ለተሰንበት ግደይ በካሊፎርኒያ የአፍሪካ እና የኢትዮጵያን የሴቶች 3000ሜ. ሪኮርድ አሻሻለች

Letesenbet ETH

አልማዝ አያና ለሁለት ዓመት ያህል ወደራቀችው የትራክ ውድድር ተመልሳለች

ትላንት ከሰዓት በስታንፎርድ ካሊፎርኒያ በተካሄደው የዩጂን ዳይመንድ ሊግ ኢትዮጵያዊቷ ለተሰንበት ግደይ በሴቶች 3000ሜ. የአፍሪካ እና የኢትዮጵያን ሪኮርድ ለማሻሻል በቅታለች፡፡ ‹‹ፕሪፎንቴይን ክላሲክ›› በሚል ስያሜ የሚታወቀው የዩጂን ዳይመንድ ሊግ ውድድር ዘንድሮ የቦታ ለውጥ አድርጎ በካሊፎርኒያ ስታንፎርድ የተካሄደ ሲሆን 13 የዳይመንድ ሊግ እንዲሁም 3 የማስታወቂያ ውድድሮችን አስተናግዷል፡፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በስታንፎርድ በሶስት የዳይመንድ ሊግ እና በሁለት የማስታወቂያ ውድድሮች ላይ ተወዳድረዋል፡፡ በውድድሮቹ ላይ ከተሳተፉት ኢትዮጵያውያን አንዳቸውም በአሸናፊነት ለመጨረስ ባይበቁም በሴቶች 3000ሜ. ለተሰንበት ግደይ የአፍሪካና የኢትዮጵያን ሪኮርድ ሰብራለች፡፡

የኦሊምፒክና የዓለም የ10 ሺህ ሜትር ሻምፒዮኗ አልማዝ አያና፣ የ1500ሜ. የዓለም ሪኮርድ ባለቤቷ ገንዘቤ ዲባባ፣ የ5000ሜ. የዓለም ሻምፒዮኗ ሔለን ኦቢሪ፣ የ5000ሜ. የአውሮፓ ሻምፒዮኗ ሲፋን ሀሳን እና ሌሎችም ጠንካራ አትሌቶች የተካተቱበት የሴቶች 3000ሜ. በስታንፎርዱ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ከፍተኛ ተጠባቂነት ነበረው፡፡ ውድድሩ ሊጠናቀቅ 800 ሜትር ሲቀረው ኢትዮጵያውያኑ ገንዘቤ ዲባባ እና ለተሰንበት ግደይ ወደፊት በመውጣት መምራት ቢጀምሩም ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሀሳን እና ጀርመናዊቷ ኮንስታንዜ ክሎስተርሀፈንም በቅርብ ርቀት እየተከተሏቸው ነበር፡፡ በለተሰንበት መሪነት የመጨረሻውን ዙር ሲጀምሩም ገንዘቤ ወደኋላ የቀረች ሲሆን ሲፋን እና ኮንስታንዜ በመሪነቱ ስፍራ ላይ ያለችው ለተሰንበት ላይ ለመድረስ ግስጋሴያቸውን ቀጥለዋል፡፡ 250 ሜትር ሲቀር
ሲፋን ለተሰንበትን አልፋት ስትሄድ ገንዘቤና ጀርመናዊቷ ኮንስታንዜ ለሶስተኛነት እየተፎካከሩ ነበር፡፡ በመጨረሻም ሲፋን በድንቅ አጨራረስ 8፡18.49 በሆነ የአውሮፓ፣ የኔዘርላንድ፣ የዳይመንድ ሊግ እና የውድድር ስፍራው ሪኮርድ እንዲሁም የወቅቱ ፈጣን ሰዓት አሸናፊ ሆናለች፡፡ ጀርመናዊቷ ኮንስታንዜ ክሎስተርሀፈን መጀመሪያ ገንዘቤን በመጨረሻዎቹ ጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ደግሞ ለተሰንበትን በመቅደም 8፡20.07 በሆነ የጀርመን ሪኮርድ እና የራሷ ምርጥ ሰዓት ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ለተሰንበት ግደይ 8፡20.27 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ በመሆን ጨርሳለች፡፡ ለተሰንበት ሶስተኛ የወጣችበት 8፡20.27 የግሏ ምርጥ ሰዓትም ኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪ በሜይ 2014 ዓ.ም. በዶሀ ዳይመንድ ሊግ አስመዝግባው የነበረውን 8:20.68 የሆነ የአፍሪካ ሪኮርድ እንዲሁም አልማዝ አያና በጁን 2015 ዓ.ም. በሞሮኮ ራባት አስመዝግባው የነበረውን 8፡22.22 የሆነ የኢትዮጵያ ሪኮርድ ያሻሻለ ሆኗል፡፡ አራተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ገንዘቤ ዲባባም 8:21.29 በሆነ ግዜ የራሷን ምርጥ ሰዓት አሻሽላለች፡፡ በለተሰንበት የአፍሪካውን ሪኮርድ የተነጠቀችው ኬንያዊቷ ሄለን ኦቢሪ በ8፡27.26 ስድስተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡

3000m Women finishing Photo © Victah Sailer

በሴቶች 3000ሜ. ውድድሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩት ሌሎች ኢትዮጵያውያን ፋንቱ ወርቁ (8፡32.10) ዘጠነኛ፣ ሰንበሬ ተፈሪ (8፡36.26) አስራ አንደኛ፣ ሃዊ ፈይሳ (8፡40.79) አስራ ሶስተኛ፣ አልማዝ አያና (8፡57.16) አስራ ስምንተኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡ በእግር ጉዳት ምክንያት ለረጅም ግዜ ከውድድር እርቃ የቆየችው አልማዝ አያና እ.አ.አ. በወርሀ ኦገስት 2017 ዓ.ም. በለንደን የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ ባለቤት ከሆነችበት የ5000ሜ. ውድድር በኋላ በስታንፎርድ ለመጀመሪያ ግዜ ወደትራክ ውድድር ተመልሳለች፡፡ በኖቬምበር 2017 ዓ.ም. የመጀመሪያ ተሳትፎዋን አድርጋ ያሸነፈችበት የኒውዴልሂ ግማሽ ማራቶን አልማዝ ከለንደኑ የዓለም ሻምፒዮና በኋላ ያደረገችው ብቸኛ የጎዳና ላይ ውድድር ነበር፡፡

በስታንፎርድ የዩጂን ዳየመንድ ሊግ የነጥብ ፉክክሩ አካል በነበረው የሴቶች 800ሜ. ውድድር ደቡብ አፍሪካዊቷ ካስተር ሴሜንያ 1፡55.70 በሆነ ሰዓት በርቀቱ 31ኛ ተከታታይ ድሏን አስመዝግባለች፡፡ ሴሜንያ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ስፖርት አስተዳዳሪ አካል ከፆታዊ የቴስቶስቴሮን ሌቭል ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያወጣው አዲስ ህግ እንዳይተገበር በፍርድ ቤት ክርክር ላይ ትገኛለች፡፡ ደቡብ አፍሪካዊቷ ከስታንፎርዱ ድሏ በኋላ እየተከራከረችበት ያለው አዲስ ሕግ የሚተገበርና በ800 ሜ. እንዳትወዳደር የምትከለከል ከሆነ በዶሀ የዓለም ሻምፒዮና ላይ በሌላ ርቀት እንደማትካፈል ተናግራለች፡፡ በስታንፎርድ አምስተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያዊቷ ሀብታም አለሙ የገባችበት 1፡59፡25 የዓመቱ ምርጥ ሆኖ ተመዝግቦላታል፡፡ በወንዶች 1 ማይል ኬንያዊው ቲሞቲ ቼሪዮት የወቅቱ ፈጣን በሆነ 3፡50.49 ሲያሸንፍ ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ የተጠበቁት ኢትዮጵያውያኑ ሳሙኤል ተፈራ (3፡53.50) እና ዮሚፍ ቀጄልቻ (3፡58.24) በቅደም ተከተል ስምንተኛ እና አስራ ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡

የዳይመንድ ሊጉ የነጥብ ፉክክር አካል ባልነበሩት ውድድሮች በወንዶች 2 ማይል በኡጋንዳዊው ጆሽዋ ቼፕቴጌ (8፡07.54) እና አሜሪካዊው ፖል ቼሊሞ (8፡07.59) የተቀደመው ሰለሞን ባረጋ በ8፡08.69 ሶስተኛ ሆኖ ጨርሷል፡፡ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ጌታነህ ሞላ በ8፡18.88 ስምንተኛ ወጥቷል፡፡ ሶስት ኢትዮጵያውያን የፉክክሩ አካል በነበሩበት የሴቶች 1500 ሜ. ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፒዬጎን (3፡59.04)፣ እንግሊዛዊቷ ላውራ ሙሪ (3፡59.47) እና አሜሪካዊቷ ሼልቢ ሁሊሀን (3፡59.64) ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ሲወጡ ጉዳፍ ፀጋዬ በ3፡59.85 አራተኛ ሆና ጨርሳለች፡፡ ለምለም ሀይሉ (4፡06.61) ዘጠነኛ እንዲሁም አክሱማዊት እምባዬ (4፡14.47) አስራ ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡

የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ዳይመንድ ሊግ ስምንተኛ ውድድር የፊታችን ዓርብ በሲውዘርላንድ ሎዛን ከተማ ሲቀጥል ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሴቶች 800ሜ.፣ በወንዶች 1500ሜ. እና 5000ሜ. የሚወዳደሩ ይሆናል፡፡