበሉ ጋቶች ፓኖም ፍፁም ቅጣት ምቱን ወደ ጎል ቀይሮም ቡድኑን አቻ አድርጓል፡፡ የጨዋታው መደበኛ ጊዜም በዚሁ ውጤት ተጠናቆ ቡድኖቹ ወደ መለያ ምቶች አምርተዋል፡፡ የመጀመሪያው መቺ ታንዛኒያዊያኑ የነበሩ ሲሆን የጆናስ ምኩዴን ምት አቤል ማሞ በድንቅ መንገድ መልሶ ሀገሩን መሪ አድርጓል፡፡ በዋልያዎቹ በኩል ጋቶች፣ መሀመድ፣ አስቻለው ታመነ እና ተቀይሮ የገባው በኃይሉ ግርማ በተከታታይ ያስቆጠሩ ሲሆን ታንዛኒያዊያም ሶስት ተከታታይ ምቶችን ካስቆጠሩ በኋላ የሾማሪ ካፖምቤም ምት በአቤል ድንቅ ብቃት ተመልሶ ዋልያዎቹ ድል አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ቡድናቸው እድለኛ ሆኖ ሳይሆን ስለሚገባው ጨዋታውን እንዳሸነፈ ገልፀዋል፡፡ ሜዳው፣ በጨዋታዎቹ መካከል የነበረው እጅግ አጭር ጊዜ እና የሴካፋ ከ20 ተጨዋቾች በላይ መያዝ ያለመቻል ደንብ የሚፈለገውን እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳይችሉ እንዳደረጓቸውም ተናግረዋል፡፡

 

  • የሚቾ ቡድን አገግሟል

 

በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ በኬኒያ በመሸነፍ ውድድሩን የጀመረው በቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ሚሉቲን ሴሬዲዬቪች ሚቾ የሚሰለጥነው የኡጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ከዚያ ሽንፈት አገግሞ ቀጣይ የምድብ ጨዋታዎቹን በድል በመወጣት ከምድቡ ያለፈ ሲሆን አሁን ደግሞ በሩብ ፍፃሜው የማላዊን አቻውን በአምበሉ ፋሩክ ማያ እና ሴዛር ኦኩቲ ጎሎች 2ለ0 በመርታት የግማሽ ፍፃሜ ስፍራውን አስተማምኗል፤ ይህ ጨዋታ በመደበኛ ጊዜ የተጠናቀቀ ብቸኛው የሩብ ፍፃሜ ፍልሚያም ሆኗል፡፡

 

  • ደቡብ ሱዳን አንገቷን ቀና አድርጋ ወጥታለች

 

በውድድሩ ምድብ ማጣሪያ ጂቡቲ እና ማላዊን ረትቶ እና ከሱዳን ጋር አቻ ተለያይቶ አንደኛ ሆኖ ለሩብ ፍፃሜው በመብቃት የውድድሩ ‹ክስተት› የሆነው የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ቡድን በሩብ ፍፃሜው ዳግም የሱዳን ደርቢ ገጥሞታል፡፡ በቅርቡ የተለያዩት ሁለቱ ሱዳኖች ሜዳ ላይ ግን በጎል መለያየት ሳይችሉ ወደ መለያ ፍፁም ቅጣት ምቶች ከተጓዙ በኋላ የሱዳኑ ግብ ጠባቂ ሳሊም ኤክራም አስደናቂ ብቃት ሱዳንን ወደ ግማሽ ፍፃሜ ሲመራ፣ ለደቡብ ሱዳን አስደናቂ ጉዞ መቋጫ ሆኗል፡፡ ኤክራም የሲልቬስተር ኦፊሪን ምት ሲያድን የመጨረሻውን ምትም ራሱ መትቶ አስቆጥሯል፡፡ በፈሊክስ ኮሞያንጊ የሚሰለጥኑት ደቡብ ሱዳናዊያኑ ግን እስከዚህ የውድድሩ ደረጃ ድረስ በመደበኛ ጊዜ አንድም ጎል ያልተቆጠረበት ቡድን ሆነው እና በአስደናቂ አቋማቸው አንገታቸውን ቀና አድርገው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡

 

  • ባለክብሯ ተሰናብታለች

 

ያለፈው ውድድር አሸናፊ እና በመጀመሪያ ጨዋታው ባላንጣው የኡጋንዳ ብሔራዊ ቡድንን ከረታ በኋላ ለውድድሩ አሸናፊነት ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው የኬኒያ ብሔራዊ ቡድን በርዋንዳ አቻው በመለያ ፍፁም ቅጣት ምቶች ተረትቶ ከውድድሩ ውጪ ሆኗል፡፡ መደበኛ ጊዜው ያለጎል አቻ ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የርዋንዳው ግብ ጠባቂ ሴለስቲን ንዳዪሺሚዬ የኤሪክ ጆሀና ኦሞንዲን ፍፁም ቅጣት ምት መልሶ እና ራሱም አስቆጥሮ የቻን አዘጋጇን ለግማሽ ፍፃሜ አብቅቷል፡፡

የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች

የግማሽ ፍፃሜ ፍልሚያዎቹ ሐሙስ ከቀትር ሰባት ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳሉ፡፡ በዚህ መሰረት ርዋንዳ ከሱዳን ሲፋለሙ አዘጋጇ ኢትዮጵያ ከውድድሩ የምንግዜም ኃያል ኡጋንዳ ጋር ትፋለማለች፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.