Sports
በቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት የተጠናቀቀው የ2007 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ዕለት ክስተቶች

የ2007 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስን አንግሶ፣ ወልዲያ ከነማን እና ሙገር ሲሚንቶን አውርዶ፣ ኤሌክትሪክን በመውረድ ስጋት አሳቅቆ ተጠናቋል፡፡ ቀጣዩ ፅሁፍ የወራጅ ቀጠና ግብግቡ ልብ-ሰቃይ የነበረበትን የሊጉን የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች እና የፍፃሜውን ስነ-ስርዓት ይዳስሳል፡፡
የአሳዳጊዎቹ ያለመውረድ ትንቅንቅ
በ1980ቹ እና በ1990ቹ በቀድሞው የሊጉ መዋቅርም ሆነ በአዲሱ የፕሪምየር ሊግ የመብራት ኃይልን (የአሁኑ ኤሌክትሪክ) ያህል በየዓመቱ ለአዳዲስ ወጣት ተጨዋቾች እድል ይሰጥ የነበረ ክለብ ማስታወስ ያስቸግራል፡፡ መብራቶች በየዓመቱ ወደተለያዩ ክለቦች የሚጓዙባቸውን ተጨዋቾች ከወጣት ቡድናቸው በሚያሳድጓቸው በርካታ ወጣቶች እና ከሌሎች ክለቦች በሚያመጧቸው ጥቂት ብዙም የማይታወቁ ተጨዋቾች በመተካት ድንቅ እንቅስቃሴ የሚያደርግ እና ለዋንጫዎች የሚፎካከር ቡድን ይገነቡ ነበር፡፡ የ1980ቹ አጋማሽ የወንድማገኝ ከበደ እና የ1990ቹ መጀመሪያ የሀጎስ ደስታ ቡድኖች ለዚህ ተጠቃሽ ይሆናሉ፡፡ መብራቶች በአዲሱ ሚሌኒየም የሌሎቹን ክለቦች አካሄድ በመከተል ከዚህ ማንነታቸው ሲያፈገፍጉ፣ አሳዳጊነታቸውን እና ለወጣቶች እድል የመስጠት ማንነታቸውን ከተረከቡ ጥቂት ቡድኖች አንዱ ሙገር ሲሚንቶ ነበር፡፡ ሙገሮች እንደመብራት ኃይል ዋንጫዎችን አያግኙ፣ አልያም ለዋንጫዎች አይፎካከሩ እንጂ በወጣቶች ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው በመስራት ከታች ከመጡበት ከ1991 ጀምሮ ለ16 ዓመታት በሊጉ መቆየት ችለዋል፤ በርካታ ከዋክብትንም በማፍራት ብሔራዊ ቡድናችንን እና ታላላቆቹን ክለቦች ጠቅመዋል፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት ወጣቶችን ከስር አሳድጎ በትልቁ ሊግ እድል በመስጠት ረገድ ከሙገር የተሻለም ሆነ የሚፎካከር ቡድን አልነበረም፡፡ እነዚህ ሁለት ‘አሳዳጊ’ ቡድኖች ባለፉት ጥቂት ዓመታት ላለመውረድ ሲጫወቱ እና በመጨረሻ ሲተርፉ ቆይተው ዘንድሮ ግን ከሁለቱ አንዱ መውረዱ ግድ እንደሆነ ሊጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲቀሩ ተረጋገጠ፡፡
ኤሌክትሪክ አሁን ከአሳዳጊነት ይልቅ ብዙ ገንዘብ በማውጣት እና የውጪ ዜጎችን በመቅጠር ላይ ትኩረት ቢያደርግም (አሁንም ግን ጥቂት ከስር ያደጉ ተጨዋቾች እንዳሉት ሳይዘነጋ) የቀድሞው ታሪኩ እና ውለታው እንዲሁም የሙገር በእዚህ ገንዘብ ሁሉን በተቆጣጠረበት ዘመን ለመርሆው ታማኝ ሆኖ መቆየቱ ለገለልተኞች ለማን ድጋፍ መስጠት እንዳለባቸው ግራ እንዲጋቡ አድርጓቸው ነበር፤ የመውረድ ነገር ሁለቱንም ባይጠጋቸውም የብዙዎች ምርጫ ነበር፡፡ ነገር ግን የአንዱ ከሊጉ መለየት የግድ ነበርና በመጨረሻው ወሳኝ ጨዋታ የኤሌክትሪክ ነጥብ መጣል እና የእራሱ ድል ማድረግ ያስፈልገው የነበረው የግርማ ሀብተዮሐንስ ሙገር መከላከያን በመርታት የእራሱን ስራ ቢወጣም፣ ቦዲቲ ላይ ኤሌክትሪክ በወላይታ ድቻ ላይ ድል በማግኘቱ አሰላን መቀመጫው ያደረገው ቡድን በአሳዛኝ ሁኔታ በከ16 ዓመታት በኋላ ከሊጉ ተሰናብቷል፡፡ እሁድ በስምንት ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ፍልሚያ ሙገሮች በርካታ አዳዲስ ወጣቶችን ይዞ ወደሜዳ የገባው መከላከያን ለማሸነፍ ተቸግረው የነበረ ቢሆንም (በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያዎች በርካታ ጥሩ የማግባት እድሎችን አምክነዋል) በጨዋታው መጠናቀቂያ ገደማ በረከት ሳሙኤል በጭንቅላቱ ገጭቶ ባስቆጠረው ጎል እጅግ ‘ውድ የመሰሉ’ ሶስት ነጥቦችን ወስደዋል፡፡
ጨዋታው እንደተጠናቀቀ የታየው ነገር አስገራሚ ድራማ ነበር፡- በተመሳሳይ ሰዓት በቦዲቲ በተደረገው ጨዋታ ኤሌክትሪክ በወላይታ ድቻ የመረታቱን የተዛባ መረጃ በመስማታቸው የሙገር ተጨዋቾች በደስታ አበዱ፤ ሜዳውንም በመዞር ሲደግፋቸው ከዋለው የአዲስ አበባ ስታዲየም ታዳሚ ጋር ፈነጠዙ፡፡ በ2003 ዋንጫውን በኢትዮጵያ ቡና ለመነጠቃቸው የኤሌክትሪክን ሚና የማይረሱት (በወቅቱ ፈረሰኞቹ አስደናቂ የድል ጉዞ ላይ እያሉ መብራቶች ወሳኝ ሁለት ነጥብ አስጥለዋቸው ነበር) የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችም በሙገር ‘መትረፍ’ እና በኤሌክትሪክ ‘መውረድ’ በደስታ አዜሙ፤ ጨፈሩ፡፡ ጥቂት የኤሌክትሪክ ደጋፊዎችም በሰሙት ዜና ተደናግጠው ከራሳቸው ጋር መቆዘም ጀመሩ፡፡ የሙገር አባላት ሜዳው ውስጥ ደስታቸውን ከገለፁ በኋላ ወደ መልበሻ ክፍል ገቡ፡፡ በዚህ አፍታ ሁሉ ነገር ግልፅ የሆነ መስሎ ነበር፡፡ በቀጣይ ሊጫወቱ የተዘጋጁት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ተጨዋቾች ጨዋታቸውን ለመጀመር ወደ ሜዳ ሊገቡ ሲሉ ግን ከስታዲየሙ አስተዋዋቂ አንድ ግራ አጋቢ ዜና ተሰማ – ኤሌክትሪክ ወላይታ ድቻን 1ለ0 አሸንፏል፤ እናም የተረፈው ሙገር ሳይሆን ኤሌክትሪክ ነው፡፡ አስተዋዋቂው የህዝቡን ግራ መጋባት በመረዳቱም ይመስላል ዜናውን በመደጋገም ይፋ አደረገ፡፡ እናም ስሜቶች ተገለባበጡ፤ የተደሰቱት አዘኑ፤ ያዘኑት ባልጠበቁት የምስራች ፈነጠዙ፡፡ በዚህ ሁሉ ውዥንብር ውስጥ ግን በዚህ ዘመን እንዲህ አይነት የመረጃ መዛባት እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ እና የሊጉ አወዳዳሪ አካል ለምን በፍጥነት ውዥንብሩን እንዳላጠራ ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኗል፡፡ የሙገሩ አሰልጣኝ ግርማ ሀብተዮሐንስ ከጨዋታው በኋላ ለኢ.ብ.ኮ በሰጡት ቃል ባለፉት ዓመታት እጅግም ባልተሻሻለው ‘ሚጢጢዬ’ በጀታቸው ለዝውውር ሚሊዮኖችን ከሚያፈሱ ቡድኖች ጋር ለመፎካከር እንደተቸገሩ ገልፀዋል፤ በየዓመቱ ብዙ ተጨዋቾች እየለቀቁባቸው በአዳዲስ ወጣቶች አዲስ ቡድን በመገንባት የመፎካከር ፈተናን ከዚህ በላይ መቋቋም እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡ የረዥም ጊዜ አገልጋዩ አሰልጣኝ ከዚህ መሰረታዊ ምክንያት ባሻገርም አነጋጋሪ የነበረው የኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከነማን ጨዋታም ለመውረዳቸው በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡
ሌሎች መነጋገሪያ ነጥቦች
- ሻምፒዮኖቹ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኝ የነበረው ደደቢትን በመርታት አጨራረሳቸውን አሳምረዋል፡፡ 1ለ0 በተጠናቀቀው ጨዋታ ዘንድሮ በጎል አግቢ አማካይነት የተገለጠው ምንተስኖት አዳነ ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሯል፡፡ የቀድሞው የተከላካይ አማካይ ወደ ፊት ገፋ ባለ አዲስ ሚና ድንቅ ዓመት (በተለይ በሁለተኛው ዙር) አሳልፏል፡፡ ምንተስኖት ከመሀል ሜዳ እየተነሳ በሊጉ ብቻ ስምንት ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን ይህም አጥቂዎች ካልተቆጠሩ በሊጉ ከፍተኛ ጎል አግቢ ያደርገዋል፤ ከአዳነ ግርማ በመቀጠልም የክለቡ ከፍተኛ ጎል አግቢ ነው፡፡
- ፍፁም ሳይጠበቅ ሁለተኛ ለመሆን የተጫወቱት አዳማ ከነማዎች የዓመቱ የመጀመሪያ የሜዳ ሽንፈታቸውን አስተናግደው ምኞታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ የደደቢት በቅዱስ ጊዮርጊስ መረታት ለአሸናፊ በቀለ ቡድን መልካም አጋጣሚ የነበረ ቢሆንም በበረከት ወልደፃዲቅ ብቸኛ ጎል በአርባምንጭ ከነማ ተረተው አጋጣሚውን ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡
- የውድድር ዘመኑ የመጨረሻ ሩብ ያልተመቸው ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር 2ለ2 ተለያይቷል፡፡ ሞገስ ታደሰ እና ፍፁም ተፈሪ ለሲዳማ እንዲሁም ፊሊፕ ዳውዝ እና ሰሎሞን ገብረመድህን ለንግድ ባንክ ጎሎቹን አስቆጥረዋል፡፡ በወልዲያ በተደረገው ጨዋታም ወልዲያ ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ 2ለ2 ተለያይተዋል፡፡ ማይክ ሰርጂ እና ወሰኑ ማዜ የወልዲያን ከሊጉ የመሰናበቻ ጎሎች በስማቸው ሲያስመዘግቡ ጋቶች ፓኖም እና ዮናስ ገረመው ለቡናማዎቹ አግብተዋል፡፡ ሀዋሳ ከነማ በበኩሉ በሜዳው ዳሸን ቢራን 4ለ2 ረትቷል፡፡ አንተነህ ተሻገር፣ ታፈሰ ሰሎሞን፣ ተመስገን ተክሌ እና ሙሉጌታ ምህረት የሀዋሳን ጎሎች ሲያስቆጥሩ የዳሸንን ጎሎች ኤዶም ሆሶሮቪ እና የተሻ ግዛው አስቆጥረዋል፡፡
- የ26 ሳምንቱ የሊግ ጉዞ ሲፈፀም ባለድሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 57 አድርሷል፡፡ ደደቢት በ13 ነጥቦች ርቆ ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ አዳማ ከነማ በ42 ነጥብ የሜዳልያውን ስፍራ አሟልቷል፡፡ ሲዳማ ቡና (40)፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (39)፣ ኢትዮጵያ ቡና (36) እና አርባ-ምንጭ ከነማ (35) ከደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ በላይ ሲያጠናቅቁ፣ መከላከያ (34)፣ ወላይታ ድቻ (33)፣ ሀዋሳ ከነማ (33)፣ ኤሌክትሪክ (30) እና ዳሸን ቢራ (30) ከደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ በታች ከወራጅ ቀጠናው በላይ ሆነው ፈፅመዋል፡፡ ሙገር ሲሚንቶ (27) እና ወልዲያ ከነማ (16) ወደ ብሔራዊ ሊጉ ወርደዋል፡፡
- በጎል አግቢነት የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኑሚ በ22 ጎሎች ከፍተኛ ጎል አግቢ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ የንግድ ባንኩ ናይጄሪያዊ የሀገሩ ልጅ ፊሊፕ ዳውዝ በ19 እና የኢትዮጵያ ቡናው ቢኒያም አሰፋ በ16 ጎሎች ተከታትለውት ጨርሰዋል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አዳነ ግርማ እና የሃዋሳ ከነማው ተመስገን ተክሌ (11 ጎሎች) እና የሲዳማ ቡናው ኤሪክ ሙራንዳ (10) ሁለት አሀዝ ጎል ላይ የደረሱ ሌሎቹ ተጨዋቾች ናቸው፡፡
- ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት የዘንድሮው ውድድር መዝጊያ ጨዋታ በኋላ በተካሄደው ደማቅ ዝግጅት ለሻምፒዮኖቹ ዋንጫ እና ገንዘብ እንዲሁም የሜዳልያ ስፍራ ይዘው ላጠናቀቁትም የገንዘብ ሽልማቶች ከመሰጠታቸው ባሻገር፣ ከፍተኛ ጎል አግቢው እና በየዘርፉ የዓመቱ ምርጥ ተደርገው የተመረጡ ግለሰቦችም ተሸልመዋል፡፡ ከፍተኛ ጎል አግቢው ሳሙኤል ሳኑሚ፣ ኮከብ ተጨዋች ተደርጎ የተመረጠው የቅዱስ ጊዮርጊሱ በኃይሉ አሰፋ እና ኮከብ አሰልጣኙ ፋሲል ተካልኝ በነፍስ-ወከፍ 25 ሺህ ብር ሲሸለሙ፣ ለአራተኛ ተከታታይ ዓመት ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኖ የጨረሰው ሮበርት ኦዳንካራ 15 ሺህ ብር ተሸልሟል፡፡ ኃይለየሱስ ባዘዘው ኮከብ የመሀል ዳኛ 10 ሺህ ብር እንዲሁም ሀይለራጉኤል ወልዳይ ኮከብ ረዳት ዳኛ 8 ሺህ ብር ተሸልመዋል፡፡ የፀባይ ዋንጫ አሸናፊ ደደቢት ሆኗል፡፡
በቡድን 1ኛ ለወጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ 150 ሺህ፣ 2ኛ ለወጣው ደደቢት 100ሺህ፣ 3ኛ ሆኖ ላጠናቀቀው አዳማ ከነማ 75ሺህ ብር በሽልማትነት ተበርክቷል፡፡
Articles
በኦስሎ ዳይመንድ ሊግ የ5000ሜ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች በአሸናፊነት አጠናቀዋል

ትላንት ምሽት በኖርዌይ ኦስሎ በተከናወነው የዳይመንድ ሊግ 5000 ሜ. ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንዶችም በሴቶችም ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያሉትን ደረጃዎች በመቆጣጠር አሸንፈዋል፡፡ በዝናባማ የአየር ሁኔታ ውስጥ በተካሄደው የሴቶች 5000 ሜትር ፉክክር ዳዊት ስዩም በመጨረሻዎቹ መቶ ሜትሮች ውስጥ ፍጥነቷን በመጨመር ጉዳፍ እና ለተሰንበትን ቀድማ አንደኛ ወጥታለች፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለኦሪገን 2022 የአለም ሻምፒዮና ከመረጣቸው ዕጩ አትሌቶች ዝርዝር ውስጥ ያልተካተተችው ዳዊት በኦስሎ ያሸነፈችበት 14፡25.84 የሆነ ሰአት የራሷ ምርጥ ሲሆን እጅጋየሁ ታዬ (14.12.98) እና ለተሰንበት (14፡24.59) ባለፈው ወር በዩጂን ካስመዘገቧቸው በመቀጠልም የዘንድሮ የአለም ሶስተኛው ፈጣን ነው፡፡ በውድድሩ ላይ ከነበሩት ሌሎች ኢትዮጵያውያን መካከል በዘንድሮው የውድድር ዓመት በርቀቱ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን ያደረገችው አልማዝ አያና በ14:32.17 ስድስተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡ ሀዊ ፈይሳ በ14:33.66፣ ፅጌ ገብረሰላማ በ14:43.90፣ እና አበራሽ ምንሴዎ በ14:47.98 በቅደም ተከተል ሰባተኛ፣ አስረኛ እና አስራ አንደኛ ሆነው ሲያጠናቅቁ ሶስቱም ያስመዘገቡት ሰዓት የራሳቸውን ምርጥ ያሻሻሉበት ሆኗል፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ እ.ኤ.አ. በጁን 2008 ዓ.ም. ያስመዘገበችውና 14:11.15 የሆነው የኦስሎ ዳይመንድ ሊግ የሴቶች 5000 ሜትር የውድድር ስፍራ ሪከርድ ይሰበራል ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ዳዊት ስዩም ውድድሩን በድል ካጠናቀቀች በኋላ ለውድድሩ አዘጋጆች በሰጠችው አስተያየት ‹‹ዛሬ ለእኔ ደስታን ስላመጣልኝ በውድድሩ ሰዓት የነበረውን ዝናብ ወድጄዋለሁ ማለት እችላለሁ፡፡ ጠንካራ ተፎካካሪዎች የነበሩበት ከባድ ውድድር ነበር እናም ሁሉንም ለማሸነፍ በቅቻለሁ። በርቀቱ የራሴን ምርጥ ሰዓት ማሻሻል መቻሌም አስፈላጊ ነበር፡፡ በስታድየሙ ውስጥ በከፍተኛ ስሜት ድጋፍ ይሰጡን የነበሩ ወገኖቻችን ነበሩ። ለሰጡን ድጋፍ እናመሰግናለን።›› ብላለች፡፡ በኦስሎ የወንዶች 5000 ሜትር የመጨረሻ ፉክክሩ በኢትዮጵያውያኑ ጥላሁን ሀይሌ እና ሳሙኤል ተፈራ መካከል የነበረ ሲሆን ጥላሁን የ1500 ሜትር ስፔሻሊስቱ ሳሙኤልን በአጨራረስ ፍጥነት ቀድሞ በ13:03.51 በአንደኛነት አጠናቋል፡፡ ሳሙኤል ተፈራ የራሱ ምርጥ በሆነ 13:04.35 ሁለተኛ ሲወጣ ጌትነት ዋለ የግሉ የዓመቱ ምርጥ በሆነ 13:04.48 ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል። በውድድሩ ላይ የነበሩት ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሚልኬሳ መንገሻ በ13:05.94 አምስተኛ እንዲሁም አሊ አብዱልመናን የራሱ ምርጥ በሆነ 13:16.97 አስረኛ ወጥተዋል፡፡

ጥላሁን ሀይሌ ውድድሩን በአሸናፊነት ካጠናቀቀ በኋላ ለውድድሩ አዘጋጆች በሰጠው አስተያየት ‹‹ሶስት ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያዎቹን ሶስት ደረጃዎች ይዘን መጨረስ መቻላችን ጥሩ አፈጻጸም ነበር። እየጠነከርኩ እንደሆነ የተሰማኝ ሲሆን በውድድሩ እና ባስመዘገብኩት ሰዓትም ተደስቻለሁ። ለረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ስለነበኩ ወደ አሸናፊነቱ መመለስ መቻሌ በጣም ጥሩ ነው።›› ብሏል፡፡
በኦስሎ የሴቶች 800ሜ. ውድድር ላይ ተፎካካሪ የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ ድሪቤ ወልቴጂ በ1፡58.69 አምስተኛ ሆና አጠናቃለች።
Articles
የዘንድሮው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ሻምፒዮና በእኔ እይታ

ከመጋቢት19-24/2014 ዓ.ም በሐዋሳ አለም አቀፍ ስቴድዮም የተደረገው 51ኛዉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሞላ ጎደል ስኬታማ በሚባል ሁኔታ ተጠናቋል፡፡ ከአምስት አመት በኋላ በድጋሚ በአካል በመገኘት ስለተከታተልኩት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሀገር አቀፍ ሻምፒዮና የግል ምልከታዬን እንደሚከተለው አጠናቅሬዋለሁ፡፡ የበለጠ ትኩረትን በሳቡት ውድድሮች ዙሪያ የተመዘገቡ ውጤቶችን በወፍ በረር በመዳሰስ ስጀምር ከፍተኛ ፉክክር በታየበት የመጨረሻ ቀን የወንዶች 5000ሜ. የአለም ከ20 አመት በታች ሻምፒዮና የ3000ሜ የብር ሜዳልያ አሸናፊው አሊ አብዱልመና 13፡45.0 በሆነ ሰዓት ከጥላሁን ሀይሌ፣ ጌትነት ዋለ እና ዮሚፍ ቀጄልቻ ቀድሞ አሸናፊ ሆኗል፡፡ የፉክክሩ አካል የነበረው እና የርቀቱ የወቅቱ የአለም ሻምፒዮን ሙክታር እድሪስ ስድስተኛ ወጥቷል። ከ20 ዓመት በታች የ3000ሜ የአለም ሻምፒዮኑ ታደሰ ወርቁ በ28፡12.0 የወንዶች 10,000ሜ. ሻምፒዮን ሲሆን በ1996 ዓ.ም. በአትሌት ስለሺ ስህን ተመዝግቦ የነበረውን 28፡16.23 የሆነ የሻምፒዮናው ሪኮርድ ለማሻሻልም በቅቷል፡፡ በ10 ሺህ ሜትር የሴቶች ፉክክር ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር በቀዳሚነት የጨረሰችበት 31፡21.5 የሆነ ሰዓት አዲስ የሻምፒዮንሺፕ ሪኮርድ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በርቀቱ የከዚህ ቀደሙ ሪኮርድ ለተሰንበት ግደይ ከሶስት ዓመት በፊት ያስመዘገበችው 32፡10.13 የሆነ ሰዓት ነበር፡፡ ሳሙኤል ፍሬው በዘንድሮ የወንዶች 3000ሜ. መሰናክል አፈፃፀም ከአለም ሁለተኛው ፈጣን በሆነ 8፡22.5 ሰዓት አሸናፊ ሲሆን ጌትነት ዋለ ከአራት ዓመት በፊት አስመዝግቦት የነበረውን 8፡28.98 የነበረ የሻምፒዮናው ሪኮርድም አሻሽሏል፡፡ በሴቶች 3000ሜ. መሰናክል ከ800ሜ ወደ ረጅም ርቀት የተሸጋገረችው ወርቅውሃ ጌታቸው በ9፡41.8 ሰዓት መቅደስ አበበን (9:43.8) በማስከትል በአሸናፊነት አጠናቃለች። አድሃና ካህሳይ (3:51.0) የወንዶች 1500ሜ ፉክክሩን በበላይት ሲያጠናቅቅ በሴቶች 1500 ሜ አያል ዳኛቸው (4:10.0) ተጠባቂዋ ዳዊት ስዩምን (4:11.1) በመቅደም በአንደኛነት አጠናቃለች። በ800ሜ. ወንዶች ቶሌሳ ቦደና (1:47.1) በሴቶች ወርቅነሽ መሰለ (2:02.1) አሸናፊ ሆነዋል። ዮብሰን ብሩ በ400ሜ/400ሜ መሰናክል (45.9/50.5) ድርብ ድል ሲቀዳጅ፣ በወንዶች ጦር ውርወራ ኡታጌ ኡባንግ ብሔራዊ ሪኮርድ በሆነ 73.28ሜ. አሸንፏል፡፡ የኋልዬ በለጠው እና ዮሃንስ አልጋው በእርምጃ ሩጫ የሻምፒዮንነት ክብርን ተቀዳጅተዋል። ጥቂት አስተያየቶች፡- የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪ እንደሆነ እና ለዕድገቱ እንደሚቆረቆር ሰው በብሔራዊ ሻምፒዮናው ላይ ስለተመለከትኳቸው አዎንታዊ እና አሉታዊ ጎኖች ጥቂት አስተያየቶቼን እንደሚከተለው አስቀምጣለሁ፡- አዎንታዊ ጎኖች • ባለው ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ሊገጥሙ የሚችሉትን ተግዳሮቶች በሙሉ በመቋቋም ፌዴሬሽኑ ውድድሩን ከአዲስ አበባ ውጭ አካሂዶ በሰላም ማጠናቀቅ መቻሉ አንደኛው ስኬቱ ነው፡፡ • በሻምፒዮናው ላይ ጥቂት የማይባሉ ታዋቂ አትሌቶች በሀገሪቱ ትልቁ የአትሌቲክስ ፉክክር ላይ ተሳታፊ ሆነው ሲወዳደሩ መመልከት የተቻለ ሲሆን በተለይም በወንዶች 5000 ሜትር ፍፃሜ ላይ የታየው የኮከብ አትሌቶች ፉክክር ልዩ ነበር፡፡ • በውድድሩ ወቅት ለአትሌቲክስ ዳኞች የብቃት ማሻሻያ ስልጠና መሰጠቱም የውድድሩን ጥራት ለማሳደግ የሚረዳ እንደመሆኑ እሰየው የሚባል ነው፡፡ • እንደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያሉት ክለቦች ለአትሌቲክስ ስፖርት የበለጠ ትኩረት በመስጠትና ተጠናክሮ በመቅረብ ከዚህ ቀደም በጠንካራነታቸው ከሚታወቁት መከላከያ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የቅርብ ተፎካካሪ ሆነው መታየት፤ የኦሮሚያ ክልል፣ ደቡብ ፖሊስ እና ሲዳማ ቡና ክለብ አትሌቶችም ጠንካራ ተሳትፎ ሳይዘነጋ የሻምፒዮናው ፉክክር ድምቀት ነበሩ፡፡ • የአንዳንዶቹ ተገቢነት አጠያያቂ ቢሆንም ብዛት ያላቸው የሻምፒዮናው ሪኮርዶች የተሻሻሉበት ውድድርም ነበር፡፡ አሉታዊ ጎኖች • የሀገሪቱ ትልቁ የአትሌቲክስ ውድድር ውጤት አሁንም በኤሌክትሮኒክስ የሰዓት መቆጣጠሪያ የማይደገፍ መሆኑ በተለይም በአጭር ርቀት እና በሜዳ ላይ ተግባራት ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች ልፋት ተገቢውን እውቅና እንዳያገኝ እያደረገ ይገኛል፡፡ የሻምፒዮናውን ውጤቶች በዘመናዊ እና ዓለም አቀፉን መለኪያ በሚያሟላ መልኩ አለመያዝ በአህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ ለተሳትፎ የሚያበቁ ውጤቶችን በማስመዝገቡ ረገድ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑ ከግምት ውስጥ ገብቶ አሁንም መፍትሄ ያልተበጀለት ጉዳይ ነው፡፡ • የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ወደ ሚዲያ/ለአጠቃላዩ ሕዝብ የሚያስተላልፈው የመጀመሪያዎቹን ሶስት ደረጃዎች ይዘው የሚያጠናቅቁ አትሌቶችን ውጤት ብቻ መሆኑ አወዳዳሪው አካል የሚያደርገውን የራሱን ውድድርም ሆነ አትሌቶቹ የለፉበትን ውጤት ከማስተዋወቅ አኳያ በቂ አይደለም፡፡ • በወንዶች የጦር ውርወራ እና የሴቶች ምርኩዝ ዝላይ ብሔራዊ ሪኮርዶች እንደተመዘገቡ ይታመናል፤ በሴቶች 100ሜ መሰናክል እና የወንዶች 400ሜ መሰናክል የተመዘገቡት ሰዓቶችም የምንግዜውም ፈጣን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ውድድሩ በኤሌክትሮኒክስ ታይሚንግ ያልተደገፈ እና የንፋስ ንባብ ያልነበረው መሆኑ ውጤቶቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ነው። • በ20 ኪ.ሜ የእርምጃ ውድድር ላይ በሁለቱም ፆታዎች የተመዘገቡት ሰዓቶች ከሚጠበቀው በላይ እጅግ በጣም ፈጣን እና እውነታዊ አለመምሰላቸው በውድድሩ ላይ የተፈጠረ አንዳች ስህተት መኖሩን የሚያመላክቱ መሆኑ፡፡ እንዲህ አይነት ለማመን የሚከብዱ እና ጥርጣሬን የሚፈጥሩ አይነት ውጤቶች ሲመዘገቡም የተፈጠረ ስህተት መኖር አለመኖሩን ለማጣራት አለመሞከሩ፡፡ • የሴቶች 10 ኪሎ ሜትር ውድድር ላይ ለውድድር የማይፈቀድ የጎዳና ላይ መሮጫ ጫማን በመጠቀም የተመዘገበ ውጤት በሪኮርድነት ጭምር ተይዞ መፅደቁ። ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከተከለከሉ ጫማዎች ጋር የተያያዙ ዓለም አቀፍ ሕገ ደንቦችን ማወቅና መተግበር ቢገባውም በሴቶች 10 ሺህ ሜትር ውድድር ላይ የተከሰተው ነገር የውድድር ሕገ ደንቦቹ መረጃ በፌዴሬሽኑ ውስጥ በትክክል የተሰራጩ እንዳልሆነ የሚያመላከት ነው፡፡ • በሴቶች 1500 ሜትር የግማሽ ፍፃሜ ውድድር ላይ አትሌት ዳዊት ስዩም የሻምፒዮናውን ሪኮርድ ያሻሻለችበት ውጤት እንደተመዘገበ በውድድሩ ወቅት በተደጋጋሚ ሲነገር ከተደመጠ በኋላ ግልፅ ባልተደረገ ምክንያት ውጤቱ በሐዋሳው ውድድር ላይ ተሻሻሉ ከተባሉት የሻምፒዮናው አዲስ ሪኮርዶች ዝርዝር ውስጥ ሳይካተት መቅረቱም የፌዴሬሽኑን ግልፀኝነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት አዎንታዊ እና አሉታዊ ጎኖች ለረጅም ግዜ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ስፖርት እንቅስቃሴዎች በቅርበት ከመከታተሌ አንፃር በራሴ እይታ ያስቀመጥኳቸው እንደመሆናቸው አንዳንዶቹ ሀሳቦች አከራካሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሆኖም የውድድር ደንቦችን በአግባቡ ከማስፈፀም አኳያ በታዩት ክፍተቶች ዙሪያ ምንም የሚያከራክር ጉዳይ ስለሌለ በወቅታዊ የውድድር ደንቦች ዙሪያ የግንዛቤ እጥረት ላለባቸው የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት በሙሉ አስፈላጊውን ገለፃ እና ትምህርት መስጠት የፌዴሬሽኑ ኃላፊነት ነው፡፡ ከውድድር ጋር የተያያዙ ደንቦችን ከመጣስ አኳያ በሀገር ውስጥ በሚደረጉ ውድድሮች እንደቀላል ነገር የሚታለፉ ጉዳዮች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይም ተደግመው እንደግል አትሌቶችን እንደቡድን ሀገርን ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍሉ ይችላሉና አስፈላጊው ጥንቃቄ ቢደረግ መልካም ነው፡፡ ባለፈው መስከረም ወር በቪየና ሲቲ ማራቶን ውድድሩን በአሸናፊነት ጨርሶ የነበረው ኢትዮጵያዊው ደራራ ሁሪሳ የገጠመውን አንዘንጋው! ሀገራችን ኢትዮጵያን በመልካም ጎኑ ስሟ እንዲነሳ በሚያደርገው እና በትልልቅ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ የኩራታችን ምንጭ በሆነው የአትሌቲክስ ስፖርት እንደጎረቤታችን ኬንያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ የብቃት ደረጃ ላይ ደርሰን ማየት የዘወትር ምኞቴ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንም የውድድሮቹን ጥራት ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራ ተስፋ አደርጋለሁ።
በመጨረሻም በሀዋሳ በተካሄደው 51ኛዉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከመሮጫ ጫማ ጋር የተያያዙ ደንቦችን በማስከበሩ ረገድ የተፈጠረውን ክፍተት እንደማስተማሪያ ብንጠቀምበት በሚል የሚከተለውን ለማለት ወደድኩ፡-
የመሮጫ ጫማ ደንቦች ለትራክ ውድድር
64 ደቂቃ ከ14 ሰከንድ በሆነ ሰዓት የዘንድሮ የራስ አል ካይማህ የግማሽ ማራቶን ውድድር አሸናፊ የሆነችው ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር በሐዋሳ በተከናወነው 51ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ 31 ደቂቃ ከ21.5 ሰከንድ በመግባት የ10,000ሜ. አሸናፊ ሆናለች፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ዓለም አቀፉን ደንብ ከግምት ባላስገባ ሁኔታ ውጤቱን በአዲስ የሻምፒዮንሺፕ ሪኮርድነት ጭምር አፅድቆት አልፏል፡፡ ይሁን እንጂ መጋቢት 20/2014 በተደረገው የሴቶች የፍፃሜ ፉክክር ላይ በኢትዮጵያ ምድር የተመዘገበ የምንግዜውም ፈጣን የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ሰዓት የሆነው ውጤት በአለም አትሌቲክስ ዘንድ እውቅና ሊሰጠው የማይችል ነው።
● ለምን?
አትሌቷ የሶል ውፍረቱ 40ሚሜ የሆነ ዙምኤክስ ቬፐርፍላይ (ZoomX Vaporfly) ጫማ አድርጋ በመወዳደሯ ምክንያት።
● ደንቡ ምን ይላል?
በትራክ ውድድሮች ላይ የሚፈቀደው ከፍተኛው የሶል ውፍረት ፡-
– 20ሚሜ ከ 800ሜ በታች ለሆኑ ውድድሮች እና ለሁሉም የሜዳ ላይ ተግባራት (ከስሉስ ዝላይ በስተቀር)
– 25ሚሜ ለ800ሜ እና ከዛ በላይ ለሆኑ ውድድሮች እንዲሁም ለስሉስ ዝላይ
– 40ሚሜ ለትራክ ላይ የእርምጃ ውድድሮች
እነዚህ ደንቦች እ.ኤ.አ. እስከ ኦክቶበር 31, 2024 ድረስ በሥራ ላይ ይውላሉ። ከኖቬምበር 1 ቀን 2024 ጀምሮ ለ800ሜ እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ውድድሮች እንዲሁም ለስሉስ ዝላይ የሚፈቀደው ከፍተኛ የሶል ውፍረትም ወደ 20 ሚሜ ዝቅ የሚል ይሆናል።
● የትራክ ላይ መወዳደሪያ ስፓይክ ጫማ ከሌለኝስ?
ደንቡ የጎዳና ላይ የመሮጫ ጫማዎች በትራክ ላይ እንዳይደረጉ አይከለክልም ነገር ግን በ25 ሚሊ ሜትሩ ገደብ ምክንያት 30 ሚሜ ወይም 40 ሚሜ የሆኑ የጎዳና ላይ መሮጫ ጫማዎች በትራክ ውድድሮች ላይ እንዲደረጉ አይፈቅድም፡፡
● ለበለጠ መረጃ :-
https://www.worldathletics.org/news/press-releases/new-athletic-shoe-regulations-approved-2022
Articles
የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ተሳትፎ ድህረ ምልከታ

በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በወረቀት ደረጃ ከውድድሩ መጀመር በፊት ቡድኑ ባመዛኙ በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኙ ወጣት አትሌቶችን ስላካተተ ቢያንስ የለመድናቸውን ሁለት ወይም ሶስት የወርቅ ሜዳልያ ድሎች እንደማያሳጣን ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ ሆኖም የሜዳ ላይ ውጤቱ እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ኢትዮጵያ በውጤታማነቷ በምትታወቅበት የአትሌቲክስ ፉክክር በአንድ የወርቅ፣ አንድ የብር፣ እና ሁለት የነሐስ በድምሩ በአራት ሜዳልያዎች ከዓለም 14ኛ ከአፍሪካ 3ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች፡፡ ይህም ሁሌም ለአፍሪካ የበላይነት ከምንፎካከራት ኬንያ ጋር ያለን ልዩነት ይበልጥ እንዲሰፋ አድጎታል፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ሌላኛዋ የምስራቅ አፍሪካ ተቀናቃኛችን እየሆነች ከመጣችው ኡጋንዳም አንሰን እንድንገኝ አድርጎናል፡፡ የቶኪዮ ኦሊምፒክ በአትሌቲክሱ ከ1992ቱ የባርሴሎና ኦሊምፒክ ወዲህ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሜዳልያ ስኬት ያስመዘገበችበትም ሆኖ አልፏል፡፡
አሉታዊ ጎኖች
ቶኪዮ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤታማነት ፈር ቀዳጅ የሆነው ታላቁ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ በ1964 ዓ.ም. በተከታታይ ሁለተኛ የኦሊምፒክ ማራቶን ድሉን የተቀዳጀባት ከተማ ናት፡፡ እናም በቶኪዮ ከተማ በተከናወነው የኦሊምፒክ ውድድር የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የሱን ክብር የሚያጎሉባቸውን ነገሮች ያደርጋሉ ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ የሆኑት ነገሮች ግን በተለይ በቡድኑ አስተዳዳሪዎች በኩል ፍፁም ኃላፊነት የጎደለውና ከጠበቅኩት በተቃራኒው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከአትሌቶች ምርጫ አንስቶ በቡድኑ የዝግጅት ወቅት በተካረረ ውዝግብ ውስጥ ነበር የከረሙት፡፡ የኦሊምፒክ ቡድኑን የማዘጋጀት እና የመምራት የጋራ ኃላፊነት የነበረባቸው ሁለቱ አካላት ይባስ ብለው ውዝግቡን ቶኪዮ ድረስ ይዘውት ሄደዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ሁለቱን አካላት በማቀራረብ በትልቁ ውድድር ላይ ያለንን ተሳትፎ እንከን አልባ ማድግ የሚጠበቅባቸውም ተመልካች ከመሆን የዘለለ ሚና አልነበራቸውም። የውዝግቡ አሉታዊ ትሩፋት በአትሌቶች ስነልቦና እና በአጠቃላይ የቡድኑ ውጤት ላይ የበኩሉን ተፅዕኖ ሳያሳርፍ እንዳላለፈ አያጠራጥርም፡፡
እንደ አለመታደል ሆኖ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያን ልዑካን የመምራት ትልቁ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ኃላፊነት የጎደላቸው ነበሩ። የስፖርቱ አስተዳደሪዎች ትላልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በመጡ ቁጥር በአትሌቶች ምርጫ ዙሪያ የነበረውን ውዝግብ እንዲያቆሙልን እመኝ ነበር። ጭራሽ እራሳቸው ችግር ፈጣሪ ሆነው መገኘታቸው አስደንጋጭ እና አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በመሮጫ መም ወይም በጎዳና ላይ በሚደረጉ ውድድሮች መሸነፍን በስፖርቱ ውስጥ ማሸነፍ እና መሸነፍ ያሉ የነበሩ እና ወደፊትም የሚኖሩ ነገሮች ስለሆኑ በፀጋ መቀበል ይቻላል፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑ የስነልቦና ጥንካሬን ሊፈጥሩላቸው የሚገቡ ኃላፊዎች የእርስ በርስ ሽኩቻ ተቃራኒውን አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳርፍ ማየት ግን ፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ ለነገሩ ከስፖርቱ እድገት ይልቅ የፖለቲካ ግዴታቸው የሚያስጨንቃቸው የስፖርት አመራሮች በበዙባት ሀገር ስፖርቱ እንዲህ የማንም መጫወቻ ሲሆን ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡
የስፖርት አመራሮች ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ሆነው ትኩረታቸውን ስፖርቱን በማስፋፋቱ እና ማሳደጉ ላይ አድርገው የሚሰሩ ስለስፖርቱም በቂ እውቀት እና ፍቅሩ ያላቸው ቢሆኑ መልካም ነው፡፡ ለቦታው በሚመጥን እና ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት በሚችል የስፖርት አመራር የሚመራ የስፖርት ተቋምን መገንባት በተመሳሳይ ሰዓት የሀገር ግንባታን የሚደግፉ ሶስት ነገሮችን ስኬታማ ያደርጋል፡፡ በስፖርት ጤናውን የሚጠብቅ ማሕበረሰብ በመፍጠር በጤናው ሴክተር ላይ የሚኖረውን ጫና ይቀንሳል፣ በሀገር ገፅታ ግንባታ እና በኢኮኖሚው ዕድገት ላይም የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ በቶኪዮ ላይ የተመለከትናቸው የሀገርን ክብር ዝቅ ያደረጉ ግዴለሽነቶች ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊታዩና አጥፊዎቹ ሊጠየቁበት ይገባል፡፡ በመጪዎቹ ዓመታት በሚጠብቁን ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይም የቶኪዮ ኦሊምፒኩን አይነት ሀፍረት እንዳይገጥመን ከወዲሁ ለችግሮቹ መፍትሔ መፈለግ አለበት፡፡
ባለፉት ዓመታት ኦሊምፒክ በመጣ ቁጥር በልዑካን ቡድኑ ውስጥ እየተካተቱ በሕዝብ ገንዘብ የሚዝናኑት የኦሊምፒክ ቱሪስቶች ጉዳይ ዘንድሮም ያልተቀረፈ ችግር ሆኖ ተስተውሏል፡፡ ከሌላው ግዜ በተለየ መልኩ ተጠባባቂ አትሌቶችን ይዞ መጓዝ ይጠይቅ በነበረው ውድድር ላይ አትሌቶቹን ትቶ ምንም የማይሰሩ ሰዎችን ይዞ መሄድ ትልቅ ቀልድ ነው፡፡
ከሜዳ ውጭ የነበረው ውዝግብ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል የነበረ መሆኑ በሜዳ ላይ የነበሩብንን ድክመቶች ሊያስረሳንም አይገባም፡፡ ስድስት የጎዳና ላይ ተወዳደሪዎቻችን እና አንድ የመም ተወዳዳሪ ውድድራቸውን ማቋረጣቸው በቶኪዮ ከታዩት ደካማ ጎኖቻችን መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ ችግሩ በዚህ ምክንያት ነው የተከሰተው ብሎ ለይቶ ለመናገር ባይቻልም ብዙ ግዜ ሲፈትነን ለሚስተዋለው የሞቃታማ ቦታ ውድድር የምናደርጋቸው ዝግጅቶችን መለስ ብሎ መመልከትን የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ የተጎዳች አትሌትን ወደውድድር እንድትገባ ማድረግ እና በሁለት ደቂቃ ውስጥ ለማቋረጥ መገደዷም የአትሌቶች የጤና ክትትል ላይ ክፍተት እንዳለ የጠቆመን ክስተት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ወደውድድር ስፍራው ካቀናበት ግዜ ጀምሮ በቶኪዮ ምንም አይነት ቡድኑን የተመለከቱ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ወይም ፕሬስ ሪሊዞች አልነበሩም፡፡ ይህም እንደተለመደው የሕብረተሰቡን እና የመገናኛ ብዙሀንን ስለቡድኑ ቀጥተኛ መረጃ የማግኘት መብት የገደበ ነበር፡፡ ጋዜጠኞችም ሚዛናዊ ሆኖ ከመዘገብ ይልቅ ጎራ ለይተው ቃላት መወራወራቸው የህዝብን ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት የነፈገ ነው፡፡
አዎንታዊ ጎኖች
ሰለሞን ባረጋ በወንዶች 10,000 ሜትር ወርቅ፣ ለሜቻ ግርማ በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ብር፣ ጉዳፍ ፀጋዬ በሴቶች 5000 ሜትር ነሐስ፣ እና ለተሰንበት ግደይ በሴቶች 10,000 ሜትር ነሐስ ማስመዝገብ መቻላቸው የሚደነቅ ስኬት ነው፡፡
የመጪው ትውልድ አካል የሆኑት ተስፈኞቹ መቅደስ አበበ፣ ፍሬወይኒ ሀይሉ፣ በሪሁ አረጋዊ እና ጌትነት ዋለን ጨምሮ አምስት አትሌቶች ለሜዳሊያ የቀረበ የአራተኛነት ደረጃን ይዘው ማጠናቀቅ መቻላቸውም መልካም ነው፡፡ በተለይ ወጣቶቹ ያስመዘገቡት ውጤት በመጪዎቹ ዓመታት ተገቢውን ድጋፍ ካገኙ የምንጓጓለትን ድል ሊያስገኙልን እንደሚችሉ ያመላከተን ነው፡፡
የሀብታም አለሙ በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በሴቶች 800 ሜትር ለመጀመሪያ ግዜ ለፍፃሜ ተወዳዳሪነት መብቃት ምንም እንኳ በፍፃሜው የሜዳልያ ድል ባይቀናትም በአዎንታዊ ጎን ሊጠቀስ የሚችል ስኬት ነው፡፡
ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃን ይዘው ላጠናቀቁ አትሌቶች በሚሰጥ ነጥብ ድምር መሰረት በወጣው የነጥብ (ፕሌስመንት) ደረጃ ሰንጠረዥ ላይ በ64 ነጥብ ዘጠነኛ ሆነን ማጠናቀቃችንም እሰየው የሚያስብል ነው፡፡
በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከአራተኛ እስከ ስምንተኛ ባሉት ደረጃዎች ውስጥ አጠናቀው ነጥብ ያስገኙ እና የዲፕሎማ ተሸላሚ የሆኑት አትሌቶች፡-
4ኛ – ፍሬወይኒ ሀይሉ – በሴቶች 1500 ሜትር
4ኛ – መቅደስ አበበ – በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል
4ኛ – ሮዛ ደረጀ – በሴቶች ማራቶን
4ኛ – በሪሁ አረጋዊ – በወንዶች 10,000 ሜትር
4ኛ – ጌትነት ዋለ – በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል
5ኛ – እጅጋየሁ ታዬ – በሴቶች 5000 ሜትር
6ኛ – ሀብታም አለሙ – በሴቶች 800 ሜትር
6ኛ – ሰንበሬ ተፈሪ – በሴቶች 5000 ሜትር
8ኛ – ዮሚፍ ቀጄልቻ – በወንዶች 10,000 ሜትር
8ኛ – ዘርፌ ወንድማገኝ – በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል

- የአትሌቲክስ የነጥብ ደረጃ ሰንጠረዥ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ባሉት ደረጃዎች ውስጥ የሚያጠናቅቁ አትሌቶች በሚያስመዘግቡት ነጥብ ድምር መሰረት የሚወጣ ሲሆን የነጥብ አሰጣጡም ለአንደኛ ደረጃ 8 ነጥብ፣ ለሁለተኛ ደረጃ 7 ነጥብ፣ ለሶስተኛ ደረጃ 6 ነጥብ፣ ለአራተኛ ደረጃ 5 ነጥብ፣ ለአምስተኛ ደረጃ 4 ነጥብ፣ ለስድስተኛ ደረጃ 3 ነጥብ፣ ለሰባተኛ ደረጃ 2 ነጥብ፣ እና ለስምንተኛ ደረጃ 1 ነጥብ ነው።
ከፊታችን ምን እየጠበቀን ነው? ምንስ እናድርግ?
ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፉ ወረርሺኝ ምክንያት ትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለሌላ ግዜ እንዲተላለፉ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ሌላ አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ቀጣዮቹ አራት ዓመታት በተከታታይ በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች የሚካሄዱባቸው ይሆናሉ፡፡ በ2022 የዓለም ሻምፒዮና፣ በ2023 የዓለም ሻምፒዮና፣ በ2024 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች፣ እና በ2025 የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ይኖራሉ፡፡ በቀጣዩ ዓመት በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ከሐምሌ 8 – 17/2014 በዩናይትድ ስቴትስ ኦሪጎን የሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዘጋጆች ሙሉ የውድድሩን ፕሮግራም፣ የማራቶን እና የእርምጃ ውድድሮች የሚካሄዱባቸውን ቦታዎች በትላንትናው ዕለት ይፋ አድርገዋል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናውን ውድድር በኃላፊነት የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ከወዲሁ ለዛ ውድድር ተሳትፎ የሚጠበቅበትን አቅዶ መንቀሳቀስ ይኖበርታል፡፡
ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጭቅጭቆችን ለማስቀረት ከወዲሁ ሁሉም አትሌቶች አውቀውት በውስጡ የሚያልፉበትን ገዢ የሆነ የመምረጫ መስፈርት ማዘጋጀት ቀዳሚው ተግባር መሆን አለበት፡፡ የመምረጫ መስፈርት ሁልግዜም በግላዊ ምልከታ እና ፍላጎቶች ላይ በሚመሰረት ምክንያት አነጋጋሪ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ቢሆንም ባለድርሻ አካላቱን በሙሉ ባሳተፈ መልኩ ውይይት ተደርጎበት ቢወጣ ሁሉንም ገዢ እና ከጭቅጭቅ የፀዳ ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህ ላይ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከተከሰቱት ሁኔታዎች አንፃር የሌሎች ሀገሮችንም ተሞክሮዎች በመዳሰስ ነገሩን ሰፋ አድርጎ መመልከት ቢቻል ጥሩ ነው፡፡ ትልልቅ ውድድሮች በመጡ ቁጥር በተደጋጋሚ እንደታዘብነው አንዳንድ አትሌቶች በቡድኑ ውስጥ ለመካተት የሚያደርጉትን ተገቢ ያልሆነ ሙከራም ማቆም አለባቸው፡፡ ከፋም ለማም ስፖርቱን እንዲመራ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም የሚያወጣቸውን መስፈርቶች ማክበርና በዛ ውስጥ ተመራጭ ለመሆን መሞከር ግድ እንደሚላቸውም መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ማኔጀሮች እና አሰልጣኞች በተለይ በማራቶን የራሳቸውን አትሌት ለማስመረጥ የሚያደርጓቸው አላስፈላጊ ግፊቶችም ሊያቆሙ ይገባል፡፡
ለውድድሮች የምናደርጋቸውን ዝግጅቶች ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ከውድድሮች በኋላ መገምገም እና መታረም ያለባቸው ነገሮች ካሉ ማረም፡፡ ከፍተኛ ሙቀት በነበረባቸው በለንደን 2012 ኦሊምፒክ ሶስቱም የወንዶች ማራቶን ተወዳዳሪዎቻችን፣ በሞስኮ 2013 የዓለም ሻምፒዮና ሁለቱ የሴቶች ማራቶን ተወዳዳሪዎቻችን፣ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ አምስት የማራቶን (ሶስቱም ወንዶች እና ሁለት ሴቶች) ተወዳዳሪዎቻችን እንዲሁም የሴቶች እርምጃ ተወዳዳሪያችን ለማቋረጥ መገደዳቸውን አስተውለናል፡፡ ስለዚህ በጎዳና ላይ ውድድሮች ከባድ ሙቀት ለሚኖርባቸው ቦታዎች እንዴት መዘጋጀት አለብን የሚለው ጉዳይም በደንብ ሊታይ የሚገባው ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ የመም (ትራክ) ተወዳዳሪ አትሌቶቻችን የውድድር ዓመቱ ሲጀምር ድንቅ ብቃታቸውን ያሳዩን እና ወደትልቅ ውድድር ሲቃረቡ አቋማቸው እየወረደ ይመጣል፡፡ አሰልጣኞቻቸው ለእነዚህ አይነቶቹ አትሌቶች ወደትልቅ ውድድር ሲቃረቡ ብቃታቸውን እያሳደጉ እንዲሄዱ የሚረዳቸውን የልምምድ ፕሮግራም ቢያዘጋጁላቸው መልካም ነው፡፡ በመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ላይ በተለይ በወንዶች አሁንም በከፍተኛ ደረጃ የሚፎካከሩ አትሌቶችን ለማፍራት ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል፡፡
-
EBS Mogachoch9 years ago
[New] EBS Drama Series – Mogachoch : ሞጋቾች | Episode 7
-
Articles9 years ago
Ethiopia’s renewable energy revolution shouldn’t fail to empower its poor
-
News2 years ago
መንግሥት ከሕወሓት ይልቅ ለአገሪቱ ሥጋት የሆኑ ሌሎች ችግሮች አሉብኝ አለ
-
Opinions2 years ago
On the TPLF’s Love Affair With ‘Genocide’
-
Music4 years ago
2019 ESFNA Atlanta: Ethiopian Day – Ethiopia Hagerachin : ኢትዮጵያ ሀገራችን
-
Music4 years ago
2019 #ESFNA Atlanta: Ethiopian Day | Neway Debebe – Hageren Alresam : ሀገሬን አልረሳም
-
Articles8 years ago
ሰበር ዜና፦ ተዋናይት ሰብለ ተፈራ (ትርፌ) በመኪና አደጋ ህይወቷ አለፈ
-
Bahilawi Zefenoch10 years ago
Bahilawi Zefenoch – ባህላዊ ዘፈኖች
Anonymous
July 25, 2015 at 3:20 pm
Etihpa VdioFLms
Anonymous
July 25, 2015 at 3:20 pm
Etihpa Films Ads
wubetueyasu
June 26, 2015 at 5:47 am
etiopayawye gegnoche ygebachewal
Anonymous
June 15, 2015 at 9:59 am
Etihpa kof
Abugela Sanjawe
June 5, 2015 at 7:30 pm
Mengizem Giyorgis ! Bulla Gellebba Dengay Kenemma Were Kenemma kechalachu deresoubin be were be sedebe wancha yelem respect St.George fc we are 12 times champions !
assefa abate
June 5, 2015 at 7:52 am
The conclusion of the league was cecpensing,and dramatic.All clubs do there best .For the next year we are expecting more.