Connect with us

Articles

በገንዘብ አቅርቦት ጥያቄ ውስጥ የሚዋልለው ኢኮኖሚ

Published

on

55d19fb9c2e729f68455beebbbe6de8b_XL

09 FEBRUARY 2014 ተጻፈ በ 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ አስገራሚ ነገር መታየት ጀምሯል፡፡ በርካቶች በደረቅ ቼክ ምክንያት ወደ እሥር ቤት የሚወርዱት የእውነትም በደረቅ ቼክ አጭበርባሪ ለመሆን ተነሳስተውና ሆነው በመገኘታቸው እንዳልሆነ የዚሁ ጉዳይ ሰለባ የነበሩ ይገልጻሉ፡፡ በየፖሊስ ጣቢያውም እንዲህ ያለው ነገር እየተበራከተ መምጣቱ እየታየ ነው፡፡

በቅርቡ አዲስ አድማስ በደረቅ ቼክ ላይ ያስነበበው ዜና ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች በደረቅ ቼክ ሰበብ እስር ቤት ከሚገቡባቸው ምክንያቶች አንዱ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ገና ለገና ከውጭ ለሚያመጡት ዕቃ ቀብድና ዱቤ ተቀብለው ዕቃው ሲመጣ ሊከፍሉ ተስማምተው ባንክ የነበራቸውን ገንዘብ አውጥተው ዕቃ የሚያስመጡ ናቸው፡፡ በመሆኑም ዕቃቸው መጥቶ ወደ ገንዘብነት እስኪቀየር ድረስ ገንዘብ ከተቀበሉት ሰው ባንክ ያልገባው ገንዘብ እስኪገባ ድረስ ታግሶ በመጠበቅ ሒሳብ መዝገባቸው ውስጥ ከገባ በኋላ እንዲወስድ ማድረግ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በነጋዴዎች መካከል የተለመደ የዕለት ተግባር ነው፡፡

በዚህ መካከል ግን ገንዘብ ሲያጥር፣ በተባለው ቀን አስገባለሁና እስከዚያ ድረስ ደረቁን ቼክ ይዘህ ጠብቅ የተባለው ነጋዴ ዕምነት እያጣ ወይም እየተጭበረበረ ይመስለውና ባንክ ቤት ሄዶ አቤት ይላል፡፡ ቼክ የተጻፈለት ነጋዴም የተባለው ገንዘብ ባለመኖሩ ምክንያት ቼኩን የጻፈው ሰው ላይ ክስ በመመሥረት የሕግ ጥያቄ ያቀርባል፡፡ ቼክ ሰጪው ለእሥር ይዳረጋል፡፡ እርግጥ የተመሰከረላቸውና የሰው ገንዘብ ይዘው እብስ የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፣ በገንዘብ እጦት ሳቢያ፣ ያሰቡት እንዳላሰቡት እየሆነ በጻፉት ቼክ የሚታሰሩ ግን እየተበራከቱ መምጣታቸው እውነት ነው፡፡

ለመሆኑ ኢኮኖሚው ውስጥ ገንዘብ አለ ወይ?

ይህ ጥያቄ የብዙ ነጋዴዎች፣ የሥራ ተቋራጮችና የሌሎችም ዘርፎች የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኗል፡፡ የገንዘብ እጥረት አለ ወይ ለሚለው ጥያቄ ምላሹ ሁለት ሆኖ ይታያል፡፡ አለም የለምም፡፡ አምራቾችና ምሁራን የገንዘብ ዕጥረቱ አለ በሚለው ይስማማሉ፡፡ መንግሥት በበኩሉ የገንዘብ ችግር የለም እያለ ይገኛል፡፡ ባንኮች የገንዘብ እጥረት እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ አምራቾችም ገንዘብ ለማግኘት መቸገራቸውን ይገልጻሉ፡፡ የገንዘብ አቅርቦት ችግር መኖሩን ኢኮኖሚስቶችም የሚስማሙበት ነጥብ ነው፡፡ ይብሱን የገንዘብ ዕጥረቱን መንግሥት እንደፈጠረው፣ ሊፈጠር የቻለውም ከሚከተላቸው የገንዘብና የፊስካል ፖሊሲዎች አኳያ እንደሆነ፣ በተለይ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ሲል የወሰደው እርምጃ ሊሆን እንደሚችል ይተነትናሉ፡፡ ወደ ቀደመው ነገር ስንመለስ የገንዘብ እጥረት ጥያቄ እየተነሳ ነው ብለናልና ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እንጀምር፡፡

የአምራቾች የገንዘብ እጦት 

በቅርቡ ለፓርላማ ጥያቄያቸውን ያቀረቡ 36 ኩባንያዎች ገንዘብ የለም ለሚለው መነሻ መንደርደሪያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የመከላከያው ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ)፣ ማሩ፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ፣ አምቼ፣ በላይአብ ሞተርስ፣ ሊፋን የተባሉትን ኩባንያዎች ጨምሮ 36 የአገሪቱ ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያዎች፣ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥር በሚገኘው ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና በሜቴክ በኩል፣ ለፓርላማው ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ካቀረቧቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ውስጥ የገንዘብ እጥረት ይጠቀሳል፡፡

ኩባንያዎቹ ፓርላማው ፊት ያቀረቡት ሰንድ ውስጥ ከቀረቡት በርካታ ጥያቄዎች መካከል፣ ከባንክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በሙሉ አቅማቸው ለመሥራት የሚያስችል የሥራ ማስኬጃ ብድር ወይም ካፒታል ሊያገኙ አለመቻላቸው አንገብጋቢ ሆኖባቸዋል፡፡ በሚፈልጉት መጠንና ጊዜ ውስጥ የሚያስፈልጋቸውን ያህል ብድር ወይም ካፒታል ለሥራ ማስኬጃ አለማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ኩባንያዎቹ ከሆነ ከአምራች ኢንዱስትሪነታቸው አኳያ በሙሉ አቅማቸው ለመሥራት ከመንግሥትም ይሁን ከግል ባንኮች በቂ የብድርና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት አያገኙም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ተስኗቸዋል፡፡ ከውጭ የሚገቡ የጥሬ ዕቃዎችን ለማስገባት የባንክ መተማመኛ ሰነድ (ኤልሲ) በአስቸኳይ ስለማይከፈትላቸው፣ ጥሬ ዕቃዎቹ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት እጅግ ዘግይተው ሆኗል፡፡ ባንኮች ከውጭ ለሚገቡ ልዩ ልዩ ሸቀጦች ብድር የሚሰጡ በመሆኑ ተጠቃሚዎች ከአገር ውስጥ ምርት ይልቅ ከውጭ በሚገባው ላይ እንዲያዘነብሉ የሚያመቻች አካሄድ መፍጠራቸውን፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የሚሠሩት ሥራ ጫና ውስጥ መግባቱን፣ እነዚህ የአገር ውስጥ አምራቾች ለምርት ሥራቸው ምንም ዓይነት የማበረታቻ ድጋፍ እያገኙ አለመሆኑን በመግለጽ ለፓርላማው ተጠሪ ኮሚቴ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንም የበጀት እጥረት ውስጥ እንደሆነና ለመንገድ ሥራዎች የሚመደብለት ገንዘብ በቂ እንዳልሆነ ለፓርማላው አሳውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም ተጨማሪ በጀት እየተባለ ይለቀቅለት የነበረው ገንዘብም ቀርቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል ፓርላማ ቀርበው እንዳስረዱት፣ በተለይ ጥገና በሚያስፈልጋቸው የአገሪቱ መንገዶች ላይ የበጀት እጥረት አሳሳቢ እየሆነ ይገኛል፡፡ ከ200 ያላነሱ የመንገድ ፕሮጅክቶችን እያስኬደ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ በአሁኑ ወቅት ለተቋራጮች ያልከፈለው ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ እንደላበት አስታውቋል፡፡ በበጀት እጥረት ምክንያት ይህንን ዕዳ መክፈል እንዳልቻለም ይፋ አድርጓል፡፡

የባንኮች የገንዘብ ጥያቄ

በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የግል ባንኮች እየበዙ መምጣት፣ የመንግሥት ባንኮች የመስፋፋት ሒደት የባንክ ኢንዱትስሪውን ፉክክር እያበረታው መምጣቱ ይነገራል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻውን ከ750 በላይ ቅርንጫፎች በአገሪቱ መክፈቱ፣ በየከተማው ውስጥ ማስፋፋቱ፣ በአዲስ አበባ በየውስጣ ውስጡ ሳይቀር መንሰራፋቱ በግል ባንኮች ዘንድ ሥጋት ሆኗል፡፡

የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች መስፋፋት የግል ባንኮች ከዚህ ቀደም በቀላሉ ያገኙት የነበረውን ደንበኛ፣ በአሁኑ ጊዜ በአቅራቢያው ወደሚያገኘው ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ጎራ በማለት ገንዘብ ማስቀመጥን ስለሚመርጥ ሽሚያው የግል ባንኮችን አሳስቧቸዋል፡፡ በዚያም ላይ ንግድ ባንክ ለ40/60፣ ለ20/80 እና ለ10/90 የቤቶች ልማት የሚሰበስበው ገንዘብም እንዲሁ ሌሎቹ ባንኮች ከዚህ ቀደም ያገኙት የነበረውን ዓይነት ተቀማጭ እንዳያገኙ እየተሻማ መጥቷል ተብሎለታል፡፡ በዚያም ላይ እንደግል ባንኮች ንግድ ባንክ የ27 ከመቶ የቦንድ ግዥ የመግዛት ግዴታ ስላልተጣለበት ጭምር የውድድሩ ሜዳ ሰፍቶ እንደተለቀቀለት በመግለጽ የግል ባንኮች ይተቹታል፡፡

ዋናው ፈተና ግን በያመቱ ለመንግሥት የልማት ሥራዎች ከሚያበድሯት እያንዳንዷ ብድር ብሔራዊ ባንክ የ27 ከመቶ ተቆራጭ በማድረግ ቦንድ እንዲገዙ ማስገደዱ በብድር አሰጣጥ ላይ የተወሰነ ጫና መፍጠሩን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ አሁንም ጫናው መቀጠሉን የሚገልጹ የግል ባንክ ኃላፊዎች አሉ፡፡

‹‹ራስ ምታት ውስጥ ባይከተንም እንደቀድሞው ጥሩ እንቅስቃሴ የለም፡፡ የገንዘብ እጥረት አለ፤›› የሚሉት የባንክ ኃላፊዎች፣ ምንም እንኳ የ27 ከመቶ የቦንድ ግዥ አምናም ሲሠራበት የቆየ ቢሆንም፣ አዲስ ገንዘብ ወደ ባንኩ እስካልመጣ ድረስ፣ አምና ከሰጠው ብድር ላይ 27 ከመቶ ተቆርጦ የተሰጠበት ያው ብድር ዘንድሮ ተመላሽ ተደርጐ ለተበዳሪ ሲሰጥም፣ እንደገና ከዚያው ላይ 27 ከመቶ ይቆረጥለታል ማለት ነው፡፡ በምሳሌ ለማሳየት መቶ ብር ያበደረ ባንክ፣ ከዚህ ገንዘብ ላይ 27 ከመቶ አንስቶ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ያደርግና ቀሪውን ያበድራል፡፡ ይህ ሌላ ተቀማጭ አላገኘም ብለን ብናስብ፣ ከሚመለስለት ይኼው ብድር ላይ መቶ ብር ሲያበድር 27 ብር አንስቶለት አበድሮ ነበር፡፡ የሚመለስለት ብድር 73 ብር ይሆናል፡፡ ይኼንን ገንዘብ  እንደገና ለማደበር ሲፈልግም 27 ብር አሁንም ቆርጦ ማንሳት አለበት፡፡ ልብ መባል ያለበት ምሳሌው ብሔራዊ ባንክ የሚጠይቃቸው ሌሎች መሥፈርቶችን ሳይጨምር የቀረበ መሆኑ ነው፡፡ የተቀማጭ መጠባበቂያ መያዝ የመሳሰሉት ብድር ከመሰጠቱ በፊት የሚሟሉ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ ከእያንዳንዱ ብድር ላይ ተቆርጠው አስቀማጩ ገንዘቡን በጠየቀ ጊዜ እንዲሰጠው ለማስቻል የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ባንኮች አዳዲስ ተቀማጭ እስካላገኙ ድረስ፣ ያላቸውን ገንዘብ እያገላበጡ በሚያበደሩበት ወቅት ጫና ውስጥ የሚገቡት በዚህ የተነሳ ነው፡፡

ይህ ሥዕል የሚያሳየውና ባንኮችም እንደሚያብራሩት የገንዘብ እጥረት እንዳለባቸው ነው፡፡ ተበዳሪዎች በተለይ ተቋራጮችም ገንዘብ ማግኘት እንዳልቻሉ እየገለጹ ነው፡፡ የባንክ ብድር ማግኘት አልቻልንም እያሉ ነው፡፡ የአንድ ሚሊዮን ብር ብድር ለማግኘት አልቻልንም የሚሉ ቅሬታዎች እየተሰሙ ነው፡፡

የኢኮኖሚ ምሁራን ምን ይላሉ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑትና የኢኮኖሚክስ ምሁሩ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ፣ የገንዘብ እጥረት አጋጥሟል በሚለው የግል ባንኮችም ሆነ የነጋዴዎች አስተያየት ላይ ይስማማሉ፡፡ ባንኮች በሚያበድሩ ጊዜ ከየብድሩ የሚቆረጠው 27 ከመቶ ወደ መንግሥት ፕሮጀክቶች የሚሔድ በመሆኑ ብድሩን እንደሚያጣብበው ያብራራሉ፡፡ መንግሥት ዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር በገንዘብ ፖሊሲው የሚተገብረው ትልቁ ሥራ የገንዘብ አቅርቦቱን በመቆጣጠር እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ የአገሪቱ ባንኮች ‹‹በአብዛኛው ብድር ሲሰጡ የቆዩት ለቢሮ ኪራይ ለሚውሉ ሕንፃዎች መሥሪያ ወዘተ ነበር፡፡ አሁን ግን ለልማት አስተዋጽኦ ባላቸው ሥራዎች ላይ ገንዘቡ እንዲውል በመደረጉ የገንዘብ እጥረት መኖሩ የሚታመን ነገር ነው፡፡ የገንዘብ አቅርቦት ትልቅ እጥረት አለበት፤›› ብለዋል፡፡

የግል ባንኮች የ27 ከመቶ ቦንድ ግዥ ሲፈጽሙ ኖረዋል፡፡ ለገንዘብ እጥረቱ መኖር ይህ የቦንድ ግዥ አሁን ዛሬ ላይ እንዴት ምክንያት ሊሆን ይችላል ለሚለው ጥያቄ፣ ዶክተሩ የድምር ውጤት ተፅዕኖ ነው በሚል ምላሻቸውን መስጠት ይጀምራሉ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የግል ባንኮች ምንም ዓይነት ብድር እንዳይሰጡ ተከልክለው እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ አሁን እየተተገበረ ያለው የ27 ከመቶ ቦንድ ግዥ፣ የንግድ ባንክ መስፋፋትና የቤቶች ቁጠባ ፕሮግራም መምጣት፣ ሕዝቡ በሌሎች የግል ባንኮች ያስቀመጠውን ገንዘብ ወደ ንግድ ባንክ መውሰዱ የግል ባንኮች ላይ የገንዘብ እጥረት እንዲከሰት ሊያደርግ እንደሚችል ይስማማሉ፡፡

‹‹ኮንዶሚንየም ለመሥራት ወደ መንግሥት ኪስ የሚገቡ ገንዘቦች ናቸው፤›› ሲሉ የገለጹት ይህ የቤቶች ፕሮግራም፣ መንግሥት እንደሚለው ለልማት እስካዋለው ድረስ ገንዘቡ በገበያው ውስጥ የሚዘዋወር ነው፡፡ በእሳቸው ትንታኔ ገንዘቡ ከመንግሥት ወጣ ወይም ከግል ባንክ መውጣቱ አይደለም የሚያጨቃጭቀው ነጥብ፡፡ ዋናው ነገር መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ እየሰበሰበ መሆኑ መታወቁ ነው፡፡

መንግሥት ገንዘብ የሚሰበስበው ለልማት ሥራዎች ነው ከተባለ፣ እንደ ህዳሴው ግድብ ያለውን ለመገንባት የሚያወጣውን ወጪ የፊስካል ፖሊሲውን የሚመለከቱ ሲሆን፣ በገንዘብ ወይም ሞኒታሪ ፖሊሲው በኩል ሊታይ የሚችለው የ27 ከመቶ ቦንድ እየገዛችሁ ገንዘብ አምጡ ማለቱ ገንዘብ ከገበያው ውስጥ ለመሰብሰብ የሚሄድበትን የፖሊሲ መንገድ ያሳያል፡፡ በመሆኑም ‹‹መገመት የሚገባን ነገር የገንዘብ አቅርቦትን በመቆጣጠር የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ እየተሞከረ እንደሆነ ነው፤›› የሚሉት ዶክተሩ፣ ይህ የሚሆን ከሆነ አምራቾችና ሻጮች ዋጋቸውን እንዲቀንሱ የሚያስገድዳቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ለምን ይሆናል ቢባል አቅርቦትና ፍላጎት አልተጣጣሙምና ነው፡፡ እንዲህ የሚያብራሩት ዶክተሩ፣ ሰው ገንዘብ ከሌለው ሊገዛ ስለማይችል ፍላጎት ይቀንሳል፡፡ የሚገዛው ከሌለ ነጋዴው ዋጋ ለመቀነስ ይገደዳል፡፡ በእጁ ያለውን ሸቀጥ ለማጣራት ዋጋ በግድ ቀንሶ መሸጥ ግድ እንደሚሆንበት ይተነትናሉ፡፡ ትልልቆቹ የብረታ ብረት አምራቾችን ጨምሮ የእህል ነጋዴዎች ሳይቀር ገበያ አጣን ማለታቸው በጋዜጣ መውጣቱን ዶክተሩ በዋቢነት ይጠቅሳሉ፡፡ ስለዚህ የገንዘብ አቅርቦት እጅጉን እየቀነሰ በመጣ ጊዜ ሰው እጅ የሚገባው ገንዘብ ስለሚቀንስ የገበያው ዋጋም ሊቀንስ እንደሚችል ተብራርቷል፡፡

በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ከአሥር በመቶ በታች ሆኗል የሚባልለት የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ ያለው ዋጋ ስለቀነሰ ሳይሆን ሰው የመግዛት አቅም ስለሌው ፍላጎቱን እየገታ ስለመጣ ነው፤ ምሁሩ የሚደርሱበት ድምዳሜ ነው፡፡ ‹‹ለምሳሌ ድሮ 100 ዳቦ የሚገዛው፣ አሁን 50 ዳቦ ብቻ ለመግዛት ስለሚገደድ፣ ዳቦ ሻጩም እንደ ድሮው የሚገዛው ስለሌለ ዋጋውን ይቀንሳል ማለት ነው፡፡››

መንግሥት ግን ገንዘብ አለኝ ይላል

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በአገሪቱ ውስጥ የገንዘብ እጥረት አለመኖሩንና ለበጀት ዓመቱ ከሚያስፈልገው ገቢ ውስጥ በስድስት ወራት ብቻ 63 ቢሊዮን ብር ከታክስ መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳይያስ ባሕረ እንደሚገልጹት፣ ልማት ባንክ  የገንዘብ እጥረት የለበትም፡፡ የሥራ ማስኬጃ ካፒታል እጥረት ለገጠማቸውም ባንኩ በየጊዜው እየሰጠ እደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል የተንፀባረቀ ነገር የለም (የገንዘብ እጥረት)፡፡ ገንዘብ እየቀረበ ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር የገለጹት አቶ ኢሳይያስ፣ የግል ባንኮች ተቀማጭ የማንቀሳቀስ አቅማቸው እያነሰ መጥቶ ከሆነ ማየቱ ተገቢ እንደሚሆንም አስታውቀዋል፡፡ የግል ባንኮች ተቀማጭ መሰብሰብ ካልቻሉ ችግር ሊያጋጥማቸው ስለሚችል በዚህ ላይ ትልቅ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ይመክራሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር ኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ገንዘብ ወደ ባንክ መምጣት እንዳለበትም ያሳስባሉ፡፡

በዚህ ላይ ሥጋታቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ቆስጠንጢኖስ ጥናት የሚፈልግና በማስረጃ ያልተደገፈም ቢሆንም፣ አብዛኛው ነጋዴ ወደ ባንክ ሥርዓት ገብቶ መነገድ እንደማይፈልግ እየተነገረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በጥሬ ገንዘብ የሚንቀሳቀስ ኢኮኖሚ እየሆነ መምጣቱ ይነገራል፤›› ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ይሄ አካሄድ ባንኮች ተቀማጭ የማከማቸት አቅማቸው ላይ ጫና እንደሚያሳርፍ ለማሳየት የተጠቀሙበት ነው፡፡

ሆኖም ባንኮች በያመቱ 40 እና 50 ከመቶ የትርፍ ድርሻ ክፍፍል ከመስጠት ይልቅ ካፒታላቸውን እያሳደጉ፣ ቅርንጫፍ እያስፋፉ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚገባቸው ይመክራሉ፡፡ ‹‹አንድ ሰው ኢንቨስት ባደረገው ገንዘብ ሁለት ሦስት እጥፍ መመለስ ከቻለ ይኼ እንደ ኢንቨስትመንት ሳይሆን እንደ ፒራሚድ ስኪም የሚቆጠር ስለሆነ ባንኮቹ ራሳቸውን መገምገም ያስፈልጋቸዋል የሚል ግምት አለኝ፡፡››

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳም የገንዘብ እጥረት አለ በሚለው ሐሳብ አይስማሙም፡፡ የገንዘብ እጥረት አለ ወይ የሚለውን ጥያቄ በጥያቄ መልሰው ሲገልጹ፣ ‹‹ገንዘብ በቃኝ የሚል ስለሌለ መጀመሪያውኑ በጀትን አብቃቅቶ መጠቀም መቻል፣ በአግባቡ ማቀድ ይገባል እንጂ በየጊዜው ገንዘብ ጨምሩ ቀንሱ መባል የለበትም፤›› ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በአሁኑ ወቅት በፊት ይከተል የነበረውን የበጀት ሥርዓት፣ መቀየሩንና ፕሮግራም በጀት በሚባለው ስልት መሠረት እየሠራ በመሆኑ አንድ ጊዜ ታቅደው ለመጡ ሥራዎች ካልሆነ በቀር እንደቀድሞው ተጨማሪ በጀት መፍቀድ ማቆሙን አስታውቀዋል፡፡ መንግሥት ለዚህ ዓመት ካቀደው 150 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ሌላ በጀት የማይሰጠው፣ የዋጋ ግሽበቱን ባለበት ለማቆየት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ተጨማሪ ገንዘብ መልቀቅ ወይም እንደ ድሮው የሚጠየቀውን ያህል ገንዘብ አትሞ ጨምሮ በመስጠት መሥሪያ ቤቶች እንዳስፈለጋቸው እያዟዟሩ የሚጠቀሙበትን አሠራር አስቀርቷል፡፡ የፌደራልም ሆነ የክልል ኃላፊዎች ለሚያቀርቡት ዝርዝር የሥራ ዕቅድ ብቻ የሚውል ገንዘብ ይሰጣቸዋል፡፡ በዚያም ላይ ያቀዱትን ሥራ እውነትም ስለመሥራታቸው ሪፖርት እንዲያቀርቡ ይገደዳሉ፤ ቁጥጥርና ክትትልም ይደረግባቸዋል፡፡ የፕሮግራም በጀት በሰባት መሥርያ ቤቶች ላይ እየተሞከረ ይገኛል፡፡ ሙሉ ለሙሉ በአገሪቱ ለመተግበር ገና ይቀረዋል፡፡

በዚህ አኳኋን የፊስካል ፖሊሲውን ዲስፕሊን ይፋ ያደረገው ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ ይህንን ማድረጉ ከገንዘብ ፖሊሲው ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድለት መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ለዚህ ዓመት ካቀደው ገንዘብ ውጭ ተጨማሪ ገንዘብ ላለመልቀቅ የወሰነበት ምክንያት የዋጋ ግሽበት ነው ማለቱ በተዘዋዋሪ፣ እንደ መንገድ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች የሚጠይቁትን ተጨማሪ በጀት እንዳያገኙ ማድረጉ ይታያል፡፡

የገንዘብ ፍሰት ችግር አላጋጠመኝም ያለው ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ተጨማሪ በጀት የማልፈቅደው፣ መጀመሪያ በአግባቡ ካለማቀድ በሚመነጭ ችግር ነው ከማለቱ ባሻገር የዋጋ ግሽበትን የሚያባብስ ሆኖ አግኝቼዋለሁ በማለቱም ጭምር ነው፡፡ ዕቅድ እየከለሱ ገና ሲታቀድ የተረሱ ሥራዎች፣ በመንገድ ሥራ ላይ ደግሞ ጨረታ መጀመሪያ ሲወጣና በኋላ ላይ ሲታይ ወጪውን ሊጨምሩ የሚችሉ ነገሮች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ተብሎ የተጨማሪ በጀት ጥያቄ ቢቀርብም መንግሥት የማያስተናግደው ጥያቄ ሆኗል፡፡ ለምን ቢባል ዋጋ ግሽበትን መነሻ ስለሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡ ስለዚህ ‹‹ከጥር ጀምሮ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ መሥሪያ ቤቶች የሚያስፈልጋቸውን ትክክለኛ በጀት፣ በአግባቡ ማቅረብ ካልሆነ በቀር፣ በመካከሉ አንድ ነገር ሲገጥማቸው ብር እንዲታተም መጠየቅ፣ ዋጋ ግሽበትን የሚያመጣ ነው፤›› በማለት አቶ ሐጂ አብራርተዋል፡፡

ይህ ከሆነ መንግሥት የዋጋ ግሽበቱን የሚቆጣጠርበትን የገንዘብ ፖሊሲ ከፊስካል ፖሊሲው ጋር ለማጣጣም ሲል ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የግንባታ ሥራዎች ላይ የበጀት ማዕቀብ እያደረገ ነው ማለት ነው፡፡ ዕርምጃው ይህ መሆኑ፣ እንኳንና የንግድና የአገልግሎት ዘርፎቹ ቀርተው፣ የመንግሥት ትልልቅ ፕሮጀክቶች ሳይቀር ገንዘብ ማጣታቸውን መግለጻቸው፣ በስተመጨረሻ ላይ የኢኮኖሚውን ግለት ወይም የዕድገት ሒደት ሊገታ እንደሚችል የሚጠበቅ መሆኑን ምሁራኑ ይስማሙበታል፡፡

ከዚህ ባሻገር ሁለቱን የሞኒታሪና የገንዘብ ፖሊሲዎች ለማጣጣም የሚያስገድዱ የብድር ዕዳና የበጀት ጉድለት መባበስ እንደሆነም ጸሐፍት ይዘክራሉ፡፡ ሆኖም የግል የገንዘብ ድርጅት ይፋ ባደረገው ሪፖርት መንግሥት በብድር ዕዳ ችግር ውስጥ እንደማይገኝ ይገልጻሉ፡፡ ይህ ማለት ግን ዕዳ ለመቀነስ በያመቱ የሚከፈል ገንዘብ የለም ማለት እንዳልሆነ ያስታውቃሉ፡፡

ምንጭ፦ ሪፖርተር

Continue Reading
Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Articles

የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ተሳትፎ ድህረ ምልከታ

Published

on

Medal Winners

በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በወረቀት ደረጃ ከውድድሩ መጀመር በፊት ቡድኑ ባመዛኙ በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኙ ወጣት አትሌቶችን ስላካተተ ቢያንስ የለመድናቸውን ሁለት ወይም ሶስት የወርቅ ሜዳልያ ድሎች እንደማያሳጣን ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ ሆኖም የሜዳ ላይ ውጤቱ እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ኢትዮጵያ በውጤታማነቷ በምትታወቅበት የአትሌቲክስ ፉክክር በአንድ የወርቅ፣ አንድ የብር፣ እና ሁለት የነሐስ በድምሩ በአራት ሜዳልያዎች ከዓለም 14ኛ ከአፍሪካ 3ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች፡፡ ይህም ሁሌም ለአፍሪካ የበላይነት ከምንፎካከራት ኬንያ ጋር ያለን ልዩነት ይበልጥ እንዲሰፋ አድጎታል፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ሌላኛዋ የምስራቅ አፍሪካ ተቀናቃኛችን እየሆነች ከመጣችው ኡጋንዳም አንሰን እንድንገኝ አድርጎናል፡፡ የቶኪዮ ኦሊምፒክ በአትሌቲክሱ ከ1992ቱ የባርሴሎና ኦሊምፒክ ወዲህ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሜዳልያ ስኬት ያስመዘገበችበትም ሆኖ አልፏል፡፡

አሉታዊ ጎኖች
ቶኪዮ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤታማነት ፈር ቀዳጅ የሆነው ታላቁ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ በ1964 ዓ.ም. በተከታታይ ሁለተኛ የኦሊምፒክ ማራቶን ድሉን የተቀዳጀባት ከተማ ናት፡፡ እናም በቶኪዮ ከተማ በተከናወነው የኦሊምፒክ ውድድር የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የሱን ክብር የሚያጎሉባቸውን ነገሮች ያደርጋሉ ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ የሆኑት ነገሮች ግን በተለይ በቡድኑ አስተዳዳሪዎች በኩል ፍፁም ኃላፊነት የጎደለውና ከጠበቅኩት በተቃራኒው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከአትሌቶች ምርጫ አንስቶ በቡድኑ የዝግጅት ወቅት በተካረረ ውዝግብ ውስጥ ነበር የከረሙት፡፡ የኦሊምፒክ ቡድኑን የማዘጋጀት እና የመምራት የጋራ ኃላፊነት የነበረባቸው ሁለቱ አካላት ይባስ ብለው ውዝግቡን ቶኪዮ ድረስ ይዘውት ሄደዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ሁለቱን አካላት በማቀራረብ በትልቁ ውድድር ላይ ያለንን ተሳትፎ እንከን አልባ ማድግ የሚጠበቅባቸውም ተመልካች ከመሆን የዘለለ ሚና አልነበራቸውም። የውዝግቡ አሉታዊ ትሩፋት በአትሌቶች ስነልቦና እና በአጠቃላይ የቡድኑ ውጤት ላይ የበኩሉን ተፅዕኖ ሳያሳርፍ እንዳላለፈ አያጠራጥርም፡፡

እንደ አለመታደል ሆኖ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያን ልዑካን የመምራት ትልቁ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ኃላፊነት የጎደላቸው ነበሩ። የስፖርቱ አስተዳደሪዎች ትላልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በመጡ ቁጥር በአትሌቶች ምርጫ ዙሪያ የነበረውን ውዝግብ እንዲያቆሙልን እመኝ ነበር። ጭራሽ እራሳቸው ችግር ፈጣሪ ሆነው መገኘታቸው አስደንጋጭ እና አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በመሮጫ መም ወይም በጎዳና ላይ በሚደረጉ ውድድሮች መሸነፍን በስፖርቱ ውስጥ ማሸነፍ እና መሸነፍ ያሉ የነበሩ እና ወደፊትም የሚኖሩ ነገሮች ስለሆኑ በፀጋ መቀበል ይቻላል፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑ የስነልቦና ጥንካሬን ሊፈጥሩላቸው የሚገቡ ኃላፊዎች የእርስ በርስ ሽኩቻ ተቃራኒውን አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳርፍ ማየት ግን ፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ ለነገሩ ከስፖርቱ እድገት ይልቅ የፖለቲካ ግዴታቸው የሚያስጨንቃቸው የስፖርት አመራሮች በበዙባት ሀገር ስፖርቱ እንዲህ የማንም መጫወቻ ሲሆን ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡  

የስፖርት አመራሮች ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ሆነው ትኩረታቸውን ስፖርቱን በማስፋፋቱ እና ማሳደጉ ላይ አድርገው የሚሰሩ ስለስፖርቱም በቂ እውቀት እና ፍቅሩ ያላቸው ቢሆኑ መልካም ነው፡፡ ለቦታው በሚመጥን እና ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት በሚችል የስፖርት አመራር የሚመራ የስፖርት ተቋምን መገንባት በተመሳሳይ ሰዓት የሀገር ግንባታን የሚደግፉ ሶስት ነገሮችን ስኬታማ ያደርጋል፡፡ በስፖርት ጤናውን የሚጠብቅ ማሕበረሰብ በመፍጠር በጤናው ሴክተር ላይ የሚኖረውን ጫና ይቀንሳል፣ በሀገር ገፅታ ግንባታ እና በኢኮኖሚው ዕድገት ላይም የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ በቶኪዮ ላይ የተመለከትናቸው የሀገርን ክብር ዝቅ ያደረጉ ግዴለሽነቶች ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊታዩና አጥፊዎቹ ሊጠየቁበት ይገባል፡፡ በመጪዎቹ ዓመታት በሚጠብቁን ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይም የቶኪዮ ኦሊምፒኩን አይነት ሀፍረት እንዳይገጥመን ከወዲሁ ለችግሮቹ መፍትሔ መፈለግ አለበት፡፡

ባለፉት ዓመታት ኦሊምፒክ በመጣ ቁጥር በልዑካን ቡድኑ ውስጥ እየተካተቱ በሕዝብ ገንዘብ የሚዝናኑት የኦሊምፒክ ቱሪስቶች ጉዳይ ዘንድሮም ያልተቀረፈ ችግር ሆኖ ተስተውሏል፡፡ ከሌላው ግዜ በተለየ መልኩ ተጠባባቂ አትሌቶችን ይዞ መጓዝ ይጠይቅ በነበረው ውድድር ላይ አትሌቶቹን ትቶ ምንም የማይሰሩ ሰዎችን ይዞ መሄድ ትልቅ ቀልድ ነው፡፡  

ከሜዳ ውጭ የነበረው ውዝግብ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል የነበረ መሆኑ በሜዳ ላይ የነበሩብንን ድክመቶች ሊያስረሳንም አይገባም፡፡ ስድስት የጎዳና ላይ ተወዳደሪዎቻችን እና አንድ የመም ተወዳዳሪ ውድድራቸውን ማቋረጣቸው በቶኪዮ ከታዩት ደካማ ጎኖቻችን መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ ችግሩ በዚህ ምክንያት ነው የተከሰተው ብሎ ለይቶ ለመናገር ባይቻልም ብዙ ግዜ ሲፈትነን ለሚስተዋለው የሞቃታማ ቦታ ውድድር የምናደርጋቸው ዝግጅቶችን መለስ ብሎ መመልከትን የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ የተጎዳች አትሌትን ወደውድድር እንድትገባ ማድረግ እና በሁለት ደቂቃ ውስጥ ለማቋረጥ መገደዷም የአትሌቶች የጤና ክትትል ላይ ክፍተት እንዳለ የጠቆመን ክስተት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ወደውድድር ስፍራው ካቀናበት ግዜ ጀምሮ በቶኪዮ ምንም አይነት ቡድኑን የተመለከቱ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ወይም ፕሬስ ሪሊዞች አልነበሩም፡፡ ይህም እንደተለመደው የሕብረተሰቡን እና የመገናኛ ብዙሀንን ስለቡድኑ ቀጥተኛ መረጃ የማግኘት መብት የገደበ ነበር፡፡ ጋዜጠኞችም ሚዛናዊ ሆኖ ከመዘገብ ይልቅ ጎራ ለይተው ቃላት መወራወራቸው የህዝብን ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት የነፈገ ነው፡፡ 

አዎንታዊ ጎኖች
ሰለሞን ባረጋ በወንዶች 10,000 ሜትር ወርቅ፣ ለሜቻ ግርማ በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ብር፣ ጉዳፍ ፀጋዬ በሴቶች 5000 ሜትር ነሐስ፣ እና ለተሰንበት ግደይ በሴቶች 10,000 ሜትር ነሐስ ማስመዝገብ መቻላቸው የሚደነቅ ስኬት ነው፡፡

የመጪው ትውልድ አካል የሆኑት ተስፈኞቹ መቅደስ አበበ፣ ፍሬወይኒ ሀይሉ፣ በሪሁ አረጋዊ እና ጌትነት ዋለን ጨምሮ አምስት አትሌቶች ለሜዳሊያ የቀረበ የአራተኛነት ደረጃን ይዘው ማጠናቀቅ መቻላቸውም መልካም ነው፡፡ በተለይ ወጣቶቹ ያስመዘገቡት ውጤት በመጪዎቹ ዓመታት ተገቢውን ድጋፍ ካገኙ የምንጓጓለትን ድል ሊያስገኙልን እንደሚችሉ ያመላከተን ነው፡፡

የሀብታም አለሙ በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በሴቶች 800 ሜትር ለመጀመሪያ ግዜ ለፍፃሜ ተወዳዳሪነት መብቃት ምንም እንኳ በፍፃሜው የሜዳልያ ድል ባይቀናትም በአዎንታዊ ጎን ሊጠቀስ የሚችል ስኬት ነው፡፡

ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃን ይዘው ላጠናቀቁ አትሌቶች በሚሰጥ ነጥብ ድምር መሰረት በወጣው የነጥብ (ፕሌስመንት) ደረጃ ሰንጠረዥ ላይ በ64 ነጥብ ዘጠነኛ ሆነን ማጠናቀቃችንም እሰየው የሚያስብል ነው፡፡

በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከአራተኛ እስከ ስምንተኛ ባሉት ደረጃዎች ውስጥ አጠናቀው ነጥብ ያስገኙ እና የዲፕሎማ ተሸላሚ የሆኑት አትሌቶች፡-
4ኛ – ፍሬወይኒ ሀይሉ – በሴቶች 1500 ሜትር
4ኛ – መቅደስ አበበ – በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል
4ኛ – ሮዛ ደረጀ – በሴቶች ማራቶን
4ኛ – በሪሁ አረጋዊ – በወንዶች 10,000 ሜትር
4ኛ – ጌትነት ዋለ – በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል
5ኛ – እጅጋየሁ ታዬ – በሴቶች 5000 ሜትር
6ኛ – ሀብታም አለሙ – በሴቶች 800 ሜትር
6ኛ – ሰንበሬ ተፈሪ – በሴቶች 5000 ሜትር
8ኛ – ዮሚፍ ቀጄልቻ – በወንዶች 10,000 ሜትር
8ኛ – ዘርፌ ወንድማገኝ – በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል

  • የአትሌቲክስ የነጥብ ደረጃ ሰንጠረዥ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ባሉት ደረጃዎች ውስጥ የሚያጠናቅቁ አትሌቶች በሚያስመዘግቡት ነጥብ ድምር መሰረት የሚወጣ ሲሆን የነጥብ አሰጣጡም ለአንደኛ ደረጃ 8 ነጥብ፣ ለሁለተኛ ደረጃ 7 ነጥብ፣ ለሶስተኛ ደረጃ 6 ነጥብ፣ ለአራተኛ ደረጃ 5 ነጥብ፣ ለአምስተኛ ደረጃ 4 ነጥብ፣ ለስድስተኛ ደረጃ 3 ነጥብ፣ ለሰባተኛ ደረጃ 2 ነጥብ፣ እና ለስምንተኛ ደረጃ 1 ነጥብ ነው።

ከፊታችን ምን  እየጠበቀን ነው? ምንስ እናድርግ?
ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፉ ወረርሺኝ ምክንያት ትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለሌላ ግዜ እንዲተላለፉ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ሌላ አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ቀጣዮቹ አራት ዓመታት በተከታታይ በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች የሚካሄዱባቸው ይሆናሉ፡፡ በ2022 የዓለም ሻምፒዮና፣ በ2023 የዓለም ሻምፒዮና፣ በ2024 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች፣ እና በ2025 የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ይኖራሉ፡፡ በቀጣዩ ዓመት በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ከሐምሌ 8 – 17/2014 በዩናይትድ ስቴትስ ኦሪጎን የሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዘጋጆች ሙሉ የውድድሩን ፕሮግራም፣ የማራቶን እና የእርምጃ ውድድሮች የሚካሄዱባቸውን ቦታዎች በትላንትናው ዕለት ይፋ አድርገዋል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናውን ውድድር በኃላፊነት የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ከወዲሁ ለዛ ውድድር ተሳትፎ የሚጠበቅበትን አቅዶ መንቀሳቀስ ይኖበርታል፡፡

ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጭቅጭቆችን ለማስቀረት ከወዲሁ ሁሉም አትሌቶች አውቀውት በውስጡ የሚያልፉበትን ገዢ የሆነ የመምረጫ መስፈርት ማዘጋጀት ቀዳሚው ተግባር መሆን አለበት፡፡ የመምረጫ መስፈርት ሁልግዜም በግላዊ ምልከታ እና ፍላጎቶች ላይ በሚመሰረት ምክንያት አነጋጋሪ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ቢሆንም ባለድርሻ አካላቱን በሙሉ ባሳተፈ መልኩ ውይይት ተደርጎበት ቢወጣ ሁሉንም ገዢ እና ከጭቅጭቅ የፀዳ ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህ ላይ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከተከሰቱት ሁኔታዎች አንፃር የሌሎች ሀገሮችንም ተሞክሮዎች በመዳሰስ ነገሩን ሰፋ አድርጎ መመልከት ቢቻል ጥሩ ነው፡፡ ትልልቅ ውድድሮች በመጡ ቁጥር በተደጋጋሚ እንደታዘብነው አንዳንድ አትሌቶች በቡድኑ ውስጥ ለመካተት የሚያደርጉትን ተገቢ ያልሆነ ሙከራም ማቆም አለባቸው፡፡ ከፋም ለማም ስፖርቱን እንዲመራ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም የሚያወጣቸውን መስፈርቶች ማክበርና በዛ ውስጥ ተመራጭ ለመሆን መሞከር ግድ እንደሚላቸውም መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ማኔጀሮች እና አሰልጣኞች በተለይ በማራቶን የራሳቸውን አትሌት ለማስመረጥ የሚያደርጓቸው አላስፈላጊ ግፊቶችም ሊያቆሙ ይገባል፡፡

ለውድድሮች የምናደርጋቸውን ዝግጅቶች ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ከውድድሮች በኋላ መገምገም እና መታረም ያለባቸው ነገሮች ካሉ ማረም፡፡ ከፍተኛ ሙቀት በነበረባቸው በለንደን 2012 ኦሊምፒክ ሶስቱም የወንዶች ማራቶን ተወዳዳሪዎቻችን፣ በሞስኮ 2013 የዓለም ሻምፒዮና ሁለቱ የሴቶች ማራቶን ተወዳዳሪዎቻችን፣ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ አምስት የማራቶን (ሶስቱም ወንዶች እና ሁለት ሴቶች) ተወዳዳሪዎቻችን እንዲሁም የሴቶች እርምጃ ተወዳዳሪያችን ለማቋረጥ መገደዳቸውን አስተውለናል፡፡ ስለዚህ በጎዳና ላይ ውድድሮች ከባድ ሙቀት ለሚኖርባቸው ቦታዎች እንዴት መዘጋጀት አለብን የሚለው ጉዳይም በደንብ ሊታይ የሚገባው ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ የመም (ትራክ) ተወዳዳሪ አትሌቶቻችን የውድድር ዓመቱ ሲጀምር ድንቅ ብቃታቸውን ያሳዩን እና ወደትልቅ ውድድር ሲቃረቡ አቋማቸው እየወረደ ይመጣል፡፡ አሰልጣኞቻቸው ለእነዚህ አይነቶቹ አትሌቶች ወደትልቅ ውድድር ሲቃረቡ ብቃታቸውን እያሳደጉ እንዲሄዱ የሚረዳቸውን የልምምድ ፕሮግራም ቢያዘጋጁላቸው መልካም ነው፡፡ በመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ላይ በተለይ በወንዶች አሁንም በከፍተኛ ደረጃ የሚፎካከሩ አትሌቶችን ለማፍራት ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል፡፡

Continue Reading

Articles

የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የቶኪዮ ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ማጣሪያ ውድድሮች የመጀመሪያ ሁለት ቀናት

Published

on

በሴቶች 5000 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ላይ የሚፎካከሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች

በቶኪዮ ኦሊምፒክ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት የኢትዮጵያ አትሌቶች የተሳተፉባቸው የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል፣ 800 ሜትር በሁለቱም ፆታዎች፣ እንዲሁም የሴቶች 5000 ሜትር ማጣሪያዎች ሌላኛዎቹ የኢትዮጵያውያን የትኩረት ማዕከል የነበሩ ውድድሮች ናቸው፡፡ ቀጣዩ ዘገባ የኢትዮጵያውያኑን የማጣሪያ ውድድሮች ተሳትፎ እና ውጤቶች አንዲሁም ተጨማሪ መረጃዎችን ይዟል፡፡

የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል

በአትሌቲክስ ውድድሩ የመክፈቻ ቀን (ዓርብ ሐምሌ 23/2013) ጠዋት ላይ በተካሄደው የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ማጣሪያ ከተሳተፉት ሶስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ከምድብ አንድ ለሜቻ ግርማ (8፡09.83) በአንደኛነት፣ ከምድብ ሁለት ጌትነት ዋለ (8፡12.55) በሁለተኛነት ለፍፃሜው ሲያልፉ በምድብ ሶስት የተወዳደረው ታደሰ ታከለ (8፡24.69) ስምንተኛ ወጥቶ ለፍፃሜው ሳያልፍ ቀርቷል፡፡ ለሜቻ ጃፓናዊው ሚዩራ ዩጂን እና ኬንያዊው ቤንጃሚን ኪይገንን በማስከተል ከምድቡ ያሸነፈበት 8:09.83 በኦሊምፒክ የማጣሪያ ውድድሮች ላይ የተመዘገበ የምንግዜውም ፈጣን ሰዓት ሆኗል፡፡ የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል የፍፃሜ የሜዳልያ ፉክክር በዋናነት በኬንያውኑ ቤንጃሚን ኪገን እና አብራሀም ኪቢዎት፣ በኢትዮጵያውያኑ ለሜቻ ግርማ እና ጌትነት ዋለ እንዲሁም በሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ መካከል እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል በ1980ው የሞስኮ ኦሊምፒክ በሻምበል እሸቱ ቱራ አማካይነት ካስመዘገበችው የነሐስ ሜልያ ድል ወዲህ በርቀቱ በወንዶች ምንም አይነት የኦሊምፒክ ሜዳልያ ድል የላትም፡፡ ሆኖም ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየታዩ የመጡ መሻሻሎች እና በዶሀው የዓለም ሻምፒዮና ላይ የተመዘገበው የብር ሜዳልያ ድል በቶኪዮም ሌላ ሜዳልያን ተስፋ እንድናደርግ ያነሳሳን ሆኗል፡፡ ዘግይቶ የተሰላፊ አትሌቶች ለውጥ ከተደረገባቸው ርቀቶች አንዱ በሆነው የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል በተጠባባቂነት የተመዘገበውና በዋናነት በ5000 ሜትር እንደሚወዳደር ይጠበቅ የነበረው ጌትነት ዋለ ወደመጀመሪያ ተሰላፊነት የመጣ ሲሆን ኃይለማሪም አማረ በመጨረሻ ሰዓት በለሜቻ ግርማ መተካቱም አነጋጋሪ የሆነ ሌላኛው ለውጥ ነው፡፡ ጌትነት በ3000 ሜትር መሰናክልም ጠንካራ ተፎካካሪ አትሌት ሲሆን በዶሀ የዓለም ሻምፒዮና ላይ አራተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ በፍፃሜው ውድድር በ2019 የርቀቱ የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮን ጌትነት ዋለ እና በወቅቱ የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊስት ለሜቻ ግርማ የሚወከለው የኢትዮጵያ ቡድን በቶኪዮ የኬንያውያኑን የበላይነት ለመግታትና አዲስ የስኬት ታሪክ ለማፃፍ እንደሚበቃ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡                     

በ1984 በሎስ አንጀለስ ከተከናወነው የኦሊምፒክ ውድድር አንስቶ በተከታታይ በዘጠኝ የኦሊምፒክ ውድድሮች ወይም ላለፉት 36 ዓመታት የኦሊምፒክ የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል የወርቅ ሜዳልያ ድል በኬንያውያን ቁጥጥር ስር ይገኛል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናም ተመሳሳይ የበላይነት ያላቸው ኬንያውያን ከ17 የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች በ14ቱ የወርቅ ሜዳልያው አሸናፊዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ከሁለት ዓመት በፊት በዶሀው የዓለም ሻምፒዮና ላይ ከኢትዮጵያውያን እና ከሞሮኮ አትሌቶች የገጠማቸው ተግዳሮት ለመሸነፍ እጅግ አቅርቧቸው የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ በአንድ ማይክሮ ሰከንድ ልዩነት አሸናፊነታቸውን ባረጋገጡበት በዶሀው ውድድር የተፈታተኗቸው ኢትዮጵያዊው ለሜቻ ግርማ እና ሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ በቶኪዮው ፍፃሜ ለሌላ ብርቱ ፉክክር እየጠበቋቸው ይገኛሉ፡፡ ባለፉት ሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች በቅደም ተከተል የብር እና የነሐስ ሜዳልያን ያገኘው ሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ በቶኪዮ ከሚወዳደሩት በሙሉ የላቀና 7፡58.15 የሆነ የራሱ ምርጥ ሰዓት ያለው ነው፡፡

ኬንያ በቶኪዮ ያለፈው ውድድር ሻምፒዮንነቱን ክብር የሚያስጠብቅላትን አትሌት ይዛ መቅረብ ሳትችል ቀርታለች፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት በሪዮ የኦሊምፒክ እንዲሁም ከሁለት ዓመት በፊት በዶሀ የዓለም ሻምፒዮን የሆነው ኮንሰስለስ ኪፕሩቶ ባለፈው ወር በኬንያ የኦሊምፒክ ምርጫ ውድድር ላይ ውድድሩን ባለማጠናቀቁ የኦሊምፒክ ሻምፒዮንነት ክብሩን ለማስጠበቅ በቶኪዮ አልተገኘም፡፡ ስለዚህ አሁን የረጅም ግዜ የበላይነታቸውን የማስጠበቅ ኃላፊነቱ በ2019ኙ የዶሀ የዓለም ሻምፒዮና ላይ በቅደም ተከተል ስድስተኛ እና ሰባተኛ ሆነው ባጠናቀቁት ቤንጃሚን ኪገን እና አብራሀም ኪቢዎት ላይ ወድቋል፡፡  

የሴቶች 800 ሜትር

ከአትሌቲክሱ የጀመሪያ ቀን የጠዋት መርሀግብሮች አንዱ በነበረው የሴቶች 800 ሜትር ማጣሪያ በምድብ ሶስት በአሜሪካዊቷ አቲንግ ሙ ተቀድማ በ2 ደቂቃ ከ01.20 ሰከንድ ሁለተኛ የወጣችው ሀብታም አለሙ ለግማሽ ፍፃሜው ያለፈች ሲሆን በሁለተኛው ቀን ምሽት ላይ በተካሄደው የግማሽ ፍፃሜ ውድድር ላይም በአሜሪካዊቷ አቲንግ ሙ ተቀድማ በ1:58.40 ሁለተኛ በመሆን በኦሊምፒክ የውድድር ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ በርቀቱ ለፍፃሜ ውድድር የበቃች ኢትዮጵያዊት ሆናለች፡፡ ሀብታም ከውድድሩ በኋላ በቶኪዮ ለሚገኘው ባልደረባችን አብይ ወንድይፍራው በሰጠችው አጭር ቃል ‹‹ውድድሩ ትንሽ ፈታኝ ነበር ነገር ግን ለሀገሬ ስል ያለኝን አቅም ሁሉ ተጠቅሜያለሁ፡፡ ክብሩ ይስፋ ለመድኃኒዓለም በመጨረሻም አሪፍ ውጤት ላይ ደርሻለሁ፡፡ ለኦሊምፒክ የፍፃሜ ውድድር ሳልፍ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም ከኢትዮጵያ ለፍፃሜ የደረሰ ያለ አይመስለኝም እና አሁንም መጨረሻዬን ያሳምርልኝ ነው የምለው›› ብላለች፡፡  

በሴቶች 800 ሜትር የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ በምድብ አራት በ2.01.98 አራተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ነፃነት ደስታ ወደ ግማሽ ፍፃሜው መቀላቀል ሳትችል ስትቀር በጀማሪዎች ስም ዝርዝር ላይ ስሟ ተካቶ በምድብ አንድ እንደምትሮጥ ስትጠበቅ የነበረችው ወርቅውሀ ጌታቸው ግልፅ ባልተደረገ ምክንያት ውድድሩን ሳትጀምር ቀርታለች፡፡

የወንዶ 800 ሜትር

የወንዶች 800 ሜትር የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ላይ የተሳተፈው ኢትዮጵያዊው መለሰ ንብረት ከምድብ ሶስት በ1:47.80 ሰባተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ለግማሽ ፍፃሜው ማለፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡ በመሐመድ አማን ስኬቶች በመነቃቃት ላይ የነበረው የወንዶች 800 ሜትር ከቅርብ ግዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ሶስት ሰዓት የሚያሟሉ ተወካይ አትሌቶችን ለማግኘት እየተቸገረችበት የምትገኝ ርቀት እንደሆነ እየታየ ነው፡፡ የኦሊምፒክ ሚኒማ ማሟላት የቻለ አንድ አትሌት ብቻ ይዘን የቀረብንበት የቶኪዮ ኦሊምፒክም ይህ ችግር እንዳልተቀረፈ የታየበት ሌላኛው አጋጣሚ ሆኗል፡፡  

የሴቶች 5000 ሜትር ማጣሪያ

በአትሌቲክሱ የመጀመሪያ ቀን ሐምሌ 23/2013 ምሽት ላይ በተደረት የሴቶች 5000 ሜትር ማጣሪያ ላይ የተሳተፉት ሶስቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሐምሌ 26/2013 ምሽት ላይ ለሚደረገው የፍፃሜ ውድድር አልፈዋል፡፡ ከምድብ አንድ ሰንበሬ ተፈሪ (14፡48.31) እና እጅጋየሁ ታዬ (14፡48.52) የኔዘርላንዷ ሲፋን ሀሳን (14፡47.89) እና ኬንያዊቷ አግነስ (14፡48.01) ቲሮፕን ተከትለው በቅደም ተከተል ሶተኛ እና አራተኛ ሆነው ሲያልፉ ከምድብ ሁለት ጉዳፍ ፀጋዬ (14፡55.74) ኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪ (14፡55.77) አስከትላ በአንደኛነት አልፋለች፡፡


ሐምሌ 26/2013 ምሽት ላይ በሚደረገው የሴቶች 5000 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ላይ የሚፎካከሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች

በሄንግሎ በተከናወነው የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ምርጫ ውድድር ላይ ባስመዘገበችው የራሷ ምርጥ 14:13.32 የርቀቱ የወቅቱ ፈጣን አትሌት ሆና ወደ ቶኪዮ ያቀናችው ጉዳፍ ለወርቅ ሜዳልያ ድል ከሚጠበቁት መካከል ናት፡፡ በሄንግሎው ውድድር ላይ ጉዳፍን በመከተል በቅደም ተከተል 14:14.09 እና 14፡15.24 በሆነ ሰዓት የጨረሱት እጅጋየሁ እና ሰንበሬም በዓለም የምንግዜም ምርጥ ዝርዝር ውስጥ የስድስተኛ እና ሰባተኛ ደረጃን ለመያዝ የበቁ ጠንካራ አትሌቶች ናቸው፡፡ የቶኪዮ ኦሊምፒክ የሴቶች 5000 ሜትር ተወዳዳሪዎች ዝርዝር ሶስቱን ኢትዮጵያውያን ጨምሮ ከዓለም የምንግዜም ምርጥ አስር የርቀቱ ሯጮች አምስቱን ያካተተ ነው፡፡ ኬንያውያኑ ሄለን ኦቢሪ እና አግነስ ቲሮፕ ከምንግዜም ምርጥ አስሮቹ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆኑ በ12ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሀሳንም የቶኪዮውን የፍፃሜ ፉክክር በጉጉት እንዲጠበቅ የምታደርግ ብርቱ አትሌት ናት፡፡

Continue Reading

Articles

ሰለሞን ባረጋ ለአስራ ሶስት ዓመት የራቀንን የወንዶች 10,000 ሜትር ድል በቶኪዮ ወደ ኢትዮጵያ መልሶታል

Published

on

218076583_1010892909482678_1235421043554241523_n

በቶኪዮ ኦሊምፒክ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአትሌቲክስ ውድድር በተጀመረ በሁለተኛው ቀን በወንዶች አስር ሺህ ሜትር ኢትዮጵያውያንን እጅግ ያስደስተው ድል በወጣቱ ሰለሞን ባረጋ አማካይነት ተመዝግቧል፡፡   
በ1980 ሞስኮ ላይ ምሩፅ ይፍጠር በርቀቱ ለመጀመሪያ ግዜ የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ካስገኘ በኋላ ከተደረጉት አስር የኦሊምፒክ የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ውድድሮች ኢትዮጵያ አምስቱን በበላይነት ለመጨረስ ችላለች፡፡ የርቀቱ ንጉሶች ሀይሌ ገብረስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ከ1992 እስከ 2008 ዓ.ም. በአራት ተከታታይ የኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ በማሸነፍ የርቀቱ የወርቅ ድል ለኢትዮጵያ ብቻ የተሰጠ እንዲመስለን አድርገውንም ነበር፡፡ ከ2008ቱ የቤይጂንግ ኦሊምፒክ የቀነኒሳ በቀለ ድል በኋላ በተከሰተው የሞ ፋራህ የበላይነት ምክንያት ተመሳሳዩን ድል በቶኪዮ ለማየት 13 ዓመታትን መጠበቅ ግድ ብሎናል፡፡ ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት በጉጉት ስንጠብቀው የቆየነውን የ10 ሺህ ሜትር የኦሊምፒክ ድል በመጨረሻም ሰለሞን ባረጋ በቶኪዮ አጎናፅፎናል፡፡ የሰለሞን የቶኪዮ የወርቅ ሜዳልያ ድል ኢትዮጵያ ካለፉት አስራ አንድ ኦሊምፒኮች በርቀቱ ለስድስተኛ ግዜ የበላይ ሆና እንድትጨርስ ያስቻለም ነው፡፡ ድሉ በቶኪዮ የአትሌቲኪስ ውድድሮች የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳልያ ድል ሆኖም ተመዝግቧል፡፡ ሰለሞን ባረጋ በ2018 የበርሚንግሀም የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር በ3000 ሜትር እና በ2019 የዶሀ ዓለም ሻምፒዮና ላይ በ5000 ሜትር የብር ሜዳልያ ካገኘ በኋላ በመጀመሪያ የኦሊምፒክ ተሳትፎው ከፍተኛ ክብር የሚሰጠውን የ10,000 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ድል ለማሳካት በቅቷል፡፡

‹‹የ200 ሜትር እና 400 ሜትር አጫጨር የፍጥነት ሩጫ ልምምዶችን ስሰራ ስለነበረ ሁለት ዙር ሲቀር ውድድሩን እንደማሸንፍ ለራሴ ነገርኩት››
ሰለሞን ባረጋ ከቶኪዮው ድል በኋላ

ሰለሞን ባረጋ ከቶኪዮው ድሉ በኋላ በስፍራው ከሚገኘው የስራ ባልደረባችን አብይ ወንድይፍራው ጋር ባደረገው አጭር ቃለ ምልልስ የሚከተለውን ብሏል ‹‹ረጅም ርቀት የእኛ ስፖርት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ሆኖም በኦሊምፒክ ውድድር ላይ ወርቅ ሜዳልያ ከወሰድን ብዙ ግዜ አልፎናል፡፡ ይህን ነገር ለመጨረሻ ግዜ ያሳካውም ቀነኒሳ ነበረ፡፡ ዛሬ በቶኪዮ ድሉን በማሳካቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በተለይ ለእኛ ከቶኪዮ ጋር አበበ ቢቂላን የምናስታውስበት ድል ስለሆነ ያንን በማሳካቴም በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ዘንድሮ ከኡጋንዳ የዓለም ሪኮርድ የሰበረው ቼፕቴጌይ እና የዓመቱን ፈጣን ሰዓት የሮጠው ኪፕሊሞ ነበሩ፡፡ እናም ውድድሩ በጣም ይፈጥናል ብዬ ነበር የጠበቅኩት ግን አልተሮጠም፡፡ ውድድሩን የጨረስነውም 27 ቤት ነው፡፡ የ200 ሜትር እና 400 ሜትር አጫጨር የፍጥነት ሩጫ ልምምዶችን ስሰራ ስለነበረ ሁለት ዙር ሲቀር ውድድሩን እንደማሸንፍ ለራሴ ነገርኩት፡፡ ኡጋንዳውያኑ አትሌቶች ዛሬ ብዙም አልታገሉም፡፡ አብዛኛውን ሰዓት ከኋላ ነው የቆዩት እና እንደዚህ ይሆናል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፡፡ እነርሱን ካሜራ ላይም እያየኋቸው ስለነበር ስለነሱ ብዙም አልተጨነቅኩም እንደውም ከእነሱ ይልቅ የእኛን ልጆች ነበረ ይወጣሉ ብዬ የጠበቅኩት፡፡ በውድድሩ መሀል ተጠባቂ የሆኑት ኡጋንዳውያን ወደኋላ ቀርተው ሶስተኛው የቡድን አጋራቸው ወደፊት ወጥቶ በሰፊ ልዩነት ሲመራ እኛ እነሱን ስንጠብቅ እሱ አዘናግቶ እንዳያሸንፍ ልዩነቱን ለማጥበብ ሞክሬያለሁ፡፡ ምናልባት እነሱ እኛን ሲጠብቁ አንተ ሂድ ያሉት ነበር የመሰለኝ፡፡ ከዚህ በፊት በእንደዚህ አይነቱ ነገር ዳይመንድ ሊግ ላይ ስለተሸወድኩኝ ያንን እንዳይደግሙ ብዬ ነበረ ልዩነቱን ለማጥበብ የሞከርኩት፡፡ የአሰልጣኜንም ምክር እየሰማሁ ስለነበረ የምሮጠው እና ወደኋላ ተመለስ እያለኝ ስለነበር ወደኋላ ተመልሻለሁ፡፡ የእነርሱ እስትራቴጂ እሱን ወደፊት እንዲወጣ አድርገው እኛን ለማድከም ነበረ፡፡ ከበሪሁን ጋር ስንነጋገር ወደፊት ጠጋ በል እያልኩት ነበረ፡፡ ከበሪሁን ጋር ልምምድም አብረን ነበረ የምንሰራው፡፡ እኔ እንደውም ከአንድ እስከ ሶስት እንወጣለን ብዬ ነበር የጠበቅኩት አጋጣሚ ሆኖ አልተሳካም ነገር ግን ወርቁን ወደኢትዮጵያ በመመለሳችን በጣም ደስተኛ ነን፡፡›› ብሏል፡፡

Continue Reading

Trending