Connect with us

Articles

“ዘመቻ መልካም አስተዳደር” የተሸነፍነውና የምንሸነፈው ጦርነት

Published

on

Lidetu Ayalew

Lidetu Ayalew

ከልደቱ አያሌው

የኢዴፓ ብሄራዊ ም/ቤት አባል

ከጥቂት ሳምንታት በፊት መልካም አስተዳደርን አስመልክቶ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ያካሄዱትን ውይይት በቴሌቪዥን ተከታትየው ነበር፡፡ ውይይቱ በባህሪው “ኢህአዴግአዊ” ስላልነበር አስገርሞኛል፡፡ ኢህአዴግ ለህዝብ ይፋ በማይሆኑ የውስጥ ድርጅታዊ ውይይቶች ላይ እንዲህ ዓይነት የሞቀ ውይይት የማድረግ የቆዬ ባህል ያለው ድርጅት ቢሆንም ለህዝብ በይፋ በሚቀርቡ ውይይቶች ላይ ግን እንዲህ ዓይነት ግልፅነት እና ድፍረት ማሳየት ባህሉ አይደለም፡፡

ኢህአዴግ በራሱ መንገድ የሚያስጠናቸው ጥናቶችም ብዙውን ጊዜ ግልፅነት፤ድፍረትና ሃቀኛነት የሚጐድላቸው ቢሆኑም በሰሞኑ የውይይት መድረክ ላይ የጥናት ውጤቶችን ያቀረቡት ተkማት ግን በሚያስገርም ሁኔታ ሙሉ ነፃነትና ድፍረት ታይቶባቸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ በመልካም አስተዳደር ችግርነት የተጠቀሱት ነጥቦች ሙሉ በሙሉ በሚባል መጠን ላለፊት በርካታ አመታት በተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በግል መገናኛ ብዙሃንና በአገሪቱ ዜጐች በተደጋጋሚ ሲቀርቡ የነበሩ ትችቶች ቢሆኑም እነዚህ ትችቶች በገዥው ፓርቲ በኩል የ “ጠላት ወሬ” ተደርገው ሲጣጣሉ የነበሩ ናቸው፡፡

ኢህአዴግ ከእንዲህ ዓይነቱ የሌሎችን ሃሳብና ትችት በጅምላ የማጣጣል በሽታው እስከወዲያኛው መፈወስ ያለበት ድርጅት ቢሆንም የሰሞኑ የመልካም አስተዳደር ውይይት ግን ሊያስመሰግነው የሚገባና “ይልመድብህ” የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡ በርግጥ ይህ ዓይነቱ ውይይት በዚህ ሳይወሰን በሌሎች መሰረታዊ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎችም ላይ ቀጥሎ ማዬትን ከልባችን እንመኛለን፡፡

ኢህአዴግ ያለ አመሉና ባህሉ በመልካም አስተዳደር ጉዳይ ላይ ለምን በዚህ መጠን በግልፅነት ለመወያየት ደፈረ? የሚለው ጥያቄ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ አንዳንዶች ውይይቱን እንዲሁ “አሉ” ለመባል የተካሄደ የይስሙላ ውይይት አድርገው አይተውታል፡፡ በእኔ አመለካከት ግን ይህ ውይይት የታይታ ሳይሆን የምር ነው፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቃለለ ከመምጣት ይልቅ ይበልጥ እየተባባሰ በመምጣት በአሁኑ ወቅት ለስርዓቱ ህልውና ተጨባጭ አደጋ እየሆነ በመምጣቱ ምክኒያት ነው—ኢህአዴግ በአጀንዳው ዙሪያ በዚህ መጠን ውይይት ለማድረግና መፍትሄ ለማፈላለግ የተገደደው፡፡ በርግጥም በአንድ አገር የአንድ ስርዓት መዳከምና መበስበስ አይነተኛ ምልክት በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየተከሰተ ያለው ዓይነት ቅጥ ያጣ የመልካም አስተዳደር ችግር በመሆኑ ኢህአዴግ ይህንን አደጋ ተገንዝቦ መፍትሄ ለማፈላለግ መሞከሩ ከራሱ የስልጣን ህልውናም ሆነ ከአገሪቱ ደህንነት አንፃር ተገቢ ዕርምጃ ነው፡፡

ነገር ግን በችግሩ ዙሪያ ግልፅ ውይይት ለማድረግና መፍትሄ ለመፈለግ መሞከሩ በራሱ የሚደነቅ ተግባር ቢሆንም ውይይቱን እንደተከታተልኩት ከሆነ ግን ኢህአዴግ እሰከአሁን ድረስ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስወገድ ባካሄዳቸው ዘመቻዎች ሁሉ ተሸናፊ የሆነውን ያህል ወደፊትም ሊያካሂድ ባሰበው ዘመቻ ተሸናፊ እንደሚሆን የሚያሳይ አንድ በቂ ምክኒያት አለ፡፡ ይኸውም የመንግስት ባለስልጣናቱ ርዕሱ—ጉዳዩን አስመልክቶ ባካሄዱት ውይይት የችግሩን አይነት፣የችግሩን ስፋትና ጥልቀት የችግሩን ፈፃሚዎችና ተጠቂዎች በተመለከተ ሰፊና ዝርዝር ውይይት ያካሄዱ ቢሆንም— ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማስገኘት የሚያስችለውን ዋናውን ጥያቄ ግን ሳያነሱትና ሳይወያዩበት ቀርተዋል፡፡ ያ መሰረታዊ ጥያቄ “ለምንድን ነው በመልካም አስተዳደር ረገድ ስርዓቱ በዚህ ዓይነት ስፋትና ጥልቀት ችግር ውስጥ የገባው?“ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ምክኒያቱም “ችግሩ ከጅምሩ ለምን ተከሰተ?” የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ አንስተን የችግሩን መሰረታዊ ምንጭ ከስር ከመሰረቱ ካልተረዳነው በስተቀር የቱንም ያህል ስለችግሩ ስፋትና ጥልቀት ወይም ስለችግሩ ፈጣሪዎችና ስለተጠቂዎቹ ማንነት ስናወራ ብንውል ወደ መፍትሄው ሊዎስደን አይችልም፡፡

በመንግስት ባለስልጣናቱ ውይይትም ሆነ ያን ውይይት ተከትሎ በተለያዩ መድረኮች ሲካሄዱ ባየናቸው ውይይቶች ይህ መሰረታዊ ጥያቄ ሲነሳ አልሰማንም፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ /ማለትም ለአንድ ትውልድ ዘመን/ የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት ያስችላሉ የተባሉ ለቁጥር የሚያታክቱ የመዋቅር ማሻሻያ ዘመቻዎች ተካሂደዋል፡፡ በውይይቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃ/ማርያም እንዳሉት መንግስት የመዋቅር ማሻሻያ ትምህርት ለመቅሰም ከአውሮፓ እስከ ኤዥያ ያልረገጠው አገር የለም፡፡ ቢያንስ አቶ መለስ “ድርጅታችን በስብሷል” በማለት የተሃድሶ ዘመቻ ከአዎጁበት ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 14 ዓመታት ኢህአዴግ በመልካም አስተዳደር ችግር ዙሪያ አታካች ግምገማና ዘመቻ አካሂዷል፡፡

በዚህ ሁሉ ዓመታት የተካሄደው ዘመቻ መፍሄት ሊያመጣ ያልቻለው የችግሩ ስፋትና ጥልቀት ወይም የችግሩ ፈፃሚዎችና ተጠቂዎች ሳይታወቁ ስለቀረ ሳይሆን ችግሩን ለመፍታት የተካሄዱት ዘመቻዎች ከችግሩ መሰረታዊ ምንጭ ጋር ፍፁም ያልተዛመዱ በመሆናቸው ነው፡፡ ካለፈው ስህተት በአግባቡ መማር ስላልተቻለ አሁንም እየተደገመ ያለው ያው ያለፈው ዓይነት ዘመቻ ነው፡፡ በእኔ በኩል “የችግሩ መሰረታዊ ምንጭ ምንድን ነው?” ለሚለው ጥያቄ የራሴን መልስ ለመስጠት ከመሞከሬ በፊት በቅድሚያ አንድ ተዛማጅ ጥያቄ እዚህ ላይ አንስቸ ልለፍ፡፡

ይህ ጥያቄየም— ለምንድን ነው፡፡ ኢህአዴግ የመልካም አስተዳደርን ትርጉም በቁንፅል የቢሮክራሲ ውጣ–ውረድ ጉዳይ አድርጐ የሚያየው? የሚል ነው፡፡ ምክኒያቱም የኢህአዴግ አንዱ ችግር –መልካም አስተዳደር ፈርጀ ብዙና በአጠቃለይ በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመለከት ፅንስ–ሃሳብ ሆኖ እያለ ኢህአዴግ ግን የአገልግሎት አሰጣጥ /service delivery/ ጉዳይ አድርጐ ይተረጉመዋል፡፡ ነገር ግን የተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶችና በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የተደረጉ የተለያዩ የጥናት ውጤቶች የሰጡትን ትርጉም ስናይ—መልካም አስተዳደር መንግስት ወይም መንግስታዊ ተቋማት የዜጐችን ሁለንተናዊ መብት ማለትም የሰብአዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መብቶች በማስከበር ረገድ ያላቸውን ፍላጐት፣አቅምና ተግባራዊ ምላሽ የሚመለከት ነው፡፡ በተለይም የሰብአዊ መብትና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቁልፍ የመልካም አስተዳደር መገለጫዎች ሆነው እያሉ በኢህአዴግ ዘንድ ግን በጨረፍታም እንዲነሱ የሚፈለጉ ርዕሱ—ጉዳዮች አልሆኑም፡፡ ይህ ቁንፅል አተረጓጐም ኢህአዴግ የቱንም ያህል ተደጋጋሚ የተሃድሶ ዘመቻ ቢያካሂድም ችግሩን በዘላቂነት እንዳይፈታ ካደረጉት ምክኒያቶች አንዱ ነው፡፡ ምክኒያቱም ሰብአዊ መብት ባልተከበረበትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሌለበት ሁኔታ “መልካም” ሊባል የሚችል አስተዳደር አይኖርም፡፡ በሌላ አነጋገር ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተከበሩበት አንድ አገርም ጐልቶ የሚታይና በኛ አገር በሚታየው መጠን ህዝብን ሊያማርር የሚችል የመልካም አስተዳደር ዕጦት ሊኖር አይችልም፡፡ በርግጥ ኢህአዴግ በዚህ ረገድ የጠራ አመለካከት ቢኖረው ኖሮ “ይህ ሁሉ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ባለበትና ህዝብ በተማረረበት አገር ያለፈውን ምርጫ እንዴት 100%ላሸንፍ ቻልኩ?” ብሎ እራሱን በጠየቀና የችግሩን ምንጭ ከስር መሰረቱ ለመረዳት በሞከረ ነበር፡፡ ምክኒያቱም ከፍ ሲል ለመግለፅ እንደሞከርኩት የአንድ መንግስት ድክመትም ሆነ ስርዓት አልበኛነት ዋና መገለጫ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ስለሆነ በአገራችን ለተከሰተው የመልካም አስተዳደር ችግር ቀዳሚ ተጠያቂ መሆን የሚገባው ኢህአዴግ አንድን ምርጫ 100% ይቅርና 50%የማሸነፍ ዕድል ባልነበረው ነበር፡፡

ይህ የሆነው ኢህአዴግ 100% ለመመረጥ በሚያስችል መጠን በሕዝብ የሚፈቀር መንግስት ሆኖ ሳይሆን የአገራችን ምርጫ ራሱ በመልካም አስተዳደር ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ ነው፡፡ ምክኒያቱም ቢሮክራሲው ውስጥ ተሰግስገው ህዝብን በደጅ—ጥናትና በሙስና ሲያማርሩት የሚውሉት ካድሬዎች ናቸው—በተመሳሳይ ሁኔታ በምርጫ ወቅት ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና መራጩን ህዝቡ በተለያዩ የአፈና ስልቶች ሲያሳድዱ የሚውሉት፡፡

በመንግስት ትዕዛዝም ይሁን በራሱ ተነሳሽነት በምርጫ ወቅት በተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በመራጩ ህዝብ ላይ የተለያዩ ተፅኖዎችን በማሳደር የፖለቲካ ሙስና ሲፈፅሙ ዝም የተባሉ /ምንአልባትም አበጀህ የተባሉ/ ካድሬዎች በተመሳሳይ ሁኔታ በህዝብ ላይ የኢኮኖሚ ሙስና ለመፈፀም መሞከራቸው አይቀሬ ነው፡፡ መንግስት የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ሲል የፖለቲካ ሙስና እንዲፈፅሙ የተጠቀመባቸው ካድሬዎች እነሱ በተራቸው የኑሮ ህልውናቸውን ለመጠበቅ ሲሉ የኢኮኖሚ ሙስና ቢፈፅሙ ምን ሊያስደንቅ ይችላል? ራሱ በፖለቲካ ሙስና ውስጥ የተዘፈቀ አንድ መንግስት ካድሬዎቹ የኢኮኖሚ ሙስና እንዳይፈፅሙ የመከላከል የሞራል ብቃትስ ይኖረዋል?ምንጊዜም በአንድ ስርዓት ውስጥ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሙስና እርስ በራስ ተመጋጋቢ ክስተቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ የመልካም አስተዳደርን ችግር ከልቡ መፍታት ከፈለገ የችግሮችን ምንጭም ሆነ የመፍትሄውን አቅጣጫ ከአገራችን የሰብአዊ መብትና የዴሞክራሲ ሆኔታ ጋር አያይዞ ሊፈትሽ ይገባዋል፡፡ ከሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ጋር የተያያዙ የፖለቲካ ሙስናዎች ተገቢውን ትኩረት ባላገኙበት ሁኔታ ከኢኮኖሚውና ከቢሮክራሲ ውጣ–ውረድ ጋር የተያያዙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት አይቻልም፡፡ ለዚህም ነው የወቅቱ የኢህአዴግ የመልካም አስተዳደር ዘመቻ ከጅምሩ ተኮላሽቷል ለማለት የምደፍረው፡፡

ስለ ኢህአዴግ ቁንፅል የመልካም አስተዳደር አተረጔጐም ይህንን ያህል ካልኩ የመልካም አስተዳደር ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት መሰረታዊ ጥያቄ ነው ላልኩትና “ለምድነው በመልካም አስተዳደር ረገድ ስርዓቱ በዚህ ዓይነት ስፋትና ጥልቀት ችግር ውስጥ የገባው?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ያለኝን የግል አመለካከት ለመግለፅ ልሞክር፡፡

በእኔ አመለካከት ለአገራችን የመልካም አስተዳደር ችግር የሚከተሉት ስድስት ነጥቦች በዋና ምክኒያትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ እነሱም

  1. በመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚሾሙት ብቻ ሳይሆን የሚቀጠሩት ቋሚ ሠራተኞች የሚቀጠሩበት ዋና መስፈርት የፓርቲ አባልነት ወይም ደጋፊነት መሆኑ፤

  2. የመንግስት እና የፓርቲ (ኢህአዴግ) መዋቅሮች የተደበላለቁበት ሁኔታ መኖሩ፤

  3. የዴሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብት ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን ነፃና ገለልተኛ አለመሆናቸው፤

  4. ለመንግስት ሰራተኞች የሚከፈለው ደመወዝና አበል ከወቅቱ የኑሮ ውድነት ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑ፤

  1. የህዝብ የተዛባ አስተሳሰብና ባህል መኖር 

  2. ህዝብ አቅመ–ቢስ /አቅም የለሽ/ እንዲሆን መደረጉ ናቸው፡፡

ከላይ ከተራ ቁጥር 1 እስከ ተራ ቁጥር 3 የተዘረዘሩት ጉዳዮች እርስ–በርስ የተሳሰሩና ተለያይተው መታየት የማይችሉ ናቸው፡፡ ሶስቱም ችግሮች መንግስት ከምንም ነገር በላይ ለፖለቲካ ስልጣን የበላይነቱ ቀናዒ ከመሆኑ ጋር የተያያዙ ችግሮች ናቸው፡፡ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ የመቀጠሉን ጉዳይ የሞት የሽረት ጉዳይ አድርጐ ስለሚያየው ሁሉንም ነገር በቁጥጥር ስር የማዋል አባዜ ተጠናውቶታል፡፡ በተለይም በግራ ፖለቲካ አራማጅነት ያደገና በሽምቅ ተዋጊነት ህይወት ውስጥ ያለፈ ድርጅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከተkማትም ጋር ሆነ ከህዝብ ጋር ያለው ግንኙነት በጥርጣሬ፣በስጋትና በፍርሃት የተሞላ ሆኗል፡፡ በዚህ ምክኒያት በድርጅታዊ አሰራር የራሱን ቁልፍ አባላት በአመራርነት በማስቀመጥ በአገሪቱ የሚገኙ ተቋማትን በበላይነት ተቆጣጥሮአቸዋል፡፡

አንድ ለአምስት በመባል የሚታዎቀውን የጥርነፋ አደረጃጀት ስልት በመጠቀምም ከሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጀምሮ የአጠቃላዩን ህዝብ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሞከረ ይገኛል፡፡ ይህንን በማድረግም በአጋጣሚና በአስገዳጂ ሁኔታ ሳይሆን ሆነ ብሎ በማቀድ የመንግስትንና የኢህአዴግን መዋቅር አንድና አንድ በማድረግ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የዕርስ በዕርስ ቁጥጥርና ክትትል /check and balance/—ስርዓት ፈፅሞ እንዳይኖር አድርጔል፡፡ እንግዲህ በመንግስት የተለያዩ መዋቅሮች መካከል የቁጥጥርና የክትትል ስርዓት እንዳይኖር በተደረገበት ሁኔታ ነው ኢህአዴግ የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመዋጋት ቆርጨ ተነስቻለሁ የሚለን፡፡ በተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች መካከል የቁጥጥርና የክትትል ስርዓት እንዲኖር የሚደረገው ለሌላ ጉዳይ ሳይሆን የመንግስት ባለስልጣናት እና ስራተኞች ያለአግባብ እንዳይባልጉና መልካም አስተዳደር ጠፍቶ በህዝብ ላይ በደል እንዳይደርስ ዋስትና ለመስጠት ነው፡፡

ታዲያ እንዲህ ዓይነት ስርዓት ሆነ ተብሎ እንዳይኖር በተደረገበት ሁኔታ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዴት ተደርጐ ሊፈታ ይችላል? ስለዚህ ኢህአዴግ በመልካም አስተዳደር ችግር ላይ ዘመቻ ሲጀምር ጦርነቱ የሚካሄደው በማንም ውጫዊ ወይም ባዕድ አካል ላይ ሳይሆን በሌሎች ላይ አፈና እየፈፀሙ ስልጣኔን ከጥቃት ይከላከሉኛል ብሎ ራሱ ካቋቋማቸው የራሱ መዋቅሮችና ካድሬዎች ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቀላል ውሳኔ አይደለም ፡፡ እንዲ ዓይነት ውሳኔ በካንሰር በሽታ የተለከፈን የራስን አካል ቆርጦ እንደመጣል ከባድ ውሳኔ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ነው—አያሌ የመዋቅር ማሻሻያ ዘመቻዎች ተሞክረው ሲከሽፉ የታዬው፡፡

ዞሮ ዞሮ በአሁኑ ወቅት ለኢህአዴግ ከፊቱ የቀረቡለት የውሳኔ ምርጫዎች ሁለት ናቸው፡፡ በካንሰር የተለከፉ አካላቱን ቆርጦ ጥሎ ህልውናውን ማራዘም፣ አሊያም በካንሰር ከተለከፋ አካላቶቹ ጋር አብሮ መኖርና የህልውናውን ዕድሜ ማሳጠር ነው፡፡ በርግጥ ተቆርጦ የሚጣለው አካል ከማይቆረጠው የገዘፈ ከሆነ የህልውናው አደጋ በዚህኛውም አማራጭ ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህንን በመረዳትም ይመስላል በውይይቱ ወቅት አንዳንድ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት የቀረበውን የጥናት ውጤት ለመቀበል ሲንገራግሩ የታዬት ፡፡ አቶ መለስም በዚህ አይነቱ የሃሳብ አጣብቂኝ/dillema/ ውስጥ ስለነበሩ ይመስለኛል ጥቂት ግለሰቦችን መቀጣጫ ከማድረግ ባለፈ ችግሩን ሳይፈቱት ለህልፈት የበቁት፡፡

ዋና ምክኒያት ነው ባይባልም በተራ ቁጥር አራት ላይ የተጠቀሰው የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ዝቅተኛነትም ለአገራችን የመልካም አስተዳደር ዕጦት አንድ ምክኒያት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ባይሆኑም በርካታ ሰዎች በመንግስት መስሪያ ቤቶች ስራ የሚቀጠሩት ህዝብን የማገልገል ዓላማ ይዘው ሳይሆን ሌላ የኑሮ አማራጭ በማጣት ነው ፡፡ ብዙውን ጊዜ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ብቃትና እድሉ ያላቸው፣ወይም የግል ሥራ ለመስራት የሚያስችል ካፒታልና እውቀት ያላቸው ሰዎች የመንግስት ስራ የመቀጠር ፍላጐት የላቸውም፡፡ እነዚህ በዕውቀትም ሆነ በካፒታል አቅማቸው ዝቅተኛ ደረጃ ያሉ ዜጐች የመንግስት ተቀጣሪ የሚሆኑት ለኑሮአቸው በቂ ደመወዝ እናገኛለን ብለው በማሰብ ሳይሆን ብዙውን ጊዜ በጉቦ ወይም በጉርሻ መልክ ተጨማሪ ጥቅም የሚያገኙበት ቀዳዳ እንደማይጠፋ በመተማመን ነው ፡፡ በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ ኢህአዴግ መለመልኩት እያለ የሚመፃደቅበት በሚሊዩን የሚቆጠር አባልም ይህንን ዓይነት የጥቅመኝነት አስተሳሰብ ይዞ የተቀላቀለ እንጂ በኢህአዴግ ፖሊሲ እምነት ያለው ወይም ህዝብን የማገልገል ዓላማ ያለው ኃይል አይደለም፡፡ ይህ በተግባር የኢህአዴግ ሆነ የህዝብ ወገንተኝነት የሌለው ፣ነገር ግን በሰልፍ የኢህዴግን የአባልነት መታዎቂያ የወሰደ ጥቅመኛ/opportunist/ ኃይል ነው በየቢሮክራሲው ውስጥ ተሰግስጐ ህዝብን እያማረረ የሚገኝው፡፡ ኢህአዴግ የፓርቲ መታዎቂያ በመያዝና በእውነተኛ እምነት የፓርቲ አባል በመሆን መካከል ያለውን ልዩነት ተረድቶ የራሱን አሰራር እስካላስተካከለ ድረስ የአገሪቱ ቢሮክራሲ መቸውንም ጊዜ ቢሆን ከሙስና የፀዳለ ሊሆን አይችልም ፡፡

አሁን በአገራችን ከሚታየው የኑሮ ውድነት አንፃር ለአንድ መንግስት ሰራተኛ (ምን ዓልባትም ቤተሰብ ላለው) ከአንድ ሺ እስከ ሁለት ሺ ብር የወር ደመወዝ እየከፈሉ ስራውን በአግባቡ እንዲሰራ መጠበቅ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ጉቦ የመብላት ፍቃድ ከመስጠት የተለየ አይመስለኝም፡፡ በርግጥ የደመወዝ ማነስ ጉቦ ለመብላት በራሱ በቂ ምክኒያት ላይሆን ይችላል፡፡ ትንሻ ደመወዛቸውን እንደምንም አብቃቅተው በድህነት እየኖሩ ያለሙስና ጥሩ አገለልሎት ለህዝብ የሚሰጡ አንዳንድ የመንግስት ሰራተኞች የመኖራቸውን ያህል በቄ በሚባል ደመወዝና የገቢ ምንጭ እያላቸውም ጉቦ ሲያባርሩ የሚውሉ የመንግስት ሰራተኞች ብዙዎች ናቸው፡፡ ከፍ— ሲል በተራ ቁጥር አምስት የተጠቀሰው የህዝብ የተዛባ አስተሳሰብና ባህል መኖርም ለመልካም አስተዳደር ዕጦት አንድ ምክኒያት የሚሆነው ከዚሁ ጋር ተያይዞ ነው፡፡

በመንግስት ኃላፊነት የያዙትን የአገልግሎት ወንበር እንደ አንድ አትራፊ የንግድ ድርጅት በመቁጠር ጉቦ ካልበሉ በስተቀር የዜጐችን ጉዳይ ላለመፈፀም የሚፈልጉ በርካታ የመንግስት ሰራተኞች የመኖራቸውን ያህል መብታቸውን በትክክለኛው መንገድ ለማስከበር ከመሞከር ይልቅ ማንም ገና ሳይጠይቃቸው ጉቦ ለመስጠት ተዘጋጅተው ወደ መንግስት ቢሮ የሚሄዱ ዜጎች ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ ሙስና በአሁኑ ወቅት በአገራችን ወደዚህ የከፋ ደረጃ የደረሰው እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ ሳይሆን በቆየው ታሪካችንም ጉቦ የመቀበልና የመስጠት ባህላዊ ዕርሾ በውስጣችን ስለነበረ ጭምር ነው፡፡ ለአገራችን መልካም አስተዳደር ችግር እየተባባሰ መምጣት ዋናው ተጠያቂ መንግስታዎ ስርዓቱ ቢሆንም ትውልዱን በጥሩ ስነ–ምግባር ኮትኩተው የማሳደግ ኃላፊነት የሚጠበቅባቸው ወላጆች፣መምህራን፣ጋዜጠኞችና መንፈሳዊ አባቶች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ጭምር የተከሰተ ችግር ነው ፡፡

ከፍ ሲል ከተራ ቁርጥ 1 እስከ ተራ ቁጥር 5 የተዘረዘሩት ነጥቦች ለመልካም አስተዳደር አለመኖር ዋና ዋና ምክናያቶች መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከሁሉም በላይ ግን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ታግለን ማሸነፍ እንዳንችል ያደረገን ዋና ምክኒያት ህዝቡ አቅም–አልባ የመደረጉ ዕውነታ ነው፡፡ ከማንም በላይ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ተዋግቶ ማሸነፍ ያለበት ህዝቡ ሆኖ እያለ ነገር ግን ህዝቡ በቢሮክራሲው ወይም በሙሰኞች የተሸነፈ አቅመ ቢስ ህዝብ ሆኗል፡፡ ዜጐች ጉዳያቸው በአግባቡ አልፈፀም ሲል፣ወይም ማንኛውም ዓይነት በደል ሲደርስባቸው ለበላይ አካል አቤቱታ ወይም ክስ አቅርበው የሚያገኙት መፍትሄ እንደሌለ ስለሚያውቁ ችግሩ እንዲፈታ የሚታገሉ ሳይሆን እራሳቸው የችግሩ አካል ሆነዋል:: ህዝቡ በመንግስት የመደመጥ መብት፣ወይም በመንግስት ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር ጉልበት እስከሌለው ድረስ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ሊመጣ አይችልም፡፡ አንድ ህዝብ ተገቢውን ጉልበት አግኝቶ የለውጥ ኃይል ሊሆን የሚችለው ደግሞ ከምንም በላይ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቱ ተከብሮ እውነተኛ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት ሊሆን ነው ፡፡ ህዝቡ በተግባር የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት ለሆን የሚችለውም ከአካባቢው አስተዳደሮዎች ጀምሮ እስከ ማዕከላዊው መንግስት ድረስ ያሉ ባለስልጣናትን በቀጥታ ምርጫ ወይም በውክልና የመምረጥና የመሻር እውነተኛ መብት ሲኖረው ብቻ ነው፡፡

አሁን ባለው የአገራችን ተጨባጭ ሆኔታህዝብ እንኳንስ የመንግስት አለቃ ሆኖ የአገሩን ዕጣ—ፋንታ ሊወስን ይቅርና ከዕለት–ተዕለት ኑሮው ጋር የተያየያዙ ጥቃቅን አገልግሎቶችን እንኳን ማስፈፀም የማይችል አቅመ–ቢስ ህዝብ ሆናል፡፡ ህዝብ ሲናገር በማይደመጥበትና ሲቆጣ በማይፈራበት አገር የመልካም አስተዳደር ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ማሰብ ዘበት ነው፡

ስለዚህ ካለፋት ዘመቻዎች በተለዬና በተሻለ –አህአዴግ የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ከልብ ካሰበ የህዝቡን የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብት ጥያቄዎች በአግባቡ በመመለስ እራሱን ሳይሆን ህዝቡን እውነተኛ የስልጣን ባሌቤት በማድረግ የመልካም አስተዳደርን ችግር ከምንጩ ለማድረቅ መወሰን አለበት ፡፡ይህ ውሳኔ የራስን አካል ቆርጦ እንደመጣል ከባድ ውሳኔ ቢሆንም አማራጭ የሌለው መፍትሄነው፡፡ አለዚያ የመልካም አስተዳደር ዘመቻዎችን ባለፈው የተሸነፍነው ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የምንሸነፈው ጦርነት እንደሚሆን ከወዲሁ የታወቀ ነው፡፡

ምንጭ:- EDPOnline.org

Articles

የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ተሳትፎ ድህረ ምልከታ

Published

on

Medal Winners

በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በወረቀት ደረጃ ከውድድሩ መጀመር በፊት ቡድኑ ባመዛኙ በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኙ ወጣት አትሌቶችን ስላካተተ ቢያንስ የለመድናቸውን ሁለት ወይም ሶስት የወርቅ ሜዳልያ ድሎች እንደማያሳጣን ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ ሆኖም የሜዳ ላይ ውጤቱ እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ኢትዮጵያ በውጤታማነቷ በምትታወቅበት የአትሌቲክስ ፉክክር በአንድ የወርቅ፣ አንድ የብር፣ እና ሁለት የነሐስ በድምሩ በአራት ሜዳልያዎች ከዓለም 14ኛ ከአፍሪካ 3ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች፡፡ ይህም ሁሌም ለአፍሪካ የበላይነት ከምንፎካከራት ኬንያ ጋር ያለን ልዩነት ይበልጥ እንዲሰፋ አድጎታል፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ሌላኛዋ የምስራቅ አፍሪካ ተቀናቃኛችን እየሆነች ከመጣችው ኡጋንዳም አንሰን እንድንገኝ አድርጎናል፡፡ የቶኪዮ ኦሊምፒክ በአትሌቲክሱ ከ1992ቱ የባርሴሎና ኦሊምፒክ ወዲህ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሜዳልያ ስኬት ያስመዘገበችበትም ሆኖ አልፏል፡፡

አሉታዊ ጎኖች
ቶኪዮ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤታማነት ፈር ቀዳጅ የሆነው ታላቁ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ በ1964 ዓ.ም. በተከታታይ ሁለተኛ የኦሊምፒክ ማራቶን ድሉን የተቀዳጀባት ከተማ ናት፡፡ እናም በቶኪዮ ከተማ በተከናወነው የኦሊምፒክ ውድድር የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የሱን ክብር የሚያጎሉባቸውን ነገሮች ያደርጋሉ ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ የሆኑት ነገሮች ግን በተለይ በቡድኑ አስተዳዳሪዎች በኩል ፍፁም ኃላፊነት የጎደለውና ከጠበቅኩት በተቃራኒው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከአትሌቶች ምርጫ አንስቶ በቡድኑ የዝግጅት ወቅት በተካረረ ውዝግብ ውስጥ ነበር የከረሙት፡፡ የኦሊምፒክ ቡድኑን የማዘጋጀት እና የመምራት የጋራ ኃላፊነት የነበረባቸው ሁለቱ አካላት ይባስ ብለው ውዝግቡን ቶኪዮ ድረስ ይዘውት ሄደዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ሁለቱን አካላት በማቀራረብ በትልቁ ውድድር ላይ ያለንን ተሳትፎ እንከን አልባ ማድግ የሚጠበቅባቸውም ተመልካች ከመሆን የዘለለ ሚና አልነበራቸውም። የውዝግቡ አሉታዊ ትሩፋት በአትሌቶች ስነልቦና እና በአጠቃላይ የቡድኑ ውጤት ላይ የበኩሉን ተፅዕኖ ሳያሳርፍ እንዳላለፈ አያጠራጥርም፡፡

እንደ አለመታደል ሆኖ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያን ልዑካን የመምራት ትልቁ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ኃላፊነት የጎደላቸው ነበሩ። የስፖርቱ አስተዳደሪዎች ትላልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በመጡ ቁጥር በአትሌቶች ምርጫ ዙሪያ የነበረውን ውዝግብ እንዲያቆሙልን እመኝ ነበር። ጭራሽ እራሳቸው ችግር ፈጣሪ ሆነው መገኘታቸው አስደንጋጭ እና አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በመሮጫ መም ወይም በጎዳና ላይ በሚደረጉ ውድድሮች መሸነፍን በስፖርቱ ውስጥ ማሸነፍ እና መሸነፍ ያሉ የነበሩ እና ወደፊትም የሚኖሩ ነገሮች ስለሆኑ በፀጋ መቀበል ይቻላል፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑ የስነልቦና ጥንካሬን ሊፈጥሩላቸው የሚገቡ ኃላፊዎች የእርስ በርስ ሽኩቻ ተቃራኒውን አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳርፍ ማየት ግን ፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ ለነገሩ ከስፖርቱ እድገት ይልቅ የፖለቲካ ግዴታቸው የሚያስጨንቃቸው የስፖርት አመራሮች በበዙባት ሀገር ስፖርቱ እንዲህ የማንም መጫወቻ ሲሆን ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡  

የስፖርት አመራሮች ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ሆነው ትኩረታቸውን ስፖርቱን በማስፋፋቱ እና ማሳደጉ ላይ አድርገው የሚሰሩ ስለስፖርቱም በቂ እውቀት እና ፍቅሩ ያላቸው ቢሆኑ መልካም ነው፡፡ ለቦታው በሚመጥን እና ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት በሚችል የስፖርት አመራር የሚመራ የስፖርት ተቋምን መገንባት በተመሳሳይ ሰዓት የሀገር ግንባታን የሚደግፉ ሶስት ነገሮችን ስኬታማ ያደርጋል፡፡ በስፖርት ጤናውን የሚጠብቅ ማሕበረሰብ በመፍጠር በጤናው ሴክተር ላይ የሚኖረውን ጫና ይቀንሳል፣ በሀገር ገፅታ ግንባታ እና በኢኮኖሚው ዕድገት ላይም የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ በቶኪዮ ላይ የተመለከትናቸው የሀገርን ክብር ዝቅ ያደረጉ ግዴለሽነቶች ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊታዩና አጥፊዎቹ ሊጠየቁበት ይገባል፡፡ በመጪዎቹ ዓመታት በሚጠብቁን ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይም የቶኪዮ ኦሊምፒኩን አይነት ሀፍረት እንዳይገጥመን ከወዲሁ ለችግሮቹ መፍትሔ መፈለግ አለበት፡፡

ባለፉት ዓመታት ኦሊምፒክ በመጣ ቁጥር በልዑካን ቡድኑ ውስጥ እየተካተቱ በሕዝብ ገንዘብ የሚዝናኑት የኦሊምፒክ ቱሪስቶች ጉዳይ ዘንድሮም ያልተቀረፈ ችግር ሆኖ ተስተውሏል፡፡ ከሌላው ግዜ በተለየ መልኩ ተጠባባቂ አትሌቶችን ይዞ መጓዝ ይጠይቅ በነበረው ውድድር ላይ አትሌቶቹን ትቶ ምንም የማይሰሩ ሰዎችን ይዞ መሄድ ትልቅ ቀልድ ነው፡፡  

ከሜዳ ውጭ የነበረው ውዝግብ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል የነበረ መሆኑ በሜዳ ላይ የነበሩብንን ድክመቶች ሊያስረሳንም አይገባም፡፡ ስድስት የጎዳና ላይ ተወዳደሪዎቻችን እና አንድ የመም ተወዳዳሪ ውድድራቸውን ማቋረጣቸው በቶኪዮ ከታዩት ደካማ ጎኖቻችን መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ ችግሩ በዚህ ምክንያት ነው የተከሰተው ብሎ ለይቶ ለመናገር ባይቻልም ብዙ ግዜ ሲፈትነን ለሚስተዋለው የሞቃታማ ቦታ ውድድር የምናደርጋቸው ዝግጅቶችን መለስ ብሎ መመልከትን የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ የተጎዳች አትሌትን ወደውድድር እንድትገባ ማድረግ እና በሁለት ደቂቃ ውስጥ ለማቋረጥ መገደዷም የአትሌቶች የጤና ክትትል ላይ ክፍተት እንዳለ የጠቆመን ክስተት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ወደውድድር ስፍራው ካቀናበት ግዜ ጀምሮ በቶኪዮ ምንም አይነት ቡድኑን የተመለከቱ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ወይም ፕሬስ ሪሊዞች አልነበሩም፡፡ ይህም እንደተለመደው የሕብረተሰቡን እና የመገናኛ ብዙሀንን ስለቡድኑ ቀጥተኛ መረጃ የማግኘት መብት የገደበ ነበር፡፡ ጋዜጠኞችም ሚዛናዊ ሆኖ ከመዘገብ ይልቅ ጎራ ለይተው ቃላት መወራወራቸው የህዝብን ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት የነፈገ ነው፡፡ 

አዎንታዊ ጎኖች
ሰለሞን ባረጋ በወንዶች 10,000 ሜትር ወርቅ፣ ለሜቻ ግርማ በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ብር፣ ጉዳፍ ፀጋዬ በሴቶች 5000 ሜትር ነሐስ፣ እና ለተሰንበት ግደይ በሴቶች 10,000 ሜትር ነሐስ ማስመዝገብ መቻላቸው የሚደነቅ ስኬት ነው፡፡

የመጪው ትውልድ አካል የሆኑት ተስፈኞቹ መቅደስ አበበ፣ ፍሬወይኒ ሀይሉ፣ በሪሁ አረጋዊ እና ጌትነት ዋለን ጨምሮ አምስት አትሌቶች ለሜዳሊያ የቀረበ የአራተኛነት ደረጃን ይዘው ማጠናቀቅ መቻላቸውም መልካም ነው፡፡ በተለይ ወጣቶቹ ያስመዘገቡት ውጤት በመጪዎቹ ዓመታት ተገቢውን ድጋፍ ካገኙ የምንጓጓለትን ድል ሊያስገኙልን እንደሚችሉ ያመላከተን ነው፡፡

የሀብታም አለሙ በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በሴቶች 800 ሜትር ለመጀመሪያ ግዜ ለፍፃሜ ተወዳዳሪነት መብቃት ምንም እንኳ በፍፃሜው የሜዳልያ ድል ባይቀናትም በአዎንታዊ ጎን ሊጠቀስ የሚችል ስኬት ነው፡፡

ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃን ይዘው ላጠናቀቁ አትሌቶች በሚሰጥ ነጥብ ድምር መሰረት በወጣው የነጥብ (ፕሌስመንት) ደረጃ ሰንጠረዥ ላይ በ64 ነጥብ ዘጠነኛ ሆነን ማጠናቀቃችንም እሰየው የሚያስብል ነው፡፡

በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከአራተኛ እስከ ስምንተኛ ባሉት ደረጃዎች ውስጥ አጠናቀው ነጥብ ያስገኙ እና የዲፕሎማ ተሸላሚ የሆኑት አትሌቶች፡-
4ኛ – ፍሬወይኒ ሀይሉ – በሴቶች 1500 ሜትር
4ኛ – መቅደስ አበበ – በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል
4ኛ – ሮዛ ደረጀ – በሴቶች ማራቶን
4ኛ – በሪሁ አረጋዊ – በወንዶች 10,000 ሜትር
4ኛ – ጌትነት ዋለ – በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል
5ኛ – እጅጋየሁ ታዬ – በሴቶች 5000 ሜትር
6ኛ – ሀብታም አለሙ – በሴቶች 800 ሜትር
6ኛ – ሰንበሬ ተፈሪ – በሴቶች 5000 ሜትር
8ኛ – ዮሚፍ ቀጄልቻ – በወንዶች 10,000 ሜትር
8ኛ – ዘርፌ ወንድማገኝ – በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል

  • የአትሌቲክስ የነጥብ ደረጃ ሰንጠረዥ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ባሉት ደረጃዎች ውስጥ የሚያጠናቅቁ አትሌቶች በሚያስመዘግቡት ነጥብ ድምር መሰረት የሚወጣ ሲሆን የነጥብ አሰጣጡም ለአንደኛ ደረጃ 8 ነጥብ፣ ለሁለተኛ ደረጃ 7 ነጥብ፣ ለሶስተኛ ደረጃ 6 ነጥብ፣ ለአራተኛ ደረጃ 5 ነጥብ፣ ለአምስተኛ ደረጃ 4 ነጥብ፣ ለስድስተኛ ደረጃ 3 ነጥብ፣ ለሰባተኛ ደረጃ 2 ነጥብ፣ እና ለስምንተኛ ደረጃ 1 ነጥብ ነው።

ከፊታችን ምን  እየጠበቀን ነው? ምንስ እናድርግ?
ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፉ ወረርሺኝ ምክንያት ትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለሌላ ግዜ እንዲተላለፉ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ሌላ አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ቀጣዮቹ አራት ዓመታት በተከታታይ በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች የሚካሄዱባቸው ይሆናሉ፡፡ በ2022 የዓለም ሻምፒዮና፣ በ2023 የዓለም ሻምፒዮና፣ በ2024 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች፣ እና በ2025 የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ይኖራሉ፡፡ በቀጣዩ ዓመት በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ከሐምሌ 8 – 17/2014 በዩናይትድ ስቴትስ ኦሪጎን የሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዘጋጆች ሙሉ የውድድሩን ፕሮግራም፣ የማራቶን እና የእርምጃ ውድድሮች የሚካሄዱባቸውን ቦታዎች በትላንትናው ዕለት ይፋ አድርገዋል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናውን ውድድር በኃላፊነት የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ከወዲሁ ለዛ ውድድር ተሳትፎ የሚጠበቅበትን አቅዶ መንቀሳቀስ ይኖበርታል፡፡

ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጭቅጭቆችን ለማስቀረት ከወዲሁ ሁሉም አትሌቶች አውቀውት በውስጡ የሚያልፉበትን ገዢ የሆነ የመምረጫ መስፈርት ማዘጋጀት ቀዳሚው ተግባር መሆን አለበት፡፡ የመምረጫ መስፈርት ሁልግዜም በግላዊ ምልከታ እና ፍላጎቶች ላይ በሚመሰረት ምክንያት አነጋጋሪ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ቢሆንም ባለድርሻ አካላቱን በሙሉ ባሳተፈ መልኩ ውይይት ተደርጎበት ቢወጣ ሁሉንም ገዢ እና ከጭቅጭቅ የፀዳ ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህ ላይ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከተከሰቱት ሁኔታዎች አንፃር የሌሎች ሀገሮችንም ተሞክሮዎች በመዳሰስ ነገሩን ሰፋ አድርጎ መመልከት ቢቻል ጥሩ ነው፡፡ ትልልቅ ውድድሮች በመጡ ቁጥር በተደጋጋሚ እንደታዘብነው አንዳንድ አትሌቶች በቡድኑ ውስጥ ለመካተት የሚያደርጉትን ተገቢ ያልሆነ ሙከራም ማቆም አለባቸው፡፡ ከፋም ለማም ስፖርቱን እንዲመራ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም የሚያወጣቸውን መስፈርቶች ማክበርና በዛ ውስጥ ተመራጭ ለመሆን መሞከር ግድ እንደሚላቸውም መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ማኔጀሮች እና አሰልጣኞች በተለይ በማራቶን የራሳቸውን አትሌት ለማስመረጥ የሚያደርጓቸው አላስፈላጊ ግፊቶችም ሊያቆሙ ይገባል፡፡

ለውድድሮች የምናደርጋቸውን ዝግጅቶች ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ከውድድሮች በኋላ መገምገም እና መታረም ያለባቸው ነገሮች ካሉ ማረም፡፡ ከፍተኛ ሙቀት በነበረባቸው በለንደን 2012 ኦሊምፒክ ሶስቱም የወንዶች ማራቶን ተወዳዳሪዎቻችን፣ በሞስኮ 2013 የዓለም ሻምፒዮና ሁለቱ የሴቶች ማራቶን ተወዳዳሪዎቻችን፣ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ አምስት የማራቶን (ሶስቱም ወንዶች እና ሁለት ሴቶች) ተወዳዳሪዎቻችን እንዲሁም የሴቶች እርምጃ ተወዳዳሪያችን ለማቋረጥ መገደዳቸውን አስተውለናል፡፡ ስለዚህ በጎዳና ላይ ውድድሮች ከባድ ሙቀት ለሚኖርባቸው ቦታዎች እንዴት መዘጋጀት አለብን የሚለው ጉዳይም በደንብ ሊታይ የሚገባው ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ የመም (ትራክ) ተወዳዳሪ አትሌቶቻችን የውድድር ዓመቱ ሲጀምር ድንቅ ብቃታቸውን ያሳዩን እና ወደትልቅ ውድድር ሲቃረቡ አቋማቸው እየወረደ ይመጣል፡፡ አሰልጣኞቻቸው ለእነዚህ አይነቶቹ አትሌቶች ወደትልቅ ውድድር ሲቃረቡ ብቃታቸውን እያሳደጉ እንዲሄዱ የሚረዳቸውን የልምምድ ፕሮግራም ቢያዘጋጁላቸው መልካም ነው፡፡ በመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ላይ በተለይ በወንዶች አሁንም በከፍተኛ ደረጃ የሚፎካከሩ አትሌቶችን ለማፍራት ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል፡፡

Continue Reading

Articles

የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የቶኪዮ ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ማጣሪያ ውድድሮች የመጀመሪያ ሁለት ቀናት

Published

on

በሴቶች 5000 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ላይ የሚፎካከሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች

በቶኪዮ ኦሊምፒክ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት የኢትዮጵያ አትሌቶች የተሳተፉባቸው የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል፣ 800 ሜትር በሁለቱም ፆታዎች፣ እንዲሁም የሴቶች 5000 ሜትር ማጣሪያዎች ሌላኛዎቹ የኢትዮጵያውያን የትኩረት ማዕከል የነበሩ ውድድሮች ናቸው፡፡ ቀጣዩ ዘገባ የኢትዮጵያውያኑን የማጣሪያ ውድድሮች ተሳትፎ እና ውጤቶች አንዲሁም ተጨማሪ መረጃዎችን ይዟል፡፡

የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል

በአትሌቲክስ ውድድሩ የመክፈቻ ቀን (ዓርብ ሐምሌ 23/2013) ጠዋት ላይ በተካሄደው የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ማጣሪያ ከተሳተፉት ሶስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ከምድብ አንድ ለሜቻ ግርማ (8፡09.83) በአንደኛነት፣ ከምድብ ሁለት ጌትነት ዋለ (8፡12.55) በሁለተኛነት ለፍፃሜው ሲያልፉ በምድብ ሶስት የተወዳደረው ታደሰ ታከለ (8፡24.69) ስምንተኛ ወጥቶ ለፍፃሜው ሳያልፍ ቀርቷል፡፡ ለሜቻ ጃፓናዊው ሚዩራ ዩጂን እና ኬንያዊው ቤንጃሚን ኪይገንን በማስከተል ከምድቡ ያሸነፈበት 8:09.83 በኦሊምፒክ የማጣሪያ ውድድሮች ላይ የተመዘገበ የምንግዜውም ፈጣን ሰዓት ሆኗል፡፡ የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል የፍፃሜ የሜዳልያ ፉክክር በዋናነት በኬንያውኑ ቤንጃሚን ኪገን እና አብራሀም ኪቢዎት፣ በኢትዮጵያውያኑ ለሜቻ ግርማ እና ጌትነት ዋለ እንዲሁም በሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ መካከል እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል በ1980ው የሞስኮ ኦሊምፒክ በሻምበል እሸቱ ቱራ አማካይነት ካስመዘገበችው የነሐስ ሜልያ ድል ወዲህ በርቀቱ በወንዶች ምንም አይነት የኦሊምፒክ ሜዳልያ ድል የላትም፡፡ ሆኖም ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየታዩ የመጡ መሻሻሎች እና በዶሀው የዓለም ሻምፒዮና ላይ የተመዘገበው የብር ሜዳልያ ድል በቶኪዮም ሌላ ሜዳልያን ተስፋ እንድናደርግ ያነሳሳን ሆኗል፡፡ ዘግይቶ የተሰላፊ አትሌቶች ለውጥ ከተደረገባቸው ርቀቶች አንዱ በሆነው የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል በተጠባባቂነት የተመዘገበውና በዋናነት በ5000 ሜትር እንደሚወዳደር ይጠበቅ የነበረው ጌትነት ዋለ ወደመጀመሪያ ተሰላፊነት የመጣ ሲሆን ኃይለማሪም አማረ በመጨረሻ ሰዓት በለሜቻ ግርማ መተካቱም አነጋጋሪ የሆነ ሌላኛው ለውጥ ነው፡፡ ጌትነት በ3000 ሜትር መሰናክልም ጠንካራ ተፎካካሪ አትሌት ሲሆን በዶሀ የዓለም ሻምፒዮና ላይ አራተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ በፍፃሜው ውድድር በ2019 የርቀቱ የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮን ጌትነት ዋለ እና በወቅቱ የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊስት ለሜቻ ግርማ የሚወከለው የኢትዮጵያ ቡድን በቶኪዮ የኬንያውያኑን የበላይነት ለመግታትና አዲስ የስኬት ታሪክ ለማፃፍ እንደሚበቃ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡                     

በ1984 በሎስ አንጀለስ ከተከናወነው የኦሊምፒክ ውድድር አንስቶ በተከታታይ በዘጠኝ የኦሊምፒክ ውድድሮች ወይም ላለፉት 36 ዓመታት የኦሊምፒክ የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል የወርቅ ሜዳልያ ድል በኬንያውያን ቁጥጥር ስር ይገኛል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናም ተመሳሳይ የበላይነት ያላቸው ኬንያውያን ከ17 የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች በ14ቱ የወርቅ ሜዳልያው አሸናፊዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ከሁለት ዓመት በፊት በዶሀው የዓለም ሻምፒዮና ላይ ከኢትዮጵያውያን እና ከሞሮኮ አትሌቶች የገጠማቸው ተግዳሮት ለመሸነፍ እጅግ አቅርቧቸው የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ በአንድ ማይክሮ ሰከንድ ልዩነት አሸናፊነታቸውን ባረጋገጡበት በዶሀው ውድድር የተፈታተኗቸው ኢትዮጵያዊው ለሜቻ ግርማ እና ሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ በቶኪዮው ፍፃሜ ለሌላ ብርቱ ፉክክር እየጠበቋቸው ይገኛሉ፡፡ ባለፉት ሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች በቅደም ተከተል የብር እና የነሐስ ሜዳልያን ያገኘው ሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ በቶኪዮ ከሚወዳደሩት በሙሉ የላቀና 7፡58.15 የሆነ የራሱ ምርጥ ሰዓት ያለው ነው፡፡

ኬንያ በቶኪዮ ያለፈው ውድድር ሻምፒዮንነቱን ክብር የሚያስጠብቅላትን አትሌት ይዛ መቅረብ ሳትችል ቀርታለች፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት በሪዮ የኦሊምፒክ እንዲሁም ከሁለት ዓመት በፊት በዶሀ የዓለም ሻምፒዮን የሆነው ኮንሰስለስ ኪፕሩቶ ባለፈው ወር በኬንያ የኦሊምፒክ ምርጫ ውድድር ላይ ውድድሩን ባለማጠናቀቁ የኦሊምፒክ ሻምፒዮንነት ክብሩን ለማስጠበቅ በቶኪዮ አልተገኘም፡፡ ስለዚህ አሁን የረጅም ግዜ የበላይነታቸውን የማስጠበቅ ኃላፊነቱ በ2019ኙ የዶሀ የዓለም ሻምፒዮና ላይ በቅደም ተከተል ስድስተኛ እና ሰባተኛ ሆነው ባጠናቀቁት ቤንጃሚን ኪገን እና አብራሀም ኪቢዎት ላይ ወድቋል፡፡  

የሴቶች 800 ሜትር

ከአትሌቲክሱ የጀመሪያ ቀን የጠዋት መርሀግብሮች አንዱ በነበረው የሴቶች 800 ሜትር ማጣሪያ በምድብ ሶስት በአሜሪካዊቷ አቲንግ ሙ ተቀድማ በ2 ደቂቃ ከ01.20 ሰከንድ ሁለተኛ የወጣችው ሀብታም አለሙ ለግማሽ ፍፃሜው ያለፈች ሲሆን በሁለተኛው ቀን ምሽት ላይ በተካሄደው የግማሽ ፍፃሜ ውድድር ላይም በአሜሪካዊቷ አቲንግ ሙ ተቀድማ በ1:58.40 ሁለተኛ በመሆን በኦሊምፒክ የውድድር ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ በርቀቱ ለፍፃሜ ውድድር የበቃች ኢትዮጵያዊት ሆናለች፡፡ ሀብታም ከውድድሩ በኋላ በቶኪዮ ለሚገኘው ባልደረባችን አብይ ወንድይፍራው በሰጠችው አጭር ቃል ‹‹ውድድሩ ትንሽ ፈታኝ ነበር ነገር ግን ለሀገሬ ስል ያለኝን አቅም ሁሉ ተጠቅሜያለሁ፡፡ ክብሩ ይስፋ ለመድኃኒዓለም በመጨረሻም አሪፍ ውጤት ላይ ደርሻለሁ፡፡ ለኦሊምፒክ የፍፃሜ ውድድር ሳልፍ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም ከኢትዮጵያ ለፍፃሜ የደረሰ ያለ አይመስለኝም እና አሁንም መጨረሻዬን ያሳምርልኝ ነው የምለው›› ብላለች፡፡  

በሴቶች 800 ሜትር የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ በምድብ አራት በ2.01.98 አራተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ነፃነት ደስታ ወደ ግማሽ ፍፃሜው መቀላቀል ሳትችል ስትቀር በጀማሪዎች ስም ዝርዝር ላይ ስሟ ተካቶ በምድብ አንድ እንደምትሮጥ ስትጠበቅ የነበረችው ወርቅውሀ ጌታቸው ግልፅ ባልተደረገ ምክንያት ውድድሩን ሳትጀምር ቀርታለች፡፡

የወንዶ 800 ሜትር

የወንዶች 800 ሜትር የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ላይ የተሳተፈው ኢትዮጵያዊው መለሰ ንብረት ከምድብ ሶስት በ1:47.80 ሰባተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ለግማሽ ፍፃሜው ማለፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡ በመሐመድ አማን ስኬቶች በመነቃቃት ላይ የነበረው የወንዶች 800 ሜትር ከቅርብ ግዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ሶስት ሰዓት የሚያሟሉ ተወካይ አትሌቶችን ለማግኘት እየተቸገረችበት የምትገኝ ርቀት እንደሆነ እየታየ ነው፡፡ የኦሊምፒክ ሚኒማ ማሟላት የቻለ አንድ አትሌት ብቻ ይዘን የቀረብንበት የቶኪዮ ኦሊምፒክም ይህ ችግር እንዳልተቀረፈ የታየበት ሌላኛው አጋጣሚ ሆኗል፡፡  

የሴቶች 5000 ሜትር ማጣሪያ

በአትሌቲክሱ የመጀመሪያ ቀን ሐምሌ 23/2013 ምሽት ላይ በተደረት የሴቶች 5000 ሜትር ማጣሪያ ላይ የተሳተፉት ሶስቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሐምሌ 26/2013 ምሽት ላይ ለሚደረገው የፍፃሜ ውድድር አልፈዋል፡፡ ከምድብ አንድ ሰንበሬ ተፈሪ (14፡48.31) እና እጅጋየሁ ታዬ (14፡48.52) የኔዘርላንዷ ሲፋን ሀሳን (14፡47.89) እና ኬንያዊቷ አግነስ (14፡48.01) ቲሮፕን ተከትለው በቅደም ተከተል ሶተኛ እና አራተኛ ሆነው ሲያልፉ ከምድብ ሁለት ጉዳፍ ፀጋዬ (14፡55.74) ኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪ (14፡55.77) አስከትላ በአንደኛነት አልፋለች፡፡


ሐምሌ 26/2013 ምሽት ላይ በሚደረገው የሴቶች 5000 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ላይ የሚፎካከሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች

በሄንግሎ በተከናወነው የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ምርጫ ውድድር ላይ ባስመዘገበችው የራሷ ምርጥ 14:13.32 የርቀቱ የወቅቱ ፈጣን አትሌት ሆና ወደ ቶኪዮ ያቀናችው ጉዳፍ ለወርቅ ሜዳልያ ድል ከሚጠበቁት መካከል ናት፡፡ በሄንግሎው ውድድር ላይ ጉዳፍን በመከተል በቅደም ተከተል 14:14.09 እና 14፡15.24 በሆነ ሰዓት የጨረሱት እጅጋየሁ እና ሰንበሬም በዓለም የምንግዜም ምርጥ ዝርዝር ውስጥ የስድስተኛ እና ሰባተኛ ደረጃን ለመያዝ የበቁ ጠንካራ አትሌቶች ናቸው፡፡ የቶኪዮ ኦሊምፒክ የሴቶች 5000 ሜትር ተወዳዳሪዎች ዝርዝር ሶስቱን ኢትዮጵያውያን ጨምሮ ከዓለም የምንግዜም ምርጥ አስር የርቀቱ ሯጮች አምስቱን ያካተተ ነው፡፡ ኬንያውያኑ ሄለን ኦቢሪ እና አግነስ ቲሮፕ ከምንግዜም ምርጥ አስሮቹ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆኑ በ12ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሀሳንም የቶኪዮውን የፍፃሜ ፉክክር በጉጉት እንዲጠበቅ የምታደርግ ብርቱ አትሌት ናት፡፡

Continue Reading

Articles

ሰለሞን ባረጋ ለአስራ ሶስት ዓመት የራቀንን የወንዶች 10,000 ሜትር ድል በቶኪዮ ወደ ኢትዮጵያ መልሶታል

Published

on

218076583_1010892909482678_1235421043554241523_n

በቶኪዮ ኦሊምፒክ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአትሌቲክስ ውድድር በተጀመረ በሁለተኛው ቀን በወንዶች አስር ሺህ ሜትር ኢትዮጵያውያንን እጅግ ያስደስተው ድል በወጣቱ ሰለሞን ባረጋ አማካይነት ተመዝግቧል፡፡   
በ1980 ሞስኮ ላይ ምሩፅ ይፍጠር በርቀቱ ለመጀመሪያ ግዜ የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ካስገኘ በኋላ ከተደረጉት አስር የኦሊምፒክ የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ውድድሮች ኢትዮጵያ አምስቱን በበላይነት ለመጨረስ ችላለች፡፡ የርቀቱ ንጉሶች ሀይሌ ገብረስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ከ1992 እስከ 2008 ዓ.ም. በአራት ተከታታይ የኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ በማሸነፍ የርቀቱ የወርቅ ድል ለኢትዮጵያ ብቻ የተሰጠ እንዲመስለን አድርገውንም ነበር፡፡ ከ2008ቱ የቤይጂንግ ኦሊምፒክ የቀነኒሳ በቀለ ድል በኋላ በተከሰተው የሞ ፋራህ የበላይነት ምክንያት ተመሳሳዩን ድል በቶኪዮ ለማየት 13 ዓመታትን መጠበቅ ግድ ብሎናል፡፡ ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት በጉጉት ስንጠብቀው የቆየነውን የ10 ሺህ ሜትር የኦሊምፒክ ድል በመጨረሻም ሰለሞን ባረጋ በቶኪዮ አጎናፅፎናል፡፡ የሰለሞን የቶኪዮ የወርቅ ሜዳልያ ድል ኢትዮጵያ ካለፉት አስራ አንድ ኦሊምፒኮች በርቀቱ ለስድስተኛ ግዜ የበላይ ሆና እንድትጨርስ ያስቻለም ነው፡፡ ድሉ በቶኪዮ የአትሌቲኪስ ውድድሮች የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳልያ ድል ሆኖም ተመዝግቧል፡፡ ሰለሞን ባረጋ በ2018 የበርሚንግሀም የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር በ3000 ሜትር እና በ2019 የዶሀ ዓለም ሻምፒዮና ላይ በ5000 ሜትር የብር ሜዳልያ ካገኘ በኋላ በመጀመሪያ የኦሊምፒክ ተሳትፎው ከፍተኛ ክብር የሚሰጠውን የ10,000 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ድል ለማሳካት በቅቷል፡፡

‹‹የ200 ሜትር እና 400 ሜትር አጫጨር የፍጥነት ሩጫ ልምምዶችን ስሰራ ስለነበረ ሁለት ዙር ሲቀር ውድድሩን እንደማሸንፍ ለራሴ ነገርኩት››
ሰለሞን ባረጋ ከቶኪዮው ድል በኋላ

ሰለሞን ባረጋ ከቶኪዮው ድሉ በኋላ በስፍራው ከሚገኘው የስራ ባልደረባችን አብይ ወንድይፍራው ጋር ባደረገው አጭር ቃለ ምልልስ የሚከተለውን ብሏል ‹‹ረጅም ርቀት የእኛ ስፖርት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ሆኖም በኦሊምፒክ ውድድር ላይ ወርቅ ሜዳልያ ከወሰድን ብዙ ግዜ አልፎናል፡፡ ይህን ነገር ለመጨረሻ ግዜ ያሳካውም ቀነኒሳ ነበረ፡፡ ዛሬ በቶኪዮ ድሉን በማሳካቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በተለይ ለእኛ ከቶኪዮ ጋር አበበ ቢቂላን የምናስታውስበት ድል ስለሆነ ያንን በማሳካቴም በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ዘንድሮ ከኡጋንዳ የዓለም ሪኮርድ የሰበረው ቼፕቴጌይ እና የዓመቱን ፈጣን ሰዓት የሮጠው ኪፕሊሞ ነበሩ፡፡ እናም ውድድሩ በጣም ይፈጥናል ብዬ ነበር የጠበቅኩት ግን አልተሮጠም፡፡ ውድድሩን የጨረስነውም 27 ቤት ነው፡፡ የ200 ሜትር እና 400 ሜትር አጫጨር የፍጥነት ሩጫ ልምምዶችን ስሰራ ስለነበረ ሁለት ዙር ሲቀር ውድድሩን እንደማሸንፍ ለራሴ ነገርኩት፡፡ ኡጋንዳውያኑ አትሌቶች ዛሬ ብዙም አልታገሉም፡፡ አብዛኛውን ሰዓት ከኋላ ነው የቆዩት እና እንደዚህ ይሆናል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፡፡ እነርሱን ካሜራ ላይም እያየኋቸው ስለነበር ስለነሱ ብዙም አልተጨነቅኩም እንደውም ከእነሱ ይልቅ የእኛን ልጆች ነበረ ይወጣሉ ብዬ የጠበቅኩት፡፡ በውድድሩ መሀል ተጠባቂ የሆኑት ኡጋንዳውያን ወደኋላ ቀርተው ሶስተኛው የቡድን አጋራቸው ወደፊት ወጥቶ በሰፊ ልዩነት ሲመራ እኛ እነሱን ስንጠብቅ እሱ አዘናግቶ እንዳያሸንፍ ልዩነቱን ለማጥበብ ሞክሬያለሁ፡፡ ምናልባት እነሱ እኛን ሲጠብቁ አንተ ሂድ ያሉት ነበር የመሰለኝ፡፡ ከዚህ በፊት በእንደዚህ አይነቱ ነገር ዳይመንድ ሊግ ላይ ስለተሸወድኩኝ ያንን እንዳይደግሙ ብዬ ነበረ ልዩነቱን ለማጥበብ የሞከርኩት፡፡ የአሰልጣኜንም ምክር እየሰማሁ ስለነበረ የምሮጠው እና ወደኋላ ተመለስ እያለኝ ስለነበር ወደኋላ ተመልሻለሁ፡፡ የእነርሱ እስትራቴጂ እሱን ወደፊት እንዲወጣ አድርገው እኛን ለማድከም ነበረ፡፡ ከበሪሁን ጋር ስንነጋገር ወደፊት ጠጋ በል እያልኩት ነበረ፡፡ ከበሪሁን ጋር ልምምድም አብረን ነበረ የምንሰራው፡፡ እኔ እንደውም ከአንድ እስከ ሶስት እንወጣለን ብዬ ነበር የጠበቅኩት አጋጣሚ ሆኖ አልተሳካም ነገር ግን ወርቁን ወደኢትዮጵያ በመመለሳችን በጣም ደስተኛ ነን፡፡›› ብሏል፡፡

Continue Reading

Trending