Uncategorized
አዳማ መሪነቱን አጠናክሮ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በድል ጉዞው ቀጥሎ ሊጉ ተቋርጧል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በስድስተኛው ሳምንት በበርካታ ውዝግቦች የተሞሉ ጨዋታዎችን ካሳየን እና ከጨዋታዎቹም በኋላ የኢትዮጵያ ቡናን ጋዜጣዊ መግለጫ ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ አነጋጋሪ ጉዳዮችን ካስተናገደ በኋላ በውጥረት መንፈስ የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎቹንም አድርጓል፡፡ የሳምንቱ ትልቁ እና በጉጉት የተጠበቀ ጨዋታው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት የሚያደርጉት ነበር፡፡ ደደቢቶች በኢትዮጵያ ቡና ላይ ካገኙት ድል እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሀዲያ ሆሳዕናን በዳካማ የቡድን እንቅስቃሴ ከረቱ በኋላ ወደዚህ ጨዋታ መጥተዋል፡፡
ሰማያዊዎቹ በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ከጀመሩበት አሰላለፋቸው በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ የራቀውን አጥቂው ዳዊት ፍቃዱን ብቻ በሄኖክ መኮንን ተክተው ሲጀምሩ፣ ፈረሰኞቹ በሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ በቋሚነት ያልጀመሩት አሉላ ግርማ እና ተስፋዬ አለባቸውን አስጀምረዋል፡፡
ደደቢት (4-4-2 የሚመስል)
ግብ ጠባቂ፡- ታሪክ ጌትነት
ተከላካዮች፡- ስዩም ተስፋዬ፣ አክሊሉ አየነው፣ ምኞት ደበበ እና ተካልኝ ደጀኔ
አማካዮች፡- ሽመክት ጉግሳ፣ ያሬድ ዝናቡ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና ብርሀኑ ቦጋለ
አጥቂዎች፡- ሄኖክ መኮንን እና ሳሙኤል ሳኑሚ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1 የሚመስል)
ግብ ጠባቂ፡- ሮበርት ኦዳንካራ
ተከላካዮች፡- አሉላ ግርማ፣ አስቻለው ታመነ፣ አይዛክ ኢዜንዴ እና ዘካሪያስ ቱጂ
አማካዮች፡- ተስፋዬ አለባቸው፣ ምንተስኖት አዳነ
በኃይሉ አሰፋ፣ ምንያህል ተሾመ እና ራምኬል ሎክ
አጥቂ፡- አዳነ ግርማ
ከሰሞኑ የመነጋገሪያ ርእስ ከነበሩ ዳኞች በአንዱ በኢንተርናሽናል አርቢትር በአምላክ ተሰማ ዋና ዳኝነት የተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ብዙ ሙከራዎችን ባያሳየንም በጥሩ የፉክክር መንፈስ የተሞላ ነበር፡፡ በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቅርብ ሳምንታት ርቋቸው የነበረ ታጋይነት፣ ታታሪነት እና የላቀ ፍላጎትን ሲያሳዩ ነበር፡፡ የአሰልጣኝ ማርት ኖይ ልጆች በተለይ ኳሱን ሲቀሙ መልሰው ለመንጠቅ ያሳዩት የነበረው ጥረት ለደደቢት ፈተና ሆኖ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ሰማያዊዎቹ ምርጡ ተጨዋቻቸው ሳሙኤል ሳኑሚን ወደ ጨዋታው ለማስገባት ተቸግረው ነበር፡፡ ፈረሰኞቹ ወደ ደደቢት ጎል ለመቅረብ ካደረጓቸው ጥረቶች በኋላ በ27ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ተሻግሮ በራምኬል ሎክ የተጨረፈውን ኳስ አዳነ ግርማ አስቆጥሮላቸው መሪ መሆን ችለዋል፡፡ ከጎሉ በኋላ አግቢው አዳነን ጨምሮ ጥቂት የጊዮርጊስ ተጨዋቾች አሉላ ግርማ ለወለደው ልጅ መታሰቢያ የሆነ የእሹሩሩ ፈንጠዝያ አሳይተዋል፡፡ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም አዳነ ሌላ እድል አግኝቶ በቮሊ የሞከረው ኳስ ለጥቂት የመረብ ጎን መትቶ ወጥቶበታል፡፡ በ43ኛው ደቂቃ ምንተስኖት አዳነ ያሾለከለትን ኳስ ምንያህል ከማግኘቱ በፊት ግብ-ጠባቂው ታሪክ ጌትነት ወጥቶ አውጥቶበታል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የባከኑ ደቂቃዎች በኃይሉ አሰፋ ለአዳነ ያቀበለውን ግዙፉ አጥቂ ወደ ጎል ቢመታውም አሁንም ታሪክ በድንቅ ሁኔታ ጎል ከመሆን ታድጎታል፡፡ በጊዮርጊሶች የ1ለ0 መሪነትም ለእረፈት ወጥተዋል፡፡
ሁለተኛው አጋማሽ የተጀመረው መሀል ሜዳ ላይ ግልፅ ብልጫ እንደተወሰደባቸው የተገነዘቡት የደደቢቱ አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት የተጨዋች ለውጥ አድርገው ነበር፡፡ አሰልጣኙ አንጋፋው ያሬድ ዝናቡን አስወጥተው በወጣቱ ወግደረስ ታዬ ተክተውታል፡፡ ለውጡ ኳስ ቁጥጥር ላይ በተወሰነ መጠን የጠቀማቸው ቢመስልም የጊዮርጊስን ግብ ክልል መዳፈር ግን እምብዛም አልቻሉም፡፡ ጨዋታውም የበለጠ ኃይል የበዛበት እና በተጨዋቾች እና ተጨዋቾች እንዲሁም በተጨዋቾች እና በዳኛው መካከል አለመግባባቶች የሚታዩበት ሆኗል፡፡ በ49ኛው ደቂቃ ስዩም ተስፋዬ በአሉላ ግርማ ላይ ሰርቷል ላሉት ጥፋት አርቢትር በአምላክ የማስጠንቀቂያ ካርድ ማውጣታቸው ክርክር ፈጥሮ የነበረ ሲሆን፣ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በመጀመሪያው አጋማሽ የማስጠንቀቂያ ካርድ የተመለከተው ተስፋዬ አለባቸው እና ብርሀኑ ቦጋለ ተጎነታትለው አጠገባቸው የነበሩት አርቢትሩ በዝምታ አልፈዋቸዋል፡፡ በ56ኛው ደቂቃ ብርሀኑ ከ35 ሜትሮች ገደማ የመታው ኳስ በሮበርት ኦዳንካራ ተይዞበታል፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኋላ አዳነ መሀል ሜዳ አካባቢ አንድ ተጨዋችን በማራኪ መንገድ አልፎ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ወጥቶበታል፡፡ ወዲያውኑ ደግሞ በኃይሉ አሰፋ በግራ በኩል ወደ ደደቢት ጎል ሲያመራ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ‹ጥፋት ተሰርቶብኛል› ብሎ ቢወድቅም አርቢትሩ ‹ለማታለል ሞክረሀል› ብለው የማስጠንቀቂያ ካርድ አሳይተውታል፡፡ በ65ኛው ደቂቃ ደደቢቶች ፀጥ ያለ ቀን ያሳለፈው አጥቂው ሄኖክ ብርሀኑን በጋናዊው አጥቂ ጆሴፍ አምዮኪ ተክተውታል፡፡ በ66ኛው ደቂቃ ሌላው ተቀይሮ ገቢ ወግደረስ በጊዮርጊስ የጎል ክልል ውስጥ ጥሩ ኳስ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ወደ ውጪ ሰዶታል፡፡ በደደቢት በኩል የታየ ምርጡ አጋጣሚ ነበር፡፡ በ68ኛው ደቂቃ ራምኬል ሎክ እንዲሁም በ70ኛው ደቂቃ ብርሀኑ ከሩቅ የመታቸው ኳሶች ኢላማቸውን አላገኙም፡፡ በ77ኛው ደቂቃ ራምኬል ሎክ ተቀይሮ በመውጣት ለብሪያን ኦሞኒ ስፍራውን ሲለቅ፣ ብርሀኑ ያልተገባ ባህሪይ በማሳየት የአርቢትሩ የማስጠንቀቂያ ካርድ መዝገብ ሰለባ ሆኗል፡፡ በ80ኛ ደቂቃ ከሰሞኑ አቋሙ የወረደው በኃይሉ በናትናኤል ዘለቀ ተተክቷል፡፡ በ83ኛው ደቂቃ ጥሩ ረዥም ኳስ የተላከለት ጆሴፍ አምዮኪ ከግብ-ጠባቂው ኦዳንካራ ጋር ቢገናኝም ኳሱን በሚገባ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቷል፡፡ ጨዋታው በዚሁ ውጤት ተጠናቀቀ ተብሎ ሲጠበቅ ተቀይሮ የገባው ብሪያን ኦሞኒ በባከኑ ደቂቃዎች ላይ በደደቢት ተከላካዮች ስህተት ያገኘውን ኳስ ግብ ጠባቂው ታሪክን አንጠልጥሎ በማግባት የቡድኑን መሪነት አስፍቷል፡፡ ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ የ2ለ0 ድል ተጠናቋል፡፡
በሌሎች ጨዋታዎች፡-
- መሪው አዳማ ከተማ እና አጥቂያቸው ታፈሰ ተስፋዬ በአስደናቂ አቋማቸው ቀጥለዋል፡፡ የሊጉ መሪዎች ወደ ሀዋሳ አምርተው ባለሜዳው ሀዋሳ ከተማን በታፈሰ ሁለት ጎሎች 2ለ1 አሸንፈዋል፡፡ ደስታ ዮሐንስ ለሃዋሳ ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሯል፡፡
- ከሰሞኑ በውዝግቦች ውስጥ የከረመው ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ጨዋታው ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ ወደ አርባምንጭ የተጓዙት የአሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች ልጆች በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩባቸው ጎሎች 2ለ0 ተረትተዋል፡፡ ለአርባምንጭ ከተማ ተሾመ ታደሰ እና በረከት ወልደፃዲቅ ጎሎቹን አስቆጥረዋል፡፡
- ሌሎቹም ከከተማቸው ውጪ የተጫወቱት የአዲስ አበባ ክለቦችም ሽንፈት ደርሶባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በድሬዳዋ ከተማ 1ለ0 ሲሸነፍ፣ መከላከያ በሲዳማ ቡና እና ኤሌክትሪክም በዳሸን ቢራ በተመሳሳይ 1ለ0 ውጤቶች ሽንፈቶችን አስተናግደዋል፡፡ ሱራፌል ዳንኤል ለድሬዳዋ ከተማ፣ ቴዎድሮስ በቀለ ለሲዳማ ቡና በራሱ ላይ እንዲሁም ሸሪፍ ዲን ለዳሸን ቢራ የማሸነፊዎቹን ጎሎች አስቆጥረዋል፡፡
- ሆሳዕና ላይ ፍፁም ያልተጠበቀ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ የሊጉ ወለል እና እስካሁን አሸንፎ የማያውቀው ሀዲያ ሆሳዕና ወላይታ ድቻን 5ለ1 ደቁሷል፡፡ እንዳለ ደባልቄ፣ አበባየሁ ዮሐንስ፣ አምረላ ዴልታታ፣ አበው ታምሩ እና ዱላ ሙላቱ ለሃዲያ ሆሳዕና ጎሎቹን አስመዝግበዋል፡፡
- ከሰባተኛው ሳምንት ጨዋታዎች በኋላ አዳማ ከተማ በ19 ነጥቦች መሪነቱን ሲያጠናክር፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ16 እና ጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ሲዳማ ቡና በ12 ነጥቦች ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ ደደቢት በ11 ነጥቦች፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ዳሸን ቢራ በእኩል 10 ነጥቦች፣ ወላይታ ድቻ በዘጠኝ፣ መከላከያ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና በእኩል ስምንት ነጥቦች እስከ 10ኛ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በእኩል ሰባት ነጥቦች 11ኛ እና 12ኛ ደረጃን ሲይዙ ባለስድስት ነጥቡ ሀዋሳ ከተማ እና አራት ነጥቦች የያዘው ሀዲያ ሆሳዕና የመጨረሻዎቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ የአዳማ ከተማው ታፈሰ ተስፋዬ በስድስት ጎሎች ከፍተኛ ጎል አግቢነቱን ሲመራ፣ የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኑሚ በአምስት ጎሎች ይከተላል፡፡
- ፕሪምየር ሊጉ በቻን ዝግጅት እና ውድድር ምክንያት ከስድስት ሳምንታት ለሚበልጥ ጊዜ ይቋረጣል፡፡ የስምንተኛው ሳምንት ጨዋታዎች ምናልባትም የካቲት 5 እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል፡፡
Articles
24ኛው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና በፖላንድ ግድኒያ ይካሄዳል

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከምስራቅ አፍሪካ አቻዎቻቸው ጋር ለአሸናፊነት ይፎካከራሉ
በባልቲክ ባሕር ዳርቻ የምትገኘው ትንሿ የፖላንድ ወደብ ከተማ ግድኒያ በሀገራት መካከል የሚካሄድ የዓመቱ ብቸኛ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር የሆነውን እና ከሰዓታት በኋላ የሚጀመረውን የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች፡፡ ስመ ጥር አትሌቶች የተካተቱበትና ከ250 በላይ ተሳታፊዎች የሚፎካከሩበት ይህ ሻምፒዮና የዓለም አትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪያን አይኖች ዳግም በምስራቅ አፍሪካውያኑ ኮከቦች ላይ እንዲያተኩሩ እንደሚያስገድድ ይጠበቃል፡፡ በሴቶቹ ውድድር ሴቶች ብቻ የተሳተፉበት ሩጫ የዓለም ሪኮርድ ባለቤቷ ኬንያዊት ፐሬስ ጄፕቺርቺር እና በወንዶች አሯሯጭነት የተመዘገበ የዓለም ሪኮርድ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ አባበል የሻነህ፤ በወንዶች በቅርቡ የ5000 ሜትር እና 10000 ሜትር የዓለም ሪከርዶችን የሰባበረው ኡጋንዳዊው ጆሹዋ ቼፕቴጊ እንዲሁም ኢትዮጵያዊው ጉዬ አዶላ ከሌሎች ተፎካካሪዎቻቸው በመላቅ በፖላንዷ የባህር ዳርቻ ከተማ ላይ የወርቃማ ድል አሻራቸውን ለማሳረፍ ተስፋ ከሚያደርጉት ከዋክብት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ አዲስ አሸናፊ አትሌት የሚጠበቅበት የወንዶቹ ፉክክር
ከ2006 ዓ.ም. ወዲህ ከተካሄዱት ዘጠኝ የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የወንዶች ውድድሮች ከአንዱ በስተቀር ሁሉም ድሎች በኤርትራዊው ዘርሰናይ ታደሰ (5) ወይም በጆፍሬይ ካምዎሮር ስም የተመዘገቡ ናቸው፡፡ ዘርሰናይ እና ካምዎሮር በግዲኒያ የማይገኙ በመሆኑም ውድድሩ ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ የወርቅ ሜዳያ አሸናፊ ስም የሚመዘግብ ይሆናል፡፡ በግዲኒያ የወንዶቹ ፉክክር ማስጀመሪያ ሽጉጥ ሲተኮስ አይኖች ሁሉ ትኩረታቸው ከዚህ በፊት በ21.1 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ተወዳድሮ በማያውቀው የወቅታዊ ምርጥ ብቃት ባለቤት ኡጋንዳዊ አትሌት ጆሹዋ ቼፕቴጊ ላይ ይሆናል፡፡ ኡጋንዳዊው ምንም እንኳን የግማሽ ማራቶን ውድድር ልምድ ባይኖረውም ባለፈው እና በዘንድሮ ዓመት በተለያዩ ውድድሮች ካሳየው ድንቅ ብቃት አንፃር እንደሚጠበቀው ሆኖ እንደሚገኝም ይገመታል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኡጋንዳ አትሌቶች ላይ እየታየ የመጣው የብቃት መሻሻል ከዚህ ቀደም ብብርቱ ተፎካካሪነት ከሚታወቁት ኢትዮጵያ እና ኬንያ አትሌቶች በተጨማሪ የዓለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የወንዶቹን ፉክክር ይበልጥ እንደሚያደምቀው ይጠበቃል፡፡ የኡጋንዳ የወንዶች ቡድን በግማሽ ማራቶን ውድድር የመጀመሪያ ተሳትፎውን በሚያደርገው ጆሹዋ ቼፕቴጊ የሚመራ ሲሆን ሌላኛው ተጠባቂ አትሌት ጃኮብ ኪፕሊሞ፣ አቤል ቼቤት እና ሞሰስ ኪቤትንም አካቷል፡፡
በወንዶቹ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም የቼፕቴጊ ብርቱ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ ተገምቷል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ሳይጠበቅ ድንቅ ውጤቶችን በማስመዝገቡ ረገድ መልካም ስም ያለው ጉዬ አዶላ ለወርቅ ሜዳያ ድሉ ከተገመቱት መካከል አንዱ ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 በዴንማርክ ኮፐንሀገን ከተካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና በፊት ብዙም እውቅና ያልነበረው ቢሆንም የራሱም ምርጥ ሰዓት ከሁለት ደቂቃ በላይ ባሻሻለበት 59፡21 የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊ ለመሆን መብቃቱ ይታወሳል፡፡ በዚያው ዓመት መገባደጃ ላይም የወቅቱን የዓለም ግማሽ ማራቶን እና የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮን ጆፍሬይ ካምዎሮር በዴልሂ የግማሽ ማራቶን ፉክርር የራሱን ምርጥ ሰዓት 59.06 በማስመዝገብ ጭምር አሸንፎታል፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ በሮጠበት የ2017 የበርሊን ማራቶን ውድድር ላይ ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ በመጀመሪያ ተሳትፎ የተመዘገበ የምንግዜም ፈጣን የሆነ 2:03:46 ሰዓት ያለው ጉዬ አዶላ በፖላንዱ የግማሽ ማራቶን ላይ ለመሳተፍ ከተመዘገቡት አትሌቶች መካከል የርቀቱን ሶስተኛ ፈጣን ሰዓት የያዘም ነው፡፡
በጉዬ አዶላ በሚመራው የኢትዮጵያ ቡድን ውስጥ የግማሽ ማራቶን ፉክክርን ከ60 ደቂቃ በታች ለመጨረስ የበቁና ልምድ ያላቸው አንዳምላክ በልሁ (59:10)፣ ልዑል ገብረስላሴ (59:18) እና አምደወርቅ ዋለልኝ (59:22) እንዲሁም ለዚህ ውድድር መምረጫ በሀገር ውስጥ የተካሄደው የ15 ኪሎ ሜትር ውድድር አሸናፊው ሀይለማሪም ኪሮስ (1:01:08) ተካተዋል፡፡
የወንዶቹ ፉክክር ያለፉት ሶስት ሻምፒዮናዎች የተናጠል የወርቅ ሜዳልያ ድልን በጆፍሬይ ካምዎሮር አማካይነት አላስቀምስ ያለው የኬንያ የወንዶች ቡድን ዘንድሮም በጠንካራ አትሌቶች የተወከለ ሲሆን በግል የወርቅ ሜልያ ድል ተስፋውን የጣለውም የ2020 የፕራግ ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮን በሆነው ኪቢዎት ካንዲዬ እና የ2017 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ አሸናፊው ሊዮናርድ ባርሶቶን ላይ ነው፡፡ ማውሪስ ሙኔኔ፣ በርናርድ ኪፕኮሪር እና በርናርድ ኪሜሊም ሌሎቹ የኬንያ ተወዳዳሪዎች ናቸው፡፡
ሁለቱን የዓለም ሪኮርድ ባለቤቶች የሚያገናኘው የሴቶቹ ፉክክር
እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ አስተዳዳሪ አካል ቤሰቶች የጎዳና ላይ ፉከክሮች ሁለት አይነት የሪኮርድ አመዘጋገብን መከተል ከጀመረ ወዲህ የግድኒያው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የሴቶች ውድድር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለቱን የርቀቱ የዓለም ሪኮርድ ባለቤቶች የሚያፎካክር ይሆናል፡፡ የሴቶቹ ውድድር ከዓለም ሪኮርድ ባለቤቶቹ ኬንያዊቷ ፐሬስ ጄፕቺርቺር (ሴቶች ብቻ የሮጡበት ሪኮርድ ባለቤት) እና ኢትዮጵያዊቷ አባበል የሻነህ (ሴቶች ከወንዶች ጋር የሮጡበት የዓለም ሪኮርድ ባለቤት) በተጨማሪ ያለፈው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮን ኢትዮጵያዊቷ ነፃነት ጉደታም የአሸናፊነት ክብሯን ለማስጠበቅ የምትፎካከርበት ነው፡፡
በ2016 ካርዲፍ ላይ የተካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን አሸናፊነት ገድልም ያላት የ27 ዓመቷ ኬንያዊት ፐሬስ ጄፕቺርቺር በ2017 እና 2018 በወሊድ ምክንያት ከውድድር ርቃ ከከረመች በኋላ በ2019 ባደረገቻቸው ውድድሮች ወደ ምርጥ አቋሟ መመለሷን አሳይታለች፡፡ ያም ሆኖ በ2016 በተፎካከሩበት የዴልሂ ግማሽ ማራቶን በጄፕቺርቺር ላይ የበላይነቱን የወሰደችው ኢትዮጵያዊቷ አባበል የሻነህ በግዲኒያም ብርቱ ተፎካካሪዋ እንደምትሆን አያጠራጥርም፡፡ በ2013 የሞስኮ ዓለም ሻምፒዮና እና በ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ የ10000 ሜትር እና 5000 ሜትር ተሳትፎዋ ብዙም አመርቂ የሚባል ውጤት ያላስመዘገበችው አባበል ከዛ በኋላ አብዛኛውን ግዜዋን ለጎዳና ላይ ሩጫዎች ሰጥታ ስትሰራ ቆይታለች፡፡ ከተሳተፈችባቸው አስራ ሁለት የግማሽ ማራቶን ውድድሮችም በአስሩ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ደረጃዎች በመያዝ ማጠናቀቅ የቻለች ሲሆን ባለፈው ዓመት በተወዳደረችበት የቺካጎ ማራቶን ላይም የራሷ ምርጥ በሆነ 2፡20፡51 ሰዓት ሁለተኛ ሆና ጨርሳለች፡፡
የግድኒያው የሴቶች ግማሽ ማራቶን ዓለም ሻምፒዮና ሌላኛዎቹ የትኩረት ማዕከሎች ሁለቱ የከዚህ ቀደም ሪኮርድ ባለቤት እንዲሁም ከሁለት ዓመት በፊት በስፔን ቫሌንሲያ በተካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የወርቅ እና የብር ሜዳልያ አሸናፊዎች ኢትዮጵያዊቷ ነፃነት ጉደታ እና ኬንያዊቷ ጆሴሊን ጄፕኮስጋይ ናቸው፡፡ ነፃነት ከሁለት ዓመት በፊት በቫሌንሲያ የቅድመ ውድድር ተጠባቂዋ ጄፕኮስጋይን በማስከተል ሻምፒዮን ስትሆን የገባችበት ሰዓት ሴቶች ብቻ የሮጡበት ሪኮርድ ባለቤት አድርጓት ነበር፡፡ ሆኖም ከዛ በኋላ ግን ላለፉት ሁለት ዓመታት አንድም የግማሽ ማራቶን ውድድር ማሸነፍ አልቻለችም፡፡ ጄፕኮስጋይ አሁንም ሙሉ በሙሉ ሪኮርዶችን ወደሰባበረችበት የ2017 ዓ.ም. ድንቅ አቋሟ መመለስ ባትችልም ባለፈው ዓመት በመጀመሪያ የማራቶን ውድድር ተሳትፎዋ የኒው ዮርክ ማራቶንን ለውድድር ስፍራው ሪኮርድ በቀረበ ሰዓት ለማሸነፍ ችላለች፡፡ ሁለቱ አትሌቶች ባለፉት ሁለት ዓመታት አቋማቸው እምብዛም አመርቂ የነበረ ባይሆንም የግድኒያውን ውድድር ዳግም ወደውጤት ከፍታ የሚወጡበት መድረክ ለማድረግ የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
በኢትዮጵያ እና ኬንያውያን አትሌቶች መካከል ብርቱ ትንቅንቅ እንደሚደረግበት በሚጠበቀው የሴቶቹ ውድድር በኢትዮጵያ በኩል ከአባበል እና ነፃነት በተጨማሪ ያለምዘርፍ የኋላው፣ ዘይነባ ይመር እና መሰረት ጎላ የሀገራቸውን ሰንደቅ በዓለም አደባባይ ከፍ እንዲል ለማድረግ የሚፎካከሩ አትሌቶች ናቸው፡፡ በኬንያ በኩልም ሮዝመሪ ዋንጂሩ፣ ዶርካስ ኪሜሊ እና ብሪሊያን ኪፕኮኤች በጉጉት የሚጠበቀውን ድል ለማሳካት ከጄፕቺርቺር እና ጄፕኮስጋይ ጎን እንዲሰለፉ የተመረጡት አትሌቶች ናቸው፡፡
የኮሮና ቫይረስ በፍጥነት በዓለም ዙሪያ እየተስፋፋና አሳሳቢነቱ እያደገ በመምጣቱ ምክንያት በርካታ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች እንዲሰረዙ ተደርገዋል፡፡ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ አስተዳዳሪ (ወርልድ አትሌቲክስ) የበላይ ተቆጣጣሪነት እ.አ.አ. በማርች 29/2020 ሊካሄድ ፕሮግራም ተይዞለት የነበረው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ለመካሄድ የበቃውም በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ምክንያት ለኦክቶበር 17/2020 እንዲተላለፍ ተደርጎ ነው፡፡
በዘንድሮው ውድድር ላይ በ2014 ዓ.ም. ያስመዘገበችውን የወርቅ ሜዳልያ ድል ጨምሮ ባለፉት አስር የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮናዎች የቡድን የሜዳልያ ድል ተቋዳሽ የሆነችው ኤርትራ እንዲሁም ባለፉት 23 የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮናዎች ላይ ያለማቋጥ ተሳታፊ የነበሩት ጃፓን እና አሜሪካ ለመሳተፍ አትሌቶቻቸውን ሳያስመዘግቡ ቀርተዋል፡፡ ካናዳም ውድድሩ ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ያስመዘገበቻቸውን አትሌቶች በኮሮና ቫይረስ ስጋት ምክንያት ወደ ፖላንድ እንደማትልክ አሳውቃለች፡፡
* የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና ጣሊያንን ጨምሮ ከአስተላላፊዎች ጋር በተናጥል ስምምነት ከተደረሰባቸው 22 ሀገሮች በስተቀር በወርልድ አትሌቲክስ የዩቲዩብ ቻናል ለመላው ዓለም በቀጥታ ይተላለፋል፡፡
Uncategorized
የኢትዮጵያ ቀን በዋሽንግተን ዲሲ በ’ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ’ ዝግጅት ሊከበር ነው – Interview with Dr. Gashaw Abeza
Uncategorized
#Ethiopia: EthioTube ከስፍራው – Town Hall in DC on Addis Politics – Opening Speech by Ermias Legesse
-
EBS Mogachoch8 years ago
[New] EBS Drama Series – Mogachoch : ሞጋቾች | Episode 7
-
Articles9 years ago
Ethiopia’s renewable energy revolution shouldn’t fail to empower its poor
-
News2 years ago
መንግሥት ከሕወሓት ይልቅ ለአገሪቱ ሥጋት የሆኑ ሌሎች ችግሮች አሉብኝ አለ
-
Opinions1 year ago
On the TPLF’s Love Affair With ‘Genocide’
-
Music4 years ago
2019 ESFNA Atlanta: Ethiopian Day – Ethiopia Hagerachin : ኢትዮጵያ ሀገራችን
-
Music4 years ago
2019 #ESFNA Atlanta: Ethiopian Day | Neway Debebe – Hageren Alresam : ሀገሬን አልረሳም
-
Articles8 years ago
ሰበር ዜና፦ ተዋናይት ሰብለ ተፈራ (ትርፌ) በመኪና አደጋ ህይወቷ አለፈ
-
Bahilawi Zefenoch10 years ago
Bahilawi Zefenoch – ባህላዊ ዘፈኖች
Anonymous
January 3, 2016 at 5:39 pm
ambesa