ሀጎስ እና ዮሚፍ ከሞ ፋራህ፤ መሐመድ አማን ከሩዲሻና አሞስ የሚፎካከሩበት የ2015 ዳይመንድ ሊግ ዘጠነኛ መዳረሻ – ሎዛን

IDL_Lausanne_CloseUp~2

IDL_Lausanne_CloseUp~2የሎዛን አትሌቲስማ ሚቲንግ 40ኛ ዓመቱን በሚያከብርበት የዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይ በለንደን ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ የሆኑ አስር አትሌቶች እንዲሁም ሰባት የዓለም ሻምፒዮኖች የሚሳተፉ ሲሆን ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በወንዶች 800ሜ. እና 5000ሜ.፤ በሴቶች 1500ሜ. እና 3000ሜ. መሰናክል ይወዳደራሉ፡፡ የዳይመንድ ሊጉ የነጥብ ፉክክር አካል ባልሆነው የወንዶች 100ሜ. (ጀስቲን ጋትሊን፣ አሳፋ ፓወል እና ታይሰን ጌይ)፣ በዳይመንድ ሊጉ የወንዶች 800ሜ. (መሐመድ አማን፣ ዴቪድ ሩዲሻ እና ኒጄል አሞስ)፣ በወንዶች 5000ሜ. (ሀጎስ ገ/ህይወት፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ እና ሞ ፋራህ)፣ በወንዶች ስሉስ ዝላይ (ፓብሎ ፒቻርዶ እና ክርስቲያን ቴይለር) ጠንካራ ፉክክሮች እንደሚያሳዩ የሚጠበቅ ሲሆን በቅርቡ ባደረጓቸው ውድድሮች ያልተጠበቀ ሽንፈትን ያስተናገዱት በወንዶች ምርኩዝ ዝላይ ሬኖ ላቪለኒዬ፣ በሴቶች 400ሜ. ሳኒያ ሪቻርድስ እና በሴቶች 100ሜ. መሰናክል ጃስሚን ስቶወርስ አይነት አትሌቶችም ወደአሸናፊነታቸው ለመመለስ ብርቱ ትግል የሚያደርጉ ይሆናል፡፡
የዓለም ሻምፒዮኑ መሐመድ አማን፣ የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑ ዴቪድ ሩዲሻ እና የኮመንዌልዝ ሻምፒዮኑ ኒጄል አሞስ አንድ ላይ የሚሮጡበት የወንዶች 800ሜ. ሶስቱም አትሌቶች በዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ ተሳትፏቸው ሁለተኛ ድላቸውን ስለማስመዝገብ የሚያልሙበት ሲሆን መሐመድ አማን እና ዴቪድ ሩዲሻ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ግዜ የሚገናኙበት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው መሐመድ አማን በሮም ዳይመንድ ሊግ ያሸነፈበት 1፡43.56 የ2015 ፈጣኑ ሰዓት ሲሆን ከሱ ቀጥሎ የተቀመጠውን ሰዓት ያስመዘገበው ከረጅም ግዜ ጉዳት መልስ በኒው ዮርክ 1፡43.58 በሆነ ሰዓት ማሸነፍ የቻለው ኬንያዊው ሩዲሻ ነው፡፡ በሮም መሐመድ አማንን ተከትሎ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ቦትስዋናዊው ኒጄል አሞስም 1፡43.80 የሆነ ፈጣን ሰዓት አስመዝግቧል፡፡
ከበርሚንግሀም ተሳትፎው በመጨረሻ ሰዓት ራሱን ካገለለ በኋላ ዳግም ወደ መም (ትራክ) ውድድር የሚመለሰው ሞ ፋራህ በዶሀ ድል ከነሳው ሀጎስ ገብረሕይወት እና በሮም የዓመቱን ፈጣን ሰዓት (12:58.39) ካስመዘገበው ዮሚፍ ቀጄልቻ ጋር የሚፋጠጥበት የወንዶች 5000ሜ. ኢትዮጵያውያኑ ሙክታር እድሪስ፣ ኢማነ መርጋ፣ የኔው አላምረው፣ ያሲን ሀጂ እና ጌታነህ ታምሬም ተፎካካሪ የሚሆኑበት ሌላኛው ተጠባቂ ውድድር ሲሆን በኬንያ በኩል የዳይመንድ ሊጉን የነጥብ ፉክክር ከሀጎስ እኩል አምስት ነጥብ በመያዝ እየመራ የሚገኘው ቶማስ ሉንጎሲዋ እና ጉልበቱ ላይ ከተደረገለት ቀዶ ጥገና አገግሞ የተመለሰው ካሌብ ንዲኩ ይጠበቃሉ፡፡
በሴቶች 3000ሜ. መሰናክል የነጥብ መሪነቱን የያዘችው ኬንያዊቷ ቨርጂና ኒያምቡራ ከሀገሯ ልጅ ሊዲያ ቼፕኩሪ እና ካለፈው ዓመት የዳይመንድ ሊጉ የአጠቃላይ አሸናፊ ኢትዮጵያዊቷ ሕይወት አያሌው እንዲሁም በቅርቡ የአሜሪካን ብሔራዊ ሻምፒዮን ከሆነችው ኤማ ኮበርን ጋር ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ የሚጠበቅ ሲሆን ብርቱካን ፈንቴ፣ እቴነሽ ዲሮ እና ብዙአየሁ መሐመድ በዚህ ውድድር ላይ የሚካፈሉ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ የሴቶች 1500ሜ. ሮም ላይ በተቀራረቢ ሁኔታ ውድድራቸውን ያጠናቀቁት ሶስት አትሌቶች – አሜሪካዊቷ ጄኒፈር ሲምፐሰን፣ ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሀሳን እና ኢትዮጵያዊቷ ዳዊት ስዩም – በድጋሚ የሚገናኙበት ሲሆን የውድድር ስፍራው ሪኮርድ የሆነው 3፡58.60 ሊሻሻል የሚችልበት ፉክክር ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ስዊድናዊት አበባ አረጋዊ፣ ኢትዮጵያውያኑ ጉዳፍ ፀጋዬ እና ሰንበሬ ተፈሪም ሌላኛዎቹ ጠንካራ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
በወንዶች 100ሜ. ጋትሊን፣ ፓወል እና ጌይ በሚያደርጉት ፉክክር የውድድር ስፍራው ሪኮርድ የሆነውን 9.69 ያሻሽላሉ ተብሎ ባይጠበቅም ፈጣን ሰዓት እንደሚመዘገብ ይገመታል፡፡ በወንዶች ምርኩዝ ዝላይ ባለፈው ዕሁድ በሀገሩና በገዛ ደጋፊው ፊት ያልተጠበቀ ሽንፈትን የቀመሰው ያለፈው ዓመት የዓለም ምርጡ ወንድ አትሌት ሬኖ ላቪለኒዬ በፍጥነት ወደአሸናፊነቱ ሊመለስ ይችል ይሆን ከሚለው ጥያቄ በዘለለ ፓሪስ ላይ ድል ከነሳው ግሪካዊው ጥምር የነጥብ መሪ  ፊሊፒዲስ ጋር የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል፡፡ በስሉስ ዝላይ ኩባዊው ፓብሎ ፒቻርዶ እና አሜሪካዊው ክርስቲያን ቴይለር ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ሲጠበቅ ኬንያዊው ጦር ወርዋሪ ጁሊየስ ዬጎ ዋነኛ ተፎካካሪ ሆኖ እየታየ ባለበት የወንዶች ጦር ውርወራ ላይም እርሱን ጨምሮ የወቅቱ ምርጥ ወርዋሪዎች – ቪቴስላቭ ቬስሌይ (ቼክ ሪፐብሊክ) እና ቴሮ ፒትካማኪ (ፊንላንድ) – ይወዳደራሉ፡፡ አሜሪካውያኑ አሊሰን ፌሊክስ እና ጄኔባ ታርሞህ ተጠባቂ በሆኑበት የሴቶች 200ሜ. ናይጄሪያዊቷ ብለሲንግ ኦካግባሬ እና የኮትዲቯሯ አሆሬም ቀላል ተፎካካሪ እንደማይሆኑ ይታመናል፡፡

የሎዛን ዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ፕሮግራም (ሰዓት በኢትዮጵያ አቆጣጠር)
1፡00 የሴቶች ዲስከስ
1፡40 የሴቶች ርዝመት ዝላይ
1፡50 የወንዶች አሎሎ ውርወራ
2፡15 የሴቶች ከፍታ ዝላይ
2፡50 የወንዶች ምርኩዝ ዝላይ
3፡03 400ሜ. ሴቶች መሰናክል
3፡10 3000ሜ. ሴቶች መሰናክል
3፡20 የወንዶች ስሉስ ዝላይ
3፡26 200ሜ. ወንዶች
3፡43 100ሜ. ሴቶች መሰናክል
3፡45 የወንዶች ጦር ውርወራ
3፡52 200ሜ. ሴቶች
4፡01 5000ሜ. ወንዶች
4፡26 1500ሜ. ሴቶች
4፡35 400ሜ. ወንዶች መሰናክል
4፡44 800ሜ. ወንዶች
¬ የውድድሩ የቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት የሚጀምር ሲሆን በዲኤስ ቲቪ ሱፐር ስፖርት 4 ላይ ይታያል

Leave a Reply

Your email address will not be published.