Connect with us

Sports

ባሬቶ ሲሸኙ ዮሐንስ ተሹሟል

Published

on

team

Mariano Barreto (Left) and Yohannis Sahle.

ያለፉት 10 ቀናት ቀድሞውንም ውዝግብ እና ክርክር በማያጣው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዙሪያ በርካታ ነገሮች ተከስተዋል፤

አነጋጋሪ ጉዳዮችም ተነስተዋል፡፡ ዋሊያዎቹን ለ12 ወራት በዋና አሰልጣኝነት የመሩት አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ የሁለት ዓመታት

የኮንትራት ጊዜያቸውን ሳያጠናቅቁ ‘በስምምነት’ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ሲለያዩ ይህ የሁለቱ ወገኖች ፍቺ በይፋ በተገለፀ ልክ

በሳምንቱ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ተደርገው መመረጡን ፌዴሬሽኑ ራሱ በይፋ

መግለጫ ልኳል፡፡ ከዚህ ውሳኔ ሶስት ቀናት በኋላ ደግሞ የቀድሞው ፖርቹጋላዊ የቡድኑ አለቃ በብዙ ጉዳዮች ዙሪያ

አስተያየቶቻቸውን የገለፁበትን የስንብት ፕሬስ ኮንፈረንስ ሰጥተዋል፡፡

የባሬቶ ስንብት

ማሪያኖ ጄሬኒሞ ባሬቶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ያሳለፏቸው ያለፉት 12 ወራት በብዙ ውጣውረዶች፣ ውዝግቦች እና

አለመግባባቶች የተሞሉ ነበሩ፡፡ ፖርቹጋላዊው ኃላፊነቱን ከተረከቡበት እለት ጀምሮ ለስራው ከተፎካከሯቸው ሌሎች እጩዎች

በልጠው የስልጣን መንበሩን ከያዙበት አከራካሪ መንገድ ጀምሮ በውጪ ምንዛሬ እስከሚከፈላቸው ደመወዝ እና ጥቅማጥቅም፣

እንዲሁም ለዝግጅት ወደ ብራዚል ቡድኑን ይዘው ከሄዱበት ውሳኔያቸው አንጋፎችን ትተው ለወጣቶች የመጫወት እድሎች

እስከሰጡባቸው ውሳኔዎቻቸው ድረስ የብዙ ውዝግቦች ምንጭ ሆነው የነበረ ሲሆን በኋላ በፉክክር ጨዋታዎች ያስመዘገቧቸው

ውጤቶች እና የቡድኑ አጨዋወትም እንዲሁ የመነጋገሪያ ርዕስ ነበር፡፡

 ውጤታማነት፡- በቁጥሮች ብቻ ከተመለከትነው የባሬቶ የፉክክር ጨዋታዎች ሬኮርድ ደካማ የሚባል ነው፡፡ በአፍሪካ

ዋንጫ ማጣሪያው ቡድኑ ወደ ባማኮ ተጉዞ በማሊ ላይ ካስመዘገበው ያልተጠበቀ አስገራሚ የ3ለ2 ድል ውጪ ማሸነፍ

ያልቻለ ሲሆን ከቀሪዎቹ አምስት ጨዋታዎች በአንዱ አቻ ተለያይቶ (ከማላዊ)፣ በአራቱ ሽንፈት አስተናግዷል (ሁለቴ

በአልጄሪያ እንዲሁም በማሊ እና ማላዊ)፡፡ በመላው የአፍሪካ ጨዋታዎች ማጣሪያም በባሬቶ የተመራው የ23 ዓመት

በታች ቡድኑ በጎረቤት ሱዳን በደርሶ መልስ ተረቶ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ዋልያዎቹ በፖርቹጋላዊው

አመራር ቀድሞ ጠንካራ ምሽጋቸው በነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም ካደረጓቸው ሶስት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ

ጨዋታዎች በአንዱም አለማሸነፋቸው እና የኦሊምፒክ ቡድኑም በድሬዳዋ ስታዲየም በሱዳን መረታቱ ሳይነሳ የማይታለፍ

በባሬቶ ዘመን የታየ የሜዳ አድቫንቴጅን ያለመጠቀም ችግር ነበር፡፡ ባጠቃላይ የባሬቶ የፉክክር ጨዋታዎች ሬኮርድ

እንዲህ ይነበባል፡- አንድ ድል፣ አንድ አቻ እና ስድስት ሽንፈቶች፡፡

 የአጨዋወት ዘይቤ፡- የባሬቶ የኢትዮጵያ ቡድኖች በተለይም ዋናው ብሔራዊ ቡድን ባደረጓቸው ጨዋታዎች በጠቅላላው

ማለት ይቻላል የ4-3-3 አሰላለፍን ይዘው ወደ ሜዳ ቢገቡም አንድ አይነት ማንነት ያላቸው ቡድኖችን በተለያዩ

ጨዋታዎች ላይ ተመልክተናል ለማለት ያስቸግራል፡፡ አሰልጣኙ ተጨዋቾቼ እንደዚያ እንዲጫወቱ አላዘዝኩም ቢሉም

በርካታ ዓላማ-የለሽ ረዥም ኳሶችን የሚጫወት፣ በማጥቃት ላይ ያተኮረ ይሁን በመከላከል ላይ የማይታወቅ፣

በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ ያልተዋጣለት ቡድንን ስንመለከት ቆይተናል፡፡

 የተጨዋቾች ምርጫ፡- ትውልደ-ህንዱ ባሬቶ ብዙ ተቃውሞ ካስተናገዱባቸው ጉዳዮች አንዱ ለአንጋፋ ተጨዋቾች ቦታ

የነፈጉበት እና ለአዳዲስ ወጣቶች እድሎች የሰጡበት የተጨዋቾች ምርጫቸው ነበር፡፡ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በፊት

ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ያበቁት እና በደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፉት እንዲሁም ከዚያ በኋላ ለዓለም

ዋንጫም ለማለፍ ተቃርበው የነበሩትን በርካታ ተጨዋቾች መጠቀም አለመፈለጋቸው በአንዳንዶች በመረረ ሁኔታ

አስወቅሷቸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በመደበኝነት የሚከታተሉ እና ያልተጠሩት አብዛኞቹ ሲኒየር ተጨዋቾች

አቋም በአስደንጋጭ ሁኔታ መውረዱን ያስተዋሉ አንዳንዶች ደግሞ በባሬቶ እነዚያን ከዋክብት አለመጥራት ብዙም

አልተገረሙም ነበር፡፡ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝን በብዙ ነገሮች ልንተቻቸው ብንችልም አቋማቸው የወረዱ ባለትልቅ

ስሞችን ባለመምረጥ ድፍረታቸው እና በብሔራዊ ቡድኑ ማልያ ባሳዩን በርካታ ወጣት ተስፈኞች (ናትናኤል ዘለቀ፣

አንዳርጋቸው ይላቅ፣ ዳዋ ሆጤሳ፣ አብዱልከሪም መሀመድ፣ ራምኬል ሎክ…) አለማድነቅ ያስቸግራል፡፡ ለክለቦቻቸው

እንኳ ገና አዲስ የሆኑት ተጨዋቾች በትልቅ መድረክ ከታላላቅ ተጨዋቾች በተቃራኒ ትከሻ ለትከሻ ሲገፋፉ መመልከት

ተስፈ እና ደስታን የሚሰጥ ነበር፡፡ ለወጣቶች እድል በመስጠት በማይሞገሰው እግር ኳሳችን ባሬቶ እነዚህን ተጨዋቾች

በተለይ ናትናኤልን ለእግር ኳሳችን እንዳበረከቱ በድፍረት ብንናገር ስህተት አይሆንም፡፡

 ዝግጅት፡- ማሪያኖ ባሬቶ ገና እንደመጡ ለእኛ ባልተለመደ መንገድ በራሳቸው ጥረት ቡድናቸውን ለሳምንታት ዝግጅት ወደ

ብራዚል ከወሰዱበት አንስቶ በራሳቸው ግንኙነቶች የአንጎላ ብሔራዊ ቡድንን ለወዳጅነት ከገጠሙበት እንዲሁሙ በሀገር

ውስጥም ሲዘጋጁበት የነበሩባቸው መንገዶች የሚደነቁ ነበሩ፡፡ በተመለከትናቸው በሀገር ውስጥ ዝግጅቶቻቸው ላይ ያሳዩት

የነበረው መሰጠት፣ ታታሪነት፣ የእንዳንዱን ተጨዋቾቹን መሰረታዊ የእግር ኳስ እውቀት ለማሳደግ ሳይሰለቹ ያደርጓቸው

የነበሩት ጥረቶች ሁሉ ምስጋና የሚያስቸሯቸው ነበሩ፡፡ በእነዚያ የልምምድ ፕሮግራሞች ባሬቶ ከፊታቸው ላሉ ጨዋታዎች

በታክቲክ ከመዘጋጀት ይልቅ መሰረታዊ እና ተጨዋቾቹ በታዳጊነታቸው ሊማሯቸው ይገቡ የነበሩ መሰረታዊ ነገሮች ላይ

ጊዜያቸውን ለማጥፋት ይገደዱ ነበር፡፡

 ግንኙነቶች፡- ባሬቶ እንደብዙሀኑ የእግር ኳስ አሰልጣኞች በአንድ ጎራ የሚደነቁ፣ በሌላኛው ጎራ የሚተቹ፤ ከተለያዩ

ወገኖች ጋር ያላቸው ግንኙነትም እንደዚያው የሚለያይ ነበሩ፡፡ እራሳቸውም በተለያዩ ቃለመጠይቆቻቸው እንዳነሱት

በፌዴሬሽኑ ውስጥ የሚቀርቧቸው እና በተቃራኒው ሊያዩዋቸው የማይፈልጉ ሰዎች ነበሩ፤ ከተጨዋቾቻቸው ጋር ከጥቂቶቹ

ጋር ካልሆነ (ለምሳሌ ባለመግባባት የቀነሱት አዳነ ግርማ) ጥሩ ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን ከጋዜጠኞች ጋርም

ከአንዳንዶቹ ጋር መልካም ከአንዳንዶቹ ጋር ግን ግላዊ ጉዳይ እስኪመስል መጥፎ ግንኙነት ነበራቸው፡፡

ባጠቃላይ የማሪያኖ ባሬቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ዘመን በበርካታ ውዝግቦች የታጀበ እና በመጨረሻም

ለፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የእርስ በእርስ መቃቃር ምክንያት ሆኖ የተጠናቀቀ ነበር፡፡ እናም በመጨረሻ

‘በስምምነት’ ተብሎ በተገለፀ የውል ማቋረጥ ባሬቶ የሶስት ወራት ደመወዝ በካሳ መልክ ተከፍሏቸው ከዋልያዎቹ ጋር

ተለያይተዋል፡፡

ባሬቶ ከስንብት በኋላስ

ማሪያኖ ባሬቶ በስምምነት ኃላፊነታቸውን እንደለቀቁ በይፋ በተገለፀ በ10ኛው ቀን ባለፈው ማክሰኞ በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፅህፈት

ቤት የስንብት ፕሬስ ኮንፈረንሳቸውን ሰጥተዋል፡፡ ፖርቹጋላዊው በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በተናገሩበት እና ስሜታዊ ሆነው በታዩበት

በዚህ ፕሬስ ኮንፈረንስ ላይ ግዴታቸው ሆኖም ይሁን እንዲሁ በፈቃደኝነት የረዷቸውን ጥቂት ግለሰቦች በስም ጠርተው ሲያመሰግኑ፣

ሊያግዙኝ ሲገባ አንድም ቀን ከጎኔ አልነበሩም ያሏቸውንም እንዲሁ በስም ጠርተው ወቅሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቺፍ

ኦፍ ስታፍ ጄነራል ሳሞራ የኑስን፣ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ እና አሰልጣኝ አብርሀም

ተክለሀይማኖትን በተለየ ሁኔታ ሲያመሰግኑ የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሀፊ አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝ፣ እንዲሁም አሰልጣኞቹ ጳውሎስ ጌታቸው፣

ፀጋዬ ኪዳነማሪያም እና ገብረመድህን ኃይሌም በቀና አጋዥነት የባሬቶ ምስጋና የደረሳቸው ሰዎች ሆነዋል፡፡ በተቃራኒው የቴክኒክ

ኮሚቴው እና የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ስራቸው ሆኖ ግን ምንም እገዛ ባለማድረግ በተሰናባቹ አሰልጣኝ ተተችተዋል፡፡

የውጪ እግር ኳስን አብዝተው የሚዘግቡት ሚዲያዎች፣ ለታዳጊ ተጨዋቾች ትኩረት የማይሰጠው እግር ኳሳችን እና መዋቅሩ

የተዛባው አጠቃላዩ የእግር ኳሱ ሲስተምም የባሬቶ የትችት ሰይፍ ያረፈባቸው እና እንድናሻሽላቸው ምክር የተሰጡን መስኮች

ሆነዋል፡፡ የእነሳልሀዲን ሰዒድ እና ጌታነህ ከበደ አይነት የብሔራዊ ቡድኑን ወሳኝ ተጨዋቾች በጉዳት እና ቅጣት ሳቢያ በብዙዎቹ

ጨዋታዎች ላይ ማሰለፍ አለመቻላቸውን ለስኬት አልባነታቸው በምክንያትነት ያነሱት ባሬቶ ምሳሌ ያደረጉት ሀገራቸው ፖርቹጋል ያለ

አንድ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ምንም ማድረግ እንደማትችል በመግለፅ ነበር፡፡ እግር ኳስ ወዳዱን እና ክብር የሰጣቸውን የኢትዮጵያን

ህዝብ በልባቸው ይዘው ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱም ባሬቶ ተናግረዋል፡፡

የዮሐንስ ሳህሌ ሹመት

የማሪያኖ ባሬቶ ከዋልያዎቹ ጋር መለያየት ይፋ በተደረገ ልክ በሳምንቱ፣ አራት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች

ለእጩነት መቅረባቸው በጭምጭምታ መልክ ከተሰማ 24 ሰዓታት እንኳን ሳይሞላ ከእጩዎቹ መካከል የደደቢቱ አሰልጣኝ

ዮሐንስ ሳህሌ (ኢንስትራክተር) ለብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነት መመረጡ መጀመሪያ በጭምጭምታ ደረጃ ከዚያም በፌዴሬሽኑ

ይፋዊ መግለጫ ተረጋግጧል፡፡ ከፌዴሬሽኑ ይፋዊ መግለጫ አስቀድሞ ዮሐንስ ቅዳሜ ከቀትር በኋላ ኢትዮጵያ ቡናን ከረቱበት

ጨዋታ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ ድረ-ገፅ በሰጠው ቃል ስለጉዳዩ እንደማያውቅ እና ለመወዳደር ሲል ያስገባው ፋይል እንደሌለ፣

ከፌዴሬሽኑ ሰዎች ጋርም በጉዳዩ ዙሪያ ምንም እንዳላወራ ገልፆ ነበር፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን ዮሐንስ ለቢቢሲ ዘጋቢ በሰጠው

ቃል በተጨዋችነት ያገለገለበትን ብሔራዊ ቡድን የማሰልጠንም እድል ስላገኘ እጅግ መደሰቱን ተናግሯል፤ ቡድኑን ውጤታማ

ለማድረግም በአቅሙ የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀቱንም አረጋግጧል፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ጁነይዲ ባሻ በበኩላቸው

ከሱፐር ስፖርት ጋር ባደረጉት ቆይታ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባለድርሻ አካላትን እና የእግር ኳስ ደጋፊዎችን በማዳመጥ ለዚህ

ውሳኔ እንደደረሰ ገልፀዋል፡፡ “የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የደደቢቱን አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና

አሰልጣኝ አድርጎ መርጧል፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ለሚዲያው እና በአጠቃላይ ለህዝቡ ግልፅ በነበረ ሂደት ነው፡፡ አንዳንድ

ጊዜ የሰዎችን ስሜት ከግምት ማስገባት ይኖርብናል” ያሉት ጁነይዲ “በቅርቡ ከአሰልጣኙ ጋር ተቀምጠን በሁሉም ነገሮች ዙሪያ

እንወያያለን፡፡ ብሔራዊ ቡድኑን ወደ ታላቅ ስኬት ለመምራትም ትክክለኛው ሰው እንደሚሆን ተስፋ አለን” ብለዋል፡፡ ይህ

የፕሬዚዳንቱ አስተያየት ግን ትንሽ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ አቶ ጁነይዲ የምርጫ ሂደቱ ለሚዲያው እና ለህዝቡ ግልፅ ነበር ማለታቸው

ፍፁም የማያሳምን ነው ምክንያቱም “ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋና አሰልጣኞች የመምረጫ መስፈርት በማዘጋጀትና የሁሉንም

ብቃትና ደረጃ በዝርዝር በማየት አራት ተወዳዳሪዎችን በኮሚቴው አማካኝነት ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለይቶ የማቅረቡ ሂደት

ከተጠናቀቀ በኋላ ዮሐንስ ሳህሌ በተዘጋጀው መመዘኛ መሰረት በቀዳሚነት ሊመረጥ ችሏል” ከሚለው የፌዴሬሽኑ የድህረ-

ምርጫ መግለጫ ውጪ አራቱን እጩዎች (ዮሐንስ ሳህሌ፣ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም፣ ፋሲል ተካልኝ እና አሸናፊ በቀለ) ለእጩነት

ያበቃቸውም ሆነ ዮሐንስን ለመመረጥ ያበቃው መስፈርት በትክክል ምንድ ነው የሚለው እስካሁን ግልፅ አልሆነም፡፡ እንደ ውበቱ

አባተ አይነት በፕሪምየር ሊጉ ስኬት ከሁሉም የሚልቅ አሰልጣኝ ለእጩነት እንኳ ሳይቀርብ በዋና አሰልጣኝነት በጣት ከሚቆጠሩ

ጨዋታዎች በላይ ያላደረገው ፋሲል ተካልኝ መታጨት እንዲሁም በሲኒየር ቡድን አሰልጣኝነት (በብሔራዊ ቡድንም ሆ በክለብ

ደረጃ) ከወራት ያልዘለለ ልምድ ያለው ዮሐንስ ከመታጨትም አልፎ መሾም እጅግ አነጋጋሪ እና የአቶ ጁነይዲን መግለጫ ፉርሽ

የሚያደርግ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ተሿሚው እና እጩዎቹ በአንድ ላይ በይፋ የተገለፁበትን ሂደት በምን አተያይ ግልፅ እንዳሉት መረዳት

ያስቸግራል፡፡

ዮሐንስ ሳህሌን በአጭሩ

የአዲስ አበባ ተወላጁ ዮሐንስ ሳህሌ በተጨዋችነት ለራስ ሆቴል እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን

ከተጫወተ በኋላ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ለመጫወት ካመራበት ኬንያ ሳይመለስ ቀርቶ ወደ አሜሪካ አቅንቷል፡፡ እዚያም

ማስሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽንን በመጀመሪያ ዲግሪ እና ስፖርት ሊደርሺፕ እና ኮቺንግን በሁለተኛ ዲግሪ ለተማረባቸው ኮሌጆች

ሲጫወት ነበር፡፡ በአሰልጣኝነት ሲ እና ቢ ፍቃዱም ከዚያ በኋላ የተለያዩ ኮሌጆችን ማሰልጠን ችሏል፤ በብራድ ፍሪድል አካዳሚም

በልጆች እና ታዳጊዎች ስልጠና ላይ ሰርቷል፡፡ የ49 ዓመቱ ዮሐንስ የካፍ ኢንስትራክተርም ሲሆን ወደ ትውልድ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ

ረዥም ጊዜ ባልቆየባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቴክኒክ ዲሬክተርነት፣ የደደቢት ጄነራል ማኔጀርነት እና የኢትዮጵያ ከ17

ዓመት በታች ቡድን አሰልጣኝነት ሚናዎች ሰርቷል፡፡ ዮሐንስ ባለፉት ጥቂት ወራት ደደቢትን በዋና አሰልጣኝነት ሲመራ የሰነበተ

ሲሆን በወጣቶች ላይ ያለውን ትልቅ እምነት እያሳየ የነበረበት ቡድን እየገነባ ይመስል ነበር፡፡ ግን ይህ ፕሮጄክት ከግብ ሳይደርስ

ዋሊያዎቹን የማሰልጠን ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ የሚደርስ ከሆነም በቅርቡ ስራውን

ይረከባል፡፡

Articles

በኦስሎ ዳይመንድ ሊግ የ5000ሜ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች በአሸናፊነት አጠናቀዋል

Published

on

Dawit-Seyaum-1
ትላንት ምሽት በኖርዌይ ኦስሎ በተከናወነው የዳይመንድ ሊግ 5000 ሜ. ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንዶችም በሴቶችም ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያሉትን ደረጃዎች በመቆጣጠር አሸንፈዋል፡፡ 

በዝናባማ የአየር ሁኔታ ውስጥ በተካሄደው የሴቶች 5000 ሜትር ፉክክር ዳዊት ስዩም በመጨረሻዎቹ መቶ ሜትሮች ውስጥ ፍጥነቷን በመጨመር ጉዳፍ እና ለተሰንበትን ቀድማ አንደኛ ወጥታለች፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለኦሪገን 2022 የአለም ሻምፒዮና ከመረጣቸው ዕጩ አትሌቶች ዝርዝር ውስጥ ያልተካተተችው ዳዊት በኦስሎ ያሸነፈችበት 14፡25.84 የሆነ ሰአት የራሷ ምርጥ ሲሆን እጅጋየሁ ታዬ (14.12.98) እና ለተሰንበት (14፡24.59) ባለፈው ወር በዩጂን ካስመዘገቧቸው በመቀጠልም የዘንድሮ የአለም ሶስተኛው ፈጣን ነው፡፡ በውድድሩ ላይ ከነበሩት ሌሎች ኢትዮጵያውያን መካከል በዘንድሮው የውድድር ዓመት በርቀቱ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን ያደረገችው አልማዝ አያና በ14:32.17 ስድስተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡ ሀዊ ፈይሳ በ14:33.66፣ ፅጌ ገብረሰላማ በ14:43.90፣ እና አበራሽ ምንሴዎ በ14:47.98 በቅደም ተከተል ሰባተኛ፣ አስረኛ እና አስራ አንደኛ ሆነው ሲያጠናቅቁ ሶስቱም ያስመዘገቡት ሰዓት የራሳቸውን ምርጥ ያሻሻሉበት ሆኗል፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ እ.ኤ.አ. በጁን 2008 ዓ.ም. ያስመዘገበችውና 14:11.15 የሆነው የኦስሎ ዳይመንድ ሊግ የሴቶች 5000 ሜትር የውድድር ስፍራ ሪከርድ ይሰበራል ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡  
ዳዊት ስዩም ውድድሩን በድል ካጠናቀቀች በኋላ ለውድድሩ አዘጋጆች በሰጠችው አስተያየት ‹‹ዛሬ ለእኔ ደስታን ስላመጣልኝ በውድድሩ ሰዓት የነበረውን ዝናብ ወድጄዋለሁ ማለት እችላለሁ፡፡ ጠንካራ ተፎካካሪዎች የነበሩበት ከባድ ውድድር ነበር እናም ሁሉንም ለማሸነፍ በቅቻለሁ። በርቀቱ የራሴን ምርጥ ሰዓት ማሻሻል መቻሌም አስፈላጊ ነበር፡፡ በስታድየሙ ውስጥ በከፍተኛ ስሜት ድጋፍ ይሰጡን የነበሩ ወገኖቻችን ነበሩ። ለሰጡን ድጋፍ እናመሰግናለን።›› ብላለች፡፡
 
በኦስሎ የወንዶች 5000 ሜትር የመጨረሻ ፉክክሩ በኢትዮጵያውያኑ ጥላሁን ሀይሌ እና ሳሙኤል ተፈራ መካከል የነበረ ሲሆን ጥላሁን የ1500 ሜትር ስፔሻሊስቱ ሳሙኤልን በአጨራረስ ፍጥነት ቀድሞ በ13:03.51 በአንደኛነት አጠናቋል፡፡ ሳሙኤል ተፈራ የራሱ ምርጥ በሆነ 13:04.35 ሁለተኛ ሲወጣ ጌትነት ዋለ የግሉ የዓመቱ ምርጥ በሆነ 13:04.48 ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል። በውድድሩ ላይ የነበሩት ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሚልኬሳ መንገሻ በ13:05.94 አምስተኛ እንዲሁም አሊ አብዱልመናን የራሱ ምርጥ በሆነ 13:16.97 አስረኛ ወጥተዋል፡፡
ጥላሁን ሀይሌ ውድድሩን በአሸናፊነት ካጠናቀቀ በኋላ ለውድድሩ አዘጋጆች በሰጠው አስተያየት ‹‹ሶስት ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያዎቹን ሶስት ደረጃዎች ይዘን መጨረስ መቻላችን ጥሩ አፈጻጸም ነበር። እየጠነከርኩ እንደሆነ የተሰማኝ ሲሆን በውድድሩ እና ባስመዘገብኩት ሰዓትም ተደስቻለሁ። ለረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ስለነበኩ ወደ አሸናፊነቱ መመለስ መቻሌ በጣም ጥሩ ነው።›› ብሏል፡፡

በኦስሎ የሴቶች 800ሜ. ውድድር ላይ ተፎካካሪ የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ ድሪቤ ወልቴጂ በ1፡58.69 አምስተኛ ሆና አጠናቃለች።
Continue Reading

Articles

የዘንድሮው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ሻምፒዮና በእኔ እይታ

Published

on

IMG_0110
ከመጋቢት19-24/2014 ዓ.ም በሐዋሳ አለም አቀፍ ስቴድዮም የተደረገው 51ኛዉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሞላ ጎደል ስኬታማ በሚባል ሁኔታ ተጠናቋል፡፡ ከአምስት አመት በኋላ በድጋሚ በአካል በመገኘት ስለተከታተልኩት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሀገር አቀፍ ሻምፒዮና የግል ምልከታዬን እንደሚከተለው አጠናቅሬዋለሁ፡፡

የበለጠ ትኩረትን በሳቡት ውድድሮች ዙሪያ የተመዘገቡ ውጤቶችን በወፍ በረር በመዳሰስ ስጀምር ከፍተኛ ፉክክር በታየበት የመጨረሻ ቀን የወንዶች 5000ሜ. የአለም ከ20 አመት በታች ሻምፒዮና የ3000ሜ የብር ሜዳልያ አሸናፊው አሊ አብዱልመና 13፡45.0 በሆነ ሰዓት ከጥላሁን ሀይሌ፣ ጌትነት ዋለ እና ዮሚፍ ቀጄልቻ ቀድሞ አሸናፊ ሆኗል፡፡ የፉክክሩ አካል የነበረው እና የርቀቱ የወቅቱ የአለም ሻምፒዮን ሙክታር እድሪስ ስድስተኛ ወጥቷል። 

ከ20 ዓመት በታች የ3000ሜ የአለም ሻምፒዮኑ ታደሰ ወርቁ በ28፡12.0 የወንዶች 10,000ሜ. ሻምፒዮን ሲሆን በ1996 ዓ.ም. በአትሌት ስለሺ ስህን ተመዝግቦ የነበረውን 28፡16.23 የሆነ የሻምፒዮናው ሪኮርድ ለማሻሻልም በቅቷል፡፡ በ10 ሺህ ሜትር የሴቶች ፉክክር ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር በቀዳሚነት የጨረሰችበት 31፡21.5 የሆነ ሰዓት አዲስ የሻምፒዮንሺፕ ሪኮርድ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በርቀቱ የከዚህ ቀደሙ ሪኮርድ  ለተሰንበት ግደይ ከሶስት ዓመት በፊት ያስመዘገበችው 32፡10.13 የሆነ ሰዓት ነበር፡፡

ሳሙኤል ፍሬው በዘንድሮ የወንዶች 3000ሜ. መሰናክል አፈፃፀም ከአለም ሁለተኛው ፈጣን በሆነ 8፡22.5 ሰዓት አሸናፊ ሲሆን ጌትነት ዋለ ከአራት ዓመት በፊት አስመዝግቦት የነበረውን 8፡28.98 የነበረ የሻምፒዮናው ሪኮርድም አሻሽሏል፡፡ በሴቶች 3000ሜ. መሰናክል ከ800ሜ ወደ ረጅም ርቀት የተሸጋገረችው ወርቅውሃ ጌታቸው በ9፡41.8 ሰዓት መቅደስ አበበን (9:43.8) በማስከትል በአሸናፊነት አጠናቃለች። 

አድሃና ካህሳይ (3:51.0) የወንዶች 1500ሜ ፉክክሩን በበላይት ሲያጠናቅቅ በሴቶች 1500 ሜ አያል ዳኛቸው (4:10.0) ተጠባቂዋ ዳዊት ስዩምን (4:11.1) በመቅደም በአንደኛነት አጠናቃለች። በ800ሜ. ወንዶች ቶሌሳ ቦደና (1:47.1) በሴቶች ወርቅነሽ መሰለ (2:02.1) አሸናፊ ሆነዋል።
ዮብሰን ብሩ በ400ሜ/400ሜ መሰናክል (45.9/50.5) ድርብ ድል ሲቀዳጅ፣ በወንዶች ጦር ውርወራ ኡታጌ ኡባንግ ብሔራዊ ሪኮርድ በሆነ 73.28ሜ. አሸንፏል፡፡ የኋልዬ በለጠው እና ዮሃንስ አልጋው በእርምጃ ሩጫ የሻምፒዮንነት ክብርን ተቀዳጅተዋል።

ጥቂት አስተያየቶች፡-
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪ እንደሆነ እና ለዕድገቱ እንደሚቆረቆር ሰው በብሔራዊ ሻምፒዮናው ላይ ስለተመለከትኳቸው አዎንታዊ እና አሉታዊ ጎኖች ጥቂት አስተያየቶቼን እንደሚከተለው አስቀምጣለሁ፡-

አዎንታዊ ጎኖች
• ባለው ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ሊገጥሙ የሚችሉትን ተግዳሮቶች በሙሉ በመቋቋም ፌዴሬሽኑ ውድድሩን ከአዲስ አበባ ውጭ አካሂዶ በሰላም ማጠናቀቅ መቻሉ አንደኛው ስኬቱ ነው፡፡

• በሻምፒዮናው ላይ ጥቂት የማይባሉ ታዋቂ አትሌቶች በሀገሪቱ ትልቁ የአትሌቲክስ ፉክክር ላይ ተሳታፊ ሆነው ሲወዳደሩ መመልከት የተቻለ ሲሆን በተለይም በወንዶች 5000 ሜትር ፍፃሜ ላይ የታየው የኮከብ አትሌቶች ፉክክር ልዩ ነበር፡፡

• በውድድሩ ወቅት ለአትሌቲክስ ዳኞች የብቃት ማሻሻያ ስልጠና መሰጠቱም የውድድሩን ጥራት ለማሳደግ የሚረዳ እንደመሆኑ እሰየው የሚባል ነው፡፡
 
• እንደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያሉት ክለቦች ለአትሌቲክስ ስፖርት የበለጠ ትኩረት በመስጠትና ተጠናክሮ በመቅረብ ከዚህ ቀደም በጠንካራነታቸው ከሚታወቁት መከላከያ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የቅርብ ተፎካካሪ ሆነው መታየት፤ የኦሮሚያ ክልል፣ ደቡብ ፖሊስ እና ሲዳማ ቡና ክለብ አትሌቶችም ጠንካራ ተሳትፎ ሳይዘነጋ የሻምፒዮናው ፉክክር ድምቀት ነበሩ፡፡  
• የአንዳንዶቹ ተገቢነት አጠያያቂ ቢሆንም ብዛት ያላቸው የሻምፒዮናው ሪኮርዶች የተሻሻሉበት ውድድርም ነበር፡፡ 

አሉታዊ ጎኖች
• የሀገሪቱ ትልቁ የአትሌቲክስ ውድድር ውጤት አሁንም በኤሌክትሮኒክስ የሰዓት መቆጣጠሪያ የማይደገፍ መሆኑ በተለይም በአጭር ርቀት እና በሜዳ ላይ ተግባራት ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች ልፋት ተገቢውን እውቅና እንዳያገኝ እያደረገ ይገኛል፡፡ የሻምፒዮናውን ውጤቶች በዘመናዊ እና ዓለም አቀፉን መለኪያ በሚያሟላ መልኩ አለመያዝ በአህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ ለተሳትፎ የሚያበቁ ውጤቶችን በማስመዝገቡ ረገድ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑ ከግምት ውስጥ ገብቶ አሁንም መፍትሄ ያልተበጀለት ጉዳይ ነው፡፡ 
 
• የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ወደ ሚዲያ/ለአጠቃላዩ ሕዝብ የሚያስተላልፈው የመጀመሪያዎቹን ሶስት ደረጃዎች ይዘው የሚያጠናቅቁ አትሌቶችን ውጤት ብቻ መሆኑ አወዳዳሪው አካል የሚያደርገውን የራሱን ውድድርም ሆነ አትሌቶቹ የለፉበትን ውጤት ከማስተዋወቅ አኳያ በቂ አይደለም፡፡
  
• በወንዶች የጦር ውርወራ እና የሴቶች ምርኩዝ ዝላይ ብሔራዊ ሪኮርዶች እንደተመዘገቡ ይታመናል፤ በሴቶች 100ሜ መሰናክል እና የወንዶች 400ሜ መሰናክል የተመዘገቡት ሰዓቶችም የምንግዜውም ፈጣን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ውድድሩ በኤሌክትሮኒክስ ታይሚንግ ያልተደገፈ እና የንፋስ ንባብ ያልነበረው መሆኑ ውጤቶቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ነው።

• በ20 ኪ.ሜ የእርምጃ ውድድር ላይ በሁለቱም ፆታዎች የተመዘገቡት ሰዓቶች ከሚጠበቀው በላይ እጅግ በጣም ፈጣን እና እውነታዊ አለመምሰላቸው በውድድሩ ላይ የተፈጠረ አንዳች ስህተት መኖሩን የሚያመላክቱ መሆኑ፡፡ እንዲህ አይነት ለማመን የሚከብዱ እና ጥርጣሬን የሚፈጥሩ አይነት ውጤቶች ሲመዘገቡም የተፈጠረ ስህተት መኖር አለመኖሩን ለማጣራት አለመሞከሩ፡፡
     
• የሴቶች 10 ኪሎ ሜትር ውድድር ላይ ለውድድር የማይፈቀድ የጎዳና ላይ መሮጫ ጫማን በመጠቀም የተመዘገበ ውጤት በሪኮርድነት ጭምር ተይዞ መፅደቁ። ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከተከለከሉ ጫማዎች ጋር የተያያዙ ዓለም አቀፍ ሕገ ደንቦችን ማወቅና መተግበር ቢገባውም በሴቶች 10 ሺህ ሜትር ውድድር ላይ የተከሰተው ነገር የውድድር ሕገ ደንቦቹ መረጃ በፌዴሬሽኑ ውስጥ በትክክል የተሰራጩ እንዳልሆነ የሚያመላከት ነው፡፡  

• በሴቶች 1500 ሜትር የግማሽ ፍፃሜ ውድድር ላይ አትሌት ዳዊት ስዩም የሻምፒዮናውን ሪኮርድ ያሻሻለችበት ውጤት እንደተመዘገበ በውድድሩ ወቅት በተደጋጋሚ ሲነገር ከተደመጠ በኋላ ግልፅ ባልተደረገ ምክንያት ውጤቱ በሐዋሳው ውድድር ላይ ተሻሻሉ ከተባሉት የሻምፒዮናው አዲስ ሪኮርዶች ዝርዝር ውስጥ ሳይካተት መቅረቱም የፌዴሬሽኑን ግልፀኝነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚከት ነው፡፡

ከላይ የተዘረዘሩት አዎንታዊ እና አሉታዊ ጎኖች ለረጅም ግዜ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ስፖርት እንቅስቃሴዎች በቅርበት ከመከታተሌ አንፃር በራሴ እይታ ያስቀመጥኳቸው እንደመሆናቸው አንዳንዶቹ ሀሳቦች አከራካሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሆኖም የውድድር ደንቦችን በአግባቡ ከማስፈፀም አኳያ በታዩት ክፍተቶች ዙሪያ ምንም የሚያከራክር ጉዳይ ስለሌለ በወቅታዊ የውድድር ደንቦች ዙሪያ የግንዛቤ እጥረት ላለባቸው የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት በሙሉ አስፈላጊውን ገለፃ እና ትምህርት መስጠት የፌዴሬሽኑ ኃላፊነት ነው፡፡ ከውድድር ጋር የተያያዙ ደንቦችን ከመጣስ አኳያ በሀገር ውስጥ በሚደረጉ ውድድሮች እንደቀላል ነገር የሚታለፉ ጉዳዮች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይም ተደግመው እንደግል አትሌቶችን እንደቡድን ሀገርን ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍሉ ይችላሉና አስፈላጊው ጥንቃቄ ቢደረግ መልካም ነው፡፡ ባለፈው መስከረም ወር በቪየና ሲቲ ማራቶን ውድድሩን በአሸናፊነት ጨርሶ የነበረው ኢትዮጵያዊው ደራራ ሁሪሳ የገጠመውን አንዘንጋው! 

ሀገራችን ኢትዮጵያን በመልካም ጎኑ ስሟ እንዲነሳ በሚያደርገው እና በትልልቅ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ የኩራታችን ምንጭ በሆነው የአትሌቲክስ ስፖርት እንደጎረቤታችን ኬንያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ የብቃት ደረጃ ላይ ደርሰን ማየት የዘወትር ምኞቴ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንም የውድድሮቹን ጥራት ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራ ተስፋ አደርጋለሁ።      
      
የ10,000ሜ. አሸናፊ የሆነችው ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር (Photo by EAF)

በመጨረሻም በሀዋሳ በተካሄደው 51ኛዉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከመሮጫ ጫማ ጋር የተያያዙ ደንቦችን በማስከበሩ ረገድ የተፈጠረውን ክፍተት እንደማስተማሪያ ብንጠቀምበት በሚል የሚከተለውን ለማለት ወደድኩ፡-

የመሮጫ ጫማ ደንቦች ለትራክ ውድድር

64 ደቂቃ ከ14 ሰከንድ በሆነ ሰዓት የዘንድሮ የራስ አል ካይማህ የግማሽ ማራቶን ውድድር አሸናፊ የሆነችው ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር በሐዋሳ በተከናወነው 51ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ 31 ደቂቃ ከ21.5 ሰከንድ  በመግባት የ10,000ሜ. አሸናፊ ሆናለች፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ዓለም አቀፉን ደንብ ከግምት ባላስገባ ሁኔታ ውጤቱን በአዲስ የሻምፒዮንሺፕ ሪኮርድነት ጭምር አፅድቆት አልፏል፡፡ ይሁን እንጂ መጋቢት 20/2014 በተደረገው የሴቶች የፍፃሜ ፉክክር ላይ በኢትዮጵያ ምድር የተመዘገበ የምንግዜውም ፈጣን የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ሰዓት የሆነው ውጤት በአለም አትሌቲክስ ዘንድ እውቅና ሊሰጠው የማይችል ነው።

ለምን?

አትሌቷ የሶል ውፍረቱ 40ሚሜ የሆነ ዙምኤክስ ቬፐርፍላይ (ZoomX Vaporfly) ጫማ አድርጋ በመወዳደሯ ምክንያት።

ደንቡ ምን ይላል?

በትራክ ውድድሮች ላይ የሚፈቀደው ከፍተኛው የሶል ውፍረት ፡-
– 20ሚሜ ከ 800ሜ በታች ለሆኑ ውድድሮች እና ለሁሉም የሜዳ ላይ ተግባራት (ከስሉስ ዝላይ በስተቀር)

– 25ሚሜ ለ800ሜ እና ከዛ በላይ ለሆኑ ውድድሮች እንዲሁም ለስሉስ ዝላይ

– 40ሚሜ ለትራክ ላይ የእርምጃ ውድድሮች

እነዚህ ደንቦች እ.ኤ.አ. እስከ ኦክቶበር 31, 2024 ድረስ በሥራ ላይ ይውላሉ። ከኖቬምበር 1 ቀን 2024 ጀምሮ ለ800ሜ እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ውድድሮች እንዲሁም ለስሉስ ዝላይ የሚፈቀደው ከፍተኛ የሶል ውፍረትም ወደ 20 ሚሜ ዝቅ የሚል ይሆናል።

የትራክ ላይ መወዳደሪያ ስፓይክ ጫማ ከሌለኝስ?  

ደንቡ የጎዳና ላይ የመሮጫ ጫማዎች በትራክ ላይ እንዳይደረጉ አይከለክልም ነገር ግን በ25 ሚሊ ሜትሩ ገደብ ምክንያት 30 ሚሜ ወይም 40 ሚሜ የሆኑ የጎዳና ላይ መሮጫ ጫማዎች በትራክ ውድድሮች ላይ እንዲደረጉ አይፈቅድም፡፡

ለበለጠ መረጃ :-
https://www.worldathletics.org/news/press-releases/new-athletic-shoe-regulations-approved-2022

Continue Reading

Articles

የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ተሳትፎ ድህረ ምልከታ

Published

on

Medal Winners

በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በወረቀት ደረጃ ከውድድሩ መጀመር በፊት ቡድኑ ባመዛኙ በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኙ ወጣት አትሌቶችን ስላካተተ ቢያንስ የለመድናቸውን ሁለት ወይም ሶስት የወርቅ ሜዳልያ ድሎች እንደማያሳጣን ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ ሆኖም የሜዳ ላይ ውጤቱ እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ኢትዮጵያ በውጤታማነቷ በምትታወቅበት የአትሌቲክስ ፉክክር በአንድ የወርቅ፣ አንድ የብር፣ እና ሁለት የነሐስ በድምሩ በአራት ሜዳልያዎች ከዓለም 14ኛ ከአፍሪካ 3ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች፡፡ ይህም ሁሌም ለአፍሪካ የበላይነት ከምንፎካከራት ኬንያ ጋር ያለን ልዩነት ይበልጥ እንዲሰፋ አድጎታል፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ሌላኛዋ የምስራቅ አፍሪካ ተቀናቃኛችን እየሆነች ከመጣችው ኡጋንዳም አንሰን እንድንገኝ አድርጎናል፡፡ የቶኪዮ ኦሊምፒክ በአትሌቲክሱ ከ1992ቱ የባርሴሎና ኦሊምፒክ ወዲህ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሜዳልያ ስኬት ያስመዘገበችበትም ሆኖ አልፏል፡፡

አሉታዊ ጎኖች
ቶኪዮ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤታማነት ፈር ቀዳጅ የሆነው ታላቁ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ በ1964 ዓ.ም. በተከታታይ ሁለተኛ የኦሊምፒክ ማራቶን ድሉን የተቀዳጀባት ከተማ ናት፡፡ እናም በቶኪዮ ከተማ በተከናወነው የኦሊምፒክ ውድድር የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የሱን ክብር የሚያጎሉባቸውን ነገሮች ያደርጋሉ ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ የሆኑት ነገሮች ግን በተለይ በቡድኑ አስተዳዳሪዎች በኩል ፍፁም ኃላፊነት የጎደለውና ከጠበቅኩት በተቃራኒው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከአትሌቶች ምርጫ አንስቶ በቡድኑ የዝግጅት ወቅት በተካረረ ውዝግብ ውስጥ ነበር የከረሙት፡፡ የኦሊምፒክ ቡድኑን የማዘጋጀት እና የመምራት የጋራ ኃላፊነት የነበረባቸው ሁለቱ አካላት ይባስ ብለው ውዝግቡን ቶኪዮ ድረስ ይዘውት ሄደዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ሁለቱን አካላት በማቀራረብ በትልቁ ውድድር ላይ ያለንን ተሳትፎ እንከን አልባ ማድግ የሚጠበቅባቸውም ተመልካች ከመሆን የዘለለ ሚና አልነበራቸውም። የውዝግቡ አሉታዊ ትሩፋት በአትሌቶች ስነልቦና እና በአጠቃላይ የቡድኑ ውጤት ላይ የበኩሉን ተፅዕኖ ሳያሳርፍ እንዳላለፈ አያጠራጥርም፡፡

እንደ አለመታደል ሆኖ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያን ልዑካን የመምራት ትልቁ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ኃላፊነት የጎደላቸው ነበሩ። የስፖርቱ አስተዳደሪዎች ትላልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በመጡ ቁጥር በአትሌቶች ምርጫ ዙሪያ የነበረውን ውዝግብ እንዲያቆሙልን እመኝ ነበር። ጭራሽ እራሳቸው ችግር ፈጣሪ ሆነው መገኘታቸው አስደንጋጭ እና አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በመሮጫ መም ወይም በጎዳና ላይ በሚደረጉ ውድድሮች መሸነፍን በስፖርቱ ውስጥ ማሸነፍ እና መሸነፍ ያሉ የነበሩ እና ወደፊትም የሚኖሩ ነገሮች ስለሆኑ በፀጋ መቀበል ይቻላል፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑ የስነልቦና ጥንካሬን ሊፈጥሩላቸው የሚገቡ ኃላፊዎች የእርስ በርስ ሽኩቻ ተቃራኒውን አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳርፍ ማየት ግን ፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ ለነገሩ ከስፖርቱ እድገት ይልቅ የፖለቲካ ግዴታቸው የሚያስጨንቃቸው የስፖርት አመራሮች በበዙባት ሀገር ስፖርቱ እንዲህ የማንም መጫወቻ ሲሆን ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡  

የስፖርት አመራሮች ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ሆነው ትኩረታቸውን ስፖርቱን በማስፋፋቱ እና ማሳደጉ ላይ አድርገው የሚሰሩ ስለስፖርቱም በቂ እውቀት እና ፍቅሩ ያላቸው ቢሆኑ መልካም ነው፡፡ ለቦታው በሚመጥን እና ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት በሚችል የስፖርት አመራር የሚመራ የስፖርት ተቋምን መገንባት በተመሳሳይ ሰዓት የሀገር ግንባታን የሚደግፉ ሶስት ነገሮችን ስኬታማ ያደርጋል፡፡ በስፖርት ጤናውን የሚጠብቅ ማሕበረሰብ በመፍጠር በጤናው ሴክተር ላይ የሚኖረውን ጫና ይቀንሳል፣ በሀገር ገፅታ ግንባታ እና በኢኮኖሚው ዕድገት ላይም የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ በቶኪዮ ላይ የተመለከትናቸው የሀገርን ክብር ዝቅ ያደረጉ ግዴለሽነቶች ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊታዩና አጥፊዎቹ ሊጠየቁበት ይገባል፡፡ በመጪዎቹ ዓመታት በሚጠብቁን ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይም የቶኪዮ ኦሊምፒኩን አይነት ሀፍረት እንዳይገጥመን ከወዲሁ ለችግሮቹ መፍትሔ መፈለግ አለበት፡፡

ባለፉት ዓመታት ኦሊምፒክ በመጣ ቁጥር በልዑካን ቡድኑ ውስጥ እየተካተቱ በሕዝብ ገንዘብ የሚዝናኑት የኦሊምፒክ ቱሪስቶች ጉዳይ ዘንድሮም ያልተቀረፈ ችግር ሆኖ ተስተውሏል፡፡ ከሌላው ግዜ በተለየ መልኩ ተጠባባቂ አትሌቶችን ይዞ መጓዝ ይጠይቅ በነበረው ውድድር ላይ አትሌቶቹን ትቶ ምንም የማይሰሩ ሰዎችን ይዞ መሄድ ትልቅ ቀልድ ነው፡፡  

ከሜዳ ውጭ የነበረው ውዝግብ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል የነበረ መሆኑ በሜዳ ላይ የነበሩብንን ድክመቶች ሊያስረሳንም አይገባም፡፡ ስድስት የጎዳና ላይ ተወዳደሪዎቻችን እና አንድ የመም ተወዳዳሪ ውድድራቸውን ማቋረጣቸው በቶኪዮ ከታዩት ደካማ ጎኖቻችን መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ ችግሩ በዚህ ምክንያት ነው የተከሰተው ብሎ ለይቶ ለመናገር ባይቻልም ብዙ ግዜ ሲፈትነን ለሚስተዋለው የሞቃታማ ቦታ ውድድር የምናደርጋቸው ዝግጅቶችን መለስ ብሎ መመልከትን የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ የተጎዳች አትሌትን ወደውድድር እንድትገባ ማድረግ እና በሁለት ደቂቃ ውስጥ ለማቋረጥ መገደዷም የአትሌቶች የጤና ክትትል ላይ ክፍተት እንዳለ የጠቆመን ክስተት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ወደውድድር ስፍራው ካቀናበት ግዜ ጀምሮ በቶኪዮ ምንም አይነት ቡድኑን የተመለከቱ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ወይም ፕሬስ ሪሊዞች አልነበሩም፡፡ ይህም እንደተለመደው የሕብረተሰቡን እና የመገናኛ ብዙሀንን ስለቡድኑ ቀጥተኛ መረጃ የማግኘት መብት የገደበ ነበር፡፡ ጋዜጠኞችም ሚዛናዊ ሆኖ ከመዘገብ ይልቅ ጎራ ለይተው ቃላት መወራወራቸው የህዝብን ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት የነፈገ ነው፡፡ 

አዎንታዊ ጎኖች
ሰለሞን ባረጋ በወንዶች 10,000 ሜትር ወርቅ፣ ለሜቻ ግርማ በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ብር፣ ጉዳፍ ፀጋዬ በሴቶች 5000 ሜትር ነሐስ፣ እና ለተሰንበት ግደይ በሴቶች 10,000 ሜትር ነሐስ ማስመዝገብ መቻላቸው የሚደነቅ ስኬት ነው፡፡

የመጪው ትውልድ አካል የሆኑት ተስፈኞቹ መቅደስ አበበ፣ ፍሬወይኒ ሀይሉ፣ በሪሁ አረጋዊ እና ጌትነት ዋለን ጨምሮ አምስት አትሌቶች ለሜዳሊያ የቀረበ የአራተኛነት ደረጃን ይዘው ማጠናቀቅ መቻላቸውም መልካም ነው፡፡ በተለይ ወጣቶቹ ያስመዘገቡት ውጤት በመጪዎቹ ዓመታት ተገቢውን ድጋፍ ካገኙ የምንጓጓለትን ድል ሊያስገኙልን እንደሚችሉ ያመላከተን ነው፡፡

የሀብታም አለሙ በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በሴቶች 800 ሜትር ለመጀመሪያ ግዜ ለፍፃሜ ተወዳዳሪነት መብቃት ምንም እንኳ በፍፃሜው የሜዳልያ ድል ባይቀናትም በአዎንታዊ ጎን ሊጠቀስ የሚችል ስኬት ነው፡፡

ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃን ይዘው ላጠናቀቁ አትሌቶች በሚሰጥ ነጥብ ድምር መሰረት በወጣው የነጥብ (ፕሌስመንት) ደረጃ ሰንጠረዥ ላይ በ64 ነጥብ ዘጠነኛ ሆነን ማጠናቀቃችንም እሰየው የሚያስብል ነው፡፡

በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከአራተኛ እስከ ስምንተኛ ባሉት ደረጃዎች ውስጥ አጠናቀው ነጥብ ያስገኙ እና የዲፕሎማ ተሸላሚ የሆኑት አትሌቶች፡-
4ኛ – ፍሬወይኒ ሀይሉ – በሴቶች 1500 ሜትር
4ኛ – መቅደስ አበበ – በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል
4ኛ – ሮዛ ደረጀ – በሴቶች ማራቶን
4ኛ – በሪሁ አረጋዊ – በወንዶች 10,000 ሜትር
4ኛ – ጌትነት ዋለ – በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል
5ኛ – እጅጋየሁ ታዬ – በሴቶች 5000 ሜትር
6ኛ – ሀብታም አለሙ – በሴቶች 800 ሜትር
6ኛ – ሰንበሬ ተፈሪ – በሴቶች 5000 ሜትር
8ኛ – ዮሚፍ ቀጄልቻ – በወንዶች 10,000 ሜትር
8ኛ – ዘርፌ ወንድማገኝ – በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል

  • የአትሌቲክስ የነጥብ ደረጃ ሰንጠረዥ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ባሉት ደረጃዎች ውስጥ የሚያጠናቅቁ አትሌቶች በሚያስመዘግቡት ነጥብ ድምር መሰረት የሚወጣ ሲሆን የነጥብ አሰጣጡም ለአንደኛ ደረጃ 8 ነጥብ፣ ለሁለተኛ ደረጃ 7 ነጥብ፣ ለሶስተኛ ደረጃ 6 ነጥብ፣ ለአራተኛ ደረጃ 5 ነጥብ፣ ለአምስተኛ ደረጃ 4 ነጥብ፣ ለስድስተኛ ደረጃ 3 ነጥብ፣ ለሰባተኛ ደረጃ 2 ነጥብ፣ እና ለስምንተኛ ደረጃ 1 ነጥብ ነው።

ከፊታችን ምን  እየጠበቀን ነው? ምንስ እናድርግ?
ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፉ ወረርሺኝ ምክንያት ትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለሌላ ግዜ እንዲተላለፉ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ሌላ አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ቀጣዮቹ አራት ዓመታት በተከታታይ በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች የሚካሄዱባቸው ይሆናሉ፡፡ በ2022 የዓለም ሻምፒዮና፣ በ2023 የዓለም ሻምፒዮና፣ በ2024 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች፣ እና በ2025 የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ይኖራሉ፡፡ በቀጣዩ ዓመት በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ከሐምሌ 8 – 17/2014 በዩናይትድ ስቴትስ ኦሪጎን የሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዘጋጆች ሙሉ የውድድሩን ፕሮግራም፣ የማራቶን እና የእርምጃ ውድድሮች የሚካሄዱባቸውን ቦታዎች በትላንትናው ዕለት ይፋ አድርገዋል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናውን ውድድር በኃላፊነት የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ከወዲሁ ለዛ ውድድር ተሳትፎ የሚጠበቅበትን አቅዶ መንቀሳቀስ ይኖበርታል፡፡

ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጭቅጭቆችን ለማስቀረት ከወዲሁ ሁሉም አትሌቶች አውቀውት በውስጡ የሚያልፉበትን ገዢ የሆነ የመምረጫ መስፈርት ማዘጋጀት ቀዳሚው ተግባር መሆን አለበት፡፡ የመምረጫ መስፈርት ሁልግዜም በግላዊ ምልከታ እና ፍላጎቶች ላይ በሚመሰረት ምክንያት አነጋጋሪ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ቢሆንም ባለድርሻ አካላቱን በሙሉ ባሳተፈ መልኩ ውይይት ተደርጎበት ቢወጣ ሁሉንም ገዢ እና ከጭቅጭቅ የፀዳ ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህ ላይ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከተከሰቱት ሁኔታዎች አንፃር የሌሎች ሀገሮችንም ተሞክሮዎች በመዳሰስ ነገሩን ሰፋ አድርጎ መመልከት ቢቻል ጥሩ ነው፡፡ ትልልቅ ውድድሮች በመጡ ቁጥር በተደጋጋሚ እንደታዘብነው አንዳንድ አትሌቶች በቡድኑ ውስጥ ለመካተት የሚያደርጉትን ተገቢ ያልሆነ ሙከራም ማቆም አለባቸው፡፡ ከፋም ለማም ስፖርቱን እንዲመራ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም የሚያወጣቸውን መስፈርቶች ማክበርና በዛ ውስጥ ተመራጭ ለመሆን መሞከር ግድ እንደሚላቸውም መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ማኔጀሮች እና አሰልጣኞች በተለይ በማራቶን የራሳቸውን አትሌት ለማስመረጥ የሚያደርጓቸው አላስፈላጊ ግፊቶችም ሊያቆሙ ይገባል፡፡

ለውድድሮች የምናደርጋቸውን ዝግጅቶች ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ከውድድሮች በኋላ መገምገም እና መታረም ያለባቸው ነገሮች ካሉ ማረም፡፡ ከፍተኛ ሙቀት በነበረባቸው በለንደን 2012 ኦሊምፒክ ሶስቱም የወንዶች ማራቶን ተወዳዳሪዎቻችን፣ በሞስኮ 2013 የዓለም ሻምፒዮና ሁለቱ የሴቶች ማራቶን ተወዳዳሪዎቻችን፣ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ አምስት የማራቶን (ሶስቱም ወንዶች እና ሁለት ሴቶች) ተወዳዳሪዎቻችን እንዲሁም የሴቶች እርምጃ ተወዳዳሪያችን ለማቋረጥ መገደዳቸውን አስተውለናል፡፡ ስለዚህ በጎዳና ላይ ውድድሮች ከባድ ሙቀት ለሚኖርባቸው ቦታዎች እንዴት መዘጋጀት አለብን የሚለው ጉዳይም በደንብ ሊታይ የሚገባው ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ የመም (ትራክ) ተወዳዳሪ አትሌቶቻችን የውድድር ዓመቱ ሲጀምር ድንቅ ብቃታቸውን ያሳዩን እና ወደትልቅ ውድድር ሲቃረቡ አቋማቸው እየወረደ ይመጣል፡፡ አሰልጣኞቻቸው ለእነዚህ አይነቶቹ አትሌቶች ወደትልቅ ውድድር ሲቃረቡ ብቃታቸውን እያሳደጉ እንዲሄዱ የሚረዳቸውን የልምምድ ፕሮግራም ቢያዘጋጁላቸው መልካም ነው፡፡ በመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ላይ በተለይ በወንዶች አሁንም በከፍተኛ ደረጃ የሚፎካከሩ አትሌቶችን ለማፍራት ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል፡፡

Continue Reading

Trending