Connect with us

Articles

የአዲስ አበባ መንግስት ሆይ የት ነው ያለኸው?

Published

on

458820167_1f7eec46a9_o

August 09, 2014 | በዳዊት ንጉሡ ረታ

ምርጫ ከመድረሱ በፊት የእውነት የእውነቱን እናውራ

በየት እንለፍ?
የአዲስ አበባ ዋና ዋና አውራ ጎዳናዎች መንግስት ህገ-ወጥ በሚላቸው የመንገድ ላይ ነጋዴዎች ተጥለቅልቀዋል። እነዚህን ህገ-ወጦች በመንግስት የሚደራጀው ጥቃቅንና አነስተኛ ሊደርሳቸው አልቻለም፡፡ ጎዳናው ላይ ተዘርግቶ የማይሸጥ ነገር የለም፡፡ ልብስ፣ የቤት ቁሳቁስ፣ ጫማ፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ ሰዓት፣ የህፃናት መጫወቻዎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ መፅሃፍ፣ ቆሎ፣ ቄጤማ… ወዘተ…
ጎዳናው ቁመታቸው ተመሳሳይ በሆኑና አብዛኞቹ ከሌሎች ክልሎች በመጡ ወጣት ነጋዴዎች ተሞልቶአል። መገናኛ፣ አራት ኪሎ፣ ካዛንቺስ፣ ሜክሲኮ፣ ስድስት ኪሎ ወዘተ….በከተማዋ ከሸማቹ የበለጠ ሻጩ የሚበልጥ በሚመስል መልኩ፣ እዚህም እዚያም ህገ-ወጥ ንግዱ ደርቶአል። አስፋልቱም፣ የእግረኛ መንገዱም ንግድ ብቻ ሆነ፡፡ በድንገት የአንዱን ነጋዴ የላስቲክ ማዳበሪያ ለሽያጭ የቀረበ ዕቃ  የደፋ ወይም ረግጦ ያበላሸ መንገደኛ፣ ከጎረምሳው ጋር አንገት ላንገት ይተናነቃል። ክፈል አልከፍልም ይባባላል፡፡ ከዚያም ሲያልፍ ቡጢ ይሰናዘራል፡፡ በገዛ መንገዱ ይህንን ስህተት ላለመስራት ሲጠነቀቅና ሲሸሽ ደግሞ ዋናውን መንገድ ትቶ ወደ አስፋልቱ ዘልቆ ይገባል፡፡….ይሄን ጊዜ ደግሞ “ለእግረኛ ቅድሚያ ባለመስጠት!” በሚለው ሪፖርት ስር አብዛኛውን ጊዜ በመገናኛ ብዙሃን የሚዘገበው  የትራፊክ አደጋ ይከሰታል፡፡….በየት እንለፍ?
ትዝብቱ የህገ-ወጥ ነጋዴዎቹ ብቻ አይደለም፤ የሸማቹም ጭምር እንጂ፡፡ በዕቅድ የመገበያየት ልምዱ እምብዛም የሌለው የከተማዋ ነዋሪ፤ ቅዳሜና እሁድን ጠብቆ አስፋልት እየተዘጋ በሚካሄደው ግብይት ብዙ ተሳታፊ አይደለም፡፡ እግረመንገዱን ወደ ስራው ሲሄድ አልያም ከስራው ሲመለስ መንገድ ላይ “በቅናሽ” ሲባል የሚሰማውን ሁሉ ሊያግበሰብስ ሲጋደል እታዘበዋለሁ፡፡ “ሶስቱን ሰርቪስ ትሪ መቶ-መቶ ብር” ሲባል መሸመት፣ “ሻርፕ በ50 በ50 ብር” ሲባል መጋደል፣” “ሰዓት በ75 ብር ሲባል …..”
ከእዚህ አሰቃቂ ትርዒት እልፍ ሲሉ ደግሞ ወኔን ቁርጥ የሚያደርግ፣ ሃሞትን ፍስስ የሚያደርግ የታክሲ፣ የሃይገር ባስና የአውቶብስ ጠባቂዎች ወረፋ መንገዱን ዘግቶት ይታያል፡፡ በየት እንለፍ?….የሚገነቡ ህንፃዎች ፓርኪንግ ስለሌላቸው መኪኖች የእግረኛ መንገድ ላይና አስፋልት ዳር መኪና ያቆማሉ፡፡ ከዚያ እንደምንም ተሽሎክሉኮ ሲታለፍ ደግሞ የኔ-ቢጤዎች ልጆቻቸውን ይዘውና ምንጣፋቸውን ዘርግተው “እያያችሁ አትለፉን!” ይላሉ። ሳንቲም ዘርዛሪ ወጣቶች መሬት ላይ ሳንቲማቸውን ደርድረው ግዛታቸውን ሲያስጠብቁ ይታያል፡፡ በእጅ በሚገፉ ጋሪዎች የሚሸጡ ነገሮች ተሞልተው አጠገብ ላጠገብ ተቀጣጥለው “ማለፍ ክልክል ነው!” ይሉናል፡፡
የተቆፋፈሩ መንገዶች እስካሁንም ቁፋሮአቸው አልተጠናቀቀም፡፡ ሰውም፣ መኪናም፣ እንስሳትም ጉድጓድ ውስጥ ገብተው አደጋ ሲደርስባቸው አይተናል፣ ሰምተናል፡፡ መንገዶች እየተዘጉ ተለዋጭ መንገዶች ግን በአግባቡ ሳይዘጋጁ እየቀሩ፣ ዛሬ ዛሬ መንገድ በራሱ ብርቅ ሊሆንብን እኮ ነው፡፡ መንገድማ ድሮ ቀረ ብለን ልንተርትም ደርሰናል፡፡ በከተማዋ አውራ መንገዶች የእግር ጉዞ/ዎክ ማድረግ ሩቅ እየሆነ ነው፡፡ ብስክሌት/ሳይክል መንዳት የማይታሰብ እየመሰለ ነው፡፡ በየት እንለፍ?
የደንብ ማስከበር ስራዎችን የሚሰሩ የየቀበሌዎቹ ምድቦች (ራሳቸው ተክለ ሰውነታቸው ድቅቅ ያሉ ነገሮች) ህገ-ወጦችን ማባረር ካቅማቸው በላይ የሆነባቸው ይመስላል፡፡ አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉት ፖሊሶችም ነገሩ ሳያታክታቸው አልቀረም፡፡ እያዩ እንዳላዩ መሆን ጀምረዋል፡፡ አዲስ አበባ መንግስት ያላትም አትመስልም፡፡ መንግስት ካለም ትኩረቱ ለህንፃ ግንባታዎች ብቻ የሆነም ያስመስልበታል፡፡
በገዛ ብራችን!
በየመኖሪያ ቤታችን መብራትና ውሃ አለመኖሩን መቼስ ተላምደነዋል፡፡ ተንቀሳቃሽ ስልካችንን አንስተን መደወል አልያም ካርድ ለመሙላት ስንፈልግ ረዘም ላሉ ደቂቃዎች መታገስ መቻልም ተዋህዶናል፡፡ ነገር ግን የገዛ ብራችንን፣ ለባንክ በአደራ መልክ “አስቀምጥልን” ብለን የሰጠነውን ገንዘባችንን ለማውጣትስ እንዴት “በኔትዎርክ የለም” ይሳበባል?…ብር ከባንክ የሚወጣበትን ምክኒያት ቤቱ ይቁጠረው! ………ስንት ነገር አለ፡፡ የባንክ አስተዳደሮች ግን ለዚህ ብዙም ግድ የሰጣቸው አይመስልም፡፡ ሱፍ በለበሱ ሰራተኞቻቸው አማካኝነት “ኔትዎርክ የለም!” ያስብሉናል፡፡ ሃላፊነቱን ወደ ቴሌ ያላክካሉ፡፡ ሌላ መፍትሄ ሲፈልጉ አይታዩም። በ“እኔ ምን ላድርጋችሁ?” ዓይን እኛኑ ላይ መልሰው ያፈጡብናል። የገዛ ብራችንን ለማውጣት፣ የገዛ ደሞዛችንን (በባንክ ለሚከፈላቸው) ለመውሰድ እንዴት መከራ ማየት ይገባናል?
ጡረታ መቀበል፣ ኮንዶሚኒየም መክፈል፣ ከውጪ የተላከ ብርን መውሰድ፣ ወደ ተለያዩ ክልሎች ለተማሪዎች የሚላኩ ተቆራጮችን መላክ ወዘተ አልተቻለም፡፡ “እዛኛው ቅርንጫፍ ሞክሩ” እንባላለን፡፡ እዚያ ስንሄድ ደግሞ “እዚያኛው ብትሞክሩስ!” እየተባለ ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ በመባከን ላይ ነው፡፡ “ታገሱን” ይባላል፡፡ እስከመቼ እንደሆነ ግን የቁርጥ ቀኑ አይነገረንም፡፡
ዝም ብሎ “እስኪ አንተ ታውቃለህ!…. እንዳደረክ አድርገኝ” ከሚል ፀሎት አልፎ “እንዴት? ለምን?” የሚል ሁሉ የሚጠብቀው ሌላ ነገር ስለሆነ፣ የሆዱን በሆዱ ይዞ በገና ለገና “ኔትዎርኩ ሊመጣ ይችላል” ጉጉት የባንኩን የእንግዳ መቀመጫ ወንበር ሲያሞቅ ውሎ ያመሻል፡፡
በገዛ ገንዘቡ…
ደሞዝ ሳይጨመርልን ዋጋ ተጨመረብን!
መንግስት “ደሞዝ ጨመረ” የተባለው ለመንግስት ሰራተኞች ብቻ ነው፡፡ አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ የመንግስት ሰራተኛ አይደለም፡፡ ጭራሹኑም ስራ የሌለውም ሞልቶ ተትረፍርፎአል፡፡ ገቢው አነስተኛው፣ ምንም ገቢ የሌለው፣ ለማኙና ሌላውም ሁሉ የዚህች ከተማ ነዋሪ የመንግስትን ደሞዝ ጭማሪ ምክኒያት በማድረግም ባለማድረግም በሁለቱም ወቅቶች ህገ-ወጥ ነጋዴዎች የሚከምሩትን የዋጋ ጭማሪ እንዴት ለመቋቋም ይቻለዋል?
ዛሬ ዛሬ የቀድሞ ዋጋዎች ሁለትና ሶስት እጥፍ ቢያሻቅቡ ህዝቡ “ተመስገን” ይላል፡፡ ምክኒያቱም ዋጋዎች እየናሩ ያሉት በመቶና በሁለት መቶ እጥፍ ነውና፡፡ የጤፍ፣ የበርበሬ፣ የቤት ኪራይ፣ የትራንስፖርት ወዘተ ዋጋዎችን ልብ ይሏል! የሸማቾች ህብረቶችና አለ በጅምላ በየዕለቱ እንደጉድ እየናረ ያለውን የዋጋ ጭማሪ ሊያስታግሱት አልተቻላቸውም፡፡ ነጋዴዎች የመንግስትን ማስፈራሪያ እየሰሙ ያሉ አይመስልም፡፡ ደሞዝ ያልተጨመረለት፣ ወይንም ጭራሹኑም ደሞዝ የሌለው ሰው፣ ደሞዝ የተጨመረለት ሰራተኛም ቢሆን በአንድነት የኑሮ ውድነቱን እየጎመዘዘው በመጎንጨት ላይ ይገኛል፡፡
ጉጉት…ተስፋ….ምኞት……ብቻ!
ኮንዶሚኒየም ይደርሰናል ብለን በተስፋ እየተጠባበቅን ነው፡፡ የከተማዋ መንግስት ግን “እኔ ብቻ ነኝ እውነተኛው አማራጭ!” የሚል በሚያስመስልበት ሁኔታ የከተማዋን ነዋሪ የቤት ፍላጎት ሊያሟላ ይባክናል። የተመዘገበውና በጉጉት ዕጣ የሚጠብቀው ቁጥር የከተማዋ መንግስት በዓመት ከሚገነባቸው ውስን ቁጥር ያላቸው ቤቶች አንፃር ሲመዘን ጭራሹኑ የማይመጣጠን ነው፡፡ የአዲስ አበባ መንግስት እስካሁንም በ1997 ዓ.ም ለኮንዶሚኒየም ቤቶች የተመዘገቡትን ነዋሪዎች ፍላጎት ሳያሙዋላ 10 ዓመታት ተቆጠሩ። በ10 ዓመታት ውስጥ ደግሞ እልፍ አዕላፋት ቤት ፈላጊዎች ተፈለፈሉ፡፡ ጉጉት፣ ተስፋ፣ ምኞት ብቻ!
መንግስት ለሌሎች አማራጮች እስካሁንም በሩን አልከፈተም፡፡ “ለቱርክ፣ ለቻይና፣ ለአሜሪካ ወዘተ ኢንቨስተሮች አማራጭ ልንሰጥ ነው!” ይባላል፣ እስካሁን ድረስ ግን በተግባር ጠብ ሲል አላየንም፡፡ መንግስት ለራሱ የሚያደርገውን ድጋፍና ማበረታቻ ለአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ብቻ እንኳን ቢያደርግ (ከሊዝ ነፃ መሬት፣ ከታክስ ነፃ ቁሳቁሶችና አቅርቦቶች፣ የረጅም ጊዜ ብድር ወዘተ) የመኖሪያ ቤቱ እጥረት በስንት እጥፍ በተቃለለ! ግን ጉጉት፣ ተስፋ፣ ምኞት ብቻ!
በየዓመቱ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ነገር የአዲስ አበባን መንግስት እየተገዳደረው እንደሆነ ይታወቀኛል፡፡ መንግስት ለሁሉም ተመራቂያን ያዘጋጀው ጎጆ አንድ ብቻ ይመስል “በጥቃቅንና አነስተኛ መደራጀት፣ ስራን ሳይንቁ መስራት…ኮብል ስቶን…ከብት ማርባትና ማደለብ” ወዘተ ይላል፡፡ ከእነዚህ ውጪ ተሰማርተው የፈጠራ ስራ ለሚሰሩ ወጣቶች የተመቻቸ ነገር የለም፡፡ ለምሳሌ የቴአትር ተመራቂዎች ፊልም ለመስራት ቢፈልጉና ለፊልማቸው የሚሆናቸውን ወጪ ለመሸፈን የአምስት መቶ ሺህ ብር ብድር ቢጠይቁ የትኛው ባንክ…የትኛው የቁጠባ ተቋም ነው ሊያበድራቸው የሚችለው?….ሲያምራቸው ይቀራል እንጂ!…ጉጉት፣ ተስፋ፣ ምኞት ብቻ!
የትራንስፖርቱ ሁኔታ ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ነገ እየባሰበት እየሄደ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ዝርጋታ በታሰበው ፍጥነት እየሄደ ነው የሚል ዕምነቱ የለኝም፡፡ የሆነው ሆኖ ባቡሩ ጉጉታችን፣ ተስፋና ምኞታችን ነው፡፡
ሆኖም ግን አሁን በሚታየው መልኩ በከተማዋ የነዋሪው ቁጥር እንዲህ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ እየመጣ ባለበት ሁኔታ ዕውን የባቡር ዝርጋታው መጠናቀቅ የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ችግር ሊፈታላት ይችላል የሚለው ትልቅ ጥያቄ የሚፈጥር ነው፡፡ ለዚህም ጠዋትና በስራ መውጫ ሰዓት ላይ የከተማዋ ነዋሪ የትራንስፖርት ፍላጎትን ብቻ በማየት ነገሩን ለመገመት ይቻላል፡፡
ጎን ለጎን ሌሎች መፍትሄዎች በአስቸኳይ የማይታሰቡ ከሆነና ባቡሩን ብቻ የችግሩ ፈቺ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ማሰቡ፤ ለእኔ  ጉጉት፣ ተስፋ፣ ምኞት ብቻ ነው የሚሆንብኝ፡፡
እነሆ የአዲስ አበባ መንግስት የት ነው ያለኸው?
እስቲ ምርጫ ከመድረሱ በፊት የእውነት የዕውነቱን እንነጋገር፡፡ አዲስ አበባ በብዙ ነገሮች ቅጥ እያጣች በመምጣት ላይ አይደለችምን?….የከተማዋ አመራር ከከንቲባ እስከ ደንምብ ማስከበር አዲስ አበባ ያቃተቻቸው አይመስልምን?..ህገ-ወጦች እንዳሻቸው የሚፈነጩባት አዲስ አበባ ለመኖሪያነት እያስቸገረችን አይደለምን?…
መጤ ድርጊቶች ከተማዋን እንደጉድ ወረዋት አዲስ አበባ በጭንቀት ተወጥራለች፡፡ ከጫት እስከ ሺሻ…ከእስቲም እስከ ልቅ ማሳጅ፣ ከሴተኛ አዳሪነት እስከ ግብረሰዶማዊነት፣ ከስራ አጥነት እስከ ማጅራት መቺነት፣ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ የመኪና ዕቃዎች ስርቆት፣ ማታለልና ማጭበርበር ወዘተ የዕለት ተዕለት ዜናዎች ሆነው እየሰማንም እያየንም ነው፡፡
በራሱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገንዘብ ድጋፍ በከተማዋ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ በተካሄደው ሰፊ ጥናት፤ አዲስ አበባ በመጤ ልማዳዊ ድርጊቶች እየተዋጠች ነው፡፡ በባህልና በማህበራዊ ስልጣኔዋ አዲስ አበባ ቁልቁል እየገሰገሰች ትገኛለች። ጥናቱ እያንዳንዱን ነዋሪ በሚያስደነግጥ መልኩ ዕውነታዎችን ፍንትው አድርጎ ሲያሳይ ማንም ልቡ ይሰበራል፡፡ ማንም ወይ አዲስ አበባ እያለ በሃዘን አንገቱን መድፋቱ፣ ደረቱን መደለቁ፣ ፀጉሩን መንጨቱ አይቀሬ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ያለእንከን ተሰርቶ ሲጠናቀቅ የማየው ፎቅ ብቻ ነው፡፡ ፎቆቹ የማናቸው የሚል ጥያቄ አሁን አላነሳም፡፡ የማንም ይሁኑ የከተማችን ድምቀቶች ናቸው።
ነገር ግን የአንድ ከተማ ስራ፣ ህንፃ መገንባት ብቻ አይደለም፡፡ በነዋሪው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ባህላዊና የጤና ጉዳዮች ዙሪያ ወዘተ እኩል መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ለልጆች መጫወቻና ለአረጋውያን ማረፊያ የሚሆኑ ክፍት ቦታዎች እያጣን ባለንበት በዚህ ወቅት፣ ከተማዋን በዓለም ካሉ 10 የቱሪዝም መዳረሻዎች አንዱዋ የማድረግ ህልም ሊሰምር አይቻለውም፡፡
የአዲስ አበባ መንግስት ካለህበት ሆነህ ድምፅህን አሰማ! እነሆ የት ነው ያለኸው?
መልሱ “ኮንዶሚኒየም እያስገነባን፣ ቀላል ባቡር እየዘረጋን፣ ከተማዋን በህንፃ እያስዋብን፣” ወዘተ በሚል ሰበባ ሰበብ ሊድበሰበስ አይገባውም፡፡ እስቲ ምርጫ ከመድረሱ በፊት የእውነት የእውነቱን እንነጋገር፡፡………የአዲስ አበባ መንግስት ካለህበት ሆነህ ድምፅህን አሰማ! እነሆ የት ነው ያለኸው?

ምንጭ፦ አዲስ አድማስ

Articles

የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ተሳትፎ ድህረ ምልከታ

Published

on

Medal Winners

በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በወረቀት ደረጃ ከውድድሩ መጀመር በፊት ቡድኑ ባመዛኙ በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኙ ወጣት አትሌቶችን ስላካተተ ቢያንስ የለመድናቸውን ሁለት ወይም ሶስት የወርቅ ሜዳልያ ድሎች እንደማያሳጣን ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ ሆኖም የሜዳ ላይ ውጤቱ እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ኢትዮጵያ በውጤታማነቷ በምትታወቅበት የአትሌቲክስ ፉክክር በአንድ የወርቅ፣ አንድ የብር፣ እና ሁለት የነሐስ በድምሩ በአራት ሜዳልያዎች ከዓለም 14ኛ ከአፍሪካ 3ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች፡፡ ይህም ሁሌም ለአፍሪካ የበላይነት ከምንፎካከራት ኬንያ ጋር ያለን ልዩነት ይበልጥ እንዲሰፋ አድጎታል፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ሌላኛዋ የምስራቅ አፍሪካ ተቀናቃኛችን እየሆነች ከመጣችው ኡጋንዳም አንሰን እንድንገኝ አድርጎናል፡፡ የቶኪዮ ኦሊምፒክ በአትሌቲክሱ ከ1992ቱ የባርሴሎና ኦሊምፒክ ወዲህ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሜዳልያ ስኬት ያስመዘገበችበትም ሆኖ አልፏል፡፡

አሉታዊ ጎኖች
ቶኪዮ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤታማነት ፈር ቀዳጅ የሆነው ታላቁ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ በ1964 ዓ.ም. በተከታታይ ሁለተኛ የኦሊምፒክ ማራቶን ድሉን የተቀዳጀባት ከተማ ናት፡፡ እናም በቶኪዮ ከተማ በተከናወነው የኦሊምፒክ ውድድር የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የሱን ክብር የሚያጎሉባቸውን ነገሮች ያደርጋሉ ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ የሆኑት ነገሮች ግን በተለይ በቡድኑ አስተዳዳሪዎች በኩል ፍፁም ኃላፊነት የጎደለውና ከጠበቅኩት በተቃራኒው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከአትሌቶች ምርጫ አንስቶ በቡድኑ የዝግጅት ወቅት በተካረረ ውዝግብ ውስጥ ነበር የከረሙት፡፡ የኦሊምፒክ ቡድኑን የማዘጋጀት እና የመምራት የጋራ ኃላፊነት የነበረባቸው ሁለቱ አካላት ይባስ ብለው ውዝግቡን ቶኪዮ ድረስ ይዘውት ሄደዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ሁለቱን አካላት በማቀራረብ በትልቁ ውድድር ላይ ያለንን ተሳትፎ እንከን አልባ ማድግ የሚጠበቅባቸውም ተመልካች ከመሆን የዘለለ ሚና አልነበራቸውም። የውዝግቡ አሉታዊ ትሩፋት በአትሌቶች ስነልቦና እና በአጠቃላይ የቡድኑ ውጤት ላይ የበኩሉን ተፅዕኖ ሳያሳርፍ እንዳላለፈ አያጠራጥርም፡፡

እንደ አለመታደል ሆኖ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያን ልዑካን የመምራት ትልቁ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ኃላፊነት የጎደላቸው ነበሩ። የስፖርቱ አስተዳደሪዎች ትላልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በመጡ ቁጥር በአትሌቶች ምርጫ ዙሪያ የነበረውን ውዝግብ እንዲያቆሙልን እመኝ ነበር። ጭራሽ እራሳቸው ችግር ፈጣሪ ሆነው መገኘታቸው አስደንጋጭ እና አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በመሮጫ መም ወይም በጎዳና ላይ በሚደረጉ ውድድሮች መሸነፍን በስፖርቱ ውስጥ ማሸነፍ እና መሸነፍ ያሉ የነበሩ እና ወደፊትም የሚኖሩ ነገሮች ስለሆኑ በፀጋ መቀበል ይቻላል፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑ የስነልቦና ጥንካሬን ሊፈጥሩላቸው የሚገቡ ኃላፊዎች የእርስ በርስ ሽኩቻ ተቃራኒውን አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳርፍ ማየት ግን ፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ ለነገሩ ከስፖርቱ እድገት ይልቅ የፖለቲካ ግዴታቸው የሚያስጨንቃቸው የስፖርት አመራሮች በበዙባት ሀገር ስፖርቱ እንዲህ የማንም መጫወቻ ሲሆን ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡  

የስፖርት አመራሮች ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ሆነው ትኩረታቸውን ስፖርቱን በማስፋፋቱ እና ማሳደጉ ላይ አድርገው የሚሰሩ ስለስፖርቱም በቂ እውቀት እና ፍቅሩ ያላቸው ቢሆኑ መልካም ነው፡፡ ለቦታው በሚመጥን እና ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት በሚችል የስፖርት አመራር የሚመራ የስፖርት ተቋምን መገንባት በተመሳሳይ ሰዓት የሀገር ግንባታን የሚደግፉ ሶስት ነገሮችን ስኬታማ ያደርጋል፡፡ በስፖርት ጤናውን የሚጠብቅ ማሕበረሰብ በመፍጠር በጤናው ሴክተር ላይ የሚኖረውን ጫና ይቀንሳል፣ በሀገር ገፅታ ግንባታ እና በኢኮኖሚው ዕድገት ላይም የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ በቶኪዮ ላይ የተመለከትናቸው የሀገርን ክብር ዝቅ ያደረጉ ግዴለሽነቶች ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊታዩና አጥፊዎቹ ሊጠየቁበት ይገባል፡፡ በመጪዎቹ ዓመታት በሚጠብቁን ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይም የቶኪዮ ኦሊምፒኩን አይነት ሀፍረት እንዳይገጥመን ከወዲሁ ለችግሮቹ መፍትሔ መፈለግ አለበት፡፡

ባለፉት ዓመታት ኦሊምፒክ በመጣ ቁጥር በልዑካን ቡድኑ ውስጥ እየተካተቱ በሕዝብ ገንዘብ የሚዝናኑት የኦሊምፒክ ቱሪስቶች ጉዳይ ዘንድሮም ያልተቀረፈ ችግር ሆኖ ተስተውሏል፡፡ ከሌላው ግዜ በተለየ መልኩ ተጠባባቂ አትሌቶችን ይዞ መጓዝ ይጠይቅ በነበረው ውድድር ላይ አትሌቶቹን ትቶ ምንም የማይሰሩ ሰዎችን ይዞ መሄድ ትልቅ ቀልድ ነው፡፡  

ከሜዳ ውጭ የነበረው ውዝግብ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል የነበረ መሆኑ በሜዳ ላይ የነበሩብንን ድክመቶች ሊያስረሳንም አይገባም፡፡ ስድስት የጎዳና ላይ ተወዳደሪዎቻችን እና አንድ የመም ተወዳዳሪ ውድድራቸውን ማቋረጣቸው በቶኪዮ ከታዩት ደካማ ጎኖቻችን መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ ችግሩ በዚህ ምክንያት ነው የተከሰተው ብሎ ለይቶ ለመናገር ባይቻልም ብዙ ግዜ ሲፈትነን ለሚስተዋለው የሞቃታማ ቦታ ውድድር የምናደርጋቸው ዝግጅቶችን መለስ ብሎ መመልከትን የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ የተጎዳች አትሌትን ወደውድድር እንድትገባ ማድረግ እና በሁለት ደቂቃ ውስጥ ለማቋረጥ መገደዷም የአትሌቶች የጤና ክትትል ላይ ክፍተት እንዳለ የጠቆመን ክስተት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ወደውድድር ስፍራው ካቀናበት ግዜ ጀምሮ በቶኪዮ ምንም አይነት ቡድኑን የተመለከቱ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ወይም ፕሬስ ሪሊዞች አልነበሩም፡፡ ይህም እንደተለመደው የሕብረተሰቡን እና የመገናኛ ብዙሀንን ስለቡድኑ ቀጥተኛ መረጃ የማግኘት መብት የገደበ ነበር፡፡ ጋዜጠኞችም ሚዛናዊ ሆኖ ከመዘገብ ይልቅ ጎራ ለይተው ቃላት መወራወራቸው የህዝብን ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት የነፈገ ነው፡፡ 

አዎንታዊ ጎኖች
ሰለሞን ባረጋ በወንዶች 10,000 ሜትር ወርቅ፣ ለሜቻ ግርማ በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ብር፣ ጉዳፍ ፀጋዬ በሴቶች 5000 ሜትር ነሐስ፣ እና ለተሰንበት ግደይ በሴቶች 10,000 ሜትር ነሐስ ማስመዝገብ መቻላቸው የሚደነቅ ስኬት ነው፡፡

የመጪው ትውልድ አካል የሆኑት ተስፈኞቹ መቅደስ አበበ፣ ፍሬወይኒ ሀይሉ፣ በሪሁ አረጋዊ እና ጌትነት ዋለን ጨምሮ አምስት አትሌቶች ለሜዳሊያ የቀረበ የአራተኛነት ደረጃን ይዘው ማጠናቀቅ መቻላቸውም መልካም ነው፡፡ በተለይ ወጣቶቹ ያስመዘገቡት ውጤት በመጪዎቹ ዓመታት ተገቢውን ድጋፍ ካገኙ የምንጓጓለትን ድል ሊያስገኙልን እንደሚችሉ ያመላከተን ነው፡፡

የሀብታም አለሙ በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በሴቶች 800 ሜትር ለመጀመሪያ ግዜ ለፍፃሜ ተወዳዳሪነት መብቃት ምንም እንኳ በፍፃሜው የሜዳልያ ድል ባይቀናትም በአዎንታዊ ጎን ሊጠቀስ የሚችል ስኬት ነው፡፡

ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃን ይዘው ላጠናቀቁ አትሌቶች በሚሰጥ ነጥብ ድምር መሰረት በወጣው የነጥብ (ፕሌስመንት) ደረጃ ሰንጠረዥ ላይ በ64 ነጥብ ዘጠነኛ ሆነን ማጠናቀቃችንም እሰየው የሚያስብል ነው፡፡

በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከአራተኛ እስከ ስምንተኛ ባሉት ደረጃዎች ውስጥ አጠናቀው ነጥብ ያስገኙ እና የዲፕሎማ ተሸላሚ የሆኑት አትሌቶች፡-
4ኛ – ፍሬወይኒ ሀይሉ – በሴቶች 1500 ሜትር
4ኛ – መቅደስ አበበ – በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል
4ኛ – ሮዛ ደረጀ – በሴቶች ማራቶን
4ኛ – በሪሁ አረጋዊ – በወንዶች 10,000 ሜትር
4ኛ – ጌትነት ዋለ – በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል
5ኛ – እጅጋየሁ ታዬ – በሴቶች 5000 ሜትር
6ኛ – ሀብታም አለሙ – በሴቶች 800 ሜትር
6ኛ – ሰንበሬ ተፈሪ – በሴቶች 5000 ሜትር
8ኛ – ዮሚፍ ቀጄልቻ – በወንዶች 10,000 ሜትር
8ኛ – ዘርፌ ወንድማገኝ – በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል

  • የአትሌቲክስ የነጥብ ደረጃ ሰንጠረዥ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ባሉት ደረጃዎች ውስጥ የሚያጠናቅቁ አትሌቶች በሚያስመዘግቡት ነጥብ ድምር መሰረት የሚወጣ ሲሆን የነጥብ አሰጣጡም ለአንደኛ ደረጃ 8 ነጥብ፣ ለሁለተኛ ደረጃ 7 ነጥብ፣ ለሶስተኛ ደረጃ 6 ነጥብ፣ ለአራተኛ ደረጃ 5 ነጥብ፣ ለአምስተኛ ደረጃ 4 ነጥብ፣ ለስድስተኛ ደረጃ 3 ነጥብ፣ ለሰባተኛ ደረጃ 2 ነጥብ፣ እና ለስምንተኛ ደረጃ 1 ነጥብ ነው።

ከፊታችን ምን  እየጠበቀን ነው? ምንስ እናድርግ?
ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፉ ወረርሺኝ ምክንያት ትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለሌላ ግዜ እንዲተላለፉ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ሌላ አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ቀጣዮቹ አራት ዓመታት በተከታታይ በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች የሚካሄዱባቸው ይሆናሉ፡፡ በ2022 የዓለም ሻምፒዮና፣ በ2023 የዓለም ሻምፒዮና፣ በ2024 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች፣ እና በ2025 የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ይኖራሉ፡፡ በቀጣዩ ዓመት በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ከሐምሌ 8 – 17/2014 በዩናይትድ ስቴትስ ኦሪጎን የሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዘጋጆች ሙሉ የውድድሩን ፕሮግራም፣ የማራቶን እና የእርምጃ ውድድሮች የሚካሄዱባቸውን ቦታዎች በትላንትናው ዕለት ይፋ አድርገዋል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናውን ውድድር በኃላፊነት የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ከወዲሁ ለዛ ውድድር ተሳትፎ የሚጠበቅበትን አቅዶ መንቀሳቀስ ይኖበርታል፡፡

ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጭቅጭቆችን ለማስቀረት ከወዲሁ ሁሉም አትሌቶች አውቀውት በውስጡ የሚያልፉበትን ገዢ የሆነ የመምረጫ መስፈርት ማዘጋጀት ቀዳሚው ተግባር መሆን አለበት፡፡ የመምረጫ መስፈርት ሁልግዜም በግላዊ ምልከታ እና ፍላጎቶች ላይ በሚመሰረት ምክንያት አነጋጋሪ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ቢሆንም ባለድርሻ አካላቱን በሙሉ ባሳተፈ መልኩ ውይይት ተደርጎበት ቢወጣ ሁሉንም ገዢ እና ከጭቅጭቅ የፀዳ ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህ ላይ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከተከሰቱት ሁኔታዎች አንፃር የሌሎች ሀገሮችንም ተሞክሮዎች በመዳሰስ ነገሩን ሰፋ አድርጎ መመልከት ቢቻል ጥሩ ነው፡፡ ትልልቅ ውድድሮች በመጡ ቁጥር በተደጋጋሚ እንደታዘብነው አንዳንድ አትሌቶች በቡድኑ ውስጥ ለመካተት የሚያደርጉትን ተገቢ ያልሆነ ሙከራም ማቆም አለባቸው፡፡ ከፋም ለማም ስፖርቱን እንዲመራ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም የሚያወጣቸውን መስፈርቶች ማክበርና በዛ ውስጥ ተመራጭ ለመሆን መሞከር ግድ እንደሚላቸውም መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ማኔጀሮች እና አሰልጣኞች በተለይ በማራቶን የራሳቸውን አትሌት ለማስመረጥ የሚያደርጓቸው አላስፈላጊ ግፊቶችም ሊያቆሙ ይገባል፡፡

ለውድድሮች የምናደርጋቸውን ዝግጅቶች ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ከውድድሮች በኋላ መገምገም እና መታረም ያለባቸው ነገሮች ካሉ ማረም፡፡ ከፍተኛ ሙቀት በነበረባቸው በለንደን 2012 ኦሊምፒክ ሶስቱም የወንዶች ማራቶን ተወዳዳሪዎቻችን፣ በሞስኮ 2013 የዓለም ሻምፒዮና ሁለቱ የሴቶች ማራቶን ተወዳዳሪዎቻችን፣ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ አምስት የማራቶን (ሶስቱም ወንዶች እና ሁለት ሴቶች) ተወዳዳሪዎቻችን እንዲሁም የሴቶች እርምጃ ተወዳዳሪያችን ለማቋረጥ መገደዳቸውን አስተውለናል፡፡ ስለዚህ በጎዳና ላይ ውድድሮች ከባድ ሙቀት ለሚኖርባቸው ቦታዎች እንዴት መዘጋጀት አለብን የሚለው ጉዳይም በደንብ ሊታይ የሚገባው ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ የመም (ትራክ) ተወዳዳሪ አትሌቶቻችን የውድድር ዓመቱ ሲጀምር ድንቅ ብቃታቸውን ያሳዩን እና ወደትልቅ ውድድር ሲቃረቡ አቋማቸው እየወረደ ይመጣል፡፡ አሰልጣኞቻቸው ለእነዚህ አይነቶቹ አትሌቶች ወደትልቅ ውድድር ሲቃረቡ ብቃታቸውን እያሳደጉ እንዲሄዱ የሚረዳቸውን የልምምድ ፕሮግራም ቢያዘጋጁላቸው መልካም ነው፡፡ በመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ላይ በተለይ በወንዶች አሁንም በከፍተኛ ደረጃ የሚፎካከሩ አትሌቶችን ለማፍራት ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል፡፡

Continue Reading

Articles

የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የቶኪዮ ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ማጣሪያ ውድድሮች የመጀመሪያ ሁለት ቀናት

Published

on

በሴቶች 5000 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ላይ የሚፎካከሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች

በቶኪዮ ኦሊምፒክ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት የኢትዮጵያ አትሌቶች የተሳተፉባቸው የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል፣ 800 ሜትር በሁለቱም ፆታዎች፣ እንዲሁም የሴቶች 5000 ሜትር ማጣሪያዎች ሌላኛዎቹ የኢትዮጵያውያን የትኩረት ማዕከል የነበሩ ውድድሮች ናቸው፡፡ ቀጣዩ ዘገባ የኢትዮጵያውያኑን የማጣሪያ ውድድሮች ተሳትፎ እና ውጤቶች አንዲሁም ተጨማሪ መረጃዎችን ይዟል፡፡

የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል

በአትሌቲክስ ውድድሩ የመክፈቻ ቀን (ዓርብ ሐምሌ 23/2013) ጠዋት ላይ በተካሄደው የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ማጣሪያ ከተሳተፉት ሶስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ከምድብ አንድ ለሜቻ ግርማ (8፡09.83) በአንደኛነት፣ ከምድብ ሁለት ጌትነት ዋለ (8፡12.55) በሁለተኛነት ለፍፃሜው ሲያልፉ በምድብ ሶስት የተወዳደረው ታደሰ ታከለ (8፡24.69) ስምንተኛ ወጥቶ ለፍፃሜው ሳያልፍ ቀርቷል፡፡ ለሜቻ ጃፓናዊው ሚዩራ ዩጂን እና ኬንያዊው ቤንጃሚን ኪይገንን በማስከተል ከምድቡ ያሸነፈበት 8:09.83 በኦሊምፒክ የማጣሪያ ውድድሮች ላይ የተመዘገበ የምንግዜውም ፈጣን ሰዓት ሆኗል፡፡ የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል የፍፃሜ የሜዳልያ ፉክክር በዋናነት በኬንያውኑ ቤንጃሚን ኪገን እና አብራሀም ኪቢዎት፣ በኢትዮጵያውያኑ ለሜቻ ግርማ እና ጌትነት ዋለ እንዲሁም በሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ መካከል እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል በ1980ው የሞስኮ ኦሊምፒክ በሻምበል እሸቱ ቱራ አማካይነት ካስመዘገበችው የነሐስ ሜልያ ድል ወዲህ በርቀቱ በወንዶች ምንም አይነት የኦሊምፒክ ሜዳልያ ድል የላትም፡፡ ሆኖም ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየታዩ የመጡ መሻሻሎች እና በዶሀው የዓለም ሻምፒዮና ላይ የተመዘገበው የብር ሜዳልያ ድል በቶኪዮም ሌላ ሜዳልያን ተስፋ እንድናደርግ ያነሳሳን ሆኗል፡፡ ዘግይቶ የተሰላፊ አትሌቶች ለውጥ ከተደረገባቸው ርቀቶች አንዱ በሆነው የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል በተጠባባቂነት የተመዘገበውና በዋናነት በ5000 ሜትር እንደሚወዳደር ይጠበቅ የነበረው ጌትነት ዋለ ወደመጀመሪያ ተሰላፊነት የመጣ ሲሆን ኃይለማሪም አማረ በመጨረሻ ሰዓት በለሜቻ ግርማ መተካቱም አነጋጋሪ የሆነ ሌላኛው ለውጥ ነው፡፡ ጌትነት በ3000 ሜትር መሰናክልም ጠንካራ ተፎካካሪ አትሌት ሲሆን በዶሀ የዓለም ሻምፒዮና ላይ አራተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ በፍፃሜው ውድድር በ2019 የርቀቱ የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮን ጌትነት ዋለ እና በወቅቱ የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊስት ለሜቻ ግርማ የሚወከለው የኢትዮጵያ ቡድን በቶኪዮ የኬንያውያኑን የበላይነት ለመግታትና አዲስ የስኬት ታሪክ ለማፃፍ እንደሚበቃ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡                     

በ1984 በሎስ አንጀለስ ከተከናወነው የኦሊምፒክ ውድድር አንስቶ በተከታታይ በዘጠኝ የኦሊምፒክ ውድድሮች ወይም ላለፉት 36 ዓመታት የኦሊምፒክ የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል የወርቅ ሜዳልያ ድል በኬንያውያን ቁጥጥር ስር ይገኛል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናም ተመሳሳይ የበላይነት ያላቸው ኬንያውያን ከ17 የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች በ14ቱ የወርቅ ሜዳልያው አሸናፊዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ከሁለት ዓመት በፊት በዶሀው የዓለም ሻምፒዮና ላይ ከኢትዮጵያውያን እና ከሞሮኮ አትሌቶች የገጠማቸው ተግዳሮት ለመሸነፍ እጅግ አቅርቧቸው የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ በአንድ ማይክሮ ሰከንድ ልዩነት አሸናፊነታቸውን ባረጋገጡበት በዶሀው ውድድር የተፈታተኗቸው ኢትዮጵያዊው ለሜቻ ግርማ እና ሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ በቶኪዮው ፍፃሜ ለሌላ ብርቱ ፉክክር እየጠበቋቸው ይገኛሉ፡፡ ባለፉት ሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች በቅደም ተከተል የብር እና የነሐስ ሜዳልያን ያገኘው ሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ በቶኪዮ ከሚወዳደሩት በሙሉ የላቀና 7፡58.15 የሆነ የራሱ ምርጥ ሰዓት ያለው ነው፡፡

ኬንያ በቶኪዮ ያለፈው ውድድር ሻምፒዮንነቱን ክብር የሚያስጠብቅላትን አትሌት ይዛ መቅረብ ሳትችል ቀርታለች፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት በሪዮ የኦሊምፒክ እንዲሁም ከሁለት ዓመት በፊት በዶሀ የዓለም ሻምፒዮን የሆነው ኮንሰስለስ ኪፕሩቶ ባለፈው ወር በኬንያ የኦሊምፒክ ምርጫ ውድድር ላይ ውድድሩን ባለማጠናቀቁ የኦሊምፒክ ሻምፒዮንነት ክብሩን ለማስጠበቅ በቶኪዮ አልተገኘም፡፡ ስለዚህ አሁን የረጅም ግዜ የበላይነታቸውን የማስጠበቅ ኃላፊነቱ በ2019ኙ የዶሀ የዓለም ሻምፒዮና ላይ በቅደም ተከተል ስድስተኛ እና ሰባተኛ ሆነው ባጠናቀቁት ቤንጃሚን ኪገን እና አብራሀም ኪቢዎት ላይ ወድቋል፡፡  

የሴቶች 800 ሜትር

ከአትሌቲክሱ የጀመሪያ ቀን የጠዋት መርሀግብሮች አንዱ በነበረው የሴቶች 800 ሜትር ማጣሪያ በምድብ ሶስት በአሜሪካዊቷ አቲንግ ሙ ተቀድማ በ2 ደቂቃ ከ01.20 ሰከንድ ሁለተኛ የወጣችው ሀብታም አለሙ ለግማሽ ፍፃሜው ያለፈች ሲሆን በሁለተኛው ቀን ምሽት ላይ በተካሄደው የግማሽ ፍፃሜ ውድድር ላይም በአሜሪካዊቷ አቲንግ ሙ ተቀድማ በ1:58.40 ሁለተኛ በመሆን በኦሊምፒክ የውድድር ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ በርቀቱ ለፍፃሜ ውድድር የበቃች ኢትዮጵያዊት ሆናለች፡፡ ሀብታም ከውድድሩ በኋላ በቶኪዮ ለሚገኘው ባልደረባችን አብይ ወንድይፍራው በሰጠችው አጭር ቃል ‹‹ውድድሩ ትንሽ ፈታኝ ነበር ነገር ግን ለሀገሬ ስል ያለኝን አቅም ሁሉ ተጠቅሜያለሁ፡፡ ክብሩ ይስፋ ለመድኃኒዓለም በመጨረሻም አሪፍ ውጤት ላይ ደርሻለሁ፡፡ ለኦሊምፒክ የፍፃሜ ውድድር ሳልፍ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም ከኢትዮጵያ ለፍፃሜ የደረሰ ያለ አይመስለኝም እና አሁንም መጨረሻዬን ያሳምርልኝ ነው የምለው›› ብላለች፡፡  

በሴቶች 800 ሜትር የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ በምድብ አራት በ2.01.98 አራተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ነፃነት ደስታ ወደ ግማሽ ፍፃሜው መቀላቀል ሳትችል ስትቀር በጀማሪዎች ስም ዝርዝር ላይ ስሟ ተካቶ በምድብ አንድ እንደምትሮጥ ስትጠበቅ የነበረችው ወርቅውሀ ጌታቸው ግልፅ ባልተደረገ ምክንያት ውድድሩን ሳትጀምር ቀርታለች፡፡

የወንዶ 800 ሜትር

የወንዶች 800 ሜትር የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ላይ የተሳተፈው ኢትዮጵያዊው መለሰ ንብረት ከምድብ ሶስት በ1:47.80 ሰባተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ለግማሽ ፍፃሜው ማለፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡ በመሐመድ አማን ስኬቶች በመነቃቃት ላይ የነበረው የወንዶች 800 ሜትር ከቅርብ ግዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ሶስት ሰዓት የሚያሟሉ ተወካይ አትሌቶችን ለማግኘት እየተቸገረችበት የምትገኝ ርቀት እንደሆነ እየታየ ነው፡፡ የኦሊምፒክ ሚኒማ ማሟላት የቻለ አንድ አትሌት ብቻ ይዘን የቀረብንበት የቶኪዮ ኦሊምፒክም ይህ ችግር እንዳልተቀረፈ የታየበት ሌላኛው አጋጣሚ ሆኗል፡፡  

የሴቶች 5000 ሜትር ማጣሪያ

በአትሌቲክሱ የመጀመሪያ ቀን ሐምሌ 23/2013 ምሽት ላይ በተደረት የሴቶች 5000 ሜትር ማጣሪያ ላይ የተሳተፉት ሶስቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሐምሌ 26/2013 ምሽት ላይ ለሚደረገው የፍፃሜ ውድድር አልፈዋል፡፡ ከምድብ አንድ ሰንበሬ ተፈሪ (14፡48.31) እና እጅጋየሁ ታዬ (14፡48.52) የኔዘርላንዷ ሲፋን ሀሳን (14፡47.89) እና ኬንያዊቷ አግነስ (14፡48.01) ቲሮፕን ተከትለው በቅደም ተከተል ሶተኛ እና አራተኛ ሆነው ሲያልፉ ከምድብ ሁለት ጉዳፍ ፀጋዬ (14፡55.74) ኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪ (14፡55.77) አስከትላ በአንደኛነት አልፋለች፡፡


ሐምሌ 26/2013 ምሽት ላይ በሚደረገው የሴቶች 5000 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ላይ የሚፎካከሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች

በሄንግሎ በተከናወነው የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ምርጫ ውድድር ላይ ባስመዘገበችው የራሷ ምርጥ 14:13.32 የርቀቱ የወቅቱ ፈጣን አትሌት ሆና ወደ ቶኪዮ ያቀናችው ጉዳፍ ለወርቅ ሜዳልያ ድል ከሚጠበቁት መካከል ናት፡፡ በሄንግሎው ውድድር ላይ ጉዳፍን በመከተል በቅደም ተከተል 14:14.09 እና 14፡15.24 በሆነ ሰዓት የጨረሱት እጅጋየሁ እና ሰንበሬም በዓለም የምንግዜም ምርጥ ዝርዝር ውስጥ የስድስተኛ እና ሰባተኛ ደረጃን ለመያዝ የበቁ ጠንካራ አትሌቶች ናቸው፡፡ የቶኪዮ ኦሊምፒክ የሴቶች 5000 ሜትር ተወዳዳሪዎች ዝርዝር ሶስቱን ኢትዮጵያውያን ጨምሮ ከዓለም የምንግዜም ምርጥ አስር የርቀቱ ሯጮች አምስቱን ያካተተ ነው፡፡ ኬንያውያኑ ሄለን ኦቢሪ እና አግነስ ቲሮፕ ከምንግዜም ምርጥ አስሮቹ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆኑ በ12ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሀሳንም የቶኪዮውን የፍፃሜ ፉክክር በጉጉት እንዲጠበቅ የምታደርግ ብርቱ አትሌት ናት፡፡

Continue Reading

Articles

ሰለሞን ባረጋ ለአስራ ሶስት ዓመት የራቀንን የወንዶች 10,000 ሜትር ድል በቶኪዮ ወደ ኢትዮጵያ መልሶታል

Published

on

218076583_1010892909482678_1235421043554241523_n

በቶኪዮ ኦሊምፒክ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአትሌቲክስ ውድድር በተጀመረ በሁለተኛው ቀን በወንዶች አስር ሺህ ሜትር ኢትዮጵያውያንን እጅግ ያስደስተው ድል በወጣቱ ሰለሞን ባረጋ አማካይነት ተመዝግቧል፡፡   
በ1980 ሞስኮ ላይ ምሩፅ ይፍጠር በርቀቱ ለመጀመሪያ ግዜ የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ካስገኘ በኋላ ከተደረጉት አስር የኦሊምፒክ የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ውድድሮች ኢትዮጵያ አምስቱን በበላይነት ለመጨረስ ችላለች፡፡ የርቀቱ ንጉሶች ሀይሌ ገብረስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ከ1992 እስከ 2008 ዓ.ም. በአራት ተከታታይ የኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ በማሸነፍ የርቀቱ የወርቅ ድል ለኢትዮጵያ ብቻ የተሰጠ እንዲመስለን አድርገውንም ነበር፡፡ ከ2008ቱ የቤይጂንግ ኦሊምፒክ የቀነኒሳ በቀለ ድል በኋላ በተከሰተው የሞ ፋራህ የበላይነት ምክንያት ተመሳሳዩን ድል በቶኪዮ ለማየት 13 ዓመታትን መጠበቅ ግድ ብሎናል፡፡ ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት በጉጉት ስንጠብቀው የቆየነውን የ10 ሺህ ሜትር የኦሊምፒክ ድል በመጨረሻም ሰለሞን ባረጋ በቶኪዮ አጎናፅፎናል፡፡ የሰለሞን የቶኪዮ የወርቅ ሜዳልያ ድል ኢትዮጵያ ካለፉት አስራ አንድ ኦሊምፒኮች በርቀቱ ለስድስተኛ ግዜ የበላይ ሆና እንድትጨርስ ያስቻለም ነው፡፡ ድሉ በቶኪዮ የአትሌቲኪስ ውድድሮች የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳልያ ድል ሆኖም ተመዝግቧል፡፡ ሰለሞን ባረጋ በ2018 የበርሚንግሀም የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር በ3000 ሜትር እና በ2019 የዶሀ ዓለም ሻምፒዮና ላይ በ5000 ሜትር የብር ሜዳልያ ካገኘ በኋላ በመጀመሪያ የኦሊምፒክ ተሳትፎው ከፍተኛ ክብር የሚሰጠውን የ10,000 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ድል ለማሳካት በቅቷል፡፡

‹‹የ200 ሜትር እና 400 ሜትር አጫጨር የፍጥነት ሩጫ ልምምዶችን ስሰራ ስለነበረ ሁለት ዙር ሲቀር ውድድሩን እንደማሸንፍ ለራሴ ነገርኩት››
ሰለሞን ባረጋ ከቶኪዮው ድል በኋላ

ሰለሞን ባረጋ ከቶኪዮው ድሉ በኋላ በስፍራው ከሚገኘው የስራ ባልደረባችን አብይ ወንድይፍራው ጋር ባደረገው አጭር ቃለ ምልልስ የሚከተለውን ብሏል ‹‹ረጅም ርቀት የእኛ ስፖርት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ሆኖም በኦሊምፒክ ውድድር ላይ ወርቅ ሜዳልያ ከወሰድን ብዙ ግዜ አልፎናል፡፡ ይህን ነገር ለመጨረሻ ግዜ ያሳካውም ቀነኒሳ ነበረ፡፡ ዛሬ በቶኪዮ ድሉን በማሳካቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በተለይ ለእኛ ከቶኪዮ ጋር አበበ ቢቂላን የምናስታውስበት ድል ስለሆነ ያንን በማሳካቴም በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ዘንድሮ ከኡጋንዳ የዓለም ሪኮርድ የሰበረው ቼፕቴጌይ እና የዓመቱን ፈጣን ሰዓት የሮጠው ኪፕሊሞ ነበሩ፡፡ እናም ውድድሩ በጣም ይፈጥናል ብዬ ነበር የጠበቅኩት ግን አልተሮጠም፡፡ ውድድሩን የጨረስነውም 27 ቤት ነው፡፡ የ200 ሜትር እና 400 ሜትር አጫጨር የፍጥነት ሩጫ ልምምዶችን ስሰራ ስለነበረ ሁለት ዙር ሲቀር ውድድሩን እንደማሸንፍ ለራሴ ነገርኩት፡፡ ኡጋንዳውያኑ አትሌቶች ዛሬ ብዙም አልታገሉም፡፡ አብዛኛውን ሰዓት ከኋላ ነው የቆዩት እና እንደዚህ ይሆናል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፡፡ እነርሱን ካሜራ ላይም እያየኋቸው ስለነበር ስለነሱ ብዙም አልተጨነቅኩም እንደውም ከእነሱ ይልቅ የእኛን ልጆች ነበረ ይወጣሉ ብዬ የጠበቅኩት፡፡ በውድድሩ መሀል ተጠባቂ የሆኑት ኡጋንዳውያን ወደኋላ ቀርተው ሶስተኛው የቡድን አጋራቸው ወደፊት ወጥቶ በሰፊ ልዩነት ሲመራ እኛ እነሱን ስንጠብቅ እሱ አዘናግቶ እንዳያሸንፍ ልዩነቱን ለማጥበብ ሞክሬያለሁ፡፡ ምናልባት እነሱ እኛን ሲጠብቁ አንተ ሂድ ያሉት ነበር የመሰለኝ፡፡ ከዚህ በፊት በእንደዚህ አይነቱ ነገር ዳይመንድ ሊግ ላይ ስለተሸወድኩኝ ያንን እንዳይደግሙ ብዬ ነበረ ልዩነቱን ለማጥበብ የሞከርኩት፡፡ የአሰልጣኜንም ምክር እየሰማሁ ስለነበረ የምሮጠው እና ወደኋላ ተመለስ እያለኝ ስለነበር ወደኋላ ተመልሻለሁ፡፡ የእነርሱ እስትራቴጂ እሱን ወደፊት እንዲወጣ አድርገው እኛን ለማድከም ነበረ፡፡ ከበሪሁን ጋር ስንነጋገር ወደፊት ጠጋ በል እያልኩት ነበረ፡፡ ከበሪሁን ጋር ልምምድም አብረን ነበረ የምንሰራው፡፡ እኔ እንደውም ከአንድ እስከ ሶስት እንወጣለን ብዬ ነበር የጠበቅኩት አጋጣሚ ሆኖ አልተሳካም ነገር ግን ወርቁን ወደኢትዮጵያ በመመለሳችን በጣም ደስተኛ ነን፡፡›› ብሏል፡፡

Continue Reading

Trending