Connect with us

Uncategorized

የኢትዮጵያ ሙስሊም ፈተና በ224 ደቂቃዎች

Published

on

Ethiopian Muslim Leaders Convicted 3

የኢትዮጵያ ሙስሊም ፈተና በ224 ደቂቃዎች

በዘላለም ክብረት

ክፍሉ ከኮሪደሩ ላይ ከተንጠለጠለ አምፖል በሚመጣ ብርሃን ፈገግ ብሏል፡፡ እኔም ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ ወደክፍሉ ስገባ ከክፍሉ አንደኛው ጫፍ ላይ አንድ ቀጠን ያለ ሰው ድምፁን በትንሹ ከፍ አድርጎ ቁርዓን ‹እየቀራ› ነበር፡፡በክፍሉ ሌላኛው ጫፍ ላይ ደግሞ አንድ ፍራሽ፣ አንድ የውሃ ጀሪካን እና ትንሽ ልብሶች በፌስታል ውስጥተቀምጠዋል፡፡ በሌላኛው የክፍሉ ጫፍ ደግሞ የሽንት ባልዲ – ሽታውን ለመቀነስ ሲባል በግማሽ ውሃ ተሞልቶተቀምጧል፡፡ ክፍሉ ውስጥ እንደገባሁ አንዱ ጫፍ ላይ ትንሽ ቆም ካልኩ በኋላ በክፍሉ ውስጥ ያገኝሁት ብቸኛውሰው ፍራሹ ላይ እንድቀመጥ በእጁ ሲጠቁመኝ ቁጭ አልኩ፡፡ ፍራሽ ላይ እንደተቀመጥኩ በፍራሹ ጫፍ ላይ የጆንግሪሻም ‘The Last Juror’ መፅሃፍ ተቀምጦ አየሁት፤ አንስቼ ስመለከተው ክፍሉ ውስጥ ያገኘሁት ሰው ቁርዓንመቅራቱን ጨርሶ እንግሊዝኛ እችል እንደሆነ ጠይቆኝ ማውራት ጀመረ፡፡ ስሙ ሐሰን ጃርሶ እንደሚባል ነግሮኝ፤በመፅሃፍ እጥረት ምክንያት ይሄን መፅሃፍ ለአምስተኛ ጊዜ እያነበበው እንደሆነም አጫወተኝ፡፡ መፅሃፉን ቃሊቲ እስርቤት በታሰረበት ወቅት እስክንድር ነጋ እንደሰጠውም ነገረኝ፡፡ እኔም ለምን እንደታሰርኩ እንደማላውቅ ነግሬው እሱለምን እንደታሰረ ስጠይቀው በዜግነቱ ኬኒያዊ፣ የቀድሞ የዓልሸባብ ወታደር እንደነበርና አሁን የ17 ዓመት ፍርደኛ ሆኖከቃሊቲ የከፍተኛ ጥበቃ እስር ቤት ከጥቂት ሰዓታት በፊት ተዘዋውሮ እንደመጣ ነገረኝ፡፡ ይህ ሚያዚያ 17/2006 የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) በገባሁበት ወቅት የገጠመኝ ጉዳይ ነው፡፡
ስለ ሐሰን ጃርሶ ከመታሰሬ በፊት አንድ ሰሞን ከአዲስ ዘመን እስከ ኢቴቪ የተቀባበሉት ጉዳይ ነበርና ሁኔታዎቹን ሲተርክልኝ ትንሽ ነገር በጊዜው ማስታወስ ችዬ ነበር፡፡
የቀድሞው ኢቴቪ የአሁኑ ኢቢሲ ‹እስልምና› እና ‹ሽብርተኝነትን› አስመልክቶ በተለይም በአለፉት አራት ዓመታት የተለያዩ ‹ዘጋቢ ፊልሞችን (documentaries)› ያቀረበ ሲሆን፤ እኔም ለአጭር ጊዜ በታሰርኩበት ወቅት ‹በዘጋቢ ፊልሞቹ› ውስጥ የተጠቀሱትን ግለሰቦችና ቡድኖች የማግኘትና በጉዳዩ ላይ የመነጋገር ዕድል አጋጥሞኝ ስለነበር ይሄን አጋጣሚ በብሔራዊ ቴሌቪዥኑ ‹እስልምና› እና ‹ሽብርተኝነትን› አስመልክቶ ከቀረቡ አምስት የተለያዩ ‹ዘጋቢ ፊልሞች› (አዲስ ግንባር፣ ጅሃዳዊ ሐረካት፣ ሐዘን ለመድረስ … ጉዞ ወደ ደሴ፣ የጥፋት መልዕክተኞች እና የማንቂያ ደወል) ጋር አያይዞ ማየት የዘጋቢ ፊልሞቹን ዓላማና የሙስሊሙን ፈተና ያሳየን ይሆናል በሚል ሐሳብ ነው ይሄን ፅሁፍ መፃፌ፡፡
ያለፉት አምስት ዓመታት በማሕበረሰብ ደረጃ ትልቅ ፈተና ከገጠማቸው ኢትዮያዊያን መካከል ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ጎልተው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ፈተናው በዋነኛነት ከመንግስት በኩል የመጣ ሲሆን፤ ይሄን ተከትሎም የውስጥ ስነ መለኮታዊ እሰጥ አገባው ሙስሊሙን እጅግ ፈተና ውስጥ እንዲዘፈቅ አድርጎታል፡፡ በተለይም በታሕሳስ 2004 ገንፍሎ አደባባይ የወጣው የሙስሊሙ የመብት ጥያቄን ተከትሎ በተለያዩ አቅጣጫዎች ፈተናው የጨመረ ሲሆን መንግስት ጉዳዩ የመብት ጥያቄ ነው ብሎ ከመቀበል ይልቅ ‹የሽብርተኞች ስራ› ነው በማለት የመብቱን ጠያቂዎች የተለያዩ ስያሜዎች በመስጠት ጥያቄዎቹን አልቀበልም በማለት ቀጥሏል፡፡ ከዚህ እምቢተኝነት ጋር ተያይዞም መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ዘጋቢ ፊልሞች በብሔራዊ ቴሌቪዥኑ በማስተላለፍ የፕሮፓጋንዳ ቀዳሚነቱን ለመያዝ አሁን ድረስ እየደከመ ይገኛል፡፡ ፕሮፓጋንዳውን በዋነኛነት እየመራው የሚገኝው ደግሞ መንግታዊው ቴሌቪዥን ነው፡፡
መንግስታዊው ቴሌቪዥን ባለፉት አመስት ዓመታት ‹እስልምና› እና ‹ሽብርተኝነትን› አስመልክቶ ካቀረባቸው ዘጋቢ ፊልሞች መካከል ቀዳሚው በመግቢያዬ የጠቀስኩት ‹አዲስ ግንባር› የተባለው ዘጋቢ ፊልም ነው፡፡ የፊልሙ ዋነኛ ማጠንጠኛም አሸባሪው አል ሸባብ ኢትዮጵያ ውስጥ የራሱን ሕዋስ (cell) ለመዘርጋት ያደረገውን ጥረት የሚያሳይ ነው፡፡ ይሄን ድርጊት ተከትሎም ነው በጊዜው ጠ/ሚኒስትር የነበሩት መለስ ዜናዊ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የአልቃይዳ ሕዋስ ተገኝቷል፡፡ የዚህ ሴል አባላት ሁሉም ሰለፊ ናቸው›› በማለት ነበር ፓርላማ ቀርበው ንግግር ያደረጉት፡፡ የሕዋሱ አመራር እንደሆነ በዘጋቢ ፊልሙ የተገለፀው ኬኒያዊው ሐሰን ጃርሶ ለፍርድ ቤትም ሆነ እኔ ማዕከላዊ ባገኝሁት ወቅት እንደነገረኝ የዘጋቢ ፊልሙን ድምፀት (tone) ከመጠራጠር በቀር የአል ሸባብ አባል እንደሆነ እሱም አይክድም፡፡ ሐሰን እጅግ ብዙ ለመስማት የሚከብዱ ሁኔታዎችን እንዳለፈ የገለፀልኝ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ በቁጥር የሚበዛው ሙስሊም ነው ከሚል የራሱ እምነት ተነስቶ እዚህ መምጣቱን ገልፆልኛል፡፡ ከዚህ ባለፈ ሐሰንም ሆነ ድርጅቱ አል ሸባብ ስለ ኢትዮጵያ ብዙም የጠለቀ ግንዛቤ አላቸው ለማለት በማያስችል ሁኔታ መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን ለማየት ፍላጎቱ ያላቸው አልመሰለኝም፡፡
‹አዲስ ግንባርን› አሁን ከእስር ከተፈታሁ በኋላ ደግሜ ስመለከተው በቀጣይ ከመጡት ዘጋቢ ፊልሞች ጋር በማነፃፀር የዘጋቢ ፊልሙ ዋነኛው ማጠንጠኛ ሆኖ ያገኘሁት ወደ ስነ መለኮታዊው ጉዳይ ወርዶ ‹ሰለፊያ› ያለውን ቡድን ኢላማ አድርጎ መምታትን እና ነባሩ እስልምና ያለውን ‹ሱፊያ› አጉልቶ ማቅረብን ‹አል ሸባብ ሰለፊ ነው› በሚለው ገለፃው ውስጥ እናገኛለን፡፡ ብሎም ‹በዋህቢያ ወይም ሰለፊያ አስተምሮ እየተመሩ [ሊያጠፉን ነው] … እነዚህን ሰዎች ማጥፋት ነው፡፡ ከኢትዮጵያ እንዲጠፉ እንጠይቃለን እኛ› በማለት ብይን ይሰጣል፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄ አደባባይ የወጣበትን አንደኛ ዓመት በሚያከብርበት ጥር 2005 ደግሞ መንግስታዊው ቴሌቪዥን ብዙ ሰዎችን ያስቆጣውን እና ቴሌቪዥን ጣቢያውን በፍርድ ቤት እስከመቆም ያበቃውን ‹ጅሃዳዊ ሐረካት› ይዞ ብቅ አለ፡፡ በዚሕኛው ዘጋቢ ፊልሙ አማን አሰፋ በተባለ የአልሸባብ ወታደር የተመራን ‹ሐረካተይ ሸባብል ሙጃሂዲን ፊ ቢላድን ሒጅራቴይን› የተባለን አንድን ቡድን (እስከ አሁን ድረስ ጉዳዩ ገና የፍርድ ቤት ውሳኔ ያልተሰጠበት ቢሆንም ከሶስት ዓመታት በፊት በጊዜው የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ሽፈራው ገ/ማርያም ‹ይህ ቡድን በኢትዮጵያ የተገኘው ሁለተኛው የአልቃይዳ ሕዋስ ነው› በማለት ፍርድ ሰጥተውበታል) የሙስሊሙን የመብት ጥያቄ ለመንግስት ለማቅረብ በሕዝብ የተወከሉትን የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ጋር (ገና ክስ በተመሰረተባቸው በሁለተኛ ወሩ) በማስተሳሰር የቀረበ ነው፡፡
ይሄን ዘጋቢ ፊልም አሁን በድጋሚ ስመለከተው እጅግ በጣም እያዘንኩ እና መጨረስ በተደጋጋሚ እያቃተኝ ነው፡፡ በእስር ላይ በነበርኩበት ወቅት በየእለቱ በዘጋቢ ፊልሙ ከቀረቡት ሰዎች ጋር እገናኝ ነበርና፡፡ አማን አሰፋ በተባለ የአልሸባብ ወታደር የተመራን ‹ሐረካተይ ሸባብል ሙጃሒዲን ፊ ቢላድን ሒጅራቴይን› የተባለውን ቡድን አስመልክቶ እኔ መናገር የምችለው በእስር ወቅት አግኝቻቸው ስለነበሩት ስለ አቶ አማን አሰፋ ብቻ ነው፡፡ አቶ አማን አሰፋ ለፍርድ ቤትም እንዳስረዱት እርሳቸውም ‹ሰልፉ እየተጎበኘ ነው› ባሉትና ዓቃቤ ሕግ በማስረጃነት ባቀረበባቸው መፅሃፋቸው እንደገለፁት የአልሸባብ ወታደር መሆናቸውን አልካዱም ነገር ግን በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ አንዳችም ጉዳት ለማድረስ እንዳልተነሱ ገልፀዋል፡፡ የዚህ ቡድን አባላት ናቸው የተባሉ ሌሎች ግለሰቦችን አስመልክቶ ብዙም የማውቀው ነገር አለ ማለት ባልችልም፤ ክሳቸውን ተመልክቼ እንደ ጋዜጠኛ ሰለሞን ከበደ ያሉ ወጣቶች ምንም በማይገባቸው ጉዳይ በግፍ እንደታሰሩ አምናለሁ፡፡
ጅሃዳዊ ሐረካትን ስመለከት እጅግ ያሳዘነኝ ጉዳይ በሕይወታቸው ተያይተው የማይተዋወቁ ግለሰቦችን እና በፍፁም ለተለያየ አላማ የቆሙ ግለሰቦችን አንድ ላይ ‹ሁለቱ ቡድኖች፡ ከአልቃይዳ፣ ሻዕቢያ፣ አልሻባብና ግንቦት ሰባት ጋር የቀጥታ እና ተዘዋዋሪ ግንኙነት በመፍጠር … › በሚል ዘጋቢ ፊልሙ የፍርድ ውሳኔ ከመስጠቱ እጅግ በጣም አስቀድሞ ብይን ሰጥቶባቸዋል፡፡ የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ (መአኮ) አባላት ከሆኑት እና አሁን በግፍ ተፈርዶባቸው በእስር ላይ ከሚገኙት አቡበክር አሕመድ፣ ካሚል ሸምሱ፣ አሕመድ ሙስጠፋ፣ ሼህ መከተ ሙሔ እና ያሲን ኑሩ (በመስከረም 2008 ከእስር የተፈታ)፤ እንዲሁም ከኮሚቴው ጋር ሰርታችኋል ተብለው የግፍ ሰለባ ከሆኑት በድሩ ሁሴን፣ ሙባረክ አደም እና አቡበክር አለሙ (በመስከረም 2008 ከእስር የተፈታ) ጋር በታሰርኩበት ወቅት እጅግ የቀረበ ግንኙነት ስለነበረኝ በዘጋቢ ፊልሙ ‹ሁለተኛው ቡድን› ተብሎ ስለተገለፀው ቡድን ብዙ መናገር እችላለሁ፡፡

የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት እና ተባብራችኋል ተብለው የተፈረደባቸው ኢትዮጵያዊያን © ማሕበራዊ ሚዲያ

የኮሚቴው አባላትም ሆኑ ከኮሚቴው ጋር ግንኙነት አላችሁ ተብለው የተከሰሱትን ግለሰቦች እጅግ የሚከበሩ እና አይነተኛ ዜጎች (ideal citizens) ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡ የታሪክ፣ የፖለቲካ እንዲሁም የሐይማኖት ንፅፅራዊ (Comparative Religion) እውቀታቸው ከፍ ያለ፤ አይደለም ከሽብርተኝነት ጋር ከግለሰብ ፀብ ጋር እንኳን ስማቸው አብሮ መነሳት የሌለባቸው፤ ይሄ ሁሉ በደል ተፈፅሞባቸውና ስማቸው ጠልሽቶ እንኳን ቂም የሚባል ነገር ማንም ላይ የማይቋጥሩ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ለሳይንሳዊ እውቀት ትልቅ ክብር የሚሰጡ (ከበድሩ ሁሴን ጋር ከስምንት ወራት በላይ አንድ ላይ አንድ ቤት ስንኖር በተደጋጋሚ አንስተን ያወራነው እና ሊያስረዳኝ የሚሞክረው ጉዳይ እሱ እጅግ ስለሚያደንቀው የታላቁ ስኮትላንዳዊ ፊዚስት ጀምስ ክለርክ ማክስዌልMaxwell’s Equations› ነው፡፡ በድሩ ሀይማኖታዊ እውቀቱ ከፍ ያለ ከመሆኑ ባለፈ በእንደ ጋንዲ አይነት ሰዎች ታሪክ የሚመሰጥ፤ በእንደ ማክስዌል አይነቱ ፊዚስት የሚደመም ሰው ነው)፣ በየቀኑ የሚያነቡና የሚፅፉ (የኮሚቴው አባላት ከታሰሩ ወዲህ ከ20 በላይ መፅሃፍትን ከእስር ሆነው ማሳተማቸውን ማየቱ ብቻ ለዚህ በቂ ነው) እንዲሁም ለሌላ ሐይማኖት ተከታዮችም ሆነ ለእንደኔ አይነቱ ሐይማኖት አልባ (Atheist) ክብር የሚሰጡ ግለሰቦችም ናቸው፡፡ ይሄን ስፅፍ ብዙ ስሜታዊ የሚያደርጉ ነገሮች እየተፈታተኑኝ ነው፡፡
እንግዲህ መንግስታዊው ቴሌቪዥን ‹ጅሃዳዊ ሐረካት› በሚለው ዘጋቢ ፊልሙ ግፍ የሰራባቸው እነዚህን መልካም ሰዎች ነው፡፡ በእስር ላይ በነበርንበት ወቅት ስለ ‹ጅሃዳዊ ሐረካት› እያነሳን ብዙ ተሳስቀናል፡፡ አቡበክር አሕመድ በድብቅ ካሜራ የተቀረፀው በረመዳን የፆም ወቅት ያለማቋረጥ ከአስራ ሁለት ሰዓታት ለሚበልጥ ጊዜ ‹ምርመራ› እየተደረገበት እኩለ ሌሊት ላይ እንደሆነ እያነሳ ‹ሕዝብ እንደሆነ እውነቱን በማግስቱ አውቋል› እያለ የሚስቅ ሰው ነው፡፡ ለማንኛያውም ዘጋቢ ፊልሙ አሁንም ዋሃቢያ/ሰለፊያ ያለውን ቡድን የችግሮች ሁሉ መነሻ በማድረግ ነባሩ እስልምና ወይም ሱፊያውን በማወደስ ተጠንቀቁ ይለናል፡፡
ሶስተኛው በመንግስታዊ ቴሌቪዥኑ የቀረበው ዘጋቢ ፊልም ደግሞ በኢትዮጵያ ፈርስት ዶት ኮም ባለቤት አቶ ቢኒያም ከበደ የተዘጋጀው ‹ሀዘን ለመድረስ … ጉዞ ወደ ደሴ› የተባለው ዘጋቢ ፊልም ነው፡፡ ይህ ዘጋቢ ፊልም በዋናነት በደሴ ከተማ የተገደሉትን የሸህ ኑሩ ይማምን አሟሟት ለማሳየት የቀረበ ሲሆን፤ ሸህ ኑሩን ወሃቢስቶች ናቸው የገደሏቸው በማለት በጉዳዩ ላይ ገና ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦችን ‹ቅጥረኛው ነፍሰ ገዳይ እና የሽብር ቡድኑ መሪ› በማለት ስማቸውን እየጠቀሰ ራሱ ከሶ ራሱ ፍርድ እዛው የሚሰጥ ነው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ግን እስከ አሁን ድረስ ጥፋተኛ ያልተባሉና ጉዳዩም ገና በሕግ ሒደት ላይ ያለ ጉዳይ ነው (በእስር ላይ በነበርኩበት ወቅት በዚህ ጉዳይ (‹የደምፃችን ይሰማ የደሴ ክንፍ አባላት› ተብለው) ተጠርጥረው ከታሰሩት አንዋር አደም እና አብዱ ያሲን ጋር ብዙ አውርተናል፤ ‹መንግስት ዜጎቹ ላይ ለምን ወንጀል እንደሚያቀነባብር አልገባንም;› ይሉኝ ነበር)፡፡ ዘጋቢ ፊልሙ የተለመደውን የሰለፊያ/ሱፊያ ክፍፍል ለማጉላት ከመሞከሩ ባለፈም አሁን ያለውን ‹የድምፃችን ይሰማ› እንቅስቃሴም ተጠያቂ ለማድረግ ይሞክራል፡፡
በመንግስታዊ ቴሌቪዥኑ የቀረቡት ከእስልምና እና ከሽብርተኝነት ጋር ተያይዘው በአራተኝነትና በአምስተኝነት ከቀረቡት ዘጋቢ ፊልሞች በግንቦት 2007 የቀረበው ‹የጥፋት መልዕክተኞች› እንዲሁም አሁን በጥር 2008 የቀረበው ‹የማንቂያ ደወል› ናቸው፡፡ ሁለቱም ዘጋቢ ፊልሞች በይዘታቸውም ሆነ በአላማቸው አንድ አይነት ሊባሉ የሚችሉ ናቸው፡፡ ‹የዛሬዎቹ አክራሪዎች የሙሃመድ አብዱል ዋሃብ አስተምህሮ ከመጣ በኋላ ብቅ ያሉ ናቸው› ከማለት ጀምሮ፤ ‹የአክራሪዎቹ መፅሃፍት ሊቃጠሉ ይገባል› በማለት ስነ መለኮታዊ ብይን የሚሰጡ ናቸው፡፡ ሁለቱም ዘጋቢ ፊልሞች በ ‹ሀዘን ለመድረስ … ጉዞ ወደ ደሴ› ዘጋቢ ፊልም ላይ ዋነኛ የትኩረት ነጥብ የነበሩትን ሸህ ኑሩ ይማምን የአክራሪነት ሰለባ በማድረግ ያቀረቡ ሲሆን፤ ከአዲስ ግንባር እና ከጅሃዳዊ ሐረካት ዘጋቢ ፊልሞች ላይ ምስሎችን በመውሰድ ሒደቱ የቀደምቶቹ ዘጋቢ ፊልሞች ቀጣይ ክፍል የሆነ ያክል እንዲሰማን ያደርጋሉ፡፡ በአጭሩ ሁለቱም ዘጋቢ ፊልሞች ‹መንግስት በሐይማኖታዊ ጉዳይ ጣልቃ አይገባም› ከሚለው ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ በተቃራኒው መንግስት ለዜጎች ይህኛው ሴክት› ይስማማችኋል ወደ ሚል ምርጫ የገባባቸው ሆነው ነው የቀረቡት፡፡
በአጠቃላይ አምስቱ ዘጋቢ ፊልሞች በተመሳሳይ ድምፀት፣ አስፈሪ እና አስገምጋሚ ማጀቢያ ሙዚቃዎችን ከጀርባቸው አድርገው፤ እጅግ ተቃራኒ የሆኑ ግለሰቦችን በአንድ ቅርጫት በመክተት የሚፈርጁ ከመሆናቸውም ባለፈ በዜጎች ላይ ፖለቲካዊ ብይን በመስጠት ሙስሊሙን የበለጠ ግራ መጋባት ውስጥ የሚከቱ እንዲሁም ሙስሊም ያልሆነውን ሕብረተሰብ ደግሞ ፍርሃትና ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በድምሩ 224 ደቂቃ የሚረዝሙት እነዚህ ዘጋቢ ፊልሞች ስለመንግስት ፍላጎት እና ሕብረተሰቡ ውስጥ ሊፈጠር ስለሚችለው ውዝግብ ብዙ የሚናገሩ ናቸው፡፡ መሰረታዊዎቹን እንኳን ብናይ፡
ሱፊያን ማጉላት – ሰለፊያን ማጠልሸት
ሁሉም ዘጋቢ ፊልሞች በአጭሩ የሚገልፁትን ነገር ቢኖር ነባሩ እስልምና (ሱፊያው) መቻቻልን የሚሰብክ እንደሆነና መጤው ዋሃቢያ (ሰለፊያ) ደግሞ ሃገሪቱን ወደ ትርምስ ለመክተት ሙስሊሙንም ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እየመሩት ስለሆነ ሰለፊያውን መፅሃፋቸውን ሳይቀር በማቃጠል ማስቆም አለብን የሚል ነው፡፡ እኔ ያገኝኋቸው የዘጋቢ ፊልሞቹ ሰለባዎች ‹ሱፊ ነኝ› – ‹ሰለፊ ነኝ› ሲሉ አልሰማሁም ሁሉም ‹ሙስሊም ነኝ› ይሉኛል እንጂ፡፡ ከዘጋቢ ፊልሞቹ ግን የአሁኑ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት እንቅስቃሴ አደባባይ ከመውጣቱ በኩል መንግስት በተለያዩ የፖሊሲ ሰነዶቹ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለን የእስልምና አክራሪነት መገለጫ ‹ሃዎርጅያ› የተባለው የእስልምና ሴክት ነው የሚለውን የቀድሞ ፍረጃውን ትቶ አሁን ነገሮችን በማስፋት ሰለፊያው (ውሃቢያው) ነው የአክራሪነቱ ሁሉ መገለጫ ወደሚል አጠቃላይ ፍረጃ እንደገባ መገንዘብ ይቻላል፡፡
የሱፊን አስተምሮ ድጋፍ በመስጠት ማጎልበት የሽብርተኝነት ዋነኛ መዋጊያ መሳሪያ እንደሆነ እንደ RAND Corporation እና Heritage Foundation ባሉ የአሜሪካ ፖሊሲ አማካሪዎች መገለፅ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ከሞሮኮእስከ ሩሲያ – ከአልጀሪያ እስከ ፓኪስታን ድረስ ይሄን መመሪያ የመከተል አዝማሚያ እንደሚታይ የቅርብ ጊዜ ሂደቶች ያመላክታሉ፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት እየተጠቀሰ ያለው የሱፊው አስተምህሮ መቻቻልን የበለጠ ይሰብካል ከሚል መነሻ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ይሄን ጉዳይ በጥልቀት ያጠኑት የበትለር ዩንቨርስቲው ዶ/ር ፌት ሙይዲን በቅርቡ በፃፉት አንድ ፅሁፋቸው ላይ፡

Promoting Sufism, particularly at the expense of other Islamic traditions is highly problematic. The perception of Sufism as […] a moderate or tolerant form of Islam cements a dichotomy between ‘good’ and ‘bad’ understanding of religion. […] Categorization of good and bad Muslims rely not on sound judgments of behaviors and actions but, rather on simple labels based on the way in which people practices their faith.

በማለት ‹ሱፊያው መልካም ነው፤ ሌላው ደግሞ ጥፋት ነው› የሚል የእስልምና አረዳድ በጣም አደገኛ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ Mark Woodward et al በበኩላቸው ‘Salafi Violence and Sufi Tolerance? Rethinking Conventional Wisdom’ በተባለና ደቡብ ምስራቅ እስያንና ምዕራብ አፍሪካን እንደማሳያ በማድረግ ባዘጋጁት ጥናታዊፅሁፋቸው ከዚህ የዶ/ር ፌት ሙይዲን ሐሳብ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ‹ሰለፊያው ጦረኛ ነው፤ ሱፊያው ሰላማዊ ነው› የሚለው አካሄድ ከእውነታው የራቀ እንደሆነ እና ስነ መለኮታዊ ልዩነትን መሰረት ያደረገ አካሔድም የባሰ ችግርን እንጂ መፍትሔን እንደማይወልድ ይገልፃሉ፡፡ ዶ/ር ፌት ሙይዲን ጉዳዩን በሚገባ አጥንተው በፃፉትና ብዙ ተቀባይነት ባገኝው ‘Sponsoring Sufism: How Governments Promote Mystical Islam in their Domestic and Foreign Policy’ በተባለው መጽሃፋቸው በተለይም አንባገነናዊ መንግስታት ሱፊያውን ደግፈው የሚቆሙባቸው ሁለት ዋነኛ ምክንያቶች አሉ በማለት ያስረዳሉ፡
  1. ሱፊያው ማሕበረሰብ በባሕሪው ከፖለቲካ ራሱን ያራቀ (apolitical) በመሆኑ አንባገነናዊ መንግስታቱ ፀጥ ለጥ አድርገው ለመግዛት ይቀላቸዋል እንዲሁም፤
  2. እስልምና በዋናነት ከሚታወቅበት ካሕን አልባነት (non-clergical) በተለየ መልኩ የሱፊ የሐይማኖት አባቶች በሱፊያው ማሕበረሰብ ውስጥ ሰፊ ተቀባይነት ያላቸው በመሆናቸው እና ማሕበረሰቡንም ከፖለቲካ እንዲርቅ ማድረግ በቀላሉ ስለሚችሉ ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡
በመንግስታዊው ቴሌቪዥን የቀረቡትን አምስቱንም ዘጋቢ ፊልሞች የተመለከተ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ሱፊያን ለማጠናከር መንገድ የመጥረግ ስራ እየተካሔደ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል፡፡ ከአሁኑ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት እንቅስቃሴ ጋር ስማቸው በመጥፎ ከሚነሱት ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት እስራኤላዊው ፕሮፌሰር ሐጋይ ኤርሊኸ ከአስር ዓመት በፊት ከሙስጠፋ ካባ ጋር በመሆን በ International Journal of Middle East Studies ላይ ‘Al-Ahbash and Wahhabiyya: Interpretations of Islam’ በሚል ርዕስ ባሳተሙት ፅሁፋቸው የኢትዮጵያንና የሊባኖስን መመሳሰል ተመልክተው በመደምደሚያቸው ላይ እንደ አህባሽ ያሉ የሱፊ አስተምህሮቶች እንዲጎለብቱ ቢደረግ መልካም እንደሆነ በገደምዳሜ ገልፀው ነበር፡፡ የዘጋቢ ፊልሞቹ መደምደሚያም ከዚህ እውነታ ጋር ይቀራረባል፤ ዶ/ር ፌት ሙይዲን በሚገልፁት መልኩ የሚሔድ መሆኑም ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡ ዶ/ር ሙይዲን ግን ‹ይህ በጣም አደገኛ አካሔድ ነው፤ ተጠንቀቁ!› እያሉ ነው፡፡
የመብት ጥያቄን መሸሽ
ሌላው የዘጋቢ ፊልሞቹ መሰረታዊ ባህሪ ለመንግስት ያልተመቹትን ሁሉንም አይነት እንቅስቃሴዎች በስመ ሙስሊም በአንድ ቅርጫት ውስጥ መክተታቸው ነው፡፡ ይሄም በተለይም ላለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እያደረጉት ያለውን እጅግ ሰላማዊና ፍትሃዊ ጥያቄ በዘጋቢ ፊልሞቹ ከነአልቃይዳ እና አልሸባብ ጋር አንድ ላይ ደምረው በማቅረባቸው የሚታይ ነው፡፡ ዜጎች ሕገ መንግስቱን ይዘው አደባባይ ወጥተው ሕግ ይከበርልን ሲሉ የሌለን ዓላማ ፈጥሮ አላማችሁ ሌላ ነው ማለት መብት ጥያቄን ላለመመለስ የሚደረግ ሙከራ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ የጠየቁት ጥያቄ የማይመለስላቸውና መብታቸው የማይከበርላቸው ከሆነ ደግሞ መብታቸውን ለማስከበር መጣራቸው አይቀርም፡፡ የመብት ጥያቄን መንግስት በዘጋቢ ፊልም አጥላልቶ ማለፉ ዘላቂነት ካለመኖሩም ሌላ ለመብት ጠያቂዎቹ ክብር አለመስጠትም ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚያመጣው አይታወቅም፡፡
‹የከሸፈ የሽብርተኝነት ትግል?›
መንግስት የመብት ጥያቄዎችን ከሃይልና ከሽብርተኝነት እንቅስቃሴዎች ጋር አመሳስሎ በዘጋቢ ፊልሞቹ ማቅረቡ ከሁሉም በላይ የሚያመጣው መዘዝ ደግሞ፤ የሚባለውን አክራሪነትም ሆነ ሽብርተኝነትን ከመከላከል ይልቅ የሚያባብስ ተግባር መሆኑ ነው፡፡ የሙስሊሙ (መአኮ) አባላት በተደጋጋሚ እንደሚሉት አክራሪነትንም ሆነ ሽብርተኝነትን መከላከል የሚቻለው ከሕዝቡ ጋር አብሮ በመስራት እንጂ መብትን የጠየቀን ሁሉ ‹አሸባሪዎች ናችሁ› በማለት አይደለም፡፡ ሽብርተኝነትን በእጅጉ የሚፀየፉትን እንደ የኮሚቴው አባላት ያሉ ሙስሊሞችን ‹ከአልሸባብ አባላት ጋር አንድ ናችሁ› ብሎ ፈርጆ ሽብርተኝነትን እታገላለሁ ማለት መቼም ፍሬ የሌለው ስራ ከመሆን አያልፍም፡፡ መንግስት አሁን የያዘው ሁሉንም ተቃውሞ በሽብርተኝነት የመፈረጅ አባዜ እጅግ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ጦስ ይዞ መምጣቱም አይቀርም፡፡
Guilty until proven Innocent
ሌላው የዘጋቢ ፊልሞቹ ተመሳሳይ ባህሪ ደግሞ በፍርድ የተያዙ ጉዳዮችን ያለምንም ሐፍረት ብይን መስጠታቸው ነው፡፡ መንግስታዊው ቴሌቪዥን አሸባሪዎች ናቸው ብሎ በመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው አባላት ላይ ውሳኔ የሰጠው ገና ዓቃቤ ሕግ ክስ በከፈተ በሁለተኛው ወር ላይ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሰጠው ግን መንግስታዊው ቴሌቪዥን ከወሰነባቸው ከሁለት ዓመት ከሰባት ወራት በኋላ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱም የመንግስትን ውሳኔ ቀድሞ እያወቀ ነፃ ናቸው ብሎ ለማሰናበት ምንም አቅም አይኖረውም፡፡ ይሄን ተገንዝበው የመአኮው አባላት እነሱን አስመልክቶ የተላለፈውን ‹ጅሃዳዊ ሐረካት› የተባለው ዘጋቢ ፊልም እንዳይተላለፍ ከፍርድ ቤት እግድ (injunction) አውጥተው ቢሔዱም ማንም ሊሰማቸው አልፈቀደም፡፡ በደንብ ከሚታወቀው ከመአኮው ሒደት ባለፈም የሸህ ኑሩ ይማም ገዳዮች ናችሁ የተባሉ ግለሰቦችም በብሔራዊ ቴሌቪዥኑ ቅጥረኛ ነብሰ ገዳይ እና ሽብርተኞች ተብለው ከተፈረጁ ሁለት ዓመታት ቢያልፉም ይህ ፅሁፍ እስከተፃፈበት ጊዜ ድረስ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ያላላቸውና ጉዳያቸውም በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ ነው፡፡
በዘጋቢ ፊልሞቹ ገና ጉዳዩ ፍርድ ቤት በር እንደደረሰ የሚሰጠው ይህ የጥፋተኝነት ውሳኔ በአጠቃላይ በፍርድ ቤት የተያዘን ጉዳይ በሚዲያ ማራገብ ከሚያመጣው ተፅዕኖ ባለፈ እንደኛ አይነት የፍርድ ቤት ነፃነት በስራ አስፈፃሚው ጉያ ውስጥ ባለ ሀገር ደግሞ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ነፃ ይሆናል ብሎ ማሰብ ራስን ማድከም ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ይህ አይነቱ ፍረጃ ዜጎች ጥፋተኝነታቸው እስኪረጋገጥ ድረስ በሕግ ፊት ጥፋተኛ ተብለው ያለመገመት (presumption of innocence until proven guilty) ሕገ መንግስታዊ መብትን በመጣስ፤ በተገላቢጦሹ ራሳቸው ንፅህናቸውን እስኪያረጋግጡ ድረስ ጥፋተኛ ናቸው (presumption of guilty until proven innocent) ወደሚል መደምደሚያ ያደርሰናል፡፡
በሙስሊሙ ውስጥ ያለውን የስነ መለኮት መሰነጣጠር መጨመር
ኢትዮጵያ በሙስሊም ሕዝብ ብዛት በዓለም ላይ ካሉት ቀዳሚ አስራ አምስት ሀገራት አንዷ ስትሆን በሕዳጣን ሙስሊሞችም ረገድ በዓለም ላይ ከሕንድ ቀጥላ በሁለተኝነት ብዙ ሙስሊሞች ሕዳጣን (largest minority) ሆነው የሚኖሩባት አገር ናት፡፡ በዚህ ትልቅ ማሕበረሰብ ውስጥ የስነ መለኮታዊ ልዩነቶች መኖራቸው ባይካድም በብሔራዊ ቴሌቪዥኑ እየቀረቡ ያሉት የዘጋቢ ፊልሞች (በተለይም ‹የጥፋት መልዕክተኞች› እና ‹የማንቂያ ደወል› በተባሉት ዘጋቢ ፊልሞች) ግን ልዩነቱን የበለጠ በማጉላት በሙስሊሙ ማህበረሰብ ውስጥ ልዩነቶቹ የጎሉ እንዲሆኑ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ መንግስት በዘጋቢ ፊልሞቹ አንዱን ሴክት ደግፎ ሌላኛውን ማጣጣሉ ሙስሊሙ እርስ በርስ ከሱፊያ – ሰለፊያ ውዝግብ ባለፈ ትናንሽ ልዩነቶችን እያነሳ እንዲጠቋቆም በር የከፈቱ ናቸው፡፡ ‹ይሄ ሽርክ ነው›፣ ‹ይሄ ቢድኣ ነው› የሚለውን ፍረጃ በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ሳይቀር መሰማት የጀመሩበት ጊዜ ነው አሁን፡፡ በሙስሊሙ ዓለም የሚገኙት ስነ መለኮታዊ ልዩነቶች ሁሉ ዛሬ በመፅሃፍት፣ በሶሻል ሚዲያ እንዲሁም በሌሎች የመገናኛ መሳሪያዎች ላይ በርከት ብለው ለኢትዮጵያ ሙስሊም በገበያ ላይ ቀርበውለታል፡፡ ኢኽዋን፣ ተብሊግ፣ ሰለፊ፣ ዋሃቢ፣ ተክፊር፣ መደኺላ፣ሐዳዲያ፣ አህባሽ፣ ተብዲዕ፣ ተፍሲቅ፣ ተድሊል፣ ኻዋሪጅ፣ ሺዓ፣ ሱፊያ፣ ቀደሪያ፣ ሙዕተዚላ፣ ሙርጂት፣ አሕመዲያ፣ ማቱርዲያ፣ አሻሪያ፣ ከራሚ፣ ጀኸሚ፣ ቲጃኒ … እያለ የማያልቅ ስም መሰጣጣትና ፍረጃው በርትቷል፡፡ መንግስት በዘጋቢ ፊልሞቹ የመጡበትን የመብት ጥያቄዎች ከመመለስ ይልቅ ይሄን ክፍፍል ማጉላትን እንደ ግብ በመያዝ ነገ ሌላ ፈተናን ይዞ መጣ ዘንድ ዛሬ የተመቻቸ ሜዳ እያዘጋጀለት ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሙስሊም የመብት ጥያቄ እንዲሁ መንግስት በዘጋቢ ፊልም አጥላልቶት የሚያልፍ እንዳልሆነ ያለፉት አራት ዓመታት ጥሩ ምስክሮች ናቸው፡፡ መንግስት ለተደራጀ የሰላማዊ ተቃውሞ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት አሻፈረኝ ባለ ቁጥር ችግሮቹ የበለጠ እየተባባሱ የሀገሪቱን ፈተና የበለጠ ያንሩታል፡፡ ይባስ ብሎም ችግሩ ላይ ሌላ ችግር እየጨመረ ሕዝበ ሙስሊሙን የበለጠ ግራ መጋባት ውስጥ ሲከተው – ሙስሊም ያልሆነውን የሌላ እምነት ተከታይም የበለጠ ፍርሃት ውስጥ እያስገባው ነው፡፡

Articles

24ኛው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና በፖላንድ ግድኒያ ይካሄዳል

Published

on

Gdynia 2020

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከምስራቅ አፍሪካ አቻዎቻቸው ጋር ለአሸናፊነት ይፎካከራሉ

በባልቲክ ባሕር ዳርቻ የምትገኘው ትንሿ የፖላንድ ወደብ ከተማ ግድኒያ በሀገራት መካከል የሚካሄድ የዓመቱ ብቸኛ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር የሆነውን እና ከሰዓታት በኋላ የሚጀመረውን የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች፡፡ ስመ ጥር አትሌቶች የተካተቱበትና ከ250 በላይ ተሳታፊዎች የሚፎካከሩበት ይህ ሻምፒዮና የዓለም አትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪያን አይኖች ዳግም በምስራቅ አፍሪካውያኑ ኮከቦች ላይ እንዲያተኩሩ እንደሚያስገድድ ይጠበቃል፡፡ በሴቶቹ ውድድር ሴቶች ብቻ የተሳተፉበት ሩጫ የዓለም ሪኮርድ ባለቤቷ ኬንያዊት ፐሬስ ጄፕቺርቺር እና በወንዶች አሯሯጭነት የተመዘገበ የዓለም ሪኮርድ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ አባበል የሻነህ፤ በወንዶች በቅርቡ የ5000 ሜትር እና 10000 ሜትር የዓለም ሪከርዶችን የሰባበረው ኡጋንዳዊው ጆሹዋ ቼፕቴጊ እንዲሁም ኢትዮጵያዊው ጉዬ አዶላ ከሌሎች ተፎካካሪዎቻቸው በመላቅ በፖላንዷ የባህር ዳርቻ ከተማ ላይ የወርቃማ ድል አሻራቸውን ለማሳረፍ ተስፋ ከሚያደርጉት ከዋክብት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

Photo Aman @angasurunning

ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ አዲስ አሸናፊ አትሌት የሚጠበቅበት የወንዶቹ ፉክክር

ከ2006 ዓ.ም. ወዲህ ከተካሄዱት ዘጠኝ የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የወንዶች ውድድሮች ከአንዱ በስተቀር ሁሉም ድሎች በኤርትራዊው ዘርሰናይ ታደሰ (5) ወይም በጆፍሬይ ካምዎሮር ስም የተመዘገቡ ናቸው፡፡ ዘርሰናይ እና ካምዎሮር በግዲኒያ የማይገኙ በመሆኑም ውድድሩ ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ የወርቅ ሜዳያ አሸናፊ ስም የሚመዘግብ ይሆናል፡፡ በግዲኒያ የወንዶቹ ፉክክር ማስጀመሪያ ሽጉጥ ሲተኮስ አይኖች ሁሉ ትኩረታቸው ከዚህ በፊት በ21.1 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ተወዳድሮ በማያውቀው የወቅታዊ ምርጥ ብቃት ባለቤት ኡጋንዳዊ አትሌት ጆሹዋ ቼፕቴጊ ላይ ይሆናል፡፡ ኡጋንዳዊው ምንም እንኳን የግማሽ ማራቶን ውድድር ልምድ ባይኖረውም ባለፈው እና በዘንድሮ ዓመት በተለያዩ ውድድሮች ካሳየው ድንቅ ብቃት አንፃር እንደሚጠበቀው ሆኖ እንደሚገኝም ይገመታል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኡጋንዳ አትሌቶች ላይ እየታየ የመጣው የብቃት መሻሻል ከዚህ ቀደም ብብርቱ ተፎካካሪነት ከሚታወቁት ኢትዮጵያ እና ኬንያ አትሌቶች በተጨማሪ የዓለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የወንዶቹን ፉክክር ይበልጥ እንደሚያደምቀው ይጠበቃል፡፡ የኡጋንዳ የወንዶች ቡድን በግማሽ ማራቶን ውድድር የመጀመሪያ ተሳትፎውን በሚያደርገው ጆሹዋ ቼፕቴጊ የሚመራ ሲሆን ሌላኛው ተጠባቂ አትሌት ጃኮብ ኪፕሊሞ፣ አቤል ቼቤት እና ሞሰስ ኪቤትንም አካቷል፡፡

በወንዶቹ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም የቼፕቴጊ ብርቱ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ ተገምቷል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ሳይጠበቅ ድንቅ ውጤቶችን በማስመዝገቡ ረገድ መልካም ስም ያለው ጉዬ አዶላ ለወርቅ ሜዳያ ድሉ ከተገመቱት መካከል አንዱ ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 በዴንማርክ ኮፐንሀገን ከተካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና በፊት ብዙም እውቅና ያልነበረው ቢሆንም የራሱም ምርጥ ሰዓት ከሁለት ደቂቃ በላይ ባሻሻለበት 59፡21 የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊ ለመሆን መብቃቱ ይታወሳል፡፡ በዚያው ዓመት መገባደጃ ላይም የወቅቱን የዓለም ግማሽ ማራቶን እና የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮን ጆፍሬይ ካምዎሮር በዴልሂ የግማሽ ማራቶን ፉክርር የራሱን ምርጥ ሰዓት 59.06 በማስመዝገብ ጭምር አሸንፎታል፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ በሮጠበት የ2017 የበርሊን ማራቶን ውድድር ላይ ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ በመጀመሪያ ተሳትፎ የተመዘገበ የምንግዜም ፈጣን የሆነ 2:03:46 ሰዓት ያለው ጉዬ አዶላ በፖላንዱ የግማሽ ማራቶን ላይ ለመሳተፍ ከተመዘገቡት አትሌቶች መካከል የርቀቱን ሶስተኛ ፈጣን ሰዓት የያዘም ነው፡፡  

በጉዬ አዶላ በሚመራው የኢትዮጵያ ቡድን ውስጥ የግማሽ ማራቶን ፉክክርን ከ60 ደቂቃ በታች ለመጨረስ የበቁና ልምድ ያላቸው አንዳምላክ በልሁ (59:10)፣ ልዑል ገብረስላሴ (59:18) እና አምደወርቅ ዋለልኝ (59:22) እንዲሁም ለዚህ ውድድር መምረጫ በሀገር ውስጥ የተካሄደው የ15 ኪሎ ሜትር ውድድር አሸናፊው ሀይለማሪም ኪሮስ (1:01:08) ተካተዋል፡፡           

የወንዶቹ ፉክክር ያለፉት ሶስት ሻምፒዮናዎች የተናጠል የወርቅ ሜዳልያ ድልን በጆፍሬይ ካምዎሮር አማካይነት አላስቀምስ ያለው የኬንያ የወንዶች ቡድን ዘንድሮም በጠንካራ አትሌቶች የተወከለ ሲሆን በግል የወርቅ ሜልያ ድል ተስፋውን የጣለውም የ2020 የፕራግ ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮን በሆነው ኪቢዎት ካንዲዬ እና የ2017 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ አሸናፊው ሊዮናርድ ባርሶቶን ላይ ነው፡፡ ማውሪስ ሙኔኔ፣ በርናርድ ኪፕኮሪር እና በርናርድ ኪሜሊም ሌሎቹ የኬንያ ተወዳዳሪዎች ናቸው፡፡

ሁለቱን የዓለም ሪኮርድ ባለቤቶች የሚያገናኘው የሴቶቹ ፉክክር

እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ አስተዳዳሪ አካል ቤሰቶች የጎዳና ላይ ፉከክሮች ሁለት አይነት የሪኮርድ አመዘጋገብን መከተል ከጀመረ ወዲህ የግድኒያው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የሴቶች ውድድር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለቱን የርቀቱ የዓለም ሪኮርድ ባለቤቶች የሚያፎካክር ይሆናል፡፡ የሴቶቹ ውድድር ከዓለም ሪኮርድ ባለቤቶቹ ኬንያዊቷ ፐሬስ ጄፕቺርቺር (ሴቶች ብቻ የሮጡበት ሪኮርድ ባለቤት) እና ኢትዮጵያዊቷ አባበል የሻነህ (ሴቶች ከወንዶች ጋር የሮጡበት የዓለም ሪኮርድ ባለቤት) በተጨማሪ ያለፈው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮን ኢትዮጵያዊቷ ነፃነት ጉደታም የአሸናፊነት ክብሯን ለማስጠበቅ የምትፎካከርበት ነው፡፡

በ2016 ካርዲፍ ላይ የተካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን አሸናፊነት ገድልም ያላት የ27 ዓመቷ ኬንያዊት ፐሬስ ጄፕቺርቺር በ2017 እና 2018 በወሊድ ምክንያት ከውድድር ርቃ ከከረመች በኋላ በ2019 ባደረገቻቸው ውድድሮች ወደ ምርጥ አቋሟ መመለሷን አሳይታለች፡፡ ያም ሆኖ በ2016 በተፎካከሩበት የዴልሂ ግማሽ ማራቶን በጄፕቺርቺር ላይ የበላይነቱን የወሰደችው ኢትዮጵያዊቷ አባበል የሻነህ በግዲኒያም ብርቱ ተፎካካሪዋ እንደምትሆን አያጠራጥርም፡፡ በ2013 የሞስኮ ዓለም ሻምፒዮና እና በ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ የ10000 ሜትር እና 5000 ሜትር ተሳትፎዋ ብዙም አመርቂ የሚባል ውጤት ያላስመዘገበችው አባበል ከዛ በኋላ አብዛኛውን ግዜዋን ለጎዳና ላይ ሩጫዎች ሰጥታ ስትሰራ ቆይታለች፡፡ ከተሳተፈችባቸው አስራ ሁለት የግማሽ ማራቶን ውድድሮችም በአስሩ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ደረጃዎች በመያዝ ማጠናቀቅ የቻለች ሲሆን ባለፈው ዓመት በተወዳደረችበት የቺካጎ ማራቶን ላይም የራሷ ምርጥ በሆነ 2፡20፡51 ሰዓት ሁለተኛ ሆና ጨርሳለች፡፡

የግድኒያው የሴቶች ግማሽ ማራቶን ዓለም ሻምፒዮና ሌላኛዎቹ የትኩረት ማዕከሎች ሁለቱ የከዚህ ቀደም ሪኮርድ ባለቤት እንዲሁም ከሁለት ዓመት በፊት በስፔን ቫሌንሲያ በተካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የወርቅ እና የብር ሜዳልያ አሸናፊዎች ኢትዮጵያዊቷ ነፃነት ጉደታ እና ኬንያዊቷ ጆሴሊን ጄፕኮስጋይ ናቸው፡፡ ነፃነት ከሁለት ዓመት በፊት በቫሌንሲያ የቅድመ ውድድር ተጠባቂዋ ጄፕኮስጋይን በማስከተል ሻምፒዮን ስትሆን የገባችበት ሰዓት ሴቶች ብቻ የሮጡበት ሪኮርድ ባለቤት አድርጓት ነበር፡፡ ሆኖም ከዛ በኋላ ግን ላለፉት ሁለት ዓመታት አንድም የግማሽ ማራቶን ውድድር ማሸነፍ አልቻለችም፡፡ ጄፕኮስጋይ አሁንም ሙሉ በሙሉ ሪኮርዶችን ወደሰባበረችበት የ2017 ዓ.ም. ድንቅ አቋሟ መመለስ ባትችልም ባለፈው ዓመት በመጀመሪያ የማራቶን ውድድር ተሳትፎዋ የኒው ዮርክ ማራቶንን ለውድድር ስፍራው ሪኮርድ በቀረበ ሰዓት ለማሸነፍ ችላለች፡፡ ሁለቱ አትሌቶች ባለፉት ሁለት ዓመታት አቋማቸው እምብዛም አመርቂ የነበረ ባይሆንም የግድኒያውን ውድድር ዳግም ወደውጤት ከፍታ የሚወጡበት መድረክ ለማድረግ የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

በኢትዮጵያ እና ኬንያውያን አትሌቶች መካከል ብርቱ ትንቅንቅ እንደሚደረግበት በሚጠበቀው የሴቶቹ ውድድር በኢትዮጵያ በኩል ከአባበል እና ነፃነት በተጨማሪ ያለምዘርፍ የኋላው፣ ዘይነባ ይመር እና መሰረት ጎላ የሀገራቸውን ሰንደቅ በዓለም አደባባይ ከፍ እንዲል ለማድረግ የሚፎካከሩ አትሌቶች ናቸው፡፡ በኬንያ በኩልም ሮዝመሪ ዋንጂሩ፣ ዶርካስ ኪሜሊ እና ብሪሊያን ኪፕኮኤች በጉጉት የሚጠበቀውን ድል ለማሳካት ከጄፕቺርቺር እና ጄፕኮስጋይ ጎን እንዲሰለፉ የተመረጡት አትሌቶች ናቸው፡፡

የኮሮና ቫይረስ በፍጥነት በዓለም ዙሪያ እየተስፋፋና አሳሳቢነቱ እያደገ በመምጣቱ ምክንያት በርካታ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች እንዲሰረዙ ተደርገዋል፡፡ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ አስተዳዳሪ (ወርልድ አትሌቲክስ) የበላይ ተቆጣጣሪነት እ.አ.አ. በማርች 29/2020 ሊካሄድ ፕሮግራም ተይዞለት የነበረው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ለመካሄድ የበቃውም በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ምክንያት ለኦክቶበር 17/2020 እንዲተላለፍ ተደርጎ ነው፡፡

በዘንድሮው ውድድር ላይ በ2014 ዓ.ም. ያስመዘገበችውን የወርቅ ሜዳልያ ድል ጨምሮ ባለፉት አስር የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮናዎች የቡድን የሜዳልያ ድል ተቋዳሽ የሆነችው ኤርትራ እንዲሁም ባለፉት 23 የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮናዎች ላይ ያለማቋጥ ተሳታፊ የነበሩት ጃፓን እና አሜሪካ ለመሳተፍ አትሌቶቻቸውን ሳያስመዘግቡ ቀርተዋል፡፡ ካናዳም ውድድሩ ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ያስመዘገበቻቸውን አትሌቶች በኮሮና ቫይረስ ስጋት ምክንያት ወደ ፖላንድ እንደማትልክ አሳውቃለች፡፡

* የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና ጣሊያንን ጨምሮ ከአስተላላፊዎች ጋር በተናጥል ስምምነት ከተደረሰባቸው 22 ሀገሮች በስተቀር በወርልድ አትሌቲክስ የዩቲዩብ ቻናል ለመላው ዓለም በቀጥታ ይተላለፋል፡፡

Continue Reading

Uncategorized

የኢትዮጵያ ቀን በዋሽንግተን ዲሲ በ’ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ’ ዝግጅት ሊከበር ነው – Interview with Dr. Gashaw Abeza

Published

on

By

የኢትዮጵያ ቀን በዋሽንግተን ዲሲ በ’ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ’ ዝግጅት ሊከበር ነው – Interview with Dr. Gashaw Abeza
Continue Reading

Uncategorized

#Ethiopia: EthioTube ከስፍራው – Town Hall in DC on Addis Politics – Opening Speech by Ermias Legesse

Published

on

By

#Ethiopia: EthioTube ከስፍራው – Town Hall in DC on Addis Politics – Opening Speech by Ermias Legesse
Continue Reading

Trending