ለተሰንበት ግደይ በዶሀ ዓለም ሻምፒዮና የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሜዳልያ ድል አስመዘገበች

17th IAAF World Athletics Championships Doha 2019 - Day Two

ለተሰንበት ግደይ የሴቶች 10 ሺኅ ሜትር የብር ሜዳልያ አሸናፊ Photo: '© Getty Images for IAAF'

ዓርብ መስከረም 16 በተጀመረው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሁለተኛ ቀን ውሎ ለተሰንበት ግደይ በ10000 ሜትር ፍፃሜ ሁለተኛ ሆና በማጠናቀቅ የመጀመሪያውን የሜዳልያ ድል ለሀገሯ አስገኝታለች፡፡ ከሁለት ዓመተ በፊት በለንደን ሻምፒዮን የሆነችው አልማዝ አያና ክብሯን ለማስጠበቅ በውድድሩ ላይ መገኘት ባልቻለችበት በዚህ ውድድር ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድ አትሌት ሲፋን ሀሳን የወቅቱ የዓለማችን ፈጣን በሆነ 30:17.62 ሰዓት የወርቅ ሜዳልያውን ወስዳለች፡፡ ዘንድሮ የኢትዮጵያ ሻምፒዮን የሆነችበት ጨምሮ በርቀቱ ሶስተኛ የውድድር ተሳትፎዋን ያደረገችው ኢትዮጵያዊቷ ለተሰንበት ግደይ የራሷን ምርጥ ሰዓት ባሻሻለችበት 30:21.23 ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳያ አሸናፊ ስትሆን ኬንያዊቷ አንገስ ቲሮፕ የራሷ ምርጥ በሆነ 30:25.20 ሰዓት የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊ ሆናለች፡፡ በፉክክሩ ተጠባቂ ከነበሩት አትሌቶች አንዷ የነበረችው ኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪ የራሷ ምርጥ በሆነ 30:35.82 አምስተኛ ሆና ስታጠናቅቅ ኢትዮጵያዊቷ ሰንበሬ ተፈሪ የዓመቱ የግሏ ምርጥ በሆነ 30:44.23 ስድስተኛ ሆና ጨርሳለች፡፡ ሶስተኛዋ የኢትዮጵያ ተወካይ ነፃነት ጉደታ በእግር ሕመም ምክንያት ውድድሩን አቋርጣ ለመውጣት ተገዳለች፡፡

ለተሰንበት ግደይ የሴቶች 10 ሺኅ ሜትር የብር ሜዳልያ አሸናፊ Photo: ‘© Getty Images for IAAF’

ለተሰንበት ከድሏ በኋላ በሰጠችን አስተያየት ‹‹ከዚህ ቀደም በብዛት የምታወቀው በ5000 ሜትር ተወዳዳሪነት የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ በ10 ሺህ ሜትርም መወዳደር ጀምሬያለሁ፡፡ ለዚህ ውድድር ከአሰልጣኜ ጋር በመቀሌ ከተማ ስዘጋጅ የቆየሁ ሲሆን የዝግጅታችን ግብ የነበረውም በሜዳልያ ደረጃ ውስጥ ገብቶ ማጠናቀቅ ነበር፡፡ ከውድድሩ በፊት አሸናፊ ስለመሆንም አስቤ የነበረ ቢሆንም በዓለም ሻምፒዮና ውድድር ላይ ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቅም ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ባገኘሁት የብር ሜዳልያ ድል በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ከቡድን አጋሮቼ ጋር ተጋግዘን ለመስራት እቅድ ነበረን፡፡ ልንተገብረውም ሞክረናል፡፡ ሆኖም በመጨረሻ እኔ ወደፊት ስወጣ ተከታትለን ለመሄድ አልቻልንም፡፡ ከኔ የተሻለ አጨራረስ የነበራት ሲፋን አሸንፋለች፡፡ በቀጣይ በኦሊምፒክ ውድድር ላይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ልምምዴን ጠንክሬ መስራቴን እቀጥላለሁ፡፡›› ብላለች፡

በዶሀ የ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያለፉት ሁለት ቀናት የውድድር ውሎዎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የማጣሪያና ፍፃሜ ውድድሮች ላይም ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በመጀመሪያው ቀን በሴቶች 800 ሜትር በስድስት ምድብ ተከፍሎ በተካሄደው የማጣሪያ ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበረችው ድርቤ ወልተጂ ከምድብ አምስት በ2፡02.71 አምስተኛ ሆና በማጠናቀቅ በፈጣን ሰዓት ወደ ግማሽ ፍፃሜው ማለፍ ችላ የነበረ ሲሆን በሁለተኛው ቀን በተካሄደው የግማሽ ፍፃሜ ፉክክር ከምድብ ሁለት በ2:02.69 ስድስተኛ ወጥታ ለፍፃሜው ማለፍ ሳትችል ቀርታለች፡፡        

በመክፈቻው ዕለት በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል ሶስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን በምድብ አንድ የሮጠችው መቅደስ አበበ ከኡጋንዳዊቷ ፔሩዝ ቼሙታይ (9:21.98)፣ የወቅቱ የዓለም ሻምፒዮን አሜሪካዊቷ ኤማ ኮበርን (9:23.40) እና ኬንያዊቷ ሴልፊኔ ቼስፖል (9:24.22) በመቀጠል የራሷ ምርጥ በሆነ 9:27.61 አራተኛ ሆና በማጠናቀቅ በፈጣን ሰዓት ሰኞ ምሽት ለሚደረገው የፍፃሜ ውድድር አልፋለች፡፡ በምድብ ሁለት የሮጠችው ሎሚ ሙለታ በ9:49.28 አስረኛ እንዲሁም በምድብ ሶስት የተሳተፈችው ዘርፌ ወንድማገኝ ሰባተኛ በመሆን ለፍፃሜው ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በመጀመሪያው ቀን ምሽት የተወዳደሩበት ሌላኛው የማጣሪያ ፉክክር በወንዶች 5000 ሜትር ሲሆን ከቀረቡት አራት አትሌቶች ሶስቱ ለፍፃሜ አልፈዋል፡፡ ያለፈው ውድድር አሸናፊነት ክብሩን ለማስጠበቅ የገባው ሙክታር እድሪስ እና ሰለሞን ባረጋ ከተሳተፉበት ምድብ አንድ ሰለሞን ባረጋ በ13:24.69 አንደኛ ሙክታር እድሪስ የዓመቱ የግል ምርጥ ሰዓቱ በሆነ 13:25.00 ሶስተኛ ወጥተዋል፡፡ በምድብ ሁለት ኢትዮጵያን ወክለው ከተሰለፉት በርቀቱ የዘንድሮው ፈጣን ሰዓት ባለቤት የሆነው ጥላሁን ሀይሌ በ13:20.45 ሁለተኛ በመውጣት ለፍፃሜው ሲያልፍ አስራ አራተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው አባዲ ሀዲስ ማለፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡ የወንዶች 5000 ሜትር የፍፃሜ ውድድር የፊታችን ሰኞ ምሽት የሚደረግ ሲሆን ከማጣሪያው ውድድር በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት ሰለሞን ባረጋ እና ጥላሁን ሀይሌ የወርቅ ሜዳልያ ድሉን ለሀገራቸው ለማስገኘት የሚችሉትን በሙሉ ለማድረግ እንደሚጥሩ ገልፀዋል፡፡

የመክፈቻው ዕለት ብቸኛ የፍፃሜ ውድድር በነበረውና ከዕኩለ ለሊት በኋላ በተካሄደው የሴቶች ማራቶን ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበሩት ሶቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውድድሩን አቋርጠው ወጥተዋል፡፡ በአስቸጋሪው ሞቃታማ አየር ታጅቦ በተካሄደው በዚህ ውድድር ላይ ኬንያዊቷ ሩት ቼፕንጌቲች (2:32:43)፣ የባህሬይኗ ሮዝ ቼሊሞ (2:33:46) እና የናሚቢያዋ ሄላ ጆሀንስ (2:34:15) በቅደም ተከተል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያሉትን ደረጃዎች በመያዝ አሸንፈዋል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ከተሳተፉት ተወዳዳሪዎች 41 ከመቶ የሚሆኑት ውድድሩን ማጠናቀቅ ሳይችሉ የቀሩ ሲሆን ውድድሩን ከጨረሱት ተወዳዳሪዎች መካከል ከ2 ሰዓት ከ40 ደቂቃ በታች ለመጨረስ የበቁትም ሰባት ብቻ ናቸው፡፡ ኬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ቤላሩስ እና ሰሜን ኮሪያ ያቀረቧቸው ሶስቱም አትሌቶች ውድድሩን ያጠናቀቁላቸው አራት ሀገሮች ሆነዋል፡፡        

በመጀመሪው ዕለት በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል የተሳተፈችው መቅደስ ውድድሩን ካጠናቀቀች በኋላ በሚዲያ ሚክስድ ዞን ውስጥ ወደልብስ መቀየሪያ ክፍል ለመሄድ ግራ ተጋብታ ታይታ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የቡድኑ ፕሬስ አታሼ አትሌቶች ውድድር ሲጨርሱ በሚዲያ ሚክስድ ዞኑ አካባቢ በመገኘት አስፈላጊውን እገዛ ሊያደርግ እንደሚገባ በተሰጠው ጥቆማ በሁለተኛው ቀን ከሴቶች 10 ሺህ ሜትር ውድድር በኋላ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሲወጣ መታየቱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

በሶስተኛው ቀን የውድድሩ ውሎ ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት ብቸኛ ውድድር የሴቶች 20 ኪሎ ሜትር እርምጃ ፍፃሜ ሲሆን ከእኩለ ለሊት በኋላ በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ የኋልዬ በለጠው በብቸኝነት ኢትዮጵያን የምትወክል ይሆናል፡፡ የዚህ ውድድር መጀመሪያ ሰዓት ቀደም ሲል ከምሽቱ 5፡30 ላይ እንደሚሆን ተገልፆ የነበረ ቢሆንም ዘግይቶ በደረገ የሰዓት ለውጥ ከምሽቱ 5፡59 ላይ እንደሚጀምር ታውቋል፡፡