ለሴት እህቶቻችን አስፈላጊ የሆኑ 10 ቫይታሚኖች

vitamin ddd

Women-Vitamins-opt

(በዳንኤል አማረ ደሴ ©ኢትዮጤና)

ለበለጠ የጤና መረጃ ይህን ገጽ ላይክ ያድርጉ www.facebook.com/EthioTena

በአሁኑ ጊዜ ሴቶች ለጤናቸው የሚጨነቁና ጤናማ የሆነ የአመጋገብ ሥርዓት የሚከተሉ ሁነዋል፡፡ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት አንዱ አስፈላጊ የሆኑ የቫይታሚን ውህዶችን የምናገኝበት መንገድ ነው፡፡ በማንኛውም የእድሜ ክልል፣ የሰውነት መጠን/ክብደት እና እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ ሴቶች የተሟላ ጤንነት እንዲኖራቸውና የተለያዩ የጤና ችግሮችን መከላከል እንዲችሉ በርከት ያሉ የተለያየ ይዘት ያላቸውን ቫይታሚኖች መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡

ቫይታሚኖች ተፈጥሮአዊ ውህዶች ሲሆኑ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻችን ተግባራቸውን በትክክል እንዲወጡ ያግዛሉ/ይረዳሉ፡፡ እያንዳንዳቸው ቫይታሚኖች የራሳቸው የሆነ ልዩ ጥቅም አላቸው፡፡ አስፈላጊ የሆነ የቫይታሚን እጥረት ከባድ ለሆነ በሽታ መከሰት የራሳቸውን ድርሻ ያበረክታሉ፡፡ ለዚህም ነው አስፈላጊ የሆኑ ቫይታሚኖችን ከምንመገበው ምግብ ወይም ከቫይታሚን እንክብሎች ማግኘት አስፈላጊ የሚሆነው፡፡

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ለሴቶች አስፈላጊ የሆኑ የመጀመሪያዎቹ 10 ቫይታሚኖች ናቸው ቢጠቀሟቸው ያተርፋሉ፦

1.ቫይታሚን ኤ (Vitamin A)

ቫይታሚን ኤ የፀረ-ኦክሲዳንት ባህሪ ሲኖረው በማንኛውም የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሴቶች ያስፈልጋቸዋል ይህ ቫይታሚን አጥንት፣ ጥርስ፣ ቆዳ፣ ስስ አካሎችን በመገንባትና ጥንካሬ በመስጠት ይጠቅማል፡፡ በተጨማሪም ቫይታሚን ኤ በከባድ ህመም የመያዝ እድልን ይቀንሳል፣ እይታን ይጨምራል፣ እርጅናን ይቀንሳል እንዲሁም በሽታ የመከላከል አቅምን ይጨምራል፡፡

ካሮት፣ ቲማቲም፣ ብሮኮሊ፣ ፓፓያ፣ ስቲናች፣ እንቁላል፣ ጉበት እና ወተት በቫይታሚን ኤ የበለፀጉ ምግቦች ናቸው፡፡

 1. ቫይታሚን ቢ2 (Vitamin B2)

ሪቦፍላቪን (Rivofavine) በመባል ይታወቃል፤ ቫይታሚን ቢ2 ለጥሩ ጤንነት፣ እንከን ለሌለው ዕድገትና ሰውነታችን ምግብን በአግባቡ እንዲጠቀም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ሃይል/ጉልበት እንድናገኝ እና በሽታ የመከላከል ሥርዓታችን እንዲጨምር ያግዛል በተቃራኒው ድንዛዜን፣ ብስጭትን፣ ጭንቀትንና ድካምን ይቀንሳል/ያስወግዳል፡፡

የቫይታሚን ቢ2 እጥረት ሰውነታችን ምግብን በአግባቡ እንዳይጠቀም ያስተጓጉላል፣ በሽታ የመከላከልና የነርቭ ሥርዓትን በማዛባት ዓይንና ምላሳችን አመድማ ቀለም እንዲሆን፣ ጉሮሮ እና አፍ እንዲቆስል፣ ከንፈራችን እንዲሰነጣጠቅ፣ ፀጉራችን እንዲደርቅ፣ የሚያሳክክና የተሰነጠቀ ቆዳ እንዲኖረን ያደርጋል፡፡

በቫይታሚን ቢ2 የበለፀጉ ምግቦች የሚከተሉት ናቸው፦ የአካል ስጋ፣ አይብ፣ ወተት፣ እርጎ፣ ቅጠላማ አትክልቶች፣ እንቁላል፣ ጥራጥሬዎች፣ አኩሪ አተር፣ አልሞንድና ለውዝ ናቸው፡፡

 1. ቫይታሚን ቢ6 (Vitamin B6)

ቫይታሚን ቢ6 ፓይሪዶክሲን (Pyridoxine) በመባል ይታወቃል ለጤናማ በሽታን የመከላከል አቅም ሥርዓት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ቫይታሚን ሰውነታችን ሆርሞንና የአእምሮ ኬሚካሎችን እንዲያመርት በማገዝ በተቃራኒ ድብርት፣ የልብ ህመም እና የመርሳት ችግር እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡

በተጨማሪም የደም ስኳር መጠን የተስተካከለ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ነፍሰጡር/እርጉዝ ሴቶች በቫይታሚን ቢ6 የበለፀጉ ምግቦች ቢመገቡ ጠዋት ጠዋት ከማቅለሽለሽና ህመም ተገላገሉ ማለት ነው፡፡ በሰውነታችን ውስጥ የቫይታሚን ቢ6 እጥረት የደም ማነስ ያስከትላል፡፡

ጥቂት ጥሩ ከሚባሉት ምግቦች ውስጥ ጤናማ የቫይታሚን ቢ6 መጠን ያላቸው የሚከተሉት ናቸው፦ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ስጋ፣ ባቄላ፣ አሳ፣ ለውዝና የደረቁ ፍራፍሬዎች ናቸው፡፡

 1. ቫይታሚን ቢ7 (Vitamin B7)

ቫይታሚን ቢ7 በሌላ ስሙ ባዮቲን(Biotin) ይባላል፡፡ ለሴሎች እድገትና ለፋቲ አሲድ ስሪት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ቫይታሚን ላብ አመንጪ እጢዎች፣ ፀጉርና ቆዳ ጤናማ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ የፀጉር እድገትን ያፋጥናል የተሰነጣጠቁ ጥፍሮችን ለማከም ይረዳል፡፡ በተጨማሪም ቫይታሚን ቢ7 ለአጥንት ዕድገትና ለመቅኒ በጣም አስፈላጊ ነው፤ እንዲሁም የኮሌስትሮል መጠን የተስተካከለ እንዲሆን ይረዳል፡፡

የቫይታሚን ቢ7 እጥረት የመከሰት እድሉ በጣም አናሳ ቢሆንም በሚከሰትበት ጊዜ ግን የፀጉር መሰባበር፣ ሽፍታ፣ ጤናማ ያልሆነ የልብ ስራ፣ የደም ማነስ እና በጥቂቱ ድብርት ያስከትላል፡፡

ጥሩ ከሚባሉ የቫይታሚን ቢ7 ምግብ ምርጫዎች መካከል ጥቂቶቹ እነሆ፦ ስኳር ድንች፣ አልሞንድ፣ ካሮት፣ ሙዝ፣ ቢጫ ፍራፍሬዎች፣ አረንጓዴ ቅጠላማ አትክልቶች፣ ቡናማ ሩዝ፣ የእንቁላል አስኳል፣ አኩሪ አተር፣ ወተት፣ አይብ፣ እርጎና ለውዝ ናቸው፡፡

 1. ቫይታሚን ቢ9 (Vitamin B9)

ቫይታሚን ቢ9 ፎሊክ አሲድ(Folic Acid) በመባል ይታወቃል ለማንኛውም ሴቶች በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የልብ ህመምን፣ ከፍተኛ የደም ግፊትን፣ አልዛይመርን፣ ድብርትን፣ ካንሰርንና የማስታወስ ችግርን በመከላከል ይረዳል፡፡ በተጨማሪም የአእምሮ ጤናን፣ ሴሎች ተግባራቸውን በትክክል እንዲወጡ ያግዛቸዋል/ያበረታታቸዋል፡፡ መካንነትን ይዋጋል በእርግዝና ጊዜ ደግሞ ለጽንሱ እድገት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

የቫይታሚን ቢ9 እጥረት በእርጉዝ ሴቶች ላይ ሲከሰት ጽንሱ ላይ የአእምሮ ችግር ያስከትላል፡፡ በቫይታሚን ቢ9 ከበለፀጉ ምግቦች መካከል ሊጠቀሱ የሚችሉት፦ ጠቆር ያለ ቅጠል ያላቸው አረንጓዴ አትክልቶች፣ የብርቱካን ጭማቂ፣ አስፓርጀስ፣ ሚሎንስ፣ እንጆሪ፣ አተር፣ ይስትና እንቁላል ናቸው፡፡

 1. ቫይታሚን ቢ12 (Vitamin B12)

ሌላው ለሁሉም ሴቶች አስፈላጊ የሆነ ቫይታሚን ቢ12 ነው፡፡ ሰውነታችን ምግብ በአግባቡ እንዲጠቀም፣ ለጤናማ የሴል ክፍፍል እና ፕሮቲን እንዲሰራ/እንዲዘጋጅ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ቫይታሚን የልብ ህመምን፣ የመርሳት ችግርን እና የደም ማነስን ይከላከላል፡፡ በተጨማሪም ድብርትን ለማከም፣ ጤናማ የበርቭ ሥርዓት እና አእምሮ ተግባሩን በትክክል እንዲወጣ በማገዝ ይረዱናል፡፡ የቫይታሚን ቢ12 እጥረት የሚከተሉትን ያስከትላል፦ ቶሎ መቆጣት፣ ድብርትና ግርታ/ውዝግብ ያመጣሉ በተጨማሪም የምላስና አፍ ቁስለት ያስከትላል፡፡

የቫይታሚን ቢ12 ጥሩ ምንጭ ከሆኑ ምግቦች መካከል፦ አይብ፣ እንቁላል፣ አሳ፣ ስጋ፣ ወተት፣ እርጎ እና ለቁርስ የሚሆኑ የጥራጥሬ እህሎች ናቸው፡፡

 1. ቫይታሚን ሲ (Vitamin C)

በሽታ የመከላከል አቅምን የሚጨምር በመባል ይታወቃል፡፡ ቫይታሚን ሲ ለሴቶች በጣም በርካታ የሆኑ ጥቅሞች ይሰጣል፦ ቁስል በፍጥነት እንዲድን ይረዳል፣ የአካል ዕድገትን ያፋጥናል፣ በአንዳንድ የካንሰር ዓይነቶች የመያዝ ዕድልን ይቀንሳል፣ የአካል ውድመትና የልብ በሽታን ይከላከላል፡፡ በተጨማሪም ቀይ የደም ሴሎች እንዲመረቱ በማድረግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

በቫይታሚን ሲ ይዘታቸው ከበለፀጉ ምግቦች መካከል፦ ብርኮሊ፣ ወይን፣ ኪዊ፣ ብርቱካን፣ ፒፐርስ፣ ድንች፣ ስትሮቤሪ(እንጆሪ)፣ ቲማቲምና ስፕራውትስ ናቸው፡፡

 1. ቫይታሚን ዲ (Vitamin D)

ቫይታሚን ዲ በፋት የሚሟሟ ቫይታሚን ሲሆን ካልሲየም የተባለው ሚኒራል እንዲመጠጥ/እንዲዋሃድ ያግዛል ይህ ካልሲየም የተባለው ሚኒራል አጥንታችን ጠንካራ እንዲሆን ከፍተኛ ድርሻ ይወጣል፡፡ ቫይታሚን ዲ ሪህና የተለያዩ አይነት ካንሰሮችን የመያዝ ዕድላችንን ይቀንሳል፡፡ በተጨማሪም በወር አበባ ጊዜ የሚከሰቱ የተለያዩ ህመሞችና ችግሮችን ይቀንሳል፣ የአይን እይታን ያስተካክላል፡፡ የዚህ ቫይታሚን እጥረት አጥንታችን ጠንካራ እንዳይሆን በማድረግ ኦስቲዮፖሮሲስ ለተባለ ችግር ያጋልጠናል፡፡

የፀሃይ ብርሃን በየቀኑ ለአጭር ጊዜ በመሞቅ(በመጋለጥ) ሰውነታችን የሚፈልገውን የቫይታሚን ዲ መጠን ያገኛል፡፡ ስስ ቆዳ ላላቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች ከ10-15 ደቂቃ የፀሃይ ብርሃን ቢያገኙ አስፈላጊ የሆነ የቫይታሚን ዲ ለሰውነታችን በበቂ ሁኔታ እናገኛለን፡፡ በተጨማሪም እንደ አሳ(ፋቲ)፣ ወተት፣ ጉበትና እንቁላል የመሳሰሉ በቫይታሚን ዲ የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ ተገቢ ነው፡፡

 

 1. ቫይታሚን ኢ (Vitamin E)

ቫይታሚን ኢ ፀረ-እርጅና ባህሪ ስላለው የሴሎች ውድመትን/ሞትን ይከላከላል፣ ከእድሜ ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሰውነት ላይ የሚከሰቱ ለውጦችን ይከላከላል፡፡ ይህ ቫይታሚን የልብ በሽታን፣ ካታራክትን(የአይን በሽታ)፣ የማስታወስ ችግርን እና ጥቂት የካንሰር ዓይነቶችን ይከላከላል፡፡

ቫይታሚን ኢ ለቆዳና ፀጉር በጣም አስፈላጊ ነው ለዚህም ነው በፀጉርና ቆዳ ውበት መጠበቂያ ምርቶች ላይ የሚካተተው፡፡ በቫይታሚን ኢ ከበለፀጉ ምግቦች መካከል፦ የመካከለኛው የስንዴ ፍሬ ክፍል፣ የለውዝ ችግኝ/ዛፍ፣ አልሞንድ፣ ስፒናች፣ ማርጋሪን፣ የበቆሎ ዘይት፣ የለውዝ ቅቤ ናቸው፡፡

 1. ቫይታሚን ኬ (Vitamin k)

ቫይታሚን ኬ የአጥንት ጥንካሬ በመጨመር፣ የደም መርጊያ ጊዜ ጤናማ እንዲሆን በማድረግ፣ ለተለያዩ የልብ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድልን በመቀነስ ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ ይህ የተለየ ቫይታሚን ሰውነታችን ሃይል በማምረትና በሽታ የመከላከል ተግባሩን በትክክል እንዲወጣ በማድረግ ይጠቅመናል፡፡

ምርጥ የሚባሉ የቫይታሚን ኬ ምንጭ ከሆኑት ምግቦች መካከል አጠቃላይ የጥራጥሬ ውጤቶች፣ አረንጓዴ ቅጠል ያላቸው አትክልቶች፣ የአሳ ዘይትና ሶይቢን ዘይት ናቸው፡፡

ለማጠቃለል ያክል አምስት(5) የሚሆኑ የተለያዩ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች በየቀኑ ቢመገቡ አስፈላጊ የሚባሉ ቫይታሚኖችን ለማግኘት ቀላል መንገድ ነው፡፡ ከተለያዩ የምግብ ዓይነቶች አስፈላጊ የሆነውን የቫይታሚን መጠን የማያገኙ ከሆነ ሃኪምዎን ወይም የጤና ባለሙያ በማማከር በእንክብል የተዘጋጁ ቫይታሚኖችን ቢወስዱ መልካም ነው፡፡

መልካም ጤንነት!!

ለበለጠ የጤና መረጃ ይህን ገጽ ላይክ ያድርጉ www.facebook.com/EthioTena

8 thoughts on “ለሴት እህቶቻችን አስፈላጊ የሆኑ 10 ቫይታሚኖች

 1. መልካም ዜጋን ለማፍራት በምታደርጉት ጥረት ከልብ እናመሰግናለን….ፈጣሪ ይባርካችሁ!!!

 2. በጣም ኣሪፍ መረጃ ነው ቀጥሉበት ከ ማህፀን ፣ የማህፀን ኢንፌክሽን እና ከመሃንነት ጋር የተዛመዱ መረጃዎችም ብትሰጡን በጣም ደስ ይለናል

Leave a Reply

Your email address will not be published.