ለአዲሱ አመት በርካታ የፖለቲካ እስረኞች በምህረት ተለቀቁ

o-BLACK-PERSON-PRISON-facebook

hands of a prisoner on prison bars

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 6፣ 2007 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አዲሱን ዓመትና የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን መጀመርን ተከትሎ ለ238 ታራሚዎች ይቅርታ ተደረገ።

የፍትህ ሚንስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ ይቅርታ ከተደረገላቸው ታራሚዎች በእነ አቡበከር አህመድ የክስ መዝገብ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ  ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በሀይል ለመናድ ተንቀሳቅሰው የተቀጡ፣ የአሸባሪው ኦነግ እና ግንቦት ሰባት አባላት፣ ራሱን የጋምቤላ ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ (ጋህዴን) አባላት ይገኙበታል።

ይቅርታ ከተደረገላቸው ውስጥ 24ቱ የአሸባሪው ኦነግ አባላት ሲሆኑ፥ ሁለቱ የአሸባሪው ግንቦት ሰባት አባላት መሆናቸውም ነው የተጠቀሰው።

ከአሸባሪው ግንቦት ሰባት ድርጅት በእነ ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ መዝገብ ተፈርዶባቸው በእስር የሚገኙ ዘሬ ይቅርታ የተረገላቸው ሁለቱ ግለሰቦች አዱኛ አለማየሁ ገብረማርያም እና አደፍርስ አሳምነው ክብረት ናቸው።

ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት በመንቀሳቀስ በቅርቡ የቅጣት ውሳኔ ከተላለፈባቸውና በእነ አቡበከር አህመድ መዝገብ ከተቀጡ 18 ግለሰቦች በጥፋታቸው በመፀፀታቸው ነው ስድስቱ ዛሬ ይቅርታ የተደረገላቸው።

እነርሱም ያሲን ኢሳ ዓሊ፣ ባህሩ ዑመር ሽኩር ፣ አቡበከር አለሙ ሙሄ፣ ሳቢር ይርጉ ማንደፍሮ እና ሙኒር ሁሴን ኑርሁሴን ናቸው።

ሌሎቹ የአሸባሪው የኦነግ አባል ሆነው ተቀጥተው እና በጥፋታቸው ተፀፀተው ይቅርታ የተደረገላቸው ከተላለፈበቻው የቅጣት ውሳኔ ከሶስት ከአራት አመታት በላይ በእስር የቆዩ ናቸው።

በአጠቃላይ ይቅርታ ከተደረገላቸው ታራሚዎች ሶስቱ ሴቶች ሲሆኑ የተቀሩት ወንዶች ናቸው።

ቀደም ብለው ከተጠቀሱት ውጪ ያሉት 205ቱ ታራሚዎች በቸልተኝነት ሰው መግደል፣ እምነት ማጉደል ፣ በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል በመሳሰሉ ወንጀሎች ተቀጥተው የተፀፀቱ ታራሚዎች ናቸው።

ሚኒስትሩ ህብረተሰቡ ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች የተፀፀቱ በመሆናቸው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ፣ ታራሚዎችም ቢሆን በቀጣይ በልማት ስራዎች ላይ እንዲሳተፉና ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።

ለመላ የኢትዮጵያ ህዝብም የመልካም ምኞት መግለጫቸውን አስተላልፈዋል።

የፍትህ ሚኒስቴር የይቅርታ ቦርድ የታራሚዎቹን መፀፀት ከግምት አስገብቶ ይቅርት እንዲያገኙ ሲያደርግ፥ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ በአዋጁ መሰረት እንደሚያፀድቁ ይታወቃል።

– Source: FBC

1 thought on “ለአዲሱ አመት በርካታ የፖለቲካ እስረኞች በምህረት ተለቀቁ

Leave a Reply

Your email address will not be published.