ሕዝባዊ ትብብር ለተቃዉሞች ስኬት ብቸኛ አዋጭ መንገድ ነው!

14218387_1187616214592655_965790004_n

በአብዱረዛቅ ሁሴን

ህዝባዊ ተቃውሞዎች በጊዜ ሂደት እየሰፉና እየተጠናከሩ እየሄዱ ነው፤ የሚያስከፍሉት መስዋትነትም እንዲሁ፡፡ የተቃውሞቹ መስፋትና መጠናከር የኢህአዴግ ራስ ምታት መሆን መጀመረቸው ከሚወስዳቸው ኢሰብአዊ እርምጃዎችና ከሚያወጣቸው የተዘበራረቁ መግለጫዎች መረዳት ቀላል ነው፡፡ ከኦሮሚያ ክልል በዘለል በአማራ ክልል እየተካሄዱ ያሉት ተቃውሞዎች የህዝብን ጥያቄ በሰላም መፍታት ለሚሳነው ኢህአዴግ ሰላሙን ነስተውታል፡፡ እስካሁን የሄደበት መንገድና የአገዛዙ ባህሪ ለሚነሱት ጥያቄዎች ተገቢ መልስ ሊሰጥ ይችላል ብሎ መጠበቅ ከባድ ነው፡፡ ተቃዉሞው እየተካረረ በሄደ ቁጥርና የሚከፈለው መስዋትነትም እየጨመረ ሲሄድ ኢህአዴግ መልስ ልስጥ እንኳን ቢል የሚሰማው መኖሩን የሚያጠራጥርበት ደረጃም እየተደረሰ ነው፡፡ ያው እስካሁን ካልተደረሰ ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህም ቀጣይ ጊዜያት መንግስት ተቃዉሞቹን ለመጨፍለቅ ያገኘውን ድንጋይ የሚፈነቅልበት እና ተቃውሞውም እየከረረና ጉልበተኛ እየሆነ የሚሄድበት ይመስላል፡፡

መንግስት ከሚፈነቅላቸው ደንጋዮች ውስጥ በቅርቡ የኮሚኒኬሽን ሚንስትር /ቤት እንዳስፈራራውም የህብረተሰብ ትስስርን ማፈራረስን አላማ ሊያደርግ እንደሚችል ነው፡፡ የሶሪያ እልቂትን እንደመማሪያ ማንሳት ትቶ እንደ ማስፈራሪያ መጠቀሙ የስርአቱን ንቅዘት ያሳያል፡፡ በከፍተኛ ጥንቃቄ እና በጠንካራ ዲሞክራሲ መታገዝ ያለበት የብሄር ተኮሩ ፌደራሊዝም ኢህአዴግን በመሰሉ አምባገን መንግስታት እጅ ሲወድቅ የሶሪያና የሩዋንዳ መሰሉ እልቂትን ለስልጣን መክረሚያ አድርገው እንደ መጨረሻ ካርድ አይጠቀሙም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካን በቅርብ ከሚያውቁና በውስጡም ካለፉ እንደ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳና ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ካሉ አንጋፋ ፖለቲከኞችና ምሁራን አፍም ተመሳሳይ ስጋት ሲንጸባረቅ መስማቱም የጉዳዩን አሳሳቢነት ያጎላዋል፡፡

አጠቃላይ ሂደቱ መስመር እንዳይለቅና መጨረሻውም የተሻለች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መፍጠር እንዲሆን ሁሉም ክፍል ሃላፊነት አለበት፡፡ እንዲህ አይነት አገራዊ ሃላፊነትን ከኢህአዴግ መጠበቅ ቢከብድም በአገዛዙ በደል እና በዲሞክራሲ እጥረት የተነሳው ህዝብ እና በተለይም እንቅስቃሴውን የሚመሩ አካለት ሃላፊነት ከሁላችንም የከበደ ነው፡፡ ይህን ፈታኝ ጊዜ በብቃት ለመወጣትና የሁላችን የሆነች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር እስካሁን በታሪካችን ተከስቶ የማያውቅ ባህሪ ያለዉን የኢህአዴግ አገዛዝ በቅጡ መገንዘብና በጥንቃቄ ማቀድን ይጠይቃል፡፡

3+1

አራት መሰረታዊ የሃይል ምንጮች አሉ፡ፖለቲካ፣ ወታደር፣ ኢኮኖሚ (3) + ህዝብ (1)፡፡ የአንድ መንግሰት ጥንካሬ እነዚህ የሃይል ምንጮች ላይ ባለው የቁጥጥር መጠን ይለካል፡፡ ዲሞክራሲያዊ በሆኑ ሃገራት ህዝብ የበላይ ወሳኝ ስለሆነ የህዝብ ምርጫ በፖለቲካው ወንበር ማን መቀመጥ እንዳለበት በመወሰን የአገሪቱን ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ተክለ ሰውነት የመወሰን አቅም አለው፡፡ የህዝብን ምርጫ መሰረት በማያደርጉ መንግስታትና ሃገራት ውስጥ ግን የሶስቱንን የሃይል ምንጮች የተቆጣጠሩ ሃይላት የአገሩቱን እጣ ፈንታ መወሰኑ ላይ ትልቅ ሚናን ይጫወታሉ፡፡ በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ዘመናዊ ታሪክ የነዚህ የአራት ሃይል ምንጮች ሚና የአንድ መንግስትን እድሜ እየለኩ ሲቆርጡ ተስተውሏል፡፡

ፊውዳላዊ መሰረት የነበረው የቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ መንግስት ዘመናዊነትን ወደ ወታደሩ ከማስገባቱ በፊት በንጉሱ አካባቢ ያሉ መኳንንት የአገሪቱን ፖለቲካዊ ስልጣን፣ ወታደራዊ ሃይልና ኢኮኖሚውን በስፋት ይቆጣጠሩት ነበር፡፡ ዘመናዊ ትምህርትና ዘመናዊነት እየተስፋፋ በመጣ ቁጥር ግን ወደ ፖለቲካዊ ስልጣን የሚመጣው ለአገዛዙ ቅርብ የነበረ ቢሆንም ከበፊት መኳንንቶችና ባላባቶች በእጅጉ ባነሰ መልኩ ለስርአቱ ስሜታዊና  እና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ የቀነሰ መሆን ጀመረ፡፡ የወታደሩ ሙሉ ለሙሉ ከፊውዳላዊ ወታደራዊ አደረጃጀት ነፃ መሆኑ የንጉሱን ስርአት ከህዝብ ተቃዉሞ ጠለላ ሊሆኗቸው ከሚችሉት ሁለት ዋነኞቹን የሃይል ምንጮች እንዲያጡ አደረጋቸው፡፡ በኢኮኖሚው (በብዛት የመሬት ባለቤትንትን ይመለከታል) ዘንድ ምንም እንኳን ለስርአቱ ቅርብ በሆኑ ሰዎች ዘንድ ቢሆንም ሊከሰት የሚችልን ተቃውሞ ለማስቆም በሚረዱት ፖለቲካዊና ወታደራዊ ተቋማት ውስጥ ግን ሁነኛ ቦታ አልነበረቸውም፡፡ ስለዚህም ንጉሱ የህዝብን ጥያቄ ከመመለስ ውጪ ለመጨፍለቅ የሚያስችል በቂ የሃይል ምንጭ ቁጥጥር ሳይኖራቸው ቀረ፡፡ ጥያቄዎችንም መመለስ ሲሳናቸውና አራተኛ ሃይል የሆነው ህዝቡ ተቃውሞውን እያፋፋመ ሲሄድ ከሶስቱ የሃይል ምንጮች አንዱ የሆነው ወታደር ከህዝቡ ጎን በመቆም የሃይል ሚዛኑን በማዛባት አገዛዙ እንዲያበቃ አደረገው፡፡

በደርግ ዘመንም እነዚህ አራት የሃይል ምንጮች ትስስር አገዛዙን እድሜ መወሰኑ ላይ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡ ደርግ ፖለቲካዊ ስልጣንን እና ወታደራዊ ሃይልን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥሩ ውስጥ አድርጎ ነበር፡፡ ፖለቲካዊ ስልጣኑን በመጠቀም የፈለገውን ሲሾም የፈለገውን ሲሽር የፈለገውን ሲከስ የፈለገውን ሲያስር ነበር፡፡ ወታደራዊ ሃይሉ ደግሞ ያለ ማንኛውንም ተቃውሞዎች ላይ ያለርህራሄ እርምጃ ይወስድ ነበር፡፡ በሁለቱም መዋቅሮች ውስጥ የደርግን ርእዮተ አለም የሚያስፈፅሙ አመራር ካድሬዎችን በርካታ ነበሩ፡፡ ደርግ በኢኮኖሚው ላይ ያለው ቁጥጥር መጠንና አይነት ግን ለስርአቱ መውደቅ ሰበብ ሆኖታል፡፡ ኢኮኖሚያዊ የሃይል ምንጭን መቆጣጠር ስንል በሁለት መልኩ ሊገለጽ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው የኢኮኖሚውን ወሳኝ ክፍሎች ፖለቲካዊ ስልጣን ባላቸው ግለሰቦች ቁጥጥር ስር መሆንን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የስልጣን ባለቤቶች ስልጣናቸውን ተገን በማድረግ ሰፊ ሃብትን ለግልም ሆነ በአካባቢያቸው ማካበት መቻልን ይመለከታል፡፡ ደርግ የሚያራምደው ርእዮተ አለም ከኢኮኖሚው የወል ተጠቃሚነትን እንጂ የግለሰብ ተጠቃሚነትን የሚፈቅድ አልነበረም፡፡ አንድ በፖለቲካዊ ሹመት ወደ ስልጣን የመጣ ግለሰብ ስልጣኑን በመጠቀም በቀላሉ ሃብት ማካበትና አካባቢው ያሉትን ሰዎችንም የምዝበራው ተጠቃሚ ማድረግ በእጅጉ ከባድ ነበር፡፡ ስለዚህም እንደዚህ አይነት ባለስልጣናትና ወታደራዊ አመራሮች ለደርግ ሊኖራቸው ከሚችለው ርእዮተ አለማዊ ቅንነት ባለፈ ስርአቱ እንዲከርም ተጨማሪ መስዋትነት ሊያስከፍል የሚችል የግልም ሆነ የቤተሰባዊ የጎላ ህልውናዊ ትስስርና ተጠቃሚነት አልነበራቸውም፡፡ አገዛዙ አረመኔነቱ እየጨመረ ሲሄድና የትጥቅ ትግሉም ሲጠናከር ስርአቱና በውስጡ ያሉ ግለሰቦች በቀላሉ መፍረክረክ ጀመሩ፡፡ በስተመጨረሻም የኢኮኖሚያዊ ሃይልን አለመቆጣጠር ከህዝብ ሃይል ጋር ሲደመር በፖለቲካና በወታደራዊ ሃይል የተንጠለጠለውን የደርግ አገዛዝን አወረደው፡፡

እነዚህ የቅርብ ጊዜ ታሪኮቻችን ሁለት ወሳኝ ነገሮች ያስተምሩናል፡፡ የህዝብ የበላይነት በማይረጋገጥባቸው አምባገነን መንግስታት ውስጥ የህዝብ ተቃውሞ ለብቻው የስርአት ለውጥን የማምጣት ሃይሉ ዝቅጠኛ መሆኑን፤ በሌላ በኩል በስልጣን ላይ ያለ አምባገነናዊ መንግስት ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ የሃይል ምንጮችን በአግባቡ ካልተቆጣጠረ ከሶስት አንዳቸው ከህዝብ ጋር በማበር መጨረሻውን በቀላሉ ሊያቀርቡት እንደሚችሉ፡፡ የኢህአዴግ መንግስት በተለይም ግንባሩን በግንባር ቀደምትነት እየመሩት ያሉት የህወሃት ልሂቃን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ የሃይል ምንጮችን መቆጣጠር መቻላቸውና በሶስተኝነትም ግለሰባዊም ሆነ ቡድናዊ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምንም እያካበቱበት በመሆኑ ከአገዛዙ ጋር ያለውን ትግል ከባድ፣ ጥንቃቄና ቆራጥነት የሚያስፈልገው እንደሆነ ያሳየናል፡፡

የህዝብ ሃይልን ማፈርጠም

የሃገርን እጣ ፈንታ መወሰን ከሚችሉ የሃይል ምንጮች ውስጥ ህዝብ ሲቀር ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የሃይል ምንጮች በኢህአዴግ በተለይም ህወሃት ሹማንቶችና አካባቢያቸው ባሉ ግለሰቦች ቁጥጥር ስር ይገኛሉ፡፡ ለነዚህ ባለስልጣናት ከስልጣን መወገድ ማለት እንደ ንጉሱና ባላባቶቻቸው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ብቻ፤ እንደ ደርግ ባለስልጣናት ፖለቲካዊና ወታደራዊ ስልጣንን ማጣት ብቻ ሳይሆን እስከዛሬ ያከማቹትን ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቁጥጥርና ጥቅም ማጣትም ጭምር ነው፡፡ የሶሪያ የእልቂት ምሳሌንም ማንሳት ያስፈለጋቸውም ለዚሁ ነው፡፡ ሶሪያን ለረጅም ጊዜ እየመራ ያለው በወታደራ መፈንቅለ መንግስት የመጣው የባዝ ፓርቲ በአብዛኛው በሶሪያ ውስጥ አስር ፐርሰንት ከማይሞሉት አለዋይቶች የተወጣጣ ሲሆን ለረጅም ጊዜም የሃገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሃይሎችን ተቆጣጥሮ ቆይቷል፡፡ ግጭቱ ከመንግስት ህዝብ አልፎ ሴክቴሪያን ቅርፅ መያዝ ሲጀምር በሽር አሳድም ሆነ ባዝ ፓርቲ ትግሉን ስልጣን ልቀቅ አትልቀቅ ብቻ ሳይሆን ስልጣንን፣ ወታደራዊን እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን ከማሳጣት አልፎ የአለዋይቶችን እልቂት የሚያስከትል እንደሆነ ስለተገነዘቡ በቁጥጥራቸው ስር ያለውን ማንኛውንም ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ኢኮኖሚዊ ሃይል በመጠቀም እስከመጨረሻው የደም ጠብታ እንዲታገሉ አስገደዳቸው፡፡ የህዝብ አመፅ ለብቻው የመንግስትን ለውጥ ማምጣትም ተሳነው፤ ህዝብን ሳይዙ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ሃይሎችንም መቆጣጠር ሃገርን ለማስተዳደር በቂ ሳይሆንም ቀረ፡፡ በስተመጨረሻም ታሪካዊቷ ሶርያ የህዝብ እልቂት ፣ ጭፍጨፋ እና የአገር ውድመት ምሳሌ አደረጓት፡፡

በአገራችን እየሰፋ ያለውንም ተቃውሞ በአግባቡ መምራት እስካልተቻለ ድረስ ወደ ተመሳሳይ የእልቂት ቦይ መፍሰሳችን እንደማይቀር መተማመኛ ማንም ሊሰጠን አይችልም፡፡  ህዝባዊ ተቃውሞው ለግዜው በቁጥጥሩ ውስጥ ያለው የህዝብ ሃይል ብቻ መሆኑን በመገንዘብ የቀሪ ሶስት የሃይል ምንጮችን ከተቆጣጠጠውን ህወሃት/ኢህአዴግን በጥንቃቄ መታገል አለበት፡፡ ትግሉ የህወሃት ልሂቃንን የያዙተን የሃይል ምንጮች በሚያቀጭጭና የህዝብ ሃይልን በሚያፈረጥም መልኩ ስትራቴጂዎች ሊኖሩት ይገባል፡፡ የሚከተሉት አካሄዶች በዚህ ረገድ ሊረዱን ይችላሉ፡፡

ኢህአዴግና ህዝብን መለየት

ኢህአዴግ ከሚያራምደው አስተሳሰብና ከሚከተለው ፖሊሲ ተጠቃሚ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል ይኖራል፡፡ ምናልባትም ይህ ተጠቃሚነት ለአንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ከሃያ አምስት አመቱ ቆይታው በተወሰኑት ውስጥ ሊሆን ይችላል፤ ለሌሎች ደግሞ እስካሁንም ሊቀጥል የሚችል፡፡ በቋንቋው መማር መቻሉን፣ የራሱን የህብረተሰብ ክፍል የማስተዳደር እድል መሰጠጥን እና የመሳሰሉ ማንነት ነክ ጉዳዮች ላይ ኢህአዴግ በሚከተለው ርእዮተ አለም ተጠቃሚ የሆኑ ህዝቦች ለአገዛዙ ቅርብ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም፡፡ ከስርአቱ ጋር የቅርብ ትስስር በመመስረትም ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን የጋበሱም በስፋት ይኖራሉ፡፡ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ከኢህአዴግ ጎን የመሰለፍ እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ሕዝብ ብቸኛ የሃይል ምንጩ የሆነው የተቃውሞ እንቅስቃሴ እነዚህን ከስርአቱ ጋር የጥቅም ትስስር እንጂ መሰረታዊ ቁርኝት የሌላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች አስፈላጊውን የቃልም ይሁን የተግባር መተማመኛ በመስጠት ለኢህአዴግ ሊሰጡ የሚችሉትን ድጋፍ መቀነስ ይገባዋል፡፡ የስርአቱ መወገድ ከነሱ ህልውና መክሰም ጋር እንደማይያዝና ዲሞክራሲያዊት በሆነች ኢትዮጵያ የሁሉም መብት ተከብሮና ታፍሮ መኖር እንደሚቻልም ተስፋን መስጠት ኢህአዴግ ላለመውደቅ ከሚደገፍባቸው ምርኩዞች ዋነኛውን እንማስወገድ ይቆጠራል፡፡

ህወሃትን ከኢህአዴግ መለየት

ህወሃት የግንባሩ ፈላጭ ቆራጭ እንደሆነ ማስረጃ ማቅረብ አያስፈልግም፡፡ በግንባሩ ስር ያሉ ሶስት ድርጅቶችን ከአመሰራረታቸው ዘመን ጀምሮ አሁንም ድረስ በፈለገው ቅርፅና መጠን እየከረከማቸው ኖሯል፡፡ ከፍተኛ አመራራቸውን ጨምሮ የፈለገውን የመሾም፣ የጠላውን የመሻር እና ያስከፋውን የማሰር አቅሙም አለው፡፡ ከጠቅላይ ሚንስቴሩ ጀምሮ የሁሉም ፓሪቲ መሪዎችን ከበስተኋላ የሚያዝና የሚያናዝዝ ህወሃት እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ እነዚህ እጣፈንታቸው በህወሃት ሹማንቶች እጅ ላይ የሆኑ አመራርና ፓርቲዎች የተቃውሞው እንቅስቃሴ በብልሃት ሊጠቀምባቸው ይገባል፡፡ ህዝባዊው ተቃዉሞው እነዚህ ፓርቲዎችና አመራሮቻቸውን በሚሰነዝራቸው ትችትም ይሁን ዛቻ ወደ ጥግ በመግፋት ከህወሃት ጋር ያላቸውን የጥቅምና የስልጣን ግንኙነት ወደ ህልውናዊ ግንኙት እንዳይቀየር መጠንቀቅ የግድ ነው፡፡ ከህዝብና ከስልጣናቹ አንዱን ምረጡ በሚል ወቅቱን ያልጠበቀ ጀብደኝት አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ የህዝብን ጥያቄ በጉልበት ለመጨፍለቅ እየሞከረ ላለው አገዛዝ ተጨማሪ የህልውና ትስስር ያላቸው ሃይላትን እንደመደጎም ስለሚቆጠር ተቃውሞዉን የሚመሩ አካላትና ህዝቡ በኢህአዴግ ውስጥም ህወሃትንና ሌሎቹን በለየ መልኩ የትግል እቅዶችን መንደፍ ያስፈልገዋል፡፡

ህወሃትን ከትግራይ ህዝብ መለየት

ህዝብ ለዘላለም ነዋሪ ሲሆን ስልጣን እና ባለስልጣናት ግን አላፊዎች ናቸው፡፡ የዲሞክራሲ ትግልን ከህዝብመንግስት ትንቅንቅ አውጥተን ወደ ህዝብህዝብ ካወረድነው ለእልቂት በር ከፋቾች እንሆናለን፡፡ ለጭቆናው መንስኤ የሆኑትን የጥቂት ልሂቃን ሃጢያት ለአንድ ሙሉ ህዝብ ማሸከም አግባብ ከፍትሃዊነት የራቀ ነው፡፡ ይህ አይነት አካሄድ ከስርአቱ ጋር ምንም አይነት ንኪኪ ከሌላቸው የትግራይ ተወላጆች አንስቶ አገዛዙን ከማናችም በላይ አምርረው የሚጠሉትን ጭምር ኢፍትሃዊ የሆነ ጫና በማሳደር ከህወሃት ጋር ህልውናዊ ትስስር እንዲመሰርቱ ሊያስገድዳቸው ይችላል፡፡ ይህ ለትግሉ ጠላትን ከማብዛቱም በላይ ለእልቂትና ለሃገር መፈራረስ ሰበብም የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብን ከህወሃት ልሂቃን አለመለየት የዲሞክራሲ እጦት ያስነሳው ተቃውሞ እና አመራሩን ሁለት የመርህ ግጭቶች ውስጥ ይከተዋል፡፡ በአንድ በኩል ህወሃት ዘርን መሰረት ያደረገ ማግለልና ጭቆና እያደረሰ ነው እያልን እኛም ተመሳሳይ አካሄድ የምንከተል ሲያስመስለን በሌላ በኩል ደግሞ ህዝብን እንደ ህዝብ የማያከብር አስተሳሰብ ህወሃት የነፈገንን ህዝብን መሰረት ያደረገች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንመሰርታለን ማለት ለትዝብት ይዳርገናል ፡፡ ስለዚህም የትግራይን ህዝብ እንደ ህዝብ የሚወነጅል አካሄድን፣ በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደርስ ስነልቦናዊ ጫናንና የሃይል እርምጃዎችን ግልጽ በሆነ ቃል ማውገዝና ለመከላከል የተቻለውን ያህል ርቀት መጓዝ አንድነቷን ለጠበቀች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለተደዋደቁ ሰማእታት ክብር መስጠት ነው፡፡

ማጠቃለያ

በስፋትና በሚያስከፍሉት ዋጋ እየጨመሩ የሄዱት ህዝባዊ ተቃውሞዎች ዲሞክራሲት ኢትዮጵያን ለመመስረት ወደሚያስችለን ግብ እንዲያደርሱን በጥንቃቄ መመራት ይገባቸዋል፡፡ ህወሃት ፖለቲካዊና ወታደራዊ ስልጣኑን ከመቆጣጠሩም ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጉልበትን ማካበቻ በማድረጉ በአገራችን ዘመናዊ ታሪክ ሶስቱን መሰረታዊ የሃይል ምንጮችን የተቆጣጠረ ብቸኛ አገዛዝ ያደርገዋል፡፡ ንጉሱ አራተኛ የሃይል ምንጭ የሆነው ህዝብ ሲያምፅባቸው ዘመናዊነት ወታደራዊ እና በከፊል ፖለቲካዊ የሃይል ምንጮች ነፍጓቸው ስለነበር በቀላሉ ከስልጣን ሊወገዱ ቻሉ፡፡ ደርግ በበኩሉ ፖለቲካዊ እና ወታደዊ ሃይልን ተቆጣጥሮ የነበረ ቢሆንም ሹማምንቱን ከርእዮተ አለም ቅንንት ባለፈ ከስርአቱ ጋር ህልውናዊ ትስስር እንዲኖራቸው ሊያደር የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን አስገኝቶላቸው ስላልነበር የህዝብ ሃይል ጫናው ሲበረታ ስርአቱ በቀላሉ መፍረክረክ ቻለ፡፡

ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊም ሆነ ኢኮኖሚያው የሃይል ምንጮች ላይ ቁጥጥር የሌለውና የህዝብን ሃይል ብቻ መሰረት ያደረገው የአሁኑ ህዝባዊ ተቃውሞ ግብ እንዲመታ ጠላትን በመቀነስ እና የህዝብን ጉልበት በማፈርጠም ላይ መሰረት ያደረገ ስትራቴጂዎችን መከተል ይገባዋል፡፡ ይህንም በሶስት እርከን በመክፈል ከኢህአዴግ ከስርአቱ ተጠቅሚያለው ከሚልው ህዝብ በመለየት፣ ህወሃትን ከኢህአዴግ በመለየትና የትግራይን ህዝብ ከህወሃት በመለየት ላይ በማተኮር ሰፊ ስራዎችን መስራት የህወሃትን በሌሎች ድጋፍ የፈረጠመውን ጡንቻ ከማመንመኑም በላይ አገሪቱን ከደገሱላት የእልቂት ድግስ በማሰናከል አንድነቷን የጠበቀች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት የሚደረገውን ትግል ስኬት ያፋጥነዋል፡፡

2 thoughts on “ሕዝባዊ ትብብር ለተቃዉሞች ስኬት ብቸኛ አዋጭ መንገድ ነው!

  1. ዎድመሞችን። ይፍታል ከእግር ጋር የምነገበት ግዜነው
    አይዝች በርቱ ይነገል

Leave a Reply

Your email address will not be published.