Connect with us

Articles

አዲስ አባባ ስለምን ታወዛግባለች?

Published

on

Addis Ababa
Addis Ababa
አዲስ አባባ ስለምን ታወዛግባለች?
በዘላለም ክብረት
ሕሩይ ሚናስ አስደናቂ ሰው ነው፡፡ የገበሬ ልጅ፣ በአስራዎቹ መጨረሻ አዲስ አበባ የገባ፡፡ ከዛም የአብነት ተማሪ ሆነና ቅዳሴና ቅኔ ሞካከረ፡፡ እሱ አልሆን ሲለው ጎዳና ወጥቶ ጎዳና አዳሪ ሆነ፡፡ ቀጠለና የለማኝ መሪ (sighted guide) ሆነ፡፡ እሱም ሲያልፍ ‹ለምን አልማርም?› ብሎ ትምህርት ተማረና ዩንቨርሲቲ በገባ በዓመቱ ‹ማርክሲስት› ሆነ፡፡ ትምህርቱንም ለአቢዮቱ ሲባል ተወውና መፅሃፍ ነጋዴ ሆነ፡፡ ማርክሲስት ነጋዴ! ‹ከወገብ በላይ ታቦት፣ ከወገብ በታች ጣኦት› እንዲሉ የትናንት ቀዳሹ ሕሩይ ዛሬ ማርክስዚምን ወደደ፡፡ የሕሩይ ማርክሲዝም ከትናንት ማንነቱ እጅግ በተለየ መንገድ ወሰደው፣ የመፅሃፍ አርታኢነት፡፡ መፅሃፍ ሲያነብ፣ ሲተረጉም፣ ሲፅፍና የአርትኦ ስራ ሲሰራ ውሎ ጫት ይቅማል፤ በዛ ላይ አረቄም ይሞካክራል፡፡ በመጨረሻ አበደ፡፡ ከዛ በኋላ ያለው የሕይወቱ ምዕራፍ ብዙ ያሳዝናል፡፡
በኋላ ከአዕምሮ ሕመሙ ሲያገግም ግን የሚገርም ነገር አደረገ፡፡ ‹እብድ› እያለ ሲያደርጋቸው ነበሩትንና የሚያስታውሳቸውን ነገሮች ሁሉ በተርታ ፅፎ ‹እብዱ› በሚል ርዕስ መፅሃፍ አሳተመ፡፡ ይህ መፅሃፉ ለሕሩይ ከብዙ ስራዎቹ አንዱ ነው፡፡ ስለ አዲስ አበባ ለመፃፍ ከሕሩይ የተሻለ ምሳሌ ማግኝት ይከብዳል፡፡ እሱም ‹ወይ ዐዲስ ዓበባ› በሚል ርዕስ (እውነትን መሰረት ያደረገ) መፅሃፍ ፅፎ አዲስ አበባ ከሩቅ ሲያይዋት ምን እንደምትመስል ይተርካል፡፡ በሕሩይ የገጠር ሕይወት አይን አዲስ አበባ ገነት ነበረች፡፡ ሕሩይ እንዲያውም በመደነቅ ‹‹ለካ የዐዲስ ዓበባን ሰው ፎቶ እያነሱ ነው ወደ ገጠር ‹ምስለ መላዕክትና ሰማዕት› እያሉ የሚልኩልን›› በማለት እሱ ከሚያውቀው ገጠርና ሕዝቡ አንፃር አዲስ አበባ ገነት፣ ነዋሪዎቿም መልዓክት እንደሆኑ ይገልፃል፡፡ ገነት ሆና ከሩቅ የታየችው አዲስ አበባ ሲገባባት ጎዳና ላይ አስተኝታዋላች፣ ‹አቢዮተኛ› አድርጋዋለች፣ አሳብዳ አስለፍልፋዋለች … በስተርጅናውም ‹ከጋራ ኮንዶሚኒየም ቤቶቿ› በአንዱ ይኖር ዘንድ ፈቅዳለታለች፡፡ ሕሩይ አዲስ አባባን ከሩቅ አይቶ ጎምጅቶባታል፡፡ አዲስ አበባን ጉያዋ ስር ሆኖም ተሰቃይቶባታል፡፡ ዛሬ ደግሞ አዲስ አበባ ሕሩይን እንከባከብኻለሁ እያለችው ነው፡፡ ሕሩይ ሚናስ – ራሱን ‹አውግቸው ተረፈ› ብሎ የሰየመ ሰው፡፡
ይህ የሕሩይ ብቻ ታሪክ አይደለም፡፡ የብዙ ኢትዮጵያዊያንም እንጂ፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አዲስ አበባን ከከተማም በላይ የስልጣኔ ምልክት አድርጎ ነው የሚቆጥራት፡፡ እንዲያውም ሌሎች ከተሞች የሚለሙት ከአዲስ አበባ የሚመጡ ነዋሪዎች እንዲዝናኑባቸው ሁሉ እስኪመስል ድረስ የሌሎች ከተሞችን ዕድገት ሁሉ ወሳኟ አዲስ አበባ እየሆነች ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ አካባቢዎች ‹የአዲስ አበባ እንግዶች መጥተዋል› ከተባለ ነገሩ ትልቅ ነው፡፡ አንዳንዴማ ‹እሷ እኮ አዲስ አበባ ቤት አላት› ሲባል ሁሉ ነው ሃብት የሚቆጠረው፡፡
አዲስ አበባ አንድ ከተማ ብቻ ነች ማለት ከባድ ነው፡፡ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ 3.6 በመቶው ብቻ ቢሆንም አዲስ አበባ የሚኖረው ቀሪው የሀገሪቱ ሕዝብ ያለ አዲስ አበባ ምንድን ነው? እስኪባል ድረስ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ለተባለው ዓለም የስበት ማዕከል (center of gravity) ናት፡፡
1. “Addis Ababa: The 3rd most ‘Primate City’ on earth”
ጅኦግራፈሩ ማርክ ጀፈርሰን በጎርጎሮሳዊያን አቆጣጠር በ1939 አንድ የከተሞች እድገት ምጥጥን (balance) የሚገልፅ ሃሳብ ይዞ ብቅ አለ፡፡ የአውራ ከተማ (Primate City) ፅንሰ ሃሳብን፡፡ እንደ ጀፈርሰን አገላለፅ አንድ ከተማ በሀገሪቱ ውስጥ ካሉት ሌሎች ከተሞች መካከል በሕዝብ ቁጥር ትልቁ ሲሆንና የሕዝብ ቁጥሩም በሁለተኝነት ከሚከተለው ከተማ በእጥፍ ሲበልጥ ያ ከተማ ‹አውራ ከተማ› (Primate City) ይባላል፡፡ (በኋላ በጀርመናዊው ጅኦግራፈር ዋልተር ክራይስትለር የተፈጠረው የCentral Place Theory (CPT) በበኩሉ አውራነት የሚለካው አውራው ከተማ ከተከታዩ በሁለት ዕጥፍ ከበለጠ ነው በማለት ሌላ መከራከሪያ አቅርቧል)፡፡ ለማንኛውም ጀፈርሰን ይሄን የከተማ አውራነት መስፈርት (primacy rule) ካስቀመጠ ከአስር ዓመታት በኋላ በተለምዶ ‘Zipf’s law’ የሚባለውና በሳይንሳዊው አጠራር ‘Rank Size Rule’ እየተባለ የሚጠራው የምጥጥን (proportionality) ሂሳብ በአሜሪካዊው የስነ ቋንቋ ምሁር ጆርጅ ዚፒፍ ብቅ አለ፡፡ ዚፒፍ ምጥጥኑን ከቋንቋ ጋር አያይዞ ያቀረበው ቢሆንም በኋላ ወደሌሎች ጉዳዮችም አድጓል፡፡ በዚህም መሰረት እንደ ዚፒፍ ሎው የአንድ ሀገር የከተማ እድገት ጤነኛ ነው የሚባለው በአንድ ሀገር ውስጥ ካለው በሕዝብ ቁጥሩ ትልቁ ከተማ ቀጥሎ በሁለተኝነት የሚገኝው ሁለተኛው ከተማ በሕዝብ ትልቁ የሆነውን ከተማ ግማሽ ያክል ሕዝብ ያለው መሆን ይኖርበታል፡፡ ሶስተኛው ትልቅ ከተማ ደግሞ የትልቁን ከተማ ሲሶ ያህል ሕዝብ ሊኖርበት ይገባል፡፡ አራተኛው ትልቅ ከተማ ደግሞ የትልቁን ከተማ ሩብ ያህል ሕዝብ ሊኖርበት ይገባል… እያለ ምጥጥኑን ይቀጥላል፡፡
እንግዲህ ይሄን ህልዮታዊ መነሻ ይዘን፡፡ የአውራ ከተማ መኖር ምንን ያመላክታል የሚለውን ጉዳይ ስናይ ነው የሕልዮቶቹ መሰረት የሚገለፅልን፡፡ አንድ ሀገር አውራ ከተማ አላት ማለት አውራ የተባለው ከተማ የሀገሪቱ የትኩረት ነጥብ (national focal point) ነው ማለት ነው፡፡ ከዛም ባለፈ ያ ከተማ የሀገሪቱን ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በዋነኛነት በያኝ (strong pull factor) ነው ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ሀገሪቱ የንጉሳዊ ግርማ (King Effect) ሰለባ ነች ማለት ነው፡፡ ስለ ሀገሪቱ ማውራት ማለት ስለ አውራው ከተማ ማውራት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በመዓከሉ (center) እና በዳር ሀገሩ (periphery) መካከል የእኩልነት ሚዛን እጅግ ተዛብቷል (imbalance) እንደማለት ነው፡፡
1.1. ሁለተኛ ከተማ (Secondary City)
በሌላ በኩል ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአውራ ከተማን ፈተና ለመከላከልና ፍትሃዊ የከተማ እድገት እንዲኖር ሲባል የዓለም ባንክን ጨምሮ ብዙ ፖሊሲ አውጭዎች የሁለተኛ ከተማ (Secondary City) አማራጭን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ማለት ከትልቁ ከተማ ባለፈ በሀገራት ውስጥ ከትልቁ ከተማ ብዙም ያልራቁ (አንዳንዶች ከ500,000 – 3,000,000 ነዋሪ ያለባቸው ከተሞች ሲሉ ሁለተኛ ከተማነትን ያብራራሉ) አማራጭ ከተሞችን መፍጠር ነው፡፡ ደቡብ ምስራቅ እስያ በዚህ በኩል በጣም የተሳካለት የዓለማችን ክፍል ነው፡፡
1.2. ኢትዮጵያስ?
የኢትዮጵያን ጉዳይ ስንመለከት ከላይ ከቀረቡት ሕልዮቶችና የፖሊሲ አውጭዎች ምክረ ሃሳብ እጅግ በተቃራኒው እናገኛታለን፡፡ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን በሃምሌ 2007 ባወጣው ሪፖርት መሰረት ኢትዮጵያ 973 ከተሞች እንዳሏት የገለፀ ሲሆን፤ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብም 19 በመቶ የሚሆነው (ይህ አሃዝ አከራካሪ ነው) በከተማ ውስጥ ይኖራል ይላል ሪፖርቱ፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ 973 ከተሞች ቢኖሯትም ከአምስቱ የከተማ ነዋሪዎች መካከል አንዱ በአዲስ አበባ ከተማ ነው የሚኖረው፡፡ በሌላ አነጋገር በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ (አዲስ አበባን ሳይጨምር) ከአንድ መቶ ሺህ ሕዝብ በላይ ያላቸው አስራ ስድስት ከተሞች ያሉ ሲሆን፤ የአስራ ስድስቱ ከተሞች ሕዝብ ተደምሮ ከአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ጋር እኩል ነው፡፡
የማርክ ጀፈርሰንን የአውራነት ሕግ (primacy rule) እዚህ ላይ አምጥተን ስንመለከት አዲስ አበባን ከአውራም አውራ ሆና እናገኛታለን፡፡ ይሄም የሚሆነው በአንድ ሀገር ውስጥ ያለው ትልቅ ከተማ (አዲስ አበባ) በሀገሪቱ ውስጥ ካለው ሁለተኛ ትልቅ ከተማ (በሃምሌው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን ሪፖርት መሰረት አዳማ ከተማ ናት ሁለተኛዋ ብዙ ሕዝብ የሚኖርባት ከተማ) በእጥፍ ከበለጠ አውራ ከተማ እንደሚባል ከላይ ያየን ሲሆን፣ በዚህ ስሌት መሰረትም አዲስ አበባ ከተከታዩ አዳማ ወደ አስራ አንድ እጥፍ እንደምትበልጥና ይሄም አዲስ አበባ ከታይላንዷ፣ ባንኮክና ከፔሩዋ ሊማ ቀጥላ በዓለም ላይ ሶስተኛዋ አውራ ከተማ ሲያደርጋት በአፍሪካ ደግሞ አንደኛዋ ያደርጋታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ግዝፈቷ የዚኮፍን የምጥጥን ሎው እንኳን መተግበር ማሰብም ከባድ ያደርገዋል፡፡ ይህ የተዛባ ምጥጥን አዲስ አበባ ከመመስረቷ ጀምሮ የተፈጠረ ነው ማለት ደግሞ ከባድ ነው፡፡ የአለፈውን የመቶ ዓመት እድገት እንኳን ብንመለከት በ1910 የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ 65,000 የነበረ ሲሆን ይህ ቁጥርም በጊዜው ከሀረር ከተማ ሕዝብ ጋር እኩል ነበር፡፡ ከሃያ አምስት ዓመታት በኋላ 1935 የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ 100,000 ሆነ፡፡ ከሌላ ሃያ አምስት ዓመታት በኋላ በ1961 የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ 443,728 ደረሰ፡፡ አሁንም ከሌላ ሃያ አምስት ዓመታትም በኋላ በ1984 የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ 1,423,111 ደረሰ፡፡ በመጨረሻም ከ35 ዓመታት በኋላ በ2015 የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ከእጥፍ በላይ ጨምሮ ዛሬ 3,194,000 ደርሷል፡፡ ከመቶ ዓመታት በፊት በጊዜው በሕዝብ ቁጥር ሁለተኛ ከነበረችው የሀረር ከተማ ጋር ተመጣጣኝ ቁጥር የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ዛሬ በሁለተኝነት ከምትገኝው አዳማ ከተማ አስራ አንድ እጥፍ በልጣ በአውራ ከተማነት በሩቅ ተቀምጣለች፡፡
ስታንሊ ብሩን የተባሉ ፀሃፊ ‹‹የአውራ ከተማ መኖር በራሱ የሀገሪቱ እድገት ጤናማ እንዳልሆነና የተዛባ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ ይሄም ማዕከሉ (center) ከዳሩ (periphery) አለመመጣጠናቸውን ያስገነዝበናል› ይላሉ፡፡ እንግዲህ የአሁኗ ኢትዮጵያን ፍትሃዊነት አዲስ አበባ በደንብ የምትገልፃት ይመስላል፡፡
አዲስ አበባ በታሪኳ ሶስት ጊዜ ከዋና ከተማነቷ የመቀየር እጣ ፋንታ ተጋርጦባት እንደምንም አልፋዋለች፡፡ የመጀመሪያው በአፄ ምኒልክ ዘመን በአካባቢዋ ያለው የማገዶ እንጨት በማለቁ ምክንያት ዋና ከተማው ወደ አዲስ ዓለም ለመቀየር በታሰበበት ወቅት ባህር ዛፍ ከአውስትራሊያ መጥቶ አዲስ አበባን ከመቀየር አድኗታል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ጣሊያን አዲስ አበባን በተቆጣጠረበት ወቅት አዲስ አበባ ተራራማ ከተማ ላይ በመሆኗ ጣሊያኖቹ የራሳቸውን የቅኝ ግዛት ዋና ከተማ (colonial city) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢ ለመመስረት ጥረት አድርገው በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ሊተዉት ችለዋል፡፡ እንዲሁም አፄ ኃይለስላሴ የቀደመውን የተንቀሳቃሽ ዋና ከተማ (roving cities) ልምድ ለማስቀጠልና የራሳቸውን ዋና ከተማ ለማቋቋም በማሰብ ባህርዳርን ዋና ከተማቸው ለማድረግ አስበው እንደነበር ታሪክ ፀሃፊው በላይ ግደይ ‹አዲስ አበባ ያብባል ገና› ባሉት መፅሃፋቸው ላይ ይጠቁማሉ፡፡ ዛሬ አዲስ አበባ ዋና ከተማ ብቻ ሳትሆን ‹ሀገር› ናት፡፡ የበታቾቿን በሩቅ የምታይ ከተማ፡፡
በሌላ በኩል እነ ዓለም ባንክ እያስተዋወቁት የሚገኝው የሁለተኛ ከተማ (Secondary City) ፅንሰ ሃሳብም በአሁኗ ኢትዮጵያ ቦታ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ በፖለቲካና የንግድ ማዕከልነት የአውራዋን አዲስ አበባን ሚዛን የሚገዳደር አይደለም፤ ተስፋ እንኳን ያለው ከተማ አለ ማለት በጣም ከባድ ነው፡፡ ይህ የአዲስ አበባ አውራነትም ከተማዋን በሀገሪቱ ውስጥ በነዋሪ ደረጃ የመሰረታዊ አገልግሎቶች በቀላሉ የሚገኝባት (the highest concentration of basic service facilities per population) ቀዳሚ ከተማ አድርጓታል፡፡ ይሄም ከተማዋን ‘privileged position’ ያሰጣት ከመሆኑም ሌላ፤ አዲስ አበባን እጅግ ግዙፍና የማይደረስባት አይነት ከተማ አድርጓታል፡፡
ከአዲስ አበባ ምስረታ ጋር ተያይዘው ከሚነገሩ አፈ ታሪኮች አንዱ፣ የአፄ ምኒልክ ሃይለ መለኮት አያት የሆኑት ንጉሰ ሸዋ ሳህለስላሴ በአንድ ወቅት ጉለሌ የሚገኝ አንድ ዛፍ ስር ቁጭ ብለው ‹እዚህ አካባቢ የልጅ ልጆቼ ትልቅ ከተማ ሲመሰርቱ ይታየኛል› ብለው ነበር ይላል፡፡ ሳህለስላሴ የዛሬዋን አዲስ አበባ ቢያዩ ‹እንዴ እኔ በራዕይ ያየሁት እኮ ሀገር አይደለም ከተማ ነው› ብለው መደናገራቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡
የፌደራል ሀገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየን ፌደራሊዝም ‹አውራ ከተማን› (Primate City) ያጠፋል፡፡ የደቡብ ምስራቅ ተሞክሮ እንደሚያሳየን ደግሞ ልማታዊ መንግስት በዛ ያሉ ሁለተኛ ከተሞችን (Secondary Cities) ይፈጥራል፡፡ አውራዋ አዲስ አበባ የአውራዎች አውራ እየሆነች እየሄደች ሲሆን፡፡ አውራ ብቻ ሳትሆን ሁለተኛ ከተማም (Secondary City) ራሷ አዲስ አበባ ነች፡፡ አዲስ አበባ ብቻዋን እንዲህ ገዝፋ የአውራም አውራ እስክትሆን ድረስ ፖሊሲ አውጭዎቹ የት ሂደው ነው ብሎ መጠየቅ እዚህ ጋር ተገቢ ነው፡፡ የአሁኗ አዲስ አበባ ሕጋዊ (Legal status) ምንድን ነው ብለንም መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡
2. አዲስ አበባ ምንድን ናት?
ኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓትን በሕገ መንግስት ደረጃ ከተቀበለች ሁለት አስርት ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓትም በሕገ መንግስት ደረጃ ዘጠኝ ክልሎችንና አዲስ አበባን እንደ አንድ የፌደራል ከተማ አስተዳደር (ድሬ ዳዋ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል ያለው የይገባኛል ጥያቄ ‹ዘላቂ የሆነ ሕጋዊ መፍትሔ እስኪያገኝ› ለፌደራል መንግስቱ ተጠሪ በመሆን በአዋጅ ቁጥር 416/1996 የተቋቋመች የከተማ አስተዳደር ናት) በማድረግ ተቋቁሟል፡፡ በሕገ መንግስቱም ሆነ በኋላ ከተማዋን በሕግ ለማቋቋም በወጡት ቻርተሮች የከተማዋ ሕጋዊ ‹ስታተስ› (ከዋና ከተማነት ባለፈ) በግልፅ ባለመቀመጡም የከተማዋ ‹ስታተስ› ለተመሳሳይ ጥያቄ የተለያዩ መልሶችን እየሰጠ ቀጥሏል፡፡ ዓለም ላይ ባሉ የተለያዩ የፌደራል ስርዓቶች ዋና ከተማ ከዚህ በሚከተሉት ሶስት ጎራዎች በአንዱ ላይ ይመደባል፡፡ ራሱን የቻለ ክልል (City State)፣ በሕግ በፌደራል ቀጠናነት የተመደበ ከተማ (Federal District)፣ እና በአንድ ክልል ውስጥ የሚገኝ አንድ ከተማ (A City in A State)፡፡ ኢትዮጵያም በሕግ የፌደራል ስርዓትን ያቋቋመች ሀገር በመሆኗ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በየትኛው ጎራ ትመደባለች ለሚለው ጥያቄ አንድ አይነት መልስ ማግኝት አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ አስቸጋሪ ሁኔታም ነው በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል መካከል ያለው ውዝግብ እንዳይፈታ አይነተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ያለው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ሶስቱ መደቦች አንፃር የአዲስ አበባን ‹ስታተስ መመልከት› ጉዳዩን በበለጠ እንድንረዳው ይረዳናልና እሱን እንመልከት፡፡ ለመሆኑ አዲስ አበባ ምንድን ናት?
2.1. ራሷን የቻለች ክልል (City State) ናት
የፌደራል ስርዓትን ተግባራዊ ያደረጉ ሀገሮች ከሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች አንዱ ዋና ከተማን መምረጥና መሰየም ነው (የስዊዘርላንድ ሕገ መንግስት በሕገ መንግስት ደረጃ ዋና ከተማ ከመሰየም የተቆጠበውም በዚህ ውዝግብ ምክንያት ነው)፡፡ የፌደራል ስርኣት የመንግስት ስራን በማዕከሉ መንግስትና በክልሎች መካከል የሚከፍል በመሆኑ ዋና ከተማዋን የትኛው ክልል ላይ ማድረግ አለብን የሚለው ጥያቄ አወዛጋቢ ነው፡፡ እንደ ጀርመን እና ቤልጅየም ያሉ የፌደራል ሀገሮች ለዚህ መፍትሔ ብለው ያቀረቡት ሀሳብ ዋና ከተማውን ራሱን የክልል ማዕረግ በመስጠት ከፌደራሉም ሆነ ከክልል መንግስታት ነፃ ማውጣትን ነው፡፡ በመሆኑም በርሊን በአሁኑ ወቅት ከአስራ ስድስቱ የጀርመን ክልሎች አንዷና ዋና ከተማ ስትሆን የቤልጀሟ ብራሰልስም ከቤልጅየም ሶስት ክልሎች አንዷ በመሆን የተፎካካሪዎቹ ፍሌሚሽና ዋሎን ክልሎች አስታራቂ ሁና በመሃል ትገኛለች፡፡
ታዲያ አዲስ አበባ ከዚህ ሞዴል ጋር ምን አገናኛት? በርግጥ አሁን በስራ ላይ ያለው ሕገመንግስት ያቋቋመው ዘጠኝ ክልሎችን ብቻ ነው፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ ከነዚህ ክልሎች ውጭ ናት፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባን በዋና ከተማነት ያቋቋመው የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 49ን በጥልቀት ስንመለከት በንዑስ አንቀፅ ሁለት ላይ አዲስ አበባን ራሷን በራሷ የማስተዳደር ሙሉ መብት ይሰጣታል፡፡ ይህ አንቀፅም በሽግግር መንግስቱ ወቅት በአዋጅ ቁጥር 07/1984 እንደ ራስ ገዝ አስተዳደር በመሆን የተቋቋመችውን አዲስ አበባን መንፈስ ያጠናክራል፡፡ ይሄንም ስንመለከት አዲስ አበባ በተግባር (de facto) ራሷን የቻለች ክልል ትመስላለች፡፡ በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ራሷን ችላ በሕግ ደረጃ (de jure) ክልል እንድትሆን ከሽግግሩ ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የሚጎተጉቱ አካላት ብዙ ናቸው፡፡
2.2. የፌደራል ቀጠና (Federal District) ናት
በሌላ በኩል የፌደራል ዋና ከተማን የመምረጥ ፈተና ለማለፍ በዛ ያሉት ፌደራል ሀገሮች ዋና ከተማዋን በፌደራል ቀጠናነት (Federal District) በሕግ በመከለል ተጠሪነቷን ሙሉ ለሙሉ ለፌደራል መንግስት የማድረግን አሰራር ይጠቀማሉ፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት አሜሪካና ሕንድ ናቸው፡፡ አሜሪካ ከሜሪላንድና ከቨርጅኒያ ግዛቶች መሬት በመውሰድ ዋሽንግተን ዲሲን በዋና ከተማነት ሰይማ (ስፋቱ ከአስር ማይል መብለጥ የለበትም የሚል ገደብ በማስቀመጥ) ተጠሪነቷን ለኮንግረስ አድርጋለች፡፡ ሕንድም ዴልሂን ዋና ከተማና የፌደራል ቀጠና አድርጋ ተጠሪነቱን ለምክር ቤት አድርጋለች፡፡ ይህ አይነት የዋና ከተማ አደረጃጀት የራሱ የሆነ (በተለይም ከምርጫ፣ ግብር እና የክልሎች መብት አንፃር) ችግሮች ያሉበት ነው፡፡ ከታች ለማየት እንሞክራለን፡፡
አዲስ አበባን ስንመለከት የህገ መንግስቱ አንቀፅ 49 (3) እና (4) አዲስ አበባ ተጠሪነቷ ለፌደራሉ መንግስት መሆኑን በመግለፅ የአዲስ አበባ ቀጠና የፌደራል ቀጠና እንደሆነ በተዘዋዋሪ ያስረዳል፡፡ ይህ ብዙ ሰዎች የሚስማሙበት ሃሳብ ቢሆንም ተያያዥ ችግሮች ግን በየጊዜው መነሳቸው አልቀረም፡፡
2.3. በአንድ ክልል የምትገኝ አንድ ከተማ (A City in a State) ናት
ሌላው ከፌደራል ዋና ከተማ አመሰራረት ጋር ተያይዞ የሚቀርበው መፍትሔ ደግሞ ዋና ከተማዋን ከክልሎች (States) በአንዱ ከተማ ላይ ማድረግና ክልሎች ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ ማድረግ የሚለው ነው፡፡ የዚህ መፍትሔ ምሳሌ ተደርጋ የምትቀርበው ካናዳ ነች፡፡ የካናዳዋ ዋና ከተማ ኦታዋ ከካናዳ ስድስት ክልሎች አንዷ በሆነችው ኦንታሪዎ ግዛት ውስጥ የምትገኝ ከተማ ነች፡፡ ኦንታሪዎም እንደ ዋና ከተማ መቀመጫ ክልልነቷ ከኦታዋ ማግኝት የሚገባት ጥቅም በሕግ የተደነገገና የፀና ነው፡፡ ይህ አካሔድ በሌሎች ክልሎች ዘንድ ቅሬታ ይፈጥራል የሚል ትችት ይቀርብበታል፡፡
የአዲስ አበባን ጉዳይ ከዚህ አንፃር ስንመለከተው ደግሞ ከላይ በጠቀስነው የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 49 (5) ላይ ‹የኦሮሚያ ክልል […] አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃል ላይ የሚገኝ በመሆኑ […] ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል› ይላል፡፡ ይሄም ማለት በሌላ አነጋገር አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የምትገኝ አንድ ከተማ ነች እንደማለት ነው፡፡
2.4. ቻርተርድ ከተማ (Chartered City) ናት
አዲስ አበባ ሶስቱንም የፌደራል ዋና ከተማ ባህሪ አዳለ በመያዝ በየትኛው ሕጋዊ ‹ሰታተስ› ላይ እንዳለች ግራ የምታጋባ ከተማ ነች፡፡ ከዚህ በባሰ ደግሞ ከተማዋ በራሴ ቻርተር የምትተዳደር ከተማ (Chartered City) ነኝ በማለት ራሷን በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ቻርተር 87/1989 አቋቁማለች (ቻርተሩ በ1995 በአዋጅ ቁጥር 311/1995 እና በአዋጅ ቁጥር 361/1995 ሙሉ ለሙሉ ተሸሽሏል፡፡ እንዲሁም በ1996 በአዋጅ ቁጥር 408/1996 በከፊል ተሻሽሏል)፡፡ ይህ በዋናነት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የከተማ ድህነትን ለመቀነስ እንደስትራቴጅ እየተወሰደ ያለ የአወቃቀር አይነት አዲስ አበባ ለምን እንደመረጠችው ብዙም ግልፅ ባይሆንም፤ በሁሉም ቻርተሮች ላይ ዋነኛ ዓላማው ‹የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን እንዳለው […] በሕገ መንግስቱ በመደንገጉ› ምክንያት እንደሆነ ተገልፆ እናገኛለን፡፡ አዲስ አበባ ቻርተርድ ከተማ ነች ማለትም ከላይ 2.1 ላይ ለማመላከት የተሞከረውን የክልል ማዕረግ (status of state) የሚያጠናክር ሃሳብ ሆኖ የከተማዋን ስታተስ ለመወሰን ከላይ ያየናቸውን የዋና ከተማ ብያኔ ክርክር የበለጠ ያጦዘዋል፡፡
እንግዲህ አዲስ አበባ ራሷን የቻለች ክልል ናት፣ ተጠሪነቷ ለፌደራል መንግስቱ የሆነች የፌደራል ቀጠና ናት፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የምትገኝ አንድ ከተማ ናት እንዲሁም በራሷ የቆመች ቻርተርድ ከተማ ነች የሚሉ የራሳቸው አሳማኝ ምክንያት ያላቸው መከራከሪዎች ይቀርባሉ፡፡ ይህ ግልፅነት የጎደለው የከተማዋ ‹ስታተስም› አሁን ከተማዋን አስመልክቶ ለሚነሱ ውዝግቦች መነሻና መድረሻ ነው፡፡
3. ‹የአንተም ተው፣ አንችም ተይ ፌደራሊዝም› እና መዘዙ
[የኢትዮጵያ የሕገ መንግስት ኮሚሽን] ሰብሳቢ [አቶ ክፍሌ ወዳጆ] [የኮሚሽኑ] አባላት ተሳትፎና ኮሚሽን የሥራ ሒደት በተመለከተ አልፎ አልፎ አባላት በስብሰባ ላይ ያለመገኝት ሁኔታ በማሳየታቸው የስራ መጓተት እየተከሰተ መሆኑን፣ ከፓናሎች የሚጠበቁ ሪፖርቶች በተፈለገው ጊዜ ሊቀርቡ እንዳልቻሉና ይኸውም የፓናል አባላቶች በስብሰባ አለመገኘት ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ገልፀው፣ ለመጪው ጊዜ በእያንዳንዱ ስብሰባ በሚነሱ ጉዳዮች ላይ በበቂ በመዘጋጀት ለውሳኔ የሚያበቃ ሰፈ ግንዛቤ በመጨበጥ መገኘት ከእያንዳንዱ አባል እንደሚጠበቅ አሳስበው፣ […] የአዲስ አበባን የመናገሻ ከተማነት ደረጃ (status) እና ወደፊት አከላለስ ሊኖራት የሚችለውን ቦታ አስመልክቶ በሚዘጋጀው የመወያያ ሰነድ (working paper) ውስጥ እንዴት ማስቀመጥ እንደሚቻል ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡››
ይህ ሐሳብ የተገለፀው የአሁኑን የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ለማርቀቅ የተቋቋመው የሕገ መንግስት ኮሚሽን ሰብሳቢ በነበሩት አቶ ክፍሌ ወዳጆ ጳጉሜ 1- 1985 በኮሚሽኑ 39ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው፡፡ እንደ ሰብሳቢው ሐሳብ ከሆነ ሕገ መንግስትን ያህል ሰነድ ለማርቀቅ የተዋቀረው ኮሚሽን አባላት በኮሚሽኑ ስብሰባ ላይ አለመገኘታቸው አሳስቧቸውና የአዲስ አበባን ደረጃ (status) ገና ሳይወስኑ እስከ አሁን መቆየታቸው አሳስቧቸው ነው፡፡ ሰብሳቢው አቶ ክፍሌ ይሄን ቢሉም ይሄን ማስጠንቀቂያ በተናገሩበት እለት እንኳን ከ27 የኮሚሽኑ አባላት መካከል ስምንት የሚሆኑት አልተገኙም ነበር፡፡ አዲስ አበባን አስመልክቶ የቀረቡት ጉዳዮች በሕገ መንግስታዊው ጉባኤ የተወሰነ ውይይት ቢደረግበትም፣ በኮሚሽን ደረጃ ብዙም ውይይት እንዳልተደረገበት በጊዜው የኮሚሽኑ አባል የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ይገልፃሉ፡፡ እንግዲህ ያ በቸልተኝነት የታለፈ ጉዳይ ነው አንዱ የዛሬው ችግር መነሻ፡፡ አዲስ አበባ የክልልም፣ የፌደራል ግዛትም እንዲሁም የአንድ ክልል ከተማ መልክ ይዛ ከሶስቱ አንዱን መሆን አለመቻሏ በጊዜው ሲሟገቱ የነበሩ ሁሉንም አካላት ለማስደሰት በሚል የታለፈ ጉዳይ ይመስላል፡፡
የተለያዩ ምሁራን አዲስ አበባን አስመልክቶ የተለያዩ ጥያቄዎችን እያነሱ ሕገ መንግስቱ መመለስ አለመቻሉን ሊያሳዩን ይሞክራሉ፡፡ መሰረታዊዎቹን ጥያቄዎች እዚህ ላይ ማንሳት ተገቢ ስለሚሆን አንስተን እንመልከታቸው፡፡
1. የአሜሪካ ዋና ከተማ የሆነችው ዋሽንግተን ዲሲ በተቋቋመችበት ወቅት መሬት ከሜሪላንድና ከቨርጅኒያ ስቴቶች ተቆርጦ ተሰጥቷት ነው የተቋቋመችው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ቨርጅኒያ መሬቴን መልሽልኝ በማለት መሬቷን በሕዝበ ውሳኔ መሬት የማስመለስ ሒደት (retrocession) መሰረት አስመልሳለች፡፡ ሜሪላንድም እስከ አሁን አልጠየቀችም እንጂ ብትጠይቅ ልታገኝ እንደምትችል የሕገ መንግስት ምሁራን ይገልፃሉ፡፡ አዲስ አበባ የምትገኝው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንደሆነ ሕገ መንግስቱ በግልፅ ይደነግጋል፡፡ ታዲያ ኦሮሚያ ‹መሬቴን ራሴ አስተዳድራለሁ› ብትል በምን አግባብ ነው መልስ የሚሰጠው?
2. አሁንም እዛው ዋሽንግተን ዲሲ እንቆይና ባራክ ኦባማን ጨምሮ ብዙ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ዋሽንግተን ዲሲ ራሷን የቻለች ሃምሳ አንደኛ የአሜሪካ ‹ስቴት› ብትሆን ፍላጎት እንዳላቸው (ከመራጭነት መብት አንፃር) ይገልፃሉ፡፡ ሐሳቡ ወደ ፊት ሊተገበር የሚችል ጉዳይ እንደሆነም ምሁራን እያስረዱ ይገኛሉ፡፡ አዲስ አበባ ራሴን ችዬ ክልል ልሁን ብትል በምን አግባብ ነው የሚስተናገደው ለሚለው ጥያቄ የራስን ክልል የመመስረት መብት የሚሰጠው የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 47 (2) መብቱን የሚሰጠው ‹ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› ሲሆን አዲስ አበባ በምን ጎራ ላይ እንደምታርፍ ምንም የተገለፀ ነገር የለም፡፡
3. አዲስ አበባ አሁን ባላት ቁመና ቻርተርድ ከተማ እንደሆነች ከላይ ለማየት ሞክረናል፡፡ ቻርተርድ ከተሞችን (Chartered Cities) ከሌሎች ከተሞች (General Law Cities) የሚለያቸው ዋነኛው ጉዳይ ደግሞ የፌደራልንም ሆነ የክልል መንግስታትን ጣልቃ ገብነትን የሚያስወግድ አሰራር መተግበራቸው ነው፡፡ ታዲያ አዲስ አበባ ቻርተርድ ከተማ እንደመሆኗ ‹የፌደራል መንግስቱን ጣልቃ ገብነት አልፈልግም› ብትል ሕገ መንግስቱ ምን መልስ ይሰጣል?
እነዚህን ሕልዮታዊ ጉዳዮች ያነሳነው የአሁኑ የኢትዮጵያ ፌደሬሽን በተግባር የሌለ ብቻ ሳይሆን በአወቃቀር ደረጃም የማይመልሳቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች መኖራቸውን ለማመላከት ነው እንጂ፤ ‹ጠያቂም መላሽም› እንደሌለ መረዳት ከባድ ሆኖ አይደለም፡፡
አዲስ አበባም ፖለቲካዊ፣ ሕጋዊ እንዲሁም መዋቅራዊ ችግሮቿ ሰንገው በያዟት በዚህ ወቅት ነው ‹የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን [የተቀናጀ] የጋራ ልማት ፕላን› ተብሎ የተሰየመው የሃያ አምስት አመታት ዕቅድ ብቅ ያለው፡፡
4. ‹[የተቀናጀ] የጋራ ልማት ፕላን› እና አዲስ አበባ
ስድስተኛው የዓለም የከተሞች ፎረም በጣሊያን ኔፕልስ ከሴፕቴምበር 02 እስከ 07 – 2012 ነበር የተካሔደው፡፡ ፎረሙ በተባበሩት መንግስታት ከተቋቋመበት ከ2002 ጀምሮ ባሉት አስር ዓመታት ውስት ለስድስተኛ ጊዜ ስብሰባ ማድረጉ ነበር፡፡ ከመላው ዓለም ከመጡ የተለያዩ ሀገር ተወካዮች አማካኝነት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተወያየ ሲሆን የፎረሙ ዋነኛ አጀንዳም ‹Urban Future› የሚል ሲሆን በዋናነትም አራት መሰረታዊ ጉዳዮችን እንደመወያያ ይዞ ተካሂዷል፡፡ ከነዚህ አራት የውይይት ርዕሶች መካከል ቀዳሚው ‹Urban Planning: Institutions and Regulations› የሚል ነበር፡፡ በውይይቶቹ መጨረሻ ‹የዓለም የከተሞች ማንፌስቶን› ጨምሮ የተለያዩ የውይይቱ ውጤቶች ይፋ የተደረጉ ሲሆን፤ ከነዚህ የውይይቱ ውጤቶች መካከልም የዓለም ከተሞች የተቀናጀ የልማት ዕቅድን (Integrated Development Plan – IDP) ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚመክረው (recommendation) ይገኝበታል፡፡ ይህ በተባበሩት መንግስታት ደረጃ የቀረበው በ2012 ቢሆንም ከዛ በፊት በ2007 ‘Leipzig Charter on Sustainable European Cities’ የአውሮፓ ሀገሮች ይሄን የተቀናጀ አካሄድ በከተሞቻቸው ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ተስማምተው ነበር፡፡
ከዚህ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገሮች የተቀናጀውን አካሄድ ተግባራዊ ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ የደቡብ አፍሪካዋ ኬፕ ታውን (ከ2012 -2017) እና የኬኒያዋ ናይሮቢ (ከ2014 -2019) በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ደቡብ አፍሪካ እንዲያውም በሃገሪቱ ላሉ ከተሞች አጠቃላይ የተቀናጀ የልማት ዕቅድን ተግባራዊ እንዲያደርጉ መመሪያ እስከማውጣት ደርሳለች፡፡
4.1. የተቀናጀ የልማት ዕቅድ (Integrated Development Plan – IDP) ምን ለማለት ነው?
አንድ አይነት እና ወጥ የሆነ መልስ ማግኝት ባይቻልም የተለያዩ ከተሞች ከሰጡት የተለያየ ትርጉም አንፃር ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን ማግኘት እንችላለን፡፡ 1. ሁሉም መሰረተ ልማት ላይ የሚሰሩ አካላት (የትራንስፖርት፣ የመብራት፣ የቤቶች ወዘተ) ተቀናጅተው ለተመሳሳይ ግብ እንዲተጉ ማድረግና 2. እቅዱን ያወጣው አካል ከእቅዱ ባለቤት (የከተማው ነዋሪ) ጋር አሳታፊ (participatory) በሆነ መንገድ በየጊዜው በመወያየት ተቀናጅቶ የሚሰራበት አካሄድ ነው፡፡ እንደ ናይሮቢ ያሉ ከተሞች በተቀናጀ የልማት ዕቅዳቸው የመሰረተ ልማት አገልግሎት (በተለይም ትራንስፖርት) በዙሪያው ካሉ አካባቢዎች (surroundings) ጋርም ለማቀናጀት ሙከራ አድርገዋል፡፡
በዚህ ጊዜ አዲስ አበባም በ1996 አዘጋጅታው የነበረው የከተማ ልማት እቅድ (ማስተር ፕላን) የትግበራ ጊዜው እያለቀ ነበርና የራሷን አዲስ ዕቅድ ለማዘጋጀት ቢሮ ከፍታ እንቅስቃሴ የጀመረችበት ጊዜ ነበር፡፡ መጀመር ብቻም ሳይሆን ስድስተኛው የዓለም የከተሞች ፎረም በተካሔደበት በመስከረም 2005 ለእቅዱ የሚያስፈልገውን መረጃ ለቀማ እንዳጠናቀቀች ይፋ አድርጋ እቅዱንም በጥቂት ወራት ውስጥ አጠናቅቄ ይፋ አደርጋለሁ ብላ ነበር፡፡ እንደተባለው እቅዱ በጥቂት ወራት ውስጥ እንደተጠናቀቀ ውስጥ ለውስጥ የተነገረ ሲሆን የመጀመሪያውንም ተቃውሞ በግንቦት 2005 ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በወጣ መግለጫ አስተናግዳ ከዛ በኋላ የሆነውና እየሆነ ያለው ጉዳይ ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ እዚህ ላይ ትክክለኛውን አከራካሪ ጉዳይ ለመለየት እንችል ዘንድ የእቅዱን መሰረት እና ይዘት ማየት ተገቢ ጉዳይ ነው፡፡
4.2. ‹ኢንደስትሪያላይዜሽን› ዘመነኛው ካርድ
‹‹የህዝባችን ኑሮ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚደርሰው አገራችን በኢንዱስትሪ የበለፀገች አገር ስትሆን ነው፡፡ አገራችን በአለም አቀፋዊው ኢኮኖሚያዊ ትብብር ውስጥ የሚኖራት ድርሻና ከዚሁ የምታገኝው ጥቅም በከፍተኛ ደረጃ ሊያድግ የሚችለው በኢንዱስትሪ የበለፀገች ስትሆን ነው፡፡ በመሆኑም የኢኮኖሚ ልማት እንቅስቃሴያችን ግብ በኢንዱስትሪ የበለፀገች አገርን መፍጠር መሆን አለበት፡፡ ሌላው ቀርቶ የግብርናና የገጠር ልማት እንቅስቃሴያችን የመጨረሻው ግብ አገራችን በኢንዱስትሪ የበለፀገች እንድትሆን ማድረግ ነው፡፡››
ይህ ሀሳብ የተገለፀው በ1994 በወጣው የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጅ ላይ ነው፡፡ ስትራቴጂው የግሉን ባለሃብት የኢንደስትሪያላይዜሽኑ መሰረት ማድረግና ግብርናው ኢንደስትሪውን እንዲመራው ማስቻል (Agriculture Development Led Industrialization – ADLI ) መሰረታዊ ጉዳይ እንደሆነ አስቀምጦ ያልፋል፡፡ ከዚህ ስትራተጅ የተከተሉት የእድገትና እና ትራንስፎርሜሽን እቅዶችም ዓላማቸው ግብርና የሚመራውን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ ኢንደስትሪ መር ማሸጋገርን (transformation) ዓላማ አድረገው የተቀረፁ ናቸው፡፡ ቁጥሮች እንደሚነግሩን ግን ኢሕአዴግ በኢንደስትሪው መስክ አልተሳካለትም፡፡ ኢንደስትሪው ያለፉት 50 አመታትን ተመሳሳይ መንገድ ይዞ የሚያዘግም ነው፡፡ ኢንደስትሪውን ይመሩታል የተባሉት ግብርና እና የግል ባለሃብቱም ከፕሮፓጋንዳ ባለፈ ብዙም በአካባቢው አይታዩም፡፡
ኢንደስትሪው የትም እንዳልደረሰ እና ‹ትራንስፎርም› የሆነ ብዙም ነገር እንደሌለ የተረዳው ኢሕአዴግ በድንጋጤ (frustration) የደቡብ ምስራቅ እስያ ተሞክሮ የሆነውን መንግስት መር (statist) ኢንደስትሪያላይዜሽን ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት ኢንደስትሪውን ይመራዋል የተባለው ገበያና የግል ባለሃብትም ከአመራርነት ወርደው ቦታቸውን ለመንግስት አስረክበው ይገኛሉ፡፡
እንግዲህ በዚህ የኢሕአዴግ የኢንደስትሪያላይዜሽን ድንጋጤ ወቅት ነው ‹የአዲስ አበባና ዙሪያዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ [የተቀናጀ] የልማት ፕላንም› የመጣው፡፡ የፕላኑ ዋነኛ ግብ ‹ሀገሪቱ የሰነቀችውን የኢንደስትሪ ሽግግር ዕውን መሆን ወሳኝ አስተዋፅኦ የሚያደርግ የኢንዱስትሪ ልማት ማስተናገድ [የሚችል ክልል መፍጠር]› እንደሆነ በእቅዱ መግቢያ ላይ ተገልፆል፡፡ (ክልል የተባለው ምን እንደሆነ ወደታች የምናው ጉዳይ ነው)፡፡ በእቅዱ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ‹‹ክልሉ የሀገሪቱን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በአጠቃላይ የዕቅዱ ዋና አካል የሆነውን የኢንደስትሪ ሽግግር በተለይም እውን በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወት ይጠበቅበታል››፣ ‹‹ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ››፣ ‹‹በ2030 በምስራቅ አፍሪካ ተወዳደሪ የሆነና በኢኮኖሚ ውስጥ መሪ ሚና የሚጫወት ማዕከል መፍጠር››፣ ‹‹የከተማዋን እና የዙሪያ ኦሮሚያ አካባቢን በጋራ በአፍሪካ ቀንድ ቀዳሚ የኢንዱስትሪ ክልል ማድረግ›› ወዘተ የሚሉ የዕቅዱ ዋነኛ ትኩረት ‹ኢንደስትሪያላይዜሽን› እንደሆነ የሚያመላክቱ ጉዳዮችን እናያለን፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘ ወዲህ የአሁኑን ጨምሮ ለአዲስ አበባ ከተማ የተዘጋጁትን እቅዶች ስንመለከት ‹የዘመኑ መንፈስ› እንደሚመራቸው እናያለን፡፡ የመጀመሪያውና በ1986 የተዘጋጀው እቅድ ዋነኛ ትኩረቱ ‹ሰላማዊ ከተማ› መገንባት እንደነበር የተገለፀ ሲሆን፤ በ1996 የፀደቀው የከተማዋ የልማት እቅድ ደግሞ በጊዜው የኢሕአዴግ ዋነኛ ማጠንጠኛ የነበረውን ‹ኢንቨስትመንት› መሰረት ያደረገ ሲሆን በጊዜው የከተማዋን መሪ ፕላን ለማጽደቅ በከተማዋ አዲስ ነጋሪት ጋዜጣ ላይ በወጣው አዋጅ ቁጥር 17/1996 ላይም እንደተገለፀው ‹‹[…] ኢንቨስትመንትን በተሳለጠና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማካሔድ [ማስቻል]…›› እንደሆነ ተገልፆ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ‹የዘመኑ መንፈስ› ኢንደስትሪያላይዜሽን ነውና እቅዱ ዋነኛ ትኩረቱን ኢንደስትሪ ላይ ማድረጉ የሚጠበቅና የሚገርም ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከተማዋ የምስራቅ አፍሪካ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለመሆን ኢንደስትሪ የምትገነባበት በቂ ቦታ የላትምና አወዛጋቢውን መስፋፋት ለማድረግ ተነሳች ማለት እንችላለን፡፡ ይሄ እንዴት ሆነ?
4.3. መሪ እቅድ (Master Plan) ወይስ አዲስ ክልል (New State)?
ሰኞ ግንቦት 18፣ 2000 በጊዜው የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የነበሩት በአቶ መኩሪያ ሀይሌ እና ከአዲስ አበባ አስራ ሰባት እህት ከተሞች አንዷ በሆነችው የፈረንሳዩ፣ የሊዮን ከተማ ምክትል ከንቲባ Monsier Hubert Julien-Laferriere መካከል አንድ የትብብር ሰነድ ተፈረመ፡፡ የትብብር ሰነዱ በሁለቱ ከተሞች መካከል የተደረገው የአምስት ቀናት ውይይት ውጤት ነበር፡፡ ለውይይቱ የመነሻ ሃሳብ ያቀረበው የፌደራል የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት በአዋጅ ቁጥር 450/1997 ከተሰጡት ስልጣኖች አንዱን በመጠቀም ሊዮን ከተማ አዲስ አበባን ልትረዳ የምትችልባቸው ሶስት አጀንዳዎችን አቀረበ፡፡ እነዚህም ሶስት አጀንዳዎች፡
1. የአዲስ አበባ ከተማን መሪ እቅድ (Master Plan) የመከለስ ስራ፣
2. በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ መካከል በጋራ ለመፍጠር ስለታሰበው ክልላዊ እቅድ (Regional Planning) እና፣
3. ስለ አዲስ አበባ ከተማ የውስጥ የልማት ስራ (Local Development Plan – LDP) ናቸው፡፡
በውይይቱ ማጠናቀቂያም በሶስቱ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ በመደረሱ የሁለቱ ከተሞች አቻ ባለስልጣናት የትብብር ሰነዱን ተስማምተው ፈረሙ፡፡ የመሪ እቅዱ እና የውስጥ የልማት ስራው ከዚህ በፊት የተለመዱ ጉዳዮች በመሆናቸው ብዙም ግርታን የሚፈጥሩ አልነበሩም፡፡ ነገር ግን በኦሮሚያና በአዲስ አበባ መካከል ሊፈጠር የታሰበው ክልላዊ የልማት እቅድ የተለመደ ስላልነበር አፈፃፀሙን ለማየት የሚያጓጓ ነበር፡፡ የዚህ ክልላዊ እቅድ መነሻ ግን አሁንም ወደኋላ ወደ 1996 ይወስደናል፡፡ በ1996 የወጣው የአዲስ ነጋሪቱ ‹የአዲስ አበባ ከተማ መሪ ፕላን አዘገጃጀትና አወጣጥ› አዋጅ ቁጥር 17/1996 በአንቀፅ 8 (2) ላይ ‹የአዲስ አበባ መዋቅራዊ ፕላን ከመዘጋጀቱ በፊት [ከኦሮሚያ ክልል ጋር] በፈቃደኝነት በጋራ ስምምነት ላይ የተመሰረተ የአዲስ አበባና አካባቢዎች ፕላን እንዲዘጋጅ አስተዳደሩ ሁኔታዎችን ያመቻቻል› በማለት ክልላዊ እቅድ መታቀድ ከጀመረ ቆየት ያለ ጊዜ እንዳስቆጠረ ያመላክተናል፡፡
አሁን መንግስት ያዘጋጀው የተቀናጀ የጋራ የልማት እቅድ ሰነድም (የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊ እዚህ ላይ ያገኘው ሰነድ) እነዚህን የኋላ ታሪክ በመያዝ ክልላዊ እቅድን (Regional Planning) ከመሪ እቅድ (Master Plan) በመቀየጥ የተዘጋጀ ነው፡፡ ያለውን የፌደራል ስርዓት አይተን ትግበራው ምን ሊመስል ነው ብለን ማሰብ የሚከብደን አይነት እቅድም ነው፡፡ የእቅዱ ስያሜ እንኳን መሪ እቅድ (Master Plan) ሳይሆን ክልላዊ እቅድ (Regional Plan) ነው፡፡ ግቡም አዲስ አበባን በ 100 ኪሎ ሜትር ሬዲየስ የሚከብ ሰፊ ክልልን ማልማት ነው፡፡ 36 ከተሞችን እንደሚያካትትም ተጠቅሷል፡፡ ከአዲስ አበባ ሌላ በስም በእቅዱ ላይ ተጠቅሰው የምናገኛቸው ከተሞችም ዱከም፣ ገላን፣ ሰበታ፣ አዋሽ፣ ለገዳዲ፣ ለገጣፎ (ሁሉም በኦሮሚያ ክልል፣ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ከተሞችን ማለት ነው) ናቸው፡፡ በልማት እቅዱ ውስጥ የተካተተው አካባቢም 85 በመቶው ገጠር እንዲሁም 15 በመቶው ደግሞ የከተማ አካባቢ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ እንዲሁም በአምስቱ ኦሮሚያ ክልል፣ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን አምስት ከተሞችን ውስጥ በ25 ዓመታት ውስጥ ከ30 ሺህ እስከ 40 ሺህ ነዋሪዎችን ማስፈርን በእቅድነት ይዟል፡፡ ይሄም ዓላማ ያደረገው ‹የክልሉን ነዋሪ ከአስከፊ ድህነት ማላቀቅ› ነው የሚል ሲሆን፤ እዚህ ላይ የየትኛውን ክልል ነዋሪ ማለታችን ተገቢ ነው፡፡
እነዚህን ጉዳዮች ስንመለከትም እቅዱ በዋናነት ክልላዊ እቅድ እንጂ የከተማ መሪ እቅድ እንዳልሆነ ለመረዳት ብዙም አያዳግተንም፡፡ ሰፊ የገጠር አካባቢን (85 በመቶው የእቅዱ አካባቢ) አካልሎ ግቡን ኢንደስትሪያላይዜሽን ማድረጉንም ስናይ ‹ግዙፏ አዲስ አበባ በተግባር ደረጃ (de facto) የራሷ የሆነ ክልል (አስረኛዋ የኢትዮጵያ ክልል) ለመመስረት ጥረት እያደረገች ነው እንዴ?› ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡ ከላይ የጠቀስነው አደናጋሪው በፌደራል ስርዓቱ ውስጥ የአዲስ አበባ ‹ስታተስ› ጉዳይም እዚህ ላይ መሰረታዊው የጥያቄ ነጥብ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
4.4. ኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ እና ‹እቅዱ›
ከላይ በተራ ቁጥር 3 ላይ ሕገ መንግስቱ በተረቀቀበት ወቅት የነበረው የአዲስ አበባን ‹ስታተስ› ግልፅ ያለማድረግ ችግርና አዲስ አበባ ከምትገኝበት ኦሮሚያ ክልል ጋር የሚኖራትን ግንኙነት ግልፅ ያለማድረግ ችግር ሕልዮታዊ ጥያቄዎችን ለማንሳት ሙከራ አድርገናል፡፡ እዚህ ላይ ደግሞ በተግባር እያጋጠሙ ያሉ ቸግሮችን በማንሳት የወደፊቱን ሁኔታ ለማየት እንሞክር፡፡
አብዛኛው የአዲስ አበባ ከተማና የኦሮሚያ ክልል ውዝግቦች የሚነሱት ከድንበርና ከሉዓላዊነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ አዲስ አበባ ያለ ቅጥ እየተስፋፋች ነው፣ የኦሮሞን ባህልና ቋንቋ እያጠፋች ነው፣ በሕገ መንግስቱ ለኦሮሚያ ክልል የተሰጣት ልዩ ጥቅም እስከ አሁን በሕግ ባለመወሰኑ ጉዳዩን አወሳስቦታል ወዘተ የሚሉ ትችቶች እየቀረቡ እስከ አሁን ቀጥሏል፡፡
4.4.1. ድንበር
የአዲስ አበባ ስፋት ባለፉት ሃምሳ አመታት ከእጥፍ በላይ አድጓል፡፡ በ1953 በሔክታር 21,800 የነበረው የአዲስ አበባ የቆዳ ስፋት በ1986 ወደ 53,014 ሔክታር ሰፍቶ፤ አሁን ያለውን የ54,000 ሔክታር ስፋት ደግሞ በ1996ቱን በከተማዋ መሪ ዕቅድ የተሰፈረላት ነው፡፡ በሀምሳ ዓመታት ውስጥ ከተማዋ በእጥፍ ያደገች ቢሆንም በአለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ግን አሁን ካላት ስፋት ብዙም የተለየ ነገር አላሳየችም፡፡ የከተማዋ ከኦሮሚያ ጋር ያላት የድንበር ውዝግብ ዋነኛ መነሻ የሆነው የድንበሩ አለመካለል (demarcation ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የተለያዩ ውዝግቦች በጊዜው እንደሚነሱ ይሰማል፡፡ ተሾመ ያሚ የተባሉ የሕግ ባለሙያም በጉዳዩ ላይ ባደረጉት ጥናት የኮልፌ-ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከቡራዩ ከተማ አስተዳደር ጋር እንዲሁም የንፋስ ስልክ-ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከሰበታ ከተማ አስተዳደር ጋር በቅርብ ጊዜያት ውስጥ የድንበር ይገባኛል ውዝግብ ውስጥ እንደገቡ ይገልፃሉ፡፡ እንዲሁም የገቢ ምንጭን አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልል የማዕድን ኤጀንሲ ቢሮ ከአዲስ አበባ አቻው ጋር የተወዛገበባቸው አካባቢዎች እንዳሉ አያይዘው ይገልፃሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ግን መንግስት ሕጋዊ መፍትሔ ከመስጠት እና የሕግ አፈታቱን ከማሳደግ ይልቅ ተለመደውን ፖለቲካዊ መፍትሔ እየሰጠ ችግሩ አሁንም በዘላቂነት ያልተፈታ ጉዳይ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡
አዲስ አበባ አሁን ካላት ቦታ ውጭ (54,000 ሔክታር ወይም 527 ኪሜ ስኩየር) መስፋት አትችልም ወይ? ለሚለው ጥያቄ ሕጋዊ መፍትሔ የሚሰጠን በ1996 የወጣው የአዲስ ነጋሪቱ ‹የአዲስ አበባ ከተማ መሪ ፕላን አዘገጃጀትና አወጣጥ› አዋጅ ቁጥር 17/1996 ሲሆን አዋጁም ‹‹[የአዲስ አበባ የ] መስፋፊያ አካባቢ [የሚባለው] በማስተር ኘላኑ የቦታ ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ ተከልሎ ባለ የአርሶ አደር ወረዳዎች ስር የሚገኝ የለማ እና ወደፊት የሚለማ መሬት የሚገኝበት አካባቢ ነው፡፡›› በማለት ከተማዋ አሁን ካላት ቦታ ውጭ እንደማትስፋፋ ይገልፃል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ያለው ግንኙነት አስመልክቶ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የመመስረቻ ቻርተር 87/1989ም ሆነ ይሄን ቻርተር ሙሉ ለሙሉ ያሻሻሉት አዋጅ ቁጥር 311/1995 እና በአዋጅ ቁጥር 361/1995 የድንበሩ ጉዳይ ‹ወደፊት በውይይት ይካለላል› ከማለት በስተቀር ያስቀመጡት ነገር የለም፡፡ በሌላ በኩል የአዲስ አበባ መለጠጥ ያሳሰበው እና ይሄም መገታት አለበት ብሎ ያሰበው የኦሮሚያ ክልል በ2000 የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን በሚል አዲስ ዞን የአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ክልልን ግንኙነት ለማሳለጥ በሚል ሰበብ አቋቁሟል፡፡ አሁን የቀረበው ‹የልማት እቅድ› ደግሞ የልዩ ዞኑን ከተሞች ሙሉ ለሙሉ በማስገባት ሌላ አዲስ መካረር ፈጥሯል፡፡
4.4.2. ቋንቋ
የአሜሪካዋ ቨርጂኒያ ስቴት ለዋና ከታማዋ ዋሽንግተን ዲሲ የሰጠሁት መሬት ይመለስልኝ በማለት መሬቷን በ1846 አስመልሳለች፡፡ በሌላ በኩል አሁን ያለችውና መሬት ከሜሪላንድ ‹ስቴት› ወስዳ የቆመችው ዋሽንግተን ዲሲ ‹ራሷን የቻለች ክልል ትሁን የሚለውም› ሃሳብ ብዙም ተቃውሞ አይቀርብበትም፡፡ ለዚህም ለስላሳ ግንኙነት ዋነኛው መሰረትም የዋሽንግተን እና የዙሪያዋ ያለው የባህልና ቋንቋ መመሳሰል ነው፡፡
በተቃራኒው አዲስ አበባ የምትናገረው ቋንቋ በዙሪያዋ ካለው ቋንቋ የተለየ ነው፡፡ አዲስ አበባ አማርኛን ታወራለች ዙሪያዋ ደግሞ ኦሮምኛን ይናገራል፡፡ የቋንቋ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባየ ይማም ‹አዲስ አበባ ለአማርኛ፣ አማርኛ ለአዲስ አበባ› ባሉት ፅሁፋቸው የአማርኛንና የአዲስ አበባን ግንኙነት ሲያስረዱ፡
ከአዲስ አበባ ከተማ ምሥረታ በኋላ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በየምክንያቱ ወደ ከተማዋ በመግባት በጉርብትና አብረው መኖርና መሥራት ጀመሩ፡፡ ይህም ሁኔታ ሕዝቦችን ከተለያየ ቋንቋ ተናጋሪነት ወደ አንድ የጋራ ቋንቋ ተጠቃሚነት አሸጋገረ:: ልሳነ ዋህድ የነበረው ብሄረሰብ ልሳነ ክልዔ እየሆነ መጣ። አማርኛ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ከተመኛውን ሁሉ የሚያገናኝ የጋራ ቋንቋ ሆነ፡፡
አዲስ አበባና አማርኛ፣ ለርስበርሳቸው ብሎም ለመላው ኢትዮጵያ የለውጥ ተምሳሌት ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ብሄረሰብ በቤቱም ሆነ በአደባባይ የሚናገረው የራሱን ቋንቋና አማርኛን ነው ለማለት ይቻላል፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ ግን ከዚህ ይለያል፡፡ በአደባባይ ሁሉም የሚናረው አማርኛን ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ መርካቶ የሚሰማው ቋንቋ ሌላ ሳይሆን አማርኛ ነው፡፡ አዲስ አበባ የሕብረ-ብሔራዊነት ተምሳሌት እንደሆነች ሁሉ፣ አማርኛም የዚሁ መግለጫ ነው፡፡ ከሁሉም ይወስዳል፣ መልሶ ለሁሉም ያሰራጫል፡፡ ሁሉንም ያገናኛል፣ ከሁሉም ቃል ይወስዳል፣ ለሁሉም ቃል ይሰጣል፡፡
በማለት ይገልፃሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት አዲስ አበባን ያለ አማርኛ ማሰብ በፍፁም የማይቻል ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በዙሪያዋ ያሉት የአዲስ አበባ ከባቢዎች ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም ‹ይህች እንደ አንድ ከተማ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያ ስልጣኔ ምልክት እየተደረገች የምትታይ ከተማ የምትናገረው ቋንቋ በዙሪያዋ ያለውን ኦሮምኛ ቋንቋ ያጨቁነዋል› የሚለው ሃሳብ የሚሰነዝሩ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ ክልላዊ የልማት እቅድ ቀርቧል፡፡ እቅዱም ከቋንቋ ጋር በተገናኝ ያለውን ተቃውሞና ውዝግብ የበለጠ አክርሮታል፡፡
4.4.3. የገበሬ መሬት ለከተሜ?
ከአዲስ አበባ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ሌላው እየቀረበ ያለው ጉዳይ አዲስ አበባ በሰፋች ቁጥር ገበሬዎችን እያፈናቀለች ቤት አልባ ታደርጋለች የሚለው ሲሆን፡፡ የተለያዩ ጥናቶችም ይሄን ያመላክታሉ፡፡ ፈየራ አብዲ የተባሉ አጥኝ አዲስ አበባ ከምስረታዋ ጀምሮ አሁን ያለችበትን ስፋት ለሜድረስ በዓመት በአማካኝ 400 ሔክታር ያህል ስትሰፋ ነበር ይላሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ከተማዋ በሕግ አግባብ ልትሰፋ የምትችለው ከተማዋ በቻርተር ከተማነት በተቋቋመችበት አዋጅ ቁጥር 87/1989 ላይ የተገለፀውን ‹የአዲስ አበባ ከተማ የከተማውን ክልል እና በመስተዳደሩ ክልል ውስጥ የሚገኙትን ሃያ ሶስት የገጠር ቀበሌዎች ያጠቃልላል›› ተብሎ በተገለፀው አግባብ ወዳሉት ሃያ ሶስት የገጠር ቀበሌዎች ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 40 (4) ላይ ‹‹የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነፃ የማግኝትና ከመሬታቸው ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ ነው፡፡›› ተብሎ የተከበረውን የገበሬዎችን መብት ይጥሳል የሚሉ ብዙ ወገኖች አሉ፡፡ ነገር ግን በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 8 ላይ ‹‹መንግስት ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሁኖ ሲያገኝው ተመጣጣኝ የካሣ ክፍያ በቅድሚያ በመክፈል […] [መሬቱን] ሊወስደው ይችላል›› ተብሎ በመደንገጉ ይህ የገበሬዎች መብት ገደብ ያለው ነው የሚለው ሃሳብም እዚህ ላይ መሰረታዊ ነገር ነው፡፡
ነገር ግን አሁን እየቀረበ ያለው ‹የተቀናጀ የጋራ እቅድ› ዓላማው ኢንደስትሪያላይዜሽን እንደሆነ ያስቀመጠ ሲሆን 1.1 ሚሊዮን ሔክታርን ያቀፈና 17 የሚሆኑ ወረዳዎችን የያዘ እንደሆነ ተገልፆል፡፡ ይሄም እጅግ ብዙ የገጠር ቀበሌዎችን እንደሚያካትት ግልፅ ነው፡፡ ኢንደስትሪያላይዜሽንን መሰረት ያደረገ እቅድ በዚህ ያህል ቦታ ሲታቀድ ገበሬዎችን በገፍ አያፈናቅልም ብሎ ማሰብ ራስን ከማሞኘት ባለፈ ፋይዳ ያለው ነገር አይደለም፡፡ መፈናቀሉንም ‹ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሁኖ ስለተገን› ነው ብሎ ማሰብ የባሰ ሞኝነት ነው የሚሆነው፡፡
ሲጠቃለልም አዲስ አበባ በተሳሳተ የከተማ ልማት ፖሊሲ ሌሎች ከተሞች በሀገሪቱ ውስጥ የሉም እስኪባል ድረስ ያለልክ ገዝፋለች፡፡ በዚህም ምክንያት አዲስ አበባ ላይ የሚደረግ ማንኛውም እቅድ አካባቢያዊ እቅድ ከመሆን ይልቅ ሀገራዊ እቅድ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በመሃሉና በዳር ሀገሩ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ከመስራት ይልቅ አሁንም በፖሊሲ ደረጃ የአዲስ አበባን ግዙፍነት በበለጠ የማስቀጠል አካሔድ ነው አሁን እየተካሔደ ያለው፡፡ ይህ አካሔድ ደግሞ በፌደራል ስርዓት ሊኖር የሚገባው ግልፅ የሆነ ድንበር እና ‹ስታተስ› ካለመኖሩ ጀምሮ የተነሳ ሲሆን፤ በተግባርም ችግሮችን በፖለቲካዊ ውሳኔ አድበስብሶ የማለፍ ውጤት ሲጠራቀም ቆይቶ አሁን ላይ የደረሰ ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ የገዘፈ እቅድን (ያውም ‹መሪ እቅድ› ይሆን ‹ክልላዊ እቅድ› በግልፅ ያልተቀመጠ እቅድ) ከአንድ ከተማ ጋር አያይዞ ማቅረብም ለጉልበተኛው የከተማ ገዥ ልሒቅ ተጨማሪ ሃይል በመስጠት ገበሬውን ከራሱ መሬት ወደ ጭሰኝነት የሚገፋ ነው የሚሆነው፡፡ ላልተሳካ ኢንደስትሪያላይዜሽን መሰረታዊ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ የፌደራል ስርኣቱን በግዴለሽነት በመግፋትና በመሰለኝ ለማሳካት መሞከር ነገም ሌላ ችግር ነው የሚመዘው፡፡ ሕሩይ ሚናስን ከሩቅ ገነት ሁና በመግነጢሳዊ ሃይሏ ስባ ቤተኛ ያደረገችው አዲስ አበባስ እስከ መቼ ነው ሀገሪቱ በፖሊሲ ክሽፈት እየወደቀች ያለችውን የተለያየ ፈተና ለማለፍ መሳሪያ የምትሆነው? የፌደራል ስርዓቱስ እስከ መቼ ነው ሕጋዊነትን ሳይተዋወቅ የሚዘልቀው?

Articles

የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ተሳትፎ ድህረ ምልከታ

Published

on

Medal Winners

በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በወረቀት ደረጃ ከውድድሩ መጀመር በፊት ቡድኑ ባመዛኙ በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኙ ወጣት አትሌቶችን ስላካተተ ቢያንስ የለመድናቸውን ሁለት ወይም ሶስት የወርቅ ሜዳልያ ድሎች እንደማያሳጣን ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ ሆኖም የሜዳ ላይ ውጤቱ እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ኢትዮጵያ በውጤታማነቷ በምትታወቅበት የአትሌቲክስ ፉክክር በአንድ የወርቅ፣ አንድ የብር፣ እና ሁለት የነሐስ በድምሩ በአራት ሜዳልያዎች ከዓለም 14ኛ ከአፍሪካ 3ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች፡፡ ይህም ሁሌም ለአፍሪካ የበላይነት ከምንፎካከራት ኬንያ ጋር ያለን ልዩነት ይበልጥ እንዲሰፋ አድጎታል፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ሌላኛዋ የምስራቅ አፍሪካ ተቀናቃኛችን እየሆነች ከመጣችው ኡጋንዳም አንሰን እንድንገኝ አድርጎናል፡፡ የቶኪዮ ኦሊምፒክ በአትሌቲክሱ ከ1992ቱ የባርሴሎና ኦሊምፒክ ወዲህ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሜዳልያ ስኬት ያስመዘገበችበትም ሆኖ አልፏል፡፡

አሉታዊ ጎኖች
ቶኪዮ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤታማነት ፈር ቀዳጅ የሆነው ታላቁ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ በ1964 ዓ.ም. በተከታታይ ሁለተኛ የኦሊምፒክ ማራቶን ድሉን የተቀዳጀባት ከተማ ናት፡፡ እናም በቶኪዮ ከተማ በተከናወነው የኦሊምፒክ ውድድር የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የሱን ክብር የሚያጎሉባቸውን ነገሮች ያደርጋሉ ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ የሆኑት ነገሮች ግን በተለይ በቡድኑ አስተዳዳሪዎች በኩል ፍፁም ኃላፊነት የጎደለውና ከጠበቅኩት በተቃራኒው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከአትሌቶች ምርጫ አንስቶ በቡድኑ የዝግጅት ወቅት በተካረረ ውዝግብ ውስጥ ነበር የከረሙት፡፡ የኦሊምፒክ ቡድኑን የማዘጋጀት እና የመምራት የጋራ ኃላፊነት የነበረባቸው ሁለቱ አካላት ይባስ ብለው ውዝግቡን ቶኪዮ ድረስ ይዘውት ሄደዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ሁለቱን አካላት በማቀራረብ በትልቁ ውድድር ላይ ያለንን ተሳትፎ እንከን አልባ ማድግ የሚጠበቅባቸውም ተመልካች ከመሆን የዘለለ ሚና አልነበራቸውም። የውዝግቡ አሉታዊ ትሩፋት በአትሌቶች ስነልቦና እና በአጠቃላይ የቡድኑ ውጤት ላይ የበኩሉን ተፅዕኖ ሳያሳርፍ እንዳላለፈ አያጠራጥርም፡፡

እንደ አለመታደል ሆኖ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያን ልዑካን የመምራት ትልቁ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ኃላፊነት የጎደላቸው ነበሩ። የስፖርቱ አስተዳደሪዎች ትላልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በመጡ ቁጥር በአትሌቶች ምርጫ ዙሪያ የነበረውን ውዝግብ እንዲያቆሙልን እመኝ ነበር። ጭራሽ እራሳቸው ችግር ፈጣሪ ሆነው መገኘታቸው አስደንጋጭ እና አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በመሮጫ መም ወይም በጎዳና ላይ በሚደረጉ ውድድሮች መሸነፍን በስፖርቱ ውስጥ ማሸነፍ እና መሸነፍ ያሉ የነበሩ እና ወደፊትም የሚኖሩ ነገሮች ስለሆኑ በፀጋ መቀበል ይቻላል፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑ የስነልቦና ጥንካሬን ሊፈጥሩላቸው የሚገቡ ኃላፊዎች የእርስ በርስ ሽኩቻ ተቃራኒውን አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳርፍ ማየት ግን ፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ ለነገሩ ከስፖርቱ እድገት ይልቅ የፖለቲካ ግዴታቸው የሚያስጨንቃቸው የስፖርት አመራሮች በበዙባት ሀገር ስፖርቱ እንዲህ የማንም መጫወቻ ሲሆን ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡  

የስፖርት አመራሮች ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ሆነው ትኩረታቸውን ስፖርቱን በማስፋፋቱ እና ማሳደጉ ላይ አድርገው የሚሰሩ ስለስፖርቱም በቂ እውቀት እና ፍቅሩ ያላቸው ቢሆኑ መልካም ነው፡፡ ለቦታው በሚመጥን እና ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት በሚችል የስፖርት አመራር የሚመራ የስፖርት ተቋምን መገንባት በተመሳሳይ ሰዓት የሀገር ግንባታን የሚደግፉ ሶስት ነገሮችን ስኬታማ ያደርጋል፡፡ በስፖርት ጤናውን የሚጠብቅ ማሕበረሰብ በመፍጠር በጤናው ሴክተር ላይ የሚኖረውን ጫና ይቀንሳል፣ በሀገር ገፅታ ግንባታ እና በኢኮኖሚው ዕድገት ላይም የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ በቶኪዮ ላይ የተመለከትናቸው የሀገርን ክብር ዝቅ ያደረጉ ግዴለሽነቶች ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊታዩና አጥፊዎቹ ሊጠየቁበት ይገባል፡፡ በመጪዎቹ ዓመታት በሚጠብቁን ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይም የቶኪዮ ኦሊምፒኩን አይነት ሀፍረት እንዳይገጥመን ከወዲሁ ለችግሮቹ መፍትሔ መፈለግ አለበት፡፡

ባለፉት ዓመታት ኦሊምፒክ በመጣ ቁጥር በልዑካን ቡድኑ ውስጥ እየተካተቱ በሕዝብ ገንዘብ የሚዝናኑት የኦሊምፒክ ቱሪስቶች ጉዳይ ዘንድሮም ያልተቀረፈ ችግር ሆኖ ተስተውሏል፡፡ ከሌላው ግዜ በተለየ መልኩ ተጠባባቂ አትሌቶችን ይዞ መጓዝ ይጠይቅ በነበረው ውድድር ላይ አትሌቶቹን ትቶ ምንም የማይሰሩ ሰዎችን ይዞ መሄድ ትልቅ ቀልድ ነው፡፡  

ከሜዳ ውጭ የነበረው ውዝግብ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል የነበረ መሆኑ በሜዳ ላይ የነበሩብንን ድክመቶች ሊያስረሳንም አይገባም፡፡ ስድስት የጎዳና ላይ ተወዳደሪዎቻችን እና አንድ የመም ተወዳዳሪ ውድድራቸውን ማቋረጣቸው በቶኪዮ ከታዩት ደካማ ጎኖቻችን መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ ችግሩ በዚህ ምክንያት ነው የተከሰተው ብሎ ለይቶ ለመናገር ባይቻልም ብዙ ግዜ ሲፈትነን ለሚስተዋለው የሞቃታማ ቦታ ውድድር የምናደርጋቸው ዝግጅቶችን መለስ ብሎ መመልከትን የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ የተጎዳች አትሌትን ወደውድድር እንድትገባ ማድረግ እና በሁለት ደቂቃ ውስጥ ለማቋረጥ መገደዷም የአትሌቶች የጤና ክትትል ላይ ክፍተት እንዳለ የጠቆመን ክስተት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ወደውድድር ስፍራው ካቀናበት ግዜ ጀምሮ በቶኪዮ ምንም አይነት ቡድኑን የተመለከቱ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ወይም ፕሬስ ሪሊዞች አልነበሩም፡፡ ይህም እንደተለመደው የሕብረተሰቡን እና የመገናኛ ብዙሀንን ስለቡድኑ ቀጥተኛ መረጃ የማግኘት መብት የገደበ ነበር፡፡ ጋዜጠኞችም ሚዛናዊ ሆኖ ከመዘገብ ይልቅ ጎራ ለይተው ቃላት መወራወራቸው የህዝብን ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት የነፈገ ነው፡፡ 

አዎንታዊ ጎኖች
ሰለሞን ባረጋ በወንዶች 10,000 ሜትር ወርቅ፣ ለሜቻ ግርማ በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ብር፣ ጉዳፍ ፀጋዬ በሴቶች 5000 ሜትር ነሐስ፣ እና ለተሰንበት ግደይ በሴቶች 10,000 ሜትር ነሐስ ማስመዝገብ መቻላቸው የሚደነቅ ስኬት ነው፡፡

የመጪው ትውልድ አካል የሆኑት ተስፈኞቹ መቅደስ አበበ፣ ፍሬወይኒ ሀይሉ፣ በሪሁ አረጋዊ እና ጌትነት ዋለን ጨምሮ አምስት አትሌቶች ለሜዳሊያ የቀረበ የአራተኛነት ደረጃን ይዘው ማጠናቀቅ መቻላቸውም መልካም ነው፡፡ በተለይ ወጣቶቹ ያስመዘገቡት ውጤት በመጪዎቹ ዓመታት ተገቢውን ድጋፍ ካገኙ የምንጓጓለትን ድል ሊያስገኙልን እንደሚችሉ ያመላከተን ነው፡፡

የሀብታም አለሙ በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በሴቶች 800 ሜትር ለመጀመሪያ ግዜ ለፍፃሜ ተወዳዳሪነት መብቃት ምንም እንኳ በፍፃሜው የሜዳልያ ድል ባይቀናትም በአዎንታዊ ጎን ሊጠቀስ የሚችል ስኬት ነው፡፡

ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃን ይዘው ላጠናቀቁ አትሌቶች በሚሰጥ ነጥብ ድምር መሰረት በወጣው የነጥብ (ፕሌስመንት) ደረጃ ሰንጠረዥ ላይ በ64 ነጥብ ዘጠነኛ ሆነን ማጠናቀቃችንም እሰየው የሚያስብል ነው፡፡

በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከአራተኛ እስከ ስምንተኛ ባሉት ደረጃዎች ውስጥ አጠናቀው ነጥብ ያስገኙ እና የዲፕሎማ ተሸላሚ የሆኑት አትሌቶች፡-
4ኛ – ፍሬወይኒ ሀይሉ – በሴቶች 1500 ሜትር
4ኛ – መቅደስ አበበ – በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል
4ኛ – ሮዛ ደረጀ – በሴቶች ማራቶን
4ኛ – በሪሁ አረጋዊ – በወንዶች 10,000 ሜትር
4ኛ – ጌትነት ዋለ – በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል
5ኛ – እጅጋየሁ ታዬ – በሴቶች 5000 ሜትር
6ኛ – ሀብታም አለሙ – በሴቶች 800 ሜትር
6ኛ – ሰንበሬ ተፈሪ – በሴቶች 5000 ሜትር
8ኛ – ዮሚፍ ቀጄልቻ – በወንዶች 10,000 ሜትር
8ኛ – ዘርፌ ወንድማገኝ – በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል

  • የአትሌቲክስ የነጥብ ደረጃ ሰንጠረዥ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ባሉት ደረጃዎች ውስጥ የሚያጠናቅቁ አትሌቶች በሚያስመዘግቡት ነጥብ ድምር መሰረት የሚወጣ ሲሆን የነጥብ አሰጣጡም ለአንደኛ ደረጃ 8 ነጥብ፣ ለሁለተኛ ደረጃ 7 ነጥብ፣ ለሶስተኛ ደረጃ 6 ነጥብ፣ ለአራተኛ ደረጃ 5 ነጥብ፣ ለአምስተኛ ደረጃ 4 ነጥብ፣ ለስድስተኛ ደረጃ 3 ነጥብ፣ ለሰባተኛ ደረጃ 2 ነጥብ፣ እና ለስምንተኛ ደረጃ 1 ነጥብ ነው።

ከፊታችን ምን  እየጠበቀን ነው? ምንስ እናድርግ?
ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፉ ወረርሺኝ ምክንያት ትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለሌላ ግዜ እንዲተላለፉ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ሌላ አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ቀጣዮቹ አራት ዓመታት በተከታታይ በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች የሚካሄዱባቸው ይሆናሉ፡፡ በ2022 የዓለም ሻምፒዮና፣ በ2023 የዓለም ሻምፒዮና፣ በ2024 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች፣ እና በ2025 የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ይኖራሉ፡፡ በቀጣዩ ዓመት በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ከሐምሌ 8 – 17/2014 በዩናይትድ ስቴትስ ኦሪጎን የሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዘጋጆች ሙሉ የውድድሩን ፕሮግራም፣ የማራቶን እና የእርምጃ ውድድሮች የሚካሄዱባቸውን ቦታዎች በትላንትናው ዕለት ይፋ አድርገዋል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናውን ውድድር በኃላፊነት የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ከወዲሁ ለዛ ውድድር ተሳትፎ የሚጠበቅበትን አቅዶ መንቀሳቀስ ይኖበርታል፡፡

ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጭቅጭቆችን ለማስቀረት ከወዲሁ ሁሉም አትሌቶች አውቀውት በውስጡ የሚያልፉበትን ገዢ የሆነ የመምረጫ መስፈርት ማዘጋጀት ቀዳሚው ተግባር መሆን አለበት፡፡ የመምረጫ መስፈርት ሁልግዜም በግላዊ ምልከታ እና ፍላጎቶች ላይ በሚመሰረት ምክንያት አነጋጋሪ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ቢሆንም ባለድርሻ አካላቱን በሙሉ ባሳተፈ መልኩ ውይይት ተደርጎበት ቢወጣ ሁሉንም ገዢ እና ከጭቅጭቅ የፀዳ ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህ ላይ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከተከሰቱት ሁኔታዎች አንፃር የሌሎች ሀገሮችንም ተሞክሮዎች በመዳሰስ ነገሩን ሰፋ አድርጎ መመልከት ቢቻል ጥሩ ነው፡፡ ትልልቅ ውድድሮች በመጡ ቁጥር በተደጋጋሚ እንደታዘብነው አንዳንድ አትሌቶች በቡድኑ ውስጥ ለመካተት የሚያደርጉትን ተገቢ ያልሆነ ሙከራም ማቆም አለባቸው፡፡ ከፋም ለማም ስፖርቱን እንዲመራ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም የሚያወጣቸውን መስፈርቶች ማክበርና በዛ ውስጥ ተመራጭ ለመሆን መሞከር ግድ እንደሚላቸውም መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ማኔጀሮች እና አሰልጣኞች በተለይ በማራቶን የራሳቸውን አትሌት ለማስመረጥ የሚያደርጓቸው አላስፈላጊ ግፊቶችም ሊያቆሙ ይገባል፡፡

ለውድድሮች የምናደርጋቸውን ዝግጅቶች ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ከውድድሮች በኋላ መገምገም እና መታረም ያለባቸው ነገሮች ካሉ ማረም፡፡ ከፍተኛ ሙቀት በነበረባቸው በለንደን 2012 ኦሊምፒክ ሶስቱም የወንዶች ማራቶን ተወዳዳሪዎቻችን፣ በሞስኮ 2013 የዓለም ሻምፒዮና ሁለቱ የሴቶች ማራቶን ተወዳዳሪዎቻችን፣ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ አምስት የማራቶን (ሶስቱም ወንዶች እና ሁለት ሴቶች) ተወዳዳሪዎቻችን እንዲሁም የሴቶች እርምጃ ተወዳዳሪያችን ለማቋረጥ መገደዳቸውን አስተውለናል፡፡ ስለዚህ በጎዳና ላይ ውድድሮች ከባድ ሙቀት ለሚኖርባቸው ቦታዎች እንዴት መዘጋጀት አለብን የሚለው ጉዳይም በደንብ ሊታይ የሚገባው ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ የመም (ትራክ) ተወዳዳሪ አትሌቶቻችን የውድድር ዓመቱ ሲጀምር ድንቅ ብቃታቸውን ያሳዩን እና ወደትልቅ ውድድር ሲቃረቡ አቋማቸው እየወረደ ይመጣል፡፡ አሰልጣኞቻቸው ለእነዚህ አይነቶቹ አትሌቶች ወደትልቅ ውድድር ሲቃረቡ ብቃታቸውን እያሳደጉ እንዲሄዱ የሚረዳቸውን የልምምድ ፕሮግራም ቢያዘጋጁላቸው መልካም ነው፡፡ በመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ላይ በተለይ በወንዶች አሁንም በከፍተኛ ደረጃ የሚፎካከሩ አትሌቶችን ለማፍራት ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል፡፡

Continue Reading

Articles

የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የቶኪዮ ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ማጣሪያ ውድድሮች የመጀመሪያ ሁለት ቀናት

Published

on

በሴቶች 5000 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ላይ የሚፎካከሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች

በቶኪዮ ኦሊምፒክ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት የኢትዮጵያ አትሌቶች የተሳተፉባቸው የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል፣ 800 ሜትር በሁለቱም ፆታዎች፣ እንዲሁም የሴቶች 5000 ሜትር ማጣሪያዎች ሌላኛዎቹ የኢትዮጵያውያን የትኩረት ማዕከል የነበሩ ውድድሮች ናቸው፡፡ ቀጣዩ ዘገባ የኢትዮጵያውያኑን የማጣሪያ ውድድሮች ተሳትፎ እና ውጤቶች አንዲሁም ተጨማሪ መረጃዎችን ይዟል፡፡

የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል

በአትሌቲክስ ውድድሩ የመክፈቻ ቀን (ዓርብ ሐምሌ 23/2013) ጠዋት ላይ በተካሄደው የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ማጣሪያ ከተሳተፉት ሶስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ከምድብ አንድ ለሜቻ ግርማ (8፡09.83) በአንደኛነት፣ ከምድብ ሁለት ጌትነት ዋለ (8፡12.55) በሁለተኛነት ለፍፃሜው ሲያልፉ በምድብ ሶስት የተወዳደረው ታደሰ ታከለ (8፡24.69) ስምንተኛ ወጥቶ ለፍፃሜው ሳያልፍ ቀርቷል፡፡ ለሜቻ ጃፓናዊው ሚዩራ ዩጂን እና ኬንያዊው ቤንጃሚን ኪይገንን በማስከተል ከምድቡ ያሸነፈበት 8:09.83 በኦሊምፒክ የማጣሪያ ውድድሮች ላይ የተመዘገበ የምንግዜውም ፈጣን ሰዓት ሆኗል፡፡ የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል የፍፃሜ የሜዳልያ ፉክክር በዋናነት በኬንያውኑ ቤንጃሚን ኪገን እና አብራሀም ኪቢዎት፣ በኢትዮጵያውያኑ ለሜቻ ግርማ እና ጌትነት ዋለ እንዲሁም በሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ መካከል እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል በ1980ው የሞስኮ ኦሊምፒክ በሻምበል እሸቱ ቱራ አማካይነት ካስመዘገበችው የነሐስ ሜልያ ድል ወዲህ በርቀቱ በወንዶች ምንም አይነት የኦሊምፒክ ሜዳልያ ድል የላትም፡፡ ሆኖም ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየታዩ የመጡ መሻሻሎች እና በዶሀው የዓለም ሻምፒዮና ላይ የተመዘገበው የብር ሜዳልያ ድል በቶኪዮም ሌላ ሜዳልያን ተስፋ እንድናደርግ ያነሳሳን ሆኗል፡፡ ዘግይቶ የተሰላፊ አትሌቶች ለውጥ ከተደረገባቸው ርቀቶች አንዱ በሆነው የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል በተጠባባቂነት የተመዘገበውና በዋናነት በ5000 ሜትር እንደሚወዳደር ይጠበቅ የነበረው ጌትነት ዋለ ወደመጀመሪያ ተሰላፊነት የመጣ ሲሆን ኃይለማሪም አማረ በመጨረሻ ሰዓት በለሜቻ ግርማ መተካቱም አነጋጋሪ የሆነ ሌላኛው ለውጥ ነው፡፡ ጌትነት በ3000 ሜትር መሰናክልም ጠንካራ ተፎካካሪ አትሌት ሲሆን በዶሀ የዓለም ሻምፒዮና ላይ አራተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ በፍፃሜው ውድድር በ2019 የርቀቱ የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮን ጌትነት ዋለ እና በወቅቱ የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊስት ለሜቻ ግርማ የሚወከለው የኢትዮጵያ ቡድን በቶኪዮ የኬንያውያኑን የበላይነት ለመግታትና አዲስ የስኬት ታሪክ ለማፃፍ እንደሚበቃ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡                     

በ1984 በሎስ አንጀለስ ከተከናወነው የኦሊምፒክ ውድድር አንስቶ በተከታታይ በዘጠኝ የኦሊምፒክ ውድድሮች ወይም ላለፉት 36 ዓመታት የኦሊምፒክ የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል የወርቅ ሜዳልያ ድል በኬንያውያን ቁጥጥር ስር ይገኛል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናም ተመሳሳይ የበላይነት ያላቸው ኬንያውያን ከ17 የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች በ14ቱ የወርቅ ሜዳልያው አሸናፊዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ከሁለት ዓመት በፊት በዶሀው የዓለም ሻምፒዮና ላይ ከኢትዮጵያውያን እና ከሞሮኮ አትሌቶች የገጠማቸው ተግዳሮት ለመሸነፍ እጅግ አቅርቧቸው የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ በአንድ ማይክሮ ሰከንድ ልዩነት አሸናፊነታቸውን ባረጋገጡበት በዶሀው ውድድር የተፈታተኗቸው ኢትዮጵያዊው ለሜቻ ግርማ እና ሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ በቶኪዮው ፍፃሜ ለሌላ ብርቱ ፉክክር እየጠበቋቸው ይገኛሉ፡፡ ባለፉት ሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች በቅደም ተከተል የብር እና የነሐስ ሜዳልያን ያገኘው ሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ በቶኪዮ ከሚወዳደሩት በሙሉ የላቀና 7፡58.15 የሆነ የራሱ ምርጥ ሰዓት ያለው ነው፡፡

ኬንያ በቶኪዮ ያለፈው ውድድር ሻምፒዮንነቱን ክብር የሚያስጠብቅላትን አትሌት ይዛ መቅረብ ሳትችል ቀርታለች፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት በሪዮ የኦሊምፒክ እንዲሁም ከሁለት ዓመት በፊት በዶሀ የዓለም ሻምፒዮን የሆነው ኮንሰስለስ ኪፕሩቶ ባለፈው ወር በኬንያ የኦሊምፒክ ምርጫ ውድድር ላይ ውድድሩን ባለማጠናቀቁ የኦሊምፒክ ሻምፒዮንነት ክብሩን ለማስጠበቅ በቶኪዮ አልተገኘም፡፡ ስለዚህ አሁን የረጅም ግዜ የበላይነታቸውን የማስጠበቅ ኃላፊነቱ በ2019ኙ የዶሀ የዓለም ሻምፒዮና ላይ በቅደም ተከተል ስድስተኛ እና ሰባተኛ ሆነው ባጠናቀቁት ቤንጃሚን ኪገን እና አብራሀም ኪቢዎት ላይ ወድቋል፡፡  

የሴቶች 800 ሜትር

ከአትሌቲክሱ የጀመሪያ ቀን የጠዋት መርሀግብሮች አንዱ በነበረው የሴቶች 800 ሜትር ማጣሪያ በምድብ ሶስት በአሜሪካዊቷ አቲንግ ሙ ተቀድማ በ2 ደቂቃ ከ01.20 ሰከንድ ሁለተኛ የወጣችው ሀብታም አለሙ ለግማሽ ፍፃሜው ያለፈች ሲሆን በሁለተኛው ቀን ምሽት ላይ በተካሄደው የግማሽ ፍፃሜ ውድድር ላይም በአሜሪካዊቷ አቲንግ ሙ ተቀድማ በ1:58.40 ሁለተኛ በመሆን በኦሊምፒክ የውድድር ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ በርቀቱ ለፍፃሜ ውድድር የበቃች ኢትዮጵያዊት ሆናለች፡፡ ሀብታም ከውድድሩ በኋላ በቶኪዮ ለሚገኘው ባልደረባችን አብይ ወንድይፍራው በሰጠችው አጭር ቃል ‹‹ውድድሩ ትንሽ ፈታኝ ነበር ነገር ግን ለሀገሬ ስል ያለኝን አቅም ሁሉ ተጠቅሜያለሁ፡፡ ክብሩ ይስፋ ለመድኃኒዓለም በመጨረሻም አሪፍ ውጤት ላይ ደርሻለሁ፡፡ ለኦሊምፒክ የፍፃሜ ውድድር ሳልፍ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም ከኢትዮጵያ ለፍፃሜ የደረሰ ያለ አይመስለኝም እና አሁንም መጨረሻዬን ያሳምርልኝ ነው የምለው›› ብላለች፡፡  

በሴቶች 800 ሜትር የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ በምድብ አራት በ2.01.98 አራተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ነፃነት ደስታ ወደ ግማሽ ፍፃሜው መቀላቀል ሳትችል ስትቀር በጀማሪዎች ስም ዝርዝር ላይ ስሟ ተካቶ በምድብ አንድ እንደምትሮጥ ስትጠበቅ የነበረችው ወርቅውሀ ጌታቸው ግልፅ ባልተደረገ ምክንያት ውድድሩን ሳትጀምር ቀርታለች፡፡

የወንዶ 800 ሜትር

የወንዶች 800 ሜትር የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ላይ የተሳተፈው ኢትዮጵያዊው መለሰ ንብረት ከምድብ ሶስት በ1:47.80 ሰባተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ለግማሽ ፍፃሜው ማለፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡ በመሐመድ አማን ስኬቶች በመነቃቃት ላይ የነበረው የወንዶች 800 ሜትር ከቅርብ ግዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ሶስት ሰዓት የሚያሟሉ ተወካይ አትሌቶችን ለማግኘት እየተቸገረችበት የምትገኝ ርቀት እንደሆነ እየታየ ነው፡፡ የኦሊምፒክ ሚኒማ ማሟላት የቻለ አንድ አትሌት ብቻ ይዘን የቀረብንበት የቶኪዮ ኦሊምፒክም ይህ ችግር እንዳልተቀረፈ የታየበት ሌላኛው አጋጣሚ ሆኗል፡፡  

የሴቶች 5000 ሜትር ማጣሪያ

በአትሌቲክሱ የመጀመሪያ ቀን ሐምሌ 23/2013 ምሽት ላይ በተደረት የሴቶች 5000 ሜትር ማጣሪያ ላይ የተሳተፉት ሶስቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሐምሌ 26/2013 ምሽት ላይ ለሚደረገው የፍፃሜ ውድድር አልፈዋል፡፡ ከምድብ አንድ ሰንበሬ ተፈሪ (14፡48.31) እና እጅጋየሁ ታዬ (14፡48.52) የኔዘርላንዷ ሲፋን ሀሳን (14፡47.89) እና ኬንያዊቷ አግነስ (14፡48.01) ቲሮፕን ተከትለው በቅደም ተከተል ሶተኛ እና አራተኛ ሆነው ሲያልፉ ከምድብ ሁለት ጉዳፍ ፀጋዬ (14፡55.74) ኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪ (14፡55.77) አስከትላ በአንደኛነት አልፋለች፡፡


ሐምሌ 26/2013 ምሽት ላይ በሚደረገው የሴቶች 5000 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ላይ የሚፎካከሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች

በሄንግሎ በተከናወነው የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ምርጫ ውድድር ላይ ባስመዘገበችው የራሷ ምርጥ 14:13.32 የርቀቱ የወቅቱ ፈጣን አትሌት ሆና ወደ ቶኪዮ ያቀናችው ጉዳፍ ለወርቅ ሜዳልያ ድል ከሚጠበቁት መካከል ናት፡፡ በሄንግሎው ውድድር ላይ ጉዳፍን በመከተል በቅደም ተከተል 14:14.09 እና 14፡15.24 በሆነ ሰዓት የጨረሱት እጅጋየሁ እና ሰንበሬም በዓለም የምንግዜም ምርጥ ዝርዝር ውስጥ የስድስተኛ እና ሰባተኛ ደረጃን ለመያዝ የበቁ ጠንካራ አትሌቶች ናቸው፡፡ የቶኪዮ ኦሊምፒክ የሴቶች 5000 ሜትር ተወዳዳሪዎች ዝርዝር ሶስቱን ኢትዮጵያውያን ጨምሮ ከዓለም የምንግዜም ምርጥ አስር የርቀቱ ሯጮች አምስቱን ያካተተ ነው፡፡ ኬንያውያኑ ሄለን ኦቢሪ እና አግነስ ቲሮፕ ከምንግዜም ምርጥ አስሮቹ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆኑ በ12ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሀሳንም የቶኪዮውን የፍፃሜ ፉክክር በጉጉት እንዲጠበቅ የምታደርግ ብርቱ አትሌት ናት፡፡

Continue Reading

Articles

ሰለሞን ባረጋ ለአስራ ሶስት ዓመት የራቀንን የወንዶች 10,000 ሜትር ድል በቶኪዮ ወደ ኢትዮጵያ መልሶታል

Published

on

218076583_1010892909482678_1235421043554241523_n

በቶኪዮ ኦሊምፒክ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአትሌቲክስ ውድድር በተጀመረ በሁለተኛው ቀን በወንዶች አስር ሺህ ሜትር ኢትዮጵያውያንን እጅግ ያስደስተው ድል በወጣቱ ሰለሞን ባረጋ አማካይነት ተመዝግቧል፡፡   
በ1980 ሞስኮ ላይ ምሩፅ ይፍጠር በርቀቱ ለመጀመሪያ ግዜ የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ካስገኘ በኋላ ከተደረጉት አስር የኦሊምፒክ የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ውድድሮች ኢትዮጵያ አምስቱን በበላይነት ለመጨረስ ችላለች፡፡ የርቀቱ ንጉሶች ሀይሌ ገብረስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ከ1992 እስከ 2008 ዓ.ም. በአራት ተከታታይ የኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ በማሸነፍ የርቀቱ የወርቅ ድል ለኢትዮጵያ ብቻ የተሰጠ እንዲመስለን አድርገውንም ነበር፡፡ ከ2008ቱ የቤይጂንግ ኦሊምፒክ የቀነኒሳ በቀለ ድል በኋላ በተከሰተው የሞ ፋራህ የበላይነት ምክንያት ተመሳሳዩን ድል በቶኪዮ ለማየት 13 ዓመታትን መጠበቅ ግድ ብሎናል፡፡ ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት በጉጉት ስንጠብቀው የቆየነውን የ10 ሺህ ሜትር የኦሊምፒክ ድል በመጨረሻም ሰለሞን ባረጋ በቶኪዮ አጎናፅፎናል፡፡ የሰለሞን የቶኪዮ የወርቅ ሜዳልያ ድል ኢትዮጵያ ካለፉት አስራ አንድ ኦሊምፒኮች በርቀቱ ለስድስተኛ ግዜ የበላይ ሆና እንድትጨርስ ያስቻለም ነው፡፡ ድሉ በቶኪዮ የአትሌቲኪስ ውድድሮች የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳልያ ድል ሆኖም ተመዝግቧል፡፡ ሰለሞን ባረጋ በ2018 የበርሚንግሀም የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር በ3000 ሜትር እና በ2019 የዶሀ ዓለም ሻምፒዮና ላይ በ5000 ሜትር የብር ሜዳልያ ካገኘ በኋላ በመጀመሪያ የኦሊምፒክ ተሳትፎው ከፍተኛ ክብር የሚሰጠውን የ10,000 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ድል ለማሳካት በቅቷል፡፡

‹‹የ200 ሜትር እና 400 ሜትር አጫጨር የፍጥነት ሩጫ ልምምዶችን ስሰራ ስለነበረ ሁለት ዙር ሲቀር ውድድሩን እንደማሸንፍ ለራሴ ነገርኩት››
ሰለሞን ባረጋ ከቶኪዮው ድል በኋላ

ሰለሞን ባረጋ ከቶኪዮው ድሉ በኋላ በስፍራው ከሚገኘው የስራ ባልደረባችን አብይ ወንድይፍራው ጋር ባደረገው አጭር ቃለ ምልልስ የሚከተለውን ብሏል ‹‹ረጅም ርቀት የእኛ ስፖርት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ሆኖም በኦሊምፒክ ውድድር ላይ ወርቅ ሜዳልያ ከወሰድን ብዙ ግዜ አልፎናል፡፡ ይህን ነገር ለመጨረሻ ግዜ ያሳካውም ቀነኒሳ ነበረ፡፡ ዛሬ በቶኪዮ ድሉን በማሳካቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በተለይ ለእኛ ከቶኪዮ ጋር አበበ ቢቂላን የምናስታውስበት ድል ስለሆነ ያንን በማሳካቴም በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ዘንድሮ ከኡጋንዳ የዓለም ሪኮርድ የሰበረው ቼፕቴጌይ እና የዓመቱን ፈጣን ሰዓት የሮጠው ኪፕሊሞ ነበሩ፡፡ እናም ውድድሩ በጣም ይፈጥናል ብዬ ነበር የጠበቅኩት ግን አልተሮጠም፡፡ ውድድሩን የጨረስነውም 27 ቤት ነው፡፡ የ200 ሜትር እና 400 ሜትር አጫጨር የፍጥነት ሩጫ ልምምዶችን ስሰራ ስለነበረ ሁለት ዙር ሲቀር ውድድሩን እንደማሸንፍ ለራሴ ነገርኩት፡፡ ኡጋንዳውያኑ አትሌቶች ዛሬ ብዙም አልታገሉም፡፡ አብዛኛውን ሰዓት ከኋላ ነው የቆዩት እና እንደዚህ ይሆናል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፡፡ እነርሱን ካሜራ ላይም እያየኋቸው ስለነበር ስለነሱ ብዙም አልተጨነቅኩም እንደውም ከእነሱ ይልቅ የእኛን ልጆች ነበረ ይወጣሉ ብዬ የጠበቅኩት፡፡ በውድድሩ መሀል ተጠባቂ የሆኑት ኡጋንዳውያን ወደኋላ ቀርተው ሶስተኛው የቡድን አጋራቸው ወደፊት ወጥቶ በሰፊ ልዩነት ሲመራ እኛ እነሱን ስንጠብቅ እሱ አዘናግቶ እንዳያሸንፍ ልዩነቱን ለማጥበብ ሞክሬያለሁ፡፡ ምናልባት እነሱ እኛን ሲጠብቁ አንተ ሂድ ያሉት ነበር የመሰለኝ፡፡ ከዚህ በፊት በእንደዚህ አይነቱ ነገር ዳይመንድ ሊግ ላይ ስለተሸወድኩኝ ያንን እንዳይደግሙ ብዬ ነበረ ልዩነቱን ለማጥበብ የሞከርኩት፡፡ የአሰልጣኜንም ምክር እየሰማሁ ስለነበረ የምሮጠው እና ወደኋላ ተመለስ እያለኝ ስለነበር ወደኋላ ተመልሻለሁ፡፡ የእነርሱ እስትራቴጂ እሱን ወደፊት እንዲወጣ አድርገው እኛን ለማድከም ነበረ፡፡ ከበሪሁን ጋር ስንነጋገር ወደፊት ጠጋ በል እያልኩት ነበረ፡፡ ከበሪሁን ጋር ልምምድም አብረን ነበረ የምንሰራው፡፡ እኔ እንደውም ከአንድ እስከ ሶስት እንወጣለን ብዬ ነበር የጠበቅኩት አጋጣሚ ሆኖ አልተሳካም ነገር ግን ወርቁን ወደኢትዮጵያ በመመለሳችን በጣም ደስተኛ ነን፡፡›› ብሏል፡፡

Continue Reading

Trending