ሐጎስ ገብረሕይወት በወንዶች 5000ሜ. የዳይመንድ ሊግ ዋንጫ አሸናፊ ሆነ

በ2016 ዳይመንድ ሊግ የመጀመሪያ ፍፃሜ አሸናፊ የሆኑ 16 አትሌቶች ዙሪክ ላይ የዋንጫ ሽልማታቸውን ተረክበዋል

ላለፉት አራት ወራት አራት ወራት ሲካሄድ የቆየው የ2016 ዓ.ም. የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ዳይመንድ ሊግ ፉክክር ከሚያካትታቸው ሁለት የፍፃሜ ውድድሮች መካከል የመጀመሪያው በትላንትናው ዕለት በስዊዘርላንድ ዙሪክ ተካሂዶ 16 አሸናፊዎች የዋንጫ ሽልማታቸውን ሲቀበሉ ኢትዮጵያዊው ሐጎስ ገ/ህይወትም በወንዶች 5000ሜ. የበላይ ሆኖ ማጠናቀቅ የቻለበትን ድል አስመዝግቧል፡፡
የተመልካችን ትኩረት ሳቢ በነበረው የወንዶች 5000ሜ. ፉክክር ከጅምሩ አሯሯጮቹን ተከትለው ሲሮጡ የነበሩት በ3000ሜ. መሰናክል ሯጭነቱ የሚታወቀው አሜሪካዊው ኢቫን ጃገር እና ኬንያዊው ኮርኔሊየስ ካንጎጎ የነበሩ ሲሆን ገና በመጀመሪያው ዙር ከተከታዮቻቸው ጋር ፈጥረውት የነበረውን የአራት ሰከንድ ልዩነትም የውድድሩ አጋማሽ ላይ ወደ አስራ አምስት ሰከንድ ከፍ አድርገውት ነበር፡፡ ውድድሩ ሊጠናቀቅ ሁለት ሺህ ሜትር ሲቀረው ውድድሩን ከፊት ሆኖ ከሚመራው ጃገር ጋር የነበራቸውን ልዩነት ለማጥበብ አንድ ላይ የጣሩት አትሌቶች ልዩነቱን ማጥበብ ቢችሉም ሊጠናቀቅ አንድ ዙር ሲቀርም ጃገር ተከታዮቹን በአምስት ሰከንድ ልዩነት በመምራት ላይ ነበር፡፡ ጃገር በመጨረሻው ዙር ላይ የመዳከም አዝማሚያ ሲታየበት አቅሙን ቆጥቦ የቆየው ሀጎስ ገብረሕይወት በመጨረሻው ዙር ከእርሱ ጋር የነበረውን ልዩነት በማጥበብና መቶ ሜትር ሲቀረው አልፎት በመሄድ በ13 ደቂቃ ከ14.82 ሰከንድ አሸናፊ ለመሆን በቅቷል፡፡
በወንዶች 5000ሜ. የዳይመንድ ሊጉ የዓመቱ የአጠቃላይ አሸናፊ የመሆን ፉክክሩ በኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች (ሙክታር እድሪስ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ እና ሀጎስ ገ/ሕይወት) መካከል የነበረ ሲሆን ከውድድሩ በፊት በ15 ነጥብ የሶስተኛነትን ደረጃ ይዞ የነበረው ሀጎስ በዙሪክ አሸናፊ ሆኖ ባስመዘገበው 20 ነጥብ አጋዥነት በአጠቃላይ በ35 ነጥብ የዳይመንድ ሊጉን ዋንጫ እና የ40 ሺህ ዶላር ሽልማት አሸናፊ ሆኗል፡፡ ከውድድሩ በፊት 30 ነጥብ ይዞ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የነበረው ኢትዮጵያዊው ሙክታር እድሪስ እስከ አራተኛ ባለው ደረጃ ውስጥ ሆኖ መጨረስ የአጠቃላይ አሸናፊ ሊያደርገው ይችል የነበረ ቢሆንም በ13፡23.05 አስረኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ በርቀቱ የሪዮ ኦሊምፒክ የብር ሜዳልያ አሸናፊ የሆነው አሜሪካዊው ፖል ቼሊሞ በ13፡16.51 ሁለተኛ ሲወጣ ኢቫን ጃገር በ13፡16.86 ሶስተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ ዮሚፍ ቀጄልቻ በ13፡19.90 ሰባተኛ፣ ኢብራሂም ጄይላን በ13፡30.55 አስራ ሶስተኛ እንዲሁም ኢማነ መርጋ በ14፡00.22 አስራ ስምንተኛ ደረጃን ይዘው ጨርሰዋል፡፡
በሌሎች ውድድሮች የተመዘገቡትን ውጤቶች አለፍ አለፍ ብለን ስንመለከት በወንዶች 100ሜ. ጃማይካዊው አሰፋ ፓወል በ9.96 (ለ97ኛ ግዜ ከአስር ደቂቃ በታች የገባበት ነው) ሲያሸንፍ አሜሪካዊያኑ ላሽዋን ሜሪት (44.64) በ400ሜ.፣ ኬሮን ክሌመንት (48.72) በ400ሜ. መሰናክል፣ ክርስቲያን ቴይለር (17.80ሜ.) በስሉስ ዝላይ ድል ቀንቷቸዋል፡፡ በሴቶች 200ሜ. የኦሊምፒክ ሻምፒዮኗ ጃማይካዊት ኤላዪኔ ቶምፕሰን የዳመንድ ሊግ ሪኮርድ በሆነ 21.86 ሰከንድ ቀዳሚ ሆና ስታጠናቅቅ ዳፍኔ ሺፐርስ በ21.86 ሁለተኛ ወጥታለች፡፡ ደቡብ አፍሪካዊቷ ካስተር ሴመንያ የ800ሜ. ፉክክሩን በ1፡56.44 ቀዳሚ ሆና በማጠናቀቅ በዚህ ዓመት ያለመሸነፍ ጉዞዋን ያስቀጠለች ሲሆን የዳይመንድ ሊጉ የአጠቃላይ አሸናፊነቷንም አረጋግጣለች፡፡
አራት ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ተሳታፊ የነበሩበት የሴቶች 1500ሜ. ፉክክር በአሜሪካዊቷ ሻኖን ሮውበሪ (3፡57.78) ቀዳሚነት ሲጠናቀቅ እንግሊዛዊቷ ላውራ ሙዪር በ3፡57.85 ሁለተኛ ወጥታ የዳይመንድ ሊጉ የአጠቃላይ አሸናፊ መሆኗን አረጋግጣለች፡፡ የዳይመንድ ሊጉን የነጥብ ፉክክር በበላይነት ስትመራ የነበረችው ኬንያዊቷ የሪዮ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ ፌይዝ ኪፕዬጎን (4፡01.86) ሰባተኛ ሆና መጨረሷ አስገራሚ ሆኖ አልፏል፡፡ በውድድሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ ዳዊት ስዩም (3፡58.63) አምስተኛ፣ በሱ ሳዶ (3፡59.47) ስድስተኛ፣ ጉዳፍ ፀጋዬ (4፡04.29) ዘጠነኛ፣ አክሱማዊት እምባዬ (4፡12.49) አስራ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል፡፡ በሴቶች 3000ሜ. መሰናክል ትውልደ ኬንያዊት የባህሬይን አትሌት ሩት ጄቤት በ9፡07.00 ቀዳሚ በመሆን የዳይመንድ ሊጉ የአጠቃላይ አሸናፊነቷን ስታረጋግጥ ኬንያዊት ሀይቪን ኪገን (9፡10.15) እና አሜሪካዊቷ ኤማ ኮበርን (9፡17.42) ሁለተኛ እና ሶስተኛ ወጥተዋል፡፡ በዚህ ፉክክር ላይ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያኑ እቴነሽ ዲሮ (9፡21.67) እና ሶፊያ አሰፋ (9፡22.09) በቅድም ተከተል አምስተኛ እና ስድስተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡
በዙሪክ የዳይመንድ ሊግ ዋንጫ እና 40 ሺህ ዶላር የገንዘብ ሽልማት አሸናፊ ከሆኑት 16 አትሌቶች መካከል ፈረንሳዊው የምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳሪ ሬኖ ላቪለኒዬ ዳይመንድ ሊጉ በ2010 ዓ.ም. ከተጀመረ አንስቶ የተደረጉትን ሁሉንም ውድድሮች በበላይነት ማጠናቀቅ የቻለ ብቸኛ አትሌት በመሆን ሰባተኛ ዋንጫውን የተቀበለ ሲሆን ዲስከስ ወርዋሪዋ ሳንድራ ፔርኮቪች እና የስሉስ ዝላይ ተወዳዳሪው ክርስቲያን ቴይለር አምስተኛ ዋንጫቸውን ተቀብለዋል፡፡
በድንቅ የአየር ሁኔታ፣ ስታድየም የሞላ ታዳሚ እና ምርጥ የቴሌቪዥን ምስል ቅንብር ታጅቦ የተከናወነው የዙሪክ ዳይመንድ ሊግ አንድ አህጉራዊ፣ ሁለት የውድድር ስፍራ እና አንድ የዳይመንድ ሊግ ሪኮርዶች የተሻሻሉበት ሆኖ ተጠናቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.