Connect with us

Articles

የውጪ ዜጋ ተጨዋቾችን ማጫወት ምን ጠቀመን? ምን ጎዳን?

Published

on

Imported Footballers in EPL

Imported Footballers in EPL

ብራዚል፣ ናይጄሪያ፣ ጋና፣ ካሜሩን፣ ሴራሊዮን፣ ኡጋንዳ፣ ቤኒን፣ ቶጎ… እነዚህን የደቡብ አሜሪካ፣ ምዕራብ አፍሪካ፣ መካከለኛው አፍሪካ እና ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ምን አንድ ላይ አሰለፋቸው ብላችሁ ብትጠይቁ መልሱ በሀገራችን ክለቦች የሚጫወቱ የውጪ ሀገር ዜጎች መገኛ ሀገራት ናቸው የሚል ይሆናል፡፡ በ1980ቹ መጨረሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኦጉስቲን የተባለ ናይጄሪያዊ አስመጥቶ ማጫወት ከጀመረ አንስቶ ያለፉት 20 ዓመታት የዋናው ሊጋችን ጉዞ በርካታ የውጪ ዜጋ ተጨዋቾችን ያሳየን ሲሆን በዚህ ሰዓት እንኳን ከላይ የተጠቀሱት ከስምንት ያላነሱ ሀገራት ዜጎች የሆኑ ከ20 የበለጡ ተጨዋቾች በፕሪምየር ሊጉ ክለቦች የተጨዋቾች ዝርዝሮች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ባለፉት በርካታ ዓመታት የውጪ ዜጋ ተጨዋቾችን በማጫወት ቀዳሚ የነበረው በገንዘብ አቅም ከተፎካካሪዎቹ ላቅ ያለው እና የብዙ የሊግ ድሎች ባለቤቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢሆንም በቅርብ ዓመታት ሌሎቹም ክለቦች በራሳቸው መልማዮች አማካይነት ያመጧቸውን አልያም እዚሁ በሀገራችን ለሌሎች ክለቦች ሲጫወቱ የነበሩ የውጪ ዜጎችን ማጫወትን ባህል አድርገዋል፡፡ በዚህ ወቅትም ከ14ቱ የፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ስምንት ያህሉ የውጪ ዜጋ ተጨዋቾችን በማጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡

ምክንያት እና ምልመላ

የፕሪምየር ሊጉ አንዳንዴም የብሔራዊ ሊጉ ክለቦች የውጪ ዜጋ ተጨዋቾችን የሚቀጥሩባቸው ምክንያቶች ሊለያዩ ቢችሉም በዋናነት ግን የቡድናቸውን ክፍተቶች በተሻሉ ተሰጥኦዎች ለመሙላት ከመሻት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተለይ የዚህ ክስተት ጀማሪ እና መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ መሆናቸው እና በነዚህ ውድድሮች ረዥም የስኬት ጉዞ ለማድረግ ያላቸው ራዕይ በሀገራችን ሊያገኟቸው ያልቻሉ ዓይነት ተጨዋቾችን (ለምሳሌ በሀገራችን ትልቅ ችግር እንዳለበት በሚወሳው የግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ) ከሌሎች ሀገራት ለመፈለግ እንዳስገደዳቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ እናም እንደ ፈረሰኞቹ ባለስልጣናት ከሆነ በሀገር ውስጥ ተጨዋቾች ብቻ በአህጉራዊ ውድድሮች መፎካከር የማይቻል ነው፡፡ ሌሎቹ የእነሱን ፈለግ የተከተሉት ክለቦች በዚህ ዙሪያ በግልፅ ሲናገሩ ባይሰሙም የብዙዎቹ ሀሳብ ግን በተሰጥኦ አልያም በሙያዊ ባህሪይ የተሻሉ ተጨዋቾችን ለመጠቀም እና በሊጉ አንፃራዊ ስኬት ለማግኘት ካለ ፍላጎት እንደሆነ ይታሰባል (ሌሎች ያልተረጋገጡ/ለማረጋገጥም የሚያዳግቱ አሉባልታዎች እንዳሉ ሆነው)፡፡ እናም አካሄዳቸው እና ተስፋቸው ቢያሳምነንም፣ ባያሳምነንም ክለቦቻችን የውጪ ዜጎችን የሚቀጥሩት ለመሻሻል ካላቸው ምኞት ነው ብለን በየዋህነት ልናምን እንችላለን፡፡

ወደ ምልመላው ስንሻገር ግን የውጪ ሀገሩ ዝውውር ከሀገር ውስጡ ዝውውር ባልተናነሰ ምናልባትም በበለጠ ብዙ ያልጠሩ እና ጥርጣሬ ውስጥ የሚያስገቡ አካሄዶች የሚስተዋሉበት ነው፡፡ በተለይ ከሌላ ሀገር በቀጥታ የመጡ ተጨዋቾች በእነማን መልማይነት፣ በእነማን አገናኝነት፣ በምን አይነት መንገድ፣ በምን ያህል የዝውውር እና የፊርማ ክፍያ እንዲሁም ወርሀዊ ደመወዝ እንደመጡ ማወቅ አስቸጋሪ አንዳንዴም የማይቻል ነው፡፡ በአጭሩ ግልፅነት የራቀው እና የተሸፋፈነ መስክ ነው፡፡ የአንዳንዶቹ ተጨዋቾች ፍፁም ደካማ መሆን እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ መጡበት ሀገር ለመመለስ መገደድ እንዲሁም የአንዳንዶች የፊርማ ክፍያ ተቀብሎ መሰወር የምልመላው እና የዝውውር ስምምነቱ ምን ያህል ጥያቄ አስነሺ እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡

የውጪ ዜጎች ስኬት

ከላይ እንደተጠቀሰው የውጪ ዜጎችን የሚያጫውቱት ከግማሽ የሚልቁት የፕሪምየር ሊጉ ክለቦችም ሆነ ሌሎች ጥቂት የብሔራዊ ሊጉ ክለቦች ለውጪ ዜጎቹ እድሎችን የሚሰጡት በቦታቸው በችሎታም ሆነ በሙያዊ ባህሪያ የተሻሉ ኢትዮጵያውያንን በማጣታቸው እንደሆነ እና በሊጎቻችን አልያም በአፍሪካ መድረክ የተሻለ ተፎካካሪ ለመሆን ካላቸው ፍላጎት እንደሆነ ይገልፃሉ፤ ባይገልፁም እንደዚያ ይታመናል፡፡ ግን ክለቦቻችን እውን ይህን ምኞታቸውን በውጪ ዜጎቹ አጋዥነት አሳክተዋል? የዚህ ጥያቄ መልስ ብዙ ሊያከራክር ቢችልም አብዛኞቹ የውጪ ዜጎቹ እንደተጠበቁት ስኬታማ እንዳልነበሩ እና ክለቦቻቸውንም በተጠበቁበት መንገድ እንዳልረዱ በብዙ ማስረጃ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በአፍሪካ መድረክ ስኬታማ ጉዞ ለማድረግ አልመው የተነሱትን ቅዱስ ጊዮርጊስን በ1990ቹ አጋማሽ አንፃራዊ የተሻለ ጉዞ እንዲያደርጉ የረዱት ኡጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ዴኒስ ኦኒያንጎ፣ እንዲሁም የሀገሩ ልጅ አማካዩ ኦሳኒ ባጆፔ እና ሌላኛው አማካይ ጋናዊው አብርሀም ኮዲሞር እንዲሁም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በወጥ አቋማቸው ፈረሰኞቹን ለተከታታይ የሊግ ድሎች እና ለካቻምናው መልካም የአፍሪካ መድረክ ጉዞ ያበቁት ኡጋንዳዊያኑ ሮበርት ኦዳንካራ እና አይዛክ ኢዜንዴ በኢትዮጵያ ምድር ከተጫወቱት በርካታ የውጪ ዜጎች መካከል በስኬት ሊጠቀሱ ሚችሉ ናቸው፡፡ ካቻምና ደደቢትን ለሊግ ዋንጫ ያበቁት ጋናዊያኑ ሻይቡ ጅብሪል እና አዳሙ መሀመድም በመለስተኛ ስኬት ይጠቀሱ ይሆናል፡፡ ከነዚህ ውጪ ያሉት ግን ለክለቦቻቸውም ሆነለሀገራችን እግር ኳስ የተለየ እሴት ማበርከት ያልቻሉ፣ ወጥ አቋም የሌላቸው፣ ከክለብ ክለብ የሚዞሩ፣ ተጠባባቂ ወንበር ላይ የሚቀመጡ ከዚያም አልፎ ከቡድን ስብስብ ውጪ ሆነው ቤታቸው ተቀምጠው ደመወዛቸውን የሚያገኙ ናቸው፡፡ ፈረሰኞቹ በየዓመቱ ከመላው አፍሪካ እና አንዳንዴም ወጣ ብለው ከአውሮፓ (ሰርቢያዊው ግብ ጠባቂ ይታወሳል) እና ከደቡብ አሜሪካ (አዲሱ ብራዚላዊ አማካይ) ተጨዋቾችን ቢያመጡም ከእነዚያ ሁሉ ተጨዋቾች መካከል ከአምስት የማይበልጡትን በስኬት ማንሳት፣ ዘንድሮ በዓመቱ መጀመሪያ ያመጧቸውን ሁለቱን አጥቂዎች ሴኔጋላዊው ኡስማን ኡምቤንጎ እና ኬኒያዊው እንድሪስ ከወራት ቆይታ በኋላ ወደየሀገሮቻቸው መመለስ፣ ሌላው ታላቅ ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ ወደ ቡድኑ የቀላቀላቸውን የሶስት ሀገራት ዜጎች የሆኑ አራት ተጨዋቾች በቋሚነት እየተጠቀመ አለመሆኑ (እንደውም አንዱ በብዙ ጨዋታዎች ከቡድኑ ውጪ ነው)፣ የተሰጥኦ ፋብሪካ የነበረው ኤሌክትሪክ በአምስት የውጪ ዜጎቹ ታግዞ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከግማሽ በታች መገኘቱ… እነዚህ ሁሉ የውጪ ዜጎች ዝውውሮች ፍፁም ስኬታማ እንዳልነበሩ እና አሁንም እንዳልሆኑ የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው፡፡

ምን ጠቀመን? ምን ጎዳን?

በአንድ ሀገር ሊግ ውስጥ የውጪ ሀገር ተጨዋቾች መብዛት ጥቅሞች እና ጉዳቶች ይኖሩታል፡፡ ጠቅለል አድርገን ጥቅሞቹን ስንመለከት የሚመጡት ተጨዋቾች ደረጃቸው ከፍ ያለ ከሆነ የሀገር ውስጥ ተጨዋቾች ከውጪ ዜጎቹ እግር ኳሳዊ ተሰጥኦን፣ ታታሪነትን እና ሙያዊ ባህሪይ (ፕሮፌሽናሊዝም) ሊማሩ ይችላሉ፤ ክለቦች በአህጉራዊ መድረክ የተሻለ ተፎካካሪ ይሆናሉ፤ ከነዚህም መነሻ የሀገሪቱ እግር ኳስ ሊያድግ ይችላል፡፡ የእኛን ጉዳይ በዚህ ረገድ ከመዘንነው ምናልባት ከሜዳ ታታሪነት ውጪ የውጪ ዜጎቹ ተጨዋቾች ያበረከቱትን ነገር መረዳት ያስቸግራል፡፡ በተሰጥኦ ረገድ ከእኛ ተጨዋቾች የላቁ የውጪ ዜጎችን (ምናልባት ከላይ ከተጠቀሱት ሁለቱ የጊዮርጊስ ግብ ጠባቂዎች በቀር) ማየታችን የሚያጠራጥር ሲሆን ከአንፃራዊው የጊዮርጊሶች ትንሽ የተሻለ የአፍሪካ ጉዞ (የሚመኙት የምድብ ድልድል ውስጥ ገብተው እንዳለማወቃቸው ግን በቂ ነው ሊባል አይችልም) በቀርም ይህ ነው የሚባል ስኬት ክለቦቻቸው እንዲያሳኩ አላገዙም፡፡

ወደጉዳቱ ስንሄድ የውጪ ዜጎች መብዛት ዋንኛው ጉዳት ለሀገር ውስጥ ተጨዋቾች የመጫወቻ እድሎችን ማነስ ወይም ማጣት ምክንያት መሆኑ ነው፡፡ በዚህ በኩል ግን ጉዳቱን እያየነው እንደሆነ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አይነት ትልቅ ክለብ ለዓመታት አራት እና አምስት የውጪ ዜጎችን በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ሲጠቀም፣ ኢትዮጵያ ቡና ሀገር ውስጥ አጥቂ አላገኘሁም ብሎ ሁለት አጥቂዎችን ከምእራብ አፍሪካ ሲያስመጣ፣ ለዓመታት ድንቅ ወጣቶችን በማሳደግ የእግር ኳሳችን መሰረት የነበረው ኤሌክትሪክ ይህ ባህሉን ትቶ ከአራት ያላነሱ የውጪ ዜጋ ተጨዋቾችን በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ሲጠቀም፣ ደደቢት እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወሳኝ ቦታዎች ለውጪ ዜጎች ትኩረት ሲሰጡ ስናይ እግር ኳሳችን እየተጎዳ አይደለም ብለን ለመናገር አቅሙ አይኖረንም፡፡ በእነዚህ ታላላቅ ክለቦች ለውጪ ዜጎቹ የበዛ ትኩረት የተሰጠው የሀገራችን ተስፈኛ ወጣቶች ወደ ጎን ተገፍተው እንደሆነ ልብ ማለት ይኖርብናል፡፡ የውጪ ዜጎቹ ይህ እድል የተሰጣቸው ከእኛዎቹ ተሽለው ተገኝተው ቢሆን ባልከፋ ነበር፡፡ ግን የተለየ ችሎታ ሳይኖራቸው እና የተለየ ጥቅም ሳያበረክቱ መሆኑ ጉዳቱን ያገዝፈዋል፡፡ ከወራት በፊት የብሔራዊ ቡድናችን አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ በጉዳት እና ቅጣት የአጥቂ እጥረት በገጠማቸው ወቅት በሀገራችን ክለቦች ውጪ ዜጎች መብዛት አማራጮቻቸውን እንዳሳነሰባቸው ቅሬታ አቅርበው ነበር፡፡ የአሰልጣኙ ቅሬታ በወቅቱ በአንዳንዶች እንደ ሰበብ ቢታይም ልብ ብለን ካስተዋልን ግን ፖርቹጋላዊው ልክ እንደነበሩ እንረዳለን፡፡ ባሬቶ ይህን ባሉ ሰዓት ከፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ሰባት ያህሉ የውጪ ሀገር ዜጋ አጥቂዎች ነበሯቸው (እንዲያውም እንደ ንግድ ባንክ፣ ጊዮርጊስ እና ቡና አይነቶቹ ከአንድ በላይ)፡፡ የእነዚህ ክለቦች የአጥቂ ስፍራዎች በውጪ ዜጎች ከተያዙ አዳዲስ እና ተስፈኛ ወጣት አጥቂዎች የት ሄደው ይጫወቱ?!

ምን ይደረግ?

ይህ ፅሁፍ የውጪ ዜጋ ተጨዋቾች ምንም አይጠቅሙንም፤ የሀገራችንን ምድር መርገጥ የለባቸውም፤ አይናቸውን አታሳዩን ከሚል አላማ የተነሳ የተፃፈ አይደለም፡፡ ነገር ግን ክለቦቻችን ከውጪ ሀገራት ተጨዋቾችን ሲያመጡ ግልፅነት ባለው ጥሩ የምልመላ እና ስምምነት መንገድ እንዲሆን፣ ደረጃቸው ከፍ ያለ እና ለተጨዋቾቻችን ማደግ እና መሻሻል እንዲሁም ለክለቦቻችን የተሻለ ጥንካሬ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ተጨዋቾችን እንዲያመጡ እንዲሁም የሚመጡት ተጨዋቾች በወጣት ተጨዋቾች ማደግ ላይ እንቅፋት እንዳይሆኑ በጥንቃቄ መራመድ እንደሚኖርባቸው አስተያየት ለመስጠት ነው፡፡ እግር ኳሱን የሚያስተዳድረው የእግር ኳስ ፌዴሬሽንም የውጪ ግዢዎች በወጣት ተጨዋቾች እድገት እና ባሉትም ተጨዋቾች የመጫወት እድል ማግኘት ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ምክንያታዊ ሆኑ ህግጋት እና አካሄዶችን እንዲደነግግ እንመኛለን፡፡  በፕሪምየር ሊጉ እየተጫወቱ የሚገኙ የውጪ ዜጋ ተጨዋቾች:-

ክለብ ተጨዋቾች
ሲዳማ ቡና 1) ኤሪክ ሙራንዳ (ኡጋንዳ – አጥቂ)፡- በ1990ቹ አጋማሽ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ይጫወት የነበረው አንጋፋው አጥቂ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ተመልሶ የሊጉን መሪዎች እያገለገለ ይገኛል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ 1) ሮበርት ኦዳንካራ (ኡጋንዳ – ግብ ጠባቂ)፡- በሀገራችን ተፎካካሪ የሌለው ግብ ጠባቂ የሆነው ሮበርት በብሄራዊ ቡድኑ ግን እስካሁን ቋሚ ተሰላፊ መሆን አልቻለም፡፡2) አይዛክ ኢዜንዴ (ኡጋንዳ – ተከላካይ)፡- ታታሪው የመሀል ተከላካይ በክረምቱ ወደ ኤሌክትሪክ ሊገባ ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም አሁን በኔይደር ዶስ ሳንቶስ ቡድን ውስጥ በፈረቃ እየተጫወተ ይገኛል፡፡

3) ብሪያን ኡሙኒ (ኡጋንዳ – አጥቂ)፡- በሴካፋ ውድድር ባሳየው ድንቅ ብቃት የብዙዎችን ትኩረት የሳበው አጥቂ በውድድር ዓመቱ አጋማሽ ፈረሰኞቹን ተቀላቅሎ የመጀመሪያ ጨዋታውን እየጠበቀ ይገኛል፡፡

4) ሉዊዝ (ብራዚል – አማካይ)፡- ብዙ የተባለለት ፈጣሪው አማካይ ልክ እንደ ኡሙኒ በቅርቡ ጊዮርጊስን ተቀላቅሎ በደጋፊዎች በጉጉት እየተጠበቀ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና 1) ኔልሰን (ናይጄሪያ – ግብ ጠባቂ):- የቀድሞው የወልቂጤ ከነማ ግብ ጠባቂ በታላቁ የሸገር ደርቢ የፍፁም ገብረማሪያምን ፍፁም ቅጣት ምት በማዳን ቡናማዎቹን ለድል ቢያበቃም ከዚያ በኋላ በሰራቸው ስህተቶች መነሻ ቋሚ ተሰላፊነቱን አጥቷል፡፡2) ኦሊቨር ዋረን (ካሜሩን – ተከላካይ)፡- ካሜሩናዊው የመሀል ተከላካይ ሚሊዮን በየነ በመጎዳቱ ምክንያት እጅግ ጥቂት የመሰለፍ እድል ቢያገኝም የሚሊዮን እና ኤፍሬም ወንድወሰንን ጥምረት ሰብሮ ቋሚ ተሰላፊነትን ለማግኘት አልቻለም፡፡

3) ሻኪሩ አላዲዬ (ቶጎ – አጥቂ)፡- በአዲስ አበባ ከተማ ካስቴል ዋንጫ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አሳይቶ የነበረው ፈጣኑ አጥቂ በዋናው ፕሪምየር ሊግ ግን ይህ ነው የሚባል መልካም አቋም ማሳየት ተስኖት የተጠባባቂ ወንበር አሟቂ ሆኗል፡፡

4) ኤዶም ሆሲያስ (ቤኒን – አጥቂ)፡- ስለ ኤዶም ምን ይባላል? ግልፁን ለመናገር ይህን ተጨዋች የመለመሉት ሰዎችም ሆኑ በኢትዮጵያ ቡና እንዲቀጥል የወሰኑት አሰልጣኞች ምን እንዳዩበት ለመናገር እጅግ ያስቸግራል፡፡ በአጭሩ ቤኒናዊው አጥቂ ከጥሩ ቁመና እና ፍጥነት ሌላ ምንም የእግር ኳስ ተሰጥኦ የማይታይበት ተጨዋች (?) ነው፡፡

ደደቢት 1) ሻይቡ ጅብሪል (ጋና – አማካይ)፡- የሰማያዊዎቹ አማካይ ለካቻምናው የሊግ ድላቸው ወሳኝ የነበረ ሲሆን በሊጉ ከሚጫወቱ ጥቂት ጥሩ የውጪ ዜጎች መካከል የሚመደብ ነው፡፡2) አዳሙ መሀመድ (ጋና – ተከላካይ)፡- አዳሙም እንደ ጅብሪል ለደደቢት የሊግ ድል ጥሩ ሚና ቢጫወትም አስደንጋጭ የአቋም መውረድ ገጥሞት ከቡድኑ ደካማ ጎኖች አንዱ ከሆነ ሰንበት ብሏል፡፡

3) ሳሙኤል ሳኑሚ (ናይጄሪያ – አጥቂ)፡- በኤሌክትሪክ (በቀድሞው መብራት ኃይል) ድንቅ ጊዜ ያሳለፈው ሳኑሚ አምና በቅዱስ ጊዮርጊስ ያልተሳካ ዓመት ካሳለፈ በኋላ ዘንድሮ በደደቢት በጥሩ አቋም ላይ ይገኛል፡፡ ናይጄሪያዊው አጥቂ ፍጥነቱ እና የአጨራረስ ብቃቱ ለየትኛውም ተከላካይ ፈታኝ ቢያደርገውም ዋዣቂ አቋሙ እና የውሳኔ ድክመቱ ወደ ሊጉ ሲመጣ ይደርሳል ተብሎ የተጠበቀበት ደረጃ እንዳይደርስ አድርገውታል፡፡

ኤሌክትሪክ 1) ሲሴ ሀሰን (ሴራሊዮን – ተከላካይ)፡- ኳስ በመንጠቅ እና የአየር ኳሶችን በመከላከል ጥሩ የሆነው የመሀል ተከላካይ በኳስ አጠቃቀሙ ረገድ ግን ደካማ ሆኖ ታይቷል፡፡2) ማይክል አዌኒ (ናይጄሪያ – ተከላካይ)፡- ያለፉትን ዓመታት ከመብራት ኃይል ጋር ላለመውረድ በመታገል ያሳለፈው አዌኒ ታታሪነቱ ቢነሳም ከስህተቶች የማይፀዳ መሆኑ ለተጠባባቂነት ዳርጎታል፡፡

3) ማሚኮ ኬዊሳ (ኡጋንዳ – አማካይ)፡- ኡጋንዳዊው አማካይ ሜዳ አካላይነቱ ቢደነቅም ቦታ አያያዙ እና ኳስ አጠቃቀሙ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡

4) ዊሊያም አሴንጆ (ኡጋንዳ – አማካይ)፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ ጥሩ ጊዜ ያሳለፈው ታጋዩ አማካይ ፈረሰኞቹን ለቅቆ ኤሌክትሪክን ከተቀላቀለ በኋላ ጥቂት ወሳኝ ጎሎችን ቢያስቆጥርም ባልለመደው ስፍራ መጫወቱ ማሳደር የሚችለውን ተፅዕኖ ያህል ማሳደር እንዳይችል አድርጎታል

5) ፒተር ንዋንድኬ (ናይጄሪያ – አጥቂ)፡- ግዙፉ አጥቂ ከሚገባው በላይ ውዳሴ እያገኘ የሚገኝ ተጨዋች ነው፡፡ የተጨዋቹ ጥንካሬ እና የሚመታቸው ምቶች አይተነበዬነት ውዳሴ ቢያስገኙለትም የአጨራረስ፣ የቦታ አያያዝ እና የሰውነቱ እንደፈለገው አለመታዘዝ ጥሩ አጥቂ እንዳይሆን አድርገውታል፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1) ፊሊፕ ዳውዝ (ናይጄሪያ – አጥቂ)፡- የቀድሞው የመብራት ኃይል እና ደደቢት አጥቂ አሁንም ለተከላካዮች አስቸጋሪ አጥቂ ቢሆንም እሱም እንደ ሀገሩ ልጅ ሳኑሚ በአቋም መዋዠቅ የሚቸገር ነው፡፡2) ሀኪም አኪንዳ (ናይጄሪያ – አጥቂ)፡- የቀድሞው የአዳማ ከነማ እና ሙገር ሲሚንቶ አጥቂ በንግድ ባንክ ቋሚ ተሰላፊ መሆን አልቻለም፡፡
አዳማ ከነማ 1) ፌቮ ኤማኑኤል (ናይጄሪያ – ግብ ጠባቂ)፡- በጥቂት ዓመታት ውስጥ በርካት ክለቦችን ያካለለው (መብራት ኃይል፣ ውሀ ስራዎች፣ ዳሸን ቢራ እና አዳማ ከነማ) ግብ ጠባቂ ከክለብ ኃላፊዎች ጋር ባለመስማማት የታወቀ ነው፡፡
ሙገር ሲሚንቶ 1) አካካፓ ጌዲዮን (ጋና – አጥቂ)፡- ጋናዊው አጥቂ በሙገር ወጣ ገባ ያለ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡
Continue Reading
1 Comment

1 Comment

  1. mesfin

    February 13, 2015 at 6:16 pm

    No creo que nos Afecta,si no al contrario que nos benificia de Aprender mas futboll y su dinamica de cambios ,si exagerar debemos contratar mas jugadores si queremos ver a nuestros pais que resalta salir de la crisis que esta sometida , Aprendi que futboll Nacio en Inglatera pero se desaroio en todo el mundo que aun reconosco que Ethiopia Aporto mucho al futboll Africano ,pero no emos avansado lo que debiamos Avansar ,por motivos Ovios, no quiero qrgumenta ya no nos sirbe, pienso que lo que estamos Aciendo nos puede server en el future, pongo ejemplo de un pais donde vivo equatorial guine ,ve si un pais deside avansar en futboll si hace lo que tiene que Acer ,en pocos tiempo lo logra

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Articles

የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ተሳትፎ ድህረ ምልከታ

Published

on

Medal Winners

በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በወረቀት ደረጃ ከውድድሩ መጀመር በፊት ቡድኑ ባመዛኙ በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኙ ወጣት አትሌቶችን ስላካተተ ቢያንስ የለመድናቸውን ሁለት ወይም ሶስት የወርቅ ሜዳልያ ድሎች እንደማያሳጣን ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ ሆኖም የሜዳ ላይ ውጤቱ እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ኢትዮጵያ በውጤታማነቷ በምትታወቅበት የአትሌቲክስ ፉክክር በአንድ የወርቅ፣ አንድ የብር፣ እና ሁለት የነሐስ በድምሩ በአራት ሜዳልያዎች ከዓለም 14ኛ ከአፍሪካ 3ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች፡፡ ይህም ሁሌም ለአፍሪካ የበላይነት ከምንፎካከራት ኬንያ ጋር ያለን ልዩነት ይበልጥ እንዲሰፋ አድጎታል፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ሌላኛዋ የምስራቅ አፍሪካ ተቀናቃኛችን እየሆነች ከመጣችው ኡጋንዳም አንሰን እንድንገኝ አድርጎናል፡፡ የቶኪዮ ኦሊምፒክ በአትሌቲክሱ ከ1992ቱ የባርሴሎና ኦሊምፒክ ወዲህ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሜዳልያ ስኬት ያስመዘገበችበትም ሆኖ አልፏል፡፡

አሉታዊ ጎኖች
ቶኪዮ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤታማነት ፈር ቀዳጅ የሆነው ታላቁ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ በ1964 ዓ.ም. በተከታታይ ሁለተኛ የኦሊምፒክ ማራቶን ድሉን የተቀዳጀባት ከተማ ናት፡፡ እናም በቶኪዮ ከተማ በተከናወነው የኦሊምፒክ ውድድር የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የሱን ክብር የሚያጎሉባቸውን ነገሮች ያደርጋሉ ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ የሆኑት ነገሮች ግን በተለይ በቡድኑ አስተዳዳሪዎች በኩል ፍፁም ኃላፊነት የጎደለውና ከጠበቅኩት በተቃራኒው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከአትሌቶች ምርጫ አንስቶ በቡድኑ የዝግጅት ወቅት በተካረረ ውዝግብ ውስጥ ነበር የከረሙት፡፡ የኦሊምፒክ ቡድኑን የማዘጋጀት እና የመምራት የጋራ ኃላፊነት የነበረባቸው ሁለቱ አካላት ይባስ ብለው ውዝግቡን ቶኪዮ ድረስ ይዘውት ሄደዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ሁለቱን አካላት በማቀራረብ በትልቁ ውድድር ላይ ያለንን ተሳትፎ እንከን አልባ ማድግ የሚጠበቅባቸውም ተመልካች ከመሆን የዘለለ ሚና አልነበራቸውም። የውዝግቡ አሉታዊ ትሩፋት በአትሌቶች ስነልቦና እና በአጠቃላይ የቡድኑ ውጤት ላይ የበኩሉን ተፅዕኖ ሳያሳርፍ እንዳላለፈ አያጠራጥርም፡፡

እንደ አለመታደል ሆኖ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያን ልዑካን የመምራት ትልቁ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ኃላፊነት የጎደላቸው ነበሩ። የስፖርቱ አስተዳደሪዎች ትላልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በመጡ ቁጥር በአትሌቶች ምርጫ ዙሪያ የነበረውን ውዝግብ እንዲያቆሙልን እመኝ ነበር። ጭራሽ እራሳቸው ችግር ፈጣሪ ሆነው መገኘታቸው አስደንጋጭ እና አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በመሮጫ መም ወይም በጎዳና ላይ በሚደረጉ ውድድሮች መሸነፍን በስፖርቱ ውስጥ ማሸነፍ እና መሸነፍ ያሉ የነበሩ እና ወደፊትም የሚኖሩ ነገሮች ስለሆኑ በፀጋ መቀበል ይቻላል፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑ የስነልቦና ጥንካሬን ሊፈጥሩላቸው የሚገቡ ኃላፊዎች የእርስ በርስ ሽኩቻ ተቃራኒውን አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳርፍ ማየት ግን ፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ ለነገሩ ከስፖርቱ እድገት ይልቅ የፖለቲካ ግዴታቸው የሚያስጨንቃቸው የስፖርት አመራሮች በበዙባት ሀገር ስፖርቱ እንዲህ የማንም መጫወቻ ሲሆን ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡  

የስፖርት አመራሮች ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ሆነው ትኩረታቸውን ስፖርቱን በማስፋፋቱ እና ማሳደጉ ላይ አድርገው የሚሰሩ ስለስፖርቱም በቂ እውቀት እና ፍቅሩ ያላቸው ቢሆኑ መልካም ነው፡፡ ለቦታው በሚመጥን እና ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት በሚችል የስፖርት አመራር የሚመራ የስፖርት ተቋምን መገንባት በተመሳሳይ ሰዓት የሀገር ግንባታን የሚደግፉ ሶስት ነገሮችን ስኬታማ ያደርጋል፡፡ በስፖርት ጤናውን የሚጠብቅ ማሕበረሰብ በመፍጠር በጤናው ሴክተር ላይ የሚኖረውን ጫና ይቀንሳል፣ በሀገር ገፅታ ግንባታ እና በኢኮኖሚው ዕድገት ላይም የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ በቶኪዮ ላይ የተመለከትናቸው የሀገርን ክብር ዝቅ ያደረጉ ግዴለሽነቶች ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊታዩና አጥፊዎቹ ሊጠየቁበት ይገባል፡፡ በመጪዎቹ ዓመታት በሚጠብቁን ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይም የቶኪዮ ኦሊምፒኩን አይነት ሀፍረት እንዳይገጥመን ከወዲሁ ለችግሮቹ መፍትሔ መፈለግ አለበት፡፡

ባለፉት ዓመታት ኦሊምፒክ በመጣ ቁጥር በልዑካን ቡድኑ ውስጥ እየተካተቱ በሕዝብ ገንዘብ የሚዝናኑት የኦሊምፒክ ቱሪስቶች ጉዳይ ዘንድሮም ያልተቀረፈ ችግር ሆኖ ተስተውሏል፡፡ ከሌላው ግዜ በተለየ መልኩ ተጠባባቂ አትሌቶችን ይዞ መጓዝ ይጠይቅ በነበረው ውድድር ላይ አትሌቶቹን ትቶ ምንም የማይሰሩ ሰዎችን ይዞ መሄድ ትልቅ ቀልድ ነው፡፡  

ከሜዳ ውጭ የነበረው ውዝግብ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል የነበረ መሆኑ በሜዳ ላይ የነበሩብንን ድክመቶች ሊያስረሳንም አይገባም፡፡ ስድስት የጎዳና ላይ ተወዳደሪዎቻችን እና አንድ የመም ተወዳዳሪ ውድድራቸውን ማቋረጣቸው በቶኪዮ ከታዩት ደካማ ጎኖቻችን መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ ችግሩ በዚህ ምክንያት ነው የተከሰተው ብሎ ለይቶ ለመናገር ባይቻልም ብዙ ግዜ ሲፈትነን ለሚስተዋለው የሞቃታማ ቦታ ውድድር የምናደርጋቸው ዝግጅቶችን መለስ ብሎ መመልከትን የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ የተጎዳች አትሌትን ወደውድድር እንድትገባ ማድረግ እና በሁለት ደቂቃ ውስጥ ለማቋረጥ መገደዷም የአትሌቶች የጤና ክትትል ላይ ክፍተት እንዳለ የጠቆመን ክስተት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ወደውድድር ስፍራው ካቀናበት ግዜ ጀምሮ በቶኪዮ ምንም አይነት ቡድኑን የተመለከቱ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ወይም ፕሬስ ሪሊዞች አልነበሩም፡፡ ይህም እንደተለመደው የሕብረተሰቡን እና የመገናኛ ብዙሀንን ስለቡድኑ ቀጥተኛ መረጃ የማግኘት መብት የገደበ ነበር፡፡ ጋዜጠኞችም ሚዛናዊ ሆኖ ከመዘገብ ይልቅ ጎራ ለይተው ቃላት መወራወራቸው የህዝብን ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት የነፈገ ነው፡፡ 

አዎንታዊ ጎኖች
ሰለሞን ባረጋ በወንዶች 10,000 ሜትር ወርቅ፣ ለሜቻ ግርማ በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ብር፣ ጉዳፍ ፀጋዬ በሴቶች 5000 ሜትር ነሐስ፣ እና ለተሰንበት ግደይ በሴቶች 10,000 ሜትር ነሐስ ማስመዝገብ መቻላቸው የሚደነቅ ስኬት ነው፡፡

የመጪው ትውልድ አካል የሆኑት ተስፈኞቹ መቅደስ አበበ፣ ፍሬወይኒ ሀይሉ፣ በሪሁ አረጋዊ እና ጌትነት ዋለን ጨምሮ አምስት አትሌቶች ለሜዳሊያ የቀረበ የአራተኛነት ደረጃን ይዘው ማጠናቀቅ መቻላቸውም መልካም ነው፡፡ በተለይ ወጣቶቹ ያስመዘገቡት ውጤት በመጪዎቹ ዓመታት ተገቢውን ድጋፍ ካገኙ የምንጓጓለትን ድል ሊያስገኙልን እንደሚችሉ ያመላከተን ነው፡፡

የሀብታም አለሙ በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በሴቶች 800 ሜትር ለመጀመሪያ ግዜ ለፍፃሜ ተወዳዳሪነት መብቃት ምንም እንኳ በፍፃሜው የሜዳልያ ድል ባይቀናትም በአዎንታዊ ጎን ሊጠቀስ የሚችል ስኬት ነው፡፡

ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃን ይዘው ላጠናቀቁ አትሌቶች በሚሰጥ ነጥብ ድምር መሰረት በወጣው የነጥብ (ፕሌስመንት) ደረጃ ሰንጠረዥ ላይ በ64 ነጥብ ዘጠነኛ ሆነን ማጠናቀቃችንም እሰየው የሚያስብል ነው፡፡

በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከአራተኛ እስከ ስምንተኛ ባሉት ደረጃዎች ውስጥ አጠናቀው ነጥብ ያስገኙ እና የዲፕሎማ ተሸላሚ የሆኑት አትሌቶች፡-
4ኛ – ፍሬወይኒ ሀይሉ – በሴቶች 1500 ሜትር
4ኛ – መቅደስ አበበ – በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል
4ኛ – ሮዛ ደረጀ – በሴቶች ማራቶን
4ኛ – በሪሁ አረጋዊ – በወንዶች 10,000 ሜትር
4ኛ – ጌትነት ዋለ – በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል
5ኛ – እጅጋየሁ ታዬ – በሴቶች 5000 ሜትር
6ኛ – ሀብታም አለሙ – በሴቶች 800 ሜትር
6ኛ – ሰንበሬ ተፈሪ – በሴቶች 5000 ሜትር
8ኛ – ዮሚፍ ቀጄልቻ – በወንዶች 10,000 ሜትር
8ኛ – ዘርፌ ወንድማገኝ – በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል

  • የአትሌቲክስ የነጥብ ደረጃ ሰንጠረዥ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ባሉት ደረጃዎች ውስጥ የሚያጠናቅቁ አትሌቶች በሚያስመዘግቡት ነጥብ ድምር መሰረት የሚወጣ ሲሆን የነጥብ አሰጣጡም ለአንደኛ ደረጃ 8 ነጥብ፣ ለሁለተኛ ደረጃ 7 ነጥብ፣ ለሶስተኛ ደረጃ 6 ነጥብ፣ ለአራተኛ ደረጃ 5 ነጥብ፣ ለአምስተኛ ደረጃ 4 ነጥብ፣ ለስድስተኛ ደረጃ 3 ነጥብ፣ ለሰባተኛ ደረጃ 2 ነጥብ፣ እና ለስምንተኛ ደረጃ 1 ነጥብ ነው።

ከፊታችን ምን  እየጠበቀን ነው? ምንስ እናድርግ?
ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፉ ወረርሺኝ ምክንያት ትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለሌላ ግዜ እንዲተላለፉ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ሌላ አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ቀጣዮቹ አራት ዓመታት በተከታታይ በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች የሚካሄዱባቸው ይሆናሉ፡፡ በ2022 የዓለም ሻምፒዮና፣ በ2023 የዓለም ሻምፒዮና፣ በ2024 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች፣ እና በ2025 የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ይኖራሉ፡፡ በቀጣዩ ዓመት በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ከሐምሌ 8 – 17/2014 በዩናይትድ ስቴትስ ኦሪጎን የሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዘጋጆች ሙሉ የውድድሩን ፕሮግራም፣ የማራቶን እና የእርምጃ ውድድሮች የሚካሄዱባቸውን ቦታዎች በትላንትናው ዕለት ይፋ አድርገዋል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናውን ውድድር በኃላፊነት የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ከወዲሁ ለዛ ውድድር ተሳትፎ የሚጠበቅበትን አቅዶ መንቀሳቀስ ይኖበርታል፡፡

ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጭቅጭቆችን ለማስቀረት ከወዲሁ ሁሉም አትሌቶች አውቀውት በውስጡ የሚያልፉበትን ገዢ የሆነ የመምረጫ መስፈርት ማዘጋጀት ቀዳሚው ተግባር መሆን አለበት፡፡ የመምረጫ መስፈርት ሁልግዜም በግላዊ ምልከታ እና ፍላጎቶች ላይ በሚመሰረት ምክንያት አነጋጋሪ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ቢሆንም ባለድርሻ አካላቱን በሙሉ ባሳተፈ መልኩ ውይይት ተደርጎበት ቢወጣ ሁሉንም ገዢ እና ከጭቅጭቅ የፀዳ ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህ ላይ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከተከሰቱት ሁኔታዎች አንፃር የሌሎች ሀገሮችንም ተሞክሮዎች በመዳሰስ ነገሩን ሰፋ አድርጎ መመልከት ቢቻል ጥሩ ነው፡፡ ትልልቅ ውድድሮች በመጡ ቁጥር በተደጋጋሚ እንደታዘብነው አንዳንድ አትሌቶች በቡድኑ ውስጥ ለመካተት የሚያደርጉትን ተገቢ ያልሆነ ሙከራም ማቆም አለባቸው፡፡ ከፋም ለማም ስፖርቱን እንዲመራ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም የሚያወጣቸውን መስፈርቶች ማክበርና በዛ ውስጥ ተመራጭ ለመሆን መሞከር ግድ እንደሚላቸውም መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ማኔጀሮች እና አሰልጣኞች በተለይ በማራቶን የራሳቸውን አትሌት ለማስመረጥ የሚያደርጓቸው አላስፈላጊ ግፊቶችም ሊያቆሙ ይገባል፡፡

ለውድድሮች የምናደርጋቸውን ዝግጅቶች ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ከውድድሮች በኋላ መገምገም እና መታረም ያለባቸው ነገሮች ካሉ ማረም፡፡ ከፍተኛ ሙቀት በነበረባቸው በለንደን 2012 ኦሊምፒክ ሶስቱም የወንዶች ማራቶን ተወዳዳሪዎቻችን፣ በሞስኮ 2013 የዓለም ሻምፒዮና ሁለቱ የሴቶች ማራቶን ተወዳዳሪዎቻችን፣ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ አምስት የማራቶን (ሶስቱም ወንዶች እና ሁለት ሴቶች) ተወዳዳሪዎቻችን እንዲሁም የሴቶች እርምጃ ተወዳዳሪያችን ለማቋረጥ መገደዳቸውን አስተውለናል፡፡ ስለዚህ በጎዳና ላይ ውድድሮች ከባድ ሙቀት ለሚኖርባቸው ቦታዎች እንዴት መዘጋጀት አለብን የሚለው ጉዳይም በደንብ ሊታይ የሚገባው ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ የመም (ትራክ) ተወዳዳሪ አትሌቶቻችን የውድድር ዓመቱ ሲጀምር ድንቅ ብቃታቸውን ያሳዩን እና ወደትልቅ ውድድር ሲቃረቡ አቋማቸው እየወረደ ይመጣል፡፡ አሰልጣኞቻቸው ለእነዚህ አይነቶቹ አትሌቶች ወደትልቅ ውድድር ሲቃረቡ ብቃታቸውን እያሳደጉ እንዲሄዱ የሚረዳቸውን የልምምድ ፕሮግራም ቢያዘጋጁላቸው መልካም ነው፡፡ በመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ላይ በተለይ በወንዶች አሁንም በከፍተኛ ደረጃ የሚፎካከሩ አትሌቶችን ለማፍራት ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል፡፡

Continue Reading

Articles

የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የቶኪዮ ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ማጣሪያ ውድድሮች የመጀመሪያ ሁለት ቀናት

Published

on

በሴቶች 5000 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ላይ የሚፎካከሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች

በቶኪዮ ኦሊምፒክ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት የኢትዮጵያ አትሌቶች የተሳተፉባቸው የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል፣ 800 ሜትር በሁለቱም ፆታዎች፣ እንዲሁም የሴቶች 5000 ሜትር ማጣሪያዎች ሌላኛዎቹ የኢትዮጵያውያን የትኩረት ማዕከል የነበሩ ውድድሮች ናቸው፡፡ ቀጣዩ ዘገባ የኢትዮጵያውያኑን የማጣሪያ ውድድሮች ተሳትፎ እና ውጤቶች አንዲሁም ተጨማሪ መረጃዎችን ይዟል፡፡

የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል

በአትሌቲክስ ውድድሩ የመክፈቻ ቀን (ዓርብ ሐምሌ 23/2013) ጠዋት ላይ በተካሄደው የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ማጣሪያ ከተሳተፉት ሶስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ከምድብ አንድ ለሜቻ ግርማ (8፡09.83) በአንደኛነት፣ ከምድብ ሁለት ጌትነት ዋለ (8፡12.55) በሁለተኛነት ለፍፃሜው ሲያልፉ በምድብ ሶስት የተወዳደረው ታደሰ ታከለ (8፡24.69) ስምንተኛ ወጥቶ ለፍፃሜው ሳያልፍ ቀርቷል፡፡ ለሜቻ ጃፓናዊው ሚዩራ ዩጂን እና ኬንያዊው ቤንጃሚን ኪይገንን በማስከተል ከምድቡ ያሸነፈበት 8:09.83 በኦሊምፒክ የማጣሪያ ውድድሮች ላይ የተመዘገበ የምንግዜውም ፈጣን ሰዓት ሆኗል፡፡ የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል የፍፃሜ የሜዳልያ ፉክክር በዋናነት በኬንያውኑ ቤንጃሚን ኪገን እና አብራሀም ኪቢዎት፣ በኢትዮጵያውያኑ ለሜቻ ግርማ እና ጌትነት ዋለ እንዲሁም በሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ መካከል እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል በ1980ው የሞስኮ ኦሊምፒክ በሻምበል እሸቱ ቱራ አማካይነት ካስመዘገበችው የነሐስ ሜልያ ድል ወዲህ በርቀቱ በወንዶች ምንም አይነት የኦሊምፒክ ሜዳልያ ድል የላትም፡፡ ሆኖም ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየታዩ የመጡ መሻሻሎች እና በዶሀው የዓለም ሻምፒዮና ላይ የተመዘገበው የብር ሜዳልያ ድል በቶኪዮም ሌላ ሜዳልያን ተስፋ እንድናደርግ ያነሳሳን ሆኗል፡፡ ዘግይቶ የተሰላፊ አትሌቶች ለውጥ ከተደረገባቸው ርቀቶች አንዱ በሆነው የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል በተጠባባቂነት የተመዘገበውና በዋናነት በ5000 ሜትር እንደሚወዳደር ይጠበቅ የነበረው ጌትነት ዋለ ወደመጀመሪያ ተሰላፊነት የመጣ ሲሆን ኃይለማሪም አማረ በመጨረሻ ሰዓት በለሜቻ ግርማ መተካቱም አነጋጋሪ የሆነ ሌላኛው ለውጥ ነው፡፡ ጌትነት በ3000 ሜትር መሰናክልም ጠንካራ ተፎካካሪ አትሌት ሲሆን በዶሀ የዓለም ሻምፒዮና ላይ አራተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ በፍፃሜው ውድድር በ2019 የርቀቱ የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮን ጌትነት ዋለ እና በወቅቱ የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊስት ለሜቻ ግርማ የሚወከለው የኢትዮጵያ ቡድን በቶኪዮ የኬንያውያኑን የበላይነት ለመግታትና አዲስ የስኬት ታሪክ ለማፃፍ እንደሚበቃ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡                     

በ1984 በሎስ አንጀለስ ከተከናወነው የኦሊምፒክ ውድድር አንስቶ በተከታታይ በዘጠኝ የኦሊምፒክ ውድድሮች ወይም ላለፉት 36 ዓመታት የኦሊምፒክ የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል የወርቅ ሜዳልያ ድል በኬንያውያን ቁጥጥር ስር ይገኛል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናም ተመሳሳይ የበላይነት ያላቸው ኬንያውያን ከ17 የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች በ14ቱ የወርቅ ሜዳልያው አሸናፊዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ከሁለት ዓመት በፊት በዶሀው የዓለም ሻምፒዮና ላይ ከኢትዮጵያውያን እና ከሞሮኮ አትሌቶች የገጠማቸው ተግዳሮት ለመሸነፍ እጅግ አቅርቧቸው የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ በአንድ ማይክሮ ሰከንድ ልዩነት አሸናፊነታቸውን ባረጋገጡበት በዶሀው ውድድር የተፈታተኗቸው ኢትዮጵያዊው ለሜቻ ግርማ እና ሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ በቶኪዮው ፍፃሜ ለሌላ ብርቱ ፉክክር እየጠበቋቸው ይገኛሉ፡፡ ባለፉት ሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች በቅደም ተከተል የብር እና የነሐስ ሜዳልያን ያገኘው ሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ በቶኪዮ ከሚወዳደሩት በሙሉ የላቀና 7፡58.15 የሆነ የራሱ ምርጥ ሰዓት ያለው ነው፡፡

ኬንያ በቶኪዮ ያለፈው ውድድር ሻምፒዮንነቱን ክብር የሚያስጠብቅላትን አትሌት ይዛ መቅረብ ሳትችል ቀርታለች፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት በሪዮ የኦሊምፒክ እንዲሁም ከሁለት ዓመት በፊት በዶሀ የዓለም ሻምፒዮን የሆነው ኮንሰስለስ ኪፕሩቶ ባለፈው ወር በኬንያ የኦሊምፒክ ምርጫ ውድድር ላይ ውድድሩን ባለማጠናቀቁ የኦሊምፒክ ሻምፒዮንነት ክብሩን ለማስጠበቅ በቶኪዮ አልተገኘም፡፡ ስለዚህ አሁን የረጅም ግዜ የበላይነታቸውን የማስጠበቅ ኃላፊነቱ በ2019ኙ የዶሀ የዓለም ሻምፒዮና ላይ በቅደም ተከተል ስድስተኛ እና ሰባተኛ ሆነው ባጠናቀቁት ቤንጃሚን ኪገን እና አብራሀም ኪቢዎት ላይ ወድቋል፡፡  

የሴቶች 800 ሜትር

ከአትሌቲክሱ የጀመሪያ ቀን የጠዋት መርሀግብሮች አንዱ በነበረው የሴቶች 800 ሜትር ማጣሪያ በምድብ ሶስት በአሜሪካዊቷ አቲንግ ሙ ተቀድማ በ2 ደቂቃ ከ01.20 ሰከንድ ሁለተኛ የወጣችው ሀብታም አለሙ ለግማሽ ፍፃሜው ያለፈች ሲሆን በሁለተኛው ቀን ምሽት ላይ በተካሄደው የግማሽ ፍፃሜ ውድድር ላይም በአሜሪካዊቷ አቲንግ ሙ ተቀድማ በ1:58.40 ሁለተኛ በመሆን በኦሊምፒክ የውድድር ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ በርቀቱ ለፍፃሜ ውድድር የበቃች ኢትዮጵያዊት ሆናለች፡፡ ሀብታም ከውድድሩ በኋላ በቶኪዮ ለሚገኘው ባልደረባችን አብይ ወንድይፍራው በሰጠችው አጭር ቃል ‹‹ውድድሩ ትንሽ ፈታኝ ነበር ነገር ግን ለሀገሬ ስል ያለኝን አቅም ሁሉ ተጠቅሜያለሁ፡፡ ክብሩ ይስፋ ለመድኃኒዓለም በመጨረሻም አሪፍ ውጤት ላይ ደርሻለሁ፡፡ ለኦሊምፒክ የፍፃሜ ውድድር ሳልፍ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም ከኢትዮጵያ ለፍፃሜ የደረሰ ያለ አይመስለኝም እና አሁንም መጨረሻዬን ያሳምርልኝ ነው የምለው›› ብላለች፡፡  

በሴቶች 800 ሜትር የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ በምድብ አራት በ2.01.98 አራተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ነፃነት ደስታ ወደ ግማሽ ፍፃሜው መቀላቀል ሳትችል ስትቀር በጀማሪዎች ስም ዝርዝር ላይ ስሟ ተካቶ በምድብ አንድ እንደምትሮጥ ስትጠበቅ የነበረችው ወርቅውሀ ጌታቸው ግልፅ ባልተደረገ ምክንያት ውድድሩን ሳትጀምር ቀርታለች፡፡

የወንዶ 800 ሜትር

የወንዶች 800 ሜትር የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ላይ የተሳተፈው ኢትዮጵያዊው መለሰ ንብረት ከምድብ ሶስት በ1:47.80 ሰባተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ለግማሽ ፍፃሜው ማለፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡ በመሐመድ አማን ስኬቶች በመነቃቃት ላይ የነበረው የወንዶች 800 ሜትር ከቅርብ ግዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ሶስት ሰዓት የሚያሟሉ ተወካይ አትሌቶችን ለማግኘት እየተቸገረችበት የምትገኝ ርቀት እንደሆነ እየታየ ነው፡፡ የኦሊምፒክ ሚኒማ ማሟላት የቻለ አንድ አትሌት ብቻ ይዘን የቀረብንበት የቶኪዮ ኦሊምፒክም ይህ ችግር እንዳልተቀረፈ የታየበት ሌላኛው አጋጣሚ ሆኗል፡፡  

የሴቶች 5000 ሜትር ማጣሪያ

በአትሌቲክሱ የመጀመሪያ ቀን ሐምሌ 23/2013 ምሽት ላይ በተደረት የሴቶች 5000 ሜትር ማጣሪያ ላይ የተሳተፉት ሶስቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሐምሌ 26/2013 ምሽት ላይ ለሚደረገው የፍፃሜ ውድድር አልፈዋል፡፡ ከምድብ አንድ ሰንበሬ ተፈሪ (14፡48.31) እና እጅጋየሁ ታዬ (14፡48.52) የኔዘርላንዷ ሲፋን ሀሳን (14፡47.89) እና ኬንያዊቷ አግነስ (14፡48.01) ቲሮፕን ተከትለው በቅደም ተከተል ሶተኛ እና አራተኛ ሆነው ሲያልፉ ከምድብ ሁለት ጉዳፍ ፀጋዬ (14፡55.74) ኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪ (14፡55.77) አስከትላ በአንደኛነት አልፋለች፡፡


ሐምሌ 26/2013 ምሽት ላይ በሚደረገው የሴቶች 5000 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ላይ የሚፎካከሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች

በሄንግሎ በተከናወነው የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ምርጫ ውድድር ላይ ባስመዘገበችው የራሷ ምርጥ 14:13.32 የርቀቱ የወቅቱ ፈጣን አትሌት ሆና ወደ ቶኪዮ ያቀናችው ጉዳፍ ለወርቅ ሜዳልያ ድል ከሚጠበቁት መካከል ናት፡፡ በሄንግሎው ውድድር ላይ ጉዳፍን በመከተል በቅደም ተከተል 14:14.09 እና 14፡15.24 በሆነ ሰዓት የጨረሱት እጅጋየሁ እና ሰንበሬም በዓለም የምንግዜም ምርጥ ዝርዝር ውስጥ የስድስተኛ እና ሰባተኛ ደረጃን ለመያዝ የበቁ ጠንካራ አትሌቶች ናቸው፡፡ የቶኪዮ ኦሊምፒክ የሴቶች 5000 ሜትር ተወዳዳሪዎች ዝርዝር ሶስቱን ኢትዮጵያውያን ጨምሮ ከዓለም የምንግዜም ምርጥ አስር የርቀቱ ሯጮች አምስቱን ያካተተ ነው፡፡ ኬንያውያኑ ሄለን ኦቢሪ እና አግነስ ቲሮፕ ከምንግዜም ምርጥ አስሮቹ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆኑ በ12ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሀሳንም የቶኪዮውን የፍፃሜ ፉክክር በጉጉት እንዲጠበቅ የምታደርግ ብርቱ አትሌት ናት፡፡

Continue Reading

Articles

ሰለሞን ባረጋ ለአስራ ሶስት ዓመት የራቀንን የወንዶች 10,000 ሜትር ድል በቶኪዮ ወደ ኢትዮጵያ መልሶታል

Published

on

218076583_1010892909482678_1235421043554241523_n

በቶኪዮ ኦሊምፒክ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአትሌቲክስ ውድድር በተጀመረ በሁለተኛው ቀን በወንዶች አስር ሺህ ሜትር ኢትዮጵያውያንን እጅግ ያስደስተው ድል በወጣቱ ሰለሞን ባረጋ አማካይነት ተመዝግቧል፡፡   
በ1980 ሞስኮ ላይ ምሩፅ ይፍጠር በርቀቱ ለመጀመሪያ ግዜ የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ካስገኘ በኋላ ከተደረጉት አስር የኦሊምፒክ የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ውድድሮች ኢትዮጵያ አምስቱን በበላይነት ለመጨረስ ችላለች፡፡ የርቀቱ ንጉሶች ሀይሌ ገብረስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ከ1992 እስከ 2008 ዓ.ም. በአራት ተከታታይ የኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ በማሸነፍ የርቀቱ የወርቅ ድል ለኢትዮጵያ ብቻ የተሰጠ እንዲመስለን አድርገውንም ነበር፡፡ ከ2008ቱ የቤይጂንግ ኦሊምፒክ የቀነኒሳ በቀለ ድል በኋላ በተከሰተው የሞ ፋራህ የበላይነት ምክንያት ተመሳሳዩን ድል በቶኪዮ ለማየት 13 ዓመታትን መጠበቅ ግድ ብሎናል፡፡ ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት በጉጉት ስንጠብቀው የቆየነውን የ10 ሺህ ሜትር የኦሊምፒክ ድል በመጨረሻም ሰለሞን ባረጋ በቶኪዮ አጎናፅፎናል፡፡ የሰለሞን የቶኪዮ የወርቅ ሜዳልያ ድል ኢትዮጵያ ካለፉት አስራ አንድ ኦሊምፒኮች በርቀቱ ለስድስተኛ ግዜ የበላይ ሆና እንድትጨርስ ያስቻለም ነው፡፡ ድሉ በቶኪዮ የአትሌቲኪስ ውድድሮች የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳልያ ድል ሆኖም ተመዝግቧል፡፡ ሰለሞን ባረጋ በ2018 የበርሚንግሀም የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር በ3000 ሜትር እና በ2019 የዶሀ ዓለም ሻምፒዮና ላይ በ5000 ሜትር የብር ሜዳልያ ካገኘ በኋላ በመጀመሪያ የኦሊምፒክ ተሳትፎው ከፍተኛ ክብር የሚሰጠውን የ10,000 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ድል ለማሳካት በቅቷል፡፡

‹‹የ200 ሜትር እና 400 ሜትር አጫጨር የፍጥነት ሩጫ ልምምዶችን ስሰራ ስለነበረ ሁለት ዙር ሲቀር ውድድሩን እንደማሸንፍ ለራሴ ነገርኩት››
ሰለሞን ባረጋ ከቶኪዮው ድል በኋላ

ሰለሞን ባረጋ ከቶኪዮው ድሉ በኋላ በስፍራው ከሚገኘው የስራ ባልደረባችን አብይ ወንድይፍራው ጋር ባደረገው አጭር ቃለ ምልልስ የሚከተለውን ብሏል ‹‹ረጅም ርቀት የእኛ ስፖርት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ሆኖም በኦሊምፒክ ውድድር ላይ ወርቅ ሜዳልያ ከወሰድን ብዙ ግዜ አልፎናል፡፡ ይህን ነገር ለመጨረሻ ግዜ ያሳካውም ቀነኒሳ ነበረ፡፡ ዛሬ በቶኪዮ ድሉን በማሳካቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በተለይ ለእኛ ከቶኪዮ ጋር አበበ ቢቂላን የምናስታውስበት ድል ስለሆነ ያንን በማሳካቴም በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ዘንድሮ ከኡጋንዳ የዓለም ሪኮርድ የሰበረው ቼፕቴጌይ እና የዓመቱን ፈጣን ሰዓት የሮጠው ኪፕሊሞ ነበሩ፡፡ እናም ውድድሩ በጣም ይፈጥናል ብዬ ነበር የጠበቅኩት ግን አልተሮጠም፡፡ ውድድሩን የጨረስነውም 27 ቤት ነው፡፡ የ200 ሜትር እና 400 ሜትር አጫጨር የፍጥነት ሩጫ ልምምዶችን ስሰራ ስለነበረ ሁለት ዙር ሲቀር ውድድሩን እንደማሸንፍ ለራሴ ነገርኩት፡፡ ኡጋንዳውያኑ አትሌቶች ዛሬ ብዙም አልታገሉም፡፡ አብዛኛውን ሰዓት ከኋላ ነው የቆዩት እና እንደዚህ ይሆናል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፡፡ እነርሱን ካሜራ ላይም እያየኋቸው ስለነበር ስለነሱ ብዙም አልተጨነቅኩም እንደውም ከእነሱ ይልቅ የእኛን ልጆች ነበረ ይወጣሉ ብዬ የጠበቅኩት፡፡ በውድድሩ መሀል ተጠባቂ የሆኑት ኡጋንዳውያን ወደኋላ ቀርተው ሶስተኛው የቡድን አጋራቸው ወደፊት ወጥቶ በሰፊ ልዩነት ሲመራ እኛ እነሱን ስንጠብቅ እሱ አዘናግቶ እንዳያሸንፍ ልዩነቱን ለማጥበብ ሞክሬያለሁ፡፡ ምናልባት እነሱ እኛን ሲጠብቁ አንተ ሂድ ያሉት ነበር የመሰለኝ፡፡ ከዚህ በፊት በእንደዚህ አይነቱ ነገር ዳይመንድ ሊግ ላይ ስለተሸወድኩኝ ያንን እንዳይደግሙ ብዬ ነበረ ልዩነቱን ለማጥበብ የሞከርኩት፡፡ የአሰልጣኜንም ምክር እየሰማሁ ስለነበረ የምሮጠው እና ወደኋላ ተመለስ እያለኝ ስለነበር ወደኋላ ተመልሻለሁ፡፡ የእነርሱ እስትራቴጂ እሱን ወደፊት እንዲወጣ አድርገው እኛን ለማድከም ነበረ፡፡ ከበሪሁን ጋር ስንነጋገር ወደፊት ጠጋ በል እያልኩት ነበረ፡፡ ከበሪሁን ጋር ልምምድም አብረን ነበረ የምንሰራው፡፡ እኔ እንደውም ከአንድ እስከ ሶስት እንወጣለን ብዬ ነበር የጠበቅኩት አጋጣሚ ሆኖ አልተሳካም ነገር ግን ወርቁን ወደኢትዮጵያ በመመለሳችን በጣም ደስተኛ ነን፡፡›› ብሏል፡፡

Continue Reading

Trending