Connect with us

Uncategorized

የዳኝነት ውዝግብ፣ ኩንጉፉ… ያሳየው ፍልሚያ በደደቢት አሸናፊነት ተጠናቋል

Published

on

Buna Dedebit

Buna Dedebit

የዳኝነት ውዝግብ፣ ኩንጉፉ… ያሳየው ፍልሚያ በደደቢት አሸናፊነት ተጠናቋል  

ደደቢት በ2000ቹ መጀመሪያ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ከተቀላቀለ ጀምሮ ለሊጉ ዋንጫ ተፎካካሪ ከመሆኑ፣ በአፍሪካ ውድድሮች ላይም በተደጋጋሚ መሳታፍ ከመቻሉ እና አንዴም ፕሪምየር ሊጉን ከማሸነፉ ባሻገር በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቁ ጨዋታዎችን ቁጥር ጨምሯል፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ታላቁ የሸገር ደርቢ ፍልሚያ በተጨማሪ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት ጨዋታዎችም በስታዲየም መቀመጫ የሚታጣባቸው፣ በውጥረት የሚሞሉ እና ካለፉም በኋላ የሚታወሱ ሆነዋል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት ያለፉት ዓመታት ጨዋታዎች ሁሉም ባይሆኑም እንኳን አብዛኞቹ የአጋጣሚ ሆኖ በወሳኝ ጊዜ የሚደረጉ፣ ውጥረት የተሞላባቸው፣ በርካታ የዳኝነት እና ሌሎች ውዝግቦችን የሚያስተናግዱ፣ በርካታ ጎሎች የሚቆጠሩባቸው፣ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ማራኪ እና ትኩረት የሚስቡ ነበሩ፡፡ አሁን በ2008 ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ሲገናኙ ውድድሩ ገና እየተሟሟቀ እንደመሆኑ እና ቡድኖቹም ከሞላ ጎደል በስብስብም ሆነ በአሰልጣኞች ረገድ አዲስ እንደመሆናቸው ከላይ የተጠቀሱት አይነት ክስተቶች እምብዛም አልተጠበቁም ነበር፡፡ ነገር ግን በአዲስ አበባ ስታዲየም የተመለከትነው ጨዋታ ይህን ግምት ያፈረሱ በርካታ አነጋጋሪ ክስተቶችን የያዘ፣ ምናልባትም ለቀጣይ ጥቂት ዓመታት ከትውስታ የማይጠፋ ፍልሚያ ሆኖ አልፏል፡፡ ጨዋታው አነጋጋሪዎቹን ክስተቶች ከማስተናገዱ አስቀድሞ ቡድኖቹ የሚከተሉትን አሰላለፎች ይዘው ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡

ደደቢት (4-4-2 የሚመስል)

ግብ ጠባቂ፡- ታሪክ ጌትነት

ተከላካዮች፡- ስዩም ተስፋዬ፣ አክሊሉ አየነው፣ ምኞት ደበበ እና ተካልኝ ደጀኔ

አማካዮች፡- ሽመክት ጉግሳ፣ ያሬድ ዝናቡ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና ብርሀኑ ቦጋለ

አጥቂዎች፡- ዳዊት ፍቃዱ እና ሳሙኤል ሳኑሚ

ኢትዮጵያ ቡና (4-1-4-1 የሚመስል)

ግብ ጠባቂ፡- ወንድወሰን ደርበው

ተከላካዮች፡- አብዱልከሪም መሀመድ፣ ኢኮ ፌቨር፣ ወንድይፍራው ጌታሁን እና አህመድ ረሺድ

አማካዮች፡- ጋቶች ፓኖም፣ መስኡድ መሀመድ፣ ኤልያስ ማሞ፣ ኢያሱ ታምሩ እና ዮሴፍ ደሙዬ

አጥቂ፡- ዊልያም ያቡን

ከጨዋታው የመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ ቡድኖቹ ምን አይነት የጨዋታ አቀራረብ ሊተገብሩ እንደገቡ መረዳት አስቸጋሪ አልነበረም፡፡ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ያሳዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በበርካታ አማካዮቻቸው ታግዘው ይህን ለመድገም ሲሞክሩ በአሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት የሚመሩት ደደቢቶች የኳስ ቁጥጥሩን ለቡናማዎቹ ትተው በሁለቱ ታታሪ አማካዮቻቸው ሽመክት ጉግሳ እና ብርሀኑ ቦጋለ መስመሮቻቸውን መዝጋትን እና በፈጣን መልሶ ማጥቃት በፈጣኖቹ አጥቂዎቻቸው ዳዊት ፍቃዱ እና ሳሙኤል ሳኑሚ መጠቀምን የመረጡ ይመስሉ ነበር፡፡ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ላይም የተመለከትነው ቡድኖቹ በእነዚህ የተቃረኑ አቀራረቦቻቸው የታክቲክ የበላይነቱን ለመውሰድ ሲታገሉ ነበር፡፡ ሁለቱም ግን እምብዛም ስኬታማ አልነበሩም፡፡ ቡናማዎቹ የፈለጉትን ያህል ኳሶችን በትክክል መቀባበል እና ግልፅ የጎል እድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ፣ ሰማያዊዎቹም የፈጣን መልሶ ማጥቃት እድሎችን ለማግኘት አልቻሉም ነበር፡፡ በግማሽ ሰዓት ውስጥ ያየናቸው የጎል ማግባት ሙከራዎችም ጥቂት ነበሩ፡፡ በአምስተኛው ደቂቃ ዮሴፍ ደሙዬ ከግራ መስመር በአየር ላይ አሻግሮ አጭሩ ኢያሱ ታምሩ በሚገባ ሳያገኘው ጭንቅላቱን ጨርፎ የሄደበት፣ በስምንተኛው ደቂቃ ዊልያም ያቡን ከሩቅ መትቶ የወጣበት፣ በ10ኛው ደቂቃ የቡናው ግብ ጠባቂ ወንድወሰን ደርበው ያመለጠው እና ስዩም ተስፋዬ ወደጎል ሞክሮ በተከላካዮች የወጣበት፣ በ21ኛው ደቂቃ ያሬድ ዝናቡ ከ35 ሜትሮች ገደማ መትቶ በአግዳሚው ላይ የወጣበት ቅጣት ምት እና በ30ኛው ደቂቃ አህመድ ረሺድ ከርቀት ወደጎል መትቶ በደደቢት ተከላካይ ተጨርፎ የወጣበት ሙከራዎች ብቻ ይጠቀሳሉ፡፡ 30ቹ ደቂቃዎች ብዙ ባያሳዩንም የመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ላይ ግን ጨዋታውን የገለባበጡ ክስተቶች ተፈጥረዋል፡፡ በ33ኛው ደቂቃ ደደቢቶች በመሀል ተከላካዩ ምኞት ደበበ እና ሳሙኤል ሳኑሚ ቅብብል በርካታ የቡና ተጨዋቾችን ቀንሰው ከሄዱ በኋላ አራት ሆነው ከሁለት የቡና ተከላካዮች ፊት ለፊት ቢገናኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ በ35ኛው ደቂቃ ላይ በጡንቻ መሸማቀቅ ጨዋታውን መቀጠል ያልቻለው ዳዊት ፍቃዱ ተቀይሮ ወጥቶ ሄኖክ መኮንን ተክቶታል፡፡ በዚያን ቅፅበት ቅያሬው ለደደቢት ጉዳት እንደሆነ ታስቦ ነበር፡፡ ሀሳቡ ስህተት እንደነበር ለመረዳት ግን አንድ ደቂቃ እንኳን አልወሰደም፡፡ ወጣቱ ሄኖክ ገና ከመግባቱ ከቡናው የመሀል ተከላካይ ኢኮ ፌቨር ስህተት ያገኘውን ኳስ ለሽመክት አቀብሎ፣ ሽመክትም ለሳኑሚ በመሬት አሻግሮለት ናይጄሪያዊው አጥቂ ከግብ ጠባቂው ጋር ቢገናኝም ከእሱ በማይጠበቅ መንገድ ሙከራው ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡ ይሄው ኳስ ግን ለቡናማዎቹ የማጥቃት እድልን ፈጥሮ በረዥሙ ለኢያሱ የተላከለትን ኳስ ከደደቢት ተከላካዮች የጨዋታ ውጪ ወጥመድ አምልጦ የገባው አማካይ በሚገባ ከተቆጣጠረው በኋላ የወጣውን ግብ ጠባቂ ታሪክን አልፎ ገብቶ ወደ ጎል የመታው ኳስ በተከላካዮች ከመስመር ላይ ከተመለሰበት በኋላ እንደገና አግኝቶ ቢመታውም ብርሀኑ ቦጋለ ወድቆ በመመለስ ከመስመር ላይ ጎል እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ የሰማያዊዎቹ አምበል ኳሱን ጎል እንዳይሆን ባደረገበት ጊዜ ግን ኳሱ በእጅ ተነክቷል ብለው የቡና ተጨዋቾች በተለይም ኢያሱ፣ ዮሴፍ እና መስኡድ ዳኛውን ተከትለው ለማነጋገር ሲሞክሩ ደደቢቶች እንደመብረቅ በፈጠነ መልሶ ማጥቃት ወደ ቡና ጎል በማምራት ሳኑሚ ያቀበለውን ኳስ ከሁለት ደቂቃዎች በፊት ተቀይሮ የገባው ሄኖክ ለደደቢት የመሪነት ጎል አስቆጥሯል፡፡ ከጎሉ በኋላ ፍፁም ቅጣት ምት እና ምናልባትም ብርሀኑን በቀይ መውጣት ተከልክለናል ብለው ያመኑት የቡና ተጨዋቾች ዋናውን አርቢትር ለሚ ንጉሴ በመክበብ ብዙ ቢጨቃጨቁም፣ ደጋፊዎችም የተቃውሞ ጩኸቶችን እና ስድቦችን ቢሰነዝሩም ውሳኔውን ማስቀየር አልቻሉም፡፡ ከብዙ ግርግር በኋላ ጨዋታው ሲቀጥል የተከሰተው ደግሞ በአርቢትሩ ውሳኔ እንደተበደሉ የተሰማቸውን እና የተበሳጩትን የቡና ደጋፊዎች የበለጠ ያስደነገጠ፣ ለማመን ያስቸገረ እና ንዴታቸውን ጫፍ ያደረሰ ለገለልተኞች እና ለደደቢት ደጋፊዎችም አስገራሚ የሆነ ሁነት ነበር፡፡ ከደደቢት የግብ ክልል ወደ ቡና የግብ ክልል በአየር ላይ የተላከን ረዥም ኳስ ለማግኘት የደደቢት ተጨዋች እና የቡናው ተከላካይ አህመድ ሲታገሉ ከጎሉ እየሮጠ የወጣው እና በእጁ ኳሱን ለማውጣት ይችል የነበረው የቡናው ግብ ጠባቂ ወንድወሰን ይህን በማድረግ ፈንታ እንደ አየር ኃል ኮማንዶ በአየር ላይ ተወርውሮ በኩንጉፉ ምት የቡድን ጓደኛው አህመድን አንገቱን ወይም ጭንቅላቱን መትቶ ጥሎታል፡፡ በዚህ ግዜ ሽመክት ኳሱን አግኝቶ ግብ ጠባቂ የሌለበት እና አንድ ተከላካይ ብቻ የቆመበት ጎል ላይ በማግባት በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት የደደቢትን መሪነት ወደ 2ለ0 አሳድጓል፡፡ አንጋፋው የቡና ግብ ጠባቂ (ወደሌሎች ክለቦች ሄዶ ዘንድሮ ከመመለሱ በፊት በ2003 ከቡድኑ ጋር ፕሪምየር ሊጉን አሸንፏል) የሰራው ስህተት ፍፁም የማይጠበቅ እና ለማመን የሚቸግር ነበር፡፡ ጭካኔ የተሞላበት ውሳኔው በአህመድ ላይ የከፋ ጉዳት አለማድረሱም እድል እንጂ ሌላ ምክንያት አልነበረውም፡፡ በስህተት አህመድን ባያገኘው ኖሮም እንዳሰበው በደደቢት ተጨዋች ላይ ድርጊቱን ፈፅሞ እሱም ለቀይ ካርድ በተዳረገ ነበር፡፡ እነዚህ ሁለት ሰዎች (አርቢትሩ ለሚ እና ወንድወሰን) ከስታዲየሙ አብዛኛው ክፍል በተቃውሞ፣ ስድብ እና የፕላስቲክ ጠርሙስ ውርወራ ታጅበው ጨዋታው ወደእረፍት አምርቷል፡፡ ግብ ጠባቂው ከስህተቶቹ ባሻገር ለደጋፊዎች ተቃውሞ ምላሽ ለመስጠት መሞከሩ ተቃውሞውን አባሰው እንጂ አላሳነሰውም፡፡ በእረፍት ሰዓት በተለይ የቡና ደጋፊዎች ቡድናቸው ባልተጠበቀ ሁኔታ ለመመራቱ የተለያዩ ወገኖችን ተጠያቂ ሲያደርጉ ይሰሙ ነበር – ብዙዎቹ አርቢትሩን እና ግብ ጠባቂውን ተጠያቂ ሲያደርጉ ጥራት ያለው ስብስብ አላዋቀረም ያሉትን የቡናን ቦርድ እና ኃላፊዎችን እንዲሁም ለዋናው ግብ ጠባቂ ኮአሲ ሀሪስተን ጉዳት ምክንያት ናቸው የተባሉትን አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲችም ሲተቹ እና ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሲሳደቡ የነበሩ ደጋፊዎችም ነበሩ፡፡

የሁለተኛው ግማሽ አጀማመር ከመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች በተሻለ የተረጋጋ ነበር፡፡ ቡናማዎቹም ሰከን ብለው እና ትኩረታቸውን ጨዋታው ላይ አድርገው ጎሎችን ለማግኘት ጥረት ማድረግ ጀመሩ፡፡ በ47ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም መሀመድ ከቀኝ በኩል በመሬት አሻግሮ በተከላካይ የተመለሰውን ኳስ ኢያሱ ለኤልያስ ማሞ አዘጋጅቶለት ኤልያስ በአግዳሚው ላይ በማጎን መልካም አጋጣሚ አበላሽቷል፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ዮሴፍ ያሻገረው ኳስ አቅጣጫውን ቀይሮ ወደጎል ሲያመራ ታሪክ አውጥቶታል፡፡ ከዚያም ሽመክት እና ስዩም በዮሴፍ እና መስኡድ ላይ በሰሯቸው ተከታታይ ጥፋቶች የማስጠንቀቂያ ካርዶች ተመልክተዋል፡፡ በ55ኛው ደቂቃ ኤልያስ እና ዮሴፍ ተቀባብለው ኤልያስ ወደጎል የመታው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል፡፡ ቡናማዎቹ በ10ቹ ደቂቃዎች የፈጠሩትን የማጥቃት ጫና ሰማያዊዎቹ በተለያዩ መንገዶች ለመቋቋም እና የተጋጣሚያቸውን የእንቅስቃሴ ቅኝት ለመስበር የተለያዩ መንገዶችን ለመጠቀም ይሞክሩ ነበር – ታሪክ በተደጋጋሚ ወድቆ ይታከም ነበር፤ ኳሱን ለመያዝ ይሞክሩ ነበር፤ እንዲሁም የተጨዋች ቅያሬም በማድረግ ያሬድን አስወጥተው ወግደረስ ታዬን አስገብተዋል፡፡ የአሰልጣኝ ጌታቸው ልጆች ጥረታቸውም ተሳክቶላቸው በበርካታ ደጋፊዎች የሚታገዘውን ተጋጣሚያቸውን ጫና ማብረድ ችለዋል፡፡ በቀጣዮቹ 20 ደቂቃዎችም ከቡና በኩል የሚጠቀስ የማጥቃት ስጋት አልተፈጠረም፡፡ በመሀል ግን አምበሉ መስኡድ መሀል ሜዳ አካባቢ በስዩም በክርን ተመትቼያለሁ ብሎ ቢወድቅም ዋናውም ሆኑ የመስመር አርቢትሮቹ ምንም ሳይሉ አልፈውታል፡፡ በ74ኛው ደቂቃ ላይ ፖፓዲች ሁለት ቅሬዎችን በማድረግ (ጥላሁን ወልዴን በአህመድ እንዲሁም አማኑኤል ዮሐንስን በኤልያስ) የተዳከመውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ነፍስ ሊዘሩበት ሞክረዋል፡፡ በ78ኛው ደቂቃ ጋቶች ፓኖም በደደቢት የጎል ክልል ውስጥ ጥሩ ኳስ ቢያገኝም በመምታት ፈንታ ተጨዋች ለማለፍ ሲሞክር ተቀምቷል፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ የመሀል ተከላካዩ ኢኮ ፌቨር በአየር ላይ በረዥሙ የላከው ኳስ ከደደቢት የመሀል ተከላካዮች ጀርባ ሮጦ ለገባው ዊልያም ደርሶ ካሜሩናዊው አጥቂ ቡድኑን በመጠኑም ቢሆን ወደጨዋታው የመለሰ ጎል አስቆጥሯል፡፡ የቡናማዎቹ ደጋፊዎች በቀሩት ደቂቃዎች ከቡድናቸው ከፍተኛ የማጥቃት ጫና፣ ተደጋጋሚ ሙከራዎች እና ቢያንስ የአቻነት ጎል ቢጠብቁም ተስፋ እንዳደረጉት አልሆነላቸውም፡፡ በ86ኛው ደቂቃ ከማእዘን ምት ተሻግሮ እና በኢኮ ተገጭቶ በድንቅ ሁኔታ በታሪክ ከመለሰው ኳስ በስተቀር አስደንጋጭ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ እንደውም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ሄኖክ በወንድወሰን እርዳታ ከሳኑሚ የተቀበለውን በጣም ጥሩ እድል ሲያመክን፣ ሳኑሚ ራሱ ከርቀት በአየር ላይ መትቶት በወንድወሰን የተያዘው ኳስም አስደንጋጭ ነበር፡፡ በደደቢት 2ለ1 ድልም ጨዋታው ተጠናቋል፡፡

  • ከጨዋታው በኋላ ጨዋታውን በመሀል ዳኛነት የመሩት ኢንተርናሽናል አርቢትር ለሚ ንጉሴ የአርቢትር ኮሚቴው የአንድ ዓመት እገዳ እንደጣለባቸው ተነግሯል፡፡

በሌሎች ጨዋታዎች፡-

  • መሪው አዳማ ከተማ አሁንም አልተቻለም፡፡ የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድን በሜዳው ዳሸን ቢራን 2ለ1 አሸንፏል፡፡ አማካዮቹ ታከለ ዓለማየሁ እና ወንድሜነህ ዘሪሁን ለአዳማ እንዲሁም ኤዶም ሆሶሮቪ (ፍ.ቅ.ም) ለዳሸን ጎሎቹን አስቆጥረዋል፡፡
  • ቅዱስ ጊዮርጊስ በደጋፊዎቹ የተቃውሞ ጩኸቶች ታጅቦ በሜዳው ሀዲያ ሆሳዕናን 2ለ0 ረትቷል፡፡ ራምኬል ሎክ እና አዳነ ግርማ በየግማሾቹ ጎሎቹን አግብተዋል፡፡ አሰልጣኝ ማርት ኖይ ለምክር ወደ ሜዳው ጫፍ በወጡ ቁጥር በተለይም በጥላፎቅ ከነበሩ ደጋፊዎች የተቃውሞ ድምፆች ይሰሙባቸው ነበር፡፡
  • በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሲዳማ ቡና 1ለ1 ሲለያዩ መከላከያ ሀዋሳ ከተማን 3ለ0 ረትቷል፡፡ በንግድ ባንክ እና ሲዳማ ጨዋታ አንተነህ ገብረክርስቶስ ለንግድ ባንክ እንዲሁም አንዱዓለም ንጉስ ለሲዳማ ጎሎቹን ሲያስቆጥሩ ሳሙኤል ታዬ እና ተቀይሮ የገባው ባዬ ገዛኸኝ (2) ለመከላከያ የማሸነፊያ ጎሎቹን በስማቸው አስመዝግበዋል፡፡
  • ቦዲቲ ላይ በተደረገ ጨዋታ ባለሜዳው ወላይታ ድቻ በድሬዳዋ ከተማ የ1ለ0 ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ ለድሬዳዋ ፍቃዱ ታደሰ ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል፡፡ የስድስተኛው ሳምንት አንድ ቀሪ ጨዋታ ሰኞ በአዲስ አበባ ስታዲየም በኤሌክትሪክ እና አርባምንጭ ከተማ መካከል ይደረጋል፡፡
  • በነዚህ ውጤቶች መሰረት አዳማ ከተማ በ16 ነጥቦች መሪነቱን ሲያጠናክር፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ13 እና ደደቢት በ11 ነጥቦች ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኑሚ በአምስት ጎሎች ከፍተኛ ጎል አግቢነቱን ሲመራ፣ የአዳማ ከተማው ታፈሰ ተስፋዬ እና የኢትዮጵያ ቡናው ዊልያም ያቡን በአራት ጎሎች ይከተላሉ፡፡
  • የሰባተኛው ሳምንት የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች ለፊታችን ሐሙስ ፕሮግራም ተይዞላቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በቻን ውድድር ምክንያት ለበርካታ ሳምንታት ውድድሩ ይቋረጣል፡፡ በዚህ መሰረት ሐሙስ በ9 ሰዓት በድሬዳዋ – ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በይርጋለም – ሲዳማ ቡና ከመከላከያ፣ በአርባምንጭ – አርባምንጭ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና፣ በጎንደር – ዳሸን ቢራ ከኤሌክትሪክ፣ በሀዋሳ – ሀዋሳ ከተማ ከመሪው አዳማ ከተማ እንዲሁም በሆሳዕና – ሀዲያ ሆሳዕና ከወላይታ ድቻይጫወታሉ፡፡ በዚያው ቀን በአዲስ አበባ ስታዲየም በ11ከ30 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደደቢት ይፋለማሉ፡፡

Articles

24ኛው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና በፖላንድ ግድኒያ ይካሄዳል

Published

on

Gdynia 2020

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከምስራቅ አፍሪካ አቻዎቻቸው ጋር ለአሸናፊነት ይፎካከራሉ

በባልቲክ ባሕር ዳርቻ የምትገኘው ትንሿ የፖላንድ ወደብ ከተማ ግድኒያ በሀገራት መካከል የሚካሄድ የዓመቱ ብቸኛ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር የሆነውን እና ከሰዓታት በኋላ የሚጀመረውን የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች፡፡ ስመ ጥር አትሌቶች የተካተቱበትና ከ250 በላይ ተሳታፊዎች የሚፎካከሩበት ይህ ሻምፒዮና የዓለም አትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪያን አይኖች ዳግም በምስራቅ አፍሪካውያኑ ኮከቦች ላይ እንዲያተኩሩ እንደሚያስገድድ ይጠበቃል፡፡ በሴቶቹ ውድድር ሴቶች ብቻ የተሳተፉበት ሩጫ የዓለም ሪኮርድ ባለቤቷ ኬንያዊት ፐሬስ ጄፕቺርቺር እና በወንዶች አሯሯጭነት የተመዘገበ የዓለም ሪኮርድ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ አባበል የሻነህ፤ በወንዶች በቅርቡ የ5000 ሜትር እና 10000 ሜትር የዓለም ሪከርዶችን የሰባበረው ኡጋንዳዊው ጆሹዋ ቼፕቴጊ እንዲሁም ኢትዮጵያዊው ጉዬ አዶላ ከሌሎች ተፎካካሪዎቻቸው በመላቅ በፖላንዷ የባህር ዳርቻ ከተማ ላይ የወርቃማ ድል አሻራቸውን ለማሳረፍ ተስፋ ከሚያደርጉት ከዋክብት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

Photo Aman @angasurunning

ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ አዲስ አሸናፊ አትሌት የሚጠበቅበት የወንዶቹ ፉክክር

ከ2006 ዓ.ም. ወዲህ ከተካሄዱት ዘጠኝ የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የወንዶች ውድድሮች ከአንዱ በስተቀር ሁሉም ድሎች በኤርትራዊው ዘርሰናይ ታደሰ (5) ወይም በጆፍሬይ ካምዎሮር ስም የተመዘገቡ ናቸው፡፡ ዘርሰናይ እና ካምዎሮር በግዲኒያ የማይገኙ በመሆኑም ውድድሩ ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ የወርቅ ሜዳያ አሸናፊ ስም የሚመዘግብ ይሆናል፡፡ በግዲኒያ የወንዶቹ ፉክክር ማስጀመሪያ ሽጉጥ ሲተኮስ አይኖች ሁሉ ትኩረታቸው ከዚህ በፊት በ21.1 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ተወዳድሮ በማያውቀው የወቅታዊ ምርጥ ብቃት ባለቤት ኡጋንዳዊ አትሌት ጆሹዋ ቼፕቴጊ ላይ ይሆናል፡፡ ኡጋንዳዊው ምንም እንኳን የግማሽ ማራቶን ውድድር ልምድ ባይኖረውም ባለፈው እና በዘንድሮ ዓመት በተለያዩ ውድድሮች ካሳየው ድንቅ ብቃት አንፃር እንደሚጠበቀው ሆኖ እንደሚገኝም ይገመታል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኡጋንዳ አትሌቶች ላይ እየታየ የመጣው የብቃት መሻሻል ከዚህ ቀደም ብብርቱ ተፎካካሪነት ከሚታወቁት ኢትዮጵያ እና ኬንያ አትሌቶች በተጨማሪ የዓለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የወንዶቹን ፉክክር ይበልጥ እንደሚያደምቀው ይጠበቃል፡፡ የኡጋንዳ የወንዶች ቡድን በግማሽ ማራቶን ውድድር የመጀመሪያ ተሳትፎውን በሚያደርገው ጆሹዋ ቼፕቴጊ የሚመራ ሲሆን ሌላኛው ተጠባቂ አትሌት ጃኮብ ኪፕሊሞ፣ አቤል ቼቤት እና ሞሰስ ኪቤትንም አካቷል፡፡

በወንዶቹ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም የቼፕቴጊ ብርቱ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ ተገምቷል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ሳይጠበቅ ድንቅ ውጤቶችን በማስመዝገቡ ረገድ መልካም ስም ያለው ጉዬ አዶላ ለወርቅ ሜዳያ ድሉ ከተገመቱት መካከል አንዱ ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 በዴንማርክ ኮፐንሀገን ከተካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና በፊት ብዙም እውቅና ያልነበረው ቢሆንም የራሱም ምርጥ ሰዓት ከሁለት ደቂቃ በላይ ባሻሻለበት 59፡21 የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊ ለመሆን መብቃቱ ይታወሳል፡፡ በዚያው ዓመት መገባደጃ ላይም የወቅቱን የዓለም ግማሽ ማራቶን እና የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮን ጆፍሬይ ካምዎሮር በዴልሂ የግማሽ ማራቶን ፉክርር የራሱን ምርጥ ሰዓት 59.06 በማስመዝገብ ጭምር አሸንፎታል፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ በሮጠበት የ2017 የበርሊን ማራቶን ውድድር ላይ ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ በመጀመሪያ ተሳትፎ የተመዘገበ የምንግዜም ፈጣን የሆነ 2:03:46 ሰዓት ያለው ጉዬ አዶላ በፖላንዱ የግማሽ ማራቶን ላይ ለመሳተፍ ከተመዘገቡት አትሌቶች መካከል የርቀቱን ሶስተኛ ፈጣን ሰዓት የያዘም ነው፡፡  

በጉዬ አዶላ በሚመራው የኢትዮጵያ ቡድን ውስጥ የግማሽ ማራቶን ፉክክርን ከ60 ደቂቃ በታች ለመጨረስ የበቁና ልምድ ያላቸው አንዳምላክ በልሁ (59:10)፣ ልዑል ገብረስላሴ (59:18) እና አምደወርቅ ዋለልኝ (59:22) እንዲሁም ለዚህ ውድድር መምረጫ በሀገር ውስጥ የተካሄደው የ15 ኪሎ ሜትር ውድድር አሸናፊው ሀይለማሪም ኪሮስ (1:01:08) ተካተዋል፡፡           

የወንዶቹ ፉክክር ያለፉት ሶስት ሻምፒዮናዎች የተናጠል የወርቅ ሜዳልያ ድልን በጆፍሬይ ካምዎሮር አማካይነት አላስቀምስ ያለው የኬንያ የወንዶች ቡድን ዘንድሮም በጠንካራ አትሌቶች የተወከለ ሲሆን በግል የወርቅ ሜልያ ድል ተስፋውን የጣለውም የ2020 የፕራግ ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮን በሆነው ኪቢዎት ካንዲዬ እና የ2017 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ አሸናፊው ሊዮናርድ ባርሶቶን ላይ ነው፡፡ ማውሪስ ሙኔኔ፣ በርናርድ ኪፕኮሪር እና በርናርድ ኪሜሊም ሌሎቹ የኬንያ ተወዳዳሪዎች ናቸው፡፡

ሁለቱን የዓለም ሪኮርድ ባለቤቶች የሚያገናኘው የሴቶቹ ፉክክር

እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ አስተዳዳሪ አካል ቤሰቶች የጎዳና ላይ ፉከክሮች ሁለት አይነት የሪኮርድ አመዘጋገብን መከተል ከጀመረ ወዲህ የግድኒያው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የሴቶች ውድድር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለቱን የርቀቱ የዓለም ሪኮርድ ባለቤቶች የሚያፎካክር ይሆናል፡፡ የሴቶቹ ውድድር ከዓለም ሪኮርድ ባለቤቶቹ ኬንያዊቷ ፐሬስ ጄፕቺርቺር (ሴቶች ብቻ የሮጡበት ሪኮርድ ባለቤት) እና ኢትዮጵያዊቷ አባበል የሻነህ (ሴቶች ከወንዶች ጋር የሮጡበት የዓለም ሪኮርድ ባለቤት) በተጨማሪ ያለፈው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮን ኢትዮጵያዊቷ ነፃነት ጉደታም የአሸናፊነት ክብሯን ለማስጠበቅ የምትፎካከርበት ነው፡፡

በ2016 ካርዲፍ ላይ የተካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን አሸናፊነት ገድልም ያላት የ27 ዓመቷ ኬንያዊት ፐሬስ ጄፕቺርቺር በ2017 እና 2018 በወሊድ ምክንያት ከውድድር ርቃ ከከረመች በኋላ በ2019 ባደረገቻቸው ውድድሮች ወደ ምርጥ አቋሟ መመለሷን አሳይታለች፡፡ ያም ሆኖ በ2016 በተፎካከሩበት የዴልሂ ግማሽ ማራቶን በጄፕቺርቺር ላይ የበላይነቱን የወሰደችው ኢትዮጵያዊቷ አባበል የሻነህ በግዲኒያም ብርቱ ተፎካካሪዋ እንደምትሆን አያጠራጥርም፡፡ በ2013 የሞስኮ ዓለም ሻምፒዮና እና በ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ የ10000 ሜትር እና 5000 ሜትር ተሳትፎዋ ብዙም አመርቂ የሚባል ውጤት ያላስመዘገበችው አባበል ከዛ በኋላ አብዛኛውን ግዜዋን ለጎዳና ላይ ሩጫዎች ሰጥታ ስትሰራ ቆይታለች፡፡ ከተሳተፈችባቸው አስራ ሁለት የግማሽ ማራቶን ውድድሮችም በአስሩ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ደረጃዎች በመያዝ ማጠናቀቅ የቻለች ሲሆን ባለፈው ዓመት በተወዳደረችበት የቺካጎ ማራቶን ላይም የራሷ ምርጥ በሆነ 2፡20፡51 ሰዓት ሁለተኛ ሆና ጨርሳለች፡፡

የግድኒያው የሴቶች ግማሽ ማራቶን ዓለም ሻምፒዮና ሌላኛዎቹ የትኩረት ማዕከሎች ሁለቱ የከዚህ ቀደም ሪኮርድ ባለቤት እንዲሁም ከሁለት ዓመት በፊት በስፔን ቫሌንሲያ በተካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የወርቅ እና የብር ሜዳልያ አሸናፊዎች ኢትዮጵያዊቷ ነፃነት ጉደታ እና ኬንያዊቷ ጆሴሊን ጄፕኮስጋይ ናቸው፡፡ ነፃነት ከሁለት ዓመት በፊት በቫሌንሲያ የቅድመ ውድድር ተጠባቂዋ ጄፕኮስጋይን በማስከተል ሻምፒዮን ስትሆን የገባችበት ሰዓት ሴቶች ብቻ የሮጡበት ሪኮርድ ባለቤት አድርጓት ነበር፡፡ ሆኖም ከዛ በኋላ ግን ላለፉት ሁለት ዓመታት አንድም የግማሽ ማራቶን ውድድር ማሸነፍ አልቻለችም፡፡ ጄፕኮስጋይ አሁንም ሙሉ በሙሉ ሪኮርዶችን ወደሰባበረችበት የ2017 ዓ.ም. ድንቅ አቋሟ መመለስ ባትችልም ባለፈው ዓመት በመጀመሪያ የማራቶን ውድድር ተሳትፎዋ የኒው ዮርክ ማራቶንን ለውድድር ስፍራው ሪኮርድ በቀረበ ሰዓት ለማሸነፍ ችላለች፡፡ ሁለቱ አትሌቶች ባለፉት ሁለት ዓመታት አቋማቸው እምብዛም አመርቂ የነበረ ባይሆንም የግድኒያውን ውድድር ዳግም ወደውጤት ከፍታ የሚወጡበት መድረክ ለማድረግ የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

በኢትዮጵያ እና ኬንያውያን አትሌቶች መካከል ብርቱ ትንቅንቅ እንደሚደረግበት በሚጠበቀው የሴቶቹ ውድድር በኢትዮጵያ በኩል ከአባበል እና ነፃነት በተጨማሪ ያለምዘርፍ የኋላው፣ ዘይነባ ይመር እና መሰረት ጎላ የሀገራቸውን ሰንደቅ በዓለም አደባባይ ከፍ እንዲል ለማድረግ የሚፎካከሩ አትሌቶች ናቸው፡፡ በኬንያ በኩልም ሮዝመሪ ዋንጂሩ፣ ዶርካስ ኪሜሊ እና ብሪሊያን ኪፕኮኤች በጉጉት የሚጠበቀውን ድል ለማሳካት ከጄፕቺርቺር እና ጄፕኮስጋይ ጎን እንዲሰለፉ የተመረጡት አትሌቶች ናቸው፡፡

የኮሮና ቫይረስ በፍጥነት በዓለም ዙሪያ እየተስፋፋና አሳሳቢነቱ እያደገ በመምጣቱ ምክንያት በርካታ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች እንዲሰረዙ ተደርገዋል፡፡ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ አስተዳዳሪ (ወርልድ አትሌቲክስ) የበላይ ተቆጣጣሪነት እ.አ.አ. በማርች 29/2020 ሊካሄድ ፕሮግራም ተይዞለት የነበረው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ለመካሄድ የበቃውም በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ምክንያት ለኦክቶበር 17/2020 እንዲተላለፍ ተደርጎ ነው፡፡

በዘንድሮው ውድድር ላይ በ2014 ዓ.ም. ያስመዘገበችውን የወርቅ ሜዳልያ ድል ጨምሮ ባለፉት አስር የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮናዎች የቡድን የሜዳልያ ድል ተቋዳሽ የሆነችው ኤርትራ እንዲሁም ባለፉት 23 የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮናዎች ላይ ያለማቋጥ ተሳታፊ የነበሩት ጃፓን እና አሜሪካ ለመሳተፍ አትሌቶቻቸውን ሳያስመዘግቡ ቀርተዋል፡፡ ካናዳም ውድድሩ ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ያስመዘገበቻቸውን አትሌቶች በኮሮና ቫይረስ ስጋት ምክንያት ወደ ፖላንድ እንደማትልክ አሳውቃለች፡፡

* የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና ጣሊያንን ጨምሮ ከአስተላላፊዎች ጋር በተናጥል ስምምነት ከተደረሰባቸው 22 ሀገሮች በስተቀር በወርልድ አትሌቲክስ የዩቲዩብ ቻናል ለመላው ዓለም በቀጥታ ይተላለፋል፡፡

Continue Reading

Uncategorized

የኢትዮጵያ ቀን በዋሽንግተን ዲሲ በ’ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ’ ዝግጅት ሊከበር ነው – Interview with Dr. Gashaw Abeza

Published

on

By

የኢትዮጵያ ቀን በዋሽንግተን ዲሲ በ’ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ’ ዝግጅት ሊከበር ነው – Interview with Dr. Gashaw Abeza
Continue Reading

Uncategorized

#Ethiopia: EthioTube ከስፍራው – Town Hall in DC on Addis Politics – Opening Speech by Ermias Legesse

Published

on

By

#Ethiopia: EthioTube ከስፍራው – Town Hall in DC on Addis Politics – Opening Speech by Ermias Legesse
Continue Reading

Trending